November 12, 2018
6 mins read

ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ የህግ የበላይነት ከሌለ ሁሉም እያዘዘ የሚኖርበት ስርአት ይፈጠራል አሉ

Screen Shot 2018 11 12 at 9.25.07 AM

የቀድሞዋ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ አመራርና የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስራችና መሪ የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ለንባብ ከበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ በዚህ ቃለምልልስ ከሌሎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዘግየት ብለው ለምን እንደመጡ ሲጠየቁ፡-

‹‹እኔ የዚህ አገር ለውጦች መታየት ከጀመሩ ወዲህ ሁልጊዜ ወደዚህ መምጣት እፈልግ ነበር›› ካሉ በኋላ ያለባቸው የቤተሰብ ሃላፊነት እንዳዘገያቸው ገልፀዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹ያው የቤተሰብ ሃላፊነት አለ፣ እና ልጄን የማሳድገው ብቻዬን በመሆኑ እንዲሁም ተማሪም ስለሆነች እነዚህን ማስተካከል ነበረብኝ፡፡ ግን ያም ቢሆን ለስራ በጣም ዘገየ የሚባል አይመስለኝም›› ብለዋል፡፡

ከጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድና አቶ ለማ መገርሳ ጋር ሲነጋገሩ የተነሱት ፎቶግራፍ በሰፊው መሰራጨቱን በማስመልከት በወቅቱ ምን እንደተነጋገሩ የተጠየቁት ወ/ሪት ብርቱካን ሲመልሱ ‹‹ብዙ ነገር አንስተናል፡፡ መጀመሪያ ምስጋና በእኔ በኩል አቅርቤያለሁ፡፡ ምክንያቱም እነሱም እንደሌሎች ታጋዮች ሁሉ ሃላፊነት ወስደው በህይወታቸውም ጭምር ይህንን ለውጥ ለማምጣት በመቻላቸው፡፡ በውስጥ ሆው ሪፎርም ለማድረግ በመሞከራቸውና ያንን ቁርጠኝነት ወስደው ለውጥ በማምጣታቸው ያለኝን አድናቆትና አክብሮትም ቸሬያቸዋለሁ፡›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ወራት ለውጡን ለማስጀመርና ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት በመልካምነት የተመለከቱት ወ/ሪት ብርቱካን ለውጡ ምንም እንኳ በህዝብ ጥያቄና በህዝብ ትግል የመጣ ቢሆንም ከውስጥ መምጣቱ ደግሞ ሊያጋጥሙ ይችሉ የነበሩ ትልልቅ ኪሳራዎችን ለመቀነስ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከለውጡ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉትን ግጭቶች የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትን በመገንባትና እነዚያ ተቋሞች በህግ በተቀመጠ ትክክለኛ አሰራር በማነፅ ለማስተካከል እንደሚቻልም ምክር ለግሰዋል፡፡

ወደአገር ቤት ከገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ትጥቅ አንፈታም ያሉትን በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ ደግሞ ‹‹እኔ እዚያ ላይ ሁለት ነገር ነው ማለት የምፈልገው፡፡ አንዱ የህግ የበላይነት መከበር አለበት፣ ምክንያቱም ህግ ያልተከበረበት አገር አገር ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡ የህግ የበላይነት ከሌለ ሁሉም እያዘዘ የየሚኖርበት ስርአት ይፈጠራል፡፡ ወደዚያ ደግሞ ማንም መግባት ይፈልጋል ብዬ አላምንም፣ መንግስትን ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ ዜጎችም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ከህግ ስር መሆንና ህግን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡.. ስለሆነም ፖለቲካችንን ከዚያ ለማፋታት በጣም የሰለጠነ ውይይትና ክርክር ወደማድረግ ለመውሰድ መሞከር አለብን፡፡ ምክንያቱም ብዙ የሚጠበቅብን የቤት ስራ አለና›› ብለዋል፡፡

‹‹እኔ የተለየ ፅናት አለኝ ብዬ አልቆጥርም›› ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን አሁን ለሴቶች እየተሰጠ ያለውን ስልጣን አድንቀው ‹‹ እኔ አሁን የተሾሙት ሴቶች ብዙ ነገር እንደሚያሳኩ እምነት አለኝ›› በማለት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ወደፊት አገራቸውን በምን መስክ ማገልገል እንዳሰቡ በተጠየቁበት ወቅት ደግሞ ትምህርታቸውም ሆነ ልምዳቸው ከህግ፣ ከፖሊሲና ከዲሞክራሲ ተቋማት ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በእነዚህ መስኮች የተሻለ ነገር ለመስራት ብቅ እንደሚሉ ተናግረዋል፡፡ ለምርጫ ቦርድ ታጭተዋል የሚባለውን ጉዳይ በተመለከተ ተጠይቀው ‹‹እካሁን በቂ መረጃ የለኝም›› በሚል መልስ አልፈውታል፡፡

 

92494
Previous Story

ሀይሌ ገብረስላሴ ስልጣን ለቀቀ

92506
Next Story

ሜጀር ጀነራል ክንፈ ወደ ሱዳን ሊያመልጡ ሲሉ ሁመራ ላይ ተያዙ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop