ሀይሌ ገብረስላሴ ስልጣን ለቀቀ

በተለያየ ጊዜ ተቃውሞው የበረታበት አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ስልጣን መልቀቁን አስታወቀ፡፡ ዛሬ በቢሮው መግለጫ የሰጠው ሀይሌ ላለፉት ሁለት አመታት አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ሲመራ እንደቆየ ገልፆ፣ በእነዚህ አመታት ውስጥ የተለያዩ ከበድ ያሉ ችግሮችን ከስራ አስፈፃሚው ጋር በመሆን ሲፈታ እንደቆየ አስረድቷል፡፡ ‹‹በተለያዩ ወቅቶች የፌዴሬሽናችንን የአሰራር ችግሮችን አንዳንድ ግለሰቦች ትልልቅ ተቋማትን መከታ አድርገው የፌዴሬሽኑንና የአለም አቀፍ አትሌቲክስ መርሆዎችን ለማስቀልበስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል›› ያለው ሀይሌ ጨምሮም ‹‹ይህም ጥረታቸው በትላንትናው እለት ማለትም ህዳር 2 ቀን 2011 ሲሉልታ ላይ በተደረገው የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ በየትም አለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች ላይ የማይፈፀም ድርጊት እንዲፈፀም አድርገዋል፡፡›› ሲል በመግለጫው ተናግሯል፡፡ ድርጊቱ ምንም የማይበጅ ጎጂና አደገኛ ነገር መሆኑን ቀድሞ እንደተረዳ የጠቀሰው ሀይሌ ይሁንና ጉዳዩን በትእግስት እንደጠበቀው፣ ድርጊቱም ከፍተኛ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል መሆኑን አስረድቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ስልጣን ለመልቀቅ ውሳኔ ላይ መድረሱንና ስልጣኑን ከዛሬ ህዳር 3 ጀምሮ የእሱ ምክትል ለሆነችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ እንዳስረከበ ተናግሯል፡፡

ሀይሌን ለስልጣን መልቀቅ ያበቃው በትላንትናው እለት የተደረገውን ተቃውሞ በተመለከተ ዘሃበሻ ማጣራት አድርጋ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጀው 2ተኛው የሱሉልታ አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ውድድር ተቃውሞ ያሰሙት የኦሮሚያ አትሌቶች እንደነበሩ ከምንጮች ለመረዳት ችለናል፡፡ የ8 እና የ12 ኪሎ ሜትር ሩጫንና የዱላ ቅብብልን ባካተተው በዚህ ውድድር አትሌቶቹ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ተቃውሞ እንዳሰሙ የጠቀሱት ምንጮች የመፈክሮቹን አይነትም በፎቶግራች አስደግፈው ልከውልናል፡፡ ትላንት በተቃውሞው ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጦ አሯሯጭ ሆኖ ወደ ውጭ ሃገር የተላከ አትሌትን ጉዳይ፣ ያሉት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በፍትሃዊነት ስለመጠቀም፣ ፌዴሬሽኑ ብር ባንክ ከዝኖ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ግንባታ ቸል ማለት እንዲሁም ለትጥቅ ብቻ እስከ 23 ሚሊዮን ብር ወጭ እያደረገ በስፖርት ትጥቅ እጦት ከስፖርቱ እየተገለሉ ያሉ ወጣቶችን አይቶ እንዳላዬ ማለፉ፣ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ሰዎች ለጥቅማቸው ሲሉ አንጋፋ አሰልጣኞችን ማግለል ይቁም እና ሌሎችም በመፈክር መልክ ቀርበው ነበር ተብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ግብረ ኃይል ቀጣይ እቅዱን ይፋ አደረገ

በቅርቡ የአለም ሻምፒዮናና የአገር አቋራጭ ውድድሮች የሚከናወኑ ከመሆኑ አኳያ የሀይሌን በዚህ ወቅት ስልጣን መልቀቅ ጊዜውን ያልጠበቀና ‹‹ለአገር ከማሰብ ይልቅ የግል ዝናን በማስቀደም ርካሽ ተወዳጅነት ለማትረፍ የተደረገ ውሳኔ ነው›› ብለዋል አንድ አስተያየት ሰጪ፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=2woW6QIeHHY

2 Comments

 1. ኃይሌ ቀንድ አወጣ!!!

  በሩጫ የምንወደው ብዙ ድል ያመጣ፤
  ባደባባይ አየን ኃይሌ ቀንድ አወጣ!!!
  ጉጅሌን በርኩሰት አገር ሕዝብ ያውቀዋል፤
  ኃይሌ ያንተን እንጃ፣ሰዉ ግና ያማዋል።
  እንኳን ሥልጣንና ገና ስትገረፍ፤
  ታወጣለህ ጉድክን በቃህ አሁን መለፍለፍ።
  ከነማን ጋር ሆነህ፣የት እንደምትገብር፣
  ምን ምን እንደምታርድ፣እንዴት እንደምትጨፍር።
  ካለብህ ቀይ ቆሌ፣በጭለማ የሚታይ፤
  ከእግዜር የሚያጣላህ መስቀል ፀበል ስታይ።
  በመምህር ግርማ መረጨትህን ካላየነው፤
  የአጋንንት ፈረስ መሆንክን ነው የማምነው።
  እናም ለቤተሰብህ ስትል መካሪ ሳታጣ፤
  ጀግናው ኃይሌ እባክህ ውጣ ከዚህ ጣጣ።
  ወይ ጉድ!!!
  ጀግናችን ምን ነካው፣ወፈፍ እያረገ፤
  ኃይሌ መካሪ አጥቶ፣ደጋግሞ ባለገ።
  ስልዚህ የባሰ ጀግናው ላይ ሳይመጣ፤
  መፍትሄ የሚሆን መላ ከየት ይምጣ?
  ኃይሌ ገ/ሥላሴ:-መጥፋት ብቻ አይደለም፤
  ገና ትረገማለህ ለትውልድ ዘላለም።
  ሮጦ ጀግና ነበር:-ሳይገጥም ከባንዳ፤
  የኢትዮጵያ ሕዝብን ለሥልጣን ሲል ከዳ።
  ብዙ ድሎች ለአገር፣በኢትዮጵያውያን ስም፤
  ዋንጫዎች ሲያመጣ በደስታ ስንስም፤
  በአክብሮት ወደድነው፣በዓለም ዙሪያ እስከጫፍ፤
  ምሥክሮች ሆንን በጀግንነት ሲጻፍ።
  በዚያ ያለም ድላችን ሕዝብ ደስብሎት ሳለ፤
  ባገራችን ደግሞ ፍትህ ተጓደለ።
  እናም ፀረ-ሕዝብን የምር ስንታገል፤
  ኃይሌ ግን ዝም አለን ይባስ ስንገደል።
  መከርን ከሻምበል:-ጦር ግጠም አላልንም፤
  ባንዳ እንዳይሆን ሰጋን ጀግናችን ቢሆንም።
  ግና ሕሊና ሸጦ፣ውስጡን እኛን ከዳ፤
  የሕዝቡንም ንብረት ሰጣቸው ለባንዳ።
  እናም ደጋገመ መንገሥም ፈለገ፤
  ምላስም አበዛ በግልፅም ባለገ።
  ይሄኔ ነበረ ርኩስ ላይ እንዳይወድቅ፤
  ጥላቻው እንዳይበዛ የነበር ስንደብቅ።
  ምሁራንን መሰሎ እንግሊዝ አበዛ፤
  ማሽሟጠጥ ጀመረ ከሃዲ ልብ ገዛ።
  በጅምላ መናቁ፤በዛና ውርደቱ፤
  በአብዮታዊ ልሳን ተሰማን ቅኝቱ።
  እንዲያ ሕዝቡን ሲንቅ፣ሲዘልፍ ሐይማኖትን፤
  አስማተኛ እያለ ሲሳደብ አባትን።
  አየን ባደባባይ ርጉም ቃል ሲናገር፤
  ጀግናችን ብለነው፣እንዲያ እንዳልነበር።
  ወዲያው ሌሎች መጡ ተያዝን የሚሉ፤
  ሰበብ ሆኖባቸው የሩጭቸው ድሉ።
  እንዲያ የተኩራራበት አሳፋሪ ቃሉ፤
  ለራሱም አሰኘው ይድረስህ ጠበሉ።
  በቃለ-መጠይቅ በሽሙጥ አንደበት፤
  እንደተናገረው ይሞክር ይግባበት።
  እናም ጀግናው ኃይሌ ነካ ያደረገው፤
  መካሪ አጥቶ አይቅር ዛሬ እንደባለገው።
  በሩጫው ድል ለሕዝብ ከዓለም ላይ ያመጣ፤
  በደስታ ያስለቀሰን ኃይሌ ቀንድ አወጣ!!!
  ስልዚህ የባሰ ጀግናው ላይ ሳይመጣ፤
  መፍትሄ የሚሆን
  መላ የሚያውቅ ይምጣ?

Comments are closed.

Share