January 27, 2014
16 mins read

ከዚህ ወዴት?

አንዱ ዓለም ተፈራ
የእስከመቼ አዘጋጅ

ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት፤ ከዕለት ዕለት ሀገራችንን ወደባሰ አዘቅት እየከተታት ነው። ያለጥርጥር ከዚህ መንገድ ቀና የሚልበት የፖለቲካ አንጀት የለውም። እያሽቆለቆለ መሄዱ፤ የመሰንበት ዋስትናውና መጥፊያው ነው።

ሕዝቡ ተማሮ ሀገር እየለቀቀ፣ በየቦታው ሕይወቱን እያጣ ነው። ሕዝቡ መሪ አጥቶ በወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ሥር እየማቀቀ ነው። ሀገሬ ብሎ መኩራት፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ መዝናናት፣ በነገ ላይ ተስፋ መጣል በኖ ጠፍቷል። ሀገራችን፣ ኢትዮጵያዊያን በያለንበት፣ የነገ ሕልውናችን ብቻ ሳይሆን፤ ዛሬ የቆምንበትን መሬት መርገጥ አቅቶናል። እንዲህ ባለ የፖለቲካ ሀቅ ውስጥ እየዋተትን ነው።

በውጭ ሀገር ያለውን ኢትዮጵያዊ (ውጭሰው – ያራዳ ልጆች ለዲያስፖራ የሰጡት ስያሜና የወደድኩት ቃል ነው) ለመከፋፈልና ፀጥ ለማድረግ፤ ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማድረግ፤ የእምነት ቤቶችን፣ የአገልግሎት ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የስፖርት ድርጅቶችን ለመቆጣጠር በመሯሯጥ ላይ ነው። እኛም ተመችተነዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የታጋዩ ክፍል ማዕከላዊ የሆነ ራዕይ፣ ተልዕኮና የዓላማ አንድነት የሌለው ነው። ኢትዮያዊነቱን የተቀበለ አለበት። ኢትዮያዊነቱን ያልተቀበለ አለበት። ታሪኬን እወዳለሁ የሚል አለበት። የታሪክ አንድነት የለኝም የሚል አለበት። በዚህ የትግል መስክ የተሠማሩት ድርጅቶች፤ በአብዛኛው የተዋቀሩትና ለሕልውናቸው ምክንያት የሚሠጡት፤ እኔ ሥልጣን መያዝ አለብኝ የሚል ምኞት ብቻ ነው። እኔ ከሌላው በአንድ ወይንም በሌላ ምክንያት የተሻልኩ ነኝ የሚል ነው።

በዚህ መሐከል፤ በውጭ ያሉ የታጋይ ድርጅቶችና በድርጅቶች ውስጥ የሌለን ግለሰቦች፤ ከተጨባጩ የሀገራችን እውነታ በጣም የራቅን ሆነናል። በሀገር ውስጥ ሆነው የሕዝቡን በደል አንስተው የሚታገሉ ድርጅቶች ደግሞ፤ የሚሠሩት በወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ሥር በመሆኑ፤ እንዳይንቀሳቀሱ ጠፍሮ በያዛቸው ሕግ ሥር ተወጥረው፤ የነጠረና የተራቀቀ የትግል ዘዴ ፈጥረው ሕዝቡን መምራት ስላልቻሉና ወይንም ሕዝቡን ስላላስተባበሩ፤ ላለው መንግሥት ህጋዊነት ከመሥጠት ሌላ፤ ለፖለቲካ ትግሉ ፋይዳ የማይሠጡ ሆነዋል ማለት ይቻላል። ሆነም ቀረም ግን እነሱው ሆነዋል የወደፊቱ ተስፋዎች። አማራጭ ከማጣት ይሁን ወይንም እነሱ ካላቸው ጥንካሬ፤ ያሉት ተስፋ እነሱ ናቸው።

በሀገራችን ያለው ሀቅ ባጭር ጊዜ የሚያባራበት ቀዳዳ ብርሃን የለም። አሁንም ሕዝቡን ያሰቃያል፣ ሕዝቡ ፈርቶት በተለዋጩ ደግሞ መንግሥቱ ህዝቡን ፈርቶ ያለበት የፖለቲካ እውነታ ሠፍኗል። እናም ወገንተኛው አምባገነን መንግሥት በጉልበቱ ከቀን ወደ ቀን ሕልውናውን ለማራዘም፤ ያስራል፣ ያሳድዳል፣ ይገድላል። ታጋዩ ክፍል ደግሞ የዚህን ሕገወጥ መንግሥት ድርጊት ይዘረዝራል። በጦር የበላይነቱን ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ይዟል። የሕዝቡ ደም እየፈሰሰ ነው። ይኼን መንግሥት በጦር የሚያቸንፍ ኃይል ባሁን ሰዓት የለም። ተግባሩን መዘከሩ ደም ማፍሰሱን አያስቆመውም። ጥያቄው፤ በዚህ ሰዓት ምን መደረግ አለበት? ነው። የዚህ ሰዓት ውሳኔያችንስ፤ የነገውን ሕልውናችንን እንዴት ያደርገዋል? ነው። ደም ማፍሰሱን አሁን ማስቆም አልቻልንም። ታዲያ አሁን ካለንበት ወደ ማስቆም የምንችልበት እንዴት ልንጓዝ እንችላለን? በተናጠል ቆመን ነው? በየድርጅቶቻችን ተሽጉጠን ነው? ወይንስ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በኢትዮጵያዊነታችን ተሰልፈን? ምን እናድርግ? በተለይ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ምን ማድረግ አለብን?
ታዲያ ምን እናድርግ? ለሚለው፤ የሚከተለውን መፍትሔ አቀርባለሁ፤

፩ኛ፤ ውይይት ማድረግ አለብን፤

ስደተኞች ነን። ስደተኛነታችን የፍላጎት ጉዳይ አይደለም። የፖለቲካ ስደተኞች ነን። በሀገራችን ያለው ፖለቲካ ውጤት ነን። የሀገራችን ጉዳይ ያሳስበናል። ይኼ ጉዳይ ሁላችንም ይነካናል። ምን እናድርግ? በሚለው ላይ፤ የወገንተኛውን አምባገነን መንግሥት ግፍ ከመዘርዘር አልፈን፤ አብረን በአንድነት ሀገራዊ ውይይት ማድረግ አለብን።

፪ኛ፤ በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ ሀቅና የትግሉን ምንነት በደንብ መተንተን አለብን፤

ምን ዓይነት መንግሥት ነው በሀገራችን ያለው? በምን መንገድ ይፈረጃል? መለወጥ አለበት ከተባለ፤ ለምን ይለወጣል? እንዴት ይለወጣል? በምን መንገድ ነው ለውጡ የሚካሄደው? እዚህ ላይ፤ በሁኑ ሰዓት ሠፍኖ ያለው፤ የዚህን መንግሥት ግፍ መዘርዘር ብቻ ነው። ይህ በቂ አይደለም። ትኩረቱ እኛ ምን እናድርግ ላይ ነው መሆን ያለበት።

፫ኛ፤
ዛሬ ዋና ዋና በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ የሆኑ መግባቢያዎች ነጥቦች ላይ መድረስ አለብን፤

አሁን በሀገራችን ያለውን የአስተዳደር ዘይቤ በሚመለከት፣ የብሔር ጥያቄ፣ የሀገሪቱን የቋንቋ ምስቅልቅል አቀማመጥ በሚመለከት፣ የደንበር ጉዳይ፣ በልማት ስም በሀገር ውስጥ ለውጭ ሀገር ድርጅቶች የተሠጡ ለም መሬቶችና የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከት? የተፈናቀሉ አማራዎችን በሚመለከት፣ የሃይማኖቱን ውጥረት በሚመለከት፣ ወ. ዘ. ተ. አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት ሊኖር ይገባል። አለበለዚያ ትግል በቀጠሮ ልናደርግ ነው።

፬ኛ፤ በትግሉ አይቀሬነት ስምምነት ላይ ከተደረሰ፤ ይህ ትግል የሚጠይቀው ዓይነት ድርጅት መመሥረት አለበት፤

በታጋዩ ክፍል የትግል አንድነት መኖሩ ግዴታ ነው። ይህ የትግል አንድነት ደግሞ ከትግሉ ራዕይ፣ የዓላማ ሂደት፣ ግብና ተልዕኮ ጋር የተያያዘ የአደረጃጀት ጥያቄ ነው። መሠረታዊ ጥያቄው የምንፈልገው ምንድን ነው? የሚለው ነው። የምንፈልገው ሥልጣን ነው? ሥልጣን ለማን? ለግላችን? ወይንስ ለሕዝቡ? የራሳችንን የግል ብልፅግና ለማራመድ? ለግለሰብ ዝናችን? ወይንስ ለሀገራችን ነፃነትና ለሕዝቡ አርነት? የግል ታሪካችንን ለማጉላት ወይንስ ሀገራችን በዓለም የሥልጣኔ ደረጃ ጎልታ እንድትታይ? የዴሞክራሲ በሀገራችን ሥር መስደድ በምን ይመሠረታል? የምንፈልጋቸውን ሰዎች ብቻ መርጠን በማቀፍ ሳይሆን፤ ሁሉን ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ በአንድ ማየት ስንችል ነው። የምንወደውን ብቻ ሳይሆን የምንጠላውን በርጋታ አዳምጠን፤ የመስማቱ አቅል ኖሮንና ዕድሉን ሠጥተን ልዩነታችን አስምረን፤ በምንስማማባቸውና በከፍተኛ ሀገራዊ ጉዳዮች አብረን መሥራት ስንችል ነው። እኛ ራሳችን ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ሥራዬ ብለን ሳንከተል፤ ለዴሞክራሲ ታጋዮችና የዴሞክራሲ ጠበቆች ልንሆን አንችልም። ለዲሞክራሲ ታጋዮች ነን ብንል ንፉቃን ነን። የሌሎች ድርጅቶችን መኖር አለመኖር ከዚህ አኳያ እንጂ፤ ስላሉ ወይንም ስለሌሉ በሚለው መነፅር መታየት የለበትም። ምን ዓይነት ድርጅት ነው አሁን ያለንበትን የፖለቲካ ምስቅልቅል ለውጦ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለድል የሚያበቃ? ምን ዓይነት ትግል ነው ሁኔታው የሚጠይቀውና ለሕዝባዊ ትግሉ አስተማማኝ መንገድ የሚሆነው?

፭ኛ፤ ይህ ድርጅት፤ የትግሉን ራዕይና የትግሉን ተልዕኮ ማርቀቅና ማስፈር አለበት፤

ይህ ታጋይ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የሚያሰባስብ ድርጅት ከተቋቋመ፤ ይህ ድርጅትና ይህ ድርጅት ብቻ የትግሉን ራዕይና ተልዕኮ ማስቀመጥ አለበት።ይህ ድርጅት የታጋይ ኢትዮጵያዊያን ድርጅት ስለሆነ፤ ለትግሉ ዓላማም የቆመ ነው። ሁሉንም ያቀፈ በመሆኑም፤ የትግሉን ራዕይና የትግሉን ተልዕኮ ለማርቀቅና ለማሳወቅ ገዴታና ኃላፊነት አለው።

፮ኛ፤ የዚህ ትግል ግብ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ ነው፤

አዎን በውጭ የምንኖርና በሀገር ውስጥ ያሉት ወቅታዊ የትግል ድርሻችን የተለያዬ ነው። በውጭ ያለነው አንፃራዊ ነፃነት ስላለን፤ ሀገር ውስጥ ያሉት ይኼ ስለተነፈጋቸው፤ ለትግሉ የምናደርገው አስተዋፅዖ የተለያዬ ነው። እናም ይህ የሚቋቋመው ድርጅት፤ በሀገር ቤትና ከሀገር ውጭ የምንገኘውን ኢትዮጵያዊያን ማሰባሰብና፤ በተቻለው መንገድ ሁለቱን ክፍሎች፤ ትግሉን በሚጠቅምና በማይጎዳ መንገድ ሊያስተሣሥር የሚችል ተገቢ አደረጃጀት መንደፍ አለበት። በሀገር ውስጥ ወይም ከሀገር ውጪ መገኘት ለትግሉ ያለንን ተሳታፊነትን አያነጣጥልም። ወጣት መሆን ወይንም ሽማግሌ መሆን ሀገር ወዳድነትን አይለያይም። የክርስትና ወይንም የእስልምና ተከታይ መሆን፤ ከኦሮሞ ወይንም ከሶማሌ፣ ከሲዳማ ወይንም ከአማራ፣ ከሁለት ወይንም ከዚያ በላይ ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ወላጆች መወለድ፤ ለኢትዮጵያዊያን የምናደርገውን ትግል አያሳንስም ወይንም አያጎለብትም። በማንኛውም መንገድ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ እኩል ተሳትፎ የሚያደርግበትን መንገድ ድርጅቱ መተለም አለበት። እያንዳንዳችን ለትግሉ የምናቀርበው አለን። ሁላችን ካልተሳተፍንበት፤ ትግሉ እውነተኛ ግቡን መምታቱ አስተማማኝ አይደለም።

፯ኛ፤ ለሚያስፈልገው መስዋዕትነት የተዘጋጁት ብቻ በድርጅቱ ማዕከላዊ አካል መካተት አለባቸው፤

ይህ ትግል በጣም ረጂምና ብዙ እልህ አስጨራሽ ነው። የሆይ ሆይታ ፈጠዝያ ጨዋታ አይደለም። ሌሎች እስር ቤት እየታጎሩበት ነው። ሀገር ለቀው እየተሰደዱበት ነው። ደም እየፈሰሰበት ነው። ሕይወት እየጠፋበት ነው። ይህ የጊዜ ማሳለፊያ ተግባር አይደለም። ሙያዬ ብለው የሚታትሩ ታጋዮችን ይጠይቃል። ሌሎች ደጋፊዎች ናቸው። በሀገር ጉዳይ፤ ይሉኝታ ቦታ ሊኖረው አይገባም። ለሕዝብ ብለው የቆሙና ሁሉን ለዚህ ተግባር የሚያቀርቡ ብቻ ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው። እንደገና፤ ይሉኝታ ቦታ ሊኖረው አይገባም። ለሀገር በአንድ እንነሳ።

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop