ሙሉጌታ አሻግሬ / [email protected]
የሕዝብ ትግል ማለት ለሕዝብ ጥያቄ እና ብሶት ምላሽ ለመስጠት ብሎም ዘላቂ መፍትሄ ለማግኘት የሚደረግ የመስዋዕትነት ሂደት ማለት ነው። ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አገር ወዳዶችና የፍትህ ናፋቂ ዜጎች ህልውናው የተረጋገጠው የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በሁለገብ የትግል ስልት ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ደፋ ቀና እያለ ይገኛል። ግንቦት ሰባት ከአፈጣጠሩ ህዝባዊ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ያልተዋጠለት ወያኔ የግንቦት ሰባት አመራሮችን በሞት ፍርድ ፣ ንቅናቄውን ደግሞ በአሸባሪነት በመፈረጅ የትግሉን እንቅስቃሴ ከጥንስሱ ለማዳፈን ተፍጨርጭሯል።
በቅርቡ በተለያዩ ሚዲያ እንደሰማነው ደግሞ የንቅናቄውን አካሄድ ለማኮላሸት እችልበታለሁ ብሎ ባመነው የአሸባሪነት ስራ በመሰማራት ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችን እስከ መግዛት ደርሷል። አፈጣጠሩ አሸባሪ የሆነው ወያኔ ይህንን መፈፀሙ የለመደው ተግባርና ያደገበት ባህሪው ቢሆንም መንግስት ነኝ እያለ በእነደዚህ ያለ የተልከሰከሰ ተግባር በመሰማራት አገር እያዋረደ ይገኛል።
ቦግንቦት ሰባት መሪዎች እና አባላቱ ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ፣ ንቅናቄውን በአሸባሪነት መፈረጅ አልፎ ተርፎም የግድያ ሙከራ ማድረግ የተፈለገውን ውጤት ያላመጣለት ወያኔ እንደራደር በሚል ግዜው ያለፈበት ብልጣብልጥነት ትግሉን ለመበረዝ መሞከሩ የእነዚህ ጎጠኞች አስተሳሰብ በምን ደረጃ ላይ እንዳለና ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀሩ የሚያሳይ ነው።
የግንቦት ሰባት ዓላማ በግልፅ የተቀመጠ የህዝቦች ጥያቄ ነው። በኢትዮጵያ ፍትሃዊና በእኩልነት የሚያምን አስተዳደር ያስፈልጋል። ዜጎች በእውቀታቸውና ችሎታቸው ሰርተው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ፤ ዜጎች በአገራቸው በየትኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሰው መኖር የሚችሉባት ኢትዮጵያ ፤ ዜጎች ሃሳባቸውን በሰለጠነ መንገድ የሚገልፁባት ኢትዮጵያ ፤ ዜጎች የተለየ አመለካከት ሲኖራቸው የማይሳደዱባት፣ የማይጋዙባት፣ የማይታሰሩባት ኢትዮጵያ ፤ ለሕግ ተገዥ የሆነ መንግስት የሚመራት ኢትዮጵያ ፤ ግለሰቦች ሳይሆኑ ሕግ የሚመራቸው ተቋማት የሚገኙባት ኢትዮጵያ። ይህ ነው የግንቦት ሰባት ራዕይ። አዎ እነዚህ ህዝቦችን በአንድ ልብ እንደ አንድ ሕዝብ ተባብሮ ለመኖር የሚያስችሉ ቁልፍ የሆኑ ጥያቄዎች ምላሽ እስካላገኙ ድረስ የሚፈለገው ዲሞክራሲና እድገት ይመጣል ብሎ መጠበቅ የቀን ቅዠት ነው።
ወያኔ የሽብርተኛ ሕግ በማለት ባወጣው ዜጎችን አሳቃቂ ሕግ መሠረት “ ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ከተወሰኑ ድርጅቶች ጋር በማንኛውም መልኩ ግንኙነት ያደረገ፣ሐሳብ የተለዋወጠ ግለሰብ ይሁን ድርጅት በሙሉ በሽብርተኛነት ይፈረጃል። ለፍርድም ይቀርባል።” ይላል። ይህ ህግ እንደ ህግ በተቀመጠበት ሁኔታ ወያኔ እንደራደር ብሎ በጓዳ በር መምጣቱ ስርዓቱ ምን ያህል የተምታታበትና የሚያደርገውን የማያውቅ፤ የተደናገሩና አዙሮ ማሰብ የተሳናቸው ግለሰቦች ስብስብ መሆኑን ያሳያል። ለእነርሱ ሕዝብ ማስተዳደር ማለት አንዱን ሕዝብ በጥላቻ ሰቅዞ በመያዝ ሌላኛው ከወንዝና ከቀበሌ በላይ እንዳያስብ በማድረግ አገራዊ ወኔን መስለብ ነው።
በማንኛውም መልኩ ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት መፍጠር አሸባሪ የሚያደርግ ሕግ ያወጣ የከፋፋይ ቡድን ይህን ‘የእንደራደር’ (እናደናግር) ጥያቄ ሲያቀርብ (ከልብ እንኳን ቢሆን) ወዲያውኑ እራሱኑ በሽብርተኝነት ያስፈርጀዋል። ይህ ካልሆነ ግን ከዚህ በፊት በስፋት እንደሚታወቀው ሕግ የሚወጣው የተወሰኑ የአገሪቱን ዜጎች ስቃይ ለማባባስና ለእንግልት ለመዳረግ እንደሆነና ከዚህ በተለየ መልኩ ሕግ የማይመለከታቸው ዜጎች እና ቡድኖች እንዳሉ የሚያሳይ ጥሩ ማስረጃ ነው።
ወያኔ ግንቦት ሰባትን ወንጀለኛ እና ሽብርተኛ ብሎ ለመፈረጅ ፓርላማ ሰብስቦ በሚድያ አደባባይ ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት ለያዥ ለገናዥ አስቸግሮ እየጮኽ እንደሆነ ሁሉ፤ የእንደራደር ጥያቄውንም ፓርላማ አቅርቦ በሚድያ ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ አለበት። ይህንን ካደረገ ETVም በሃያ ምናምን ዓመቱ አንድ ቁምነገር እንደሰራ ይቆጠርለት ነበር። ወያኔ አሁን የተያያዘው የልጆች ጨዋታ አኩኩሉ ከአንድ መንግስት ነኝ ባይ ቡድን እንደማይጠበቅ ተገንዝቦ ለህዝቦች እኩልነትና ሰላም የሚበጁ ስራዎችን መስራት ያስፈልገዋል። አዎ ንቅናቄው እንዳለው ወያኔ ከድርድሩ በፊት እዚያው መሬት ላይ ያሉትን ያፈጠጡ የዲሞክራሲና የሕዝቦች እኩልነት እጦት ጥያቄዎችን በመመለስ ከእንቅልፉ እንደነቃ ማሳየት መቻል አለበት።
ወያኔ አይኔን ግንባር ያርገው የተለመደ ክህደቱን እንዳይደረድር በአሁኑ ግዜ ያለውን የአገሪቱ ሁኔታ በጥቂቱ ማስታወስ ግድ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የወያኔ ማጎሪያ ስፍራዎች አሁንም በነጻነት ሲቃ በሚቃትቱ ሕዝቦች ተሞልተዋል። ኢትዮጵያ ዜጎች ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የመኖር ዋስትና በማጣት ነገን በጥርጣሬ የሚኖሩባት አገር ሆናለች። ኢትዮጵያ ከአንድ ህዝብ (ዘውግ)መወለድ ሃጥያት የሆነባት አገር ሆናለች። ኢትዮጵያ ዜጎች ሃሳባቸውን መግለፅ አይደለም ማሰብ አትችሉም የተባለባት አገር ሆናለች።በአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንደ አገር የዜግነት ዋስትና ወደ መቃብር ተወርውሮ ግለሰቦችና ቡድኖች ፈላጭ ቆራጭ የሆኑባት አገር ሆናለች። የአገሪቱ ሉዓላዊነት ተሸጦ የዓለም መሳለቂያ ሆናለች። ከዚህ በከፋ መልኩ ወያኔ ዜጎች በስደት የሚደርስባቸውን ስቃይ ‘ሕገወጦች’ በማለት ለባሰ ስቃይ በማጋለጥ የረከሰና የደነቆረ መግለጫ የሰጠ ቡድን ነው።
ስለዚህ ‘እንደራደር’ ብሎ አዲስ ድራማ በህዝቦች ስቃይ ላይ መተወን ትግሉን ወደ ጠነከረ ደረጃ ሊያሳድገው ካልሆነ በስተቀር ወያኔ ያሰበውን የማዘናጋት ህልም እውን አያደርገውም።
የዜጎች ድምፅ ይሰማ። መከፋፈል ይቁም። ጎጠኝነት ይቁም። አድልዎ ይቁም። መፈናቀል ይቁም። እስራት ፣ ግርፋት፣ እንግልት ይቁም። ሁሉም ዜጎች የዜግነታቸው ዋስትና ይረጋገጥ። ህዝቦች ከታሰሩበት ትናንሽ ‘የክልል’ እስር ቤት ይፈቱ። ማንኛውም ዜጋ ባመነበት እና በፈቀደው አስተዳደር ይተዳደር።
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!