ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሰኔ 19፣ 2016(ሰኔ 26፣ 2024)
ሰላም አቶ ኤፍሬም ኢትዮጵያን እናድን የሚለውን ጽሁፍህን አነበብኩት። መልካም ጽሁፍ ነው። ይሁንና ጽሁፍህ ገለጻ(Descriptive) ነው እንጅ አናልይቲካል አይደለም። እነ ማዲሰን፣ ቶማስ ጀፈርሰን፣ ቤንጃሚን ፍራንክሊንና የኋላ ኋላ ደግሞ እነ አብርሃም ሊንከንና ሃሚልተን አሜሪካንን እንደ ፌዴራል ስቴት ወይም እንደ ህብረ-ብሄር ሲመሰርቱ ከምንም ተነስተው አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ አብዛኛዎቹ አሜሪካንን በመጀመሪያው ወቅት እንደ ህብረ-ብሄር የገነቡት መሪዎች በጣም አዋቂዎች ነበሩ። አንድ አገር እንዴት ኦርጋኒካሊ እንደሚገነባና በማኑፋክቸር እንደሚጠነክር ያውቁ ነበር። እንደ ቤንጃሚን ፍራንክሊን የመሳሰሉት ደግሞ ሳይንቲስቶችና ፈጣሪዎች ነበሩ። የመጀመሪያው የአሜሪካን የፋይናንስ ሚኒስተር የነበረው ሃሚልተን ደግሞ የእንግሊዝን ነፃ ንግድ ፖሊሲ በመቃወምና የዕገዳ ፖሊሲ በመከተል ነው በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያ ወይም ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የቻለው። ለዚህ ደግሞ የክሬዲት ሲስተም በማቋቋምና ኢንዱስትሪ ለመትከል ለሚፈልጉ ግለሰቦች ርካሽ ብድር ወይም በዝቅተኛ ወለድ ገንዘብ እንዲበደሩ በማድረግ ነው ቀስ በቀስ አሜሪካ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንድትሆን ለማድረግ የበቃው። ሌላው በእኛ ኢትዮጵያውያኖች ዘንድ የሚዘነጋው ነገር አሜሪካ የተቆረቆረችውና ወደ ኃያልነት ልትቀየር ይቻለችው የኢንዲያኖችን አገር በመውረርና ወደ 17 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን በመግደል ወይም በማረድና ስልጣኔያቸውን በማውደም ነው። ከዚህም በላይ በእነ ቶማስ ጀፈርሰን ዘመን የባርያ ንግድና የባርያ ስራ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፉበት ዘመን ነበር። ይህም ማለት የአሜሪካን ካፒታሊዝም ካለፕላንቴሽን ኢኮኖሚና ሰፊውን የጥቁር ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ ሳይበዘብዝ አልተገነባም። ይህ መረሳት የለበትም። እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ጥቁር አሜሪካኖች በከፍተኛ ደረጃ የሚበዘበዙበትና የሚናቁበት ጊዜ ነበር። በዚህ ዐይነቱ ሁኔታና አብዛኛዎቹም አሜሪካንን የመሰረቱ ነጮች ከአውሮፓ የሄዱ ስለነበሩና ቀድሞውኑ የተስፋፋውን ዕውቀት ይዘው በመውሰድና በማዳበር ነው ትልቅ አገር ለመገንባት የቻሉት። ለዚህ የሚሆኑ ደግሞ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን በመገንባት የሰለጠነ ሰው ለማፍራት ችለዋል። በሌላ አነጋገር አንድ አገር በፌዴሬሽን መልክ ብቻ ማዋቀሩ በቂ አይደለም። የግዴታ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፋት፣ ከተማዎችን መገንባትና ከተማዎችንም በባቡር የሃዲድ መስመር ማገኛት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንድ አገር ለመጠንከር የሚችለው።
ወደ ጀርመን ስንመጣ ታሪኩ በ1871 ዓ.ም በቢስማርክ ዘመን የተጀመረ ሳይሆን በጀርመንም ሆነ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ለህብረ-ብሄር ምስረታ የሚያገለግሉ ቅድመ-ሁኔታዎች ከአስራ ሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ ሆነዋል። በመጀመሪያ ደረጃ የማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ከተማዎች የሚባሉትን በስነ-ስርዓት ለመገንባት ችለዋል። በዚያው መጠንም ፕሮቶ ኢንዱስትሪያላይዜሽን(Proto Industrialization or Industrialization before Industriaization) የሚባለው ነገር በጀርመንም ሆነ በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የተለመደ የምርት እንቅስቃሴ ነበር። ይህም ማለት የዕደ-ጥበብ ስራ መስፋፋትና ምርቱም በነጋዴዎች አማካይነት መሸጥ ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል። በተለይም በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የመንፈስ ተሃድሶ መስፋፋት መጀመሩ የአንዳንድ ሰዎችን ጭንቅላት ሊከፍት ችሏል። በተለይም የሬናሳንስ፣ የፕሮቴስታንቲዝምና የኢንላይተንትሜት እንቅስቃሴዎች ለምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማድረግ ችለዋል። በተጨማሪም በ15ኛው ክፍለ-ዘመን የማተሚያ ማሽን በጉተንበርግ አማካይነት ሲፈጠርና መጽሀፎችንም እንደልብ ማተምና ማስፋፋት ሲጀመር ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማበርከት ችሏል። ከዚያ በኋላ ነው የተፈጥሮ ሳይንስና የፍልስፍና ምርምር የተስፋፋውና መጻፍም የተጀመረው። እንደ ጀርመን ያሉት አገሮች በመሳፍንት አገዛዝ የተከፋፍሉ ቢሆንም በየክልላቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይካሄድ ነበር። ከተማዎችና መንደሮች በሚገባ ተገንብተዋል። የገበያ አዳራሾች በዘመኑ በሚያምር መልክ ተገንብተዋል። ይህ ዐይነቱ የንግድ እንቅስቃሴና የከተማዎች ግንባታ የኋላ ኋላ ለህብረ-ብሄር ግንባታ ምስረታ አመቺ ነበር። ይሁንና ጀርመን ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ጋር ስትወዳደር ኋላ-የቀረች አገር ስለነበርች ቢስማርክ የመጀመሪያው ቻንስለር ሆኖ ከመመረጡ በፊት የፕረሺያ የፍጹም ሞናርኪዎች የትምህርት ሬፎርም በማድረግ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚያመች ሁኔታ አበጅተዋል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ እንደ ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ጎተ፣ ሺለርና ሌሎች አያሌ የፈልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች በመፈጠራቸውና የሃሳብ መንሸራሸርም ያደርጉ ስለነበር የኋላ ኋላ ላይ ጀርመንን እንደ አንድ ግዛት መገንባቱ ከባድ አልነበረም። በዚህ ላይ የከበርቴው መደብ በየቦታው ቀስ በቀስ መዳበር በመቻሉና ከየክልሉ ወጥቶ በኢኮኖሚና በንግድ እንቅስቃሴ መሳተፍ ይፈልግ ስለነበር በጊዜው የነበረው የጉምሩክ ዕገዳ በድርድር እንዲነሳና ጀርመንም እንደ አንድ አገር እንድትታይ ተቀባይነት ያለው ስራ ለመሰራት ቻለ። ስለሆነም ይህ ሁኔታ ሰፋ ላለ የውስጥ ገበያ በሩን መክፈት ቻለ። ነጋዴዎችና ዕቃዎች፣ እንዲሁም ምሁራን ካለምንም ገደብ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመሄድ ዕድል በማግኘታቸው የተነሳ ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ አዳዲስና ፈጣሪ ኃይሎች ብቅ እንዲሉ አስቻለ።ይሁንና አንዳንዶች የጀርመንኛ ተናጋሪ የሆኑ ቦታዎችና በመሳፍንታት የሚገዙ በአንድ አገዛዝ ስር ለመጠቃለል ፍላጎት ስላልነበራቸው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ኃይልን መጠቀም አስፈልጎ ነበር። አንዳንዶችን በማታለልና በጉቦ በመግዛት ወደ አንድ አገዛዝ እንዲመጡ ሲደረጉ፣ እምቢ ባሉት ላይ ደግሞ ጦርነት ማካሄድ አስፈልገ። የኋላ ኋላ ላይ ጀርመንም ከውስጥ የመጠናከር ዕድል ስላጋጠማት ከአውስትሪያና ከፈረንሳይ የመጣባትን ጦር በመከላከልና በአሸናፊነት በመውጣት የመጀመሪያው የተጠቃለለ አገዛዝ ሊመሰረት ቻለ። እነቢስማርክም ይህንን ዕድል በመጠቀም ነው ሁለ-ገብ የሆነ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያ ወይም ኢኮኖሚ መገንባት የቻሉት። በጊዜው የነበሩት በጥሩ የኢኮኖሚ ዕውቀት መንፈሳቸው የታነፀ ግለሰቦችና ፈላስፋዎች በአገዛዙ ላይ ጫና በማድረግ ነው ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ መገንባት የተቻለውና ጀርመንም በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝንና ፈረንሳይን ቅድማ ለመሄድ የቻለችው። በአጭሩ ቀድሞ ከሁለትና ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት የቤት ስራ ባይሰራና ቅድመ-ሁኔታዎች ባይነጠፉ ኖሮ ጀርመን የኋላ ኋላ እንደ አንድ ህብረ-ብሄር ልትገነባ ባልቻለች ነበር። ይሁንና በተለይም ካፒታሊዝም እየተስፋፋ ሲመጣና ማበጥም ሲጀመር ሙሉ በሙሉ ያልተዳከመው ሃላ-ቀር የሆነው የፕረሺያ የመንግስት አወቃቀርና የሚሊታሪ መንፈስ ለመስፋፋት በመፈለጉ የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት በጀርመን ምድር ተቀሰቀሰ። ቀጥሎም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በመቀስቀስ በአውሮፓ ምድር ከፍተኛ እልቂትን አስከተለ። እስከዚያን ጊዜ ድረስ የተገነቡ የሚያማምሩ ከተማዎችና ስልጣኔዎች እንዳለ ወደሙ። ውጤቱም በአውሮፓ ምድር ከ50 ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንዲያልቅ አደረገ። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን አገሯንና ኢኮኖሚዋን እንደገና ከዝቅተኛ ሁኔታ በመነሳት መገንባት ነበረባት። ለማንኛውም ካፒታሊዝም በአሜሪካንም ሆነ በተቀሩት የአውሮፓ አገሮች ሊያድግና ሊስፋፋ ቢችልም ይህ ማለት ግን እኛን ነፃነትን አጎናጽፎናል ማለት አይደለም። የካፒታሊዝም ማደግና ወደ ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም መሸጋገር የአውሮፓን አገሮች ኋላ-ቀር የሚባሉ እንደ አፍሪካና ላቲን አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮችን እንዲወሩና ጥሬ-ሀብታቸውን እንዲዘርፉ አስቻላቸው። የካፒታሊዝም ማደገና ማበጥ ከሰላማዊ መንገድ ይልቅ አመጸኛና ጦረነት አስፋፊ በመሆን የሌሎች አገሮችን ዕድገት ማጨናገፍ ቻለ። ይህ ጉዳይ ዛሬም ያለና በገሃድና በድብቅ በተወሳሰበ መልክ የሚካሄድ ነው። ስለሆነም የአሜሪካንና የአውሮፓውን የኦሊጋርኪ መደብና የሚሊተሪ ኢንዱስትሪ ስብስብ(Military- Industrial Complex) ኤሊት እንደ ቅዱስ ኃይል ማየቱ ከፍተኛ የዋህነትና እንደ ወንጀለኛም የሚያስቆጥር ነው። የዚህን አደገኛነትና አጥፊ ተልዕኮዉን ስንረዳ ብቻ ነው አገራችንን ከጥፋት ማዳንና በተሟላ መልክም መገንባት የምንችለው።
ወደ አገራችን ስንመጣ ታሪኩ አንተ እንዳስቀመጥከው በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በሰሜኑ ክፍል የነበረው የፊዩዳሉ ስርዓት የኢኮኖሚ መሰረቱ ሙሉ በሙሉ በእርሻ ላይ የተመሰረተ ነበር። ይህም ማለት የዕደ-ጥበብ ስራዎችና የንግድ እንቅስቃሴ በሚገባ የዳበሩ አልነበረም። እንዳለ የንግድ እንቅስቃሴ አልነበረም ማለት ይቻላል። የሚመረተው ማንኛውም ነገር ገበያ ላይ ውጥቶ ካልተሸጠና ገንዘብም የመገበያያ መሳሪያ ሆኖ መዳበር የማይችል ከሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ማደግና መስፋፋት አይችልም። በዚህ ላይ መንደሮችና ከተማዎች በስነ-ስርዓት አልተገነቡም ነበር። አብዛኛው ህዝብ ተሰበጣጥሮ ካለመገናኛ የሚኖር ነበር። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ አንጥረኛው የተወሰኑ ነገሮችን ሊያመርት ቢችልም ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ ይዞ በመሄድ የመሸጥ ዕድል አልነበረውም። በዚህ ላይ ምሁራዊ እንቅስቃሴ የዳበረ አልነበረም። እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ድረስ ማለት ይቻላል በሰሜኑም ሆነ በደቡቡ ክፍል በፍልስፍናና በተፈጥሮ ሳይንስ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም፤ ዛሬም የለም። አብዛኛው አካባቢ እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ስለነበር ወደ ኋላ ለተነሱት እንደ አፄ ቴዎድሮስና እንድ አፄ ምኒልክ ለመሳሰሉት ለተገለጸላቸው መሪዎች አንድ የጠነከረ ህብረ-ብሄር ለመገንባት ቀላል አልነበረም። አብዛኛው መሳፍንትና የፊዩዳል መደብ ከክልሉ ባሻገር የሚያስብ ስላልነበር ሁሉንም በአንድ አገዛዝ ጥላ ስር ለመጠቅለል በጣም አስቸጋሪ ነበር። ለዚህ ነው አፄ ቴዎድሮስ ሲነሱና ሲነግሱ አብዛኛው መሳፍንት ማመጽና ተንኮል መስራት የጀመረው።
ወደ ደቡቡ ክፍል ስንመጣም እንደዚሁ ወደ ኋላ የቀረ ነበር። ትንሽ አድገው ይታዩ የነበሩ እንደ ሃዲያና ሌሎች አካባቢዎች በ16ኛው ክፍለ-ዘመን በኦሮሞዎች መስፋፋት የተነሳ ስልጣኔያቸውና አገዛዛቸው ስለወደመ ሁኔታው የኋሊት ጉዞ ነበር። ኦሮሞዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛት ሲስፋፉ ይዘው የመጡት ስልጣኔ ስላልነበር ለአካባቢው ዕድገት ያደረጉት አስተዋፅዖ ምንም አልነበረም። እንዲያውም በአንፃሩ የነበረውን ስልጣኔ ማውደም ነው የጀመሩት። አፄ ምኒሊክ ከአደዋ ድል በኋላ ወደ ደቡቡ ክፍል ግዛታቸውን ሲያስፋፉ በየአካባቢው የዳበረ ምንም ነገር አልነበረም። አብዛኛው ህዝብም በአደንና በፍራፍሬ ለቀማ የሚኖር ነበር። የዕደ-ጥበብ ስራ አይታወቅም ነበር። መንደሮችና ከተማዎችም አልተቆረቆሩም ነበር። ባጭሩ ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚሆን ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ አልነበረም። እንደሚታወቀው አንድ ህዝብ ሊተሳሰርና ብሄራዊ ስሜቱ ሊዳብር የሚችለው ሰፋ ባለ የኢኮኖሚ እንቅቃሴ፣ በመንደሮችና በከተማዎች በስርዓት መገንባትና በዚህ አማካይነት ህዝቡ መተሳሰር ሲችል አንድን አገርና ህዝብ እንደ ህብረ-ብሄር መገንባት ይቻላል። ባጭሩ አፄ ምኒልክ ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ግዛት ሲስፋፉ ሀ ብለው መጀመር ነበረባቸው። አስቸጋሪውም ነገር ከእሳቸው በስተቀር የተገለጸለት ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስላልነበር ደብተራዎችን ነበር በማሰማራት የተለያዩ አካባቢዎችን ለማስተዳደር የሞከሩት። እንግዲህ ያለውን ክፍተት ማየቱ ከባድ አይሆንም ማለት ነው። ይህንን ሁሉ የማትተው ነገሩን ከአውሮፓው የምሁር እንቅስቃሴና የአገር ግንባታ ታሪክ በመነሳትና በእነሱም መነጽር ስለምመለከት ነው። ይህ አካሄድ ትክክል ይመስለኛል። ምክንያቱም ተበታትኖ የሚኖር ህዝብ በማንኛውም መስክ የማደግ ዕድል አይኖረውም። ምሁራዊ እንቅስቃሴ ካልዳበረና የፈጠራ ስራ ካልተካሄደ ደግሞ ልዩ ልዩ ምርቶችን በማምረት ለመጠቀም ለሚፈልገው ህዝብ ማቅረብ አይቻልም። ሰፊውንም ህዝብ ከአደጋ ለመከላከል የሚቻለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት የተለያዩ መሳሪዎችን መስራት ሲቻል ብቻ ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በየቦታው የቮኬሽናል ትምህርት ካልተስፋፋ ቴክኖሎጂዎችንና የሰለጠኑ ሰዎችን ማፍለቅና ለሰፊው ህዝብ ግልጋሎት መስጠት አይቻልም። ባጭሩ በአፄ ምኒልክ ዘመን የነበረው ሁኔታ ይህ ሲሆን፣ የኦሮሞና የትግሬ ኤሊቶች የሚያውሩት ትረካ ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የለውም። በተለይም የእሮሞ ኤሊቶች ከአውሬነት ባህሪያችን ተላቀቅን ብለው የሚበሳጩ ከሆኑ ወደዚያው እንዲመለሱ ማድረግ ይቻላል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያን እየለቀቁ መውጣት አለባቸው እንጂ እዚያ ተቀምጠው ህዝብን ማረድ የለባችውም። በእኔ ዕምነት አፄ ምኒልክ ጥበባዊና የተገለጸላቸው ብቸኛው ንጉሰ ነገስት ናቸው ማለት ይቻላል። ለረጅም ዓመታት ቢቆዩ ኖሮ ምናልባት ኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል ያጋጥማት ነበር የሚል ግምት ነበረኝ።
ወደ አፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ስንመጣ አንዳንድ ስራዎች ቢሰሩም እነዚህ ስራዎች በተለይም የታዳጊውን ትውልድ መንፈስ በጥሩ ሁኔታ የሚያንጹ አልነበሩም። በዘመናዊነት ስም ተግባራዊ የሆኑት ነገሮች በሙሉ ብልህና አዋቂ ከማድረግ ይልቅ ጮሌዎች ነው ያደረጉን። አራዳነት የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ነው የሚታወቀው። ይህ ዐይነቱ የመንፈስ መቀረጽ በጊዜው ከተስፋፋው የትምህርት ዐይነት ጋር የሚያያዝ ነው። ይህንን ዐይነቱን የትምህርት አሰጣጥ እነ ጀርመን በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጋር ካስፋፍትትና ካዳበሩት በግሪክ ፍልስፍና ላይ ከተመሰረተው ክላሲካል የትምህርት ዐይነት ጋር ማወዳደር ይቻላል። የእኛው ትምህርት ጭንቅላትን የሚያሾል አይደለም። ለፈጠራና ለምርምር የሚያመች አይደለም። ይባስ ብሎ ለአመጽና ለግብዝነት የሚዳርግ ነው። ሰለሆነም ነው የተኮላሸ የዘመናዊነት አካሄድ ኋላ ቀር አስተሳስበ ጋር ሲጋጭ አርቆ አሳቢ ከመሆን ይልቅ አመጸኛ ሊያደርገን የበቃው። በዚህም ምክንያት ነው የኋላ ኋላ ላይ አብዮቱ ሲፈነዳ የአብዛኛው ፖለቲከኛ ባይ ነኝ የፊቱ ገጽታ ሲገለጥ ወደ ፋሺሽታዊ ድርጊት መለወጥ የጀመረው። ስለዚህ ነው በተለይም የንዑስ ከበርቴው መደብ ወደ ፋሺዥምነት የተቀየረው። የሲግሙንድ ፍሮይድን ስራ ስናነብ ይህንን ነው የሚያስረዳን። አሁንም ያለው ችግር ይህ ነው።
ወደ ብሄረሰብ ጥያቄ ስንመጣ የተነሳበት ዋና ምክንያት ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎችና ሌሎች ብሄረሰቦች ከአማራው ጋር ሲወዳደሩ በመበደላቸው ምክንያት ሳይሆን የእሮሞና የትግሬ ኤሊቶች ከተማሪው እንቅስቃሴ የተወረወረላቸውን መፈክር ቀለብ በማድረጋቸው ነው የተሳሳተ ትረካ ማስፋፋት የጀመሩት። በዚህ ላይ ደግሞ በዘመናዊነት ስም የተስፋፉት ትምህርትቤቶች፣ ለምሳሌ እንደ ጄኔራል ዊንጌት የመሳሰሉት እንደ መለሰ ዜናዊ የመሳሰሉትን ተንኮለኛና አመጸኛ ሰዎች ለማፍራት የሚያመቹ ነበሩ። ወደ ወለጋም ስንሄድ የጀርመኑ ሃዘን ብላት የሚባለው መርዘኛ ቄስ መርዙን መርጨት የጀመረው የተከፈተለትን በር በመጠቀም ነው። ሰለሆነም ኦነግ የሚባለው መርዘኛ ድርጅት በመፈጠር መበጥበት የጀመረው በተበላሸ አስተሳሰብ ወይም በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላቱ በመቀረጹ ነው። ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ያልተስተካከለ የኢኮኖሚ ግንባታ ባለበት አገር ውስጥ ለእንደዚህ ዐይነት ድርጅቶች መስፋፋት በጣም የሚያመች ነው። ጥሩ ጥሩ ነገሮች ካልተሰሩና በተለይም ወጣቱ መንፈሱ በእነዚህ ነገሮች ካልተያዘ ወደ መጥፎ ነገር እንደሚያደላ የታወቀ ጉዳይ ነው። የስለላ ድርጅቶችም እየገቡ ያለውን የተዝረከረከ ሁኔታ በመጠቀም ያልበሰሉና ማሰብ የማይችሉ ግለሰቦችን በመመልመል ሁኔታውን ያባብሱታል። ባጭሩ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በተሰራ የፖለቲካና የዕድገት ፖሊሲ ስህተት ምክንያት ነው የነፃነት አውጭ ድርጅቶች እንደ አሸን ሊፈልቁ የቻሉት። የተማሪውም እንቅስቃሴም የፔሪፈሪ ካፒታሊዝም ትምህርት ውጤት እንጂ የእነ ሶክራተስ፣ ፕሌቶ፣ የእነ ላይብኒዝ፣ ካንትና የእነሄግል ውጤት ባለመሆኑ ትንሽ ትንሽ ቀለብ ያደረገውን ማርክሲዝምን በማራገብ ነው ግራ የሚያጋባ ህኔታ ሊፈጠር የቻለው። በአጠቃላይ ሲታይ ዛሬ የተፈጠውን ሁኔታ ከአጠቃላዩ የህብረተሰብአችን አወቃቀርና ከካፒታሊዝም በተኮላሽ መግባት ጋር በማነፃፀር ደረጃ በደረጃ ቢጠና ኖሮ ነገሩን የበለጠ ግልጽ ማድረግ ይቻላል። ችግሩ ግን አብዛኛዎቻችን በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት የሰለጥን በመሆናችን ነገሩን ጠለቅ ብለን የማየትና ሰፋ ያለና ስርዓት ያለው ትንተና መስጠት አንችልም።
ከዚህ በተረፈ ሁሉንም ነገር በነፃ አውጭ ድርጅቶች ብቻ ማሳበቡ ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀርም በተገለጸለት መሰረት ላይ የተነገባ አይደለም። በአገራችን ምድር ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ የተነሳ ስለመንግስት አፀናነስ፤ አገነባብና ዋና ተግባሩም ምን እንደሆነ ማጥናት አልተቻለም። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ዘመናዊ ቢሮክራሲ ሲቋቋም በአቦ ሰጡኝ እንጂ በቲዎሪ ደረጃ በሳይንስ በማጥናትና የሰውንም ጭንቅላት በማሾልና ምሁራዊ ባህርይ እንዲኖረው በማድረግ አልነበረም። ስለሆነም የመንግስቱ መኪና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትና የአገር ግንባታ የሚያመች አልነበረም፤ አይደለምም። በአብዛኛው ጎኑ የጨቋኝነት ባህርይ የነበረው ነበር ማለት ይቻላል። በፖለቲካ ረገድ የሚያስብና የሚተነትን የመንግስት መኪናና ቢሮክራሲ አልነበረም የተዋቀረው። ስለሆነም አብዛኛው ነገር በተጠና መንገድ ሳይሆን በግምትና ግብታዊ በሆነ መልክ የሚካሄድ ነበር ማለት ይቻላል። ይህንን ለማወቅ ከተፈለገ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን እንደ አሸን የፈለቁትን መንደሮችና ከተማዎች በሚገባ ዞር ብሎ ማየት ያስፈልጋል። በአጭሩ ለሰው ልጅ መኖሪያ ሆነው ጥበባዊ በሆነ መልክ የተሰሩ አልነበሩም። ስርዓት አለነበራቸውም። መንፈስን ለመሰብሰብና ተፈጥሮን ለመቃኘት የሚያስችሉ አልነበሩም። ይህ ዐይነቱ የመንደሮችና የከተማዎች አገነባብ አመጽኝነትን የሚጋብዝ ነው። ተራ የሶስዮሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው የከተማ አገነባብ በሰው ልጅ አዕምሮና የአኗኗር ስልት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ ሊረዳ ይችላል።
ለማንኛውም የኢትዮጵያን የድሮውንም ሆነ የዛሬውን እንደ አገር የመገንባትና ወደፊትም የመቀጠል ዕድል መረዳት የሚቻለው ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖና ውጤቱን ስሌት ውስጥ ስናስገባ ብቻ ነው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ በዕውቅ በሳይንስ የተገነባ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ የተኮላሸ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የውጭ ተፅዕኖ አለበት። በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአስቀያሚነት ማህተሙን አሳርፎብናል። ነገሮችን እንዳንረዳ ዐይናችንና ጭንቅላታችንን ሸፍኖብናል። ሰው ከመሆንና እንደ ሰው ከማሰብ ይልቅ አውሬ እንድንሆን አድርጎናል። ማህበራዊ ከመሆን ይልቅ ኢ-ማህበራዊ እንድንሆን አድርጎናል። አርቆ አሳቢና ለወገን ተቆርቋሪ ከመሆን ይልቅ አመጸኛና ትዕቢተኛ አድርጎናል። በአጭሩ አገር ገንቢና ታሪክ ሰሪ ከመሆን ይልቅ አገር አፍራሽ አድርጎናል።
ኤፍሬም ማዴቦ በተደጋጋሚ የምታወጣውን ጽሁፍህን ሳነብ የምገነዘበው ነገር ኢትዮጵያን እንደ ደሴት አድርገህ ነው የምትመለከተው። የውጭ ኃይሎች ተፅፅኖ እንደሌለባት ነው። ግሎባል ካፒታሊዝም ያሳደረብንን ተፅዕኖና ውጤቱን ለማየት የምትችል አይመስለኝም። በየኤፖኩ የተደረጉ ነገሮችን በመመርመር ሀተታ ለመስጠት መሞከር ሳይሆን የቃላት ድርደራ ነው የማየው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ በሳይንስን ዲስክሪፕቲቭ ይባላል። የነገሮችን ውስብስብነትና ዲያሌክቲካዊ አስተዳደግ እንድንረዳ የሚያድረግን አይደለም። ለዚህም ነው በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን የጎሳ ፌዴራሊዚምንና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በግልጽ ለመገንዘብ የማትችለው። በእኔ ዕምነት ወያኔ የአሜሪካንና የእንግሊዞች ፕሮጀክት የነበረ ነበር። አቢይ አህመድም ያንኑ በመቀጠል ነው አገራችንን ለመበታተን የሚሯሯጠው። በራሱ ዕውቀትና እሳቤ ሎጂካዊ በሆነ መንገድ በመረዳት አይደለም ፖለቲካ የሚባለውን ነገር የሚያካሄደው። ወያኔና በአቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ኤሊት በሙሉ ለውጭ ኃይሎች የሚያመች ስራ ነው የሚሰሩት። አገር ቤት ገብተህ አምስት ዓመት ያህል ስትቀመጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተስፋፋውን የብልግና ኢንዱስትሪ ብትመለከት ኖሮ ይህ ዐይነቱ የብልግና ኢንዱስትሪ መስፋፋት በቀጥታ ከኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው። በዚህ መልክ ነው መንፈሱ የተሰለበ የንዑስ ከበርቴውን መደብ በማፍራትና በማደለብ አገር የሚወድመው። ይህም በአሜሪካን ካፒታሊዝም የሚመራው የግሎባል ካፒታሊዝም አንደኛና ዋናው ስትራቴጂ ነው። ሳሚር አሚን የሚባለው ግብፃዊው የኢኮኖሚ ጠበብት እንደሚለን ዓለምን የኒዎ-ሊበራል ገበያ ወይም ማርኬት የመለወጡ ጉዳይ በአገራችን ምድር የተፈጠረው ካለምክንያት አይደለም። ናኦሚ ክላይን የምትባለው የካናዳ ኢኮኖሚስቷ ዘሾክ ዶክትሪን(The Shock Doctrine) በሚለው ግሩም መጽሃፏ ይህንን የአሜሪካን ኢምፐሪያሊዝምን ቆሻሻ ስራ ነው የምታትተው።
ይህ ዐይነቱ ቆሻሻ አስተሳሰብ ነው በተለይም የትግሬና የኦሮሞ ኤሊቶችን ጭንቅላት በመያዝ አገርን የሚያተራምሱት። የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በመጠቀም ነው በዘረፋና በውንብድና ስራ የተሰማሩት። ወያኔዎች ስልጣን ላይ ከወጡና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ጀምሮ ሆን ብለው የያዙት ስራ የአገርን ሀብት መዝረፍና ማዘረፍ ነው። ካድሬዎችም ይሉን የነበረው ኢትዮጵያን የምንፈልጋት ለዘረፋና ትርፍ ለማትረፍ ብቻ ነው በማለት ነበር የሚያፌዙብን። በመቀጠልም ኢትዮጵያን በማፍራረስ ብቻ ነው ታላቋን ትግራይ መገንባት የምንችለው ነው እያሉ ያወሩ የነበረው። በአቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ኤሊትም ይህንን መስመር በመከተል ነው አገርን የሚበዘብዘውና የሚያፈራርሰው። ስለሆነም ኢትዮጵያን ስናፈርስ ብቻ ነው ታላቋን ኦሮሚያ መገንባት የምንችለው እያሉ የሚነግሩን። ይህ ዐይነቱ አሰራርና አነጋገር በቀጥታ ከጭንቅላት መቀጨጭ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው የሚያረጋግጥልን። ጭንቅላታቸው ዲያሌክቲዊ በሆነ መልክ ያልተገነባ መሆኑን ነው የሚያረጋገጠው። ሎጂካሊ ማሰብ የማይችልና ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት የማይገባው ሰው ብቻ ነው እንደዚህ ብሎ ማሰብ የሚችለው። በጣም የሚያሳዝን ነገር በአገራችን ምድር ተከስቷል ማለት ይቻላል። ታዲያ በተበላሸ ወይም በተሳሳተ መልክ የሚያስቡትን የትግራይና የኦርሞ ኤሊቶች ምን ማድረግ ይቻላል? ለእነዚህ ዐይነት ሰዎችስ መፍትሄው ምንድን ነው? በትግራይና በኦሮሞ ኤሊቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም በሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ከፍተኛ የጭንቅላት መቀጨጭ ይታያል። አብዛኛው ሰው ከዕውነተኛ ዕውቀት ጋር የተራራቀና መጽሀፍም ለማንበብ የሚፈልግ አይደለም። ወርቃማ ጊዜውን በአልባሌ ቦታ ሲያሳልፍ ነው የሚታየው። ታዲያ በእንደዚህ ዐይነት የጭንቅላት በሽታ በተስፋፋባት አገር ውስጥ ኢትዮጵያን እንዴት ማዳን ይቻላል? በእዚህ ላይ በከፍተኛ ደረጃ በኢትዮጵያና በአማራ ስም የሚያወናብዱ ቡድኖችና ግለሰቦች ተስፋፍተዋል። አሜሪካ አድነን፣ ከእኛ ጋር ተሰለፍ እያሉ ይማፀናሉ። ፓለቲካህን አስተካክል እያሉ ከተጨባጩና ከሳይንስ ውጭ የሆነ ነገር ሲናገሩ ይሰማሉ። በመሃከላችን ከፍተኛ መወናበድ ይታያል። ካለውጭ ዕርዳታና ኃይል የራሳችንን ዕድል በራሳችን መወሰን የማንችል ነው የሚመስለን። በአጠቃላይ ሲታይ ለአብዛኛዎቻችን ጊዜው ያለፈብን ይመስለኛል። ሃያና ሰላሳ ዐመታት ብዙ ወርቃማ ጊዜያችንን ከራሳችን ጋር ስንታገል አሳልፈናል። ወጣቱ ትውልድ ደግሞ የፌስ ቡክና የኋትሳፕ ዘመን ትውልድ ስለሆነ የፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ፣ እንዲሁም የጥሩ ጥሩ ሊትረቸሮች መጽሀፎችን የማንበብ ልምድና ፍላጎት የለውም። እንደሚታወቀው አንድ አገር የሚገነባው በጥሩና በትክክለኛው ዕውቀት ብቻ ነው። በዚህ ላይ ሊሰራ የሚችል ታታሪ ትውልድ ካልተፈጠረ ኢትዮጵያን የማዳኑ ዕድል የመነመነ ነው ማለት ነው።
በሌላ ወገን ግን በእርግጥስ ኢትዮጵያን ለማዳን ከተፈለገ እስካሁን ድረስ ከተከተልነውና ከምናራምደው ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ፍልስፍና የሆነ ፖለቲካ መላቀቅ አለብን። ማንኛውም የህብረተሰብ ጥያቄዎች ወደ ውጭ ወጥተው ለውይይትና ለክርክር መቅረብ አለባቸው። የህብረተሰብ ጥያቄዎችም ወይንም ደግሞ የአንድን አገር ዕድል የሚወስኑ ነገሮች በጥናት በተደገፈ መልክ መቅረብ አለባቸው። የሚነሱትም ጥያቄዎች ህብረተሰብአችንን የሚመለከቱና ለህብረ-ብሄር ምስረታና ለጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያግለግሉ መሆን አለባቸው። እነዚህም ጥያቄዎች መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? በምንስ መልክ መዋቀር አለበት? ተግባሩስ ምንድን ነው? የመንግስትንስ መኪና የሚቆጣጠሩ ሰዎች ምን ዐይነት ዕውቀትና ባህርይ ሊኖራቸው ይገባል? እያልን በማንሳት በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ በሚገባ ማብላላት አለብን። እንደሚታወቀው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተዋቀረው የመንግስት መኪናና ቢሮክራሲው በሳይንስና በፍልስፍና በተጠና መልክ ሳይሆን በአቦሰጡኝ በመሆኑ በተለይም አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣናቸው ከወረዱ በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነትና ማስፈሪያነት ተለውጧል። በደርግ ዘመን የሆነውን ሁኔታ አብዛኛዎቻችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ደግሞ የአንድ ጎሳ መጨፈሪያ በመሆን ዲሞክራሲን አፋኝና የአገርን ሀብት መዝረፊያ መሳሪያ ለመሆን በቅቷል። በዚያው መጠንም ብሄራዊ ነፃነታችን ለማስደፈር ተበቅቷል። አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ደግም ወደ ግል-ሀብትነት ተለውጧል። የህግ-የበላይነትም የሚባለው ነገር ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኗል። በአጭሩ የመንገስቱ መኪናና አገዛዙ እንዳለ ወደ ዘመናዊ ፈሺሽትነት ለመለወጥ ችለዋል። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የአገዛዝ መዋቅርና የሚቆጣጠሩት ሰዎች እንዳለ መገርሰስ አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ህዝባዊ ተሳትፎ ያለበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የሚቻለው።
ከዚህ በተረፈ አገራችንን በምን መልክ ነው ቀስ በቀስ ከታች መገንባት ያለብንና የምንችለውስ? ምን ዐይነትስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብንከተል ነው ህዝባችንን ከድህነት ለማውጣት የምንችለውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መገንባት የምንችለው? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች መነሳትና በበቂው መብላላት አለባቸው? የአንድ አገር ዕድል የሚወሰነው በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ስለሆነ በዚህ ላይ የጠራ አቋም እስከሌለን ድረስ ኢትዮጵያን እንደ አገርና እንደህብረብሔር በፍጹም መገንባት አንችልም? ሌሎች የሚነሱ ጥያቄዎች የብሄራዊ ነፃነት ጉዳይና በተለይም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር የሚኖረን ግኑኘነት ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ እስከምከታተለው ድረስ ግራ ነኝ በሚለውም ሆነ የቀኝ ፖለቲካን በሚያስተጋባው ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ነኝ ባይ ዘንድ አሜሪካንን በሚመለከት ከፍተኛ መቅለስለስ ይታያል። የአሜሪካንን ጉዳይ አታንሳብኝ የሚሉም ብዙ ፖለቲክኛ ነን ባዮች አሉ። ጥያቄው አሜሪካንን ከመጥላትና ከመውደድ አንፃር መታየት ያለበት ጉዳይ ሳይሆን እንዴት አድርገን ነው ጠንካራና ብሄራዊ-ነፃነቷ የተከበረች ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው? ከሚለው አስተሳሰብ መነሳት ያለብን ይመስለኛል። በእኔ ሳይንሳዊ ግንዛቤና ፍልስፍናዊ ዕምነት መሰረት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጠቅላላው ሰው ልጅ ፀር ነው። በየአገሮች ውስጥ የተሟላና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ዕንቅፋት የሚፈጥር ነው። የፖለቲካና የሚሊተሪ-ኢንዱስትሪ ስብስብ ኤሊቱ በመሰይጣናዊ መንፈስ በመመራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን የሚያካሂድ ነው። በሰዎች መሞት የሚደሰት ነው። መንፈሰ-አልባ የሆነና የራሱንም አገር ገደል ውስጥ እየከታት ነው። ስለሆነም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአጠቃላይና፣ በተለይም ደግሞ በግሎባል ካፒታሊዝም ላይ የጠራ አቋም እንዲኖረን ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻና በጠንካራ መንፈስ ተነሳስተን በቅንነትና በአገር ወዳድነት ስሜት ከሰራን ኢትዮጵያን ማዳን እንችላለን የሚል ዕምነት አለኝ።
ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታዬ ስነሳ ኤፍሬም ማዴቦ የምትሰጠው ትንታኔ መሰል ነገር ኢትዮጵያን መልሶ የሚያድናት አይደለም። ምክንያቱም የዕውቀት መሰረትህ ኤምፔሪሲዝም ስለሆነ ነገሮችን በጥልቀትና በተወሳሰበ መልክ ለማየት አያስችለንም። በተለይም በኢኮኖሚ ሙያ ሰልጥነህ ልክ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚለውን አገርን የሚያከረባብተውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩትን ነገር የምታውቅ ወይም የምትረዳ አይመስለኝም። በተለይም በዚህ ላይና በአጠቃላይ ሲታይ በግሎባል ካፒታሊዝም ላይ በቂ ግንዛቤ የሌለው ሰው አገርን የማዳን ተልዕኮ በፍጹም ሊኖረው አይችልም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም መሰሪህ ስራ ሲታወቅና በይፋ ለውይይት ሲቀርብና ሲተነተን ብቻ ነው ኢትዮጵያን ለማዳን ፍቱን ስራ መስራት የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ!!