በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
የሕግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀ
የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት
አዲስ አበባ መስከረም 2006 ዓ.ም
ማውጫ
በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
የሕግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀ
የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት
አዲስ አበባ
መስከረም 2006 ዓ.ም
ማውጫ
ተ.ቁ ዋና ዋና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ገፅ
መግቢያ ————————————1
በአንድነት አባላት ላይ የተፈጸሙ ዋና ዋና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ——–2
1.1 2005 ዓ.ም ድረስ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ———–2
1.2 2004 ዓ.ም ድረስ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ———–6
1.3 በ2003 ዓ.ም የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች —————8
1.4 አመለካከትንና እና ሀሳብን በነፃ የመያዝ የመግለፅ መብት ላይ የተፈፀመ ጥሰት- 10
1.5 የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ——————————— 11
2. የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ——————————— 24
3. በሌሎች የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች– 25
4. በዜጎች ላይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ———26
4.1 በለገ-ጣፎ ለገ-ዳዴ ከተማ —————————26
4.2 በሞጆ አካባቢ ———————————– 28
4.3 በጉረ ፈርዳ አካባቢ ——————————– 29
4.4 በቤንቺ ማጂ ዞን ——————————— 30
4.5 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ——————31
4.6 በህዝበ ሙስሊም ———————————– 32
4.7 በቁጫ ህዝብ ላይ የተፈጸመ የስብአዊ መብት ጥሰት ——- 33
5. ማጠቃለያ —————————————- 34
6. አባሪ ———————————————
መግቢያ
ለዘመናት የዓለምን ህዝቦች ሲያሳስቡ ከኖሩት አበይት ጉዳዮች አንዱ የሰው ልጆች መብቶችና ነጻነቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የደረሰው ጭካኔና አረመኔነት የተሞላበት ኢሰብአዊ ጭፍጨፋና እልቂት ለአለም መንግስታትና ህዝቦች ታላቅ ትምህርት በመስጠቱ የሀገሮች ዳርድንበር ወይም ሉአላዊነት ሳያግዳቸው የሰው ልጅ በመሆናቸው ብቻ ሊከበሩላቸው የሚገቡ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶች ነጻነቶችና ክብሮችን የሚመለከቱ በርካታ አለም አቀፍ ስምምነቶችና ድንጋጌዎችን አውጀዋል፡፡ ተግባራዊነታቸውንም ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ የታደላቸው መሰረታዊ መብቶች አሉት በህይወት የመኖር፤ የአካል ደህንነት የማሰብ፤ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ የመዘዋወር መብቶች በምሳሌነት የሚገለጹ ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎችም መብቶች ከሰው ተፈጥሮ የሚመነጩ እንጂ መንግስት በህግ የሚቸራችው አይደሉም የሚለው እምነት በተባበሩት መንግስታት ሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ እንዲሁም በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ተቀባይነት ያገኘ ገዢ ሀሳብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶችን የሚመለከቱ አለም አቀፍ ሰነዶችንና ስምምነቶችን ተቀብላ በማጽደቅና በሕገ መንግስቷ ውስጥ በማካተት እውቅና ብትሰጥም የዜጎችን መብት በመጣስ ግን ከአለም አገሮች ሁሉ በግንባር ቀደምትነት ስሟ ተደጋግሞ ከሚነሱት አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን በፍፁም አምባገንነት እየገዛ የሚገኘው የኢህአዴግ መንግስትም ወታደራዊውን የደርግ መንግስት በጠመንጃ ሀይል አሽንፎ ከገረሰሰው ጊዜ ጀምሮ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ዘብ እንደሚቆም ደጋግሞ በመማል ከመናገር አልፎ በ1987 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ በዋለው የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ የሀገሪቱ የበላይ ህግ አንድ አካል በማድረግ እውቅና ቢሰጥም በዓለም አቀፍ ሰነዶችና በህገመንግስቱ እውቅና የተሰጣቸውን የዜጎች ሰብአዊ መብቶች በመሸራረፍና በመጣስ በሀገሪቱ ህዝቦች ላይ የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ወደር የማይገኝለት ሆኗል፡፡
የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከሚፈጽምባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም ዜጎች ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ሲሆኑ በተጨማሪም ኢህአዴግንና አገዛዙን ይቃወማሉ ተብለው በሚጠረጠሩና በፈረጃቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል፡፡ በመሆኑም የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) አባላትና ደጋፊዎች የኢህአዴግ አገዛዝ ኢሰብአዊ ድርጊት ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች ሲሆኑ በዋናነት ከተፈጸምባቸው የመብት ጥሰቶች መካከል አካል ማጉደል ድብደባ እገታ ህገወጥ እስር ስወራና የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ኢህአዴግ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲታረም ለማድረግና ለማጋለጥ እንዲሁም የሚፈጽመውን ኢሰብአዊ ድርጊት የአገር አቀፍና የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት፤ ለሰብአዊ መብት የሚቆረቆሩ መንግስታትና ግለሰቦች ጭምር በኢህአዴግ መንግስት ላይ ግፊትና ተፅእኖ እንዲያደርጉ ለማሳወቅ የአንድነት ፓርቲ በህግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ በኩል ይህንን የሰብአዊ መብት ሪፖረት አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርቱ በዋናነት በአራት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል በአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ስም ዝርዝር መቼ እንዴት እና የድርጊቱ ፈጻሚ አካላትና ማንነት ዘርዝሮ ይዟል፡፡ በሁለተኛው ክፍል በሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች አባላትና ደጋፊዎች ላይ ያተኩራል፡፡ የሪፖርቱ ክፍል ሶስት በፖለቲካና የህሊና እስረኞች ላይ ታስረው በሚገኙባቸው ማረሚያ ቤቶች ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ የሚያስረዳ ሲሆን ክፍል አራት ደግሞ በዜጎች ላይ የደረሱ ዋና ዋና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የጉዳቱን ዓይነት መቼ የትና በማን እንደተፈጸመ በመዘርዘር ይገልጻል በመጨረሻም ማጠቃለያ ሀሳብን አካቷል፡፡
ክፍል አንድ
በአንድነት አባላት ላይ የተፈጸሙ ዋና ዋና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
1.1 በ2005 ዓ.ም የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
1. አቶ ሀሰን ሰይድ
የወረዳ 28 የምርጫ ክልል አንድነት ኮሚቴ ሰበሳቢ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ከብሄዊ የመረጃና ደህንነት ሠራተኞች የዛቻና ማስፈራሪያ ተግባሪት ሲፈፀምባቸው ከቆዩ በኋላ በ19/02/2005 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ላይ የመኖሪያ ቤታቸው በፖሊስና በደህንነት ሰራተኞች ተከቦ እጅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ከሰዓት እላፊ ውጭ አልሰጥም ሲነጋ መያዝ ትችላላችሁ ማለታቸውን በስልክ ሁኔታውን በወቅቱ ለወረዳው ምክትል ሰብሳቢ ማሳወቃቸውን ከአካባቢ መረጀ ተረጋግጧል፡፡
2. በፓርቲው ከፍተኛ አመራር ላይ የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት
1. አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን የብሔራዊ ም/ቤት አፈጉባኤ
2. አቶ በላይ ፍቃደ የኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ
3. አቶ ስዩም መንገሻ የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ
4. አቶ ፀጋዬ አላምረው የፋይናንስ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ
ነሐሴ 26 ቀን 2004 ዓ.ም በሰበታ ከተማ ነዋሪ የሆኑትን ጓደኛቸውን ጠይቀው ሲመለሱ ከቀኑ 11፡30 ሰዓት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የአቶ በላይ ፍቃደን መኪና የአገር ውስጥ የመረጃና ደህንነት ሰራተኞች በመኪና ከኃላና ከፊት በማጀብ ከሰበታ ከተማ መውጫ ላይ በማስቆም ከመኪና በማስወረድ መኪናዋን ከመፈተሻቸውም በላይ የፓርቲውን አመራሮች ወደ አንድ ኮንቴነርና ጨለማ ቦታ በመውሰድ አካላዊ ፍተሻ ከህግ አግባብ ውጭ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ስድብ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰውባቸዋል አስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ድረስም ማጉላላትና ማንገላታት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በተጠቀሰው ቀን ሰዓትና ቦታ ላይ በሌላ ሚኒባስ መኪና የነበሩትን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች
1. አቶ ደምሴ መንግስቱ ሥ/አስፈጻሚና የህግና ሰብአዊ መብቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
2. አቶ ክብረት ሀይሌ የብ/ም/ቤት አባልና የህግና ሰብአዊ መብቶች ቋሚ ኮሚቴ አባል
3. አቶ ወንደሰን ክንፈ የወረዳ 04 አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ እና
የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አባል
4. አቶ ፋንታሁን ብርሀኑ የወረዳ 11 አንድነት ኮሚቴ የሕ/ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ
5. አቶ ድንቁ ወ/ማርያም የአንድነት ፓርቲ ብ/ም/ቤት አባል
6. አቶ ዲንሰፋ ———የሚኒባስ ሹፌር እና ስሙ ያልታወቀ የሚኒባስ ረዳት
ወደ አ/አባባ በመንቀሳቀስ ላይ በነበሩበት ወቅት የከተማው ፖሊስና ትራፊክ ፖሊስ አባላት የሆኑ የሚኒባሱን ሹፌርና ረዳት በማስወረድ እነዚህ ከአ/አበባ ጭናችሁ ያመጣሀቸው ሰዎች ምን እየተነጋገሩ እንደነበር ንገሩን በማለት ማስፈራራትና ዛቻ ከፈጸሙባቸው በኃላ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለጻቸው መኪናውን በማስገደድ ወደ ሰበታ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሄድ ከማድረግም በላይ በመኪናው ውስጥ የነበሩትን ሰዎች በማስገደድ ወደ ፖሊስ ጣቢያው አስገቧቸው፡፡ በወቅቱ አቶ ደምሴ መንግስቱ ይህ ተግባር ከህግ አግባብ ውጭ ነው በማለት በመከራከራቸው ተሸክመውና እያዳፉ ወደ ጣቢያው ግቢ አስገብተዋቸዋል፡፡በወቅቱ የጣቢያው አዛዥ ም/ኮማንደር ሃይልዬ አቶ ደምሴ መንግስቱን ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ሌሎቹ ላይ ደግሞ የማስፈራራት ዛቻ እንዲሁም ስድብ በመፈጸም የአካል እና የመንፈስ ጉዳት አድርሰውባቸዋል፡፡ የያዙትን መኪና በመፈተሽ፤ አስገድደው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ያለምንም ወንጀል በማገት በመኪናው ሹፌርና በአንድነት ሥራ አስፈጻሚና የብሔራዊ ም/ቤት አባላት ላይ ከአራት ሰዓታት በላይ ማዋከብ ማጉላላትና ዛቻን የመሳሰሉ የመብት ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል፡፡በመጨረሻም ከምሽቱ 04፡00 ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡
3. አቶ ጌቴ መቅጫ
በምስራቅ ጎጃም ዞን የጉምድዌ ወረዳ ምርጫ ክልል አንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ ሲሆኑ የካቲት 26/2005 ዓ.ም የአንድነት ፓርቲ አባል በመሆናቸው ብቻ በሚኖሩበት ቀበሌ 07 ሊቀመንበር ድብደባ ተፈፅሞባቸው የአካል ጉዳት (የእጅ ስብራት አደጋ) ደርሶባቸዋል በተጨማሪም በወቅቱ የገንዘብ ዘረፋም ተፈጽሞባቸዋል (150 ብር)
4. አቶ ምቹ ተፈራና መስፍን ፀጋው
በምስራቅ ጎጃም ዞን የጉምደዌ ወረዳ አንድነት ፓርቲ አባላት ሲሆኑ መጋቢት 07/2005 ዓ.ም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ብቻ ከወረዳው ሰብሳቢ በመቀጠል በብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት ሰራተኞች በነጭ ኮብራ መኪና አፍነው ከወሰዷቸው በኃላ እስካሁን የት እንዳደረሷቸው አልታወቀም፡፡
5. አቶ ነጋ አበጀ
በምዕራብ ጎጃም ዞን የአንድነት ፓርቲ ሥ/አስፈጻሚ ኮሚቴ ፀሀፊ ሲሆን የብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት ሰራተኞች ለሶስት ቀናት በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ሲከታተሉት ከቆዩ በኃላ መጋቢት 06/2005 ዓ.ም በመኪና አፍነው ወስደውታል፤ የት እንዳደረሱት በትክክል አይታወቅም፡፡ ከላይ የተገለጸው መረጃ ከተጠናቀረ በኃላ አቶ ነጋ አበጀ ሚያዝያ 08/2005 ዓ.ም ስትፈለግ ትመጣለህ በሚል ያለምንም የፍርድ ሂደት ከአንድ ወር በኃላ ተፈቷል፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ ወደ ባህርዳር ፖሊስ ጣቢያ ቁጥር ዘጠኝ ተወስዶ ታስሮ የነበረ ሲሆን ወደ አልታወቀ እስር ቤት አይኑን ተሸፍኖ ተወስዶ መመለሱንም ገልጿል፡፡
6. አቶ አንጋው ተገኝ
በሰሜን ጎንደር ዞን የታች አርማጭሆ ወረዳ የአንድነት ፓርቲ ሥ/አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሆን መጋቢት 13/2005 ዓ.ም የአንድነት ፓርቲ አባል በመሆኑ ብቻ የሳንጃ ፖሊስ ጣቢያ ባልደረቦች አስገድደውና አፍነው በመውሰድ በሳንጃ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁንም ጉዳዩ ለሚመለከትው የዳኝነት አካል አልቀረበም ከእስርም አልተፈታም፡፡ ከላይ የተገለጸው መረጃ ከተጠናቀረ በኃላ አቶ አንጋው ተገኝ መጋቢት 22/2005 ዓ.ም ስትፈለግ ትመጣለህ በሚል ያለምንም የፍርድ ሂደት ተፈቷል፡፡ ሲለቀቅም ከአሁን በኃላ የገዢው ፓርቲ ልሳኖችን ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ጋዜጦችን ማንበብ እና ገዢውን ፓርቲ መቃወም እንደሌለበት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡
7. አቶ አለሙ ታፈሰ
በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ብሔር ልዩ ዞን (ከሚሴ) የአንድነት ፓርቲ ኮሚቴ አባል ሲሆን የካቲት 13/2005 ዓ.ም በከሚሴ ከተማ ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ካፊቴሪያ ውስጥ ቦንብ ስለፈነዳ በአሸባሪነት ጠርጥሬሀለሁ በማለት የአካባቢው ፖሊስ ከህግ አግባብ ውጭ አስረዋቸዋል፡፡ እስካሁንም ጉዳዩ ለሚመለከትው የዳኝነት አካል አልቀረበም ከእስርም አልተፈታም፡፡ በዚሁ ልዩ ዞን በተለይ በከሚሴ ከተማ በፓርቲው አባላት ላይ በተደጋጋሚ ወከባ እንግልት አድሎ ማስፈራራትና ዛቻ በኢህአዴግ ካድሬዎችና ተሿሚዎች እየተፈጸመ ይገኛል፡፡
8. አቶ ፀጋዬ እሸቴ
በሰሜን ጎንደር ዞን በደባርቅ ወረዳ ነዋሪ እና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባል የሰሜን ጎንደር ዞን አንድነት ፓርቲ በጠራው ስብሰባ ላይ ለመካፈል በመሄድ ላይ በነበሩበት ወቅት መጋቢት 08 2005 ዓ.ም ተይዘው ለስር ተዳርገዋል፡፡ ከላይ የተገለጸው መረጃ ከተጠናቀረ በኃላ አቶ ፀጋዬ እሸቴ መጋቢት 10/2005 ዓ.ም ስትፈለግ ትመጣለህ በሚል ያለምንም የፍርድ ሂደት ተፈቷል፡፡
9. በኮንሶ ልዩ ወረዳና በደራሼ ዞን የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
1. አቶ ትኩ ከትክተው ————– የአንድነት ፓርቲ አባል
2. አቶ ኩበያ ኪራሞ ————— የአንድነት ፓርቲ አባል
3. አቶ መጫሮ አሌ —————- የአንድነት ፓርቲ አባል
4. መ/ር ካሱ ቱታ —————- የአንድነት ፓርቲ የወጣቶች ተጠሪ
5. አቶ ዱባ ቱታ ——————የአንድነት ፓርቲ አባል
6. አቶ ጎዳኔ ኩልሴ —————–የአንድነት ፓርቲ አባል
7. አቶ ወገኔ ኩልሴ —————–የአንድነት ፓርቲ አባል
– የአንድነት ፓርቲ አባላት በመሆናቸው የተነሳ መጋቢት 13/2005 ዓ.ም የልማትና የምርጫ እንቅፋት ናችሁ ምክንያቱም የአንድነት/መድረክ አባላት ናችሁ በሚል ሰበብ የኮንሶ ልዩ ወረዳ ፖሊሶች ከህግ አግባብ ውጭ አስገድደው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰዷቸው በኃላ በጣቢያው አዛዥ አያኖ ግርግዴ ትዕዛዝ እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡ እስካሁንም ጉዳዩ ለሚመለከትው የዳኝነት አካል አልቀረበም ከእስርም አልተፈቱም፡፡
በተጨማሪም የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ዜጎች መታሰራቸውን ከኮንሶ ልዩ ወረዳና ከደራሼ ዞን አንድነት ፓርቲ ኮሚቴዎች የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል፡፡
10.አቶ ግርጃ ሐለኬ ሎኮ
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የቦሬ ምርጫ ክልል የአንድነት ፓርቲ አባልና አስተባባሪ በነሀሴ 9 ቀን 2005 ዓ.ም በአካባቢው የፓርቲ ስራ ላይ በነበሩበት ቀን ለምን ታደራጃለህ አሸባሪ ነህ በማለት በፖሊስ ተይዞ በይርባ ሙዳ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ይገኛል፡፡ አቶ ግርጃ ሐለኬ በመምህርነት ሞያ ለመሰማራት የኮሌጅ ትምህርቱን እየተከታተለ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የማሰቃየት እርምጃ በተለይ ድብደባ እየተፈፀመበት ይገኛል፡፡ በወቅቱ የድርጅቱ ንብረቶች የሆኑ
- ከምርጫ ቦርድ የተሰጠ የፓርቲው ፈቃድ
- የ 53 ሙሉ አባላት ፎርም (የተሞላ) እና ያልተሞላ 105 ፎርም
- የ 33 እጩ አባላት ፎርም (የተሞላ) እና ያልተሞላ 67 ፎርም
- ብር 953.50
- 114 የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች
እንዲሁም አቶ ግርጃ ሐለኬ ንብረት የሆኑ ሻንጣና ሌሎች ንብረቶች በፖሊስ ተወስደዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች አምስት የአንድነት አባላት ለደህንነታቸው ከፍተኛ ስጋት ላይ ናቸው፡፡
1.2 በ2004 ዓ.ም የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
- 10. አቶ መኳንንት ብርሃኑ
የወረዳ 28 የምርጫ ክልል አንድነት ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው በማያገለግሉበት ወቅት በየካቲት 16/2004ዓ.መ ከመንገድ ላይ በደህንነት ሰራተኞች (ስምንት ሰዎች አቶ አባተ፣ አቶ አያልነህ እና ሌሎች 6 ማንነታቸው ያልተወቀ ሰዎች) ወደ ሲምሲ አካባቢ በመውስድ እግርና እጃቸውን በካቴና በማሰር፤ ሽጉጥ በአፋቸው ውስጥ በመደቀን፣ ቀዝቃዛ ውሃ በመድፋት፣ ልብስ እንዳይቀይሩ በማድረግ ኢሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ ገርጀ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ በወቅቱ ፍ/ቤት ባለማቅረብ እና የምርመራ ጊዜውን በማራዘም እንግልት ማጉላላት እና ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያዋርድ አያያዝ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ አቶ መኳንንት ብርሃኑ እስከ መጋቢት 3/2004 ዓ.ም ድረስ ያላግባብ ያለምንም ወንጀል ታስረው ከቆዩ በኋላ በዋስ ተለቀዋል እስከአሁንም በወንጀል ክስ አልተመሰረተባቸውም፡፡
- 11. አቶ ቢንያም ገናናው
የአንድነት ፓርቲ የወረዳ 21/22 ህ/ግንኘነት ኃላፊ የነበሩ በተለያዩ ወቅቶች በተለይ በየካቲት 2004 ዓ.ም በእሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ማዋከብ ማስፈራራት ዛቻና መረጃ አቀብለን በሚል ምክንያት በደል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በዚህም ሰብአዊ ክብራቸውና የፈለጉትን የፖለቲካ አመለካከት የመያዝ መብታቸው ተገፏል፡፡ በአሁኑ ሰአት ለህይወታቸው በመስጋት ከፓርቲ ሀላፊነታቸው ለቀዋል፡
- 12. አቶ በሽር ባሳዬ
አቶ በሽር በሳዬ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በሊሆር ቀበሌ ገ/ማህበር (ሀገረ ማርያም) ነዋሪ እና የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባልና አመራር ሲሆኑ የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን በወረዳው ለሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች ለማሰራጨት በሚጓዙበት ጊዜ በአካባቢው ካድሬዎች በመያዝ ከመጋቢት 20/2004 እስከ ሀምሌ 27/2004 ዓ.ም ድረስ በእስር ከአራት ወራት በላይ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ክስ ተመስርቶባቸው በወረዳው ፍ/ቤት የአንድ ዓመት እስራት ቢወስንባቸውም ይግባኝ በመጠየቅ የኦሮሚያ ከፍተኛ ፍ/ቤት በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በተሰማሩበት ቡና ተረክቦ በመሸጥ ስራ የአካባቢው ካድሬዎች ቡና አምራች ገበሬዎች ለአቶ በሽር ቡና እንዳታስረክቡ በማለት ሰርቶ የመኖር መብታቸው ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ በተደጋጋሚ በሚደረግባቸው ጫና ምክንያት በሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ የኢኮኖሚና የመኖር መብት ላይ ከፍተኛ ስጋት አሳድረውባቸዋል፡፡
- ከላይ በተጠቀሰው ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ያታኔ ምትኩ እና ወጣት ባናታ በሌላ
ሀምሌ 11/2004 ዓ.መ በአካባቢው ፖሊስ ተይዘው የታሰሩ ሲሆን የተያዙበት ምክንያትም የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ሞተዋል ብላችሁ አስወርታችኋላ የሚል የፈጠራ ክስ ነው፡፡ ለአምስትና ሰባት ቀናት ታሰረው የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ከተፈጸመባቸው በኋላ ፍ/ቤት በዋስ ፈቷቸዋል፡፡
- 14. የ፶ አለቃ ሽፈራው ተሰማ
በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ነዋሪ የሆኑና የምርጫ ወረዳ 26/27 የአንድነት ኮሚቴ ፀሀፊ ሲሆኑ ሰኔ 7/2004 ዓ.ም ለ25 ዓመታት ከሚኖሩበትና ከሰሩት ቤት በአቃቄ ክ/ከተማ ወረዳ 06 አስተዳደር ያለማስጠንቀቂያ እና ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤታቸው ከነንብረታቸው ታሽጎ እና ለሌላ ግለሰብ ተሰጥቶ ያለመጠለያ ከነቤተሰባቸው ተጥለው ፤ ፍትህ ተነፍገው በችግር ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንድነት ፓርቲ የህግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ የህግ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ በኩል በተሰጣቸው የህግ የምክር አገልግሎት መሰረት የኢህአዴግ ካድሬዎችና አመራሮች እንዲሁም የመንግስት አስፈፃሚ አካላትና ሹመኞች የተፈፀሙባቸውን በደል በህግ አግባብ ለሚመለከተው ፍ/ቤት ክስ እንዲመሰርቱ ተደርጎ የአቃቄ ቃሊቲ የመጀመሪያ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት፡-
1. ረዳት ሳጅን ሀብታሙ ገረመው በአንድ ወር እስራት እና ሁለት አመት በገደብ
2. አቶ ኃይለስላሴ ዓለምሰገድ የግንባታና ዲዛይን ኃላፊ በስድስት ወር እስራትና ሁለት ዓመት በገደብ
3. ረዳት ሳጅን ገብረ መስቀል ገብሬ ክስ ተመስርቶበትና ተመስክሮበት እያለ ለጊዜው ከአካባቢው ተሰውሯል፡፡
የሀምሳ አለቃ ሽፈራው ተሰማ ተከራይተውት የነበረውን ቤት የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተቀራምተውታል፡፡ በዚሁ መሰረት ዋናውን ቤት አቶ ዘብረኸ ያይኖም የአቃቄ ቃሊቲ ክ/ከተማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ሀላፊ እና ሰርቪስ ቤቶቹን ደግሞ ለአቶ ገበየሁ ቸኮል የወረዳ 06 ካድሬና የካቤኒ ኃላፊ ተሰጥቷል፡፡ ይሁንና የፍ/ቤቱ ውሳኔ የመኖሪያ ቤታቸውና ንብረታቸው ተመልሶላቸው በመጠለያ እጦት በችግር ከሚሰቃዩት ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲመለሱ ባለመደረጉ አሁንም የፍትህ ያለህ በማለት በችግር ላይ ናቸው፡፡
- 15. በህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ወቅት የተፈጸመ የሰብአዊ መብት ጥሰት
1. ወ/ሮ እመቤት ሀይሌ …. የወረደ 12/13 አንድነት ኮሚቴ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ
2. አቶ ነብዩ ባዘዘው ……… የወረዳ 12/13 አንድነት ኮሚቴ የሕ/ግንኙት ጉዳይ ኃላፊ
3. አቶ መኳንንተ ብርሃኑ … የወረዳ 28 አንድነት ኮሚቴ የሕ/ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ
4. አቶ ቅዱስ ………………. የአንድነት ወጣቶች ሥ/አስፈጻሚ አባል
5. አቶ አበበ ቁምላቸው …… የወረደ 28 አንድነት ኮሚቴ የሕ/ግንኙት ጉዳየ ኃላፊ
6. አቶ ደምሴ መንግስቱ …..ሥ/አስፈጻሚና የህግና ሰብአዊ መብቶች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
ከላይ ስማቸው የተጠቀሰው አባላት የምርጫ ወረዳ 12/13 አንድነት ኮሚቴ በወቀታዊ ጉዳዮች ላይ ከደጋፊዎችና ከወረዳው ነዋሪዎች ጋር ለመወያየት ላዘጋጀውና ከሚመለከተው የመንግስት አካል የህዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ወይም ፍቃድ በመያዝ የቅስቀሳ ስራ በሚያካሂዱትበት ወቅት ሀምሌ 13/2004 ዓ.ም በየካ ክ/ከተማ በሚገኘው ወረዳ 4 አሰተዳደርና በፈረንሳይ አካባቢ ንዑስ ማዘዣ ጣቢያ የፖሊስ አባላት አማካኝነት አነዲሁም በሀምሌ 14/2004 ዓ.ም በፈረንሳይ ኬላ አካባቢ በፌደራል ፖሊስ በመወሰድ ለሰባት ሰአታት ያክል በፈረንሳይ ፖሊስ ጣቢያ ታግተው ዛቻ ማስፈራራት እና እንግልት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በዚህ ድርጊት ፓርቲው ህግን አክበሮ በነጻ የመንቀሳቀስ ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር የመወያየት መብት ላይና በአባላት ሰብአዊ ክብር ለምሳሌ እንደ የመሰብሰብ የመደራጀት መብቶች ላይ ጥሰቶች ተፈጽሟል፡፡
- 16. አሊ መሀመድ ከድር
በከሚሴ ከተማ ቀበሌ 01 ነዋሪ እና የአንድነት አባል ሲሆን በፌደራል ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሀምሌ 16/2004 ዓ.ም ከምሽቱ 02 ሰዓት እስከ 05 ሰዓት ድረስ የመኖሪያ ቤታቸውን ከመፈተሹም በላይ ዛቻ ማስፈራሪያና እንግልት በቤተሰባቸው ላይ ተፈጽሟል፡፡
1.3 በ2003 ዓ.ም የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
- 17. አቶ አንዷለም አራጌና መ/ር ናትናኤል መኮንን
በመስከረም 3/2003 ዓ.ም በፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊና ም/ሊቀመንበር አቶ አንዷለም አራጌና የብሔራዊ ም/ቤት አባልና ነባር ታጋይ መ/ር ናትናኤል መኮንን ላይ ሽብርተኛ በሚል ቅጽል ስም በወንጀሉ ተጠርጥረዋል በማለት ፓርቲውን ለማዳከም፤ ወጣት ታጋዮች እንዳያቆጠቁጡ እና በሰላማዊ ትግሉ ላይ ዜጎች እምነት እንዲያጡ ለማድረግ የኢህአዴግ መንግስት አኬልዳማ የሚል ድራማ እና በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ሰብአዊ መብትና ክብር የሚያዋርድ ተግባር በመፈፀም ለረጅም ግዜ በቆየው የምርመራ ሂደትም ሆነ በፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተደጋጋሚ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡-
– ድብደባና ቶርቸር
– በጨለማ ቤት ለረጅም ግዜ ማሰር
– በቂ ህክምና በወቅቱ እንዳያገኙ ማድረግ
– በእስረኛ ማስደብደብ
– ዘመድ፤ ጓደኛና የሀይማኖት አባት እንዲሁም ሌሎች ሊጠይቋቸው የሚፈልጉ ወዳጆቻቸውን እንዳይጎበኟቸው ማድረግ
– አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዳይደርሷቸው ማድረግ እንደ መጻህፍት
- 18. አቶ ጋሪያ ወልዴ
በቤንች ማጂ ዞን በ29/06/03 ዓ.ም የአንድነት አባልና በ2002 ምርጫ ታዛቢ በመሆናቸው ብቻ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የስጋ ንግድ ድርጅታቸው የተዘጋባቸው የሰጋ ቤት ንግድ ድርጅታቸው ሰራተኛ የነበረው ሰው በህመም ምክንያት ሆስፒታል ውስጥ መሞቱ እየታወቀ ደበድበህ ገድለሀል በሚል ሰበብ ከእነልጆቻቸው ለእስር የተዳረጉና የንግድ ድርጅታቸው እንዲዘጋና ከነቤተሰባቻቸው ለችግር እንዲዳረጉ ሆኗል፡፡
- መ/ር ፈይሳ ገመቹ
በክብረመንግስት ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በ 12/07/03 ከሌሊቱ 7 ሰዓት የሰሌደ ቁጥሩ መከ 1446 በሆነ መኪና ተገድዶ (ታፍኖ) በመውሰድ ለእሰር ተዳርጓል፡፡
- አቶ ጆቢር ዋቆ
በደርጫ ደማ ወረዳ በ15/07/03 ዓ.ም የወረዳው አንድነት አባልና ተወካይ በመሆኑ ብቻ ከሌሊቱ 6 ሰዓት የሰሌዳ ቁጥር ፖሊስ 0142 በሆነ መኪና ተገድደው ከመኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ ለእስር ተዳርገዋል፡፡
- 21. አቶ ገዛኸኝ መኮንን
በክብረ መንግሰት ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ ሲሆኑ በ01/07/03 ዓ.ም ከሚኖርበት የቀበሌ ቤት ከዘጠኝ ቤተሰባቸው ጋር ተገድደው ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡና መጠለያ አልባ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
- 22. አቶ አለባቸው አሰፋ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ከተማ የካቲት 2003 ዓ.መ በምሽት ፖሊስ ጣቢ ተወስደው በአደራ ለአንድ ቀን ታሰረው ካደሩ በኋላ የፖሊስ ኮሚሽነሩና የመረጃ ክፍል ኃላፊው ዘንድ ቀርበው በማስጠንቀቂያ ለጊዜው ሊለቀቁ ችለዋል፡፡
- 23. አቶ ኡመድ አፋአስ ዓሊ
በአፋር ከልል አሚባራ በ04/09/03 ዓ.ም ከአካባቢው ወደ ኤርትራ የሚሄዱ ሰዎች ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ሰበብ በጸጥታ ሰዎች ከመዋከባቸው በላይ ወደ አዋሽ ተወስደው ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
- 24. አቶ ብርሃኑ ፋቄ
በሀዋሳ ከተማ ዙሪያ በ26/08/03 ሆን ተበሎ በተጠነሰሰ ሴራ በሁለት ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን አንደኛው እጃቸውን ወጥሮ በመያዝ ሌላኛው ደግሞ በጩቤ ወግቶ ለማምለጥ ሲሞክሩ በአካባቢው ነዋሪዎች ትብበር ከተያዙ በኃላ ሴራው የተቀነባበረው በገዥው ፓርቲ አባላት መሆኑን የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
- 25. አቶ በላቸው ቢያብስ
የምስራቅ ጎጃም ነዋሪ በ05/07/03 ዓ.ም ጀምሮ የዞኑ አንድነት ፓርቱ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊና አባል በመናቸው በቻ ከህግ አግባብ ውጨ ለእስር ተዳርገዋል፡፡
- 26. አቶ ካሳ ገብርዬ
በሰሜን ወሎ ነዋሪ በ 23/07/03 ዓ.ም ደንቡ በሚፈቅድላቸው መሰረት ሰራ ተወዳድረው ቢያልፉም የአንድነት አባል በመሆናቸው ብቻ በስራው ላይ ሊቀጠሩ አልቻሉም፡፡ ቅሬታቸውን ለአቤቱታ (ቅሬታ) ሰሚ ኮሚቴ አቀርበው ያቀረቡት አቤቱታ ትክክለኛነቱ ላይ ኮሚቴው ቢስማማም በስራው ላይ እንዲቀጠሩ ግን ውሳኔ ለመስጠት አልቻሉም፡፡
1.4 አመለካከትንና እና ሀሳብን በነፃ የመያዝ የመግለፅ መብት ላይ የተፈፀሙ ጥሰቶች
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ሕገ መንግስት አዋጅ ቁ 1/1987 ክፍል ሁለት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚለው ስር አንቀጽ 29(2) ላይ “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሁፍ ወይም በህትመት፤ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፤ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶች ያካትታል” በሚል በግልፅ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ የህገ መንግስት አንቀጽ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁ 590/2000 አንቀጽ 4 የመገናኛ ብዙሀን ነጻነት እውቅና አግኝቷል፡፡ ቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ ነው በማለት የፕሬስ ነጻነትን አረጋግጦ እናገኛለን፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከዚህ በላይ በተመለከተው የሕገመንግስት አንቀጽ ላይ እና በአዋጅ ቁ 590/2000 የተጠበቁ ህገመንግስታዊ መብቶችን መሰረት በማድረግ የፖሊቲካ ፕሮግራሙንና ደንቡን ለአባላቱ፤ ለደጋፊዎቹና ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ በማስተዋወቅ በሀገር አቀፍ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ በዲሞክራሲያዊ ስርአት የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር “ፍኖተ ነፃነት” በሚል ጋዜጣ በማሳተም በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ በማሰራጨት ሀሳቡን ሲግልጽ ነበር፡፡ ህግን በወረቀት ላይ መጻፍ እንጂ ማክበር እና መጠበቅ የማያውቀው አምባገነኑን የኢህዴግ መንግስት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ላይ ጥበቃ ያገኘውን የአመላከከት እና ሀሳብን በነጻ የመያዝና የመግለፅ መብት በሚጥስ ሁኔታ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነውን “ፍኖታ ነፃነት” ጋዜጣን በየትኛውም ማተሚያ ቤት ውስጥ እንዳይታተም በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ክልከላ በማድረግ ህትመቱ እንዲቋረጥ አድርጓል ይህ የአምባገነኑ የኢህአዴግ ድርጊት የሚያረጋግጠው በኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ተጠናክሮ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲሰፍን ምንም አይነት ፍላጎት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ይህ የአንድነት ልሳን የሆነው “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ ህትመት በአምባገነኑ መንግስት ጣልቃ ገብነት በመቋረጡ ምክንያት የአንድነት አባላት፤ ደጋፊዎችና ዜጎች ሀሳባቸውን በጋዜጣው ላይ የመግለጽ መብታቸው ተጥሷል፡፡ አንድነት ፓርቲም ጋዜጣውን ተጠቅሞ ፕሮግራሙን፤ ፖሊሲዎቹን፤ ደንቡን፤ ዕቅዱን፤ አላማውን እና የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለደጋፊዎቹ ለአባላቱና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዳያስተዋውቅና እንዳያሰራጭ በአጠቃላይም ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሀሳቦችና አመለካከቶች በነጻ በህዝቡ ውስጥ እንዳያንሸራሽሩ በማድረግ ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱና እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የመንቀሳቀስ ህጋዊ መብቱ ተጥሷል፡፡
1.5 የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል አፋኝ የሆነውን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆኑ እንዲሻር በሚሊዮን የሚቆጠር ፊርማ ለማሰባሰብ አንድነት ለሶስት ወራት የህዝባዊ ንቅናቄ ፕሮግራም አውጥቶ ከሰኔ ወር መጀመሪያ ጀምሮ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ህጋዊ በሆነ አካሄድ ይህ ኢ-ህገመንግስታዊ አዋጅ ለማሰረዝ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ በፓርቲው አባላት ላይ ሰፊ የእስር፤ የማወከብና የማሰቃየት እርምጃ በፀጥታ ሀይሎችና በኢህአዴግ ካድሬዎች በመፈፀም ላይ ነው፡፡ የዚህ እርምጃ ዋና አላማ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ክብር እና ነፃነት በማፈን በአምባገነንነት አገዛዙ ዛሬም ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ለሰላማዊ ትግልም በሩን ጥርቅም አድርጎ መዝጋቱን የሚያሳይ ነው፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአብዛኛዎቹ እንቅስቃሴው ባተኮረባቸው አካባቢዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የአንድነት አባላት ላይ ቅስቀሳ አድርጋችኋል በራሪ ወረቀት አሰራጭታችኋል በሚል የእስር፤ ዛቻ፤ ማስፈራራት፤ ድብደባ እና መሰል የመብት ጥሰቶች በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ሠራተኞች፤ በፀጥታ ኃይሎች እንዲሁም በኢህአዴግ አባላት በተለይ በባለስልጣናት፤ ካድሬዎች፤ ሊግና ፎረም አደረጃጀቶች ተፈጽሞባቸዋል አሁንም ሂደቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
በሰሜን ጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ አብርሃጅራ ከተማ
1. አቶ አለልኝ አቦሀይ — ከሰኔ 22/2005— ሀምሌ 19/2005 ዓ.ም ጀምሮ
2. አቶ እንግዳው ዳኘው — ከሰኔ 22/2005 — ሀምሌ 19/2005 ዓ.ም ጀምሮ
3. አቶ አብርሃም ልጅአለም– ከሰኔ 22/2005 — ሀምሌ 19/2005 ዓ.ም ጀምሮ
4. አቶ አንጋው ተገኝ—– ከሰኔ 22/2005 — ሀምሌ 19/2005 ዓ.ም ጀምሮ
በሰሜን ጎንደር፡- ጎንደር ከተማ
5. አቶ ማሩ አሻገረ —— ከሰኔ 26 — ሀምሌ 16/2005 ዓ.ም ጀምሮ
6. አቶ አምደማሪያም እዝራ —ከሰኔ 26– ሀምሌ 16/2005 ዓ.ም ጀምሮ
7. አቶ ስማቸው ግቤ —— ከሰኔ 25 — ሀምሌ 2/2005 ዓ.ም ጀምሮ
በሰሜን ጎንደር፡- በወገራ
8. አቶ ጀጃው ቡላዴ —– በሰኔ 25 2005 ዓ.ም ታስረው ተለቀዋል
9. አቶ ጋሻው ዘውዴ —– በጥይት የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸዋል
በሰሜን ጎንደር፡- በአለፋ ጣቁሳ
- መምህር አወጁ ስዩም -ከሰኔ 26 — ሀምሌ 16/2005 ዓ.ም
- ድርሻ አደራጀው ——- ከሰኔ 26 — ሀምሌ 9/2005 ዓ.ም
- አይቸው ተገኝ ———- መስከረም 29/2006 እስካሁን አለተፈቱም (ም/ጎጃም ሜጫ ወረዳ)
- እያዩ ተኮላ ——- ከሰባት ወራት እስር በኃላ ከጥቅምት 26/2006 ዓ.ም (ም/ጎጃም ሜጫ ወረዳ)
በደቡብ ወሎ ወረባቦ ወረዳ
- አቶ መሀመድ ሸሪፍ
- አቶ ጀማል ሰኢድ
- አለሙ አባይነህ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
- አቶ ብሩክ አሻግሬ – በሀምሌ 03 /2005 ታስሮ በዋስ ተፈቷል
- አቶ ወንድይፍራው ታረቀኝ – በሀምሌ 03 /2005 ታስሮ በዋስ ተፈቷል
- አቶ ሙሉጌታ ተፈራ — ከሰኔ 30 2005 – ሀምሌ 02 /2005 ዓ.ም
- አቶ ስንታየሁ ቸኮል — ከሀምሌ 2 /2005 ዓ.ም እስከ ሀምሌ 7 /2005 ዓ.ም
- አቶ ዳንኤል ፈይሳ —- ከሀምሌ 2 /2005 ዓ.ም እስከ ሀምሌ 7 /2005 ዓ.ም
- አቶ አበበ ቁምላቸው — ከሀምሌ 2 /2005 ዓ.ም እስከ ሀምሌ 7 /2005 ዓ.ም
ሀምሌ 8/2005 ዓ.ም
የካ ክ/ ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- ኤፍሬም ሰለሞን
- ታሪኬ ከፋ
- ፍቃዱ በቀለ
- ዘገዬ እሸቴ
- ተፈሪ ተሾመ
- ብስራት ተሰማ
- መኳንንት ብርሀኑ
- ፋና ወልደጊዮርጊስ
- አምቦ ጅማ
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- አስር አለቃ ሽፈራው ተሰማ
- ፋንቱ ዳኜ
- ገነት ሰለሞን
- አላዛር አርአያ
- ሳሙኤል ኢሳያስ
- ደመላሽ ሙሉነህ
- አማኑኤል መንግስቱ
- ታሪኩ ጉዲሳ
ጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- አስማረ ንጉሴ
- 41. ፍቃደስላሴ ግርማ
42. አሸናፊ አስማረው
- 43. ዳንኤል ሙላት
44. ለሚ ስሜ
- 45. ታሪኩ ጉዲሳ
- 46. ሰይፈ ገብሬል ተኮላ
- 47. መሳይ ትኩ
ጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- ደረጀ ጣሰው
- 49. ወርቁ አንድሮ
- 50. ኃይሉ ግዛው
- 51. ገዛኸኝ አዱኛ
52. ባዩ ተስፋዮ
53. ንጉሴ ቀነኒ
ሀምሌ 9 2005 ዓ.ም
ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- ሰለሞን አበራ
- አዲሱ ካሳሁን
- እንግዳ ወርቅ ማሞ
- አለማየሁ በቀለ
- ባቡሽ ካሳሁን
- አዲስ አለም ሸዋንግዛው
- ግርማ ሹሜ
- ባይሳ ደሬርሳ
- በወላይታ ሶዶ ከተማ
ወ/ሮ ሀድያ መሀመድ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የወላይታ ሶዶ አባል ሲሆኑ አንድነት በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚያካሂደው ህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ህግን አክብረው ቢንቀሳቀሱም እንደተለመደው ኢህአዴግ የጸጥታ ሀይሉን ለህገወጥ ፖለቲካዊ ግቡ ማሳኪያና ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖችን ማጥቂያ አድርጎ በመጠቀም ላይ መሆኑን በግልጽ ከሚያሳዩ ማስረጃዎች መሀል ወ/ሮ ሀድያ መሀመድ ላይ የደረሰው ግፍ ዋና ማሳያ ነው፡፡ ወ/ሮ ሀድያ መሀመድ ባለፉት ሶስት አመታት በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በአኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር የመብት ጥሰት ሲፈጸምባቸው የቆዩ ሲሆን አንድነት በወላይታ ሶዶ ከተማ ባካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ምክንያት ሀምሌ 26 2005 ዓ.ም ከቀኑ በ 7 ሰዓት አካባቢ መ/አለቃ ሀብታሙ በተባሉ የትራፊክ ፖሊስ አማካኝነት ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ በሚል ተወስደው ለ18 ቀናት “በተከለከሉ ቦታዎች ወረቀት በትነሻል፤ ህዝብና መንግስትን ለማጋጨት ሙከራ አድርገሻል” በሚል ክስ በእስር ቆይተዋል፡፡ በዚህ ግዜ ውስጥ የተለያዩ ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ አያያዞችን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በሀምሌ 26 2005 ዓ.ም በተለይ የመሀል መርካቶ ጣቢያ አዛዥ የሆኑት ኢንስፔክተር ላሊሼ ጉሮሯቸውን በማነቅና በመወርወር ከጠረንጴዛ ጋር በማጋጨት ድብደባ ከመጸምም በላይ “ ቶርች ስትደረጊ ሰገራና ሽንትሽ ሲቀላቀለቀል ትለፈልፊያታለሽ “ በማለት በህግ ጥበቃ ስር ባለሉበት ሁኔታ ከሌሎች መርማሪዎች ጋር በመሆን የአካልና የመንፈስ ስቃይ አድርሰውባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ስልክ ቁጥር በመውሰድ እና በመደወል የማስፈራራት የመዛት ተግባራት እየተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት ከእስር በ 10000 ብር ዋስ ከወጡም በኋላ በየትኛውም ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ በመከተል በኢህአዴግ አባላት የማስፈራራት ዛቻና ያለእረፍት ክትትል በማድረግ ከማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት ለማራቅ ከእሳቸው ጋር የታዩ ሰዎችን በስልክ በማስፈራራት ከማህበረሰቡ እንዲገለሉ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ሀድያ መሀመድ በወላይታ መጀመሪያ ደ/ፍ/ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ከተጠየቀባቸው በኃላ ክሱ በከፍተኛ ፍ/ቤት እንዲታይ በማድረግ ከ18 ቀናት አስር በኃላ በ10000 (አስር ሽህ ብር) ዋስ ከእስር ተለቀው ያላቸውን የመከላከያ ማስረጃ ለጥቅምት 21 2006 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ፍ/ቤቱ ወስኖ በክርክር ላይ ይገኛሉ፡፡ ወ/ሮ ሀድያ መሀመድ ለእርሳቸውም ይሁን ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ዋስትና የሚሰጣቸው አካል በማጣት በከፍተኛ ስጋት ላይ ናቸው፡፡
- አቶ ብርሀኑ ገረፉ ያኢ
አቶ ብርሀኑ ገረፉ ያኢ በአቃቄ ቃሊቲ ክ/ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የአንድነት አ/አበባ ዞን ም/አባልና የወረዳ 26/28 ጸሀፊ ሲሆኑ ሀምሌ 28 2005 ዓ.ም ከጧቱ 1፡30 አደይ አበባ አካባቢ ወደ ስራ ሲሄዱ እግረመንገዳቸውን በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ህዝባዊ ንቅናቄ ፕሮግራም የተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶችን በመስጠት ላይ በነበሩበት ጊዜ ሲቪል የለበሰ ሰው እጃቸውን በአናታቸው ላይ አድርገው ጭቃ ላይ እንዲበረከኩ በማድረግ ከሌሎች የፖሊስ ባልደረባ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሆን ያለርህራሄ በሰደፍ አናታቸውን ጀርባቸውን በመቀጥቀጥ ሲደበድቧቸው ሌሎቹ የፖሊስ ባልደረቦች እጃቸውን ጠምዘው በማሰቃየት በግራ እጃቸው ላይ ከፍተና ጉዳት አድረሰውባቸዋል፡፡ ሳሪስ አካባቢ ከሚገኘው አቦ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመውሰድ በተለያዩ መርማሪዎቸ ከተመረመሩና ቃል ከሰጡ በኃላ ሀምሌ 29 2005 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ላይ በዋስ ተለቀዋል፡፡ በምርመራው ወቅት ማስፈራራትና ዛቻ የመሳሰሉ ሰብአዊ በብቶቻቸውን የሚጋፉ አያያዞች ነበሩ፡፡
ነሀሴ 4/ 2005 ዓ.ም
አቃቄ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- አብርሃም አራጌ
65. አማኑኤል መንግስቱ
66. መሳይ ትኩ
67. ተፈሪ ተሸመ
68. ገዛኸኝ አዱኛ
69. ዘሪሁን እርገጤ
70. ንጉሴ ቀነኒ
- 71. ዳንኤል በቦክስ የተደበደበና ጉዳት የደረሰበት
ጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- ሐይሉ ግዛው
73. ወርቁ አንደሮ
74. ሰፈው መኮንን
ቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
- ነብዩ ባዘዘው
76. ቴድሮስ ታደሰ (ሹፌር) ነሀሴ 5 ቀን ከቀኑ በ10 ሰአት አካባቢ ከእስር ተለቀዋል፡፡
በመስከረም 15 2000 ዓ.ም
ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ
ከቀኑ 10 ሰዓት ሲሳይና ሳጅን አለማየሁ በተባሉ የትራፊክ ፖሊሶች ተይዘው እስከ ምሽቱ 1 በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይተዋል፡፡ የሁለት አባላት ስልካቸው ተቀምቶ መረጃቸው ተሰርዞባቸዋል (ፎርማት ተደርጓል)
- ዘላለም ደበበ
- አበበ ቁምላቸው
- ሙሉጌታ ተፈራ
- ስንታየሁ ቸኮል
- ፋናዬ ወ/ፃደቅ
- ተፈሪ ተሾመ
- ኢስማኤል (ሹፌር)
ጉለሌ ክ/ከተማ ሽሮ ሜዳ ማዘዣ ጣቢያ
ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ በሁለት ፖሊሶችና ሶስት ሲቪል በለበሱ ሰዎች ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኃላ እነዚህን የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ እያደረጉ የነበሩ አባላት ለማስፈታት የሄዱትንም የአንድነት ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶና አቶ ዳንኤል ሙላት ጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመውሰድ እስከ ምሽቱ 1፡30 አግተው አቆይተዋቸዋል፡፡
- ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
- የማነ አሰፋ
- ኢስማኤል ዳውድ
- አብርሃም ታደለ
- ወርቁ አንደሮ
- ወንደሰን
- ቢንያም
አራዳ ክ/ከተማ ብርሃንና ሰላም አካባቢ ንዑስ ማዘዣ ጣቢያ
ከቀኑ 5፡30 አካባቢ በአራት ኪሎ ቅስቀሳ ላይ በነበሩ የአንድነት አባላትን በሁለት ፖሊሶችና (ኪዳኔ የተባለ) አንድ ሲቪል በለበሰ ሰው ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኃላ እስከምሽቱ 1 ሰዓት ታግተው ተለቀዋል በተለይ በአዛሪያ መላኩ ላይ በመርማሪ አብዮት ደምሴ ዛቻና ማስፈራራት ተፈፅሞበታል፡፡
- ኤፍሬም ሰለሞን
- ሽባባው መንግስቱ
- ዳንኤል ፈይሳ
- ስንታየሁ ቸኮል
- ትዕግስቱ ደሳለኝ
- ሀብታሙ ታፈሰ
- ዳግማዊ ተሰማ
- ሳሙኤል ይትባረክ
- ቴድሮስ
100. ኩምሳ በረደድ
- ፋና ወ/ጊዮርጊስ
102. አዛሪያ መላኩ
103. ተፈሪ ተሾመ
104. ኢስማኤል አፀዳ (ሹፌር)
መስከረም 16/2005 ዓ.ም
በቤላ አካባቢ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ የአንድነት እና መኢአድ አባላት በፈረንሳይ አካባቢ ን/ማ/ጣቢያ ፖሊሶች ከቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ ተይዘው በየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ታግተው ተለቀዋል፡፡ በዚህ ወቅት አንዳንድ እንግልቶች ዛቻና ማስፈራራት ተፈፅሞባቸዋል፡፡
105. አብርሀም ታደለ
- 106. ደመላሽ ካሳዬ
107. አሸናፊ አሳምረው
108. የማነ አሰፋ
109. ኢስማኤል ዳውድ
- ቢያዝን ብሩ
- አብርሀም ገ/ሊባኖስ
- ካሳሁን ማሞ (ሹፌር)
መስከረም 17/ 2005 ዓ.ም
- ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ — ሊቀመንበር
- የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ —- ም/ሊቀመንበር
- ስዩም መንገሻ —– የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ
- ዳንኤል ተፈራ —- የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
- አስራት ጣሴ —– ዋና ፀሀፊ
- ሽመልስ ሀብቴ —- የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ
- ሀብታሙ አያሌው — የሕዝብ ግንኙነት ም/ኃላፊ
120. ተክሌ በቀለ —– የፋይናንስ ጉዳይ ኃላፊ
- ብሩ በርሜጅ —— የብሔራዊ ም/ቤት አባል
122. አበበ አካሉ —— የብሔራዊ ም/ቤት አባል
123. እንግዳ ወ/ፃዲቅ—— የብሔራዊ ም/ቤት አባል
124. አለባቸው ነጋሽ
125. መኳንንት ብርሀኑ
126. እንዳልካቸው ባዩ
127. ብስራት ተሰማ
128. ወንደሰን ክንፉ
129. ኃይሉ ግዛው
130. ደረጀ ጣሰው
- ገዛኸኝ አዱኛ
132. ባዩ ተስፋዬ
133. ወርቁ አንደሮ
134. አለባቸው ነጋሽ
135. አጥናፉ ሙላት
136. ኤፍሬም ሰለሞን
137. ደርበው ደምሴ
138. ወንድፍራው
139. ብሩክ አሻግሬ
140. ተፈሪ ተሸመ
- ዳግማዊ ተሰማ
142. ዘመዴ ክፍሌ
143. ሙሉጌታ ተፈሪ
144. መምህር አጥናፉ
መስከረም 18 20005 ዓ.ም
በቅስቀሳ ስራ ላይ እንደነበሩ ከቀኑ 5 አካባቢ ሲሆን ስድስት ኪሎ ላይ በደንብ ማስከበር አገልግሎት ሰራተኞና የፖሊስ ባልደረባ በሆነው ዘመድኩን ካሳ ተይዘው ወደ ጉለሌ ፖሊስ መምሪያ ተወስደው ከቀኑ 10 ላይ በዋስ ተፈተዋል፡፡
145. ብሩክ አየለ
146. አቤል መና
147. ዘላለም ታደሰ
በቅስቀሳ ስራ ላይ እንደነበሩ ከቀኑ 8፡30 አካባቢ ሲሆን በአፍንጮ በር በፖሊስ ተይዘው ወደ ጉለሌ ፖሊስ መምሪያ ከተወስዱ በኃላ ከምሽቱ 12 ላይ በዋስ ተፈተዋል፡፡
148. ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
149. ፋና ወ/ፃዲቅ
150. እንግዳ ወረቅ ማሞ
- እሸቱ ወ/ፃዲቅ
152. መሀመድ በድሩ
ለህይወታቸው ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው አባላት
ከዚህ በታች ስማቸው የተገለጸው የአንድነት አባላት በወረዳቸውና በፓርቲው ውስጥ በሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ ለህይወታቸው በጣም ስጋት ላይ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ ከብሔራዊ ደህንነትና መረጃ ሰራተኞች፤ ከፀጥታ ሀይሎች እና ከኢህአዴግ አባላት በደረሰባቸው ድብደባ፤ ማስፈራራት፤ዛቻ፤ እስር፤ ማንገላታት፤ ስራቸውን ማወክ እና ሌሎች የመኖርና የመስራት መብታቸውን የሚገፉ ተግባራት ምክንያት ለደህንነታቸው ከለላ የሚሰጣቸው የተጣሰውን መብታቸውን የሚያስከብርላቸው አካል አጥተው የህግ ያለህ እያሉ ይገኛሉ፡፡
- ሙሉጌታ ተፈሪ — የምርጫ ክልል ወረዳ 15 አባል ሲሆን በአካባቢው ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ በመሆኑ በተለያዩ ወቅቶች በተለይ በቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በተደጋጋሚ ታስሮ በዋስ ተፈቷል፡፡ በ23/12/2005 ዓ.ም ከቀኑ በ6 ሰአት አካባቢ ሲቪል በለበሱ ሰዎች የሊስትሮ ስራ በሚሰራበት ቦታ (ቂርቆስ ክ/ከተማ አስተዳደር አጥር ሰር/ካዛንቺዝ) እንዲሁም በተከታታይ ቀናት እጅግ ፀያፍ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም እና በማስፈራራት ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ አድርገውታል፡፡
በተደጋጋሚ በወረዳ 8 ተመራጮች የሊግ አባላት እና ሌሎች ሰዎች ዛቻ ማስፈራራት ተፈፅሞበታል በዚህም ምክንያት አካባቢውን ለተወሰነ ጊዜ ለመልቀቅ ተገዷል፡፡ ይህንን እኩይ ተግባር የኢህአዴግ አባል መሆናቸውን ተገን አድርገው በህዝብ የተሰጣቸውን ስልጣን ያላግባብ በመጠቀም እየፈፀሙ ያሉ የኢህአዴግና የፀጥታ ሀይሎች፡-
– የሺ ጤና — የወረዳ 8 ተመራጭ
– አበበች ገለቱ– — የወረዳ 8 ተመራጭ
– ቴዲ አለሙ— የወረዳ 8 ተመራጭ (ካዛንቺዝ ጤና ጣቢያ የሚሰራ
– አበበ (የፌደራል ፖሊስ አባል)
– ሳጅን ቶሎሳ
– ስሙ ያልታወቀ የወረዳ 8 የጥበቃ ሰራተኛ
- ስንታየሁ ቸኮል
በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የም/ወረዳ 20/21 ሰብሳቢና የህግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ በፓርቲው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸውና በሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ስኬት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በሀምሌ 2 እሰከ 7/2005 በን/ላፍቶ ፖሊስ መምሪያ እንዲሁም ሀምሌ15/2005 በቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ በእስር ቆይተዋል፡፡ በዚህ ወቅት በቁጥጥር ስር በዋሉበት የፖሊስ ጣቢያ በመገኘት በተደጋጋሚ አቶ ግርማ የተባሉ የብ/ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ባልደረባ በካቴና ከጠረንጴዛ ጋር በማሰር ሆነ ብሎ የአካል ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በኩላሊትና የጎን አጥንቶቻቸው ላይና አይናቸው ላይ ዘላቂ ጉዳት እንዲደርስባቸው አድረገዋል በህክመና ቢረዱም እስካሁን ከበሽታው ሊያገግሙ አልቻሉም፡፡ በዚህ ኢሰብአዊ ድርጊት በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉበት የፖሊስ ጣቢያ ባልደረቦች ለምሳሌ ኢንስፔክተር ግዛቸው የቂርቆስ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ሀላፊ በማሰቃየቱ ተሳትፈዋል በዚህ ወቅት ሌሎች በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተግባሩን በማየት እንዲሸማቀቁ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመባቸው አቶ ስንታየሁ ቸኮል መብታቸውን በህግ ለመጠየቅ ወንጀሉ እንዲጣራላቸውና በአጥፊዎቹ ላይ ህጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ለመጠየቅ ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ መምሪያ ማመልከቻ ለማስገባት ቢሄዱም እንዳንጨምርልህ በማለት አሁንም የሞያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ በተጨማሪም በመስከረም 19/2005 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 አካባቢ ቀበና አካባቢ ከሚገኘው የአንድነት ቢሮ ወጥተው ታክሲ ሊሳፈሩ ሲሉ በሶስት የብ/ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ሰራተኞች አማካኝነት ታግተው ሊወሰዱ ሲሉ በአካባቢው በነበሩ ሰዎችና የድርጅቱ አባላት ሳይታፈኑ ቀርተዋል፡፡ አሁንም አቶ ስንታየሁ ተደጋጋሚ የሆነ ማስፈራራትና ዛቻ ከስራ ማባርር የመሳሰሉ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡
- ዘላለም ደበበ
በሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ከነበራቸው አባላት መካከል አንዱ የነበሩት እና በተለይ እንቅስቃሴው ላነገባቸው ዜጎች ህገመንግስቱን የሚሸራርፍ እና የፖለቲካ ስልጣንን ለማራዘም የሚያገለግል የፀረ ሽብር ህጉ አይነት አፋኝ ህጎችን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ በቅስቀሳ ስራ ላይ ባደረጉት ተሳትፎ ምክንያት ከመስከረም 19 ቀን ጀምሮ በብሄራዊ የደህንነትና የመረጃ አገልግሎት ሰራተኞች ማስፈራት ዛቻ ስራንና አጠቃላይ ህይወትን ማወክ የመሳሰሉ ሰብአዊ ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀምባቸው ቆይቷል በተለይ መስከረም 30 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡15 አካባቢ በስራ ቦታቸው ማለትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ቤተ መጽሐፍት ሁለት ሰዎች በመገኘትና ሊያናግሯቸው እንደሚፈልጉ በመግለጽ ከስራ ቦታ አፍነው ለመውሰድ ባዘጋጁት መኪና እንዲገቡ ቢጠይቋቸውም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እጅግ አጸያፊ ስድቦችን እና ማስፈራሪያዎችን በመጠቀም አስገድዶ ለመውሰድ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ በምዝገባ ላይ የነበሩትን የመጀመሪያ አመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትኩረት በመሳቡና በአካባቢው መልካም ያልሆነ ሁኔታ በመፈጠሩ አቶ ዘላለም ደበበ ከአካባቢው ለመራቅ በእግር ከዩነቨርስቲው ግቢ ወጥተዋል፡፡ የህ ነገር ሆነ ተብሎ የተማሪዎችን ስነልቦና ላይ ጫና ለማድረግ ጥቅም ላይ የዋለ ነው፡፡ ግለሰቡን ስድስት ሆነው አስገድደው ወደ ኮሪያ ዘማቾች መናፈሻ (ናይጀሪያ ኤምባሲ አካባቢ) በመውሰድ እስከ ምሽቱ 12፡30 ሁለት የፖሊስ ደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች በማስጠበቅና በማገት ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያዋርዱ አጸያፊ ተግባራትን ፈጽመውባቸዋል፡፡
- መምህር አበበ አካሉ
መምህር አበበ አካሉ የፓርቲው የብሄራዊ ም/ቤት እና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባል በተለይ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በጎንደር፤ ደሴ፤ አዲስ አበባ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩ ጠንካራ ታጋይ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሙስናን ከመዋጋትና ሙሰኞችን ከማጋለጥ አኳያ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን በማስረጃ አስደግፈው ይጽፉ ነበር፡፡ ለአብነት በፍኖተ ነጻነትና በኢትዮ ምህዳር ጋዜጦች በለገጣፎና ለገዳዴ ከተሞችና አካባቢው በአስተዳደሩ ባለስልጣናት አርሶ አደሮችን ያለካሳና በዝቅተኛ ካሳ ሲያፈናቅሉ አጋልጠዋል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች በግል ህይወታቸው ላይ ተደጋጋሚ የመብት መገፈፍ ሲደረግባቸው ቆይቶ ጥቅምት 14 ቀን 2006 ዓ.ም በ7፡00 ሰአት ላይ ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ በላንድ ክሩዘር መኪና መንገድ በመዝጋት በጠራራ ፀሀይ በሶስት የብሄራዊ የመረጃ እና ደህንነት ሰራተኞች ታፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስደዋል፡፡
መምህር አበበ አካሉ በዚህ ሰዋራ ቦታ ኢሰባአዊ በሆነ መንገድ አከላዊ ድብደባ እና የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የማሰቃየቱ ተገባሩ የአልኮል ሽታ ያለው ነገር በመጋት፤ ሽጉጥ ደቅኖ በማስፈራራት እየተፈራረቁ ድብደባ በመፈፀም ክብርን የሚዋርዱ ስድቦችን በመሳደብና ሌሎች አፀያፊ ነገሮችን በማድረግ ሰላማዊ ትግሉን ካላቆሙ “በሽብርተኝነት ወንጀል በመክሰስ መንግስትን በሀይል ለመጣል በሚል ክስ ወህኒ እንደሚማቅቁ” በማስፈራራት ከፍተኛ የስነልቦና ጫና ካደረሱባቸው በኃላ ከምሽቱ 1፡00 ላይ በመኪና ወደ መንገድ ዳር በማውጣት ወርውረዋቸው ሄደዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የደረሰባቸውን አካላዊ ጉዳት ለማስታመም በመኖሪያ ቤታቸው ህክምና እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ አባላት ላይ ደረሰ የሰብአዊ መብት ጥሰት
ሀምሌ 25 2005 ዓ.ም አቶ እንግዳ ወ/ፃድቅ የብ/ም/ቤት አባልና አቶ የማነ አሰፋ የድርጅት ጉዳይ ፅ/ቤት ሀላፊ በራሪ ወረቀቶች ሲያድሉና ሲለጥፉ አሸባሪዎች ናቸው የአሸባሪነት ወረቀት እያሰራጩ ናቸው፤ በሚል ሰበብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ከተወሰኑ ሰዓታት በኃላ በማስጠንቀቂያ ተፈተዋል
ሀምሌ 26 2005 ዓ.ም ከቀኑ በ5፡00 ሰዓት አካባቢ በመቀሌ ከተማ ዙሪያ ዃሂት አካባቢ
- አቶ ደምሴ መንግስቱ—- የህግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
- አቶ የማነ አሰፋ———- የአንድነት ፓርቲ ድርጅት ጉዳይ ፅ/ቤት ኃላፊ
- አቶ ክብሮም ብርሃነ—— የመቀሌ ከተማ አንድነት ተጠሪ
በራሪ ወረቀት ሲያድሉና ፖስተር ሲለጥፉ በወረዳው ፖሊስ ኃላፊ ካሳሁን አለሙ እና በወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ዋና ሳጅን ወልዳይ በላይ በቁጥጥር ስር ውለው ከብዙ እንግልት ዛቻ ማስፈራሪት በኃላ ከቀኑ 8፡00 በማስጠንቀቂያ ከስር ተለቀው አካባቢውን ለቀው (ኩኸ) እንደወጡ ተደርጓል፡፡
- ሀምሌ 26/2005 ዓ.ም ከቀኑ 10፡30 በሮማነት አደባባይ አካባቢ በሞንታርቦ የሚኪና ላይ ቅስቀሳ እንደተጀመረ የአቶ ነፃነት ዘገየ (ሹፌር) መንጃ ፍቃድ በመንጠቅ በቅስቀሳ ላይ የነበሩትን
- አቶ ክብሮም ብርሃነ
- አቶ አርአያ ፀጋዬ
- አቶ እንግዳ ወ/ፃድቅ
በሁለት ሞተረኛ ፖሊሶች ተገደው ወደ መቀሌ ዋና ፖሊስ መምሪያ በመወሰድ ለተወሰኑ ሰዓታት ታግተው የተፈቱ ሲሆን በተለይ የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊ ኢንስፔክተር ኃ/ማርያም ለሹፌሩ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሁለተኛ በመኪናህ ላይ ሞንታርቦ ጭነህ ብትሰማራ መንጃ ፍቃድህን ተነጥቀህ መኪናህ ይታሰራል በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል
ሀምሌ 27 2005 ዓ.ም ከቀኑ 5፡00 ሰዓት በሮማናት አደባባይ ሞንታርቦ በማስቀመጥ ቅስቀሳ ተጀምሮ ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ የቀዳማይ ወያኔ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዋና ዛዥ ዋ/ኢ/ር አንድነት ነገሰ የቅስቀሳ መሳሪያዎቹን ን በመኪና አስጭኖ በመውሰድ እንዲሁም በወቅቱ በቅስቀሳ ላይ የነበሩትን
- አቶ እንግዳ ወ/ፃድቅ
- አቶ አርአያ ፀጋዬ
- አቶ ክብሮም ብርሃነ ወደ ፖሊስ መምሪያ ተወስደው ታስረዋል፡፡ በተለይ አቶ አርአያ ፀጋዬ እና አቶ ክብሮም ብርሃነን እጅግ ሞራልን የሚነኩ ስድቦች ዛቻና ማስፈራሪያ ተደርጎባቸዋል፡፡ አቶ እንግዳ ወ/ፃድቅ ወደ ሌላ እስር ቤት ተወስደው ሀምሌ 28 ከጧቱ 3 ሰዓት አካባቢ ከስር ተፈተዋል፡፡ ንብረቱም ከሶስት ቀናት ውጣ ውረድ በኃላ ተመልሶላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ አስተዳደሩና የጸጥታ ሀይሉ በወሰዱት የከፋ እመቃ ሳይካሄድ ቀርቷል በዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች አላማቸውን ለህዝብ የማስተዋወቅ መብቶቻቸው ዜጎችም በነጻነት የመደራጀትና ሀሳብን የመግለጽ መብቶቻቸው ተገድበዋል፡፡
በፍቼ ከተማ በአንድነት አባላት ላይ የደረሰ የሰብአዊ መብት ጥሰት
ቀን ነሀሴ 15 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡15 አካባቢ ፓርቲው እያከናወነ ለሚገኘው የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ የሰላማዊ ሰልፍ ዝግጅትን ለማስተባበር ተልከው በነበሩት
- ነብዩ ባዘዘው————- የአዲስ አበባ ዞን የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ
- መሳይ ትኩ ዋቅጅራ—– የምርጫ ወረዳ 10 ሰብሳቢ
ማረፊያ በያዙበት ሀመረ ሆቴል ውስጥ በ11 ሰዎች በዱላና በአካል ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በዚህም በሁለቱም ተወካዮች ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን በተለይ በአቶ መሳይ ትኩ ላይ የእጅ ስብራት ደርሶባቸው በህክምና ላይ ናቸው፡፡ ድብደባው የተቀነባበረ መሆኑን በወቅቱ የታዩት አካባቢያዊ ሁኔታዎች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ ድብደባው ሲፈጸም ተደብዳቢዎቹ ሲጮሁ የፍቼ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢ/ር ወጋየሁ እና የወንጀል መከላከል ሀላፊ ኢ/ር ሀብታሙ ወዲያው በመምጣት ደብዳቢዎቹን ዱላቸውን ቀምተው ከአካባቢው እንዲሄዱ አድርገዋቸዋል፡፡ በተጨማሪም ዋና የድርጊቱ አቀናባሪ የሆነው የፍቼ ከተማ የፀጥታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሀይለየሱስ በየነ ከሹፌር አሸናፊ ጋር በመሆን ከተማው ከደረሱበት ቀን ጀምሮ ክትትልና ልዩ ልዩ የስነልቦና ጫና ሲያደርሱባቸው ነበር፤ አንዱ ደብዳቢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥበቃ ሰራተኛ መሆንና የያዘውን ዱላ ነጥቀው በቁጥጥር ስር ሳያዉሉ መልቀቃቸው እንዲሁም ለኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሲነገራቸው ወደ ከተማዋ ስትመጡ አሳውቃችሁን ቢሆን ኖሮ ድብደባ አይፈፀምባችሁም ነበር የሚል መልስ ሰተዋቸዋል፡፡
በነሀሴ 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለዞኑ ፍትህና ፀጥታ ሀላፊ አቶ ሰለሞን ለዞኑ ፖሊስ ኃላፊ እና ለፍቼ ፖሊስ መምሪያ እንዲሁም ለኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ቢያሳውቁም እስካሁን ወንጀሉን በፈፀሙት ተጠርጣሪዎች ላይ ምንም ህጋዊ እርምጃ አልተወሰደም፡፡
በአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማጠቃላይ
ዓመተ ምህረት | ስድብ ዛቻ ማስፈራራት | እገታ እንቅስቃሴን መገደብ | ህገወጥ ብርበራና እስር | ድብደባ አካል ማጉደል | መሰወር አድራሻ ማጥፋት | ንብረት ዘረፋ | የመግደል ሙከራ |
2005 | 162 |
100 |
115 |
6 |
3 |
1 የአባል እና በርካታ የፓርቲው ንብረቶች |
1 |
2004 |
8
|
6 |
5 |
2 |
– |
– |
– |
2003 |
1
|
– |
6 |
2 |
– |
– |
– |
ድምር |
173 |
106 |
126 |
10 |
3 |
1 |
1 |
ክፍል ሁለት
በመድረክ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ደጋፊዎች ላይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
በ2003 ዓ.ም
- በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ በሰበብ አስባብ ከ300 በላይ ዜጎች ህገመንግስታዊ መብቶቻቸው ተጥሰው ለእርስና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡
- ጭካኔ በተሞላበት የእስር አያያዝ ከዘመዶቻቸው እንዳይገናኙ ተከልክለዋል በዚህም በህገ መንግስቱ በአንቀጽ 18 (1) እና 21(2) እውቅና የተሰጣቸው ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ተጥሰዋል፡፡
- በራሳቸው ላይ ማስረጃ እንዲሆኑ ከመገደድም በላይ ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆኑትን ደግሞ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው እና እራሳቸውን ስተው ሆስፒታል እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ በዚህም በህገ መንግስቱ በአንቀጽ 19 (5) እውቅና የተሰጣቸው የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ተጥሰዋል፡፡
- ለምሳሌ ስድስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ በፅኑ ቆሰለው ህክምና ላይ አንደነበሩ
- ከዩኒቨርሲቲዎተ በዲግሪ ለመመረቅ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን ያዘጋጁና የምረቃ ጊዜያቸውን እየተጠባበቁ ያሉ ተማሪዎች የሚገኙበት መሆኑ
- ከነዚህም ውስጥ ከአዲስ አበባ፣ ከሀዋሳ፣ ከጅማና ከሀገረማሪያም ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል
- ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ደግሞ የባኮ፣ የደኖ፣ የአምቦና ከጨሊያ 2ኛ ደረጀ ት/ቤቶች ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡
ክፍል ሦስት
የፖለቲካና የህሊና እስረኞች
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት፤ ጋዜጠኞች ታስረው በሚገኙበት ማረሚያ ቤቶች ያለውን አጠባበቅና አያያዝ ለማወቅ የአንድነት ፓርቲ የህግና ሰብዓዊ መብቶች ቋሚ ኮሚቴ ስር የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ 18 የሚደርሱ መጠይቆችን በማዘጋጀት ለማጣራት ሙከራ አድርጓል፡፡
ሀ. በቃሊቲ ማረሚያቤት የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች
1. አቶ አንዷለም አራጌ
2. አቶ እስክንድር ነጋ
3. ወ/ት ርዕዮት ዓለሙ በታሰሩበት ማረሚያቤት ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን አስመልክቶ ያለውን አያያዝና አጠባበቅ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም የቅርብ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው እንዳይጠይቋቸው ከህግ አግባብ ውጭ በመከልከሉ ነው፡፡
ለ. በዝዋይ ማረሚያ ቤት የታሰሩት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች
1. መ/ር ናትናኤል መኮንን
2. አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) አንድ ላይ ሲሆኑ
1 አቶ በቀለ ገርባ
2 አቶ ኦልባና ሌሊሳ
3 አቶ ዘርይሁን ገ/እግዚአብሄር በሌላኛው ክፍል የግንቦት 7 እና ኦብነግ አባላት ናቸው ተብለው በአሸባሪነት ከተፈረደባቸው ፍርደኞች ጋር ታስረው ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም
1. ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ
2. ሻ/ል የሺዋስ ይሁን
3. አቶ አንዷለም አያሌው አንድ ላይ ከሌሎች ታራሚዎች ጋር በማረሚያ ቤቱ ታስረው የሚገኙ ሲሆን ይህ ሪፖርት ከተጠናቀረ በኃላ አቶ አንዷለም አያሌው በጨለማ ቤት በእስር እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በግንቦት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዝዋይ ማረሚያ ቤት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ አባላት የተዘጋጀውን መጠይቅ ለመሙላት ችለዋል፡
በዚህም መሰረት በመጠይቁ ላይ በመለኪያነት የቀረቡት በጣም ጥሩ፤ ጥሩ፤ በቂና ከበቂ በታች የሚል ሲሆን ከተጠቀሱት የመብት አይነቶች መካከል ከቤተሰብና ጓደኛ ጋር መገናኘት መብት በጥሩ ሁኔታ የሚታይ ነው፡፡ ምናልባት ከማረሚያ ቤቱ ርቀት አንጻር ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አሳድሮብናል፡፡ በተቀሩት የመብት ዓይነቶች የምግብና ውሃ አቅርቦት፤ የማረፊያ ቤት፤ የህክምና የልብስና መኝታ አገልግሎቶች፤ የግልንጽህና መጠቀሚያ መጸሐፍት፤መጽሄት ጋዜጣና የመሳሰሉት የመረጃ ምንጮች፤ የአካል ብቃት ማጠናከሪያ ልምምድ መዝናኛ፤ ቤተመጽሀፍት ፤ የእኩልነት መብት፤ ትምህርት፤ ሀይማኖት እስረኞች ስለሚያቀርቧቸው ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ከበቂ በታች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት መብቶችን መሰረት የተደረገው የፖሊቲካና ህሊና እስረኞችን በሚመለከት ሲሆን ሌሎች ታራሚዎችን በተመለከተ የተሻለ መብት ያላቸው መሆኑ ሲታወቅ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ጋዜጠኞች የሆኑት የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በማረሚያ ቤቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አድሎአዊ አሰራር የሚፈጸምባቸው ሲሆን ከሌሎች ታራሚዎች በተለየ ሁኔታ ማግለልና በእኩልነት የመታየት መብቶቻቸው አለመጠበቁን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ክፍል አራት
በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች
4.1 ለገ-ጣፎ ለገ-ዳዴ ከተማ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር እጦት ከሚታይባቸው በተለይም ከሰሐራ በታች ካሉ ደሀ ሀገሮች መካከል የምትመደብ በትሆንም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ግን ከቀርብ ዓመታተ ወዲህ መልካም አስተዳደርን በሀገሪቱ ውስጥ ለማስፈን እየሰራሁ ነው ቢልም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡
መልካም አስተዳደር በየትኛውም ተቋም በመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የንግድ ድርጅቶች፤ ሆስፒታሎች፤ የትምህርት ተቋሞችና ኢንሰቲቲዮቶች፤ የወታደራዊ ተቋሞች፤በሀይማኖት ድርጅቶች ጭምር አስፈላጊ እና ለሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ነጻነቶች መከበር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ለዚህም እነዚህ ተቋማት አላማዎቻቸውን በተሳካ ሁኔታ ከግቡ ለማድረስ ብቃት ያለው አመራር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ታዋቂው የስራ አመራር ባለሙያ ፒተር ድረከር ይህን ሁኔታ ሲገልጸው “there are no under developed countries as such but under managed only” ይህ ማለት “በዓለም ላይ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሀገሮች አሉ ከማለት በአመራር የተበደሉ አገሮች ማለቱ ይሻላል፡፡” እንደማለት ነው የተጋነነ ቢመስልም ሀቅነቱ ግን ከፍተኛ ነው፡፡
ለዚሀ እንደ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው ከአዲስ አበባ ከተማ ሰሜን ምስራቅ ሃያ አንድ (21) ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የምትገኘውን ለገ-ጣፎ ለገ-ዳዴ ከተማ ማየት ይቻላል፡፡ ይህቺ ከተማ 2431 ሄከታር ስፋት እና 18177 ህዝብ ይኖርባታል ተብሎ ይገመታል እናም በዚች ከተማ ውስጥ የተፈጸመውን የህግ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ማሳየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
ይህቺ ከተማ ቀደም ብሎ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነባር የከተማ ነዋሪዎች እና በርካታ በተለይ በእርሻ ስራ ላይየተሰማሩ አርሶ አደሮች የሚኖሩባት አካባቢ ነበረች፡፡ በርካታ አርሶ አደሮች የከተማውን ልማት ለማፋጠን በሚል በአነስተኛ የካሳ ክፍያ የእርሻ መሬታቸውን እንዲለቁለዚህም ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል በማለት ከተነገራቸው በኋላ ያለምንም የካሳ ክፍያ መሬቱን እንዲለቁ እና ቤትም የሰሩበተመሳሳይ መልኩ እንዲያፈርሱ ተደርጓል፡፡ በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች ከነቤተሰባቸው ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ተደርጓል፡፡በዚህም ሰብአዊ ክብራቸው እና መብታቸው ተጥሷል፡፡
– ከሐምሌ ወር 1998 ዓ.ም በፊት ከአርሶ አደሩ መሬት በመግዛት ቤት ሰርተው መኖር የጀመሩ እና ከተማዋ በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ስር መተዳደር ከጀመረች በኋላ (1998 ዓ.ም) ቤት ገዘተው የገቡ ነዋሪዎች እና ነባር ነዋሪዎች በጋር በመሆን ካርታ የከተማው አስተዳደር መስጠት ሲጀምር ሳይነገራቸው በመቅረቱ ማግኘት የሚገባቸውን ካርታ ለማግኘት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ቢጠይቁም መብታቸውን የሚያስከብርላቸውና መልስ የሚሰጣቸው አካል አላገኙም፡፡
– በከተማዋ ከነባር ነዋሪዎች ይልቅ በውል ለማይታወቁ ግለሰቦች ከ90% በላይ የሚሆነው ካርታ (ለተለያየ ድብቅ ስሞች) ተሰጥቶዋል፡፡ በአንጻሩ ነባር ነዋሪዎች ተብለው ከተጠቀሱት ነዋሪዎች ውስጥ የተሰጠው ካርታ ከ500 የማይበልጥ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በ2002 ዓ.ም የተካሄደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የከተማዋ ነዋሪ 5000 ነው ይላል ነገር ግን የከተማው አስተዳደር ባወጣው መረጃ ቁጥሩን 18000 ያደርሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በከተማዋ ለ20000 ነዋሪዎች ካርታ መሰጠቱ የህዝብ አስተዳደር የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህን የተከተለ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ደረጃ የት እንዳለ ያሳያል፡፡
4.2 በሞጆ አካባቢ
በሞጆ ነዋሪ ላይ በደረቅ ወደብና በመንገድ ግንባታ ምክንያት ብዙ የገጠርም ሆነ የከተማ ነዋሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ያለበቂ ጊዜና የካሳ ክፍያ እንዲነሱ እና በንብረታቸው ላይ ጉዳት እንዲደርስ እንዲሁም በሰብአዊ መብታቸው ክብራቸው ላይ ጥቃት የተፈፀመባቸው ዜጎች ሲኖሩ ከነዚህም መካከል የመጀመሪያዋ ተጎጂ የሆነችው ወ/ሮ የኔነሽ ደመቀ ትባላለች፡፡
ወ/ሮ የኔነሽ ደመቀ በሞጆ አካባቢ ነዋሪ ስትሆን በ1978 ዓ.ም የደርግ መንግስት ባወጣው የሰፈራ ፕሮግራም ከነበረችበት በመነሳት ወደ ሰፈራ ገብታ እዛም ብዙ ሳትቆይ ከደርግ ውድቀት በኃላ ያለ ህዝብ ፈቃድ ወደ ሰፈራ በግዳጅ ስለገባች ስርአቱ ሲወድቅ እና ወደ ነበሩበት ሲመለሱ እርሷም ተመልሳለች፡፡ የመሰረተ ልማት ባልተማላበት እና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ በሌለበት ለ 22 ዓመታት ስትኖር በግሏ 15 የመብራት ምሶሶ በማስተከል፣ከ100 በላይ የባህር ዛፍ ተክል ዕድሜያቸው 20 እና ከዚያ በላይ ጌሾ ከግማሽ ቀረጥ በላይ ፣12 ክፍል ቤት ፤112 ቆርቆሮ የለበሰ የቆሮቆሮ መጋዘን ቋሚ ንብረቶችን አፍርታለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ንብረቶች ያለ በቂ ካሳ፤ ባለንብረቷ ሳትስማማና ያለበቂ ጊዜ ከ3986 ካሬ መሬት ጋር ለኢንቨስትመንት በሚል ካሳ ክፍያውን ሳትወስድ ቤቶችን በማፍረስ ንብረት አልባና ከነቤተሰቧ መጠለያ አልባ እንድትሆን ተገዳለች፡፡
ይህንን ንብረት በ1999-2000 ዓ.ም የደረቅ ወደብ በሞጆ አካባቢ ለመገንባት መንግስት በያዘው ዕቅድ መሰረት ለደረቅ ወደቡ ግንባታ 17 ቀረጥ የእርሻ መሬት በ7ብር ከ30 ሳንቲም በጊዜው ዋጋ ለቅቃ ባገኘችው የካሳ ክፍያ በ4000 ካሬ መሬት ላይ ያረፈ ንብረት ነበር ፡፡
ካሳን የመውሰድ እና ያለመውሰድን በተመለከተ በህግ የተቀመጠ መብት እንዳለ ይታወቃል በአዋጅ ቁጥር 455/97 የወጣውን የ3 ወር የጊዜ ገደብን እንዲሁም ላለመውሰድ እምቢ የተባለበትን ምክንያት እስከሚመለከተው አካል ድረስ ማሳወቅ ቢቻልም ነገር ግን በህግ የተሰጠን እና በተፈጥሮ ለሰው ልጆች የተሰጠውን መብት በመጣስ ማንም በሌለበት ቀን በሰጡት የሁለት ቀን ገደብ ቤቱን በማፍረስ የተጣሰ የሰብአዊ እና የህግ ጥሰት(ካሳ ያልተከፈለበትን ቤት ነው ያፈረሱት)፡፡
መንግስት በህግ /በአዋጅ 455/97 በደንብ ቁጥር 135/99 ማፈናቀያ ካሳ እንደሚከፍል በማያሻማ ሁኔታ ተቀምጦ እያለ ለ 2 ዓመት እስካሁን አለመክፈሉ እንደዚሁም ለአርሶ አደሩ ይዞታ የማፈናቀያ ካሳ የተሰጠውን መብት ከከተማው ጋር በማያያዝ ለአርሶ አደሩ የተሰጠውን መብት እንዲያጣ ተደርጓል፡፡
4.3 በጉረ ፈርዳ አካባቢ
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 25 ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል እንደሆኑ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የህግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል እንዲሁም በአንቀጽ 41.1 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመተዳደሪያነት የመረጠውን ስራ የመስራት መብት አለው ይላል ይሁን እንጂ እነዚህ መብቶች በእቅድ እና በተደራጀ ሁኔታ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ የመሰራታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ጥሰት ሁነኛ ማሳያ ድግሞ በአማራ ህዝብ (አማርኛ ተናጋሪ ዜጎች) ላይ በተለይ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ጉረፈርዳ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ በዞን ምክር ቤት እና በክልሉ መንግስት ውሳኔ (በክልሉ ፕሬዝደንት በተፈረመ ደብዳቤ ቁጥር ደሕ 00058756 01 በቀን 11/10/2001 ዓ.ም) አንዲት አለማቀፍ ህግ ተቀብላለች ተብላ በምትታመን ሀገር እና ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እየተከተለች ነው በምትባል ሀገር ውስጥ ስርአትን (ወንጀልን) የሚፈጽሙ ፈር የለቀቁ የመንግስት ሹመኞች እና ፈር የለቀቀ መንግስት ያለበት ሀገር ላይ የዜጎች ሰብዊ መብታችን ይከበር ጥያቄ በተመሳሳይ መልኩ በቤንች ማጂ ዞን በገረ ፈርዳ ቁጥራቸው ወደ 82 የሚደርሱ አባዋራዎች ላይ የተከሰተ ነው፡፡
እነዚህ አባዋራዎች ለረጅም አመታት በክልሉ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል በሰፈራ መልክ የመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰፋሪዎች በህጋዊ መንገድ ከመንግስት አካላት እና በሀገራችን ወግ ባህል መሰረት የሀገር ሽማግሌዎች ባሉበት ህጋዊ ሰነድ የተሰጣቸው ሆነው ሳለ በህገወጥ መንገድ መሬት ይዛችኃል በማለት የዞኑ መስተዳድር እና የክልሉ መስተዳድር በጣምራ ንብረታቸውን ወርሰው ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ እያፈሱ ከአካባቢው አስወጥተዋቸዋል፡፡
በሌላ መልኩ ዜጎች በሀገሪቱ ህገመንግስት አንድ የአገሪቱ ዜጋ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ተዘዋውሮ የመኖር ንብረት የማፍራት መብቱ የተጠበቀ ነው ይላል፡፡ በዚህም መሰረት በሰፈራ መልኩ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ የሰፈሩ ዜጎች ለረጅም ዓመታት ያፈሩትን ንብረት ሜዳላይ ጥለው እንዲሰደዱየማድረጉ ሂደት በመጠን እና በኢሰብአዊነቱ እስከ የካቲት 2005 ዓ.ም ቀጥሏል፡፡ የነዚህን ዜጎች ህገመንግስታዊ መብት ሊያስከብር የሚችል መንግስታዊ አካል ያለመኖሩ ነገሩ ፖለቲካዊና በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች በሰዎች ላይ ሲደርሱ ምን ያህል የኢኮኖሚ፤የማህበራዊ እና የስነልቦና ጫና እንደሚስከትል ለማንም ሰብአዊ ፍጡር ግልጽ ነው ይህም ጉዳቱ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና በማህበረሰቦች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት የሚጎዳ ነው፡፡
4.4.በቤንች ማጂ ዞን
– በቤንች ማጂ ዞን በተለያዩ ቀበሌዎች ለረጅም ዓመታት ከነባሩ ህዝብ ጋ በጋራ ተሰብስበው ይኖሩ የነበሩ ዜጎች “አዲስ መጤ” ወይም ነባር ነዋሪ ያልሆነ በሚል ለሰበብ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዚያት ከ17 (አስራ ሰባት) በላይ አውቶብሶች በመጫን ወደ ተለያዩ የአማራ ብሄራዊ ክልል በሀይልና በግድ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉን በቅርብ ግዜ የተፈናቀሉት ዜጎች ያስረዳሉ፡፡ይህ ሀላፊነት የጎደለው ዜጎችን አስገድዶ ከቦታ ቦታ የማፈናቀል ድርጊት የተከናወነው በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችን እና ህዝቦች እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት መካከል የተደረሰ ስምምነት መሆኑን ተፈናቀዮቹ ይገልጻሉ፡፡ ዜጎቻችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር የመኖርና ሀብትን የማፍራት ህገመንግስታዊ መብታቸውን በጣሰ መልኩ የማፈናቀሉን ድርጊት በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ግልጽ ትዕዛዝና የቤንች ማጂ ዞን አስተዳደር የማስፈጸም ሀላፊነት እንዳለበት የተጻፈው ግልፅ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
– ሰኔ 10 ቀን 2001 ዓም ለቤንች ማጂ ዞን አስተዳደር ሚዛን ተፈሪ በሚል ስድስት ነጥቦችን የሚያትት ሰርኩላር ለቤንች ማጂ ዞን ዋና አስተዳድር በክልሉ ርዕሰ መስታዳደር ክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ መተላለፉን ከደብዳቤው የተገኘው ማስረጃ ያረጋግጣል፡፡
– በሌላ በኩል ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም በቤንች ማጂ ዞን ለሱፒ ቀበሌ አስተዳደር በህገወጥ መንገድ መሬት የያዙ አርሶ አደሮችን ይመለከታል በሚል በአቶ መረባ ቴሶ የተፈጥሮ ሀብትና አካበበቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ተወካይ ፊርማ የተሰራጨ ደብዳቤ ዜጎች የያዙትን መሬት ሙሉ ለሙሉ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርጉና መሬቱን ያላስረከቤቡ በጎጥ በመለየት ሪፖርት እንዲደረግ ጥብቅ መመሪያ መተላለፉን ከደብዳቤው ለመረዳት ይቻላል፡፡
– ከጥር 03 ቀን 2005 ዓ.ም በቤንች ማጂ ዞን በሚኒት ጎልዲያ ወረዳ በደምባብ ቀበሌና በፋርፋጅ ቀበሌ “አካባቢውን ልቀቁልን ወደ አገራችሁ ሂዱልን በሚል ሰበብ ከሁለቱም ቀበሌዎች ከ370 (ከሶስት መቶ ሰባ ) በላይ ሚሆኑ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ተደርጓል፡፡ ማፈናቀል ብቻ ሳይሆን ንብረት አልባ ተደርገዋል፡፡
– በፋርፋጅ ቀበሌ ከ330 ያላነሱ ዜጎች ከሚኖሩበት ቀዮና የአፈሩትን ሀብትና ንብረት ጥለው ወደተለያዩ ዘመዶቻቸውና ወደማያውቋቸው ግለሰቦች ዘንድ በመቀላቀል ቤተሰብ ለቤተሰብ የተበታተነ መሆኑን፤
– የተፈናቃይ ዜጎች ንብረት የሀኑ 61 በላይ የቀንድ ከብቶች የተዘረፈባቸው መሆኑን
– ቁጥራቸው ከ40 ያላነሱ በደምባብ ቀበሌ ይኖሩ የነበሩ አባዋራዎች መጠለያ አልባ ሆነው ሜዳ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን (ይህ ሪፖርት እስከተጠናከረበት ግዜ)
– በተደረገው ዜጎችን የማፈናቀል ድርጊት ህይወታቸው ያለፈና የቆሰሉ መኖራቸው ታውቋል፡፡
ሀ. በተገኘው መረጃ ህይወታቸው አልፉል ተብሎ የተጠቀሱት
1. አቶ ስራው አሰፋ ——– ከፉርፋጅ ቀበሌ
2. አቶ ገደፋው ——— ከፉርፋጅ ቀበሌ
3. አቶ አልቻል ጌታቸው —- ከደምባብ ቀበሌ
4. አቶ በዛብህ ጌታቸው —— ከደምባብ ቀበሌ
5. አቶ የኔአለም ዋሴ ——— ከደምባብ ቀበሌ
6. አባ ተስፋዬ ————— ከደምባብ ቀበሌ ናቸው፡፡
ለ. ከቆሰሉት መካከል
1. አቶ አዝመራው ገበያው ——- ከደምባብ ቀበሌ
2. አቶ ተስፋው እጅጉ ———— ከደምባብ ቀበሌ በእጅና እግራቸው ላይ በደረሰው አደጋ በባልቱማ ጤና ጣቢያ ህክምና የተደረገላቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
4.5.በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት
በተመሳሳይ ሁኔታ በቤኒሻንጉል ክልል በካማሺ እና በአሶሳ ዞኖች ከጥር ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ከሁለቱ ዞኖች በየጊዜው በጥቂቱ በጥቂቱ ሲያባርሩ የነበረ ሲሆን ከመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ግን ከአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ 2000፤ ከካማሺ ዞን ያሶ ወረዳ ከ8000 በላይ ከቡለን ወረዳ ከ5000 በላይ እንዲሁም ከሌሎች ወረዳዎች በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን በገፍ አንድን የህብረተሰብ ክፍል የማጽዳት አላማ ባነገበ መልኩ በማጎሪያ ጣቢያ ከማጎር ጀምሮ እሰከ በረሀብ፤ በውሀ ጥም፤ በሙቀትና በበሽታ እንዲያልቁ ማድረግን ጨምሮ በማጋዝ ንብረታቸውን በማውደምና በመውረስ ከአካባቢው እየተደበደቡና እየተሰቃዩ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ በዚህ ብቻ የሚያበቃ ያለመሆኑን አሁንም የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በዚህ ሰብአዊ መብቶች በሙሉ አንድ በአንድ ከመጣሳቸውም በላይ በዜጎች ላይ የሞት፤የአካል ጉዳት፤ ከባድ የሆነ የስነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል ተጽእኖውም ቀጣይ መሆኑ በተለይ በወጣቶችና ተማሪዎች ላይ የማረሚያ ርምጃ እስካል ተወሰደ ድረስ ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ ይህ ኢሰብአዊ ድርጊት ታቅዶና በተቀናጀ መልኩ በየአካባቢው መፈፀሙ ችግሩን ውስብስብና በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ስቃይና መከራ ለመቀነስም ሆነ ለማስወገድ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
4.6.በህዝበ ሙስሊም ላይ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች
- አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት በኢፌደሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 11 (1) ላይ የተመለከተውን መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ አንቀጽ 11 (3) መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሀይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ተብሎ የተቀመጠውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ በሙስሊም መሪዎች ምርጫ ውስጥ እጁን በማስገባት የእስልምና ተከታይ ዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በመጣስ ላይ ይገኛል፡፡
- በህገ መንግስቱ አንቀጽ 27 የሀይማኖት፤ እምነትና የአመለካከት ነፃነት በሚለው ስር (1) ማንኛውም ሰው የማሰብ ህሊናና የመረጠውን ሀይማኖት ወይም እምነት መያዝ ወይም የመቀበል ሀይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግልየማምለክ መከተል መተግበር ማስተማር ወይም ለመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ ንዑስ አንቀጽ (3) ሥር ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነት በሀይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይችልም፡፡ የሚለውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ አል ሀበሽ የሚባለውን የኢስላም አስተምህሮ በሙስሊሙ ላይ በግዳጅ ለመጫን፤ ድጋፍ በመስጠት የሙስሊም ማህበረሰብ የሚፈልገውን አይነት አስተምሮ እንዳይከተል ጣልቃ በመግባት ላይ ነው፡፡
- መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ መግባቱን ያቁምልን በማለት በህገ-ምንግስቱ አንቀጽ 30 ላይ የተረጋገጠላቸውን የመሰብሰብ፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብታቸውን ተጠቅመው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄ ያቀረቡ የእስልምና እምነት ተከዮታች ላይ ድብደባ ህገወጥ እስር እና ህገ ወጥ ብርበራ በማድረግ መብታቸውን ጥሷል፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መርጦ የወከላቸውን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የሆኑ 29 ሰዎችን የፀረ ሽብር ህግ አዋጅ ቁ 625/2003 መሰረት በማድረግ የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
መንግስት በህገመንግስቱ አንቀጽ 20(3) ላይ የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ላይ ባሉበት ግዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፤ በምስክርነትእንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው የሚለውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ በመተላለፍ “ጅሀዳዊ ሃረካት” የሚል ዶኩመንተሪ ፊልም በማስተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ባሉት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በሆኑት 29 ተጠርጣሪዎች ላይ እስከ ሚፈረድባቸው ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በመጣስ ወንጀለኛ አድርጓቸዋል፡፡
4.7 በቁጫ ህዝብ ላይ የተፈጸመ የስብአዊ መብት ጥሰት
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በጎፋ ዞን ቁጫ ወረዳ የሚኖሩ የቁጫ ህዝቦች ባነሱት የመብት ጥያቄ ምክንያት በዞኑ አስተዳደርና በጸጥታ አካላት የከፋ የመብት ጥሰትና ማሰቃየት እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ፡፡ የህዝቡን ጥያቄ አንግበው ወደ ተለያዩ አካላት ጥያቄውን ይዘው በማስፈጸም ላይ በሚገኙ ተወካዮች ላይ ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በማድረግ ሰላማዊና ህጋዊ የሆነውን የህዝቡን ጥያቄ በማሰርና በማሰቃየት ለማፈን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በቁጫ ህዝብ ላይ በተደጋጋሚ የማስፈራራት ዛቻ ድብደባ እና እስር እየተፈጸመ ነው፡፡ በዚህ ዘመቻ በእስር ከተሰቃዩት መካከል
- ደፋሩ ዶሬ 11. እዮብ ጠና 21. አየለ አካኮ 31. ተክሉ ንኮላ
- ሸምበል ሸዋ 12. እስራኤል ሰርካ 22. ይሳቅ ታንጋ 32. እንዳቦ ንኮላ
- አማኑኤል ጎቶሮ 13. ዘውዴ ሰርካ 23. አየለ አሻቦ 33. ሀይሌ ንጉስ
- ትኮን አሸጎ 14. ሕዝቆል ቶማስ 24. ጴጥሮስ ዘውዴ 34. በርገነ ባሳ
- አበራ ገ/መስቀል 15. ብርቁ አንበሴ 25. አብርሀም አንጃ 35. ስሞን ደግሰው
- ጴጥሮስ ሀላላ 16. ባንቲርጉ ሄባና 26. ፈለቀ ደረጀ 36. መንግስቱ ሞና
- ወ/ሮ ግስታነ ሐላላ 17. መንግስቱ ገበየሁ 27. ሉቃስ ጎጃ 37. ሻንካ ባሳ
- መ/ር መሸሻ ዘማ 18. እንግዳ ቃኘው 28. ደረሴ ፖላ 38. ተማሪ ምስጥር ብርሀኑ
- መ/ር ደለቦ ሞንጃ 19. ጳውሎስ ኩሉላ 29. ዶላ ዳድሶ 39. ተማሪ አዝመን ብርሀኑ
- ሻ/ባሻ ፋንታሁን ታደሰ 20. ጋጋ ጋዳቦ 30. አስፋው ኤና 40. ፍቅሩ ኃ/ጊዮርጊስ
VI.ማጠቃለያ
የኢህአዴግ መንግስት የአገዛዙ መሳሪያ የሆኑትን የፖሊስና የደህንነት ተቋማትንና አባላቱን በመጠቀም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፤ በሲቪክ ማህበራትና በዜጎች ላይ በተፈጥሮ ያገኙትን መብት እንዲሁም በህገ መንግስቱና ሀገሪቱ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ሰነዶችና ስምምነቶች ጭምር የተረጋገጡ መብቶችን በመጣስ ዘግናኝ እና አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያደረገ ይገኛል፡፡
አገዛዙ በነዚህ ንፁሀን ዜጎች ላይ ከሚፈፅማቸው ዋና ዋና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች መካከል በድብደባ አካል ማጉደል፤ በህገወጥ መንገድ በቁጥጥር ስር በማዋል አስሮ ማሰቃየት፤ ማዋከብ፤ ማስፈራራት፤ መዛት፤ በማስገደድ መረጃ ከፓርቲያቸው እዲያመጡ ማድረግ፤ የፖለቲካ አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ፤ ከፖለቲካ ተሳትፎ እንዲርቁ በቤተሰብ በኩል ጫና ማድረግ፡፡ መኖሪያ ቦታን በህገወጥ መንገድ መበርበር፤ ይዞታንና ንብረትን ነጥቆ መውሰድ፤ አስገድዶ ቃል መቀበል፤ ድብደባ፤ ቶርቸር፤ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሶቦችን በእስረኞች ማስደብደብ፤ በቤተሰብ በጓደኛ በሀይማኖት አባት እንዳይጎበኙ መከልከል፤ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን በእኩል ሁኔታ ተወዳድረው ስራ እንዳይቀጠሩ የቅጥር አድሎ መፈፀም፤ በስራ ላይ ያሉትን በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እድገት እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች አንዳያገኙ ማድረግ እንዲሁም በችሎታቸው ልክ ወይም በእኩል ተወዳድረው የተሻሉ ኃላፊነቶችን እንዳይዙ ማድረግ፤ ይዞታቸውን ያለምንም ካሳ ወይም ከህጉ ከተፈቀደው መጠን ባነሰ ዋጋ በመገመት መኖሪያ ቦታንና ንግድ ቤትን በማፍረስ ዜጎችን መጠለያ አልባና ስራ አጥ ማድረግ፤ አማሪኛ ተናጋሪ በሆኑ ዜጎች ላይ ሌሎችን ማነሳሳት ከመኖሪያ አካባቢያቸው በሀይል ማፈናቀል መግደል መደብደብ ንብረት አልባ ማድረግ ማንኛውንም ኢሰብአዊ ድርጊት መፈፀም ወደ ሀገራችሁ ሂዱ እስከሚለው ድረስ፤ ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን በመጣስ የፓርቲ ልሳን የሆነን ጋዜጣን እንዳይታተም እንዳይሰራጭ ልዩ ልዩ ገደቦችን ማድረግ፤ መንግስትና ሀይማኖት የተለያዩ ናቸው አንዱ ባንዱ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚለውን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ ለአንዱ አስተምሮ ድጋፍ በማድረግ ሌሎችን አስተምሮዎች ለአክራሪነት ጽፈኝነት እና ሽብርተኝነት የተጋለጡ ናችው በማለት መጫን በተከታዮቹ ላይ ማስፈራራት መዛት ማሰር መደብደብ የኢኮኖሚ ጫና ማድረግ በሽብርተኝነት መፈረጅ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው በፍርድ ሂደት ላይ እያሉ ወንጀለኛና ጥፋተኛ ናቸው በማለት በሚድያ መፈረጅ በፍርድ ሂደቱ ላይ ጣልቃ መግባት፤ አባላቱንና ደጋፊዎቹን በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ በማደራጀት ሁሉንም የአመራር ቦታዎች የየሀይማኖቱ አሰራሮች ከሚፈቅዱት ውጭ ምርጫን በማካሄድ መቆጣጠር በዚህም በአማኞች መካከል መከፋፈልንና ልዩነትን መፍጠር አድሎ ምዝበራ እንዲስፋፋ ማድረግ፡፡
የኢህአዴግ አገዛዝ ከላይ በጥቂቱ የተጠቀሱትን ኢሰብአዊ ድርጊቶች የሚፈፅመው ህግን ከለላ በማድረግና በማንአለብኝነት እንዲሁም በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው ሰብአዊና መሰረታዊ መብቶች ነፃነቶችን በሚገድቡና ከሀገሪቱ የበላይ ህግ ከሆነው ህገ መንግስት ጋር ግልጽ ተቃርኖ ባላቸው ህጎች ደንቦች መመሪያዎች እና የአሰራር ስርአቶች በመጠቀም ሲሆን እንዲሁም ከህግ በላይ በሆኑት ባለስልጣኖች፤ ካድሬዎች እና አባላቱ በመጠቀም ነው፡፡ በተጨማሪም በሶስቱ የመንግስት አካላት መካከል ግልጽ የሆነ የስልጣን ክፍፍል እንዳይኖር በማድረግና የመንግስትን ስልጣንን የሚገድቡ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በመጣስ፤ ሲቪል ሰርቪሱም በገልለልተኝነት ዜጎችን እንዳያገለገል ዋናው ስራው የፓርቲ ስራ እንዲሆን በማድረግ ከሁሉም በላይ ለሰብአዊ መብት መከበር ለዴሞክራሲያዊ ስርአት መረጋገጥ ዋስትና ተስፋ መተማመኛና ከለላ ሊሆኑ የሚችሉትን ተቋማት በተለይ የፍትህ፤ የምርጫ ቦርድ፤ የሚድያ፤ የሲቪክ ማህበራት፤ የትምህርት እንዲሁም በገለልተኝነት መቆም የሚገባቸውን የመከላከያና የፀጥታ ተቋማትን የአሰራር ነጻነት ሽባ በማድረግና በመቆጣጠር በዜጎች ውስጥ የነበረውን በሰላማዊ መንገድና በውድድር የስልጣን ሽግግር በሀገሪችን ይካሄዳል የሚለውን ተስፋ በማጨለም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
በጥቅሉ ስርዓቱ የዜጎችን ተፈጥሯዊ እና ሕገ መንግስታዊ ከለላ ያገኙ እንዲሁም ሀገሪቱ ተቀብላ ያጸደቀቻቸውን አለም አቀፍ የስብአዊ መብት ሰነዶችንና ስምምነቶችን በመጣስ የዜጎችን መብቶችንና ነጻነቶችን በመሸራረፍ ወደ ፍፁም አምበገነናዊነትና ጠቅላይነት ተሸጋግሯል፤ ተለውጧል፡፡ ስርአቱ በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት እውቅና የተሰጣቸውን ከአንቀጽ 14 እስከ 28 የተዘረዘሩትን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በተለይም በህይወት የመኖር መብት፤ የአካል ደህንነት መብት፤ በህግ ፊት እኩል የመታየት፤ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጭ ነፃ ሆኖ የመቆጠር፤ ሀሳብን በነጻነት የመያዘ መብቶች ላይ እቀባ በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እንቅፋት ሆኖል፡፡ በመሆኑም ዜጎች ለመብታቸው ለሀገራቸው ሰላም እና ደህንነት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እና የተረጋጋ የስልጣን ሽግግር እንዲሁም የሰላማዊው የፖለቲካ ውድድር ጨርሶ ከአማራጭነት እንዳይወጣ በመንግስት ላይ ወቅታዊና ተገቢ ጫና ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም ሰላም ወዳድ የሆኑ የኢህአዴግ አባላት በወንጀልና በሙስና የተጨማለቀውን ድርጅታቸውን በማደስ የበኩላቸውን አስተዋፅዎ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የተለያዩ የመንግስት ተቋማትም ለምሳሌ ምረጫ ቦርድ፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ የእንባ ጠባቂ ተቋም፤ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፤ የዋና ኦዲተር፤ የፍትህ ተቋማት አና ሌሎችም አሰራሮቻቸውን በመፈተሸ በስርአቱ የሚፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ሙስና በማጋለጥ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ማበብ የማይተካ ሚና ያላቸውን ነፃ ገለልተኛ የሚሰሩ ተቋማት ለመፍጠር መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሀገራችን የሚገኙ የሲቪክ ማህበራትም ለህግ የበላይነት ለሰብአዊ መብት መከበር እና ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ማበብ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል በተለይ ለሰብአዊ መብት ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ትልቅ አስተዋፅዎ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ቁልፍ ሚና ያለው ሚድያ እና የትምህርት ተቋማት የሰብአዊ መብት ማክበርን ማስከበርን መርሁ የሚያደርግ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማህበረሰቡ የፖለቲካ ባህል ከምንአገባኝ፤ ምንቸገረኝ፤ አድርባይ እና ሀይል አምላኩ ከመሆን እንዲወጣና እንዲፀዳ የበኩላቸውን አስተዋፅዎ እንዲወጡ እንጠይቃልን፡፡ የአለምአቀፉ ማህበረሰብም በሀገራችን ለሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ሽግግር አውንታዊ ሚና ለመጫወት ለሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ነፃነቶች መከበር ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ጥሪያችንንም እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም ይህ የሰብአዊ መብት ሪፖርት በሀገራችን ለሚካሄደው የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ለሰብአዊ መብት መከበር አስተዋፅዎ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ እንዲሁም በድርጅታችን ሲዘጋጅ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን በማስረጃና በሌሎች ምክንያቶች ለቋሚ ኮሚቴው ከሚቀርቡ አቤቱታዎች እና ጉዳዮች እጅግ ጥቂቱን ክፍል የያዘ በመሆኑ ጉዳያቸው ያልተካተተ አባላትን ደጋፊዎችን ዜጎችን ይቅርታ እየጠየቅን ሪፖርቱ ያሉበትን ውስንነቶች ወደፊት ለማስተካከል ከየትኛውም አካል የሚቀርብ አስተያየት በቀናነት የምንቀበል መሆኑን እንገልፃለን፡፡
አባሪ
በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
የሕግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀ
የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት
አዲስ አበባ
መስከረም 2006 ዓ.ም