ከፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)
ትዝብት አንድ፣
በባህርዳሩ ሰልፍ ያሰደደመኝ ነገር ቢኖር የወጣቱ ቁጥር ነው፤ “ወጣቱ በአደገኛ ሱሶች በመጠመዱ ለመብቱ መቼውንም አይነሳም” እየተባለ ሲሟረትበት የነበረው ከሟርትነት ያለፈ አለመሆኑን አስመስክሯል ። ወጣት ካለ አገር አያረጅም።
ትዝብት ሁለት፣
በፍጥነት እያደገች የምትገኘዋ ባህርዳር ለብአዴን የአመራር ስኬት ማሳያ ሆኗ በተደጋጋሚ ትቀርባለች። ሰልፉ ባህርዳር ላይ የተካሄደ መሆኑ ለብአዴን ትልቅ ሞት ነው ምክንያቱም “ህንጻ የገነባንለት፣ መንገዱን ያሳመርንለት፣ ሆቴል በሆቴል ያደረግነው የባህርዳር ህዝብ እንዲህ ካዋረደን፣ የደብረታቦር፣ የሞጣ፣ የደብረ-ብርሃን፣ የደሴ፣ የወልድያ፣ የጋይንት፣ የወረታ፣ የመራዊ፣ የፍኖተሰላም፣ የማርቆስ፣ የደጀን፣ የቡሬ፣ የቴሊሊ፣ የደንበጫ፣ የእንፍራንዝ፣ የዳባት፣ የአጣየ ወዘተ ህዝብ ምን ይለን ይሆን?” ብሎ የብአዴን አመራር እንዲደናገጥና ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርገው ነው።
ትዝብት ሶስት፣
ባህርዳር ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የክልሉ ነዋሪዎች ተደባልቀው የሚኖሩባት፣ የኢትዮጵያ አዲስ አበባ ማለት ናት። ስለዚህም ተቃውሞው የባህርዳርን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የክልሉን ህዝብ በመላ የሚወክል ነው።
ትዝብት አራት፣
ባህርዳር የባለስልጣኖች መኖሪያና መዝናኛ ከተማ ናት። 24 ሰዓታት ልዩ ጥበቃ ይደረግላታል። የባህርዳር ህዝብ ማስፈራሪያውና የደህንነት ክትትሉ ሳያስፈራው፣ ሆ ብሎ አደባባይ መውጣቱ ለለውጥ ቆርጦ መነሳቱን የሚያሳይ ነው።
ትዝብት አምስት፣
ሰልፉን ከጀርባ ሆነው በማስተባበር የብአዴን አመራሮችም ተሳትፈዋል፤ ለነገሩ የአለምነውን ንግግር ቀርጸው የሰጡንም እነዚሁ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፤ በክልሉ ህዝብና በውስጥ ሆነው ብአዴንን ለማዳከም በሚሰሩት አመራሮች መካከል ያለው መናበብ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን ይህ ሰለፍ አሳይቷል።
ትዝብት አምስት፣
መኢአድና አንድነት ሰልፉን ባህርዳር ላይ ለማድረግ መወሰናቸው የሚደነቅ ነው። ብአዴንን ዋጋ በማስከፈል ጥሩ ትርፍ አግኝተዋል።