October 23, 2013
30 mins read

ፍራንክፈርት፣ ሳዋ ፣ሳሃራ ፣ ሜዲትራንያን፣ ላምባዱሳ

በልጅግ ዓሊ
ይህ የሆነው ጀርመን ፍራንክፈርት ውስጥ ነው። ወቅቱ በጋው ላይ ነው። እንደ አብዛኛው የአውሮፓ
ከተማዎች የፍራንክፈርት ውበት በበጋው ደመቅ ያለ ነው። በእንደዚህ ደስ በሚል ቀን ከትልቁ ባቡር ጣቢያ
ተነስቼ ሃብትቫኸ(Hauptwache) ወደሚባለው የከተማው ማዕከል ከዚያም አልፌ በእግር መጓዝን
እወዳለሁ። በጉዞዬ ወቅት በስተጎን እያለፍኩት የምሄደው ካይዘር መንገድ(Kaiserstraße) በመባል
የሚታወቀው የሴተኛ አዳሪዎች መንደር አለ። እዚህ መንገድ አካባቢ ተኮልኩለው የሚውሉትን ዕጽ
ተጠቃሚዎች በጎን እየገላመጥኩና የስልጣኔን በሽታ እያወገዝኩ አልፋለሁ።

እነሱን አልፌ ሴተኛ አዳሪዎቹ ከሚገኙበትን ፎቅ ስደርስ የተለመደውን ግር ግር ማየት ደስ ይለኛል።
ሴቶቹን ፍለጋ ፎቁን ለመውጣት የሚራወጠው ጎረምሳና አንዳንዴም የሽማግሌ ችኮላ የማያቋርጥ የሁል ጊዜ
ክስተት ነው። ገና ጀርመን እንደመጣን ለማየትም ይሁን ለሌለ ነገር በዚህች ፎቅ ዙሪያ ያልተመላለስን
አልነበረም። የተለያዩ ሃገር ሴቶች በሚማርክ ሁኔታ ደንበኛ ሲጠብቁ ማየት የሚገርም ነው። ገንዘብ ቀንሺ፣
የለም አንተ ጨምር፤ ክርክሩ አይጣል ነው። በምንም ቋንቋ የማይግባቡ የሁለት አህጉር ሰዎች በምልክት
ተግባብተው አንሶላ ተጋፈው በትንሽ ደቂቃ ይለያያሉ። ተግባራዊ ንቅናቄ እንጂ ንግግር የለም። በገንዘብ
የተስማማው ጭልጥ ብሎ ክፍሉ ውስጥ ሲገባና ከትንሽ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ላብ ጠምቆት የግንባሩን ላቦት
እየጠረገ ፈትለክ ብሎ ለማምለጥ የሚደርገው ሙከራ ሲገባ አንበሳ ሲወጣ ድመት ያስመስለዋል። ጥድፊያው
ከበዛበት የአውሮፓ ኑሮ ጋር እንኳን ሲወዳደር ካይዘር መንገድ ላይ ከሁሉም የበለጠ ጊዜ ወርቅ ነው።
ሰውየው ከወጣ በኋላ እመቤቲቱ ተሽሞንሙና እንደገና ከሌላው ጋር መደራደር ትጀምራለች። ይህ ሁሉ
በሃብታሙ የጀርመን ሃገር በሕግ ተፈቅዶ የሚደረግ አይመስልም።
ከፎቆቹ በታች ደግሞ እየተከፈለ የሚታይ ራቁታቸውን የሚደንሱ ቆነጃጅቶች አሉ። እነዚህን ማየት
የሚያዘወትሩት በብዛት ግዜ ያለፈባቸው ሽማግሌዎች ናቸው። ልብ ብሎ ለተመለከታቸው ሽማግሌዎቹ እኛ
ካረጀን ምን ዓይነት ሰውነት ተፈጥሮ ይሆን? ብለው ይህኑን አዲስ ሰውነት በማየት ልጅነታቸው ይመለስ
ይመስል ጠዋት ማታ ይመላለሳሉ።
ይህን ሁሉ ቲያትር ሳይመለከት ሻንጣ እየጎተተ ወደ ከባቡር ጣቢያ የሚነጉድ መንገደኛ ደግሞ ባቡር
እንዳያመልጠው ይኳትናል። እኔም ይህንን ሁሉ እየታዘብኩ የተለመደ ጉዞዬን እቀጥላለሁ። ፍራንክፈርት
በየዓመቱ ትለወጣለች። ሕንጻዎቹም እኛ ስንመጣ እንደነበሩት አይደሉም። ቁመታቸው እያደገ፣ ጥራታቸው
እየጨመረ መሄዱ የሚገርም ነው። የስራ መስኮችም በዚያው ልክ ይከፈታሉ። የውጭ ዜጋው ቁጥርም
ከሥራው መስክ ጋር አብሮ ይጨምራል።
ከሌሎች ከተሞች የሚገኙ ዜጎቻችን ሥራ ፍለጋ ወደ ፍራንክፈርት በመምጣታቸው የዜጎቻችንን
ቁጥር በዚያው ቀጥር እያበዛው መጥቷል። ከቁጥራችን መብዛት የተነሳ እንኳን የሩቁን፣ ከቅርብ ጎረቤቶቻችን
ጋር መነጋገር ተስኖናል። ከመብዛታችን የተነሳ መንገድ ላይ ስንተያይ ሰላም መባባል ከቆመ ስንበትበት ብሏል።
እንዲውም የቆየና አዲስ መጤ የሚ’ለይበት በሰላምታ ሆናል። የቆየው የስደተኛ ጉዳዩ ስለተፈጸመለት
የማያውቀውን ሰው ሰላም ማለቱን ትቶታል። አዲሱ ግን የሃገሩን ልጅ ወገኑን ሲያይ ብቸኝነቱ የሚቀልለት፣
ችግሩም የሚፈታለት፣ እየመሰለው ሰላም ማለት ያበዛል።
እኔ ግን ገና እንደ አዲስ መጤ ነው የሚያደርገኝ። ሰላም ሳልል ማለፍ አሁንም አይሆንልኝም።
እንኳን የሃገራችንን፣ የአህጉራችንንም ዜጎችን አላልፍም። እንዲውም በሰላምታዬ ግራ ተጋብተው የት ነው
የምናውቀው ብለው ለሚጨነቁት የተደጋገመ ሰላምታ እሰጣለሁ። በመርሳታቸው ራሳቸውን እንደ ጥፋተኛ
ቆጥረው ዓይናቸውን እስከሚያጥፉ ድረስ ትክ ብለው የሚያዩኝ ጥቂት አይደሉም።
ከዕለታት በአንዱ የተለመደ ጉዞዬ ላይ ወጣት የሆነ ዜጋችንን ሰላም አልኩት። ፈገግ ብሎ ጠጋ አለኝ።
ሁኔታው ከዚህ ቀደም የሚያውቀኝ መሆኑን ያሳብቃል። ዘንግቸው ይሆን? አሁን ጉድ ፈላ። አሁን የት ይሆን
የሚያውቀኝ? እኔው ራሴ ግራ ተጋባሁ። ሰላምታ ተለዋውጠን መንገዳችንን አንድ አድርገን ጉዟችንን ቀጠልን።
“እዚሁ ፍራንክፈርት ነው የምትኖረው?’’¤የኔ ጥያቄ ነበር።
“አይደለም አብረን ነው የምንኖረው ያወቅከኝ መስሎኝ ነው’ኮ።’’¤ረጋ ብሎ መለስ።

“ኦ ይቅርታ ዘንግቼ ይሆናል።’’ እንደ ሃፍረት ተሰማኝ። ማፈሬን አውቆብኝ በፈገግታ አበረታታኝ።
“ሰፈር ሁልጊዜ መንገድ ላይ ሰላም ስለምትለን የለየኸን መስሎኝ ነበር።’’
አሁን ገባኝ። የምኖርበት አካባቢ ከሚገኘው ቡና ቤት ደጃፍ ላይ በበጋው ተሰብስበው ከማያቸው
ወጣቶች መሃል ነው። “ይቅርታ ብዙ ስለሆናችሁ አልለየኋችሁም። ሁል ጊዜ ቡና ቤቷ ጋ ተሰብስባችሁ
ሳያችሁ ከእናንተ ጋር ተቀምጬ መጫወትን እፈልጋለሁ ግን እንዳልደብራችሁ በሚል ስጋት. . .’’ብየ የት
እንደምንተዋወቅ ሲገባኝ በድፍረት ቀጠልኩ።

“ሁል ጊዜ ሰላም ስትለን ደስ ይለናል። ለጓደኞቼ በሞላ ትመቻቸዋለህ። ከቆዩት ሰዎች በደንብ ሰላም
የምትለን አንተ ነህ። ምን ችግር አለው ብትመጣና ብትቀመጥ። መጫወት እንችላለን። ግን አንዳንዱ የእኛ
ጨዋታ ላይመችህ ይችላል።’’¤
እንዲህ የተጀመረ ጓደኝነት ነበር “ቀለበቴን ስጧት’’¤በሚለው መጽሐፌ ውስጥ የተካተተውን “የሁለት
ትውልድን ወግ’’¤ የወለደው። በሁለት ትውልድ ወግ ውስጥ የሰሃራን ጉዳይ ስተርክ በወቅቱ ከወጣቶቹ
የሰማሁት አንድ ሌላ የሚያሳዝን ታሪክ ወደፊት የተሟላ መረጃ ሳገኝ እጽፈዋለሁ ብዬ የቆጠብኩት ጉዳይ
ነበር። ሳዋ – የኤርትር ወታደር ማሰልጠኛ ቦታን ይመለከታል። ጥረቴ ሁሉ ሳይሳካ ዓመታት ተቆጠሩ።
በእርግጥ ስለ ሰዋ ከሚሰማው በላይ የተጨበጠ ማስረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ግን ምክንያት አለው።
የኢሳያስ አፍወርቂ የስለላ ሰንሰለለት ረጅም ነው።
ችግሩ እንደዚህ ነው። ሳዋ ውስጥ የሚካሄደው ግፍ በጣም አስከፊ ነው። ከመገረፍ እስከ መገደል
በየቀኑ የሚደረግ ክስተት ነው። ሳዋን መቃወም በግል ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ላይም መዓትን መጥራት ነው።
የኢሳያስ ሰላዮች እንኳን ኤርትራ ውስጥ ውቅያኖስ ተሻግረው አውሮፓ ውስጥ የሚጠረጥሩት ግለሰብ ከኖረ
ይህን ሰው አያድርገኝ ማለት ነው። ሽማግሌ አባቱ ወይም አሮጊት እናቱ፣ ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ
የሚደርሰባቸው መከራ አይጣል ነው። ኤርትራ በዓለም ከሚገኙት አሰቃቂ እስር ቤቶች አንዷ ለመሆን
የበቃችው በዚህ የስለላ ድርጅት ምክንያት ነው። ኤርትራ ውስጥ ስንት የፖለቲካ እስረኞች አሉ? ከሚለው
ቁጥር ስንት ነጻ ሰዎች አሉ የሚለው መቁጠር ያንሳል ይላሉ። ታዛቢዎች።
ከወጣቶቹ ጋር ስንወያይ የሰማኋቸው አስገራሚ ታሪኮች ለዚህ ምስክር ይሆናሉ። አንድ ጊዜ
ለመጥፋት ጉዞ የጀመረ፣ ሕይወቱን ለማጣት የሚያጣጥር ሰው ሕይወቱን ለማዳን በቅርብ በሚገኘው ከተማ
የማይሄድበት፣ ዕርዳታ የማይጠይቅበት፣ ሃገር ኤርትራ ነች። ልጅ አባቱን፣ ወንድም እህቱን ፣ ጎረቤት ጎረቤቱን
የሚሰልልበት ሃገር ኤርትራ ነች። አንዴ ከዛች ሃገር ፣ ከሰዋ ስልጠና ለመጥፋት ጉዞ ከጀመሩ መቀጠል እንጂ
አቋርጦ መመለስ የሚባል ነገር የለም። እንኳን ራስ መሞከር የሚጠፉ ሰዎች መኖራቸውን እያወቁ አለመናገር
የሚስከትለው አደጋ ከባድ ነው።
ይህ ከሳዋ ጋር የተያያዘ የከረመ ታሪክ ለብዙ ጊዜያት አብሮኝ ኖሯል። በተለይ በቅርብ ጊዜ ተሳክቶልኝ ሰሃራ
በርሃን ለማየት ችያለሁ። በዚያ ሙቀቱ በበዛበት፣ ዱቄት የሆነው አሸዋ አይን ውስጥ
እየገባ በሚቆረቁርበት፣ እግር አሸዋው ላይ መራመድ አቅቶት ባለህበት ሂድ
እንደተባለ ወታደር አንድ ቦታ በሚረግጥበት፣ ሙቀቱ ሰውነትን ላብ በላብ
በሚደርግበት፣ ቦታ ላይ ብቻ ሆኖ ሞትን መጠበቅ ምን ይመስላል? የዛ ወጣት
ታሪክ ሰሃራ በርሃ ውስጥ ትዝ አለኝ። እንዲህ ባለው በርሃ ውስጥ ጥርት ያለውን
ሰማያዊ ሰማይ እየተመለከተ ወጣቱ፤ ጉልበቱ ደክሞ፣ ልቡ በውሃ ጥማት ፈንድታ
ነው ለዛለለም ያሸለበው።
ይህ በርሃ ውስጥ ሕይወቱ ያለፈው ወጣት ከአዲስ አበባ በወያኔ ከተባረሩትና ኤርትራዊ ሃማሴኖች
“አምቼ’’¤ ብለው ከሚጠሯቸው መሃል አንዱ ነበር። “አምቼ’’¤ ተብለው የተጠሩበት አዲስ አበባ ውስጥ
በሚገጣጠመው መኪና አምሳያ ነው። የተገጣጠሙ ኤርትራውያን ለማለት ነው። ወጣቱ በወያኔ ተባሮ፤ ተገዶ
ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ኤርትራ ተላከ። በኤርትራ ስልጣን ላይ ከሚገኙት ሃማሴኖች ጋር ምንም አንድ ዓይነት
የሚያደርገው ጉዳይ አልነበረም። “ናፅነት’’¤ የሚሉትንም ሆነ የሻዕብያን ዓላማ አይጋራቸውም። በትዕግስት ግን
ችሏቸው ኖረ። በተለይ ያሰቃዩት የነበሩት “አመቼ’’¤ተብለው እንደሱ ከአዲስ አበባ ከመጡት ውስጥ የሻዕብያ
አባል የሆነ ዘመድ ያላቸው ለኢሳያስ ታማኝ ለመባል ጭራቸውን የሚቆሉት ነበሩ።
በዚህ በዛም ብለው ለሳዋ ወታደርነት መለመሉት። ከሳዋ ጠፍቶ ጉዞ ወደ ሱዳን ከሌሎቹ ጓደኞቹ
ጋር ጀመረ። የኤርትራ በረሃ ውስጥ እንዳለ ያለመደውን በረሃ ስላልቻለው ደከመ። ውሃ ጥማቱ በዛበት። ጉዞ

መቀጠል አቃተው። ሌሎቹን ጓደኞቹን ትተውት እንዲሄዱ ጠየቃቸው። እነሱም ትንሽ ራቅ ካሉ በኋላ ቅርብ
ወደሚገኘው የገበሬ ቤት እንደሚሄድ አሳመናቸው። እሺ ብለው ትንሽ አለፍ ብለው ይመለከቱት ጀመር።
ወጣቱ ግን ከተቀመጠበትም አልተነሳም። ይበልጥ መሬቱ ላይ ተኝቶ ሞቱን ይጠብቅ ጀመር። ጓደኞቹ ሊነጋ
ሰለሆነና ቢያዙ የሚመጣውን አደጋ በመገመት ጥለውት ሄዱ። ልጁ እዛው ቦታ ላይ በውሃ ጥም ልቡ ፈንድታ
ሞቶ ጠዋት ገበሬዎች አገኙት። ቤተሰቦቹ እንደ አጋጣሚ የሚያውቁት የሻዕብያ ባለስልጣን ነበርና በገንዘብ
ብዛት ካለ ብዙ ስቃይ ክፉውን ቀን ተወጡት።
“ሳዋ በምድር ላይ ከሚገኙት ገሃነብ ስፍራዎች ሁሉ የከፋ ነው። ስልጠናውን ተወው ማንም ወታደር
ይሰለጥናል። ሳዋ ግን መሰልጠን ብቻ ሳይሆን በተለይ አዲስ አበባ የነበርነው ኤርትራውያን ለነጻነት ትግሉ
ብዙ አስተዋጽዖ አላደረጉም በሚል ቂም የያዙ የሻብዕያ ወታደሮች ቂማቸውን የሚወጡበት ቦታ ነው።
በውስጣቸው ያለውን የበታችነት ስሜት እኛን በማሰቃየት የበላይነታቸውን ለማሳየት እንቅልፍ ያጡ
ይመስላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አምቼ ያልሆኑት ወጣቶች እኛ ባመጣነው ነጻነት ትንደላቀቃለህ በማለት
ከመከራው ትንሽ እንዲቀምሱ መከራቸውን ያሳይዋቸዋል። በተለይ ጴንጤዎችና ጆሆቫዎች የሚታሰሩት ሳዋ
ውስጥ ነው። ለሻዕብያዎች ኤርትራ የእነሱ ብቻ ነች። ሌሎቻችን ግን ለእነርሱ ሸክም ነን። ሊጠፉ አስበዋል
በሚል ብቻ የምንገረፈውን ልነግርህ አልችልም። ተመልሶ ወደ ሳዋ መሄድ ማለት በቁም በእሳት መቃጠል
ነው። ስለዚህ በመንገድ እንሞታለን እንጂ ተመልሰን የኤርትራን ምድር አንረግጥም።’’
ይህ ነበር የብዙዎቹ ቃል ስለ ሳዋ። ወጣቶቹ ይህንን ጉዳይ ሲያስረዱኝ ፊታቸው ላይ እመለከት
የነበረውን ጥላቻ አስታውሰዋለሁ። ያ ኤርትራውያን በተለይ በውጭ የነበሩት ከነፃነት በኋላ የነበራቸው የተስፋ
እንጀራ እንዲህ መለወጡ ምን ጊዜም ይገርመኛል። ብዙውን የማስታውሰው ነው።
ፍራንክፈርት ገና እግራችን ሲረግጥ፣ የኤርትራ “ናፅነት’’¤ ገና ፈር ሳይዝ፣ ባቡር ጣቢያው (ሃብት
ባንሆፍ ውስጥ) አንድ ኢንተር ሲቲ የሚባል ቡና ቤት ነበር። አሁን ፍራንክፈርት ባቡር ጣቢያ ስለ ተቀያረ ያ
ቦታ በሌላ ተለውጧል። እዛ ቡና ቤት ፀጉራቸውን ያጎፈሩ፣ ሰውነታቸው ኪሲታ የሆኑ ብዙ ኤርትራውያን
የሻዕብያ ደጋፊዎች ተሰብሰበው ፖለቲካ ይቀዱ ነበር። የጀበሃ ደጋፊዎች ደግሞ ከባቡር ጣቢያው ፊትለፊት
የነበረ የግል ቡና ቤት ነበራቸው። ሁለቱ እንደ ዘይትና ውሃ አይደበላለቁም ነበር።
እዚህ ቡና ቤት የሻዕብያ ደጋፊዎች ተሰብስበው በየቀኑ የሚወያዩትን ለመስማት እጓጓ ነበር። አንድ
ቀን ተሳካልኝ። እነሱ የማያውቁት ካስል ከሚባለው ቦታ የመጣ የጀበሃ አባል እያስተረጎመልኝ ሰማሁት።
በውይይታቸው ኤርትራ በቅርብ እንደ ታይዋን ፣ እንደ ሆንግ ኮንግ፣ እንደ ጃፓን ትሆናለች የሚል የተስፋ
አምባሻ ይግምጡ ነበር። እንደ አማራጭ መፈክር “ኤርትራ የግላችን፣ ኢትዮጵያ የጋራችን’’¤የሚል የስግብግቦች
መፈክርም ነበራቸው። በትግራይ ተወላጆች ላይ የነበራቸውም ንቀት አልፎ አልፎ “አጋሜ’’¤ የሚለውን እንደ
ሃገር መጠሪያ ቃል ሳይሆን እንደ ስድብ ይጠቀሙበት ነበር። “ሃድጊ’’¤ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ስም
ነው። ብዙዎቹን ገደብ የሌለው የኢሳያስ ፍቅር ናላቸውን አዙሮት ነበር። ይህ አላግባብ የሆነ የመሪ ፍቅር
የሚያመጣውን በሽታ ከልምድ ሰለማውቀው ከልቤ ነበር ያዘንኩላቸው።
ይህ ለኢሳያስ የነበራቸው ቅጥ ያጣ ፍቅር አንድ ነገር አስታወሰኝ። እድገት በሕብረት ታውጆ ጃንሜዳ
ተሰልፈን በነበረበት ወቅት እነ መንግሥቱ በጂፕ ሆነው በዘማቹ ውስጥ ሲሄዱ ላንቃችን እስከሚሰነጠቅ
“መንጌ’’¤ ብለን የጮኽንለት ፋሽሽቱ መንግሥቱ ከጥቂት ዓመታት በኋላ እኛኑ እየገደለ በየመንገዱ መጣሉ
ነበር ትዝ ያለኝ። የኢሳያስም ከዛ የበሳ ሆነና አረፈው። ሚኒስተር በጥፊ የሚመታ፣ የፈለገውን የሚያስገድል፣
የሚያስር፣ የውጭ ጋዜጠኛን የሚሳደብ ቅጥ ያጣ ባለጌ መሪ ሆነ።
ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ያ የብዙ ሰዎች ሕይወት የፈሰሰበት “ናፅነት’’¤ ያመጣል ተብሎ የነበረው
ብልጽግና ቀርቶ፣ ኩሩ የነበረው የኤርትራ ሕዝብ ተዋርዶ፣ በስደት በበረሃና በባሕር የሚያልቀውን ወጣት
ስቆቃ የሚሰቀጥጥ ሆኗል። ኤርትራም እንኳን ታይዋንን ልትመስል መንግስት ከሌላት ከሶማሊያ ብሳ
በኢኮኖሚ ወድቃ ትገኛለች። እነዛም አፍሮ ኤርትራውያን እንደ በፊቱ የተስፋውን ምግብ መመገብ አቁመው
በተስፋ መቁረጥ በካይዘር መንገድ በሚገኙት ቁማር ቤቶች ወይም ርካሽ የቢራ ቤቶች ብዙዎቹ ደንበኛ
ሆነዋል። የበረቱት ወደ አሥመራ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባ ንግድ ጀምረዋል። ወጣት ኤርትራውያን በተለይም
“ከናፅነቱ’’¤በኋላ የተወለዱት የሃገራቸው ሁኔታ ያኔ ፍራንክፈርት ስንመጣ እንደነበሩት አፍሮ የሻዕቢያ አባላት አይመለከቱትም።

ወጣቶቹ እንደ ሻዕብያው ተዋጊዎች በባዶ ተስፋ ተወጥረው “ሓደ ሕዝቢ፣ ሓደ ልቢ’’¤
የሚለውን ባዶ መፈክር ማሰማት ትተዋል። ሻብያዎቹ በርሃ እንደነበሩበት ወቅት
ተርበው መኖር አይሹም። አዲሱ ትውልድ መቸገርን አይፈልግም። በየቀኑም
በኤርትራ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው “የናጽነት’’¤ የጦርነት ታሪክ አይመስጣቸውም።
ነጻነቱ ለውጥ ከሌለውና የባሰ ከሆነ ባፍንጫችን ይውጣ ባዮች ናቸው። በዚህም
ምክንያት መከራውን ችለው ወደ ተሻለ ዓለም ጉዟቸውን ቀጥለዋል።
አብዛኛዎቹ የኤርትራ ወጣቶች ሃገራቸውን ለቀው በሱዳን አድርገው በሰሃራ በርሃ አቆርጠው ሊቢያ
ከደረሱ በኋላ በመርከብ ወደ ኢጣሊያን ላምባዱሳ ይጓዛሉ። ይህ አስከፊና አደገኛ የሆነ ጉዞ ለብዙ ወጣቶች
ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በሜዲትራንያን ባሕር ውስጥ በሚደርሰው አደጋ
ከሚሞቱት ስደተኞች ውስጥ የኤርትራውያን ቁጥር ከፍተኛ ነው። በዚህ አሰቃቂ ጉዞ የሚሳተፉት
ኤርትራውያን ብቻ አይደሉም። ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሊዎች ፣ ሶርያውያን፣ ግብጾችና ሌሎችም የአፍሪካ
ሃገሮች ዜጎች ይጓዛሉ።
እንደ አጋጣሚ ሰሃራ በተጓዝኩበት ወቅት ሜዲትራንያን ባሕር ጠረፍ ላይ
በድብቅ ቦታ ከኢሳያስ ጨካኝ አገዛዝ ያመለጠውን ወጣት በስልክ አነጋግሬው
ነበር። ዘመዶቹ ስዊድንና ጀርመን እንደሚገኙ አስረድቶኝ፣ ዋናው ዓላማው
ከእነርሱ መገናኘት ነበር። በሜዲትራንያን ባሕር ጠረፍ ላይ ወደ ላምባዱሳ
የሚወስዱትን መርከቦች ዓይነት ተመልክቻቸዋለሁ። ብዙዎቹ ተጥለው የሰነበቱ
ሲሆኑ በኢጣሊያን ፖሊሶች ቢያዙ እንኳን እንደ ንብረት ብዙ ጉዳት
የማያስከትሉ ናቸው። (ፎቶው ስደተኞቹን ወደ ላምባዱሳ(ኢጣልያ)
የሚያጓዙበት መርከብ ዓይነት ነው።
ይህንን ወጣት ስለጉዞው በትክክል ጠይቄው ነበር። አንድ ሺህ ኢሮ ከፍለው በመርከብ ከሚሻገረው
ግለሰብ ጋር ይገናኛሉ። ቀሪውን አምስት መቶ ኢሮ መርከብ ላይ ሲሳፈሩ ለመክፈል ይስማማሉ።
የሜዲትራንያን ባሕር ማዕበሉ ቀዝቀዝ በሚልበት ወቅት ይነገራቸውና ይዘጋጃሉ። ዝግጅቱ ቀላል ነው። ሁለት
ወይም ሦስት ሱሪ መልበስ፣ ከላይም ልብስ መደራረብ፣ የሚብለጨልጭ ወይም የሚያበራ ነገር አለመያዝ ብቻ
ነው። በትንንሽ ጀልባ ተሳፍረው ተለቅ ወደ አለው መርከብ ይወሰዳሉ። በዛ ተጭነው ጉዞ ወደ ላምባዱሳ
ያደርጋሉ። ጉዞው ምንም ቅርብ ቢሆን በመርከቦቹ እርጅና፣ ሳያስቡት በሚነሳ ማዕበል ፣ ባልተጠበቀ ንፋስ
ምክንያቀት የሚፈጠረው አደጋ ብዙ ነው።
ሊቢያ ውስጥ እነዚህ ስደተኞች የባሕሩን መርጋትና፣ አመቺው ጊዜ እስከሚዘጋጅላቸው ድረስ
በድብቅ ቤት ውስጥ ይቀመጣሉ። ማንም ሰው እንዳያያቸው ከተደበቁበት አይወጡም። የሚያጓጉዟቸው
መርከበኞች እስኪጠሯቸው መደበቅ ነው። ከዛ በኋላ ቀኑ ሲደርስ አንድ በአንድ ይሳፈሩና ጉዞ ይጀምራሉ።
የሊቢያ ሁኔታ ለጥቁሮች ከጋዳፊ በኋላ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። ለጥቁር ያለቸው ጥላቻ ድሮ ከነበረው በብዙ
እጅ ጨምራል።
ቱኒዚያ ውስጥ ከሊቢያ ርካሽ ነዳጅ እያመጡ የሚሸጡ ግለሰቦችን ወደ ሰሃራ እየተጥጋን ስንሄድ
አግኝቼ ነበር። ከመኪና ወርጄ ወደ ሊቢያ መሄድ እንደምፈልግና ሊወስዱኝ ይችሉ እንደሆን ለሙከራ ያህል
ጠይቄያቸው ነበር። ቱኒዚያኖቹ በግልጽ ይህ ሊሆን እንደማይችልና በተለይ አፍሪካውያን ሊቢያ ውስጥ
በአሁኑ ወቅት እየተሰቃዩ እንደሆነ ነው ያስረዱኝ። ስለ ሊቢያ ሁኔታ ሲያስረዱኝ በአሁኑ ወቅት ሕግ
እንደሌለና ጠብመንጃ ብቻ ሃገሪቷን እንደሚገዛ ነበር የነገሩኝ። በጣም የሚገርመው እኔ ከቱኒዙያ ሳልወጣ
የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስተር በታጠቁ ሰዎች ታግቶ ነበር። በኋላም ተፈታ።
ለአንድ ሳምንት ያህል ከሳሃራ ጀምሮ የሜዲትራንያንን ባሕር ዳርቻ እየዞርኩ ለማየት ሞክሬለሁ።
የሚጠቀሙባቸውን መርከቦች ተመልክቻለሁ። የማይመለከታቸው ሰዎች ደህንነት ለመጠበቅ ስል ለጊዜው
ሙሉውን ሪፖርት አዘግቸዋለሁ። የምጠብቃቸው ሁኔታዎች ሲሳኩ ደግሞ ሙሉውን ለአንባብያን ለማድረስ
እሞክራለሁ።
ክፍል አንድ ሲመች ይቀጥላል። ቱኒዚያ Oct. 17/2013
[email protected]
ስለ ስደተኞቹ የሚያስብ ሁሉ በሰላም ይክረም

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop