ናትናኤል ካብትይመር (ኦስሎ ኖርዌይ)
“ . . . . . . .የኢትዮጲያ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የህዝብንና የመንግስትን ንብረት ለግል ጥቅማቸው በማዋል ክስ የመሰረተባቸውን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን . . . . . . “ የኢቲቪ ዜና
““. . . . . ጉድ ፈላ በቃ ቀጥሎ ሴትዮዋ ነች . . . . . “ የዋህ ኢትዮጲያውያን
“. . . . . . . እባካችሁ በጥቂት ሺህ ብሮች የወር ደሞዝ የህዝብ አገልጋይ ነን እያላችሁ የሰባት ሚሊዮን ብር መኪና አትንዱ . . . . .”“ አፈጉባኤው
“. . . . . . .የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስናን በማጋለጥ ጋር በተያያዘ በታሸገ ውሃ ተመርዘው ነው የሞቱት መባሉን ባናረጋግጥም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በኦሮሚያ ክልል መንግስታዊ ስብሰባዎች የታሸገ ውሃ መቅረብ መቆሙን አውቀናል . . . . . . “ ለስርዓቱ እጅግ የቀረቡ የመንግስት ጋዜጠኞች
ባለፈው ሰሞን ጥቂት የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና ሰበብ ተብሎ ዘብጥያ ሲወርዱ የታሳሪዎች ቁጥር ከወትሮው ለየት በማለቱ ፀረ ሙስና ስራውን ጀመረ ብለው ተስፋ የጣሉ ኢትዮጲያውያን ጥቂት አልነበሩም። እንደው የህዝባችን የዋህነት ነው እንጂ ፀረ ሙስና ከተመሰረተ ጀምሮ አንድም ቀን እንደስሙ ስራውን ሰርቶ እንደማያውቅ ፣ ጥቅሙም ሌላ እንደሆን የታወቀ ነው። እንጂማ ገና ያኔ እነ አቶ ታምራት ላይኔ ፣ እነ አቶ አባተ ኪሾ የመሳሰሉት በሙስና ሰበብ ወደ እስር ሲወርዱ በህዝብ ገንዘብ ጠግበው የደለቡ የመንግስት ባለስልጣናትና አጋፋሪዎቻቸው የውስኪ ብርጭቆአችውን እያጋጩ ሲሳለቁ ማንም የነካቸው አልነበረም። ምክንያቱም ነገሩ ሌላ ነው። የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ለመንግስት የሚሰጠው ጥቅም ሌላ ነው።
ሁሌ ሳስበው የሚያስገርመኝ እንደ ህወሃት መንግስት የተለያዩ አለማቀፋዊ መሰረት ያላቸውን ህግጋትና ደንቦች ለራሱ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ እየሸነሸነ የሚያውል መንግስት ያለ አይመስለኝም።
የኢትዮጲያ ፀረ ሙስና ኮሚሽንን የህወሃት መንግስት ሲያያቸው ያላማሩትን ፣ የውስጥ ጉዱን የሚያወጡበት የመሰለውን የገዛ ባለስልጣናትና ሹመኞቹን ማስወገጃ አርጎ ይጠቀመዋል ፥
የፀረ ሽብር ህግን ህዝብ የወደዳቸውን ፣ አካሄዳቸው ያሰጋውን ፣ እውነትን ለህዝብ የሚያጋልጡትን ጋዜጠኞችንና አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ አመንጪ አካላትን ማስወገጃ አርጎ ይጠቀመዋል ፥
መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥን (Business Process Reengineering) የህወሃት ካድሬዎችንና በሲቪል ሰርቪስ በኢሃዴጋዊ አገዛዝ ያጠመቃቸውን ጆሮ ጠቢዎች በየመንግስት መስሪያ ቤቶች ለመሰግሰግ ይጠቀመዋል ፥
አገር አቀፍ የመረጃ ደህንነት ጥበቃ (National Information Network Security) ሲስተሙን የተለያዩ የዜና አውታሮችንና ድረ ገፆችን በሃገር ውስጥ እንዳይታዩ ለመዝጋትና አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ አመንጪ አካላትን መረጃ ለመበርበሪያ ይጠቀመዋል ፥
አንዳቸውም ለተፈጠሩበት ፍልስፍና በሃገራችን በአግባቡ ስራ ላይ ሲውሉ አይታዩም : ሌሎችም ብዙ አሉ።
“ኧረ ይሄ አሰራር መጥፎ ነው” ሲባል ዋናውን ጥያቄ ሆን ብሎ በማድበስበስ “ህጉን የገለበጥነው በቀጥታ ካደጉት ሃገራት ነው” ይባልና ያልተጠየቀው ይመለሳል።
“የለም የለም ህጉን አተረጓጎማችሁ ልክ አይደለም” የሚል ጫን ያለ ጠያቂ ሲመጣባቸው “መጠነኛ የአፈፃፀም ችግር ስላለ ነው በቅርቡ እንቀርፋለን” ይላሉ ከዛሬ ስንት አመት ጀምሮ።
ወደ ዋናው ሃሳቤ የሙስና ጉዳይ ልመለስና በአንድ ወቅት ከአንድ ጋናዊ ጓደኛዬ ጋር ስለ አህጉራችን አፍሪካ መሪዎችና ባለስልጣናት መረን የወጣ ሙስናና ገንዘብ መውደድ ባህሪ ስንወያይ በማልረሳው መልኩ እንዲህ አለኝ ፥
“የሚገርምህ በምሳሌ ባስረዳህ የአፍሪካ ሃገራት ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር በሃገራቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲወያዩ ‘. . የሚያስፈልገን ከሃምሳ ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው ስለዚህ እነዚህን ሃገራት ብድርና እርዳታ እንጠይቃለን በተጨማሪም ከህዝቡ መዋጮ እንጠይቃለን . .’ ብለው ስብሰባውን ይቋጫሉ ነገር ግን ሁለቱም እያንዳንዳቸው ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ በአውሮፓና አሜሪካ በሚገኙ ባንኮች በድብቅ እንዳስቀመጡ ይተዋወቃሉ። መሪዎቻችን ከግለኝነትና ከስግብግብነት ካልወጡና ከነዚህም ችግሮች የፀዳ አመራር ካላገኘን ገና የአፍሪካችን መከራ ብዙ ነው” አለኝ።
እኔም የሃገሬ መንግስት ከቀበሌ ጀምሮ የሾማቸው ሹመኞችና ባለስልጣናት ፣ የሚነዷቸው መኪኖች ፣ የሚኖሩበት ውብ ቪላዎች ፣ ታማኝ ምስኪን የመንግስት ሰራተኞች ፣ እንደ ቁመናው ያላማረበት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ህንፃ ፣ የኢቲቪ ሙስና ነክ ዜና በቅፅበት በአምሮዬ ውልብ ውልብ እያሉ አለፉ።
በኢትዮጲያ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ አነስተኛ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። በተያያዘም የመንግስት ባለስልጣናትና ሹመኞችም የመንግስት ሰራተኞች መሆናቸውንም እናውቃለን። ይህ ማለት ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናትና ሹመኞች ደሞዛቸው ከመንግስት ሰራተኞች እኩል በመንግስት የደሞዝ እርከን መሰረት ነው ማለት ነው። ሌላው የመንግስት ሰራተኛ በኑሮ ውድነት ናላው ሲዞር ባለስልጣናቱ ግን ደሞዛቸው ስንት እንደሆነ እንኳን አያውቁትም ምክንያቱም የገንዘቡ መጠን የሚነዱትን የሚሊዮኖች ብር መኪና የቀናት ነዳጅ እንኳን አይሸፍንም ፥ ታዲያ ማወቁ ምን ያረግላቸዋል።
ደሞዛቸው ትዝ የሚላቸውና ብዙ ግዜ በርካቶቻችንን የሚያስገርመንና በቁጭት ፈገግ የሚያስብለን የገቢ ማሰባሰቢያ ወይም ቴሌቶን ሲዘጋጅ “ክቡር ሚኒስትር እከሌ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ሰጥተዋል ሞቅ ያለ ጭብጨባ” ሲባል ወይም የሚንስትሮቹ ሚስቶች ምን ያህል ቆጥበው ፣ ለፓርቲያቸው አዋጥተው ፣ ተቸግረው ፣ ተቸጋግረው ፣ ልጆቻቸውን እንደሚያስተምሩ ሲያወሩ ነው።
ኧረ ይሄ ነገር ልክ አይደለም ሲባል ፥ “ሃገር ለማሸበር” ወይም “የጥላቻ ፖለቲካ” ይባላል። ሲጀመር ውል ያለው የፖለቲካ ስርዓት የህወሃት መንግስት የለውም ሲቀጥል . . . . . . . .ግድ የለው አሁን ከዋናው ርዕሴ አልውጣ።
በርካታ የመንግስት ሹመኞችና ባለስልጣናት ቢሮ እንደው እግር ጥሏችሁ ከሄዳችሁና ቀና ብላችሁ አስተውላችሁ ከሆነ በግርግዳቸው ላይ የለጠፏት ወረቀት “ታማኝነት ፣ ግልፅነት ፣ የህዝብ አገልጋይነት ፣ ቅንነት ፣ የመሳሰሉት ውብ ቃላቶች” በተርታ ተለጥፈው ይታያሉ ነገር ግን ዝቅ ብላችሁ የሹመኛውን ወይም የባለስልጣኑን ፊት ስትመለከቱት “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚባለው አበው ለምግብ ይሁን ለህዝብ ገንዘብ በውል ሳይለዩ ያወረሱን ብሂል ሁለመናውን ወርሶት ታዩታላችሁ። ሹመኛና ባለስልጣን እየተፈራረቀ “ምነው በኔ ተጀመረ እንዴ” እየተባባለ ያችን ምስኪን ሃገር ይግጣል።
ሙስናና ንቅዘት በሃገር ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ዲሞክራሲያዊ እድገት ላይ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ እጅግ ብዙ ነው። ስልጣንን መከታ በማድረግ የሚገኝ ገቢ መዘዝ የሃገርን ሃብት በማውደም ብቻ አያበቃም። የመንግስት ስልጣንና ሹመት ሃገርንና ህዝብን ማገልገል መሆኑ ይቀርና የቤተሰብ እንዲሁም የዘመድ አዝማድ የገቢ ምንጭና ህልውና ወደመሆን ይሸጋገራል። በዚህም ሳቢያ ደግሞ በተገቢው መልኩ የአገልግሎት ግዜ ሲያበቃ በሂደት የመተካካት ፣ ለተተኪው ስልጣንን ማሳለፍ ወይም መልቀቅ የሚለው መሰረታዊ የዲሞክራሲና የሃገር እድገት መርህ ይጣስና ስልጣንና ሹመት የቤተሰብና የዘመድ አዝማድ የኑሮ ምሰሶ ሆኖ ስለሃገር እድገት ማሰብ በራስ ወዳድነትና በግለኛ የማይጠረቃ ፍላጎት ይተካና ስልጣን ወይም ሹመት ላይ እስከወዲያኛው ሙጭጭ ማለትን ያመጣል።
በቅርቡ የተካሄደው የኢህአዴግ ስብሰባ “ . . የፓርቲያችን ዋናው ችግር ሙስናና አድር ባይነት ነው ስለዚህ . . . “
የሚቀጥለው የኢህአዴግ ስብሰባ “ . . . . ባለፈው ያልናችሁ ዋናዎቹ ችግሮቻችን ሙስናና አድርባይነትን የምንዋጋበትን እቅድ በአፋጣኝ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ እናወጣለን . . . . .”
እኔ በዚህች ላብቃ . . . . . መስናና ዘረፋው ግን አምሮበት እንደቀጠለ ነው።