ፊታችሁን ወደምስራቅ አማራ! (ሙሉአለም ገ/መድህን)

በምስራቅ አማራ ቀጣና ‹‹የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዮ ዞን›› በሚል አደረጃጀት ‹‹ከሚሴ›› ላይ በተዋቀረው መዋቅር ውስጥ እየተሰሩ ያሉ አሻጥሮችን የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች የሚያውቁት አይመስልም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ‹‹ልዮ ዞኑ›› እምነትን ተገን ያደረጉ አክራሪዎች መመሸጊያ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አካባቢውን በ‹ሳተላይት› እንምራው የሚሉ የኤርትራ ማሽላ አሳጫጅ መኮንን የነበሩ አካላት ማህበራዊ መሰረት ፍለጋ አይናቸውን ጥለውበታል፡፡ እናም ይሄ ‹‹ልዮ ዞን›› የጥቃት አድራሾች መመሸጊያና የስምሪት ማዕከል ሆኗል፡፡ ከዚህ ‹‹ልዮ ዞን›› የሚነሱ ኃይሎች ለሰሜን ሸዋ አጎራባች ወረዳዎች የጸጥታ ስጋት ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡ በርግጥ ይሄን አደጋ ዘግይተውም ቢሆን ያስተዋሉት የአዴፓ አመራሮች ችግሩን ለመቅረፍ ‹‹በኦሮሞ ብሄረሰብ እና ሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ሰላምን ለማጎልበት እና የህዝብ ደህንነት ለማረጋገጥ የፖለቲካና ድርጅት ስራዎች ማጠናከሪያ›› የሚል ዕቅድ አዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም ዕቅዱ ገቢር መሆን ሳይችል የሰኔ 15ቱ ክስተት ሂደቱን አደናቅፎታል፡፡ ቀድሞውንም የዘንዶው ጭንቅላት አልተቆረጠም ነበርና ዘንዶው ከጎሬው ለመውጣት የድኀረ-ሰኔ 15 ከባቢ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል፡፡

ከሰሞኑ የታየው የታጣቂ ኃይሎች ጥቃት አንደኛው መነሻቸው ከዚህ ‹‹ልዮ ዞን›› ሆኖ ታይቷል፡፡ ‹‹ታጣቂ ኃይሎች›› በሚል የገለጽኳቸው የኦነግ ሰራዊት ማለት ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ ግን የየትኛው ‹‹ኦነግ››[አመራር] የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያስፈልገዋል፡፡ እንደአሜባ ስምንት ቦታ ከተበጣጠሰው ኦነግ ውስጥ የትኞቹ አመራሮች ታጣቂ ቡድን አላቸው የትኞችስ የላቸውም የሚለው ጉዳይ ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡ (በጽሁፉ መደምደሚያ ላይ ጥቆማ ይገኛል)

ባለፈው ዓመት መጋቢት/ሚያዚያ 2011ዓ.ም ላይ ለደረሱ ጥቃቶች ከሚሴ ላይ ያሉ የ‹‹ልዮ ዞኑ›› አመራሮች የችግሩ ምንጭ የክልሉ ልዩ ኃይል የፈጠረው ነው የሚል አቋም በመያዝ በ OMN እና መሰል ጽንፈኛ የኦሮሞ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲያንጸባርቁ ታይቷል፡፡ አዴፓ እነዚህን አመራሮች ባህርዳር ድረስ ጠርቶ ቢያነጋግርም ከመሰል ጥፋታቸው ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡ ቀደም ሲል በሰሜን ሸዋ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ባሉ አመራሮች በኩል የችግሩ ምንጭ ኦነግ እና ታጣቂው ነው በማለታቸው እውነታውን ለማዳፈን የክልሉን ልዮ ኃይል በድፍረት ተጠያቂ ሊያደርጉ የሞከሩት የ‹‹ልዮ ዞኑ›› አመራሮች የጥቃቱ ተባባሪ መሆናቸው ተገማች ነበር፡፡ ከዚያ ጥቃት ጋር በተያያዘ መረጃ ተገንቶባቸው የተያዙ የ‹‹ልዮ ዞኑ›› አመራሮችና ሚሊሻዎች ጉዳይ ተዳፍኖ መቅረቱ ለሰሞኑ ጥቃት መንገድ ከፍቷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንበሳን ለአመንቲ ?? (እውነቱ  ቢሆን)

የክልሉ ልዩ ኃይል ወደ ‹‹ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን››ም ሆነ ወደ የትኛውም የክልሉ አካባቢ ተንቀሳቅሶ ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር የማንንም ፈቃድ እንደማይጠይቅ እየታወቀ፣ የክልሉን ልዮ ኃይል እንደ ባዕድ (በነሱ አጠራር ‹Ormi› ) በመቁጠር በተደጋጋሚ የሃሰት ውንጀላ በአደባባይ አሰምተዋል፡፡ ይሄ ለመሪ ድርጅቱ አዴፓ ከባድ ሊባል የሚችል የፖለቲካ ኪሳራ ነው፡፡ በስሩ ‹‹አለ›› በሚባል መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች የጸጥታ ኃይሉን ስም በሃሰት ሲያጠፉም ሆነ ወደ‹ልዮ ዞኑ›› አይግባ ሲሉ፣ ስምሪት ክልከላው ፖለቲካዊ አመጽ ስለመሆኑ የፖለቲካ ሀ…ሁ… ነው፡፡

በአካባቢው የሚገኘው ያልተመዘገበ መሳሪያ ላይ ቁጥጥር እና ዳሰሳዊ ጥናት ለማካሄድ ሲሞከር የዞኑ አስተዳደር መዋቅር ለዚህ ተባባሪ አለመሆኑ ይታወሳል፤ አመራሩ በየደረጃው ጠንካራ የድርጅት እና የመንግስት መዋቅር ፈጥሮ ችግሮችን ቀድሞ ከመከላከል ይልቅ የችግሩ ምንጭ ሲሆን ታይቷል፡፡ የፖለቲካ መመሪያም ሆነ ትዕዛዝ የሚቀበለው ከባህርዳር ሳይሆን አርሲ ላይ ቤዙን ካደረገው ኃይል ስለመሆኑ ፍንጭ የሚሰጡ ፍሬ ነገሮች ይታያሉ፡፡
ባለፈው ዓመት የኦሮሚያ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመው ስድስት ወራት ከሰሩ በኋላ ከኃላፊነታቸው የተነሱት ብ/ጀኔራል ከማል ገልቹ ከሚሴ ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት ላይ ናቸው፡፡

• ሰውየው የኦሮሞ አንድነት እና ነጻነት ግንባር (ኦአነግ) የተሰኘ ፓርቲ ይዘው ወደሀገር ቤት እንደገቡ ይታወቃል፡፡

• ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ የፓርቲ ፖለቲካ ስራውን የሙሉ ጊዜ አድርገውታል፡፡

• ዋነኛ ማህበራዊ መሰረታቸው አርሲ ላይ ቢሆንም፣ ተጨማሪ ማህበራዊ መሰረት ፍለጋ ‹ከሚሴ› ላይ ታድመዋል፡፡

• የ‹‹ልዮ ዞኑ›› መዋቅር ውስጥ ለፓርቲያቸው የሚሰሩ ሰዎችን በመመልመል ሂደት ላይ ስለመሆናቸው መረጃዎች አሉ፡፡

• ከሰሞኑ ‹‹ከሚሴን ወደ እናት ኦሮሚያ እንመልሳት›› የሚል አንድ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የድሮን ጥቃትን ለመከላከል - ተግባር ቁጥር ፪

• ይሄ ‹‹ኮሚቴ›› በስራ አጥ ወጣቶች የተሞላ ቢሆንም፣ ከውጭና ከውስጥ (ከዞኑ አመራር) ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዲቀበል፣ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ ሁኔታዎች ተመቻችተውለታል

• የሰሞኑ ጥቃት አድራሾች አንደኛው መነሻቸው ከዚህ አካባቢ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

• ከዚህ ቀደም አክራሪ የኦሮሞ ልሒቃን ምስራቅ አማራን በተመለከተ ‹‹ሰሜን ኦሮሚያ›› የሚል ትርክት ፈጥረው የኦነግን የህልም ካርታ ለማጽናት ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል፡፡

(ከዚህ በላይ የተመለከቱትን ነጠብጣቦች ስናገናኛቸው ምን ስዕል ይሰጡናል?)
ለሁሉም! ብ/ጀኔራል ከማል ገልቹ የኦሮሞ አንድነት እና ነጻነት ግንባር (ኦአነግ) የተሰኘውን ፓርቲያቸውን ይዘው በትኩረት እየሰሩ ነው፡፡ ከአርሲ ባልተናነሰ መልኩ ከሚሴ ላይ አይናቸውን ጥለዋል፡፡ በቦታው ‹‹የእኛ›› የሚሏቸው አባላትንም መልምለዋል፡፡ ከአመራሩም ጋር ሆነ ከቢሮክራሲው ጋር ቅርበት ለመፍጠር የከበዳቸው አይመስልም፡፡ ሰውየው በቀጣ ምርጫ ‹‹ልዮ ዞኑን›› ለመረከብ ከወዲሁ የፖለቲካ ስራዎችን እየሰሩ ናቸው፡፡ ይሄ ባይሳካ እንኳ ለድኀረ-ምርጫ ግጭት የተዘጋጀው ‹‹ከሚሴን ወደ እናት ኦሮሚያ እንመልሳት›› ባይ ‹‹ኮሚቴ›› ለ‹Insurgency› የተዘጋጀ ነውና ግጭት አይቀሬ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ‹‹ልዮ ዞኑ››ን ከኦሮሚያ ጋር ለማዋሃድ መልክዓ-ምድሩ ባይፈቅድ እንኳ፣ ዞኑ ከአፋር ክልል ጋር ተዋሳኝ በመሆኑ ጥያቄው ‹‹ወደአፋር ክልል እንጠቅለል›› ሊቀየር ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ‹‹የኩሽ ጥምረት›› የሚባለው አዲሱ ትርክት የፖለቲካ ዋጋ አይጠፋውም፡፡ ዓላማው የምስራቅ አማራን ግዛት ትርጉም አልባ ለማድረግ ያለመ ከመሆኑ አኳያ ሰዎቹ ስለ ‹Consequence› ፖለቲካው አያገባቸውም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጀርባ አንዴ በሃይማኖት ሌላ ጊዜ ‹‹ኦሮሙማ›› በሚል ሰባ ዓመት ሙሉ ተሞክሮ ባልተሳካ የፖለቲካ አጀንዳ ራሳቸውን የከለሉ የታንጎ ዳንሰኛ ፖለቲከኞች አሉበት፡፡ Twist …!
አፋር ‹‹የኩሽ›› ተረት ተረትን የማይቀበል ይልቁንስ ራሱን ከማዕከላዊው ፖለቲካ መነጠል የማይፈልግ በዛው ልክ ደግሞ ከቀንዱ ሀገራት (ጅቡቲና ኤርትራ ካሉ አፋሮች) መነጠል የማይሻ ሦስት ማዕዘን ቅርጹን በወል ትዝታ ማስጠበቅ የሚፈልግ መሆኑ ለአማራ ፖለቲካ ምቹ ዕድል ቢሆንም፤ ምስራቅ አማራ ላይ የዛሬን እና የመጪው ጊዜ የደህንነት ስጋቶችን ታሳቢ ያደረገ የጸጥታ እና የአመራር ስምሪት ያስፈልጋል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ በሰላሳ ሳንቲም መቀነሱ አነጋጋሪ እየሆነ ነው

1 Comment

  1. በመጀመርያ የአማራ ክልል የተባለው አማራዎች ብቻ የሚኖሩበት ማለት አይደለም፣ የተሰጠው ስም አሳሳች ስለሆነ “የሰሜን ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል” መባል ነበረበት። አማራ፣ ኦሮሞ፣ አገው፣ ቅማንት፣ ወይጦ፣ ሽናሻ፣ አርጎባ የመሳሰሉ ነባር ህዝቦች ያሉበት ክልል ነው። እነዚህ ህዝቦች ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ተፈጥሮአዊ መብት አላቸው።
    የአማራ ክልል ልዩ ሃይል የተባለው የአማራን የበላይነት በነዚህ ህዝቦች ላይ በጉልበት ለመጫን ብሎ ከሁሉም ጋር ሲላተም ይታያል፣ ጉሙዞችን እና ቅማንቶችን ሲጨፈጭፍ፣ ኦሮሞና አገው ላይ መዝመትን ዋና ስራው አድርጎአል። ይህን የአማራ የበላይነት ለመጫን የሚደረገውን የትጥቅ ዘመቻ መመከት የሚጠበቅ ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ነው። ከዚያም አልፎ በአማራ ክልል ባለስልጣናት እና ራሳቸውን በሾሙ አክራሪ የአማራ ጎበዝ አለቆች የሚፈጸመው ግፍ ከበዛ እና የክልሉ መንግስት ተጠሪነቱ ለሁሉም ካልሆነ፣ ወደ ሌላ ክልል ለመጠቃለል ሙሉ መብት አላቸው። ከሚሴ ኦሮሚያን ለመቀላቀል የግድ የጋራ ድንበር አስፈላጊ አይደለም።

    ያ እንዳይሆን ከጠብመንጃ ይልቅ ዲሞክራሲ እና ፈደራሊዝም ምን እንደሆኑ ካሁኑ ብታጠኑና ብትለማመዱ መልካም ነው።

Comments are closed.

Share