February 2, 2014
34 mins read

ድርቅ ለመታው ፖለቲካ ማዳበሪያ፦

መመካከር፤ መተቻቸት አእምራችንን ያሰፋዋል የሚል እምነት ስላለኝ የተሰማኝን ለማካፈል ስለሆነ ጽህፏ ለምን እንደ ምትበጅ ሰከን ብላችሁ እንድታነቧት በትህትና አሳስባለሁ፟፦

ኢትዮጵያን የሚጠብቋት ልጆቿ መሆኑ አይታበልም። ሲጠብቋት ግን በዘር፤ በጐሳ በቋንቋ ሳይለያዩ በጋራ መሆን አለበት። በዚህ ሁኔታ አገራችን ታፍራ ተከብራ ኑራለች። አንድነቷን ጠብቃ በቆየች አገራችን ላይ የተደቀነው አደጋ እጅግ ከባድ ነው። የአገራችን ችግር ውስብስብ ሆኖ የጐሳ ፖለቲካን ብሎም ዘረኝነትን መዋጋት ሲቻል ባለፈ ታሪክ ዙሪያ የሚደረገው እሰጥ አገባ ችግሩን እያሰፋው ከመሄድ ውጭ መፍትሄ አይገኘለትም።

በተለይ በአጼ ምኒሊክ ዙሪያ የሚናፈሰው “ወሬ” ልበለው በጣም ትውልዱን እንደሚጐዳ እርግጠኛ ነኝ። ያሳዝናል ቀዳማዊ ኃይለስላሴን፤ ደርግን፤ ወያኔን መውቀስ፤ ሁሌ መውቀስ መቼነው ዋናውን ጠላት ለይተን የምናውቅ? ለእኔ ዋናው ጠላት ዘረኛው ወያኔ/ ኢሕአዴ ነው። መጥኒ ለዚህና ለመጭው ትውልድ?። ውሀ እያሳሳቀ ይወስዳል እንዲሉ የዘር ፖለቲካም እያባበለ ሰዎች ሳይወዱ ከማን አንሸ እልሕ እየተናነቃቸው እንዳንጠፋፋ መስከን ግድ ይላል።

ኢትዮጵያ እንደ አገር ልትፈጠር የቻለችው በአንድ በሄር ወይም ብሄረሰብ ተጋድሎ ሳይሆን አማራው፤ ጉራጌው ትግሬው፤ ሽናሽኑ፤ አገው፤ እስላም ክርስቲያኑ ውዘተ በከፈሉት መራር የሕይወት ዋጋ ነው። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ለመሆን በቅታለች። ይሁን እንጂ ከአስተዳደር ድህነት ነፃ የሆነበችበት አጋጣሚ አልታየም። ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለበት ችግር ተላቅቆ የመብቱ ባለቤት ሆኖ በፈለገበት ቦታ ተዛውሮ የመስራት፤ መንግስትን ሲፈልግ የመሾምና የመሻር የማይገሰስ መብቱ እውን እንዲሆን በስውርና በግልጽ ገዥዎችን ከመታገል የተቆጠበበት ጊዜ የለም። እንዲሁ ከተማሪዎች ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ድረስ የተለያዩ የትግል ስልቶች ተካሂደዋል።

ሕዝባቸውን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት የተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝባቸውን ለማደራጀትና ለማታገል እንዲሁም የተሟላ ዜና ለሕዝባቸው ለማዳረስ በፈቃደኝነት የተዋቀሩ ሚድያዎች እንደነበሩና አሁንም እንዳሉ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የዘር ፖለቲካውን በጋራ መታገል ሲቻል ዛሬ ባለፈ ታሪክ ዙሪያ አጼ ምኒሊክ፤ አጼ ቴዎድሮስ፤ አጼ ዮሐንስ ወዘተ ይህን አደረጉ፤ በሚል አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ባልተገባ ነበር። እነዚህ አለኝታዎቻችን እኮ በዘር፤ በጐሳ በቋንቋ፤ በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ ኢትዮጵያን አስረክበውናል። በነበራቸው አቅም ሰርተው አልፈዋል። እናም ከሰሩት ሥራ ውስጥ ጠቃሚውን በመውሰድ ጐጅ የሚባለውን ማሻሻል ሲቻል የተጀመረው ትግል ፈር እንዲስት ማድረግ ለማን እንደሚበጅ አንባቢ ፍርዱን ይሰጥ ከማለት ውጭ ሌላ የምለው አይኖረኝም።

ከላይ ይህን ካልኩ ዘንዳ ስው ስለመሆናችን አንዳንድ ነገሮችን ልጠቃቅስ። ሰው መጀመሪያ ሲወለድ ይዞት የሚወለድ የተለየ ዘር ሳይኖረው ሰው የሚለውን ሥም ይዞ ወዚህች ምድር እንደሚመጣ ታሪክ ይነግራል። ሰው ሲወለድ ሰውነቱንና ሕይወቱን ይዞ ብቅ ሲል አማራ፤ ትግሬ ጉራጌ ሽናሽን፤ ወላይታ፤ ኦሮሞ ወዘት ነኝ ብሎ አይደለም። ሰው ከምንም ዓይነት ዘር ወይም ጨቋኝ ቤተሰብ ልውለድ የማለት ምርጫ የለውም። ሰው ጾታውን ቤተሰቡን፤ ቆዳውን፤ ቀለሙን ወይም ዜግነቱን መርጦ አይወለድም። ነገር ግን ይህ እውነተኛ የሰው ልጅ ታሪክ ሆኖ እኛለ አንዳንድ እውቀት አለን የሚሉ ሰዎች ዘርን ለይቶ ያልተወለደን ህብረተሰብ በመለያየት ለዝና፤ ለሥልጣን ሲባል ሰዎች የዘር ሐረግ እየቆጠሩ በጥላቻ እንዲተያዩ በመደረጉ በሰዎች ዘንድ መከባበርና አንድነት ጠፋ። ክፋትና መጨካከን ተስፋፋ። ይህን እሆናለሁ ብለን ባንወለድም ቅሉ ከተወለድና ካደግን እንድናስብበት ከእግዜአብሄር በተሰጠን አእምሮ ከፉና ደጉን የመለየት ኃላፊነት የራሳችን ሆኖ እያለ ለምን እንደማንጠቀምበት ግራ ያጋባል።

በአገራችን ላይ እየደረ ያለው ችግር ለማንም ትውልደ ኢዮጵያዊ ግልጽ የሆነ ይመስለኛል። ችግሩ እንዲወገድ ሁሉም ፓርቲዎች ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር እንደሚታገሉ ፕሮግራማቸውን በወረቀት ላይ አስቀምጠው ሲነግሩን እንሰማለን። ይሁን እንጂ አብዛኞች ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሚጠቅም ሁኔታ እየታገሉ አይደለም። ምክኒያቱም በደጋፊነትም ሆነ ውጭ ሆኖ እንደሚስተዋለው ከሆነ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጐን በመተው ሳይሆን ከዚህ በፊት የለሉ ቁርሾዎችን እያፈላለጉ እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ ይታያሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለአንዲት የቆየች ኢትዮጵያ የሚጠቅም ሥራ መስራት ሲጠበቅባቸው ኢትዮጵያን በመበታተን ሥራ በመጠመዳቸው አሳዛኝ መሆኑ አልቀረም። ጠቅለል ባለ መልኩ ሕዝቡን የመብቱ ተጠቃሚ ማድረግ ቀርቶ ራሳቸውን ከድሃ አስተሳሰብ ነፃ አላወጡም ቢባል ቢያንስ ነው።

አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ትግል ሲል መጀመሪያ ብዙ መመዘኛዎችን ሊያሟላ ግድ ይለዋል። ይህ ሲባል ቅድሚያ የራሱን ማንነትና ይዞት የተነሳውን ፕሮግራም አበጥሮ ሊያውቅ ይገባዋል። ወደፊት ትግሉን ለመግፋት ደካማና ጠንካራ ጐኖቹን ማለት በትግሉ ጉዞ ላይ የሚሳካና የማይሳካለት መሆኑን አስቀድሞ ማወቅ ይጠበቅበታል። የፖለቲካ ፕሮግራሙ ከሕዝብ ጋር መሄድና አለመሄዱን፤ የደጋፊዎቹን ወይም የአባላቱን ማንነት ማወቅ ያስፈልገዋል።

ከላይ በመጠኑ የተጠቀሱትን ካገናዘበ በኋላ የፖለቲካ ትግሉን የትርፍ ሰዓት ሳያደርግ፤ እውቀትና ጉልበቱን መርምሮ በምን መልክ መጠቀም እንደሚችል ጥርት ባለ ሁኔታ ሊያውቀው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ድርጅት ከሌሎች ድርጅቶች ተለይቶ ለስኬት እንደማይበቃ ተረድቶ ተባብሮ ለመታገል ዝግጁ መሆኑን ማመን አለበት። ከዚህ ሳንወጣ ጥንቃቄ ሊደረግበት ያውም እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው መሪው ትግል ሲል ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲል መሥዋእትነት ሊከፍል እንደሚችል እርግጠና ስለመሆኑ ከሕሊናው ጋር ተሟግቶ ውሳኔ ላይ መድረስ አለበት። ነገር ግን በአቋራጭ ለሥልጣና ለዝና ሲል ትግል መጀመር ያለበት አይመስለኝም።( ይህ የራሴ እምነት ነው) ምክንያቱም የዝና ትግል ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ብሎም ለራሱ የሚሰጠው ጥቅም ስለማይኖር ፈጥኖ ይከስማል። ተመልሸ ትግል ልቀጥል ቢልም አይታመንም። ስለዚህ ለስኬቱም ሆነ ለውድቀቱ ቁልፉ መነሻው ይሆናል ማለት ነው።

የፖለቲካ ደርጅት መሪ ለዝና ሲል ትግል መጀመር የለበትም ስል ያለምክኒያት አይደለም። ከዚህ በፊት የታዩት የትግል ዓይነቶች መጀመሪያ የአንበሳነት ባሕሪ አሳይተው ፈጥነው የከሰሙትን ማቢ ማድረግ ይቻላል። ይህ ማለት መጀመሪያ ሲነሱ መድረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ስላልነበራቸው ነው ማለት ይቻላል ስለዚህ ከአላማ የለሽ የትግል ሩጫ ለመዳን መጀመሪያ የመሪውን ውሳኔ ይጠይቃል። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት በጣም ቀላል ነው። እንዲሁ በትግል ሥም ሌሎች እንዲከተሏቸው /አባል እንዲሆኑላቸው/ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ማድረግም ቀላል ነው። አንዳንድ ሰዎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ምንነት ማለት ፕሮጋማቸውን በውል ሳያገናዝቡ ከአገር ፍቅር አንፃር ይሁን በዋህነት አባል ይሆናሉ። የህቡዕ ድርጅት እንደሆነ ይነገራቸውል፤ የሚታዘዙትን ወርሃዊ መዋጮ መክፈል ይጀምራሉ። ይሁን እንጅ የድርጅቱ አካሄድ ያላማራቸው ወጣ፤ ገባ ማለታቸውን እየተመለከትን ነው። በመሆኑም ራሱን ለእውነት ያላነሳሳ ህቡዕ ድርጅት ብዙ ሳይቆይ ባለበት መርገጥ ይጀምራል። የዚህ ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት የሚያመላክተው ነገር ቢኖር ድርጅት ፈጣሪዎች ከራሳቸው ጥቅም አንፃር መሆኑን ነው። የዚህ ዓይነት አደረጃጀት መጨረሻው ብዙ ሳይጓዝ ተሸናፊ ስለሚሆኑ በሕዝብና በደጋፊዎች ላይ እምነትን ያሳጣሉ።

የፖለለቲካ ድርጅት መሪዎች እንዲተባበሩ ሕዝቡ ከ20 ዓመታት በላይ ደጋግሞ ቢጠይቃቸውም የሕዝባቸውን ጀሮ ለማዳመጥ ዝግጁ ሆነው አልተገኙም። ሕዝቡም የተባበሩ ጥያቄው ተቃባይነት ባለማግኘቱ ዛሬ ዛሬ ተባበሩ የሚለውን ቀይሮ “ተሰባበሩ፤ ወይም አርፋችሁ” ተቀመጡ፤ የትግሉ አቅጣጫ አልገባችሁም እስከ ማለት የደረሰ ስለመሆኑ ከአንዳንድ ምንጮች መረዳት ይቻላል። መቼም ይህን እውነት ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው መገንዘብ ያዳግተዋል ለማለት አይቻልም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በመረጠው መንግሥት የመተዳደር ፍላጐቱን በ1997 ምርጫ ወቅት አሳይቶ ነበር፡፤ይሁን እንጂ የፈለገውን ግን ሳያገኝ ቀርቷል። ለዚህ በዋናነት የተጠያቂነት ድርሻ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች መሆናቸው አይካድም። ለዚህ ብዙ ማስረጃ ሳያስፈልግ በቅንጅትና በኅብረት ጊዜ የተደረገውን ተመልሶ ማስታወስ በቂ ነው። ሕዝቡ በተቃዋሚዎች ላይ ያለው እምነት እየተሟጠጠ ተስፋ የመቁረጥ አጋጣሚዎች ሰፍተዋል። ቀጣዩ ምርጫ 2007 እየተቃረበ ሲመጣ ኢሕአዴግ አስቀድሞ እየተዘጋጀ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ባንፃሩ ተቃዋሚዎች ለሚቀጥለው ምርጫ ምን ያሕል ተዘጋጅተዋል የሚለውን በውል ለመረዳት የሚያዳግት ነው። ምክንያቱም ተቃዋሚዎች ካለፈ ስህተታቸው ተምረው ምን ያልህ ሕዝቡን አደራጅተዋል? እንዳለፈው ችግር ቢፈጠር ለቆሙለት አላማ መስዋዕት ለመክፈል ቁርጠንነታቸው ምን ያህል ነው? ወይስ እንዳለፈው ቆሳቁሰው ሕዝቡን አጋልጠው ለተወሰነ ጊዜ ታስረው ሲፈቱ ውጭ ለመውጣት? ይህ ጉዳይ ምርጫው ሲደር በእውን የሚታይ ስለሚሆን ይታሰብበት ከማለት ውጭ በእርግጠኝነት ይህ ይሆናል ለማለት ያስቸግራል። ይሁን እንጂ በተቃዋሚዎች ዙሪያ የሚታዩ መጐሻሸሞች መኖራቸው አይካድም። አንድነት ከሌለ ደግሞ የሕዝቡ ተስፋ መጨለሙ አይቀሬ ነው።

ቢሆንም የኢትዮጵያን የቆየ ታሪክ ወደ ኋላ ተስበን ስንቃኝ ሕዝቡ እርስ በርሱ በመተማመን፤ በመመካከር በጋራ ችግሮቹን በመፍታት አገሩን ከጠላት ጠብቆ የቆየ ኩሩ ሕዝብ ነው። ለመሰረቱና ለአንድነቱ ማስረጃ አማራው፤ ከትግሬ፤ ኦሮሞው፤ ከወላይታ፤ ጉራጌው ወዘተ ዘር ሳይለይ ተጋብቶ ተዋልዷል። ኦሮሞ ’ትግሬ፤ አማራ፤ ሶማሊ፤ ወዘተ አጋዥና አጋር ከሆነው ወንድሙ ጋር በሕግ የምትተዳደር የሰዎች መብት እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማሳደግ አንዱ ብሄር ሌላኛውን ብሄር በጥላቻ ዓይን አይመለከትም ነበር። ዛሬም ቢሆን የምናየው ሕዝቡ አገሩን፤ ኃይማኖቱን ወዳድ በመሆኑ በአንድነቱና በዜግነቱ ስለሚኮራ ለከፋፋዎች በር ላለመስጠት፤ አንድነቱ እንዳይናድ የሚያደርገው ተጋድሎዖ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን የአገር አንድነትና የሕዝብ መብት እንዳይረጋገጥ በተፈጠረው የጐሳ ፖልቲካ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የተረጨውን መርዝ ለመቋቋም አጋዥ የፖለቲካ ድርጅት እንደሚያስፈልገው እየጠየቀ ነው። ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ የተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ስቪክ ማኅበራት መኖራቸው እውነት ነው። ይሁን እንጂ ስንቶች ናቸው ለመስዋእትነት የተሰለፉ የሚለውን በውል ለመለየት አስቸጋሪ ነው።

መሪነን የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦች ልዩነቶችን ከማጥበብ ይልቅ በጐሳ ፖለቲካ ምክኒያት አንዱን ብሄር ጨቋኝ አንዱን ተጨቋኝ በሚል የቋንቋ ልዩነት እንዲፈጠርና የሕዝቦች ጭቆና እንዲራዘም፤ ራሳቸውን ከሥልጣን ወንበር ለማውጣት ሲሉ በጋራ የኖረን ሕዝብ በመለያየት አንዱ ብሄር ከሌላውኛው ጋር እንዲጋጭ በማድረግ የወንድማማችነት ባህሪ መልኩን እየቀየር በጥላቻ እንዲተያይ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም። ያለው መንግሥት በሕዝብ ምርጫ ሳይሆን በጉልበት መቀመመጡ ሃቅ ነው፡፡ ይህ መሆኑ እየታወቀ ሁሉም ባይባሉ አብዛኛች የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ያላቸውን ልዩነት በማጥበብ በጉሳ ቁንቋ ብሎም በሃይማኖት ሳይወሰኑ ያላቸውን ችግር በሰለጠነ አስተሳሰብ በውይይትና በስልት ኃይላቸውን አስተባብረው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ አብረው መስራት ይጠበቅባቸዋል።ይህ ሲባል ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን ያገባኛል የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ የመተባበር ግዴታ ያለበት ይመስለኛል። ይህ ካልሆነ ግን ለጭቆናው መራዘም የሁሉም ድርሻ እንዳለው ማወቅ ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው መንግሥት ሥልጣኑን ለማስቀጠል ሲል ተቃዋሚ የሚላቸውን ሁሉ ለመደፍጠጥ የሚችለውን ሁሉ እያደረግ ነው፤ ይህ ደግሞ የሚጠበቅ ነው። ባንፃሩ ተቃዋሚ ነን የሚሉ የፖልቲካ መስመር ዘርግተው በጋራ መንቀሳቀስ የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን ከሕዝቡ ውጭ ሆነው ሳያደራጁ ለሥልጣን ሽኩቻ ሲጉሻሸሙና ሲሰዳደቡ ማየት ምን ያህል ዝቅጠት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በሥመ ተቃውሞ ያለ ተስፋ አሮጌውን አመት በአዲስ ዓመት መተካትም አድሮ ጥጃ ማለት ቢያንስ ነው። ይህ ሲባል ሁሉንም ፖለቲካና ስቪክ ማኅበራትን በጥቅሉ ለማጣጣል እንዳልሆነ አንባቢ ልብ ሊል ይገባል። ጠንካራ ተቃዋሚዎችና ሚዲያዎች አሉ፤ይሁን እንጂ ትግሉ ወደፊት እንዳይገፉ አብዛኞች በለበጃ ሰርጅተው ለመጣል በሚያደርጉት የውስጥ ሴራ ባሉበት ዳዲ እያሉ እንዲያውም እየከሰሙ ማንነታቸው እስከ መረሳት የደረሱ እንዳሉ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።

ኢትዮጵያዊያን ስንባል ከዓለም የተለየ ባህሪ እንዳለን እርግጥ ነው። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ አያቶቻችን፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን እንደ ዛሬው በጉሳ፤ በሃይማኖት ሳይለያዩ አገራቸውን ከውጭ ወራሪ ሃይል ለመከላከል መተኪያ የሌለ ሕይወታቸውን መስዋታቸው ነው። ስለዚህ በጋራና በአንድነት በመቆማቸው የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌ ለመሆን የበቁት በዚህ ሁኔታ ይመስለኛል። ብሄራዊ አንድነቷን ጠብቀው ለዚህ ትውልድ የቆየችው በሕዝቡ አንድነት በጀግና ልጆቿ ደምና አጥንት በፀረ-ኮሎኒያሊዝም አቋማቸው ነው።

ከታሪክ እንደምንረዳው ቀደምት መንግሥታት በሕዝብ ላይ ጭቆና ቢያደርሱም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፈው ባለመስጠት በማጠናከረው ነው ያቆዩአት። የማይካድ ነገር ቢኖር በፊውዳሉ ሰረዓት በሥልጣን ይገባኛል የእርስ በርስ ውጊያ ነበር። ነገር ግን የአገራቸውን አንድነት፤ ታሪካቸውን ለማናጋት እንዳልነበር ታሪኮቿ ይነገሩናል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር በሃይማኖት በጾታ ወዘተ ሳይለያይ ተጋብቶ ተዋልዶ አብሮ የኖረ ሕዝብ ነው፡፤ መከራውንም ደስታውንም በጋራ ተካፍሎ ይህችን አገር ለኛ አስረክቧል። በእኛ ዘመን በተፈጠረው የጉሳ ፖለቲካ ምክንያት አገርና ሕዝብ ተጉድቷል፡፤ በሚፈጠረው የዘር ፖለቲካ የአገሪቱ አንድነት የሕዝብ መብት በከፍተኛ ደረጃ ተናግቷል። ብዙዎች ታሰረዋል፤ ተሰደዋል ከስራቸው ተፈናቅለዋል፤ ከቀያቸውም የተፈናቀሉ መኖራቸውም ሃቅ ነው፡፤

በአገራችን ሰላምና መረጋጋት ሊመጣ ከተፈለገ ሁሉም ብሄር-ብሄረሰቦች ለፍትህ ሲሉ በጋራ ከቆሙ ትክክለኛው እኩልነትና አንድነት እውን ይሆናል። ከነዚህ ከቀደምት ከአባቶቻችን የምንማረው ነገር ቢኖር የአገርና የሕዝብ ችግር የሚፈታው በጉሳ ፖለቲካ ጥላቻን በማናፈስ እንዳልሆነ ልብ ልንለው ይገባል። በአገራቸን ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የግድ እርቀ ሰላም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ የእምነት መፍለቂያ ብልህና አዋቂ ሰዎች ስላሏት ይቅር መባባል የሚከብድ አይሆንም። አንዳንዶች በኢትዮጵያ ውስጥ ፈረንጆች በኢሕአዴግ ላይ ተጽኖ አድርገው ሰላም ሊያመጡ እንደሚችሉ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይህ በጣም የተሳሳተ ስሌት ነው፡፤ ከዚህ በፊት ፋሽስት ጣሊያን አገራችን በወረረበት ጊዜ ጃንሆን የውጭ አገር ፈረንጆችን እርዳታ በጠየቁ ጊዜ ምን መልስ እንደተሰጣቸው ማወቅ ያስፈልጋል። ፈረንጅ “ሰላቶ” ከራሱ ጥቅም ባሻገር ለኢትዮጵያ ጥቅም ያስባል ብሎ መገመት መጃጃል ይሆናል። በፈረንጅ ከማመን በራስ ሕዝብ ላይ በመተማመን የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ እንዲሉ መድሃኒቱ የራስ ሕዝብ ነው።

አንዳንድ ፖለቲከኞች የውጭ ዲፕሎማሲ እንደሚጠቅም ያምናሉ፤ ይህን እኔም እጋራዋለሁ። ይሁን እንጂ ከተሞክሮ አንፃር እውነታዎች ሲዳሰሱ አውሮፓና አሜሪካ 20 ዓመት መቀመጥ ብቻውን ለውጥ ይመጣል ብሎ ለመገመት ያዳግታል። ስለሆነም ትክክለኛ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ የወንበር ጥም ሳያጠቃቸው አገራቸው ገብተው ሕዝባቸውን መታደግ አለባቸው። ሌላው የጠላቴ ጠላት በሚል በዋናነት ለአገራችን ውድቀትና ለባሕር በራችን መዘጋት ኤርትራ መሆኗ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቶም የሚረሳው አይደለም። ስለሆነም ገና አማራጭ የለም በማለት ከኤርትራው ኢሳይያስ አፈወሪቂ ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያን እታደጋለሁ ማለት የሚቻል አይመስለኝም። ከኢትዮጵያ ሕዝብ መረጃ እንዳገኘሁት ከሆነ በኤርትራ በኩል በሚደረገው ትግል ነፃ እወጣለሁ የሚል እምነት የለውም። እንዲያውም ወሬውን መስማት አይፈልግም። እውነቱ ይህ ነው። ከዚህ ቀደም የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ በኤርትራ በኩል ከተቻለ ጥሩ ነው የሚል አመለካከት ነበረኝ። ግን ኢሳይያስን ማመን ጉም መጨበጥ ስለሚሆን በበኩሌ የኤርትራ ጉዳይ አያምረኝም።

በመጨረሻም፦ መንግሥት በዘረኝነት ሥልጣን ከአንዱ ወደ ሌላ እንዳይሸጋገር ቆርጦ መነሳቱ አሊ አይባልም። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብ ሳይወክላቸው አንዳንዶች እንገነጠላለን የሚል መርዝ እየረጩ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለዚህ ዘረኝነትና መገንጠል በዚህ ዓለም ላይ ለማንም አልበጀ። የሚያዋጣው ለችግር መፍትሄው ይቅርታ ነው። ቀጣዩ ትውልዱ ከዚህኛው ትውልድ የተሻለ እንዲሆን ከዚህ በፊት የነበረውን ጐጅ አስተሳሰብ በተሻለ ሁኔታ ሰርቶ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት ያለበት ይህ ትውልድ ይመስለኛል። ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ የእያንዳንዱን ቆራጥ ውሳኔ ይጠይቃል። በብልሹ አስተዳደር ምክኒያት በራሱ አገር ኑሮ ላለመሞት የተሻለ አገር ፍለጋ መሄድ ተገቢ ቢሆንም ለችግሩ መፍትሄይ አይሆንም። ውጭ ሆኖ ትግል በታሪክ አልታየም።

ከዚህ ላይ ለእያንዳንዳችን የሚሆን ጥሩ ምሳሌ አለ። ማዘር ትሪስ እንዳለችው በዚህ ዓለም ላይ የበሽታዎች ሁሉ በሽታ ለማንም ሰው ምንም አይነት መፍትሄ የማይሰጥ ሰው ሆኖ መኖር ነው ያለችው ሊያነቃቃን ይገባል።
የሰው ልጅ የአንድን ሰው ችግር ለማቃለል እንደ ተፈጠረ አድርጐ ራስን ማየት መጀመር ወቅት አሁን ነው። የምሁር ማንነቱና መታወቂያው ለለውጥ ጥሩ ፈር ቀዳጅና ለችግሮች መፍትሄ ሰጭ ሲሆን ነው። መፍትሄ ሰጭ ካልሆነ ግን አልቻልኩም ብሎ ለሌላ ሰው መስጠት ይጠበቅበታል እንጂ መፍትሄ አልባ ሙጭጭ ማለት የለበትም። ስለሆነም ሁሉም ተቃዋሚዎች የታሪክ ሰው መባል ከፈለጉ የሕዝቡን ጀሮ ማዳመጥ አለባቸው። ለአገርና ለሕዝብ ሲባል እርቅ አድርገው ፕሮግራማቸውን አቻችለው ውጤት ሊያመጣ በሚያስችላቸው የትግል ስልት ላይ ወደፊት መገስገስ ይጠበቅባቸዋል። ሕዝቡም በተስፋ ከጐናቸው ይቆማል። ለሙሉ ፖለቲካ ሥራቸው አባላትም ደመዝ ሊከፍሉ እንደሚችሉ ከተሞክሮ መረዳት ይቻላል። ገና ለገና ላም አለችኝ በሰማይ ወተቷን አላይ እንዲሉ አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጦ ፈረንጅ በኢሕአዴግ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል ብሎ የመጠበቅ ተስፋ መቆም አለበት። ፈረንጅ እኮ ጥቅሙን እንጂ የኢትዮጵያ መፈራረስ ደንታው አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነቱ ትግሉ አገር ቤት መሆኑን ነው። ከዚህ ዘረኛ መንግሥት ለመላቀቅ መስዋዕት ግድ ይላል። ከዚህ ውጭ ሩቅ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል ትግል መምራት ከዚህ በፊት በታሪ አልታየም።

ስለዚህ ተቃዋሚዎች ሕዝቡን የማያዳምጡና የማይተባበሩ ከሆነ ሦስት አማራጭ እንዲኖራቸው ማስገደድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። አንደኛው ምርጫ ከሕዝባቸው ጐን ሆነው እያደራጁ እንዲያታግሉ፤ ሁለተኛው ምርጫ ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ አርፈው መቀመጥና ትግሉን ለሚችል ተቃዋሚ ቦታውን መልቀቅ ይሆናል፤ ሦስተኛው ምርጫ ኢንተርኔት ላይ ለሚያደርጉት ትግል ድጋፍ መንፈግ፤ ገቢያቸው እየነጠፈ ስለሚሄድ ባሉበት ደርቀው እንዲቀሩ ማድረግ።
ስለዚህ ያላቸው ምርጫ የራሳቸው ይሆናል ማለት ነው። ለዛሬ በዚህ አበቃሁ።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!!!!

ታክሎ ተሾመ

ለአስተያየት [email protected]

[email protected]

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop