December 22, 2023
12 mins read

እናትዋ ጎንደር እና አደይ ትግራይ፡- ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት!! – በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

‹‹እግዚኦ ቦኡ አሕዛብ ውስተ ርስትከ ወአርኮሱ ጽርሐ መቅደስከ ወርሰይዎ ለጎንደር ከመልገተ ዓቃቤ ቀምሕ››

(ደርቡሾች ጎንደርን ወረው ሕዝቡን በጨፈጨፉና አብያተክርስቲያናትን ባቃጠሉ ጊዜ የጎንደር ሊቃውንት ለትግራዩ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ከላኩት ደብዳቤ የተወሰደ)

ከሰሞኑን የፋኖ ታጣቂዎች በእስር ላይ የነበሩ የትግራይ ክልል ታጋዮችን ከእስር ቤት አስለቅቀው በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ መደረጋቸውን የሚዘግቡ ዜናዎችን ሰምተናል፡፡ ይህ ዜና የሁለቱን ሕዝቦች ጥብቅ የሆነ የታሪክ ትስስር፣ የሃይማኖትና የባህል መዋረስና እንዲሁም የአማራና የትግራይ ሕዝብ፤ ከጉራዕ እስከ ጉንደት፣ ከመቅደላ እስከ መተማ፣ ከአምባላጌ እስከ ዐድዋና ማይጨው… ወዘተ. ድረስ በደማቸውና በአጥንታቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የከፈሉትን መሥዋዕትነት የሚያውቁ ኢትዮጵያውያንን አስደስቷል፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን፤ የዛሬን አያድርገውና የቀደሙ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት የፍቅርና የአንድነት ድርና ማግ ላይለያዩ በጥብቅ የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብም በታሪኩ- በደጉም በክፉም ጊዜ ይህን የታሪክ ክብርና ኩራት የተካፈለ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ በውስጥ ጉዳያቸው አለመስማማትና ልዩነት ቢኖራቸውም እንኳ በኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ መቼም ቢሆን ቃላቸው አንድ ነበር፡፡

ኢትዮጵያን እኛ በሕይወት ቆመን እያልን እንዴት ባዕዳን በግፍ ይወሯታል፤ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ ነጻነት ወይም ሞት!! በሚል ጽኑ የቃል ኪዳን ውል በደማቸውና በአጥንታቸው የቆመች፣ ነጻይቷን ኢትዮጵያን አውርሰውናል፡፡ ይህን እውነታ የተገነዘቡት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ከጥቂት ሳምንት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፤ ‹‹የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል የመነሻ ሐሳብ›› በሚል አርእስት ባስነበቡት ጽሑፋቸው፤

የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ትስስር ከጥንት ጀምሮ እየጠበቀና ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተወሳሰበ በመሄድ አገር በጋራ ከመመሥረትና ከመገንባት አልፎ ከቅርበታቸው የተነሳ ባህላዊ፣ … ምንም እንኳ አገር በመመሥረትም ሆነ መንግሥትን በማቋቋም ረገድ በሁለቱም ሕዝቦች የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የተቀናቃኝነትና የተፎካካሪነት ሁኔታ የነበረና አሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡

የአገርን ዳር ድንበር ከወራሪ ኃይሎች በመከላከል ረገድም ይሁን የሕዝቦችን ነፃነት አስከብሮ ለማቆየት በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ፣ የሁለቱም ሕዝቦችና ልሂቃን አሻራ ከፍተኛ መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚያም አልፎ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመልካም ጉርብትና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ማኅበራዊ ግንኙነት ፈጥረው አብረው የኖሩና አብረው የሠሩ ሕዝቦች መሆናቸው ሲታሰብም፣ በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል የሻከረ ግንኙነት ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ለምን ቢባል ሁለቱም ሕዝቦች በጋብቻ ተሳስረው ተዋልደው በቀላሉ ላይለያዩ ተዛምደዋል፡፡ ሲሉ ያወሳሉ፡፡

በርግጥም እነዚህ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በጀግንነት የተዋደቁ ሕዝቦች በመካከላቸው ጠላትነትና መለያየት እንዲኖር የሚማስኑ መስሪዎችንና ከፋፋዮችን ማስቆም የሚቻለው የትናንትናውን የአብሮነት ታላቅ ታሪካቸውን በመዘከር፣ በመንገርና በማስተማር ነው፡፡ እስቲ ወጌን ፈር ለማስያዝ ያህልና ሐሳቤንም ያጠናክርልኝ ዘንድ ከሰፊው ታሪካችን አንድ ሰበዝ ልምዘዝ፤

ጣሊያኖች በኢትዮጵያውያን ላይ ያላቸውን የበላይነት በመተማመን እንደሚሳካላቸው አምነው ነበር ‘ክተት ሰራዊት፤ ምታ ነጋሪት!’ ብለው ከሮማ ገሥግሠው ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጡት፡፡ ጣሊያኖች ይህን ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግም ሲሉ በጥር 1885 ዓ.ም. መረብን ተሻገሩ፡፡ ራስ መንገሻን በቆአጢት ለመክበብ ቢፈልጉም ራሱ ሳይያዙ ወደ ደቡብ ሸሹ፡፡ ራስ መንገሻ ከደብረ ኃይላት እንደሸሹ ዜና የሚሆን ፉከራ ፎከሩ፡፡ እንዲህ ሲሉ… ቃሉም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ እንደ እሳት ተዛመተ፤

‘‘እሪ በሉ ለጎንደር ንገሩ፣

እሪ በሉ ለሸዋ ንገሩ፣

እሪ በሉ ለወሎ ንገሩ፣

እሪ በሉ ለጎጃም ንገሩ፣

መንገሻ ለቀቀ ተከፈተ በሩ፡፡’’

ሰሜን ኢትዮጵያ ሀገራችንን በተለያየ ጊዜ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ላሰቡና ለሞከሩ የውጪ ሀገራት ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች ሁሉ መግቢያ በር ነበር፤ ነውም፡፡ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረርና የመቆጣጠር ሕልማቸው የተቀበረው ከሀገራችን የተለያዩ ግዛቶች በመጡ እምቢ ለነጻነቴ! እምቢ ለሀገሬ! ባሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባትና እናት አርበኞች ነበር፡፡ ጉንደት፣ ጉራዕ፣ ዶጋሊ፣ መተማ፣ አምባላጌ፣ መቀሌ፣ ማይጨው፣ ዐድዋ… የኢትዮጵያውያን የእምቢ ለነጻነቴ ተጋድሎ ፣ የነጻነት ችቦ ለዓለም ሁሉ ከፍ ብሎ የበራባቸው በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ደምና አጥንት የተዋቡ የነጻነታችን ዓርማና ኩራት ናቸው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ የአማራንና የትግራይ ሕዝቦችን ለዘመናት የዘለቀና በኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ የተጋመደ  አንድነታቸውን የሚመሰክር ሌላ የታሪክ እውነታ ልጥቀስ፤

ደርቡሾች ጎንደርን ወረው ሕዝቡን በፈጁት፣ ከተማውን በዘረፉትና በአብያተክርስቲያናትን በቃጠሉ ጊዜ የጎንደር ሊቃውንት በመግቢያ ላይ የጠቀስኩትን የሚከተለውን ድብዳቤ ጽፈው ለዐፄ ዮሐንስ ልከውላቸው ነበር፤

‹‹እግዚኦ ቦኡ አሕዛብ ውስተ ርስትከ ወአርኮሱ ጽርሐ መቅደስከ ወርሰይዎ ለጎንደር ከመልገተ ዓቃቤ ቀምሕ›› (‹‹አቤቱ ንጉሥ ሆይ፡- አረማውያን በምድርህን ወረሩ፣ ቤተ መቅደስህንም አረከሱ፣ ጎንደርንም አፈራረሷት፡፡››)

ይህ የጎንደር ሕዝብና ሊቃውንት የድረሱልን ጦማር/ደብዳቤ የደረሳቸው ዐፄ ዮሐንስ ዛሬ ነገ ሳይሉ ነበር ወደ ጎንደር የዘመቱት፡፡ ንጉሡ ከደርቡሾች ጋር በነበረው ውጊያም እንደ ተራ ወታደር በመካከል ገብተው ሲዋጉና ሲያዋጉ በመተማ ግንባር ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን የሠዉት፡፡ ዐፄ ዮሐንስ የጎንደር ሊቃውንት የይድረሱልን ጥሪ ሲደርሳቸው ይህ የጎንደር/የአማራ ሕዝብ ጉዳይ እንጂ የትግራይ ወይም የእኔ ጉዳይ ነው አላሉም እናም ከትግራይ ድረስ ገሥግሠው መጥተው ነው መተማ ላይ አንገታቸው የሰጡት፡፡

ዐፄ ዮሐንስ የግብጽንና ጣሊያንን ወረራ ኃይል ለመመከት ባወጡት ዐዋጅ ልሰናበት፤

ሀገሬ ሆይ ስማ…! መኳንንቶች፣ ወታደሮች፣ ሕዝቦቼ ስሙ፡፡ በመጋቢት 25 ቀን በምፅዋ መንገድ አቅንተህ ለጦርነት እንድትገሰግስ የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ ያዝሃል፡፡ ወደፊት ገስግስ እንጂ ወደኋላ አትቅር፡፡ የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ ልብ አድረገህ ተመልከት ኢትዮጵያ የተባለች፡-

አንደኛ እናትህ፣

ሁለተኛ ዘውድህ ናት፣

ሦስተኛ ሚስትህ ናት፣

አራተኛ ልጅህ ናት፣

አምስተኛ መቃብርህ ናት!!

እንግዲህ የእናትን ፍቅር፣ የዘውድን ክብር፣ የሚስትን ደግነት፣ የልጅን ደስታ፣ የመቃብርን ከባቲነት እንደዚህ መሆኑን አውቀህ ነገ ከነገ ወዲያ ሳትል ተነሳ፡፡

 

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop