ጎበዝ ምንድን ነው ነገሩ? – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ7 ሰዓታት በመብራት እጦት ሥራ አቁሞ ነበር

የኃይለማርያም ደሳለኝ መንግሥት እንዴት ይጠየቃል?
ከመሐመድ አሊ መሀመድ
የገዥው ፓርቲ ልሳን እንደሆነ የሚታወቀው ፋና FM ሬዲዮ በቀትር የዜና እወጃው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከትናንት 10 ሠዓት ጀምሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ የሆስፒታሉ ታክሚዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አረዳን፡፡ ሬዲዮው የሆስፒታሉ ዲዝል ጄኔሬተርም አገልግሎት እንደማይሰጥ አክሎ በመግለፅ የችግሩን አሳሳቢነት ብቻ ሳይሆን ያለንበትን ሁኔታም ፍንትው አድርጎ አሳየን፡፡ ያለንበትን ሁኔታ በሌላም መንገዶች ስለምናውቀው አሁን አሳሳቢው ጉዳይ በሆስፒታሉ ውስጥ በቀዶ ጥገና ህይወታቸው መትረፍ የሚችል፣ በሰው ሠራሽ መንገድ የሚተነፍሱ ሰዎችና በማሞቂያ ክፍል ውስጥ ያሉ ህፃናት ህይወት ጉዳይ ነው፡፡ በመብራት መቋረጥ ምክንያት ለሚጠፋው ውድ የሰው ህይወት ተጠያቂው ማነው? የሆስፒታሉ አስተዳደር? የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን? ወይስ ይህ መስሪያ ቤት በሥሩ ያለ ክላስተር ክላስተር አስተባባሪ ሚኒስቴር? መነው ተጠያቂው? በአጠቃላይ የኃይለማርያም ደሳለኝ መንግሥት ተጠያቂ የሚሆን አይመስላችሁም? ግን እንዴት?

– የራድዮ ፋና ዜና እንደወረደ ይኸው፦
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በኤሌትሪክ መቋረጥ ለ7 ሰዓታት ስራ አቁሞ ነበር

በባሃሩ ይድነቃቸው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 13፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥቁር አንበሳ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ለሰባት ሰዓታት መብራት ባለመኖሩ ሆስፒታሉ ተገቢ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ ነበር።

የኤሌክትሪክ ሀይሉ በመቋረጡ የቀዶ ጥገናና ጽኑ ህሙማን ታካሚዎች፣ ጠቅላላ ቀዶ ጥገና እና ድንገተኛ ቀዶ ጥገና ህክምና የሚሰጥባቸው ክፍሎች እንዲሁም ያለ ጊዜያቸው የተወለዱና ሙቀት የሚፈልጉ ህጻናት ሙቀት የሚያገኙባቸው ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመው ነበር።

ዛሬ ማለዳ ላይ ዘጋቢያችን በሆስፒታሉ ባደረገው ቅኝት ወቅት የኤሌትሪክ ሃይል በመቋረጡ የተነሳ ሃኪሞቹ ለታካሚዎቹ ኦክስጂን በእጃቸው እየጨመቁ ሲሰጡ አስተውሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ከኢትዮጵያዊነት ዉጭ አማራጭ አይኖርም !

የህክምና ባለሙያዎቹ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በእጃቸው ለነዚህ ከሞት አፋፍ ለደረሱና በተፈጥሮ መተንፈስ ላልቻሉ ህሙማን ዓየር በእጃቸው ሲሰጡ ቆይተዋል።

ያነጋገርናቸው ተረኛ የህክምና ባለሙያዎች እንደገለፁልን ለቀዶ ጥገና ዛሬ ተቀጥረው የነበሩና ያለ ምግብ የቆዩ ህሙማን አገልግሎቱን ማግኘት ስለማይችሉ ለሌላ ጊዜ ቀጠሯቸው እንዲዛወር ተደርጓል።

ይህም ሆስፒታሉ ላይ የስራ መደራረብ ፈጥሮበታል ነው ያሉን ።

ሆስፒታሉ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀበለው ከሁለት ምንጮች ነው።

ነገር ግን የሀይል ማስተላለፊያው ላይ በደረሰ ችግር ምክንያት ኃይል እንዳጣ ተገልጿል።

በማንኛውም ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በሆነ ምክንያት ሊቋረጥ እንደሚችል ቢታወቅም፥ የሆስፒታሉ መጠባበቂያ ጄኔሬተር በማርጀቱ የተነሳ እንደ ሌለ የሚቆጠር ነው ይላሉ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ማህሌት ይገረሙ ።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አሁን ሆስፒታሉ ያለውን ጄኔሬተር ለማደሰ በሂደት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶክተር ማህሌት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሶስተኛ የኃይል ምንጭ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ዛሬ ምናልባትም ለ7 ሰዓታት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ሌላ ጊዜ ለብዙ ሰዓታት ቢቋረጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም።

ይህ እንዳይሆን ግን ሆስፒታሉ ያሉትን አነስተኛ ጄኔሬተሮች ወሳኝ ለሆኑት ክፍሎች የመትከል እቅድ እንዳለውና ከዚህ ባለፈም አዲስ ጄኔሬተር ለመግዛት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተገልፆልናል ።

Share