በላይነህ አባተ ([email protected])
መደመር ወይም ማቀላቀል የተባለው የይሁዳ ማእበል እንደ ገለባ የጠረጋቸው ብዙ ምሁራንና ጋዜጠኛ ተብዮዎች ሰሞኑን ደማሪዎቻቸው በቁማር ምዕራፍ-አንድ ተደላድለናል በሚል እንደ ፊኛ በሚተነፍስ ጥጋብ እነሱ የፈለጉትን የካድሬ መፈክር አልተናገሩም ብለው ቅሬታቸውን እንደ ጎርፍ እያዥጎደጎዱት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው እነዚህ አንደ ለማኝ እህል እየታፈሱ የሚደመሩ ወይም የሚቀላቀሉ ጥሬዎች ዛሬም ተዓይናቸው ጆሮሯቸውን የሚያምኑ በሽተኞች መሆናቸውን ነው፡፡
ይህ የማያባራ አዙሪት የሚያመለክተው ደማሪዎቻቸው ዛሬም እንደ በፊቱ “ኢትዮጵያ እኮ ሱስ ናት፤ ስንኖርም ስምሞትም ኢትዮጵያ፤ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አገር ናት” እያሉ ቢወሸክቱ ተፈርኦን ቤት ያደጉት ባህር አሻጋሪዎች ሙሴና ኢያሱ መጡ እያሉ እንደገና መቀመጫቸውን እንደ ጋሊሊዮ ፔንዱለም እያወዛወዙና ላባቸውን እንደ ዝናብ እያወረዱ ዳንኪራ የሚመቱ አድሮ ቃሪያዎች መሆናቸው ነው፡፡
እነዚህ አድሮ ቃሪያዎች የሰይጣን ተከታዮች የሚናገሩትን ለመስማት የሚጠባበቁትና የሚቀባጥሩትን ማዳማጥ የሚያቆሙት መቼ ይሆን? ተጀርባው ጦር የያዙ ፈሪሳዊ አረመኔዎችን አስከትሎ ጉንጭ የሚስመውን ይሁዳ በሥራው እንጅ ሥሞ በጦር በሚያስወጋ ምላሱ መመዘኑን የሚያቆሙት መቼ ይሆን? እነዚህ ድንፈፎች ተሰይጣን ተከታይ ይሁዳዎች ዘንድ መልካም ነገር ይመጣል ብለው የበሬ ቆለጥ ይወድቅልኛል ብላ ስትከተል እንደኖረችው ቀበሮ ሲንዘላዘሉ ኖረውና ሕዝብ አስፈጅተው ማለፍን የሚያቆሙት መቼ ይሆን?
ተደማሪ ምሁራንና ጋዜጠኛ ተብዮዎች ዛሬም እንደ ጋማ ከብት ነድተው ተደመሯቸው ሙሴዎች መልካም ነገር ጠብ ይላል በሚል የጅላንፎ ልብ የሚናገሩትን ለመስማት ጆሯቸውን የጅብ ጠረን እንደ ሸተታት አህያ ከፍተው እየተጠባበቁ ነው፡፡ እነዚህ ተደማሪ ምሁራንና ጋዜጠኞች “ሙሴ መጣ” የሚል የካድሬ ድስኩር ለፍልፈውና አዘናግተው ያስጨረሱት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ጭራሽ ሳይፀፅታቸው ዛሬም አማራ ተዳራጅቶ ራሱን ተጭራቆች እንዳይከላከል ቀበቶ የማስፈታትን የደማሪዎቻቸው ቁማር ምዕራፍ-ሁለት እያራመዱ ነው፡፡
ጅላንፎ ምሁራን፣ ጋዜጦችና ሌሎችም በስብከት እስተንፋስ እንደ ብናኝ ተጠርገው የሚሄዱ ገለባዎች ተዓይን ጆሮን የማመን ደዌ የሚድኑት መቼ ነው? እነዚህ እያዘናጉ ንፁኻንን ያሳጨዱ ከንቱዎች ተዚህ ሕዝብን ታስፈጀ ቆሌና አቴቴ የሚላቀቁት የትኛው ፃድቅ በመላእክት ክንፍ መጥቶ “ተዓይንህ ጆሮህን የማመን እርኩስ ባህሪም ሆነ የሰይጣን ተከታይ ይሁዳዎችን መስማትን አቁም!” እያለ ፀበል ቢያርከፈክፍባቸው ነው? እግዚኦ!
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.