December 17, 2022
34 mins read

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የነጻነትና የአንድነት፣ የሰላምና የልማት ትእምርት/Symbol እንጂ የድኅነት እና የጉስቁልና ምክንያት አይደለችም!!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ*

(ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሑፍ የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን እምነት፣ አስተምህሮ ለማወገዝ ወይም ለመተቸት አሊያም ደግሞ የእምነቱ ተከታይ የሆኑትን አማኞችንም ለመንቀፍ የተጻፈ ጽሑፍ አይደለም፡፡ ‘‘ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው፤’’ እንደሚባለው- የሁላችንም እናት፣ የጋራ በሆነች ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁላችንም ተከባበረንና ተዋደን ለመኖር የሚያስችሉንን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ትውፊታዊ እሤቶቻችን ከፍ በማድረግ በሰላምና በወንድማማችነት የአንድነት መንፈስ የጋራ በሆነች ኢትዮጵያችን በሰላምና በፍቅር መኖር እንዳለብን የምረዳ ሰው ብቻ ሣይሆን ለተግባራዊነቱም በጽናት የምቆም፣ የምታገልም ሰው ነኝ፡፡

ስለሆነም ይህ ጽሑፍ ከሃይማኖቶች አስተምህሮ፣ ከሥነ-ምግባርና ሀገሪቱ ከምትመራበት ሕገ-መንግሥት ባፈነገጠ መልኩ በአንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ እየተደረጉ ያሉ ሕገ ወጥ የኾኑ አካሄዶች ሊታረሙ፣ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል የሚል መልእክትን ያዘለ ብቻ መሆንኑን አንባብያን ከወዲሁ እንዲረዱልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃለሁ!!) 

  1. እንደመንደርደሪያ

በዚህ ሰሞን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆነ ዮናስ አክሊሉ የተባለ ‘‘አገልጋይ’’፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ምእመኖቿን ለማጽናት፣ ለምክርና ለተግሣጽ የምትጠቀምባቸውን እንደ ተኣምረ-ማርያም እና ገድለ-ተክለሃይማኖት የመሳሰሉ አዋልድ መጻሕፍትን እያጣቀሰ- ‘‘…ይህ በቅዱስ ወንጌል ላይ የተደረገ ክህደት፣ ምንፍቅና ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ተኣምረ ማርያም እና ገድለ ተክለሃይማኖት የመሳሰሉ መጻሕፍት ‘‘ወንጀለኞች’’ ናቸውና ሊወገዙ ይገባቸዋል!’’ የሚል መልእክትን አስተላልፏል፡፡

ዮናስ አክሊሉ ያለበትን የእምነት ተቋም አስተምህሮ ለተከታዮቹ ከማስተማር ባለፈ በምን ምክንያት ወደሌላ የእምነት ተቋም ተሻግሮ እንዲህ ዓይነቱን ፍጹም ድፍረት የተሞላበት ዘለፋና የውግዘት ቃል ለማስተላለፍ እንደፈለገ አልገባኝም፡፡ ይህን በጊዜው ግለሰቡ መልስ ይሰጥበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት በምትጠቀምባቸው መጻሕፍት ዙሪያ አገልጋይ ዮናታንና ተከታዮቹ ላለባቸው ጥያቄና ላስተላለፉት የውግዘት ቃል እንደየደረጃው – ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ /ዶግማዋንና ቀኖናዋን/ በተመለከተ ምላሽ የሚሰጥ ዝግጁ የኾነ ‘የሊቃውንት ጉባኤ’ ስላላት በእነርሱ በኩል ተገቢውን ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡

አስገራሚው ነገር ዮናታን በውግዘትና በወንጀለኛነት ከጠቀሳቸው የኢትዮጵያ ቤ/ክን መጻሕፍትም ባሻገርም፤ ‘‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የድኅነትና የጉስቁልና ምክንያት መሆኗን፤’’ ጭምር በአደባባይ ለማወጅ ደፍሯል፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የድኅነትና የጉስቁልና ተምሳሌት አድርጎ የመግለጽ ሁኔታ አዲስ ክሥተት አይደለም፡፡ ይህን እሳቤ ከጥቂት ዓመታት በፊትም ፓ/ር ቶሎሳ ጉዲና (ዶ/ር) የተባሉ የፕሮቴስታንት እምነት አገልጋይና መሪ የኾኑ ሰው፤

‘‘…የኢትዮጵያ ቤ/ክ ለምእመኖቿና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድኅነትን፣ የጉስቁልናን እና የመከራ ቀምበር የጫነች ተቋም ናት…’’ በሚል በአደባባይ ተናግረው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ይህ የፓስተር ቶሎሳ ንግግርም በወቅቱ በአባቶችና በምእመናን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር፡፡ በዛው ሰሞንም የአሜሪካ ሬዲዮ መምህር ዶ/ር ዘበነ ለማንና ፓስተር ቶሎሳ ጉዲናን ጋብዞ- ፓስተሩ ቤተክርስቲያኒቱን በወቀሱበት ሐሳብ/ትችት ላይ በመመርኮዝ አከራክሮቸው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እንደገና ከዓመታት በኋላም ‘‘አገልጋይ’’ ዮናታን ተመሳሳይ የኾነ ክስንና ዘለፋን በአደባባይ አቅርቧል፡፡

በመሠረቱ ‘የብልጽግና ወንጌል/the Prosperity Gospel’ ሐሳብ አቀንቃኞች ‘‘የኢትዮጵያ ቤ/ክን በሕዝቦቿ ላይ የጉስቁልና፣ የመከራ ቀምበርን የጫነች ተቋም ብቻ ሳይሆን የዕድገትና የብልጽግና እንቅፋት መሆኗን…፡፡’’ ጭምር በግልጽ መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡

ይህን የተሳሳተ እሳቤ ማረም ያስፈልጋልና በዚህ በዛሬው ጽሑፌ፤ ‘‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የነጻነትና የአንድነት፣ የሰላምና የልማት ትእምርት/Symbol እንጂ የድኅነት እና የጉስቅልና ምንጭ ወይም ምክንያት አለመኾኗን፤’’ ከታሪክ መዛግብት በማጣቀስ ጥቂት ነገር ለማለት እፈልጋለኹ፡፡

ስለሆነም በቅድሚያ፤ ‘‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤ/ክን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁር ሕዝብና በአጠቃላይም የሰው ልጆች ሁሉ የነጻነትና የአንድነት ትእምርት/ሲምቦል መሆኗን’’ ከመግለጽ ለመጀመር እወዳለኹ፤

 

  1. የኢትዮጵያ ቤ/ክን እንደ ‘የነጻነት እና የአንድነት ትእምርትነት’

ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ኪነ-ሕንፃ፣ ሥነ ጽሑፍ… ወዘተ ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለ ነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ናት፡፡

 

ከዚህም የተነሣ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ምክንያቱ ቤተክርስቲያኒቱ ስለ አገር ክብር፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው፡፡ እናም ይህች ጥንታዊትና ጠንካራ ሃይማኖታዊ ተቋም መምታት ለብዙዎቹ የኢትዮጵያንን የነፃነትና የአንድነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል፡፡

 

በኢጣሊያ ፋሽስት የዐድዋውን አሳፋሪ ሽንፈት ለመበቀል ለሁለተኛ ወረራ በመጣበት ጊዜም- ቤተክርስቲያኒቱ በዐድዋው ዘመቻ እንዳደረገችው ሁሉ- ሕዝቡ ከፈጣሪው ዘንድ ለተቸረው ለነጻነቱ፣ ለክብሩና ለሃይማኖቱ ቀናኢ እንዲሆን በማስተማር ረገድ የምታደርገውን ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ተልእኮዋንአስቀድሞ ለማጨናገፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤክርስቲያን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያን ውድመት አካሂዷል፡፡ ይህን እውነታ የሚዘክሩ ከታሪክ መዘግብቶቻችን ጥቂት ማሳያዎችን ብቻ ለማንሳት ልሞክር፡

 

ፋሽስት በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ዳግመኛ ወረራው በበቂ ኹኔታ ተዘጋጅቶና የዐድዋውን ሽንፈት በሚገባ ለመበቀል የመርዝ ጋስ ጭስ ሣይቀር ታጥቆ ነበር የመጣው፡፡ በተጨማሪም ፋሽስት ሕዝቡን በዘር፣ በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል በአንድነቱ እንዳይቆምና እንዲሁም ስለ አንድነቱና ነጻነቱ የሚያስተምሩና በጽናት እንዲቆሙ የሚመክሩ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን የሃይማኖት ተቋማት ለማዳከምና ለማፍረስ ከተቻለም በሮም ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ለማድረግም ከፍተኛ የሆነ ዘመቻን ከፍቶ ነበር፡፡

 

ስለሆነም ፋሽስት በዚህ ዘመቻው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ዋንኛ ዒላማው አድርጓት ነበር፡፡ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል የግፍ ግድያ፣ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መዘረፍና መውደም እንዲሁም ደግሞ የበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የኾኑ ካህናት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና ምእመናን ጭፍጨፋም የዚሁ የኢጣሊያ ፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያራምድ የነበረው የከፋና እኩይ አቋሙ ማሣያዎች ናቸው፡፡

 

ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሊኒ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ንቀትና ጥላቻ ያሳየበትና ቢቻለውም ቤተ ክርስቲያኒቱን በፋሽስት ወይም በሮማ አስተዳደር ሥር እንድትሆን የነበረውን ሕልም የሚያጋልጠው እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 16/1935 በአስመራ ለሚገኘው ለጦር አዝማቹ ለማርሻል ባዶሊዮ ያስተላለፈው ጥብቅ ምሥጢራዊ ቴሌግራም እንዲህ ይነበባል፡-

 

በቁጥር 421M እና በቁጥር 426 ዳግም ያስተላለፍክልኝን የምስጢር ቴሌግራም ደርሶኝ በሚገባ አይቼዋለሁ፡፡ የአክሱም ገዳም ተቀደሰ ሥፍራ እንደመሆኑና ካለውም ጥንታዊ ታሪክና ቅርስ አኳያ በጦር መሣሪያም ሆነ በማናቸውም ዓይነት ወረራ እንዳይነካና የኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ መቆየት አለበት የሚለውን የውጭ መንግሥታት አሳብ ከምንም አልቆጥረውም ማለትህና ወደፊትም ይህን አሳብ የምቀበል ሰው አይደለሁኝም ማለትህ ትክክለኛ ነህ፤ ጥሩም አድርገኻል፡፡ አሁን የቀረህ ደግሞ የአክሱምን ገዳም ካህናትና መነኮሳት ብዛታቸውንና ማዕረጋቸውን ጠይቀህ ካወቅህ በኋላ በገናናዋ በሮምና በሞሶሎኒ ዙፋን ሥር እንተዳደራለን የሚሉ እንደሆነም በውል አጽፈህና እያንዳንዳቸውን አስፈርመህ ቃል የገቡበትን ሰነድ ወደ እኔ እንድትልክልኝ ነው፡፡     

 

የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለምስራቅ አፍሪካ ለቅኝ ግዛት ሚ/ሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልእክት ‹Ethiopia and Eritrea› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፡-

 

… The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favorable attitude. A telegram of March 1, 1937.

 

ትርጉም፡- ‘‘በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተወሰደው የግድያ ርምጃ ብዙዎችን እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ አድርጓል፤ ይህ ዓይነቱ ርምጃ ለኢጣሊያን እንዳይገዛ ሕዝቡን በሚያነሣሡና በዱር በገደል በአርበኝነት በተሰማሩት ፋኖዎችም ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል…፡፡’’

 

በተመሳሳይም የፋሽስት ጦር በደብረ ሊባኖስ ገዳም ባሉ መነኮሳት አባቶችና አገልጋዮች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ያስተላለፉት ትእዛዝ በተመለከተ በወቅቱ የፋሽስት አዛዦች የተለዋወጡት ደብዳቤ እንዲህ ይነበባል፡-

 

ለኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ ጠቅላይ ግዛት

የፕሮቶኮል መዝገብ ቁጥር 9325

አዲስ አበባ ግንቦት 24/1937 ዓ.ም.

 

ጥብቅ ምስጢር፡- ለጄኔራል ማሌቲ- ደብረ ብርሃን፣

ለክቡር ምክትል ገዥ ኤታማጆር- አዲስ አበባ፣

ለፖለቲካ ጉዳይ ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፣

ለጦር ፍርድ ቤት- አዲስ አበባ፣

ለካራቢኜራዎች ዋና አዛዥ- አዲስ አበባ፡፡

 

ቁጥር 26609- የደብረ ሊባኖስ ጉዳይ ሙሉ ሓላፊነቱ የእርስዎ እንደሆነ አረጋግጬያለሁ፡፡ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና ዲያቆናት ሁሉም አንድ ሣይቀር በጥይት እንድትፈጇቸው አዝዣለሁ፡፡ ትእዛዝህን በአስቸኳይ አስፈጽሜያለሁ በሚል ቃል እንድታረጋግጥልኝ ይሁን!

ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ፡፡

 

በወቅቱ በግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እጃቸው አለበት በሚል በገዳሙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ የተወሰደውን የግድያ እርምጃ ኢጣሊያዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience በሚለው መጽሐፋቸው፡-

 

‹‹… የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገ/ማርያም ወ/ጊዮርጊስ ጭምር እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1937 ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ በትዕዛዙ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጋዙ በኋላ የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት 26 ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ …፡፡›› በማለት ገልጸውታል፡፡

 

እንግዲህ እነዚህ በጥቂቱ ለማሳያነት ያነሳኋቸው ታሪካዊ ሰነዶች የሚነግሩን ሐቅ ቢኖር- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን- ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት ያላትን ጽኑ አቋም በደም ማኅተም የመሰከረች ጥንታዊት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት ተቋም መሆኗን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤ/ን እነዚህን የውጪ ሀገራት ወረራና ጥቃት በማወግዝ ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነጻነቱና ሰብአዊ ክብሩ ቀናኢ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች ተቋም መኾኗ የታሪክ ድርሳናት ይመስክሩልናል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና አንድነት የነበራት ልዩ ስፍራና የከፈለችው ይህ ዋጋ ከሀገራችን ምድር ተሻግሮም በመላው ጥቁር ሕዝብ ልብ ውስጥ የሰረጸ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክን በመላው ዓለም የነፃነት ተምሳሌት ሆነው ተደርገው እንዲሳሉ አድርጓል፡፡

 

ታሪክ እንደሚነግረን፤ እ.ኤ.አ በ1884 ዓ.ም. በተካሄደው የበርሊኑ ኮንፈረንስ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ በተቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን አኩሪ ነጻነታቸውን፣ ታሪካቸውንና ሥልጣኔያቸውን በመጠበቅና በማስከበር- በዐድዋ ላይ ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነፃነት ቀንዲል የለኮሰውን የኢጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ ለመላው አፍሪካና ጥቁር ሕዝብ ታላቅ ታሪክን በደማቸው ጽፈዋል፡፡ ይህን የታሪክ ሐቅ በተመለከተ አንዳንድ የውጪ የታሪክ መዛግብትን በጥቂቱ ለማየት እንሞክር እስቲ፤

ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ የተባለ የፈረንሳይ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. 1963 ዓ.ም ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል ጋዜጣ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፤ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቋታላችሁን?!›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ፡-

 

‘‘…ኢትዮጵያን ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉባት ሀገር መሆኗን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖት የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነቷን አስከብራ ቆይታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡

 

ከሁለት ሺ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሳም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ ቆይታለች…፡፡’’ በማለት ምስክርነቱን አስፍሯል፡፡

 

በሌላ በኩል አሜሪካዊው የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁር እና በኢትዮጵያ ዙሪያ ሰፊ ምርምር ያደረጉት ዶናልድ ሌቪን- በተለይ ደግሞ በብዙዎቻችን ኢትዮጵያውያን ዘንድ ‘‘Wax and Gold’’ በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው የሚታወቁት እኚህ ምሁር ኢትዮጵያውያን በዐድዋው ጦርነት ወቅት- የኢትዮጵያ ቤ/ክን ወንድ፣ ሴት፣ ቄስ፣ መነኩሴ ሳይባል ተባብረው ወራሪውን የኢጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበትን ጦርነት በጸሎት ተጋድሎና በማስተባበር ያደረገችው ተሳትፎ በአፍሪካና በመላው ጥቁር ዓለም ልዩ ስፍራና ክብር ሊያሰጣት እንዳቻለ The Battle of Adowa as Historic Event በሚለው ጥናታዊ ጹሑፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፤

 

For a number of colonized African countries, the Ethiopian victory at Adowa symbolized and signaled the possibility of the future emancipation. Hence the Black South African of the Ethiopian Church came to identify with the Christian kingdom in the Horn, a connection that leads South African leaders to write Menelik for help in caring for the Christian communities of Egypt and the Sudan.

በዚህ በዐድዋ ጦርነት በወራሪው የኢጣሊያ ጦር ላይ ኢትዮጵውያን የተጎናጸፉት ድል በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካ እንዲሁም በመላው አፍሪካ ትልቅ የሆነ ብሔራዊ ኩራትንና ጽናትን ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም አፍሪካውያን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ ለነጻነት ትግላቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን የነጻነት ትግላቸው ዓርማቸውና ሰንደቃቸው አድርገው ተቀበሏት፡፡ በተለይ ለደቡብ አፍሪካውያን የፀረ-አፓርታይድና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ቤተክርስቲያኒቱ በትልቁ ትነሳለች፡፡ ለአብነትም፤

አፍሪካዊው የነፃነት አርበኛ፣ የዓለም የሰላም ኖቤል አሸናፊ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ ስለ ዐድዋ ድል፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በኋላም በአገራቸው በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነፃይቱ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስምና ጥላ ስር የተቀጣጠሉ የፀረ-ቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ የነፃነት እንቅስቃሴዎችን በማስመልከት ከእስር በተፈቱ ማግሥት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ቤ/ን ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው፤

Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. …The Adwa victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.

(Nelson Mandela, Speech to the Free Ethiopian Church of South Africa፣ 1991)     

በተጨማሪም ይህን የታሪክ ሐቅ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2002 ዓ.ም. የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሆኑት ታቦ እምቤኪ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ትልቅ ኩራትና መነቃቃት የፈጠረች መሆኗን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ገልጸውት ነበር፤

‘’…The Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church…’’

 

የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕ/ት ታምቦ ኢምቤኪ- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የነጻነት የተጋድሎ ታሪክና የኢትዮጵያ ቤ/ን ታላቅ አስተዋጽዖን በተመለከተ ያደረጉት ንግግራቸውን የአማርኛ ትርጉም በጥቂቱ ቀንጭቤ ላስነብባችኹ፡-

 

ዘመናዊው የአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ የመነጨው ወደ ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ ነበር፣ የዚህ ንቅናቄ የቀድሞ መስራቾች የሀገራችን የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ አፍሪካውያ ልሂቃን ናቸው፤ የተነሱትም ከአብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ቤቶች ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን የቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ዘመናዊ የአፍሪካ ልሂቃን ከአውሮፓውያን ሚስዮኖች እራሳቸውን አላቀው በቤተክርስቲያናቱ ላይ ባለቤትነታቸውን ሲያውጁ፣ እንደመነሻ የተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፰ ላይ ይገኛል፤ ይህም፡

 

‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡›› የሚለው ነው፡፡ እንደ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቀድድም ሰለባ ሆና በኖረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መነሳሳትን ይሰጣቸው ነበር፤ እናም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተተነበየው ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ስትዘረጋ ቤተክርስቲያናችን በአፍሪካዊ ስነ ምግባር ትሞላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡

 

ይህች እውነተኛ የአፍሪካ ቤተክርስቲን ደግሞ አፍሪካያን በሙሉ ነፃነታቸው፣ ባህላቸው፣ ልዑላዊነታቸው፣ ማንነታቸውና ሰብአዊነታቸው እንዲከበር ላላቸው ህልም እንደማከማቻ ቦታ ሆና ታገለግላለች ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ እውነታ እና ታሪካዊ ሐቅ ላይ ተመስርተው ነበር እነዚህ የጠቀስናቸው ቤተ ክርስቲያናት እራሳቸውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብለው የሰየሙት፡፡ በአህጉራችን ላይ የመጀመሪያው ዘመናዊ የብሔራዊ ንቅናቄ የሆነው የደቡብ አፍሪካው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ANC) የተወለደውም ከነዚሁ ከሀገራችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው…፡፡’’                                     

 

(ይቀጥላል…)

 

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

 

(ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በምዕራብ እና በደቡብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት በዋና ጸሐፊነት፤ በታሪክ ጥናትና ቅርስ ጥበቃ ምርምር ሥራ ያገለገሉ ሲሆን በአሁን ሰዓትም በጥናትና ምርምር ሥራ ላይ እየሠሩ ይገኛሉ)፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop