ህጻን ሄለን ሀድጉ
ህጻን እየሩሳሌም ሃይላይም በእንባ ታጅባ ከመቀሌ መከላከያው ከወጣ በሁዋላ ታፍና ወደ ጦርነት መግባቱዋን ትናገራለች
***********************************
ከትግራይ፡ መቀሌ አስከ አፋር ድረስ ባልጠና ጉልበታቸው ተጉዘዋል። ከወንዝ ውሃና ከደረቅ ብስኩት ውጭ ለዛለ የህጻን ጉልበታቸው ያገኙት የለም። በህወሃት የሽብር ቡድን ተገደው ድንገት በገቡበት ውጊያ ብዙ እህት ወንድሞቻቸውን አጥተዋል።
“ምርኮኞቹ” ህጻናት ከእንባ ጋር እየታገሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ህወሃቶች እንዳይገድሉን ፈርተን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየተማገድን ነው ሲሉ ነው የተማረኩ ህጻናት “ወታደሮች” ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት።
ከእነዚሁ ታዳጊ ህጻናት “ወታደሮች” መካከል ኢየሩሳሌም ሃይላይ አንዷ ናት፤ እየሩሳሌም ሐምሌ 7 ቀን 2013 ከመቀሌ በድንገት ከቤቷ እንደወጣች ታፍና ወደ ጦርነት መምጣቷን ትናገራለች።
ምንም ዓይነት ሥልጠና ሆነ መሣሪያ ሳታገኝ ”አሸንፈን አዲስ አበባ እንገባለን” በሚል ባዶ የተስፋ ቃል እየሸነገሉ ወደ ጦርነት እንዳስገቧቸውም ትገልጻለች።
በመጨረሻም ጦርነቱ ሲጀመር እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ህጻናት “ደንግጠን ራሳችንን ለማዳን ለመከላከያ ሠራዊት እጃችንን ሰጥተናል” ትላለች ኢየሩሳሌም።
ሌላዋ ህጻን ሄለን ሀድጉ በበኩሏ ከመቀሌ በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሥመር አቅጣጫ አምጥተው አፋር ክልል እስከሚገቡ ድረስ ወዴት እየወሰዷቸው እንደሆነ ሳታውቅ መቆየቷን ታስታውሳለች።
በጦርነት ውስጥ ደረቅ ብስኩትና የወንዝ ውሃ እየጠጡ መቆየታቸውን የምትናገረው ሄለን፣ “ጓደኞቼ ራሳቸዉን ለማትረፍ በጭንቅ ላይ በነበሩበት ወቅት በአገር መከላከያ ተማርኬ ሕይወቴ በመትረፉ ተደስቼያለሁ” ብላለች።
የትግራይ ሕዝብ የህወሓት አሸባሪ ቡድን ራሱን በሥልጣን ላይ ለማቆየት ህጻናትን በግፍ ወደ ጦርነት በመማገድ እየፈጸመ ያለውን ግፍ እንዲያቆም እንዲታገለውም ጠይቃለች።
ሌላው ህጻን ኢሳያስ ዓለም በበኩሉ ጁንታዉ የትግራይ ህጻናትን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን ይመሰክራል።
እሱን ጨምሮ ሌሎች የእድሜ እኩዮቹ ተምረው ነገ የተሻለ ዜጋ ለመሆን ፍላጎትና ህልማቸው ቢሆንም፤ ጁንታው እንዳይገላቸው በመፍራት በተዋጊነት መሰለፋቸውን ይናገራል።
በጁንታው ተገድደው ወደጦርነት የገቡትና በመከላከያ ሰራዊት ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ህይወታቸው ተርፎ የተማረኩት ህፃናት “የጁንታው አመራሮች የራሳቸዉን ልጆች በውጭ አገር እያስተማሩ የእነሱና የቤተሰቦቻቸው ሕይወት ተስፋ በመደብዘዙ ተቆጭተናል” ይላሉ።
ህፃናቱ፣ የትግራይ ሕዝብ ራሱን በሥልጣን ለማቆየት ሲል ህጻናትን በግፍ ወደ ጦርነት የሚማግደውን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሊታገለው እንደሚገባ ነው በአፋር ግንባር በሀገር መከላከያ ሰራዊት የተማረኩተ ህጻናት “ወታደሮች” የገለጹት።
ጁንታዉ በኢትዮጵያ ላይ በጀመረዉ አጥፍቶ መጥፋት ዘመቻ፣ የትግራይ ህጻናትና ሴቶችን በተዋጊነት መጠቀም ከጀመረ ሰነባብቷል።
የሰሞኑን በአፋር ክልል ፈንቲ-ረሱ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በከፈተዉ ጥቃት የተማረኩት እነዚሁ ህጻናት፣ የጁንታው አሳፋሪና ከሰብዓዊነት የወጣ ባህሪን ዓለም በትኩረት ሊያየው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሺን ምክትል ኮሚሽነር መሀመድ አህመድ እንደገለጹት ጁንታው በዞኑ ያደረገዉን ወረራ የአፋር አርብቶ አደር ከመከላከያ ሠራዊትና ልዩ ሃይል ጎን በመቆም እየደመሰሰዉ ነዉ ።
ጁንታዉ ዛሬ በሀገር ላይ የከፈተዉ ጥቃት የቆየ ሀገር የማፍረስ ህልሙን እውን ለማድረግ በግልጽ የጀመረው መሆኑን ገልፀዋል።
በጦርነቱም ህጻናትን በሃሺሽ አስክሮ በማስገባት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆኖ ከማንም በላይ የትግራይ እናቶችና ህጻናት ጠላትነቱን እያስመሰከረ ነዉ”ብለዋል
በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ራሱን ለማቆየት ህፃናትን በጭካኔ ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን አሸባሪ ቡድን፣ ከመከላከያና ከሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመቆም እንዲታገለው ጠይቀዋል።
አሸባሪው ህወሃት ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ያልደረሱትን ህጻናት እያስገደደ ለሦስት ቀናት ያልበለጠ ሥልጠና በመስጠት ወደ ውጊያ አስገብቶ መቋቋም በማይችሉት ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ገልጿል።
“በጦር ሜዳ ካሰለፋቸው ህጻናት ድል አገኛለሁ ብሎ በማሰብ እያስጨረሳቸው ይገኛል” ያለው ሚኒስቴሩ፤ ይህ ሳይበቃ በውጊያ የተገደሉትን ህጻናት ሬሳ በመሰብሰብ “የኢትዮጵያ መንግስት ሠራዊት ገደላቸው” ብሎ በውጊያ ያስጨረሳቸውን ህጻናት አስከሬን መነገጃ ለማድረግ የተለመደውን የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት አስከሬናቸውን ኹሓ ላይ ሰብስቦ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
(ኢ.ፕ.ድ)