emaለዚህ ሥርዓት መዳበር ዋና ሚና ከሚጫወቱት ተቋማት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች የሀገሪቱን ሕጎች አክብረው በሰላማዊ መንገድ እስከተንቀሳቀሱ ድረስ ማንም አካል በሐይል እንቅስቃሴያቸውን ሊያስቆም አይገባም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመለከትነው እንዳለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔዎቻቸውን እንዳያደርጉ እየተከለከሉ ይገኛሉ። ለአብነትም የካቲት 26/2015 ዓ.ም እናት ፓርቲ እንዲሁም በዛሬው ዕለት መጋቢት 03/2015 ዓ.ም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጉባኤ እንዳያደርጉ ክልከላ ተደርጎባቸዋል።
ይኽ ተግባር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያከስም ዓይን ያወጣ ህገ ወጥ ተግባር በመሆኑ የመንግስትን ድርጊት በጽኑ እናወግዛለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሠል ድርጊቶችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት የምንረዳ ቢሆንም የችግሩን ልክ በሚመጥን መልኩ ሐላፊነቱን እንዲወጣ እንጠይቃለን።
በተጨማሪም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግስት የፀጥታ ሐይሎች በሕግ ከተሰጣቸው ስልጣን በመተላለፍ እንዲህ አይነት ሕገወጥ ድርጊቶችን ባለመፈፀም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መዳበር ገለልተኛ ተቋምነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ እናቀርባለን።
እንዲህ አይነት ሕገወጥ ተግባር ሲፈጸም ምንም እንዳልተፈጠረ የምትመለከቱ የመንግስት አካላት እና የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን በዝምታ የድርጊቱ ተባባሪ መሆናችሁን እናሳውቃለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነት