ከሁለት መቶ አመታት በፊት የነበሩ፣ የአሜሪካን ፕሬዘዳንት፣ ቶማስ ጀፈርሰን፣ ከተናገሯቸው በርካታ የሚጠቀሱ ንግግሮች መካከል አንዱ፣ ስለ መንግስት ሃላፊነት የተናገሩት ንግግር ነው። ” የአንድ መንግስት ሃላፊነት የሚመራዉን አገርና ህዝብ ደህንነትና ደስታ ማስጠበቅ ነው። መንግስት የሚኖረው ለዜጎች ጥቅም እንጂ ለገዢዎች ጥቅም አይደለም” ነበር ያሉት።
“ኢትዮጵያ መንግስት አላት” ነው የሚባለው። “የመንግስት ሃላፊዎች ምን ያህል ዋና ሃላፊነቶቻቸውን እየተወጡ ነው ?” ለሚለው ጥያቄ ግን፣ እየሰሩ ያሉትን በማየት መመዘኑ አስቸጋሪ አይደለም የሚሆነው።
የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስቱ ቁንጮ የሆኑት፣ ዶር አብይ አህመድ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው። በትረ ስልጣን ከጨበጡ አራት አመት ሆኗቸዋል። በርሳቸው ዘመን፣ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊያና ማህበረሰባዊ ቀውሶች ውስጥ የተዘፈቁበት፣ በሕይወት የመኖር ዋስታ ያጡበትና ደህነንታቸው ትልቅ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ዘመን ነው የሆነው። ምንም እንኳን “ለውጥ” የተባለው መምጣቱ ትልቅ ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ጭሮ የነበረ ቢሆንም፣ በሕወሃት/ኢሕአዴግ ጊዜ ከነበረው ሁኔታዎች የከፋ እየሆኑ ነው። ከዳጡ ወደ ማጡ፣ ከእሳት ወደ ረመጥ እየተሸጋገርን ነው።
በትግራይ፣ በቤኔሻንጉል፣ በሰሜን ወሎ፣ በራያ፣ በጠለምት፣ በስሜን ጎንደር፣ በዋገመራ፣ በአፋር፣ በወለጋ፣ በጉጂ፣ በምእራብና ሰሜን ሸዋ ጦርነቶች ወይም አለመረጋጋቶች አሉ። በሶማሌ ክልልና በደቡብ ባሌና ቦረና ዞኖች ድርቅ ገብቷል። በዜጎች ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው። ከተሞች ወድመዋል። በሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። የኑሮ ውድነት ከመክበድ አልፎ ወገብ እየሰበረ፣ ብዙዎችን መሬት ላይ እየጣለ ነው። በኢትዮጵያዉያን መካከል የዘር መካረሩ እጅግ በጣም አስፈሪ በሆነ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት፣ በፈተናዎች ስርቆትና፣ በአራሚዎች በርካታ ስህተቶች ምክንያት ችግሮች ተፈጥረዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ተስፋ የሚያጨለም፣ ትውልድ የሚገድል ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህም ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ውዝግቦች እየተነሱ ነው። ንጹሃን ዜጎች በተለይም በአዲስ አበባ በግፍና በጅምላ እየታሰሩ ነው። ባለስልጣናት እንደፈለጉ ህዝብንና አገርን እየሰደቡ፣ እኛን ለምን ተቃወማችሁ፣ “እኛ ተሰደብን” በሚል ከሕግ በላይ ሆነው ዜጎችን እያሰቃዩ ነው። በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያዉያን በስጋትና በፍርሃት ውስጥ እየኖሩ ነው። በአገራቸውም በቅያቸው ሁሉ ነገር ጨለማ እየሆነባቸው።
እነዚህን መሰረታዊ የሕዝብ ችግር የመፍታት፣ የመቅረፍና፣ ለሕዝብ ተስፋ የመስጠት ሃላፊነት የመንግስት ነበር። ግን የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት እንኳን ችግሮችን ሊፈታ የችግሮቹ አካል እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው። መንግስት ሕዝብ እያለቀ ጨዋታ ነው የያዘው።
ብዙ በዜጎች ሕይወትና ደህንነት ዙሪያ የተገናኙ አንገብጋቢ ጉዳዮች እያሉ፣ የብልጽግና መንግስት አጀንዳዎቹ አድርጎ እየተንቀሳቀሰባቸው ያሉ ጉዳዮችን ስንመለከት “አራት ኪሎ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ? ወይስ የቡርኪና ፋሶ ? “፣ እንድንል የሚገፋፋ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድ፣ በዚህ ሳምንት፣ አስፈላጊና አንገብጋቢ ናቸው ብለው፣ ሄደው ከጎበኟቸው ቦታዎች መካከል፣ የጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት፣ በአዳማ ያለ የቆርቆሮ ፋብሪካ፣ ለጤና ባለሞያዎች የተደረገ ሽልማትና ድግስ፣ የገበታ ለአገር በሚል በጎርጎራ ያለ ፓርክ ይገኙበታል። በሰቆጣ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በዱብቲ፣ በነቀምቴ፣ በደብረ ብርሃን፣ በቆቦ ፣ በምንጃር … ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ካምፖችን፣ አንዳቸው ጋር ሄደው፣ ለመግብኘት፣ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አልሞከሩም። የፈረንሳይዋ ንግስት ማሪ አንቷኔት ፣ ህዝቡ ተርቦ ዳቦ ብሎ ሲጠይቅ፣ “ኬክ ለምን አትሰጧቸውም” እንዳለችው፣ “ዘይት ተወደደ፣ ኑሮ ተወደደ” ሲባሉ፣ ቅጠል አሳይተው፣ “ዘይት ሳትጨምሩ፣ ጨው ብቻ አድርጋችሁ ለምን አትበሉም ?” የሚል የስላቅና የንቀት ምላሽ ነበር የሰጡት።
የኢትዮጵያ ችግር የተፈጥሮ ሃብት ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር በሕዝብና በሕዝብ መካከል ያለ ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር ለሕዝብና ለአገር የሚያሰብ መሪ አለመኖሩ ነው።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው የዶር አብይ አህመድ መንግስት ለገዢዎች ጥቅም የቆመ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ አይደለም። ቅድመ ሁኔታዎቹ የግለሰቦችን ተክለ ሰውነት መገንባት፣ ድግስና ሽብረቃ ማብዛት እንጂ፣ ታች ወርዶ ኢትዮጵያዊያንን ቀና ማድረግ ላይ አይደለም።
ለሕዝብ ያልቆመ መንግስት እስከቀጠለ ድረስ የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎቶች አይከበሩም። የሕዝብ መከራና ስቃይ እየተባዛና እየጨመረ ይሄዳል ። አገርም ትፈርሳለች።
“በትንሹ ያልታመነ በትልቁ አይሾምም” ይላል ታላቁ መጽሃፍ። ላለፉት አራት አመት አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻግር ያልቻለ ወደፊትም ሊታመን አይችልም። የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት እንዲለወጥ ካልተደረገ ፣ በበፊቱ አሰራር፣ በበፊት ስርዓት፣ በበፊት የጎሳ ሕግ መግስትና የጎሳ አወቃቀር ፣ በበፊቱ ሰዎች አገር እየተመራች፣ የባሰ እንጂ የተሻለ ነገር አይመጣም።
ለውጥ የተባለው ሙሉ እንደተቀለበሰና የባሰ አገዛዝ እንደመጣ በመረዳት፣ ከአራት አመታት በፊት ሕወሃት/ኢሕአዴግን ለማስወገድ ይደረግ ከነበረ ትግል በተጠናከረ ሁኔታ ኦህዴድ/ብልጽግና ለመታገል ፣ ዜጎች ዘር፣ ኃይማኖት ሳይለያቸው መረባረብ አለባቸው የሚል እምነት አለን።
አዎን ዜጎች ምርጫ አለን። ዝምታን መርጠን ጥቂቶች አገርን ሲያፈርሱና ህዝቡን ለመከራ ሲዳርጉ ማየት፣ ወይንም የድርሻችንን በመወጣት አገራችን፣ ሕዝባችንን፣ ከተሞቻችንን፣ ቅያችን፣ ቤተሰቦቻችን ማዳን፣ ለልጆቻችንም ደግሞ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ ማድረግ። ምርጫው የኛው ነው።