T.G (ጠገናው ጎሹ)
“ምነው እሸቱን ለቀቅ አድርገው እንጅ” ከማለት ጀምሮ የውግዘትና የመርገም ናዳ ሊያወርዱ የሚችሉ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንደማይሆን በሚገባ እረዳለሁ። ለዚህ ያለኝ ምላሽ ይህ አስተያየቴ ህዝብ ከሚገኝበት ፖለቲካ ወለድ አስከፊ፣ አስጨናቂና አሳፋሪ ሁኔታ አንፃር ሲታይ አንዳንድ የእሸቱ አስተሳሰቦችና አካሄዶች ሚዛናዊነትን ወይም የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን የሳቱ በመሆናቸው ላይ እንጅ ከእሸቱ የግል ሰብእና፣ ህይወት፣ አስተሳሰብና አመለከካት ፣ አኗኗር፣ እምነት፣ ወዘተ ላይ ፈፅሞ አይደለምና አይጭነቃችሁ የሚል ነው።
“አይ በምንም ሁኔታ እሸቱንና መሰሎቹን መተቸት ጭፍን ጥላቻና ጨለምተኝነት ነው” ከሚል የድንቁርና ወይም የየዋህነት ተሟጋችነት ጋር ግን ፈፅሞ አልስማማም። አገርን ወይም ህዝብን አስመልክተን በምንሰጠው ሃሳብና በምናደርገው ድርጊት ውስጥ የተሳሳተ ወይም የተንሻፈፈ ወይም በመሬት ላይ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነታ እንደሌለ ቆጥሮ በስሜት እየጋለበና እያስጋለበ መሠረታዊና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን ከሚጠይቀው የጋራ ጉዳያችን ሊያንሸራትተን የሚችለውን መንገድ በሂሳዊ አስተያየት መሞገትንና መሟገትን መልመድ አለብን የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ።
ትውልድ ገዳይ በሆነ ሥርዓት ተሰቅዞ የተያዘውን ትውልድ ምንም ጥረት እንደማያደርግ (“ድዱን በማስጣት የሚደሰት እንደሆነ “) ፣ የፈጣሪውን ሃያልነትና ርዳታ የማይጠይቅ እና የማያውቅ እንደሆነ፣ ምንም አይነት የፈጠራ ፍላጎትና ችሎታ እንደሌለው ፣ ወዘተ አድርጎ ለማሳየት የሞከረበትን ሌክቸር በጥሞና ለሚገመግም ወገን ይህ ትውልድ በምንምና እንደምንም (by any means) ራሳቸውን ስኬታማነት ላይ ያገኙና የሚያገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች አንደበት መፍቻና መሠልጠኛ እየሆነ እንደሆነ ለመረዳት አይከብደውም።
ስኬትን እጅግ ፈታኝ ከሆነው ነባራዊው እውነታ ውጭ የሚገኝ ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ሌክቸር እንስጣችሁ የሚሉ ወገኖችን ለምንና እንዴት ሳይሉ የአድናቆት ግትልትል ማግተልተል በእጅጉ የሚሳሰብ ጉዳይ ነው ። ለዘመናት በመጣንበትና አሁንም በባሰ አስከፊነት በምንገኝበት የፖለቲካ ሥርዓት ሥር ሆነንም “ስኬት በስኬት ለመሆን የሚግደን ነገር የለም” ብሎ መቀበል ልክ የሌለው ድንቁርና ወይም እያወቁ አሳሳችነት ነው። ለፈጠራ እና ለስኬት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ይልቅ ተቃራኒውን የሚያደርግ ሥርዓተ ፖለቲካ ሥር በሰደደበትና በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ “ከፈለጋችሁና ከጣራችሁ እንደ እኔ ስኬት በስኬት ትሆናላችሁ” የሚልን ስብከት ለመረዳትና ለመቀበል በእጅጉ ያስቸግራል።
እጅግ አስከፊ በሆነ የፖለቲካ እውነታ (tragic political reality) ውስጥ የራስን ስኬት በምሳሌነት ወስዶ ጥረት ላደረገና ለሚያደርግ ሁሉ በጣም የሚቻል እንደሆነ ሌክቸር ማድረግ አጠቃላይ እውነትን በተወሰነ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ከሚገኘው መሪር እውነታ ጋር እየቀላቀሉ “እውነታው ይህና ይህ ብቻ ነውና በፈጣሪና በእኔ ይሁንባችሁ እመኑኝ” ማለት ወይ የአስተሳሰብ ቁንፅልነት ወይም ግብዝነት ወይንም ደግሞ ግልብ ስሜትን በመኮርኮር የሶሻል ሚዲያ ንግድን የማሳለጥ ዘዴ ነው የሚሆነው ።
ከነፈተናውም ቢሆን ጥረት ማድረግን ማበረታታት አንድ ነገር ነው። ጥረትንና ስኬታማነትን የሚገድል ሥርዓተ ፖለቲካ የመኖሩን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ይህንኑ እንዴት መቋቋም ወይም መጋፈጥ እንደሚቻል ምንም አይነት ቃል ሳይተነፍሱ የራስን ስኬት ለሁሉም የሚሠራ ተምሳሌት እያደረጉ ሌክቸር ማድረግ ወይ ድንቁርና ወይም የሁሉን አውቃለሁ ግብዝነት ወይንም ልክ የሌለው የግል ዝና እና ስኬት ፍለጊነት ነው።
የጥረትና የፈጠራ በሩን ያለ መራር ትግል እንዳይከፈት አድርጎ የዘጋውን የእኩይ ፖለቲካ ሥርዓትን የማስወገዱ ጥረት ስኬታማ እስካልሆነ ድረስ ስኬት የአገርና የብዙሃኑ መሆኑ ይቀርና የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ይሆንና እነርሱንም የአድርባይነት ወይም የርካሽ ህዝበኝነት ሰለባ በማድረግ የባርነት ዘመንን ያራዝማል። ለዚህ ነው እንደ እሸቱ አይነቱን የስኬታማነት ሌክቸር ካላስፈላጊ ይሉኝታ ወይም እጅግ ከተጋነነ ሙገሳ ወጥቶ ሂሳዊ በሆነ ምልከታ ማየትና ማሳየት ተገቢና አስፈላጊ የሚሆነው።
ይህ ትውልድ መወቀስም ካለበት የራሱን የነፃነትና የፍትህ ታሪክ በመሥራት ችሎታውንና እውቀቱን ተጠቅሞ ለራሱም ሆነ ለአገሩ ስኬትን ለማላበስ የሚያስችል አመች ሁኔታ (favorable environment) ለመፍጠር ባለመቻሉ እንጅ በወንጀለኛና በሙሰኛ ሥርዓት ሥር እየጓጎጥክም ቢሆን ለምን እንደ እኔ/እንደ እኛ ስኬት በስኬት አልሆንክም በሚል የግብዝነት አቀራረብ መሆን አልነበረበትም ። መሆንም የለበትም።
እሸቱ ሃይማኖታዊ እምነትን ከገሃዱ ዓለም ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ እይታ ጋር እያቀላቀለ ባቀረበው ሌክቸር ውስጥ ለዘመናት የዘለቀውና በአሁኑ ወቅትም በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ እየሆነ የቀጠለው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ እንኳንስ የአኗኗር ስልትን በአዳዲስ ፈጠራ ለማሻሻል የእለት እንጀራን አሸንፎ በህይወት መቆየትን በእጅጉ ፈታኝ የማድረጉን መሪር እውነታ አንድም ቦታ ላይ ሳት ብሎት አላነሳም (አልጠቆመንም) ።
እሸቱ ይህንን በራሱ ስኬታማነት ከልክ ባለፈ የተለጠጠውን (የተጋነነውን) ሌክቸሩን እያስደመጠን ያለው የ12ኛ ክፍል መለቀቂያ ፈተና ከወሰደው ከ8 መቶ ሽ በላይ የዚህ ወጣት ትውልድ አባል 3+ % ብቻ እንዲያልፍ በማድረግ ከፍተኛ የትውልድ ገደላ በተደረገበት እና ትውልድ በሞላ አስከፊ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በሚገኝበት መሪር ወቅት ነው። ይህንን የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ውጤት የሆነውን እጅግ አስከፊና አስደንጋጭ እውነታ አሳምሮ የሚያውቀው እሸቱ ግን “ከራስ ስንፍና ካልሆነ በስተቀር” ስኬታማነት የሚቻል መሆኑን ከእርሱ እንድንማር 1ኛ ፣ 2ኛ ፣ ወዘተ እያለ በጠቀሳቸው ማሳያዎቹ ይነግረናል/ይሰብከናል።
ለነገሩ በተወሰነ ሙያና በሆነ አጋጣሚ ስኬታማነትንና ታዋቂነትን ማግኘት ማለት ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ ሁሉንም ያወቅን እየመሰላቸው ከእኛ ወዲያ ላሳር የሚሉ ወገኖችን አደብ ግዙ ከማለት ይልቅ በየአዳራሹ፣ በየአደባባዩ ፣ በየሶሻል ሚዲያውና በየአጋጣሚው ወደ አምልኮ የሚጠጋ ሙገሳ ለጋሾች ሆነን ለመቀጠል ፈቃደኞች እስከሆን ድረስ የእነርሱ ስኬት የሌላውም ስኬት ሊሆን ያልቻለበትንና የማይችልበትን ነባራዊና መሪር ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የስብከት አተላ ሊግቱን ቢቃጣቸው የሚገርም አይደለም።
ተወለድኩበት፣ አደግሁበት እና ፊደል ቆጥሬ አደግሁበት የሚለው የአገሩ ህዝብ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት የገዛ ምድሩ ምድረ ሲኦል ስትሆንበት እያየ እንኳን ከምር እግረ መንገዱንም አስገንዝቦን ለማለፍ የሞራል ወኔው የሚጎድለው ሰው ስለ ምን አይነትና ስንት አይነት ስኬት ሌክቸር እንደሚያደርግ ለመረዳት ያዳግታል።
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ለዚህ አይነት መሬት ላይ ካለው ሰፊና አስከፊ መሪር እውነት ውጭ ለሚደሰኩረው የስኬት ምንነትና እንዴትነት ሃይማኖትን (ፈጣሪን) ጨምሮ ዋቢውና ተባባሪው ለማድረግ የሄደበት ርቀት ነው። አዎ! ርግጥ ነው አብዛኛው የመሠረታዊ እውቀት ጉድለት (lack of being well informed) ያለበት እንደ እኛ አይነት ማህበረሰብ ለዚህ አይነት ስሜታዊነት ለሚያጠቃው ስብከትና ዲስኩር በቀላሉ ተጋላጭ ቢሆን የሚገርም አይደለም። ከዚህ እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ሰብረን መውጣትና ጥረታችን የሚወልደውን ስኬታማነት በአግባቡ የሚያስተናግድ ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ማድረግ ካለብን ብቸኛው መውጫ መንገድ የምንገኝበት ፈተኝ ሁኔታ ሁለንተናዊና ውስብስብ መሆኑን አውቀን ለተገቢው ሁለንተናዊ ለውጥ እውን መሆን ሁለገብ ጥረት ማድረግ ነው።
አዎ! የአገራችን ህዝብ እጅግ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ስለ መኖሩ ለማወቅና ለማሳወቅ አንዳችም የሞራል ወኔ ሳይኖረው በየቦታውና በየክፍለ ዓለሙ እየዞረ እንደ ሃይማኖታዊ እምነት የመሰሉ እጅግ ስሜትን የሚስቡ ጉዳዮችን እያዘጋጀና እድሜ ለዘመኑ ቴክኖሎጅ በአሽብራቂ ገፅታ እያሳየ “ይህንን ያህል ሰብስክራይበር አገኝሁ” በሚል ስኬቴን ተመልከቱልኝ ከማለት አልፎ ፈጣሪን ጨምሮ ከመከረኛው ህዝብ ተነጥሎ እርሱ ጋር የሚዞር ዝና እና የተለየ ጥቅም ፈላጊ ማስመሰሉን “ተው በቅጥ አድርገው” ለማለት የማይደፍር ትውልድ የሸፍጥ ኑሮና አኗኗር ሰለባ ሆኖ ይቀጥላታል።
አዎ! የፈጣሪ ምድር የምንላት የአገረ ኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የባህር ማዶ ገዳምና ቤተ እምነት የማሠራት ዘመቻውን ያለምንም ጥያቄ ተቀበል ሲለው ከንፈር እየመጠጠ የሚቀበል እና ይህንን ካላደረገ የገነት በር እንደሚዘጋበት ሲነግረረው (ሲሰበከው) “ምነው አደብ ግዛ እንጅ” ለማለት የሚሳነው ትውልድ የታላቁ አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን አድራጊ ሳይሆን ከንቱ ናፋቂ ሆኖ ቢቀጥል ያሳዝን እንደሆነ እንጅ የሚገርም አይሆንም።
እውነት ነው ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ እጅግ ስሜትን የሚስቡና ጥያቄ ማንሳትን እንደ ሃጢአተኝነት ሊያስቆጥሩ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ለሶሻል ሚዲያ ቢዝነስ ማሳለጫነት በመጠቀም ረገድ ከእሸቱ ውጭ የተሳካለት ሌላ ሰው ያለ አይመስለኝም።
አዎ! በእርግጥ ለስኬት ጥረት የግድ ነው። ጥረትን ስኬታማ ለማድረግና ለማስደረግ የሚያስችል ወይም የሚያግዝ ሁኔታ ጨርሶ በሌለበት የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ “ያልተሳካላችሁ ወይም የወደቃችሁ እንደ እኔ ጥረት ስለማታደርጉና የፈጣሪን ተአምራዊ ሥራ ስለማትቀበሉ ነው “የሚል አይነት እጅግ ግብዝነት የተሞላበት ስብከት ከቶ የትም አያደርስም። ይህ አይነት ስብከት ሲቀርብለት ያለምንም ጥያቄ የሚቀበል ትውልድ የራሱን እጣ ፈንታ እያበላሸ የመሆኑን መሪር እውነት ተረድቶ በእውነተኛና ትክክለኛ ፍኖተ እምነት ፣ነፃነት፣ ፍትህና ርትዕ ፣ ሰላም ፣ ፍቅር፣ እና የጋራ ብልፅግና ላይ መሰባሰብ ይኖርበታል።
ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ከቀጠለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አዙሪት ሰብረን በመውጣት የተሻለ ሥርዓተ ማህበረሰብን እውን ማድረግ ካለብን ከመሪሩ እውነታ እየሸሹ ስለ ሰላምና ስለ ፅድቅ ሌክቸር እናርጋችሁ የሚሉንን ወገኖች ከቻልን አደብ እንዲገዙ በመንገር እና ቢያንስ ደግሞ ወደ አምልኮ የሚጠጋ ሙገሳን በቅጡ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ መግባባት ይኖርብናል።