January 25, 2014
34 mins read

የኛ ነገር፡ የተሸነፈ ርእዮተአገርና ገፊ ፖለቲካ፤ (ተክለሚካሄል አበበ )

ስለመጪው ሶስተኛ ሪፐብሊክ፤ ካለፈው የቀጠለ፤ ሀ
ትንሽ ወደኁዋላ፤ እንደ መግቢያ
1. ግንቦት፤ 2003/2011፤ በቶሮንቶ ከተማ፤ ጃዋርና ኦባንግ፤ አሎ አይደሂስና (ሸጋ የአፋር ሰው ነው) አበበ በለው በእንግድነት የተገኙበትን ሕዝባዊ ስብሰባ ተንተርሼ፤ አንድ ወርቅ የሆነ ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡ ጽሁፉን ያላነበባችሁ ብታነቡት፤ ያነበባችሁትም ብትደግሙት አይቆጫችሁም፡፡ ጽሁፉ ይቀጥላል ብዬ ጊዜ ጠፋና ቀጣዩን ክፍል ሳላቀርብ ቀጠልኩ፡፡ ስለኦባንግ ገጠመኝ ተርኬ፤ ስለጃዋር ጀምሬ ነበር ያቆምኩት፡፡ አሁን መቀጠሉ ወቅታዊ መስሎ ታየኝ፡፡ ከስብሰባው በፊት ይመስለኛል ስለወቅታዊና መሰረታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ስናወራ፤ ተራው ህዝብ ለገዢ መደቦች ስራ ተጠያቂ ባሆንም፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ግን፤ ተራው የአማራ ህዝብ፤ ገዢው መደብ የፈጠረውን ርእዮተአገር በገቢርም በነቢብም ተቀብሎ ኖሮበታል፤ በብዙ ስፍራዎችም ይሄንን ርእዮተ-አገር ተጠቅሞ ሌሎችን ጨቁኖበታልም፤ ብሎ ለማስረዳት ሞከረ፡፡ ምሳሌ ሰጠ፡፡ ነገሩ ከአመታት በፊት የሆነ፤ የተለመደ ሁሉም ወይም ብዙዎቹ ኦሮሞዎች እለት ተእለት የሚጋጥማቸው ቢሆንም፤ ነጥባችንን ለማስረዳት ይጠቅማልና እጠቅሰዋለሁ፡፡ እነሆ አጋጣሚው፡፡

ጃዋር መሀመድ
2. ጃዋር የገጠር ልጅ ነው፤ ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ ላይ ራሱ እንዳለው፡፡ የዛሬ አስራምናምን አመት፤ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ከተማ ቤት ተከራቶ ትምህረቱን የሚከታተለው ታዳጊው ወጣት፤ ጃዋር ሲራጅ መሀመድ፤ አንድ ቀን አምሽቶ ዝናብ እየደበደበው ይመስለኛል ወደተከራው ቤት ይመጣል፡፡ አከራዩ ደግ አማራ ሴት፤ ለጃዋር ምግብ ሰጥታ፤ እሳት አንድዳ እያሞቀችዉ፤ ከላዩ ላይ ጋቢ ደርባ “ለምን እስኪመሽ ቆየህ አሁን ከመንገድ አንድ ጋላ ቢያገኝህና አንገትህን ቢልሀስ” አለችው፡፡ የዚህን ልጅ ስሜትና ምላሽ ለመረዳት ኦሮሞ መሆን አያስፈልግም፡፡ ራስን በሱ ቦታ ማስቀመጥና ነገሩን የራስን ጎራ ያለስስት በመተቸት ፈቃደኝነት ማሰላሰል እንጂ፡፡

3. ልክ ጅሁርና ጋይንት፤ ቢቸናና አንኮበር እንደምትኖር አንዲት አማራ ኢትዮጵያዊት፤ ይህቺ ሴት ክፋት እንደሌላትና የንግግሩዋን ፖለቲካዊ አንድምታ፤ በዚህ ልጅ ቀጣይ ማንነት ውስጥ የሚኖረውንም ፋይዳ እንደማታውቅ አሳምሮ መገመት ይቻላል፡፡ ይሄንን አጋጣሚ የነገረን ጃዋር ግን የሚለው፤ ይህቺ የዋህ ሴት የኢትዮጵያ ገዢ መደብ አካላት ያሰራጩትንና ለገዢ መሳሪያነት የተጠቀሙበትን የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ዝቅ የማድረግ አመለካከት፤ ሳታውቀው ከነፍሱዋ አዋህዳዋለች ነው፡፡ ስለዚህም፤ በቀጥታ ይሄንን የተወሰነ ብሄርን ዝቅ የማድረግ ባህል በመፍጠርና በመቅረጽ ባትጠየቅም፤ የዚህ ባህል በረከት ተቁዋዳሽ በመሆንና አውቃም ሳታውቅም ይሄንን ባህል እድሜ በመስጠት ተሳታፊ ነች ሲል ተከራከረ፡፡ በላይኛው ጽሁፍ ላይ ሰፈርኩትን የኦባንግን ገጠመኝ ጨምረን ካየነው፤ የጃዋር መከራከሪያ ስሜት ይሰጣል፡፡

ገረሱ ቱፋ፤

4. የላይኛው የጃዋር ገጠመኝ ቀሽም ሊመስል ይችላል፡፡ ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ እንዳልባል እንጂ፤ የገረሱ ቱፋ የከረሩ ምሳሌዎች ደግሞ አሉ፡፡ አንዱን ልጥቀስ፡፡ ኦሮሞው ወዳጄ ገረሱ ቱፋም፤ እንዲሁ ልጅ ሆኖ ሳለ፤ ጾም መሆኑን ረሳና፤ ወተት ጠጣ፡፡ እናቱ ወደንስሀ አባታቸው ላኩት፡፡ ቄሱ ቃል በቃል ምን ብለው እንደመለሱለትና ልቡን እንዳደሙት የነገረኝን በደንብ አላስታውሰውም፡፡ ብቻ፤ “ኤድያ ደግሞ፤ የጋላ ጹዋሚ ብሎ ነገር የለም” ብለው መለሱለት፡፡ “ለጋላ ንስሀ አባት ዲያቆን መች አነሰው” አይነት የሚለውን፤ የተለመደውን ክብረ-ነክ ተረት የሚያጠናክርና የሚያናንቅ መልስ ነው፡፡ በወቅቱ ገረሱ የሱ ጣፋት መስሎት ነበር፡፡ ነፍስ እያወቀ ሲመጣ ግን የሱ ጥፋት ሳይሆን ልክ እንደጃዋር ቀላቢ፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፤ በቄሱ ውስጥ የተተከለውን የሱን ብሄር ዝቅ የሚያደርግ ገዢው መደብ የፈጠረው ንቀትና ጥላቻ ተገለጸለት፡፡ ከአመታት በሁዋላ፤ እነሆ በገረሱ ነፍስ ውስጥ አብሮ የሚኖርና ዘወትር ቄሱ ስለወጡበት ህብረተሰብ ሲያስብና እኛ ጋር ክርክር በገጠመ ቁጥር ትዝ የሚለው መርዝ አጋጣሚ ሆነ፡፡ እንደውም ኢትዮጵያ ስትባል፤ የኚህን ቄስ ጋቢ የደረበች የአማሮች ፈጠራ መስላ ታየችው፡፡

5. ይሄ ሁሉም ሆኖ፤ ጃዋር እንደውም ኢትዮጵያ ኦሮሞነትን የሚያንጸባርቅ ቀለም ከቀባናት፤ አንድ ነን ወይም ልንሆን እንችላለን የሚለውን ሀሳብ ይቀበል ነበር፡፡ የኛን ቄስ ንግግር ፖለቲካዊ አንድምታ ከተደራ በሁዋላ ለቀብር ካልሆነ ቤተክርስቲያን ደርሶ የማያውቀው ገረሱ ግን፤ የኢትዮጵያ አንድነት የሚባል ነገር አገባውም፡፡ አንድ አይደለንም ባይ ነው፡፡ ከሆንም፤ አንድነታችን የጎደፈ አንድነት ሆኖ ነው የሚታየው፡፡

6. ብዙ እላይ ከጠቀስኩዋቸው የከፉ ምሳሌዎችን ማንሳት ይሻላል፡፡ ግን እነዚህ የኦሮሞም ይሁን ሌሎች ብሄርተኞች የሚያነሱዋቸውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክሶች በንደዚህ አይነት አጋጣሚዎችና ማስራጀዎች ለማስረዳት መሞከር፤ የክሱን ስፋትና ጥልቀት ማሳነስ ይመስለኛል፡፡ ማውራቱ ነገሩን ያቀለዋል፡፡ ያንን ስሜትና እውነታ መኖር ግን ከሕመም በላይ ነው፡፡ በዚህ አገባብ ውስጥ ነው ያለፉት ሶስት ወራት የነጃዋር ንትርክ የተጀመረው፡፡

7. እነዚህን ምሳሌዎች ያነሳሁዋቸው፤ አንደኛ፤ በዚህ ሰሞን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዝልዘላችንን ተቆጣጥረውት የቆዩትን ከአኖሎ ሀውልት እስከ በደሌ ኮንሰርት፤ ከምኒሊክ ቅድስና እስከ ጃዋር ትንተና ያሉትን ጉዳዮች ስንመለከት፤ በተወሰነ መልኩ የነዚህን ሰዎች ስሜት ለመረዳት የነዚህን ሰዎች አመለካከት የለወጡ ወይንም ያዳበሩ አጋጣሚዎችን መስማት ራሳችንንና የምንደግፈውን ርእዮተአገረ ለመደገፍ ከመሽቀዳደም ይልቅ የሰዎቹን ክስ በትእግስት ወደማድመጥ ሊወስደን ይችላል በሚል እምነት ነው፡፡ ሁለተኛ፤ የጃዋርና የገረሱ ፖለቲካዊ ማንነት የተወለደውና የተሞረደው ከንደዚህ አይነት ፖለቲካዊና ማሀበራዊ ክስተቶች ነውና እነጃዋር የሚሉትን መስማትም መገምገምም ያለብን በዚህ ማእቀፍ ውስጥ እንደሆነ ለማሳየትና፤ በዚያ አይነት ጉዞ ውስጥ ያደጉና የነቁ ወጣቶች ኢትዮጵዊነት ለምን እንደሚያስጸይፋቸው ሲናገሩ፤ በተስኪያን እንደገባች ውሻ ከማባረር፤ እንደግለሰብም ይሁን እንደተቁዋም፤ እነዚህን ልጆች ጸረ-ኢትዮጵያ አድርገን ከመፈረጃችን በፊት፤ ህመማቸውን ለማድመጥና ለማከም መጣር ይገባል፡፡ ኢህአዴግ ወደቆ እንድትኖር የምንፈልጋት ኢትዮጵያም፤ እነዚህን ህመሞች ለማስታመም የሚችል ህገመንግስታዊ፤ ስነልቡናዊና ፖለቲካዊ ዝግጅት ከሌላት፤ የተቃውሞ ፖለቲካችን በርግጥም የመፍትሄ ሳይሆን፤ የማውገዝ ብቻ ይሆናል፡፡ የዛሬው ጽሁፌ ስለዚህ ፖለቲካዊ ህክምናና ብናደርግ ስለሚበጁን ነገሮች መንገድ ለመጠቆም ነው፡፡ በዚህኛው ክፍል ጠቅላላ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ መፍትሄዎች ይጠቆማሉ፡፡

መጀመሪያ አፍሪካዊ ወይስ ኢትዮጵያዊ?

8. ባለፈው ሰሞን፤ አልጀዚራ ላይ በቀጥታ ስርጭት ይመስለኛል፤ ጃዋር ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከተውን ጥያቄ ተጠየቀ፡፡ “መጀመሪያ ኦሮሞ ነህ፤ ኢትዮጵዊ?” የሚል፡፡ የሚቀጥለው ምሳሌ መቶ በመቶ ላይመሳሰል ይችላል፡፡ የተወሰነ መመሳሰል ግን አለው፡፡ አንድ ሰላሳ አመት ካናዳ ወይም አሜሪካ ውስጥ የኖረ ኢትዮጵያ፤ ወይንም እነዚህ አገር ውስጥ የተወለደ ናይጄሪዊ ይህንን ጥያቄ ቢጠየቅና፤ መጀመሪያ ናይጄሪያዊ ነኝ ብሎ ቢናገር፤ አሜሪካኖችን ወይንም ካናዳዎችን የሚያስቆጣ አይመስለኝም፡፡ ጃዋር ከኢትዮጵ በፊት መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ብሎ ሲናገር ግን ብዙዎች አኮረፉ፡፡ ንትርክ ተጀመረ፡፡ የነቁና የበቁ የሚመስሉ የአንድነት አቀንቃኞች ራሱ ተቆጡ፡፡ አሁን በእመብርሀን ይሄ ምኑ ያበሳጫል? በዚህ መደንገጥም መቆጣትም የለብንም፡፡ ማድረግ ካለብን መጠየቅ ብቻ ነው፡፡ ችግሩ፤ እንድንሸመድድ እንጂ፤ እንድንጠይቅ በሚያበረታታ ባህል ውስጥ አላደግንምና፤ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ልጁን ወደመዘልዘሉ ዘለልን፡፡

9. አንደኛ፤ ከአገሬ በፊት ብሄሬን ነኝ የሚለው መልስ እንደየአመለካከታችን ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥም ሰው ከአገሩ በፊት ብሄሩን ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነህ አፍሪካዊ ቢባልና መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ቢመልስ፤ ምንም ብዙ ቁጣ የሚቀሰቅስ አይመስለኝም፡፡ ያ ባይሆንም እንኩዋን፤ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች አንድ ወጥ የሆነ ሳንሳዊ መልስ ስለሌላቸው፤ ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሲጠየቁ፤ ብዙ ሳያወጡ ሳያወርዱ እንዲህ አይነት መልስ ቢመልሱ፤ ሲሆን ሲሆን መልሳቸውን መቀበል፤ ያለበለዚያም የመልሳቸውን መሰረት ለመረዳት መሞከር እንጂ፤ ግፋ ካለም መልሳቸው ለምን ስህተት እንደሆነ ለመጠቆም መሞከር እንጂ፤ በመልሳቸው ማውገዝ አግባብ አይደለም፡፡ ለጃዋር የተሰጠው ተቃውሞ ደግሞ በብዛት የመጣው የአሜሪካና ካናዳ እንዲሁም የአውሮፓ ፓስፖርታቸውን ተሸክመው መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነን ብለው ከሚናገሩ ሰዎች አንደበት መሆኑን ስናይ፤ አንዳንድ ግዜ ሚዛናችን ምን ህል የተዛባ ነው ያሰኛል፡፡

ጃዋር ሚናገረውን ያውቃል፤ ያለውንስ ለምን አለ?

10. በመሰረቱ፤ ይህ ልጅ መቼም ሰው ነውና አንዳንድ ግዜ አግባብ ያልሆነ ነገር ቢያመልጠውም፤ የሚሰራውንም የሚናገረውንም ያውቃል፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ ኦባንግ ሜቶ እንዳለው፤ “በኢትዮጵያዊነታችን ያጣነው ነገር ስላለ ብቻ ኢትዮጵያዊነታችን ይሰረዛል ማለት አይደለም”። ጃዋር፤ ልክ እንደ ኤርትራ እዚያ አካባቢ ኦሮሞ ወይንም ኦሮሚያ የሚባል መንግስት እስካልተመሰረተ ድረስ፤ ቢወድም ባይወድም፤ ጥንትም አሁንም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ያውቀዋል፡፡ ኤርትራ ተፈጥራም እንኩዋን፤ ኤርትራዊነትና ኢትዮጵያዊነት በሁለቱ አገሮች መካከል እንደሚሰመር ድንበር ይቀላል ማለት አይደለም፡፡ ጥምር ዜግነት የሚሉትን ጽንሰሀሳብም ማስታወስ አይጎዳም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆንም ሙሉ በሙሉ የስራችንና የምርጫችን ውጤት ሳይሆን፤ የትውልድና የሕግ ጉዳይ ነው፡፡ ጃዋር እስከቅርብ አመታት ድረስ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዞ እንደሚዞር እገምታለሁ፡፡ ልጁ እያለ ያለው ግን፤ ህግና አለማቀፍ ፖለቲካ አስገድዶኝ ኢትዮጵዊ ብሆንም፤ ፖለቲካዊ ነፍሴ ኢትዮጵያዊ አይደለም ነው፡፡

11. ነፍስ እንደዜግነት በህግ አትገደድም፡፡ ነፍስ ዜግነቱዋን ወይም ማንነትዋን ትመርጣለች እንጂ፡፡ ነፍሱ ማንነትዋን መረጠች፡፡ የኛ ስራ መሆን ያለበት፤ መናደድ ወይም ማበድ ሳይሆን፤ መጀመሪያ ማብረድ፤ ልክ አሁን እኔ እንደማደርገው፤ ከዚያ መጠየቅ ነው፡፡ ይሄ ልጅ ለምን እንደዚያ አለ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነው ብለን፤ በየሬድዮና ቴሌቪዥናችን ስንሰቅለው፤ በየስብሰባና በየመድረካችን ስናቀርበው፤ ድንገት ተነስቶ እንዴት እንዲህ ጉድ አረገን፡፡ ብዙዎቻችን ግን አልጠየቅንም፡፡ ፈረድን እንጂ፡፡ አትፍረድ ይፈረድብሀል የሚል ብሂል ባነገበ ሀይማኖት ክርስትና የተነሳን ሁሉ ፈረድን፡፡

እንደሚመስለኝ፤ እኔ እንደማስበው፤

12. ጃዋር፤ ያንን የቴሌቪዥን ውይይት የሚከታተል ሁለት ትልልቅ ቡድን እንዳለ ያውቃል፡፡ አንደኛው በተለምዶ የአንድነት ሀይል የሚባለው፤ ሁለተኛው የነጻነት ወይንም የኦሮሞ ብሄርተኛ ሀይል፡፡ ሌሎች ሶስተኛም አራተኛም ቡድኖች ኖራሉ፡፡ ያለውን ፖለቲካዊ ራእይ በተደጋጋሚ የፈነጠቀው ጃዋር፤ ዞሮ ዞሮ የአንድነቱ ሀይል በጥርጣሬ እንደሚያየው ወይንም የብሄር ማንነቱን ጨፍልቆ እንጂ እሱ በሚፈልገው መልኩ እንደማይቀበለው በተለያየ አጋጣሚ አስተውሎዋል፡፡ ስለዚህ በሱ ቦታ ላለ፤ ከላይ በአንቀጽ 2፣ 3፣ እና አራት በጠቀስናቸው የእለት ተእለት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክስተቶች ውስጥ ላደገና ለሚኖር ኢትዮጵያዊ፤ እንደዚያ ባለ ፍጥነትን በሚጠይቅ አጣብቂኝ ውስጥ የሚሰጠው መልስ መጻኢ የፖለቲካ እድሉ ላይ እንደሚያጠላበት ያውቃል፡፡ ስለዚህ፤ መጀመሪ ኦሮሞ ነኝ አለ፡፡ በተወሰነ መልኩም ኢትዮጵያዊነት እንደተጫነበት ጠቀሰ፡፡

13. አስቀድመን ጃዋር ላይ የጫንበት ማንነት ወይንም ዜግነትና ለተጠየቀው ጥያቄ እኛ ያዘጋጀልነት መልስ ከሌለ በስተቀር፤ የሚሰማውን ማንነትና ውስጡ የሚቀበለውን ዜግነት የሚያውቀው እሱ እንጂ፤ እኛ አይደለንም፡፡ ስለዚህም በወቅቱ ብሄርን ማስቀደሙ ምክንያታዊ ውሳኔ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ብልሀትም ነው፡፡ በርግጥም በሁዋላ የተከተለውን እሱንና አመለካከቱን የማሳደድ ዘመቻና ውግዘት ለተመለከተ፤ የጃዋር መልስ ትክክል ነበር ያሰኛል፡፡ ምክንያቱም እኝ የቀረጽንለት ኢትዮጵያ ለሱ ስሜት መፈናፈኛ የሌላት ሆና ተገኝታለችና፡፡ ጃዋር የቆየ የኢትዮጵያውን ልሂቃን፤ ”የኛ መንገድ ብቸኛውና አማራጭ የሌለው ምርጥ መንገድ ነው፤ ከኛ እውቅናና መንገድ ውጪ የሚጉዋዝ ውጉዝ ይደምሰስ”፤ የሚል ትውልድ ያጫረሰና፤ እነፍቅረስላሴ ወግደረስ ከ20 አመታት እስርም በሁዋላ ያልለወጡት፤ ችኮ ፖለቲካዊ ስነልቡና ሰለባ ነው የሆነው፡፡ እንደውም፤ ለጃዋር፤ እኛ ከቀረጽንለት ኢትዮጵያ ይልቅ፤ ኢህአዴግ የፈተለለት ኢትዮጵያ የተሻለች ብትመስለው አይገርመኝም፡፡

የብሄር ፖለቲካን፤ በከፊል መቀበል ነው፤

14. እነዚህ ወጣቶችም ሆኑ የፖለቲካ ንስሀ አባቶቻቸው፤ በዚህ በአልጀዚራ ላይ የሰማነውን አይነት፤ ኢትዮጵዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፤ ለኛ ለመቀበል የሚያስቸግረን ንግግር ሲናገሩ፤ የቆሰለውና እንዲህ ወዳለው ስሜት ውስጥ የሰነቀራቸውን ፖለቲካዊ ሕመም በማከም ፈንታ፤ እንደጠላት የሚፈርጅ አካሄዳችንና ራሳችንን የኢትዮጵያ አንድነት ጋሻዣግሬዎች አድርጎ የመሾም ባህላችንን ነው፤ እነዚህን ሰዎች ወደጽንፈንነት የሚመራቸው፡፡ ያ ደግሞ ለኛም ለኢትዮጵያም አይበጅም፡፡ በዚህ ረገድ ይሄን ያህል አመት በኢህአዴግ መበለጣችን ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ምክንያቱም፤ ኢህአዴግ ለነጃዋር፤ የአንድነቱ ሀይል ለመቀበል የሚያዳግተውን፤ ኦሮሚያ የሚባል ክልል/ካርታ፤ ሙሉ ነጻነት ባይኖረውም በራሱ ቁዋንቁዋ የሚተዳደር መንግስት ሰጥቶዋቸዋልና፡፡ ስለዚህ ከአንድነት ሀይሉ ውግዘት ጋር ሲወዳደር ብቻ ሳይሆን፤ ራሱን ችሎም፤ ኢህአዴግ ለብሄር ፖለቲከኞች የሰጠው ፖለቲካዊ ገጸ-በረከት፤ ልብ የሚማርክ ነው፡፡

15. የዚህ የብሄር ፖለቲካ ርእዮተአገር እንደአዲስ በመጣበት ሰዓት ለብዙዎቻችን አዲስና አስደንጋጭ ነበርና ባንቀበለው አይገርመኝም፡፡ እኔና ተስፋዬ ”ጋላው”፤ ስለሺና ወዲ ትግሬው በብሄር ሳይሆን በሰፈር፤ በቁዋንቁዋ ሳይሆን በክፍል፤ በሀይማኖት ሳይሆን፤ በእድሜ ተከፋፍለን ኩዋስ ስንጠልዝ፤ ሴት ስናባርር፤ ጠላ ስንገለብጥ፤ ድግስ ስናሳድድ ነበርና ድንገት የመጣው፤ በርግጥም የብሄር ፖለቲካ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ከ22 አመታት ሽንፈት በሁዋላም ግን ራሳችንንና አስተሳሰባችንን አሸናፊ ሆኖ ከወጣው የብሄር ፖለቲካ ጋር ማጣጣም አለመቻላችን ግራ ነው የገባኝ፡፡ ለዚህም ነው፤ የብሄርተኞችን ቁስል በማከክና በማከም ረገድ ኢህአዴግ በልጦናል፡፡ እኛ እንደውም ቁስሉን የምናክም ሳሆን የምናመረቅዝ ሆነናል፡፡

16. ኢህአዴግ ለነሱ አስቦም ይሁን ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም፤ የብሄርን ፖለቲካ በሚገባ ተጠቅሞበታል፡፡ 22 አመታት ያለብዙ ፈተና መርቶበታል፡፡ ስለዚህም እነሌንጮ ለታ እነሌንጮ ባቲ እንኩዋን፤ እንደገና ወደሁዋላ የኢህአዴግን አስተዳደር ተቀብለው ለመኖር እያኮቦኮቡ ነው፡፡ ምክንቱም ኢህአዴግ ጠላት ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ከተሰለፈው ወደሁዋላ ሊጎትተን ይፈልጋል ብለው ከሚፈሩት የአንድነት ሀይል የተሻለ ጠላት እንደሆነ ያውቁታልና፡፡ ስለዚህ ይሄንን ጎሳን ወይንም ብሄርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካዊ መሳሪያ ይዞ፤ ኢህአዴግ ሌላ 20 አመት ቢገዛም አይገርመኝም፡፡

17. እንደፖለቲካዊ ስበስብ፤ ሙሉ በሙሉ የኢህአዴግን የብሄር ፖለቲካ ባንቀበለውም እንኩዋን፤ ኢህአዴግ ክፉ መንግስት እንደሆነ ቢያውቁም፤ በተወሰነ መልኩ በፊት ያልነበረንን መብት አስከብሮልናል ብለው፤ የኢህአዴግን የብሄር ፖለቲካ ተቀብለው ኢህአዴግን በሀይለኛው የሚደግፉትን ቡድኖች የሚማርክ አማራጭ ማቅረብ አልቻልንም፡፡ እንደግንቦት ሰባት ያሉ በንጽጽር የተሸሉና የሰለጠኑ አባላት ያሉበት ድርጅት እንኩዋን፤ ብዙውን እንዲህ ያለውን ፖለቲካዊ ጉዳይ፤ ”ህዝቡ ይወስናል”፤ የሚል የስንፍናና የሽሽት አንቀጽ ሰንቅረው፤ በጎን ሸውደው አልፈውታል፡፡ በዚህ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን፤ እንኩዋን የሚያሸንፍ፤ የሚያሰልፍም አማራጭ ርእዮተ-አገር ባልቀየሱበት ሁኔታ ነው፤ ይባስ ብለን፤ በተወሰነ መልኩም ከኛ ጋር ለመስራት የሚጥሩትን ጃዋሮች አመናጭቀን የምንገፋው፡፡ የዚህኛው ገፊ ፖለቲካ መጨረሻ፤ ልጆቹ ልክ እንደ ሌንጮ ለታ ወደጠላት ጎራ እንዲገቡ መገፋፋት ያለበለዚም ሌላ የፈተና ግንባር እንዲፈጥሩ ማበረታታት ነው የሚሆነው፡፡

18. ባንድ በኩል የሌንጮን ወደኢትዮጵያ የመመለስ ውሳኔ፤ ድፍረትና ብልሀት የተሞላበት ውሳኔ ነው ብዬ ባደንቅም፤ በሌላ በኩል ግን የሌንጮ ወደኢትዮጵያ የመመለስ ውሳኔ የአንድነቱን ሀይል ፖለቲካዊ ችኮነትና ውድቀትም ያሳያል፡፡ ሌንጮስ እድሜውም እየገፋ ነውና እንደጎልማሳነት ዘመኑ ብዙ ላያስቸግረን ይችላል፡፡ መጪውን ዘመን የሚዳኙትን፤ እነጃዋር መሀመድን፤ እነገረሱ ቱፋን ግን በትእግስት ልናስተናግዳቸው ሲገባ፤ ሌንጮን መማረክ የተሳነን፤ በኛ ብሶ፤ ደግሞ ይሄንንም ልጅ፤ ጃዋርን ገፋነው፡፡ ከገፋነው በሁዋላ፤ ምንስ ቢል፤ ምንስ ቢያደርግ፤ ምን ይደንቃል፡፡ ከሲያትል እስከ ለንደን፤ ከቶሮንቶ እስከ እስከ ሚኒያፖሊስ ቀድሞም የድርጅት ድክመት ይዞት እንጂ፤ በቁዋፍ የነበረውን የኦሮሞ ብሄርተኛ፤ ለዘብተኛ የነበረውን ሁሉ፤ ኦሮሞ ይቅደም እያለ ሰበሰበው፡፡ እርግጠኛ ነኝ፤ ጃዋር በህልሙም በእውኑም ያላሰበውን ፖለቲካዊ መድረክ ፈጠርንለት፡፡ ገፊ ፖለቲካችን እኛኑ ሳይፈጀን፤ ይሄንን ገፊ የፖለቲካ ቅኝታችንን መለወጥ አለብን፡፡

ሶስት ሀይሎች፤ አንድነት፤ ነጻነት እና ኢህአዴግ

19. እንደሚመስለኝ፤ ይህ ልጅ፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ በዋንኛነት፤ ሶስት አገራዊ ሀይሎች የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ለመለወጥ ትግል እንደገጠሙ ገምቶዋል፡፡ አንደኛው አህአዴግና አጋሮቹ፤ ሁለተኛው በተለምዶ የአንድነት ሀይል የሚባለው ቡድን፤ ሶስተኛው ደግሞ የነጻነት ሀይሎች ወይንም የዘውግ ብሄርተኞች የሚባሉት ናቸው፡፡ እንደሚመስለኝ የጃዋር ጠቅላላ ስሌት የሀይል ሚዛኑን ወደኦሮሞ ብሄርተኞች መድፋት ነው፡፡ ኢህአዴግ ኖሮም ይሁን ኢህአዴግ ወድቆ የምትቀጥለው ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ አወሳሰን ላይ፤ ቀደም ሲል ኦሮሞ፤ በድምስሱ ደግሞ እስላም ኦሮሞው የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለምዶ የአንድነት ሀይል እየተባለ የሚጠራው ሀይል በተዘረረበት ወይንም እርስበርሱ በተከፋፈለበትና በአንድነት ለመስራት በየወንዙ እየተማማለ መሀላውን በየጋራው በሚያፈርስበት ሰዓት፤ ሲሆን ሲሆን ኦሮሞውን አንድ አድርጎ፤ አንድም ባይሆን አጠናክሮ መያዝ፤ በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የይል ሚዛኑንን ወደነርሱ እንዲሆን ያሰፋዋል ብሎ ያምናል፡፡

20. ስለዚህ ጃዋር መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ሲል፤ ይሄንን ኦሮሞን እንደአንድ ሀይል አጠናክሮ መጉዋዝ፤ መጪዋን ኢትዮጵያን ለመቅረጽ ያስችለናል ከሚል ስሌት ተነስቶ ይመስለኛል፡፡ ምክንቱም፤ ይሄ ልጅ ዞሮ ዞሮ፤ አማራ ወይንም አምሀራይዝድ ሌሎች የበዙበት የአንድነቱ ሀይል በቀላሉ እንደማይቀበለው ያውቀዋል፡፡ ትግሉን እንደከዳ፤ ከአማራ ጋር እንዳበረ እየተከሰሰም ቢሆን፤ ይህ ልጅ አምስት ስድስት አመት፤ ከአንድነት ሀይሉ ጋር አብሮ በልቶ ጠጥቶ፤ ተከራክሮና ተደራድሮ አየው፡፡ አንድነት ጭፍለቃ ነው የሆነበት፡፡ መፈናፈኛ አሳጣው፡፡ ስለዚህ፤ ጃዋር ተገኑን፤ ወይም ኮንስቲቲወንሲውን መምረጡ ነው መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ ያሰኘው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ አማሮችና ትግሬዎች እየተፈራረቁ ይህቺን አገር መርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ እኛ እንምራ ነው ነገሩ፡፡ በትግሬ ታኮ ወይንም በአማራ ጥላ ስር ሳይሆን፤ በራሳችን መታወቂያ፡፡ አገሪቱን መምራት ካልቻልንም፤ ቢያንስ የራሳችንን እጣ ፈንታ እንወስን ነው፡፡ የኛ ምላሽ ….

ይቀጥላል፤
ተክለሚካኤል አበበ፤ ጥር፤ 2006/2014፡፡ ተረንቶ፤ ካናዳ፤

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop