December 20, 2022
40 mins read

አዲስ አበባ ወይስ አዲስ አባባ? – ክፍል ሁለት

“You can fool some people some time, but you can’t fool all the people all the time” – The late Bob Marley

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትና በሌሎችም የተለያዩ መድረኮችና በማህበራዊ ሜዲያ፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰቀለው ለምንድነው የሚል ጥያቄ በተነሳ ቁጥር የሚመለሰው መልስ ከላይ ወደ ታች በደም የሚተላለፍ ይመስል፣ ሊሴ ገ/ማሪያም ትምህርት ቤት የፈረንሳይ፣ እንግሊዝ ትምህርት ቤት የእንግሊዝ፣ጀርመን ትምህርት ቤት ደሞ የጀርመን ባንዲራ ይሰቀላልኮ የሚል ነው። እንዲህ አይነቱ በፍጹም ሰው ሰው የማይሸት አሳፋሪ የመላ መላ ንግግር ካሁን በኋላ መቆም አለበት። ልክ ነው በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ትምህርት ቤቶች መግቢያ ላይ የኢትዮጵያና የየአገሮቹ ባንዲራ ይሰቀላል፣ ነገር ግን እነዚህ ባንዲራዎች በሆቴሎች፣ በባንኮችና በየመንግስት መስሪያ ቤቱ በራፍ ላይ እንደሚሰቀለው ባንዲራ በየጧቱ ይሰቀላሉ እንጂ ተማሪዎች ተሰልፈው መዝሙር እየዘመሩ አይደለም የሚሰቀለው።  በእነዚህ አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎቹንና ባንዲራውን የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ትምህርት ቤቶች የአዲስ አበባ ህዝብ ገንዘብ የሌለባቸው በግል ኃብት የሚተዳደሩ ትምህርት ቤቶች ስለሆኑ ለምን ብለን ልንጠይቃቸው አንችልም። የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ግን ባንተ፣በሱ፣በሷና በእኛ የግብር ገንዘብ የሚተዳደሩ ስለሆነ፣ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ምንም ነገር ሲሆን ለምን ብለን የመጠየቅ፣ እየሆነ ያለውን ነገር ካልወደድነው ደሞ የማስቆም የዜግነት መብት አለን- ችግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈላጭ ቆራጮቹ “ቤርቤረሰቦች” ናቸውና ዜጎች ግብር መክፈል እንጂ መብታቸውን መጠየቅ አይችሉም!

ባለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ አበባን የሚያናውጣትን የባንዲራ ቀውስ በተመለከተ፣የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና የአዲስ አበባ ፖሊስ ሐሙስ ህዳር 29 ቀን በሰጡት መግለጫ ሁለቱም ችግሩን ፍጹም ለችግሩ ባዕድ ከሆኑ አካላትና ምክንያት ጋር ለማያያዝ ሲሞክሩ ታይቷል። ወ/ሮ አዳነች “የአዲስ አበባ ህዝብ አስተዋይ ህዝብ ነው፣ልጆቹን ይምከር። ይህ የአዲስ አበባ ህዝብ አጀንዳ አይደለም። ይህ የነሸኔ የተለያዩ የነጽንፈኛው ፋኖ ከዚያ በኋላ ደሞ የምዕራባዊያን እጅ ያለበት አጀንዳ ነው” ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል። እንደ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የፖለቲካ ሊቅ ባልሆንም፣ ዛሬ ባለንበት የአለም ተጨባጭ ሁኔታ እስራኤልና ፍልስጥኤም አንድ አይነት አጀንዳ ሊኖራቸው እንደማይችል ሁሉ ዛሬ ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ኦነግ ሸኔና ፋኖም በምንም አይነት አንድ አይነት አጀንዳ ሊኖራቸው አይችልም። ፋኖ የአማራ ክልል መንግስት ያደረገለትን የጭንቅ ቀን ጥሪ ተቀብሎ ከአገር አፍራሾች ጋር የታገለ ኃይል ነው፣ ኦነግ ሽኔ ዛሬም ትናንትም አገር አፍራሽ ነው። ወደ አዲስ አበባ ጉዳይ እንምጣ ከተባለም፣ኦነግ ሸኔ የባንዲራው ይሰቀል ፕሮጀክት አባት ነው፣ ፋኖ ግን በፍጹም በዚህ አይታማም። ለመሆኑ የዚህ የሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ የ”ባንድራ ስቀሉ አንሰቅልም” ግርግር አባት ማነውና ነው ሸኔ ፋኖ እየተባለ ሌላ የእንጄራ አባት የሚፈለግለት? ማነው መዝሙሩ ይዘመራል ባንዲራውም ይሰቀላል ብሎ የተናገረው? ያ ንግግር አይደለም እንዴ ዛሬ በተግባር እየተተረጎመ ያለው?

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዶር ዘላለም ሙላቱም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተነሳው ረብሻ ምክንያቱ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸውን፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ መሰቀሉንና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር መዘመሩን የማይደግፉ ሰዎች መኖራቸው ነው ብለዋል። የመጀመሪያው ምክንያት ፍጹም ከእውነት የራቀና በአዲስ አበባ ደረጃ የአንድ ትልቅ ተቋም መሪ ከሆነ ግለሰብ ቀርቶ ከማህበራዊ ሜዲያ አሉባልተኛም የማይጠበቅ ተራ ውሸት ነው። በዛሬዋ በብዙ ነገሮች ላይ ስምምነት በሌለባት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሁላችንንም የሚያስማማ ጉዳይ ቢኖር “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር አለበት” የሚለው ሃሳብ ነው፣ ይህ ደሞ ባለፉት ሰላሳ አመታት በተግባር የታየ ጉዳይ ነው። ምነው ታዲያ ዛሬ ላይ ይህንን ከአመታት በፊት ያለቀለት ጉዳይ እያነሳን ለፖለቲካ አጀንዳችን ሽፋን መስጫ እናደርገዋለን?

የአዲስ አበባ ፖሊስ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ “የዜጎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብትና ማንነታቸውንና ባህላቸውን መግለጽን እንደጫና እና በኃይል በሌሎች እንደተጫነ አድርገው የሚያምኑ ኃይሎች” እንዳሉና በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የሚታየው ችግርም ከነዚህና ከሌሎችም የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግሯል። ከዚህ በተጨማሪ በአንድ በኩል ከሰሞኑ የነበረው ተቃውሞ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶችን “የረብሻና የጥፋት ብሎም የውድመት መድረክ ለማድረግ” የታቀደ ነበር  ያለ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹በሕጋዊ ሽፋን የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንንት በሚያውኩ ልዩ ልዩ ሕገወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቡድኖችና ግለሰቦች ከአጥፊ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል” ብሏል። ይህ አባባል የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የግለሰቦችንና ባጠቃላይ የዜጎችን መሰረታዊ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመቃወም ህገመንግስታዊ መብት ለመገደብ የሚደረግ ሙከራ አካል ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? እነዚህ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብቶች የአንድን ወገን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም ተብሎ ሲጣሱ፣ሲገደቡ ወይም ሲታገዱ ደሞ ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም የተዘጋጀን ሰዎች እንዳለን መታወቅ አለበት!!!

ማንም ሰው፣ቡድን ወይም ድርጅት ህገመንግስታዊ መብቴንም ሆነ ሰብዓዊ መብቴን የመከልከል ወይም የማገድ ምንም አይነት መብት እንደሌለውና፣ የህግ ዋናውና ተቀደሚው ስራ ይህንን መብቴን መጠበቅና ማስጠበቅ መሆኑን ጠንቅቄ የማውቅ ሰው ነኝ። እኔም አጠገቤ ያለውን ዜጋ ህገመንግስታዊና ሰብዓዊ  መብት የማክበር ግዴታ እንዳለብኝና፣ ይህንን ግዴታዬን እስካልተወጣሁ ድረስ ወይም የሌሎችን መብት እስከጣስኩና ነጻነታቸውን እስካላከበርኩ ድረስ በህግ መጠየቅ እንዳለብኝም የምረዳ ሰው ነኝ።

 

ለመሆኑ ሽሮሜዳ እንጦጦ አምባ ት/ቤት ተጀምሮ በፍጥነት ወደ ተለያዩ ት/ቤቶች የተዛመተው ግርግር ምክንያቱ ዜጎች በአፍ ቋንቋቸው በመማራቸውና ማንነታቸውንና ባህላቸውን ለመግለጽ በመሞከራቸው ነው? በፍጹም አይደለም! በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር የለባቸውም ብሎ የሚሞግት ሰው በጭራሽ የለም! ደሞስ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልልን ባንዲራ ከመስቀል ጋር ተያይዞ የተነሳው ረብሻ በእርግጥ የታቀደ ነበር? ማነው ያቀደው? የባንዲራው ጉዳይ ከየት እንደመጣና ማን እንዳመጣው በግልጽ እየታወቀ ለምንድነው ጣታችንን ሌሎች ላይ የምንጠቁመው? በህጋዊ ሽፋን የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉ የትኞቹ ናቸው? የኢዜማን፣ የአብንን እና ሌሎች ሶስት ፓርቲዎች በጋራ የሰጡትን መግለጫ ተመልክቻለሁ። የእነዚህ ኃላፊነት የሚሰማቸው ፓርቲዎች መግለጫ ትኩረት አንድና አንድ ሃሳብ ላይ ነው፣ እሱም ይህ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተጀመረውና ማህበረሰቡን ያስቆጣ ህገወጥ የባንዲራ ስቀሉ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ይቁም የሚል ነው። የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንንት በሚያውኩ ልዩ ልዩ ሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩት? ከመቼ ጀምሮ ነው የዜጎችን መብት አክብሩ፣ የማህበረሰቡን ፀጥታ ከሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች ታቀቡ ማለት ህገወጥ የሆነው?

አንድን ችግር ለማቃለል ቢቻል ደሞ ለማጥፋት መጀመሪያ ችግሩ ምን መሆኑን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፣ ቀጥሎ የችግሩን ምንጭ (Root Cause) እና የችግሩን ባለቤቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው። እነዚህ ከታወቁ በኋላ ነው ችግሩን እንዴት እናጥፋው፣መቼ እናጥፋው፣ ከነማን ጋር እናጥፋው የሚሉ ጥያቄዎች የሚቀጥሉት። ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የተከሰቱት ችግሮች በቀጥታ ከኦሮሚያ ክልል መዝሙርና ባንዲራ ጋር የተያያዙ ናቸው እንጂ ተማሪዎች ለምን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይማራሉ የሚል አይደለም።

ለምንድነው አገራችን ከምንግዜም በላይ ሰላምና መረጋጋት በሚያስፈልጋት ግዜ እንዲህ አይነት ህዝብን የሚከፈፍል አላስፈላጊ ስራ የሚሰራው? የፌዴራል ዋና ከተማ በሆነችውና እራሷን በራሷ በምታስተዳድር ከተማ ውስጥ ቀርቶ፣ በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች ውስጥም ቢሆን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የኢትዮጵያ ባንዲራ አይደለም እንዴ? ታዲያ ለምንድነው ሁላችንንም የሚያስማማ፣ የሚያቀራርብና የሚያስተሳስር ብሔራዊ መዝሙርና ብሔራዊ ባንዲራ እያለን በክልሎች ብቻ መዘመር ያለበትን መዝሙርና በክልሎች ብቻ መሰቀል ያለበትን ባንዲራ አለቦታው እንዲዘመርና እንዲሰቀል እያደረግን የሰላም መደፍረስ ምክንያት የምንሆነውና መቀራረብ ሲገባን የምንራራቀው? የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ የብሔር ብሔረሰቦች መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ የተጀመረው የአንድን ክልል መዝሙር መዘመርና ባንዲራ መስቀል አላማና ግብ ምንድነው የሚለው ጥያቄ እንዲመለስለት ይፈልጋልና ይህንን ጥያቄ የሚመለከታችሁ ወይም “መዝሙሩ ይዘመራል፣ ባንዲራውም ይሰቀላል” ያላችሁ ሰዎች መልሱለት!

ባለፉት አራት አመታት ውጭ አገር የሉት፣አገር ውስጥ ያሉት፣በተቃዋሚ ተርታ የተሰለፉት፣ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉት፣በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትና መሳሪያ ያነገቡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሁሉም በአንድ ድምጽ አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት የሚል ድምጽ በተከታታይ አሰምተዋል፣ ይህንን በአፋቸው ያሰሙትን ድምጽ በተግባር ለመተርጎም የየራሳቸውን እርምጃም ወስደዋል።

በ2011 ዓም መስከረም ወር ላይ ኦፌኮን ጨምሮ አምስት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዲስ አበባ በወረራ ከኦሮሞዎች ላይ የተወሰደች ከተማ ናትና ወደ ባለቤትዋ መመለስ አለባት ብለዋል። በመጋቢት ወር 2011 ዓም ደሞ ኦህዴድ የአዲስ አበባ ኮንደሚኒየም ዕደላን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ላይ ምንም ነገር ሲሰራ ያለ ኦሮሞ ህዝብና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፈቃድ መሰራት የለበትም ካለ በኋላ፣ የክልሉ ፓርቲና መንግስት አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ ሌት ከቀን እንደሚሰራ ተናግሯል። እነዚህ ሁለት “አዲስ አበባ የኛ ናት” የሚሉ መግለጫዎችና ንግግሮች በግለሰብ ደረጃ ያበዱትን እነ በቀለ ገርባን፣ መረራ ጉዲናን፣ ብርሃነ መስቀል አበበንና ህዝቅኤል ጋቢሳን ወዘተ ሳይጨምር ነው። ከሰሞኑ አዲስ አበባ ላይ የምንመለከተው የባንዲራችን ይሰቀል አጀንዳ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሁሉ የሚደግፉት የጋራ ፕሮጀክት ነው። ታዲያ ይህ በየትምህርት ቤቱ የሚታየው የባንዲራ ትርምስ የትልቁ አዲስ አበባን የኦሮሞ እናደርጋለን የሚለው ፕሮጀክት አካል ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለን? ደሞስ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲህ አይነቱን ህገወጥነት መዋጋት ተፈጥሯዊ መብታችን አይደለም እንዴ? አዲስ አበባን የኛ እንጂ የኔ ማለት ይቻላል እንዴ?

ለመሆኑ አዲስ አበባ የማናት? የአዲስ አበባ ከተማ ማንነትና የከተማዋ ባለቤትነት መብት የሚመነጨው በከተማዋ ውስጥ ከሚኖረው በእግዚአብሔር አምሳያ ከተፈጠረው ሰው/ህዝብ ነው ወይስ ከግዑዙ መሬት? አዲስ አበባ በጆግራፊ አቀማመጧ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው የምትገኘው ማለት ባሌ፣አርሲና ወለጋ ውስጥ የሚኖረው አዲስ አበባን አንድም ቀን አይቷትም በስም ጠርቷትም የማያውቅ ኦሮሞ፣ ከቅድም አያቶቹ ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ ከኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይበልጥ የአዲስ አበባ ከተማ ባለቤት ነው ማለት ነው? የአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት የሚወሰነው በመሬቱ ነው የምትሉ ከሆነ የመሬቱ ባለቤት አዲስ አበቤ ነውና ባለቤትነቱን አክብሩለት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ማንነት የሚወስነው በህዝቡ ነው ከተባለም አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ከ2/3ኛው በላይ ኦሮሞ አይደለምና ማንነቱን አክብሩለት። ከዚህ ውጭ የሆነ የተናጠል፣ የዕብሪት፣የጉልበትና ከህዝብ ይበልጥ መሬትን የማስቀደም አባዜ ያለመሰልጠን ምልክት ነው!

የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ክልል የወሰን ጉዳይ ያለቀለት ጉዳይ ይመስላል፣ እንጦጦ አምባ፣ቀጨኔ ደብረ ሰላምና ብሔራዊ የህጻናት መዋያ ትምህርት ቤቶች የሚገኙበት የሽሮ ሜዳ፣ቀጨኔና ቂርቆስ የሚባሉ ቦታዎች ደሞ በቀኃሥ ዘመን በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳደር ውስጥ ያልነበሩ፣ በደርግ ዘመን በሸዋ ክፍለ ሐገር አስተዳደር ውስጥ ያልነበሩ፣ ኢትዮጵያ ፌዴራል የመግስት መዋቅርን በተከተለችባቸው ባለፉት 30 አመታትም በኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ውስጥ ሆነው የማያውቁ ሁሌም አድራሻቸውም መታወቂያቸውም አዲስ አበባ የሆነ ቦታዎች ናቸው። ስለዚህ በዚህ ከላይ እስከታች ድሩም ማጉም አዲስ አበቤ በሆነ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የኦሮሚያን ክልል መዝሙር አንዘምርም፣ ባንዲራውንም አንሰቅልም ሲሉ ምክንያት አላቸውና ተማሪዎቹንም ወላጆቻቸውንም ሰብስበን ምክንያታቸውን መስማት ነው ያለብን እንጂ፣ተማሪዎቹን እያሳደድን መደብደብና ወላጆቻቸውን ቢሮ ድረስ እየጠራን ልጆቻችሁ እንዲታዘዙ አድርጉ ማለት ህገ ወጥነት ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መብት ያለን ግድየሽነትም ነው። የማን አባት ነው ከሱም ከልጆቹም ማንነት ጋር የሚጋጭ መዝሙር ልጆቹ ሲዘምሩ ዝም ብሎ የሚመለከት? የማን እናት ናት የአገሯ ብሔራዊ ባንዲራ እያለ ልጆቿ እሷንም አዲስ አበባንም የማይመስል ባንዲራ ሲሰቅሉ እጇን አጣጥፋ የምትመለከት? ደሞስ የአንዳንድ ክልሎች መዝሙር አዲስ አበባ ተወልደው የሚያድጉና ከኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርና ከኢትዮጵያ ባንዲራ ውጭ ሌላ ምንም የማያውቁ ልጆች እንኳን ሊዘምሩት ሌላ ሲዘመርውስ መስማት አለባቸው እንዴ? ለመሆኑ በትግራይና በኦሮሚያ ክልል መዝሙሮች ውስጥ ያሉ ወንድማማችነትንና የአንድ አገር ዜግነትን ሳይሆን ጠላትነትን የሚሰብኩ አንዳንድ ስንኞችን ስንመለከት፣ እነዚህን መዝሙሮች በጋራ ልንዘምራቸው ቀርቶ መዝሙሮቹ እንደ አንድ አገር ህዝብ አንድ ላይ የሚያኖሩን ናቸው እንዴ? እኔ ስንኞቹን እዚህ ላይ ደርድሬ ላሳያችሁ ብሞክር እጄም የሚታዘዝልኝ አይመስለኝምና እስኪ መዝሙሮችን እዩዋቸውና እናንተው ፍረዱ! 3ቱን ክልሎች ክልላዊ የህዝብ መዝሙሮች – የአማርኛ ትርጓሜ አንብቡና – ፍርዱን ለህሊናችሁ ስጡት! – ሄርሜላ አረጋዊ – ሐበሻ (Zehabesha) የዕለቱ አብይ ዜና | ሰበር ዜና | አስተያየትና ትንታኔ | ዜና የኢትዮጵያ (amharic-zehabesha.com)

ወ/ሮ አዳነችና የ“ባንዲራችንን ስቀሉ” ፕሮጀክት ባለቤቶች ሊገነዘቡት የሚገባ አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ፣ የአዲስ አበባ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩት የቀለም ትምህርት እንዲማሩላቸው ብቻ አይደለም። ትምህርት ቤቶች ጨዋ (Virtuous)፣ አገራቸውን የሚወዱና በስነምግባር የታነጹ ዜጎች የሚፈጠሩበት ቦታዎች ናቸው። ስለዚህ የአዲስ አበባ ወላጅ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት የሚልከው ከቀለም ትምህርት ባሻገር ልጆቹ ኢትዮጵያን እንዲማሩለት፣ኢትዮጵያን እንዲዘምሩለትና ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ልጆች ጋር ሆነው የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ እንዲያደርጉና ነገና ከነገወዲያ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ደሞ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው የኢትዮጵያን ችግር ማስወገድ የሚያስችላቸውን የጋራ እሴትና ማህበራዊ ወረት እንዲገነቡ ነው። እንዲህ አይነት አገራዊ እይታ ነው የአዲስ አበባ ወላጅ ፍላጎት እንጂ፣ ልጆቹ የዘር ፖለቲካ እየተጋቱ እንዲያድጉ፣ ከትልቅነት ትንሽነትን እንዲመለከቱ፣ከትልቋ ኢትዮጵያ ጎጣቸውን እንዲያስበልጡ ወይም ኢትዮጵያን ትተው አንድን ክልል ከፍ እንዲያደርጉ በፍጹም አይፈልግም። ጎጠኞቹ የሚገባቸው ከሆነ፣የነሱ ክልልና ባጠቃላይ ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የነሱም ልጆች በአንድ ቋንቋ፣ ባህልና ትርክት አጥር ውስጥ ታጥረው ከሚያድጉ፣ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ጋር የሚያስተሳስራቸውን ቋንቋ፣ ባህልና ትርክት እየተማሩ ቢያድጉ ነው።

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አፋን ኦሮሞ በቋንቋ ደረጃ ለተማሪዎች መሰጠት አለበት፣ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር መዘመር አለበት፣ ባንዲራውም መሰቀል አለበት የሚል ድምፅ በተደጋጋሚ ይሰማል። አንዳችን የሌላችንን ቋንቋ ብንማር ይጠቅማል በሚለው ሃሳብ እኔም ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ። ቋንቋ መማር የሚጠቅመን ግን በግድ ተማሩ ስንባል አይደለም፣ደሞም የክልል መዝሙር መዘመርና የክልል ባንዲራ መስቀል ቋንቋ አያስተምርንም። የኦሮሚያን ባንዲራ አለቦታውና አለአድራሻው ወይም ምንም ትርጉም በሌለው ቦታ ላይ በጉልበት መስቀልና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አፋን ኦሮሞ ቢማሩ ይጠቅማል ማለት እጅግ በጣም የተለያዩ አባባሎች ናቸው፣ አባባልሎቹ ብቻ ሳይሆን አላማቸውም በጣም ይለያያል። የህዝብ ጥያቄ አፋን ኦሮሞ ለምን እንማራለን የሚል አይደለም፣ጥያቄው ጉልበትና ኃይልን ምን አመጣው ነው፣ጥያቄው ይህ የተናጠል እርምጃ አላማው ምንድነው ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ትልቁ ጥያቄ እራሷን በሯሷ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ ሥልጣን ባላት አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ከሌሎች ክልሎች ባንዲራ ተለይቶ በትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ እንዲሰቀል የሚደረገው ለምንድነው የሚል ነው።

አዲስ አበባን ጨምሮ በየትኛውም ክልል ውስጥ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር እየዘመሩ የኢትዮጵያን ባንዲራ መስቅል ሲገባቸው፣ ለምንድነው የአንድ ክልል ባንዲራ ተመርጦ አዲስ አበባ ውስጥ እንዲሰቀል የሚደረገው? በየክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የክልላቸውን መዝሙር እየዘመሩ ባንዲራቸውን መስቀል ይችላሉ፣ ግን እሱም ቢሆን መሆን ያለበት በቅድሚያ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር እየተዘመረ የሁላችንም አርማ የሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ነው፣ ደሞም የሁላችንም የሆነው ባንዲራ ከአንድ ክልል ባንዲራ ይበልጣልና፣ የክልል ባንዲራ መውለብለብ ያለበት ከኢትዮጵያ ባንዲራ ዝቅ ብሎ ነው። ሰሚ ጆሮ ካለ፣ በጨቅላ ህጻናት አዕምሮ ውስጥ እንዲህ አይነት መልካም ዘር ስንዘራና ከሱ ውጭ የሆነውን ሁሉ እንደጠላት ሳይሆን እንደወዳጅ የሚመለከት ጨዋ ዜጋ ስንፈጥር ነው በሰላም ጎን ለጎን አብረን የምንኖረውና ሁላችንም ኢትዮጵያን አገራችን ብለን የምንጠራው።

አገራችን ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙባት አገር ናት፣ይህ የሚነግረን ኢትዮጵያ ለአገራዊ አንድነት ብቻ ሳይሆን ለብዝሃነትም፣ ለብዝሃነት ብቻ ሳይሆን ለአገራዊ አንድነትም ከፍተኛ ቦታ መስጠት ያለባት አገር መሆኗን ነው። ኢትዮጵያ እንደ አገር የምትቆመው በሁለቱ መሰረቶች ላይ ነውና አንዱን ከሌላው ለይተን መምረጥ አንችልም። እኛ ኢትዮጵያዊያን በብዝሃነት ውስጥ ጠንካራ አገራዊ አንድነት፣ በጠንካራ አንድነት ውስጥ የሚናበብ፣ የሚግባባና የሚከባበር ብዝሃነት የሚኖረን ማንነታችን፣ቋንቋችን፣ባህላችንና ሃይማኖታችን እኩል ሲከበሩ ነው። አንዳችን ለሌላችን ባህልና ሃይማኖት እውቅና መስጠትና ማክበር እንጂ የግድ መከተል የለብንም። ጠንካራ ብሔራዊ አንድነት እንዲኖረንና ጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ማህበረሰብ ለመገንባት ግን አንዳችን የሌላችንን ቋንቋ ማክበር ብቻ ሳይሆን መናገርም መቻል አለብን።

አገራችን ኢትዮጵያ ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋ እንደሚያስፈልጋት ሳይታለም የተፈታ ነው፣ ከአማርኛ ጋር ጎን ለጎን የስራ ቋንቋ መሆን ከሚገባቸው የአገራችን ቋንቋዎች ውስጥ አንዱና የመጀመሪያው አፋን ኦሮሞ መሆኑም ብዙ የሚያነጋግር አይመስለኝም። አፋን ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የሚያደርጉት ግን ኦሮሚያ ክልልና ወ/ሮ አዳነች አይደሉም። ይህ ሁላችንም ቁጭ ብለን፣ተነጋግርንና ተስማምተን የምንወስነው ውሳኔ ነው። ይህንን ለማድረግ ደሞ በጣም ምቹ የሆነ አገራዊ መድረክ እየተፈጠረ ነው። ኦሮሚያ ክልልም፣ ወ/ሮ አዳነችም፣ የኦሮሞ ልህቃንና ሶሻል አክቲቪስቶችም የጉልበት መንገዳቸውን አቁመው አገራዊ የምክክር ጉባኤውን ቢጠብቁ በጡንቻ የሚሞክሩትን በሃሳብና በመግባባት እንዲያገኙ እኛም እናግዛቸዋለንና ይህንን በጉልበት የማይችሉትንና ሁላችንንም ተሸናፊ የሚያደርገውን የጨለማ መንገድ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ በማክበር እንጠይቃቸዋለን!

ኢትዮጵያ ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን የስራ ቋንቋ ስናደርግ አንደኛ- ለረጂም ግዜ የተጠየቁ ቋንቋችንና ባህላችን እውቅና ማግኘት አለባቸው የሚለውን ህዝባዊ ጥያቄ እንመልሳለን፣ ሁለተኛ- የቋንቋ እኩልነትን እናከብራለን፣ ሶስተኛ- ያለ አስተርጓሚ የሚግባባ ትልቅ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኤኮኖሚያቂ ማህበረሰብ እንፈጥራለን፣ አራተኛ- ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች እንዲቀራረቡና አንዱ የሌላውን ባህል፣ ወግና ታሪክ በቀላሉ እንዲያውቅ መንገድ እንከፍታለን፣አምስተኛ- በትላልቆቹ አገራዊ ተቋሞችና በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ሄዶ መስራት የሚችል ወጣት የስራ ኃይል በመፍጠር ዛሬ በክልሎች መካከል የሚታየውን ኤኮኖሚያዊና የተማረ የሰው ኃይል  ልዩነት ማጥበብ እንችላለን። እነዚህ እሴቶች ናቸው የጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት መሰረት የሚሆኑት። በእነዚህ አገራዊ እሴቶች የተገነቡና አገራቸውን የሚወዱ ወጣት ዜጎች የምንፈጥረው ግን ቁጭ ብለን ተነጋግረን፣ ተግባብተንና ተስማምተን በወደፊቱ ትልልቅ የአገራችን ጉዳዮች ላይ የጋራ ውሳኔ ስንወስን ነው እንጂ፣በየትምህርት ቤቱ እየሄድን ቋንቋችንን ተናገሩ፣ መዝሙራችንን ዘምሩ፣ ባንዲራችንን ስቀሉ እያልን ህጻናትን ስናስጮህ አይደለም።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አማርኛ የፌዴራሉ መንግስት የስራ ቋንቋ ነው፣የፌዴራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው ይላል። ይሄው ህገ መንግስት የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል ይላል። ስለዚህ ተስማምተን ይህንን ህገመንግስት እክስናሻሽለው ድረስ አዲስ አበባ ውስጥ የስራ ቋንቋ አማርኛ ነው፣ የትምህርት ቋንቋም አማርኛ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ በየትኛውም ቦታ መሰቀል ያለበት ባንዲራ ግን ህገ መንግስቱ ተሻሻለም አልተሻሻለ የኢትዮጵያ ባንዲራ ብቻ ነው አዲስ፣ወይም አዲስ አበባ ክልል ስትሆን የኢትዮጵያንና የራሷን ባንዲራ ትሰቅላለች። ይህ እስኪሆን ድረስ አዲስ  አበባ የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ከተማ ናት፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፣ አዲስ አበባ በአስተዳደር የየትኛውም ክልል ውስጥ የማትገኝ እራሷን በራሷ የምታስተዳድር ከተማ ናት። ይህንን የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ መብት ኦሮሚያን ጨምሮ አስራ አንዱም ክልሎች ማክበር አለባቸው።

አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞዎች ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው የሚል ጥያቄ ካነሱ፣ ጥያቄው አግባብ ያለው ህጋዊ ጥያቄ ነውና መስተናገድ አለበት። ግን ጥያቄውን ለማስተናገድ በጣት የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተማሪዎች የሚማሩበት ክፍል በእያንዳንዱ የአዲስ አበባ ት/ቤት ውስጥ እንደ እድር ድንኳን መተከል የለበትም፣ ወይም አዲስ አባባ ውስጥ ተማሪዎችን በአፋን ኦሮሞ ለማስተማር ህጻናትን ከቱሉ ዲምቱ፣ከሱሉልታና ከቡራዩ በአውቶቡስ ማመላለስ አያስፈልግም። አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሞን ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ማድረግና አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያን ክልል ባንዲራ መስቀል ፍጹም የተለያዩ ሃሳቦች ናቸው፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ነው፣ ከህዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጭ ባንዲራዬ አለቦታው ይሰቀል ማለት ግን በበረኪናም ታጥቦ የማይጠራ ቆሻሻ የፖለቲካ አጀንዳ ነው።

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop