August 12, 2024
79 mins read

ገንዘብን ለገበያ ተዋንያን ልቅ በማድረግ፣  ወይም በገበያ እንዲተመን በማድረግ የአንድን  አገር ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት ይቻላል ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ነሐሴ 5 2016 (ነሐሴ 12 2024)

ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንገስት ተብዬው ተጨማሪ ብድር ለማግኘት ሲል ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የቀረበለትን ቅድመ ሁኔታ ማለትም ገንዘብን በገበያ እንዲተመን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተስማምቷል። የኢትዮጵያን ብር በገበያ ወይም  በአቅራቢና በጠያቂ እንዲተመን ከመደረጉ በፊት ህወሃት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ በተለይም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮችን ኢኮኖሚ ከዓለም ገበያ ጋር እንዲቀናጅ ወይም የዓለም ገበያን ፍላጎት ለማሟላት መስተካከል አለበት በማለት ያወጣውን የዋሽንግተን ኮንሴንሰስ((Washington Consensus) በመቀበል በተለይም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ስልጣን እንዲለቅ እስተገደደበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር እንዲቀንስ ተደርጓል። ከኢትዮጵያ ብር መቀነስ ጋር ሌሎች ተጨማሪ ቅድመ-ህኔታዎችም ተግብራዊ ሆነዋል። እነዚህም 1ኛ) ለሶሻል መስክ የሚወጣው ወጭ መቀነስ አለበት፤ በተለይም የመግዛት አቅሙ ደካማ ለሆነው የህብረተሰብ ክፍል  መንግስት የሚደጎመውን ወጪ መቀነስ አለበት። 2ኛ) በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ መደብሮችና ኢንዱስትሪዎች ወደ ግል መዘዋወር አለባቸው፤ በእርግጥ በሽያጭ።  3ኛ) የውስጡም ሆነ የውጭው ገበያ ልቅ መሆን አለባቸው፤ ይህንን ሊበራላይዜሽን ብለው ይጠሩታል።፡ በተለይም በውጭው ንግድ ላይ መንግስት የሚያደርገው ቁጥጥር ከተነሳ፣ ለምሳሌ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ ከቀነስ የመዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾች ግር ብለው በመምጣት ኢንቬስት በማድረግ የስራ መስክ በመክፈትና የመግዛት ኃይልን በመጨመር ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ ትልቅ ዕምርታን ሊሰጡት ይችላሉ የሚል ዕምነት በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ኢኮኖሚስቶች ዘንድ አለ።

ከካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ስንነሳና ስንመረምር ይህ ዐይነቱ የተቋም ማስተካከያ ዕቅድ(Structural Adjustment Programmes) የገበያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሲባል በአንዳቸውም የካፒታሊስት አገር ተግባራዊ የሆነበት ጊዜ የለም። ሌሎች በኋላ ላይ የተነሱ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋንና ሲንጋፖር፣ እንዲሁም ቻይና ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን የተቋም ማስተካከያ ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ አይደለም ወድ ውስጥ ያተኮረ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባትና፣ እንዲሁም ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማምረት በውጭ ንግዳቸው ውጤታም ለመሆን የበቁት።

ወደ ተቋም ማስተካከያው ዕቅድ(Structural Adjustment Programmes) ስንመጣ ተቋም የሚለው ፅንሰ ሃሳብ  የሚነሳው ጠቅላላውን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ አወቃቀር(Socio-Economic Formations) በመመርመርና ለኢኮኖሚው ዕድገት ማነቆ የሆኑት ምን ምን ነገሮች ናቸው  ብሎ በመጠየቅና በመመርመር አይደለም።  ከመንግስት የቀረቡለትን ስታትስቲክሶች በማየትና የተወሰኑ ፓራሜትሮችን የማክሮ ኢኮኖሚ መስረታዊ ነገሮች አድርጎ በመውሰድና  ብቻ ነው የተቋም ማስተካከያ መደረግ አለበት በማለት የሚደነግገው።  በተለይም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የሚቀርቡት ቅድመ-ሁኔታዎች ተግባራዊ ከሆኑ  ኢኮኖሚው እስትንፋስ በማግኘት ሊያድግ ይችላል የሚለው ግምት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ በሆኑባቸው አገሮች በሳይንስ ያልተረጋገጠና ውጤታማም ያልሆነ  የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ለምሳሌ የጋና አገዛዝ ቀደም ብሎ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የዓለም ባንክን ምክርና ግፊት በመቀበል ተግባራዊ ያደረገው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋናን በዕዳ ከመተብተብ ባሻገር የጋና ገበሬ በካካኦ ምርት ላይ ብቻ እንዲያተኩርና መንግስቱም በውጭ ካፒታል ጥገኛ እንዲሆን ነው የተደረገው። ከዚህ ሀቅ ስንነሳና የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን የፖሊሲ ምክር ተቀብለው ውጤታማነትን ካላሳዩት ሌሎች አገሮች ተጨባች ሁኔታ ስንነሳ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የፖሊሲ ምክር ወደ ውስጥ ያተኮረ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል አይደለም።  በሌላ ወገን የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ በሚገባ ተግባራዊ መሆኑ የሚረጋገጠው 1ኛ) ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሲገነባ ብቻ ነው። 2ኛ) ለሰፊው ህዝብ ወይም ስራ ፈላጊ ለሆነው በቂ የስራ መስክ ሲከፈት ነው። 3ኛ) የውስጡ ገበያ(Home Market)  እንዲያድግ ከተፈለገ የግዴታ በየጊዜው የሰራተኛውና የተቀረው ሰፊ ህዝብ የመግዛት ኃይል(Buying Power) ማደግ አለበት። 4ኛ) ለውስጥ ገበያ ዕድገት የሚያመቹ  በስራ-ክፍፍል ላይ(Division of Labour) የተመሰረቱ ትናንሽና መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች የግዴታ በየቦታው መስፋፋት አለባቸው። በእነዚህ መሀከልም መተሳሰር(Value-added Chain) መኖር አለበት። በሌላ አነጋገር፣ አንድ የፍጆታ ምርት የሚያመርት ኢንዱስትሪ ከሌላ ኢንዱስትሪ፣ ለምሳሌ ተለዋወጭ ምርቶችን ከሚያመርት ኢንዱስትሪ ምርቶችን በመግዛትና በመገጣጠም ወይም እንደ መጨረሻ የፍጆታ ምርት በማምረት ገበያው ላይ ማቅረብ አለበት። በዚህ መልክ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መሀከል ብቻ ሳይሆን በእርሻው ዘርፍና የተለያዩ ለምግብና ለመጠጥ የሚውሉ ፍራፍሬዎችን የሚያመርቱ ገበሬዎች፣ ለምሳሌ እንደ ፓፓያና ማንጎ ወይም ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማቅረብ የብርቱካንም ሆነ የፓፓያ ጭማቂ ወይም ጂውስ በማመረት ገበያ ላይ በማቅረብና በመሸጥ ለገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት ልዩ ዕምርታን ይሰጠዋል። 5ኛ) ለተቀላጠፈ የገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት የግዴታ የተቀላጠፈና ለሁለ-ገብ ዕድገት(Holistic) የሚያመችና የቆመ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝና የመንግስት መዋቅር ያስፈልጋል። አፋኝና ዘራፊ መንግስት ካለ፣ በተለይም በመዋዕለ-ነዋይ ስም የአገርን ሀብት ለውጭ ተዋንያን ልቅ የሚያደርግና እንዲዘረፍ የሚያደርግ አገዛዝ ወይም ኤሊት ስልጣን ላይ ካለ በፍጽም ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ የገበያ ወይም የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሊገነባ አይችልም። 6ኛ) ወደ ውስጥ ላተኮረና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ የግዴታ በመንግስት የሚደጎም በየቦታው የሚንቀሳቀስና የተዘረጋ የምርምርና የዕድገት ተቋም(Research & Development) መኖር አለበት። ከካፒታሊስት አገሮች ልምድና ሁኔታ ስንነሳ መንግስታት በየዓመቱ ላቋቋመቸው የምርምርና የፈጠራ ተቋማት በጀት ይመድባሉ። እነዚህም ተቋማት ከተለያዩ ስትራቴጂክ ኢንዱስትሪዎች ጋር ተባብረው በመስራት አዳዲስና ለህዝቡ የሚጠቅሙ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለጠቅላላው ኢኮኖሚ መንቀሳቀስ እንደመሰረት የሚሆኑ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን በማምረት አጠቃላዩ ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ያደርጋሉ። 7ኛ) ለገበያ ኢኮኖሚ በጥልቀትና በዐይነት ማደግ የግዴታ ለሰው ልጅ መኖሪያ የሚያገለግሉ ከተማዎችና መንደሮች ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባት አለባቸው። እንደሚታወቀው የገበያ ኢኮኖሚ በአየር ላይ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን በምድር ላይ እንደመሆኑ መጠን በሚገባ የተዋቀሩና በስርዓት የተገነቡና ልዩ ልዩ ተግባሮችን ሊያሟሉ የሚችሉ ልዩ ልዩ ህንጻዎች መገንባት አለባቸው። በተለይም የቤቶችና የህንፃዎች አሰራር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተና ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያገልና በቆሻሻ ቦታዎች እንዲኖር የሚያስገድደው መሆን የለበትም። በሌላ ወገን ግን የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ከ1980 መጀመሪያ ጀምሮ በአፍሪካና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚሰሩ ህንጻዎችና የከተማ ግንባታዎች ሰፊውን ህዝብ የሚያገሉና በቆሻሻ ቦታ ላይ እንዲኖሩ የሚያስገድዱ ናቸው። ይህ ዐይነቱ የከተማ አገነባብ የኒዎ-ሊበራል የከተማ አገነባብ ዕቅድ(Neo-liberal Urban Planning) በመባል ሲታወቅ፣ ለማጅራት መቺዎች፣ ለሌቦች፣ ለድረግ ሻጪዎች፣ ለሴተኛ አዳሪዎችና ለልዩ ልዩ የብልግና ኢንዱስትሪ መስፋፋት የሚያመች ነው። በዚህ ዐይነቱ የተበላሽ የከተማ አገነባብ የሚጠቁት በተለይም ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ህፃናት ናቸው። እንዲያም ሲል ይህ ዐይነቱ የከተማ አገነባብ ለፈጠራና የሰውን መንፈስ ለመሰብስበ የሚያመች ሳይሆን፣ በተለይም በከተማዎች ውስጥ የሚኖር ህዝብ አስተሳሰቡ ሁሉ ማቴሪያላዊ በሆኑ ነገሮችና በገንዘብ ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ አንዱ ሌላውን እየፈራና እንዳያምን እየተደረገ(Hobbesian World View) የሚኖርበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም የኣነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የየኒው-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአንድ አገር ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገትን የሚፈጥርና የሰው አስተሳሰብና አኗኗርን እንዲዘበራረቅ የሚያደርግ ነው። በተለይም ከተለያዩ የአንድ አገር ቦታዎች ሰው ስራ ለመፈለግ ሲል ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲሰደዱ የሚያደርግና ጥቂት ከተማዎች እንዲጨናነቁ ይደረጋሉ። በሌላ አነጋገር፣ በአንዳንድ ከተማዎች ውስጥ አርቲፊሻል በሆነ መልክ የህዝብ ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብና ቤቶችንም በዕቅድ ለመስራት በጣም የሚያስቸግር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ከዚህ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ስንነሳ በአንድ አገር ውስጥ ብዙ ሰዎች ስራ ለመፈለግና የተሻለ ኑሮ ለመኖር ሲሉ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ የሰውን ፍሰት ለመግታትና የመኖሪያ ቤቶችን ላለማጣበብ ሲባል የግዴታ በአገር ውስጥ በተለያዩ ክፍለ-ሀገራት ከተማዎችንና መንደሮችን በተሟላ መልክ መገንባት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ  ነው በአንድ አገር ውስጥ የተስተካከለ ዕድገትን ማምጣት የሚቻለው። 8ኛ) ለገበያ ኢኮኖሚ በጥልቀትና በስፋት ለማደግ የግዴታ በተለይም ሰፊውን ህዝብና ዕቃዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር የሚያስችሉ የመገናኛና የማመላለሻ መሳሪያዎች፣ ለምሳሌ እንደ ባቡር ሃዲድና ሰብ ዌይ( Suburban rail  ways) እንዲሁም አውቶቡሶች መኖር አለባቸው። እነዚህ ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው ስለገበያ ወይም ሰለካፒታሊስት ኢኮኖሚ ማውራት የሚቻለው። አንድ አገርም በዚህ መልክ ብቻ ነው  በተሟላና በተስተካከለ  መንገድ የሚገነባው።

በአጭሩ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በኢኮኖሚ ታሪክና በሳይንስ መነፅር ሲመረመር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተብሎ ሊጠራ አይችልም። በብዙ መቶዎች የሚቆጥሩ ስለካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ የሚያትቱ መጽሀፎችን ላነበበና ለተመራመረ የሚያረጋግጠው ማንኛውም የካፒታሊስት አገር በተወሳሰበ መልክ ለማደግና ዓለምን ለመቆጣጠር የቻለው በእነዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የረቀቀውን ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን፣ ግን ደግሞ ፖሊሲ ያልሆነውን በመከተል አይደለም። የካፒታሊስት አገሮችን የኢኮኖሚ ታሪክ ላጠናና ለተመራመረ ካፒታሊዝም ዛሬ በምናየው መልኩ ከማደጉ በፊት ልዩ ልዩ የዕድገት ደረጃዎችን አልፏል። ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት በመነሳት ነው ወደ ተወሳሰበና በኦሊጎሎፒስቶች ወይም በሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ቁጥጥር ስር የወደቀ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሊያድግ የቻለው። ካፒታሊዝምም በዚህ መልክ ሊያድግ የቻለው በተለይም በምዕራብ አውርፓ አገሮች ውስጥ ከ13ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በዕውቅ ከተማዎች በመገንባታቸውና የዕደ-ጥበብ ስራ ተግባርም እንደ አሸን በመፍለቁ ነው የኋላ ኋላ ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት የተጣለው። ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ደግሞ አገዛዞች፣ በጊዜው ፍጹም ሞናርኪዎች  የውስጥ ገበያቸውን ለማስፋፋት ሲሉ የግዴታ በዕውቅና በዕቅድ ላይ የተመሰረተ የአገርና የኢኮኖሚ ግንባታ ተግባራዊ ለማድረግ ችለዋል። አዳም ስሚዝ የሚስተው ነገር  ይህንን ዐይነቱን በፍጹም ሞናርኪዎችና ቀደም ብሎ ተግባራዊ የሆነውን አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያብብ የተወሰዱትን እርምጃዎች ነው። በአዳም ስሚዝ ዕምነት የገበያ ኢኮኖሚ  በረቀቀው እጅ(Invisible Hand) እንደሚያድግ ነው። ይህንን የአዳም ስሚዝን አስተሳሰብ የሚፃረር በፕሮፌሰር ኤሪክ ራይነርት ስለ ካፒታሊዝም የኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዴት ሀብታም አገሮች ሀብታም ሊሆኑ ቻሉ፣ ደሃ አገሮች ደግሞ ለምን ደሃ ሆነው ለመቅረት ተገደዱ(How Rich Countries become rich… and how poor countries stay poor) በሚለው ግሩም መጽሃፋቸው ውስጥ ቀርቧል። ሌላው አዳም ስሚዝ የሚስተው ነገር ለካፒታሊዝም ማደግና ዓለምን ለመቆጣጠር የባሪያ ንግድና የቅኝ-ግዛት ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ከቁጥር ውስጥ አለማስገባቱ ነው። ሌላው አዳም ስሚዝና ሌሎች የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የሚስቱት ነገርና በጣምም አደገኛ የሆነው የተሳሳተ አስተሳሰብ እንደ ጋሊሊዮ፣ ሬኔ ዴካ፣ ኒውተንና ላይብኒዝ፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግም አያሌ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋፅዖ ከቁጥር ውስጥ ካለማስገባት ነው። ምክንያቱም ቀደም ብሎ ፈጠራና የሳይንስ ግኝት እንደ መሰረት ባይጣሉ ኖሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሊፈጠሩ ባልቻሉ ነበር። ምክንያቱም ካፒታሊዝም በጥልቀትና በስፋት ሊያድግ የሚችለውና ልዩ ልዩ የረጅምና የአጭር ዕድሜ ያላቸው መሳሪያዎችም ሆነ የፍጆታ ዕቃዎች በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ስለሚመረቱ ነው። በተጨማሪም ልዩ ልዩ የመጓጓዣ መሳሪያዎች፣ ለምሳሌ እንደባቡር ሃዲድና አውሮፕላን፣ እንዲሁም መኪና የመሳሰሉት አንዳንድ ሳይንቲስቶችና የመፍጠር ችሎታ ባላቸው ካፒታሊስቶች ለመፈጠርና ለጠቀሚታ በመዋል ነው ካፒታሊዝም በጥልቀትና በስፋት ሊያድግ የቻለው። ይህም ማለት ካፒታሊዝም ልያድግ የሚችለው በኃይልና(Energy) በማሽን፣ እንዲሁም በሰው የማሰብ ኃይልና በጉለበት በመተጋዝ  ብቻ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የካፒታሊዝምን የዕድገት ታሪክ ስናነብና ስንመራመር የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል የፖሊሲ አውጭዎች እንደሚሉትና እንደሚያስፋፉት ሳይሆን የአንድ አገር ኢኮኖሚና ህብረተሰብ ሊያድጉ የሚችሉት በዕውቅና በታቀደ መልክ ብቻ ነው። በተለይም በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመታገዝና በመደገፍ ብቻ ነው። በአንፃሩ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትንና የእነ ዓለም ባንክን፣ በአጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው የሚባለውን መንገድ የተከተለ አገር አናርክሲዝምና በቀላሉ መቋጠሪያ የማይገኝለትን የዘለዓለማዊ ቀውስ ነው የሚፈጥረው። ሶሶይሎጂያዊና የሰነ-ልቦና ቀውስ፣ እንዲሁም የአካባቢ ቀውስ(Ecological Crisis) በመፍጠር አንድ አገርና ከተማ ጦርነት የሚካሄድባቸው መድረክ ይሆናሉ ማለት ነው። ባጭሩ አሳቢና ፈጣሪ የሆነ ማህበረሰብ ሳይሆን የሚፈጠረው መንፈሰ-አልባ ማህበረሰብና በደመ-ነፍስ እየተመራ አገርን የሚያክረባብትና የጥሬ-ህብትን የሚሸጥ ኤሊት የሚባለው ነገር ነው የሚፈጠረው። በተግባርም የሚታየውና በተለይም አብዛኛዎቹ የአፍሪካና የደቡብና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች በዚህ መልክ በተፈጠረ ኤሊትና ለፋይናንስ ካፒታል ታዛዥ በሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነው የሚሰቃዩትና ከአገራቸውን ተሰደው እንዲኖሩ የተገደዱትና የሚገደዱት።

ይህንን ካልኩኝ በኋላ ሰለ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ስለገበያ ኢኮኖሚ አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን ልበል። ሃይንሬሽ ፔሽና(Heinrich Pesch) ሌሎች የሰብአዊነት ባህርይ ያላቸው ታላላቅ ኢኮኖሚስቶችና የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚያስተምሩን የኢኮኖሚ መሰረታዊ አስተሳሰብና ዋናው ተግባርም የሰውን ልጅ መሰረታዊ ፎላጎቶች(Basic Needs) ማሟላት ነው። የሰው ልጅ ለመኖር፣ ለማሰብና ለመስራት ሲል የግዴታ የተሟላ ዲዬት መመገብ አለበት። መብላትና መጠጣት አለበት። ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው። ይህ ሲሟላ ብቻ ነው ማንኛውም ግለሰብ አሳቢና ፈጣሪ ሊሆን የሚችለው። እንደሚመስለኝ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ኤክስፐርት ነን ባዮች የሚበሉና የሚጠጡ አይመስሉም። ስለሆነም ስለሌላው ሰው ሊያስቡ አይችሉም። በእነሱ ዕምነትም ሁሉም ነገር በገበያ ላይ የሚገኝ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ገበያ ላይ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ምግቦችንና መጠጦችን፣ እንዲሁም ዕቃዎችን ለመግዛት የግዴታ ገንዘብ የሚሉት ነገር መኖር አለበት። ገንዘብን ለማግኘት ደግሞ የግዴታ ሰፊው ህዝብ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይሁንና ግን የካፒታሊዝምን የዕድገት ታሪክ በምንመራመርበትና ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት ሁሉም ወይም አብዛኛው ህዝብ ገበያ ላይ የሚቀርቡ ነገሮችን እየገዛ የመጠቀም ዕድል አልነበረውም። አሁንም በመንግስታት በጀት የሚደጎም ስፋ ያለ የህብረተሰብ ክፍል አለ። በተለይም እንደ ቤት የመሳሰሉት ነገሮች ለገበያ ተዋንያን ብቻ የሚተዉ አይደሉም።  በተወሳሰበ መሳሪያና የመንግስት በጀት ዝቅተኛ ደሞዝ ላለው ቤቶች ይሰራሉ።  የቤት ኪራያቸውም የቀነሰና እንደየግለሰቡ ወይም ቤተሰብ ገቢ በተመጣጣኝ ኪራይ የሚከራዩ ናቸው።  በግለሰብ ኩባንያዎችም የሚሰሩ የመኖሪያ ቤቶችም ኪራያቸው ከሚፈለገው በላይ እንዳያድግ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት እንድ ብላክ ሮክ(BlackRock) የመሳሰሉት ታላላቅ የሀብታሞችን ገንዘብ የሚያስተዳድሩና የጥሬ ሀብትን  የሚቆጣጠሩ ቤቶችን እየገዙና እያሳደሱ ለብዙ ዓመታት የኖሩ ኗሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲወጡ እያደረጉ ነው። በተጨማሪም የትላልቅ መደብሮችን ቤትች ኪራይ ከፍ በማድረግ የብዙ ዓመታት ዕድሜ ያላቸውን ባህላዊ መደብሮችን(Super Markets) እንዲከስሩና ሱቆችም እንዲዘጉ እያደረጉ ነው። ይህም የሚያሳየው በአብዛኛዎች የካፒታሊሱት አገሮች የመንግስታት ኃይል እየተዳከመ በመምጣት ላይ ነው ማለት ነው። በተለይም ትላልቅ ኩባንያዎች ፓርሊሜንታሪያን ከሚባሉት ከህግ አውጭዎች ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ስለሆነ አገዛዞች እንደፈለጉ ህገ-መንግስቱ በሚያዘው መሰረት ትላልቅ ኩባንያዎችን በፍጹም መቆጣጠርና ኃይላቸውንም ለመግታት ወደ ማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ያም ሆኖ መንግስታት ቁጥጥር እንዲያደርጉና የቤት ኪራይም እንዳይጨምር በየጊዜው ሰለማዊ ስልፍ ይደረጋል። የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶችም በከፍተኛ ደረጃ በመታገል በመንግስታት ላይ ጫና ያደርጋሉ።

ወደ ሌሎች ነገሮች ጋ ስንመጣ ሌሎችም ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮች በዝቅተኛ ቀረጥ የሚሸጡ ናቸው። ምክንያቱም ተዘዋዋሪ ቀረጥ(Indirect Tax) በቀጥታ ለመንግስት ገቢ ስለሚሆን መንግስት ምግብ ነክ የሆኑ ነገሮች በጣም ዝቅ አድርጎ ነው የሚቀርጠው። ከካፒታሊስት አገሮች ልምድ ስንነሳ ሁሉም ነገር ለገበያ መተው አለበት፤ የዕቃዎችም ዋጋ በጠያቂና በአቅራቢ የገበያ ህግ ብለው በሚጠሩት መስራት መተመን አለበት ብለው ለገበያው ተዋንያን የሚተውት ነገር አይደለም። ይህም ማለት በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ገበያ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው። አጠቃላይ የሆነ ቀውስም በሚታይበትና ብዙ ሰው ከስራ መስኩ በሚባረርበት ጊዜ መንግስት ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ በተለይም በፊስካል ፖሊሲ(Fiscal Policy) አማካይነትና ተጨማሪ ገንዘብ በተለያዩ የመንግስት ሴኩሪቲ ወም ቦንድስ አማካይነት ከባንኮችና ከውስጥ የካፒታል ገበያ በመበደር  ኢኮኖሚው ከገባበት ቀውስ እንዲወጣ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን ይወስዳል።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታና ማረጋገጫ ስንነሳ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ በአጭሩ የዓለም ኮሙኒቲውና  የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት በተቋም ማስተካከያ(Structural Adjustment Programmes) አማካይነት እንደኛ  አገር ያለው ኢኮኖሚ በፍጹም ሊያድግ አይችልም። ለምሳሌ ኢኮኖሚክስ ስንማር በኢኮኖሚክስ ሊትሬቸር ውስጥ አንድ አገር ገንዘቧን ከዶላር ጋር ሲነፃፅር ብትቀንስ ለውጭ የምታቀርበውን ምርት በብዛት ልትሸጥ ትቾላለች የሚል ተጽፎ አይገኝም። ይህንን የፈጠሩት ለዓለም የገንዘብ ድርጅትና ለዓለም ባንክ ተቀጥረው የሚሰሩ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ነው። ይህንንም ቲዎሪ ሊያፈልቁ የቻሉት ኤላስቲሲቲ ኦፍ ዴማንድ(Elasticity  of Demand) ከሚለው ቀላል የኢኮኖሚ ሎጂክ በመነሳት ነው። በቲዎሪው መሰረት ለምሳሌ የአንድ ዕቃ ዋጋ ከሚሸጥበት ዋጋ አንድ በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ከቀነሰ ሰው የመግዛት ፍላጎቱ ያይላል። በትክክልም በተለይም በክረምትና በበጋ ወራት ማለቂያዎች ገደማ ላይ የክረምትም ሆነ የበጋ ልብሶችና ጫማዎች ዋጋቸው ይቀንሳል። በዚህ ጊዜ ሰው ተንጋግቶ ይገዛል። አንዳንድ ምግብ ነክ ነገሮችም የመቆያ ጊዜያቸው ሊያልቅ ሲል ዋጋቸው ይቀንሳል። ስለሆነም ምግብ ነክ ነገሮችንም ይገዛል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ግን የአንድን አገር ገንዘብ ለምሳሌ የዓለም አቀፍ መገበያያያና ሬዘርብ ከረንሲ ከሆነው ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ቢቀንስ(Devaluation) የሚሰራ አይደለም። ለምሳሌ የጥሬ ሀብትና የእርሻ ምርት አምራች አገሮች የምርቶቻቸውን ዋጋ የሚደነግጉት ራሳቸው አይደሉም። በተለይም ትናንሽ ቡና አምራች ገበሬዎች ቡና ለማምረት የሚያወጡትን ወጪና የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ቡና ለማምረት ያባከኑትን የስራ-ጉልበት በማስላት አንድ ኩንታል ቡና በዚህ የስሌት ዋጋ ነው የምሸጠው አይሉም። ለምሳሌ የትናንሽ የቡና አምራች ገበሬዎችን የኑሮ ሁኔታ ለተመለከተ ከሰላሳና ከአርባ ዓመታት በላይ ቡና እያመረቱና እየሸጡ ከጎጆ ቤት ያልተላቀቁ አሉ። አብዛኛዎችም ጫማና ልብስ የመግዛት አቅም ስሌላቸው የተቦጫጨቀ ልብስ የሚለብሱና ባዶ እግራቸውንም ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀው የሚጓዙ ናቸው። በቡና ምርትና መሸጥ የሚጠቀሙት የቡና ነጋዴዎችና በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡናንና ሌሎች የጥሬ ሀብቶችን የሚቆጣጠሩ ትላልቅ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ናቸው። የቡና ዋጋና ሌሎች የጥሬ-ሀብቶች ዋጋም በእነዚህ ትላልቅ ኩባንያዎች፣ ካርቴሎች በመባል በሚታወቁ የሚደነገግ ነው። እንደ ቡና የመሳሰሉትም በኮታ ስለሚሸጡ አንድ አገር ገንዘቧን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር እንዲቀንስ በማድረጓ ምርቷን እንደልብ በዓለም ገበያ ላይ የመሸጥ ዕድል በፍጹም አይኖራትም። ወያኔ በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ተገዶና ተመክሮ የኢትዮጵያን ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ እንዲል ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የምርት መጠን በከፍተኛ ደረጃ አልጨመረም። ከውጭ ንግዱ  የምታገኘውም የውጭ ከረንሲ በፍጹም አልጨመረም። ይባስ ብሎ ብሩ እንዲቀንስ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ንግድ ሚዛኗ(Trade  Balance) በክፍተኛ ደረጃ እየተዛባ ነው የመጣው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ አ. አ በ2023 ዓ.ም ወደ ውጭ ከላከችው ምርቶች ወደ $ 6.2 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ስታገኝ፣ ከውጭ ደግሞ ወደ $ 13.6 ቢሊዮን የሚጠጋ ልዩ ልዩ ዕቃዎችን አስመጥታለች።  ይህም ማለት ወደ $ 7.4 ቢሊዮን የሚጠጋ የንግድ ኪስራ ደርሶባታል ማለት ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ከቀነሰበት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ በኪሳራ የሚንቀሳቀስ ነው ማለት ነው።  በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋርስ ሲነፃፀር በመቀነሱ  አገራችን ከሰረች እንጂ በምንም ዐይነት አላተረፈችም።  ከዚህ ጋር ተያይዞ የውጭው ዕዳዋም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። በአሁኑ ወቅት ዕዳዋ ወደ $ 30 ቢሊዮን እንደሚጠጋ ስታትስቲክስ ያረጋግጣል። ይህም የሚያሳየው ከውጭ ንግዷ በምታገኘው የውጭ ምንዛሪ የውጭ ዕዳዋን በተለይም አገልግሎት(Debt Service) ብለው የሚጠሩትን፣ ወለድና የተወሰነውን ካፒታል በየጊዜው ለመክፍል እንደማትችል ነው። ለመክፍል ከፈለገች ወይም የዶላር ችግር ካለባት የግዴታ ለዓለም የገንዘብ ድርጅት በማመልከት ተጨማሪ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት አለባት። ይህ ዐይነቱ ሂደት ዕዳን ማስተካከል(Debt Restructuring) ተብሎ ሲጠራ፣ ይህ በራሱ በወለድ ላይ ተጨማሪ ወለድ(Compound Interest) እንዲያድግ የሚያደርግ ነው። ስለሆነም ዕዳው እየቀነሰ የሚመጣ ሳይሆን እየጨመረና አገሪቱ የመክፈል አቅሟ እየተዳከመ እንዲመጣ የሚያደርግ ነው። ባጭሩ አንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር፣ በተለይም ወደ ውጭ የምትልከው ምርት የእርሻ ውጤት ብቻ ከሆነ ገንዘቧን ከዶላር ጋር በመቀነሷ ተጨማሪ ገዢ ማግኘት አትችልም። የአገር ውስጥ ገበያዋም በፍጹም ሊያድግ አይችልም። በአንፃሩ ድህነትና ኋላ-ቀርነት ስር እየሰደዱ እንዲሄዱ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ሌላ አማራጭ መንገዶችን እንዳትፈልግ የሚያደርግና ያለንንም የጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት በስነ-ስርዓት እንዳንጠቀም የሚያደርግ ነው። ሰለሆነም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የተሟላ ዕድገት እንዳይተገበር ያደርጋል።

ከዚህ ቀላል ሀቅ ስንነሳ የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስተር ተብዬው አቢይ አህመድ ሊያስተምረን እንደሚሞክረው ዶላርን  ከዓለም  የገንዘብ  ድርጅትና   ባንክ  መበደር  ልክ  ከእናት  እንደመበደር  የሚቆጠረው ነው   አባባል በጣም አደገኛ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሁለቱ የዓለም አቀፍን ስም የተከናነቡት ተቋማት እንደኛ የመሳሰሉ አገሮችን የማቆርቆዝና ወደ ኋላ ቀርተን ለዝንተ-ኣለም እንድንደፋደፍ የሚያደርጉትንና ያላቸውን ፀረ-ዕድገትና ሚና አለመረዳት ነው። ሁለቱ ተቋማት በመሰረቱ የዓለምን ገበያ የሚቆጣጠሩ ታላላቅ ኩባንያዎችንና የካፒታሊትስት አገሮችን ጥቅም የሚያሰጠብቁ ናቸው። ዋና ዓላማቸውም በተለያዩ መሳሪዎች ሀብት ከሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም ከአፍሪካ ወደ ካፒታሊስት አገሮች እንዲፈስ በማድረግ፣ በዚያው መጠንም ጥቁሩ የአፍሪካ ህዝብ ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረት ነፃና ርስ በርስ የተሳሰረ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። የተለያዩ የማቆርቆዣ መሳሪዎችን  በመጠቀምና እነዚህንም እንደ ፖሊሲ በማቅረብ  የአፍሪካን ዕድገት መግታት ነው። ከተለያዩ የማቆርቆዣ መሳሪዎችም ውስጥ አንዱና ዋናውን ሚና የሚጫወተው ደግሞ አፍሪካን በዕዳ መተብተብ ነው።

የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በውስጡ ኢኮኖሚ ላይ በተለይም በዋጋ ዕድገት ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ደግሞ እንመልከት። እንደሚታወቀው የአንድ አገር ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃር አርቲፊሻል በሆነ መልክ እንዲቀንስ(Devalutaion) በሚደረግበት ጊዜ የዋጋ ግሽበትን ነው የሚያስከትለው። በተለይም ከውጭ የሚገቡና ለማምረቻ የሚያገለግሉ የምርት መሳሪያዎችና፣ በተለይም በግማሽ መልክ ተፈብርከው የሚመጡ ዕቃዎች፣ መድሀኒቶችና ምግብ ነክ ነገሮች ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለምሳሌ አንድ የአገር ውስጥ አምራች ከውጭ የመለዋወጫ ዕቃዎችን የሚያስመጣና ምርትን የሚያመርት ከሆነ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዝበ ካለው ዶላር መግዛት ይችላል፤ በዚያው መጠንም ገበያ ላይ ወጥቶ የሚሸጠውም ምርትም ዋጋው በክፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። ምክንያቱም የማምረቻው ዋጋ ስለሚጨምር። በብዙ ሚሊዮን  የሚቆጠር ዶላር ለመግዛት የማይችል አምራች ኃይል ደግሞ የሚፈልገውን መጠን ከቀየረ በኋላ ክወጭ የሚያሰምጣውም ምርት መጠኑ ይቀንሳል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የአገር ውስጥ አምራች የግዴታ በዝቅተኛ ካፓሲቲ እንዲያመርት ይገደዳል ማለት ነው። ይህም በራሱ የግዴታ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። ምክንያቱም ቋሚ ወጪዎች(Fixerd Costs) ስለማይቀየሩና ኢንዱስትሪውም በከፍተኛ ወይም በዝቅተኛ ካፓሲት ቢንቀሳቀስም ቋሚ ወጪዎች ስለማይቀንሱ ነው።  ከዚህ መጠነኛ ትንተና ስንነሳ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ እንዲቀንስ በመደረጉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥልቀትም ሆነ በዐይነት ለማደግ አልቻለም። የገበያ ኢኮኖሚም በተስተካከለ መልክ ሊያድግና፣ መለስተኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በመቋቋም በተለይም ስራ ለሚፈልገው ሰፊ ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍቱ አልቻሉም። አሁን ደግሞ ገንዘቡ ለገበያ ተዋንያን ልቅ ሲደረግና በገበያ እንዲተመን ሲደረግ(Free Floating) ያለውን ቀውስ የሚያባብስ እንጂ አገራችንና ህዝባችን ለገቡበት በነፃ ገበያ ስም ለሚካሄድ የተወሳሰበ ቀውስ በፍጹም መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ቅነሳና ገንዘብ በገበያ ላይ እንዲተመን ማድረግ በኢኮኖሚ ሎጂክ የሚደገፍ አይደለም። ራሳቸው የካፒታሊስት አገሮችም  በኢኮኖሚ ግንባታ ታሪካቸው ውስጥ በፍጹም ተግባራዊ አድርገው የማያውቁትን ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ነገር ነው  እንደኛ ባለው ደከማ አገር ላይ  በመጫን የባሰ ድህነትና ጥገኝነት ውስጥ የሚከቱን። ዋና ዓላማቸውም በየጊዜው በነፃ ገበያ ስም አሳበው ደካማና ዕውቀት የሌላቸውን አገዛዞች በማስገደድ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውን ፖሊሲና በኢኮኖሚ ሎጂክ የማይደገፍን ነገር ተግባራዊ በማድረግ ልንወጣ የማንችለው ማጥ ውስጥ መክተት ነው። በአጭሩ ቀናውንና የስልጣኔውን፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚመሰረተውን ሁለ-ገብ ዕድገት በዕቅድና በጥናት ተግባራዊ እንዳናደርግ ያግዱናል ማለት ነው። ረጋ ብለን እንዳናስብ በማሯሯትና ተንጋግተው በመምጣት እኛው ራሳችን የአገራችንን ዕድል ወሳኞች ሳንሆን እነሱ እንደ አድራጊና ፈላች ቆራጭ ሆነው ይቀርባሉ። ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ምንም ነገር ለማድረግ አትችልም፤ ለማድረግ ከፈልግ ደግሞ እናሳይሃለን በማለት ይዝቱብናል። ገፍተውም በመሄድ የርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳና አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ እንድንገባ ያደርጉናል። ባጭሩ አስተሳሰባቸውና አሰራራቸው ዘመናዊ መስለው ቢመጡም ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው። የሰውን  ልጅ ነፃነት የሚቀናቀኑና ጭንቅላታቸው በሀብት የቦዘ ነው። የታሪክን ሂደት ለመግታት የማያደርጉት ሙከራ የለም።

ነገሮችን ይበልጥ ለመረዳት አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን እንመልከት። በተለይም ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ነገር ዘርዘር ባለመልክ እንመልከት። በመሰረቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ በኬይንስ የተፈጠረ ሲሆን፣ የተማርነውም የማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ እንደሚያረጋግጠው እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ በፈጠሩትና በማይታወቀዉ የተወሰኑ ፓራሜትሮች ላይ፣ ለምሳሌ ገንዘብን ከዶላር ጋር ሲነፃፅር መቀነስ፣ በተለይም ለማህበራዊ መስክ የሚወጣውን በጀት መቀነስ፣ በመንግስት ቁጥጥር  ያለን ሀብት መሽጥና የውጭውንም ሆነ የውስጡን ገበያ ሊበራላይዝ ማድረግ  የሚያተኮር አይደለም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶችና የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የተጣመመና ሳይንሳዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ሲሆን፣ የእንግሊዙን ኢኮኖሚስት የኬይንስን አስተሳሰብ ወይም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳለ የሚፃረር ነው። ኬይንስ የተባለው የእንግሊዙ ኢኮኖሚስት በ1929-1930 ዓ.ም የተከሰተውን ትልቁን የኢኮኖሚ ቀውስ(The Great Economic Depression) በሰፊው ካጠና በኋላ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በየጊዜው ከፍና ዝቅ እያለ ስለሚያድግ በተለይም ዕድገቱ ዝቅ በሚልበት ጊዜው የስራ አጥ ቁጥሩ ስለሚጨምር መንግስት በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት የግዴታ ኢኮኖሚው እንዲስተካከል እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ይላል። መንግስት በትላልቅ ፕሮጀክቶች፣ በመንገድና በባቡር ሃዲድ ስራ፣ በትምህርትቤቶችና በክሊንኮች፣ እንዲሁም በውሃና በትራንስፖርቴሽን፣ በመብራት(Electricity) ወይም ለሰፊው ህዝብ ግልጋሎት (Public Goods) በሚሰጡ ላይ ኢንቬስት በማድረግ ኢኮኖሚው ከገባበት ቀውስ እንዲወጣ ለማድረግ ይችላል ይላል። በእሱ ዕምነትም ሁሉንም ነገር ለገበያው ልቅ ማድረግ በ1929-30 ዓ.ም እንደታየው ቀውስ በተደጋጋሚ ስለሚከሰትና ከፍተኛ የማህበራዊ ቀውስም ስለሚፈጠር ይህ እንዳይሆን ከተፈለገ የግዴታ መንግስት በጣልቃ-ገብ ፖሊሲ አማካይነትና ገንዘብ በተለያዩ መሳሪያዎች ከውስጥ ባንኮች በመበደር ወይም ማዕከላዊ ባንኩ እንዲያትም በማድረግና ይህ ገንዘብ በቀጥታ ምርታማ በሆኑ ነገሮች ላይና በፈጠራ ላይ የሚውል ከሆነ ጠቅላላው ኢኮኖሚ ከገባበት ቀውስ ሊወጣ ይችላል ይላል‹፣ ትክክልም ነው። በዚህ መልክ ሰፋ ያለ የስራ መስክ ሲከፈት ሰፊው ህዝብ የመግዛት አቅሙ ያድጋል። በዚህ አማካይነት ገበያ እያደገ ሲመጣና የአምራቾችም ሆነ የሰራተኛው ገቢ እያደገ ሲመጣ መንግስትም በቀጥታና በተዘዋዋሪ(Direct  & Indirect Taxes) የሚያገኘው ገቢ ያድጋል። በዚህም አማካይነት ከባንክም ሆነ ከካፒታል ማርኬት የተበደረውን ገንዘብ የመክፈል አቅሙ ይጨምራል ይለናል። በእርግጥም መጀመሪያ ላይ በሩዘቤልት የሚመራው የአሜሪካ አገዛዝ በ1930ዎቹ፣  አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮችና አገዛዞች ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተከተሉትና ተግባራዊ ያደረጉት ፖሊሲ የኬይንስን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ከዚያም ቀድመው በመሄድና ከተማዎችንና መንደሮችን በአዲስ መልክ በመገንባት ነው። ለምሳሌ ጀርመን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጊዜ እንግሊዝና አሜሪካ ከተማዎቿን፣ 80% የሚሆነውን እንዳለ በቦንብ አውድመዋል። ከዚህ ጋር ተደምሮ መብራትና የውሃ ቧንባዎች  እንዳይሰሩ ለመሆን በቅተዋል። ቤቶች እንዳለ ፈራርሰዋል። በተለይም በአውሮፓ ምድር ለስድስት ወራት ያህል ክፍተኛ ክረምትና ቅዝቃዜ ባለበት አገር ይህንን ዐይነቱን ሁኔታ ለገበያ ተዋንያን መልቀቅ በፍጹም አይቻልም። ስለሆነም የጀርመንም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ አገዛዞች በክፍተኛ ርብርቦሽና የመንግስታት ጣልቃ-ገብነት ነው ከገቡበት አዘቅት ማንሰራራት የጀመሩት። በከፍተኛ ደረጃ በእንግሊዝና በአሜሪካን ቦንብ የተደበደበችውና በተለይም እንደበርሊን የመሳሰሉት ትላልቅ ከተማዎቿ ከ80% በላይ የወደሙባት ጀርመን  መንግስትና ህዝቡ ጠቅላላውን ኢኮኖሚውን ለመገንባት የቻሉት ከ15-20 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ከዚያም በኋላ ነው ጀርመን በኤክስፖርት መስኳ በማደግ አሜሪካንን ቀድማ ለመሄድ የቻለችው። ኢኮኖሚውም በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ በመመስረቱና ይህም ዋና የጀርባ አጥንት በመሆኑ ነው የጀርመን ማርክ ወይም ገንዘብ ጠንካራ ሊሆን የቻለው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኦይሮ ነው የመገበያያው ገንዘብ። ይህም የሚያረጋግጠው የአንድ አገር ገንዘብ ሊጠነክር የሚችለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሲደገፍና የመሽከርከር ኃይሉም ሲጨምር(The Velocity of Money)ብቻ ነው። ሌላ ምስጢር የለውም። እንደኛ አገር የተዝረከረክ ኢኮኖሚ ያለው አገር ሁልግዜ ለአደጋ ይጋለጣል።

ለማንኛውም በአሁኑ ወቅት የአባዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ገንዘቦች በወርቅ የተደገፉ አይደሉም። ማዕከላዊ ባንኮች ግን ከፍተኝ የወርቅ ክምችት አላቸው።  በአጠቃላይ ሲታይ ከካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ስንማር እያንዳንዱ አገር ኢኮኖሚውን ማሳደግና አገር መገንባት የቻለው ከውጭ በመበደር ሳይሆን የአገሩን ገንዘብ በማተምና ጥበባዊ በሆነ መልክ ምርት በብዛትም ሆነ በዐይነት እንዲመረት በማድረግ ነው። በተለይም በመንግስታት ቁጥጥር ስር ያሉ የቁጠባ ባንኮችና አገርን ለመገንባት የሚያገለግሉ ልዩ ዐይነት የባንኮች አወቃቀር ርካሽ ብድርን ለአምራች ኃይሎች በማቅረብ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ችለዋል። ይህ ነው በኬይንስ የተፈጠረውና ተግባራዊ በመሆን ውጤታማ የሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ። ማክሮ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ትልቅ ነገር ከሚለው ከግሪክ የተወሰደ ቃል ሲሆን የብዙ ነገሮች ውህደት ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማክሮ ከማይክሮ ውጭ ሊታሰብ በፍጹም አይችልም። ለምሳሌ የካፒታሊስት አገሮችን ኢኮኖሚ አወቃቀር ስንመለከት በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ትናንሽና ማዕለከኛ ኢንዱስትሪዎች አሉ። ትላልቅ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎችም አሉ። ትላልቅ ኩባንያዎችም በትናንሽ ኢንዱስትሪዎች የሚመኩ ናቸው። ለምሳሌ መኪና የሚያመርተው በዓለም የታወቀውና ትልቁ የመኪና አምራች መርቼዲስ ቤንዝ በመባል የሚታወቀው ኢንዱስትሪ ወደ 5000 የሚጠጉ ልዩ ልዩ የመለዋወጫና የሚገጣጠሙ ምርቶችን ከሚያመርቱ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር የተሳሰረ ነው። እነዚህ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ልዩ ልዩ ምርቶችን፣ ለምሳሌ እንደ ጎማ፣ መስታወትና ሌሎች የመለዋወጫ ምርቶችን አምርተው ለመርቼዲስ ይሸጣሉ። መርቼዲስ የመኪናውን ዲዛይንና ካሮሰሪውን ከሰራ በኋላ በመገጣጠም የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን መኪናዎችን ያመርታል። በዚህ መልክ የተሳሰሩና በስራ ክፍፍል የሰለጠኑ ኢንዱስትሪዎች ለአጠቃላይ የካፒታሊዝም የሀብት ክምችት(Capitalist Accumulation) መሰረት ይሆናሉ ማለት ነው። የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና  ከአገልግሎትና ከንግድ መስኩ ጋር ተዳምረው ለብዙ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ የስራ መስክ ይከፍታሉ። በአጠቃላይ ሲታይ በሁሉም ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት መስኩ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞችና የሚመረቱትም ምርቶችና አገልግሎቶች እንደማክሮ ይቆጠራሉ። ስለሆነም በማይክሮና በማክሮ ኢኮኖሚክስና በፖሊሲው መሀከል ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት አለ ማለት ነው። አንዱን ነገር ከሌላው ነጥሎ ማየት አይቻልም ማለት ነው። ከዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ አተናተንና ተጨባጩም ሁኔታ ስንነሳ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ፣ እንዲሁም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውና ፖሊሲም ተብሎ ሊጠራ የሚችል አይደለም።

አሁን ካለንበት የተወሳሰበ ቀውስ ለመውጣት የግዴታ ከብዙ አገሮች፣ በተለይም ኋላ ላይ ከአደጉ አገሮችና በቴክኖሎጂ ከመጠቁ የምንማረው ነገር አለ። በመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ሚና ግልጽ በሆነ መልክ መቀመጥ አለበት። መንግስት ወይም አገዛዝ በኢኮኖሚና በአገር ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት መታወቅ አለበት። በተለይም የመፍጠር ስሜት በሌለበትና የንግድና ኢንፎርማል መስክ ብለን የምንጠራው በተስፋፋበት አገር ውስጥ መንግስት ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ እንዳይወስኑ በሩን ሁሉ መዝጋት አስፈላጊ ነው። ከእንግዲህ ወዲያም በፍጹም ከእነዚህ ተቋማት አለመበደር። ተከታታይ ብድር ልንወጣው የማንችለው ማጥ ውስጥ ነው የሚከተን። በሶስተኛ ደረጃ፣ የአገራችንን ገንዘብ ከእንግዲህ ወዲያ ከዶላር ጋር ሲነፃፅር አለመቀነስ። የገንዘቡ የመግዛት ኃይል በገበያ ህግ መተመን አለበት የሚለው ነገርም  መነሳት አለበት። የአገራችን ገንዘብ ቋሚ በሆነ መልክ(Fixed Exchange Rate) መተመን አለበት። ተለዋዋጭ መሆን የለበትም። ከበስተጀርባው በወርቅ መደገፍ አለበት። ይህ ማለት ግን ገንዘቡ በወርቅ ይለወጣል ማለት አይደለም። በአራተኛ ደረጃ፣ የጥቁር ገበያ የሚባለውን መቆጣጠርና በዚህ ላይ የተሰማሩትን በከፍተኛ ቅጣት እየቀጡ ትምህርት ማስተማር። የሚያሳዝነውና የሚያስቀው ነገር በመንግስትና በማዕከላዊ ባንኩ የጥቁር ገበያ ዕውቅና ተስጥቶታል፤ በትቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ  እንደፈለጋቸው ይወራጫሉ። በተዘዋዋሪ የጥቁር ገበያ ህጋዊ እንዲሆን ተደርጓል ማለት ነው። የጥቁር ገበያን ላንዴም ለመጨረሻም ጊዘ ለማጥፋት ልዩና የሰለጠኑ ተቆጣጣሪ ፖሊሶችን ማሰማራት ያስፈልጋል። በአምስተኛ ደረጃ፣ ከውጭ በምንም ዐይነት የቅንጦት ዕቃዎችን አለማስገባት። እንደመኪና፣ መጠጥና ሌሎችም የቅንጦት ዕቃዎች መከልከል ወይም በከፍተኛ ቀረጥ በመቅረጥ መገታት አለባቸው። በስድስተኛ ደረጃ፣ ትላልቅ ሆቴልቤቶችን አለመስራት። በተጨማሪም ሪል ስቴት የሚባለው የህንፃ አሰራር መቆም አለበት። እንደነዚህ የመሳሰሉት ህንፃዎችን ለመስራት ከውጭ የማለቂያ ዕቃዎች ከፍተኛው ወጭ እየተመደበላቸው እንዲመጡ እየተደረጉ ነው። በሰባተኛ ደረጃ፤ የውጭ ምንዛሪን ለአስፈላጊ ነገሮች ብቻ ለምሳሌ ለማሽን፣ ለልዩ ልዩ የመለዋወጫ ዕቃዎችና መድሀኒቶች ብቻ መመደብ። ይህ ዐይነቱ ዘዴ የከረንሲ ቁጥጥር(Currency Controlling)  በመባል    ሲታወቅ ቻይና ውስጥ በተግባር የተመነዘረና ውጤታማ የሆነ ነው።  በዚህ መልክና በአገር ወዳድነት ስሜት በታታሪነት ስንሰራና፣ በተጨማሪም ሀቀኛ ከሆን ብቻ ነው አገራችንና ህዝባችንን ከገቡበት ቀውስ ውስጥ ለማውጣት የምንችለው።

አሳዛኙ ነገር አብዛኛዎቻችን በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሰለጠን በመሆናችንና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ተግባራዊ ከሚሆነው ወይም ከሆነው ጋር የማወዳደር ዕድል ስለማይኖረንና ስለማንፈልግም አንድን ነገር ብቻ እንደ ርዕዮተ-ዓለም ሙጭጭ አድርጎ በመያዝና አሱን እየመላለሱ ተባራዊ በማድረግ አንድን አገር እናፈራርሳለን። ህዝብን እናደኸያለን። አቅመ-ቢስም እንዲሆን እናደርጋልን። አገራችንን ወደ ኒዎ-ሊበራል የገበያ አዳራሽ በመለወጥ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ እናደርጋለን። ኪሳችን በገንዘብ ሲያብጥ የምናደርገውን አናውቅም። ይህን ሁሉ የታሪክ ወንጀል እየፈጸምን ካለኛ አዋቂ የለም እያልን በሰው ላይ እንሳለቃለን። አገርን አፈራርስን፣ ህዝብን አቅመ-ቢስና ደሃ አድርገን፣ እንዲሁም የብልግና ኢንዱሱትሪ እንዲስፋፋ ካደረግን በኋላ አንድ ቀን ሁላችንም ወደማይቀረው ዓለም እንጓዛለን። እዚያም ፍርዳችንን እናገኛለን።

ከዚህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ዝቅጠት ለመውጣትና አዲስ ታሪክ ለመስራትና ለማስመዝገብ ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ሁሉንም ነገር ማድረግ ይቻላል፤ ቅንጆ ቆንጆ ስራዎችንም መስራት ይቻላል። ታሪክን በአዲስ መልክ እንዲጻፍ ማድረግ የምንችለው ልዩ ልዩ መጽሀፎችን በማንበብና በማወዳደር ብቻ ነው።  በሌላ ወገን ግን በእኔ የፀና ዕምነት ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለኢኮኖሚም ሆነ ሰፋ ላለ የህብረተሰብ ዕድገት አስፈላጊ ቢሆንም በአገራችን ምድር በሰፈነው አገዛዝና የመንግስት አወቃቀር  መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት በፍጹም አይቻልም። መታወቅ ያለበት ነገር በአገራችን ምድር ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝና ኤሊት ነኝ የሚለው በሙሉ ዝቃጮች ናቸው። ሰውነታቸውን ከማደለብ በስተቀርና በመኪናዎችና በልብስ ከመሽብረቅረቅ በስተቀር የሚታያቸው ምንም ነገር የለም። የዛሬን እንጂ የነገን የሚያስቡ አይደሉም። ለልጆቻችን ምን ታሪካዊ ነገር ሰርተን መሄድ አለብን ብለው የሚያስቡ አይደሉም። እነዚህ ሰዎች እንደሰው ቢንቀሳቀሱም ጭንቅላታቸው ደንዟዟል። የሚታዩ ነገሮችን ማየት የማይችሉ ናቸው። ስለሆነም ስለ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በምናወራበት ጊዜ ከመንግስትና ከፖለቲካ አወቃቀሩ፣ ከተቋማትና ተቋማትን ከሚቆጥጠሩት ሰዎች ውጭ ማየት አንችልም። በሌላ አነጋገር፣ አካሄዳችን ሁለ-ገብ መሆን አለበት። በከፍተኛ የጭንቅላት ስራና የስብአዊነት አስተሳስብና በዚህ መሰረተ-ሃሳብ ብቻ በመመራት ነው በአገራችን ምድር ዐይነተኛ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው። ባጭሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የህብረተሰብ ግንባታን ከመንግስት አወቃቀር፣ የመንግስቱን መኪና ከሚቆጣጠሩትትና ከውጭ ሆነው እንደፈለጉ ከሚያሽከረክሯቸው የውጭ ኃይሎች ውጭ ነጥሎ ማየት ከፍተኛ ስህተት መስራት ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው። ስለሆነም አላፈናፍንም ያለውንም ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይልና የአሰራር ዘዴውን ማወቅ ይስፈልጋል። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የኣለም ባንክ፣ በአጭሩ የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው የሚያስፋፉት የነፃ ገበያ የሚባለው ነገርና ፖሊሲያቸው ሳይንሳዊ መሰረት እንደሌላቸው  ማወቅ ይኖርብናል። አካሄዳቸውና አረማመዳቸው የህብረተስብንና የተፈጥሮን ህግ እንደሚፃረር ንመገንዘብ ይኖርብናል። ዋና ዓላማቸውም ለዝንተ-ዓለም የበላይነት ይዞ መቆየትና በተቻለ መጠን የዓለምን የትሬ-ሀብት መቆጣጠር ነው። የብላክ ሮክ ዋና ማኔጀር እንደሚለው የሰውን ልጅ እያስገደድን አስተሳሰቡን መቀየር አለብን  የሚለው አደገኛ አስተሳሰብ ከዚህ ዐይነቱ ስሌት የመነጨ ነው። ይህን አደገኛ አስተሳሰብና አካሄድ ለመግታት የግዴታ የማሰብ ኃይልን ማዳበር ያስፈልጋል። የተሻለ የአሰራር ስልትና መፍትሄም እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል። መልካም ግንዛቤ!!

            fekadubekele@gmx.de

            www.fekadubekele.com

 

Literature

Aglietta, Michael, A Theory of Capitalist Regulation: Th US Experience, London, 1979

Arie Arnon, Monetary Theory and Policy from Hume and Smith to Wickel: Money Credit and

the Economy, New York, 2011

Bernard Lietaer, Christian Arnsperger et al., Money and Sustainability: From Outdated

Finance System to a Monetary ecological System, Berlin 2013

David S. Landes, The Unbounded Prometheus: Technological Changes & Industrial

Development in Western Europe from 1750 to the Present, UK, 2003

David S. Landes, The Wealth and Poverty of Nations: Why Some are Rich and some so poor

New York & London

Erick, S. Reinert, How Rich Countries Got Rich… and Why Poor Countries Stay Poor,

London, 2007

Fekadu Bekele, African Predicaments and the Method of Solving them Effectively, Berlin, 2016

Fekadu Bekele, ካፕታሊዝም፤ የካፒታሊዝም ዕድገትና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍልስፍና አፀናነስ፣ በርሊን፣ 1994

Frederic Soddy, Wealth, Virtual Wealth and Debt: The Solution of the Economic Paradox,

London, 1983

Frederick G Lawrence, Patrick H, Byrne et al, Collected Works of Bernard

Lonergan: Macroeconomic Dynamics; An Essay in Circulation and Analysis,

London, 1999

Helmut Creutz, The Money Syndrome; Ways out of Market Economy Crises, Berlin, 1995

James Angresano; The Political Economy of Gunnar Myrdal, US, 1997

John Maynard Keynes; The General Theory of Employment Interest and Money, London, 1967

Karl Marx, Capital Vol. 1: A Critical Analysis Capitalist Production, York, 1975

Karl Marx, Capital Vol.2: The Process of Circulation of Capital, New York, 1975

Karl Marx, Capital Vol. 3: The Process of Capitalist Production as a Whole, New York, 1975

Kate Raworth, Doughnut Economics:  Seven Ways to Think Like a 21st-Century Economist,

London, 2017

Paul Mattick, Marx & Keynes: The boundary of mixed economic systems, Viena, 1971

Per Molander, The Anatomy of Inequality: where it comes and how we can control it,

Frankfurt am Main, 2017

Robert J. Gordon, Macroeconomics, New York, 2000

Stephan Schulmeister; The Road to Prosperity, Salzburg, 2018

Steve Keen, Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned? New York, 2011

Thomáš Sedláček, The Economy of Good and Evil, New York, 2011

Vivian Walsh & Harvey Gram, Classical and Neoclassical Theories of General Equilibrium:

Historical Origin s of Mathematical Structure, New York& Oxford, 1980

William H. Branson & James A. Litvack, Macroeconomics, New York, 1972

 

ማሳሰቢያ 1፤ አብሮ በማጥናትና በመከራከር ብቻ ነው ጠቃሚና ገንቢ ትምህርት ለመቅሰም የሚቻለው። የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ ተጨባጭና ለአገር ግንባታ የሚሆን ዕውቀት ሊያስጨብጠን በፍጹም አይችልም። በተለይም የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማነፃፀርና የኢኮኖሚ ዕድገትን ከታሪክ አንፃር መመርመሩ በጣም አስፈላጊ ነው። ታሪክ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ነገር ባለበት ሊቆም አይችልም። ዛሬ ያለው የኢኮኖሚ ስርዓት ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ በዚህ መልክ ሊሰራና ሊቀጥል ይችላል ብሎ ማሰብ የታሪክንና የሰውን ልጅ ውስጣዊ ኃይል አለመረዳት ነው። እብሮ ለመማርና ዕውቀታቸውንም ሊለግሱ የሚፈልጉ ካሉ አንድ የመወያያ ክፍል በመክፈት ሃሳብ ለሃሳብ ለመለዋወጥ እንችላለን።  በተረፈ ይህ ግለሰብ የራሱን መድረክ በመክፈት ለማስተማር ዝግጁ ነው።

ማሳሰቢያ 2  ስለካፒታሊስት ኢኮኖሚ አወቃቀርና ውስጣዊ አሰራርና የአመራረት ዘዴ፣ እንዲሁም ዕድገት ለማወቅ የፈለገ ሰው የግዴታ በካርል ማርክስ የተጻፈውንና በፍሪድሪክ ኤንግልስ በመጠናቀር እንዲታተም የተደረገውን ሶስት ቅጽ መጽሀፎች ማንበብ ብቻ ሳይሆን በሚገባ አጥንቶ መረዳት ያስፈልጋል። እነዚህን ሶስት ቅጾችና፣ በተጨማሪም በፈረንሳዩ ኢኮኖሚስት በአግሌይታ ሚካኤል የተጻፈውን መጻፍ ያላነበበ ሰው አስር ጊዜ ማክሮ ኢኮኖሚ እያለ ቢወተውት ስለገበያ ኢኮኖሚ አወቃቀርና አሰራር በፍጹም ሊረዳ አይችልም። የማርክስ የኢኮኖሚክስ ስራዎችም በአንዳንድ በታወቁ ኢኮኖሚስቶች በአንዳንድ ትላልቅ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በግሩም መልክ በትምህርት መልክ ይሰጣሉ። የማርክስ የኢኮሚክስ ስራዎችም ስለኮሙኒዝም የሚያትቱ ሳይሆኑ እንዴት የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንደተጸነስና ኦርጋኒካል በሆነ መልክ እንዳደገ የሚያትት ሲሆን፣ በተለይም በገንዘብና በምርት ክንዋኔ መሀከል ያለውን መተሳሰርና ባንኮችም ለኢኮኖሚው ዕድገት ዕምርታ ያላቸውን ትልቅ ሚና የሚያሳይ ነው። ስለሆነም የማርክስን ዳስ ካፒታልና በታወቁ የማርክስን ስራዎች ከተረጎሙና ከታወቁ ኢኮኖሚስቶች ጋር ሳይተዋወቁ ስለኢኮኖሚክስ ምንነት በፍጹም መረዳት አይችልም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

193058
Previous Story

ከፋኖ መንደር የምስራች ተሰማ | አማራ ፋኖ በጎንደር አርበኛ ባየ ቀናዉ!

Amhara Fnaos m456
Next Story

የአማራ ፋኖ የሚታገለው በአንድ አና ለአንድ መርህ ነው! ሁለት መስመር እና ሁለት አላማ የለውም

Latest from Blog

“መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የሚለው የዲያስፖራ ከንቱ አታካራ! – ክፍል ሁለት

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) በአንዳንድ ስብሰባዎችና የሕዝብ መገናኛ መድረኮች የሚታየው የአንዳንድ ዲያስፖራዎች  “መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የበከተ ከንቱ አታካራ በልጅነታችን ወላጆቻችን ትምህርት እንዲሆነን ይተርኩልን የነበረውን ከጫጉላ ወጥተው ጎጆ ለመመስረት የታከቱ ሁለት ያልበሰሉ ባልና ሚስትን ታሪክ

መነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ እና ወያኔያዊ መሠረቱ

የማይወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል። የዛሬን አያድርገውና የትግሬ ልሂቆች “ትግራይ የጦቢያ መሠረት ናት ።  ጦቢያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይ ያለ ጦቢያ ሊታሰቡ አይችሉም” በማለት ጦቢያዊ ከኛ ወዲያ ላሳር እያሉ አለቅጥ ይመጻደቁ፣ ይኩራሩ፣ ይታበዩ ነበር። ወያኔ

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባሉ

ለአመታት በእረስር ላይ የሚገኙት  አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና የዕርስ በዕርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀሎች ጥፋተኛ መባላቸው ታውቋል፡፡ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱበት ክሶች በዛሬ ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ

ከ”ችርቻሮ” ድል አልፎ ለመሄድ የአንድነት አስፈላጊነት – ግርማ ካሳ

በአሁኑ ጊዜ ሁለት የፋኖ አሰላለፎች አሉ:: መኖር ያልነበረበት:: አንከር ሜዲያ ከሁለቱም አሰላለፎች፣ ሁለት ፋኖ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ሁለቱን አደመጥኩ፡፡ በሰማሁት ነገር ተደስቻለሁ:: ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅም አድርጎኛል:: የአማራ ህዝባዊ ድርጅት የፖለቲካ
Go toTop