September 25, 2023
2 mins read

በቃኝ አለ! (ለህልውና ትግል ለሚፋለመው ለመላው የአማራ ሕዝብ)

ጊዜው በሂደት ሲደርስ፣

ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ፣

እምቢኝ አለ…

የመከራን ስቃይ ቀንበር-ላንዲት ዕለት ላይሸከም፣

የሰቆቃን ብርቱ ሕመም- ለዘወትር ላይታመም፣

የትርክቱን ቅጥፈት ስንክሳር – ላንዲት ቅፅበት ችሎ ላይኖር፣

በሆድ-አምላክ፣ በምስለኔ – በቅጥረኞች ላይጠፈር…፣

በቃኝ አለ አመረረ! – ነጻነቱን አበሰረ!

ለዘመናት ችሎ…ችሎ..፣ – “ለምጣዱ ሲባል..” ብሎ፣

“ያይጥ መንጎች” መጨፈሪያ፣ – አሰስ-ገሰስ ማራገፊያ..፣

ሆኖ ኖሮ በትዕግስቱ፣  – ሲመስልበት የፍርሃቱ…

ጊዜ ቆጥሮ፣ ቀን አስልቶ፣ – ብድግ ቢል አንዴ አግስቶ፣

አጠገቡ እሚቆም ጠፋ፣ – አይጥ ሁሉ የደነፋ፡

ንጹሃንን ሲያርድ የኖረ – ትዕዛዝ ሰጥቶም ያሳረደ፣

የቁርጧ ቀን ስትመጣ – ብርድ-ብርድ አለው ራደ!

ግንባር-ቀደም ፊታውራሪ፣ – ከሌሎች ጋር ሆኖ መሪ..፣

በገነባት አገሩ ላይ  – ሲነሳበት መኖር ከልካይ፣

ወዴት አለው ሌላ አገር? – ከዚህች ንፁህ ምድሩ በቀር፤

እናም ሲብስ መገፋቱ፣ – ውርደት፣ ድፍረት…የንቀቱ…፣

አሻፈረኝ፣ እምቢኝ አለ! – በናት አገር ምድሩ ማለ!

ሳይወድ-በግድ የገባበት – ለህልውና መሰረቱ፣

በነጻነት ሊኖር በአገር- ተገላግሎ ከፋሽስቱ፣

በሚከፍለው መስዋዕትነት – እንዲከበር ሰውነቱ፣

አገር-ምድሩ ከጎኑ ነው – ፋኖ ልጁም ሠራዊቱ!

“መጀመሪያ መቀመጫ..” – አማራነት መነሻዬ፣

መዳረሻ የሩቅ ግቤ – እናት አገር ኢትዮጵያዬ፣

ብሎ ምሎ ስንቁን ቋጥሮ፣ ትጥቅ አጥብቆ፣

በትህትና፣ በጨዋነት ሥነ-ምግባር በሃቅ ልቆ፣

ተዘጋጀ፣ ለድል ጉዞ፣ በድል ምዕራፍ አሸብርቆ!

ጌታቸው አበራ

መስከረም 2016 ዓ/ም  (ሰፕቴምበር 2023)

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop