በላይነህ አባተ ([email protected])
በጊዜ ያለመዘጋጀትን ጎጅነት አባቶች በተረት ሲገልጡ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥስ ይላሉ”፡፡ ለዚህ አባባል እንግዳ ለሆነ ተረቱ የሚገልጠው ሰርገኛ ከደጅ ቆሞ በሆታ ግባ በሉኝ እያለ በርበሬ ተጓሮ ቀንጥሶ፣ ፈጭቶ፣ ድልህ አዘጋጅቶና ወጥ ሰርቶ ሰርግ ለመደገስ የመደናበርንና የመንደፋደፍን ከንቱነት ነው፡፡
አያቶቻችንና ወላጆቻን ያሳደጉን ሰርገኛ ሲመጣ በርበሬ ቀንጣሾች እንድንሆን አድርገው ሳይሆን ክፉ ቀን ሲመጣ ለመቋቋም የምንችል ዝግጁዎች አድርገው ነበር፡፡ አባቶቻችን ምኒሽር፣ በልጅግ፣ ጓንዴና እናት አልቢን ፈቶ መገጣጠም ማስተማር የሚጀምሩት ገና የስድስትና የሰባት ዓመት ልጆች ሳለን ነበር፡፡ አሁን ትችላለህ ወይ ብላችሁ አፋጣችሁ አትያዙኝ እንጅ በስምንት አመቴ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ረጅም ምኒሽርና እናት አልቢን ፈትቼ መግጠም እችል ነበር፡፡ የነፍጥ አገጣጠሜን ትክክለኛነት የሚመለከተው አባቴ “ጠመንጃህን እንደዚህ ፈታተህ ሳለ አጥቂ ጠላት ቢመጣብህ ራስህን ለመከላከል ቅድሚያ መግጠም ያለብህ የትኞችን የጠመንጃ ክፍሎች ነው” ብሎ በጥያቄ ያፋጥጥና በፍጥነት ማድረግ ያለብኝን ያስተምረኝ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አባቶች ምግብ ስንበላ ውሀ እንዳንጠጣ ይመክሩን ነበር፡፡ ይህንን ያነበበ ኢሳይንሳዊ አድርጎ ሊነቅፍ ይችላል፡፡ አባቶች ይኸንን የሚያስተምሩት ግን ይህቺ ምድር ከኢፍትሐዊነትና ከመከራ ከቶውንም ስለማትላቀቅ ውሀ ከማይኖርበት ሥፍራ ለሚጥል የመከራ ዘመንም እያዘጋጁን ነበር፡፡
አያቶቻችንና ወላጆቻችን በዚህ መልክ ያሳደጉን ሰው በጦርነት ወቅት ራሱን ለመከላከል መዘጋጀት ያለበት በሰላም ጊዜ መሆኑን ለማስተማር እንደነበር የገባኝ ያኔ ሳይሆን በጣም ዘግይቶ ነበር፡፡
የዚች ዓለም የማያባራ ተንኮል የገባችው አያቶቻችንና ወላጆቻችን በዚህ መልከ እያሳደጉን ሳለ የመጤ ባህል ወረርሽኝ ክፉኛ በአይበሉብሽ ጥፊ መትቶ አጠናገረንና ኮሚኒስት አስተማሪዎቻችን እያዬን ጎፈሬአችንን የተከረከመ ጥድ አስመስለን መሄድ ጀመርን፡፡ አዘናጊ የምእራባውያን የባህል እክክ ንፍርቅ ስላደረገን እነሱ ከጠመንጃ አልፈው አቶሚክ ቦንብ በሚሰሩበት ሰዓት እኛ ጠምንጃ መያዝ ያለመሰልጠን ምልክት ነው ተባልንና እርግፍ አርገን ተውን፡፡ ስለጠመንጃ የተማርነውን ጥበብም እረሳን፡፡ አባቶች እጅግ ተጠብበው የቀመሩትን ሽለላና ፉከራ የድንቁርና ምልክት ነው ብለው ጥባ ጥቤ ሲጫወቱብን እርግፍ አርገን ትተን በፈረንጅ ቅጥ የሌለው ዳንስ እንደ ጠገበ ጥንዚዛና ፌንጣ መንፈራገጥ ጀመርን፡፡ ሌላው ሳይቀር የታማኝነትና የቃል ኪዳን ምልክት የሆነውን ማተብ ያለመሰልጠን ምልክት ነው ስለተባልን ተአንገታችን ቦጭቀን ጣልን፡፡ “ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው!” እንደሚባለው አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በራሳችንን ቋንቋ መጠቀም ያለመሰልጠን ወይም ያለመማር ምልክት እየመሰለን በፈረንጅ ቋንቋ ታልሆነ በራሳችን ቋንቋ ለማንበብ እንደ ዲዳ የምንተባተብ፣ ለመጻፍ ጣታችን እንደ ሰካራም እጅ የሚንቀጠቀጥ፣ ለመናገርም አንደበታችንን በፍቅር እንደነሆለለ ጎረምሳ ጥርቅም የሚያደርገን ሆንና አረፍን፡፡
በዚህ መልክ ከቅደምት አባቶችቻችን ጋር የሚያይዘን እትብት ቡድስድስ አርገን ቦጭቀን ከእነሱ ጋር በቆዳ ቀለም ብቻ የምንመሳሰል አዲስ ተክሎች ሆነን ቁጭ አልን፡፡ የቀደምት አባትና እናቶቹን ግንድ ትቶ ተሌላ ግንድ ተጣብቆ የበቀለ ተክል አዲስ ተክል እንዲያውም አለቦታው የበቀለ አረም መሆኑን ዘነጋን፡፡ ይህ የኣዲስ ተክልነት፣ የአደራ በላነት ወይም የአደራ ቀበኛነት ባህሪያችንም ለዛሬው መከራ አጋልጦ ሰጠን፡፡ የፈረንጅ ዓይን አይተው ምን እንደሚያስብ አንጠርጥረው ተሚያውቁት ቀደምት አባቶቻችን የሚያገናኘን እትብት ቦጫጭቀን በመጣላችን “ቋንጃችሁን ልንሰበር መጣን!” ብለው እየነገሩንም በጊዜ ዝግጁ ስላልነበርን ይኸንን ትውልድ ለዘር ፍጅት አጋልጠን ሰጠን፡፡
ደግነቱ ተከፊሉ የሰፈር አውደልዳይና ባንዳ በቀር አዲሱ ትውልድ የሚመስለው እኛን ሳይሆን ቅድመ አያቶቻንን መሆኑ በጀን፡፡ የቀደምት አባቶች አዙሮ ማያ አንገት እያጠረንም የራሳችንን ትውልድ እንደ ብቁና ብሩክ ቆጥረን የራሳችንን ኃላፊነት ስላልተወጣን የባከነውና ባንዳ የሆነውን የአዲስ ትውልድ ክፍል ስንወቅስ ትንሽ እንኳ ስግጥጥም አይለን፡፡ የቤተመንግስቱ፣ የቤተክህነቱና የመስጊዱ አስተዳደር በባንዳና በሆድ አደር ከርሳሞች ጢም እስቲል ተሞልቶ አስርተ ዓመታት በቆየበት አገር ከፊሉ አዲስ ትውልድ በሆዱ እሚገዛ ባንዳ መሆኑ ብዙም አይግረመን፡፡
ይልቁንስ በዚህ ትውልድ ጣት መቀሰሩን ትተን እኛ የአባቶቻን አደራ እንደ ቆሎ እምሽክ አርገን ቆርጥመን የበላን ጉዶች ይህንን ትውልድ እንዲህ ብለን ይቅርታ መጠየቅና ጥልቅ ምስጋና ማቅረብ አለብን፡፡ “ቀደምት አባቶች ያስረክቡንን ዋንጫ ለእናንተ ማስረክብ ሲገባን እንደ ሰካራም ብርጭቆ ስብርብር አርገን ወርውረን ለአደጋ ስላጋለጥናችሁ ተእግራችሁ ስር ተደፍተን ይቅርታ እንጠይቃለን! እኛ ወላጆቻችሁና ታላላቆቻችሁ የራሳችንን የጀግንነትና የወኔ ባህል አፈር ድሜ አስግጠንና የሚያዘናጋ የባእድ ባህል ወርሰን ሰልጥነናል በሚል የባርነት መንፈስ ነፍዘን ተግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አሳለፍን፡፡ እናንተ ግን እኛ የጣልነውን የጀግንነትና የወኔ ባህል ተጣልንበት አንስታችሁ ወደ ቅድመ አያቶቻችሁ መንበር በመስቀል ላይ ስላላችሁ የቅደም አያቶቻችሁ መንፈስ ይባርካችሁ፣ ይቀድሳችሁ፡፡ እኛ ሰልጥነናል ብለን ቡጭቅጭቅ አርገን የጣልነውን ማተብ አንስታችሁ በማሰራችሁ እምነትንና ቃል ኪዳን የሚወደው እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ፡፡ እኛ የሰለጠን መስሎን ተፈረንጅ በኮረጅነው ተልካሻ ቦክስ፣ ቴስታና ጅዶ የቀየረነውን ነፍጥ አንስታችሁ ዘራችሁን ተመጥፋት በማዳን ላይ ስላላችሁ የማንም ዘር ተምድር እንዲጠፋ የማይፈልገው እግዚአብሔር ዘራችሁን ያብዛላችሁ፡፡ እኛ መቀመጫችንን እንደ ውሀ ወፍጮ ሞተር እያሽከረከርን ስናብድ የኖርንበትን የፈርንጅን ዳንስ አሽቀንጥራችሁ በቅድመ አያቶቻችሁ እስክስታ፣ ቀረርቶና ፉክራ እየተገማሸራችሁ ስላላችሁ የቅድመ አያትን አደራ መጠበቅ የሚወደው መለኮት ይጠብቃችሁ፡፡ በደስታም ሆነ በሐዘን ወቅት ቅድመ አያቶቻችሁ በብሉይ ኪዳን ትዕዛዛት መሰረት በጠበቡት የባህል ልብስ ደምቃችሁና ተውባችሁ እየታያችሁ ስላላችሁ መለኮት በሄዳችሁበት ሁሉ ይከተላችሁ፡፡”
ለማሳረግም ተቀደምት አባቶቻችን የልጅ አስተዳደግ ሥስልትና ትምህርት በሚመሳሰለው ኤሶብ (Aesop) ጥልቅ ትምህርታዊ ተረት ልሰናበታችሁ፡፡
ከእለታት አንድ ቀን አንድ ከርከሮ ኩንቢውንና አቀንጣጤውን በዛፍ ግንድ ሲስል ቀበሮ አገኘው፡፡ ቀበሮው ከርከሮው የሚያደርገው ነገር ገረመውና ጠጋ ብሎ “ ወንድም ከርከሮ እዚህ አካባቢ የዱር እንሰሳ አዳኝም ሆነ ሌላ የሚየሰጋ ነገር ፈጥሞ አላይም፡፡ በአሁኑ ወቅት ጫካው፣ ጋራውና ሜዳው ሰላም ነው፡፡ ለምንድን ነው ኩምቢህንና አቀንጣጤህን የምታሰላው?” ሲል ጠየቀው፡፡ ከርከሮውም “ አደጋ ሲመጣማ ራስህን ለመከላከል እመር ብልሀ ጉርንቦ ማነቅ እንጅ መሳሪያ የማዘጋጃ ጊዜ አይኖርህም” ሲል በሰላም ጊዜ ለጦርነት የመዘጋጀትን ጥበብ ብልጥ ለሚባለው ቀበሮ ሳይቀር አስተማረው፡፡
ይህ ትምህርት የኤሶብ ተረት በመባል ይታወቅ እንጅ ቀደምት አባቶቻችን ለአምስት ሺ ዘመናት ከትውልድ ትውልድ እያስተላለፉ አገር የገነቡበት፣ ክብርና ነፃነታቸውን የጠበቁበት ጥበብ ነው፡፡ የዛሪውም ሆነ መጪው ትውልድ መከተል ያለበት ይኸንን ዘመን የማይሽረው ጥበብ ነው፡፡ ትውልድ ሙጪጭ አርጎ መያዝ ያለበት ተዓለም በፊት ፊደልና የጊዜ ቀመር ቀርጸው፣ ተኖህ የሰላም ቀስተ ደመና የተወሰደ በተስፋ ያሸበረቅ ሰንደቅ ሰቅለው፣ በብሉይ ኪዳን የተደነገገ ድንቅ የአለባበስ ጥበብን ጠብበው፣ እረኛው ዳዊት ያንቆረቆራቸውን ዋሽንት፣ በገና፣ ክራርና መሰንቆ እየተጠቀሙ እንኳን ቆሞ እሚሄድን ሙትን ከመቃብር የሚነሽጡ የጀግነንት፣ የወኔ፣ የደስታና የሐዘን ዜማዎች በአለት ላይ ተክለው የሄዱትን ቀደምት አባቶችና እናቶች ፈለግ ነው፡፡
የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ መገንዘብ ያለበት እንደ ከበደ ሚካኤል ታሪኬ ባጭሩ ወኔና ጀግነንት በአንድ ሳምንት ተረግዘው፣ ተወልደው፣ አድገውና ጎርምሰው ጎልማሳ ስለማይሆኑ ከልጅነት ጀምሮ በሽለላ፣ በፉከራና ሌሎችም ጣመ ዜማዎች መታነፅ በሰላም ጊዜ ለጦርነት የመዘጋጃ ዋና ዋና መንገዶች መሆናቸውን ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.