በዘንድው ሃጅ ጸሎት የተወገዱት ሰው ሰራሽ አደጋዎች !

ጀማራት ፣ ሙና ሙዝደሊፋና አረፋ ዛሬ … !
ከነብዩ ሲራክ ሳዑዲ አረቢያ

የመካና መዲናን መስፋፋት ተከትሎ ወደ ሳውዲ አረቢያ መካና መዲና ለሃጅ ጸሎተኞች ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጓል። የጸሎተኛው ቁጥር ለየሃገራቱ ኮታ በመመደቡ በዘንድሮው የሃጃጆች ከግማሽ በላይ ቀነሰ ቢባልም በዘንድሮ ሃጅ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ያላነሱ ከሁለት መቶ ሃገራት ወደ ሳውዲ አረቢያ ገብተዋል። ከመካ ተጀምሮ ሙና ሙዝደሊፋና አረፋት የሚጠናቀቀውን የጸሎት ስነ ስርአት በያዝነው ሳምንት ሃሙስ በይፋ መጠናቀቁን ከትናንት በስቲያ ምሽት በጅዳና መካ አል ሙከረማ አስተዳዳሪ በኩል ይፋ ሆኗል። የሃጅ ጸሎት በሰላም ሲጠናቀቅ የጸሎተኛ ህዝብ ብዛቱን ፣ የጸሃይ ሃሩሩንና የአገልግሎት አሰጣጡን ጉድለት ተከትሎ የከፋ አደጋም ባለመደረሱ እንዲህ ነው ተብሎ የተመዘገበ የሞት አደጋ አልሰተሰማም !
የሳውዲ አረቢያን ስደትን ሙጥኝ ማለት ከጀመርኩባቸው ሁለት አስርት አመታት ሊደፍኑ በተቃረቡት አመታት እንደታዘብኩት እና በአደባባይ እንደሚታወቀው የሃጅ ጸሎት ሲከዎን የሰው ብዛትና መጨናነቅ ተከትሎ የሚሞቱት ሰዎች መስማት አመት አመት የተለመደ ነበር ። ከአመታት ወዲህ ግን እድሜ ከነዳጅ ለማይተናነሰው የኡምራና ሃጅ ጸሎተኛው ተጓዥ ገንዘብ ነባር ችግሩ በውሉ የተመከተ ይመስላል ። ከምንም በላይ የመካና መዲና የአለም ሙስሊም ቅዱሳን ቦታዎችን በመፈገፍ እና በማስተዳደር የሚመሰገኑት የሳውዲ አሚሮች የጸሎተኛውን ችግሮችን ከስር መሰረታቸው በማስጠናት በሞላ በተረፈው መዋዕለ ንዋይ ተደግፈው መንገዱን ሁሉ የወት የማድረግ ጅማሬ ስርአት ዛሬን ሆነን ስናየው እየተሳካ ሄዷል ማለት ይቻላል። ቅዱሳኑን ቦታዎች የማስፋፋቱ ስራ ገና ሳይጠናቀቅ አመርቂ ውጤት ማሳየት መጀመሩን ከወዲሁ መታየት መጀመሩን እማኝ ዋቢ እያቀረቡ መናገር ከሚቻልበት ደረጃ ተደርሷል !
ዛሬ ከፍተኛ አደጋዎች ይከሰቱ የነበሩባቸው ጀማራት እና የሙና ፣ሙዝደሊፋ ኮረብታዎች …
ጀማራት – ከሃጅ ስነ ስርአት ውስጥ አንዱ የሆነው ሰይጣንን በድንጋይ የመውገር ስነ ስርአት የሚደረግበት ቦታ ጀማራት ተብሎ ይጠራል። በዚህ ሰይጣን ማውገዣና መወገሪያ ምሳሌነት በሚታወቀው ቦታ ለሃጅ የመጣው ምዕመን በነፍስ ወከፍ ጸሎት በማድረግ ሰባት ያህል ድንጋይ (ጠጠር) በጎድጓዳው ስፍራ ላይ ይወረወራል። በዚህ ሰይጣን መወገሩን ማዘከሪያ ቦታ በጀማራት ከአመት አመት በርካታ አደጋዎች ተስተናግደውበታል።
ድንጋይ የመወርወር ስርአቱን ለመፈጸም ከሚጎርፈው ሃጃጅ አንጻር በጃማራት አካባቢ ለሚፈጠር አደጋ እንደ ምክንያት የሚነሳው የምዕመናን ግፊያ ፣ በመስተንግዶው ቅንጅት እጥረትና በመሳሰሉት ችግሮች ሲሆኑ አደጋው እስከ ህይዎት መቅጠፍ የተሸጋገረበት ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ሰይጣን በድንጋይ የሚወገርበት ይህ መታሰቢያ ቦታ ካለፉት ሁለት ሶስት አመታት ወዲህ ለውጥ ታይቶበታል። በጀማራት የሳውዲ መንግስት እና ህዝቡ ትብብርና አስገራሚ ቅንጅት ታክሎበት የድንጋይ መወርወሩ ስርአት መከወኛ ጀማራት በአስገራሚ ድልድይ በረቀቀ መንገድ በመሰራቱ የባጀበት ችግር እንዲቆም ተደርጓል ። የጀማራት አካባቢ ዛሬ ከፍተኛ የሰው ሃይል አርፎበትና ደጎስ ያለ ወጭ ወጥቶበት በአንድ ጊዜ ሽዎችን ሲያስተናግድ በቀን ሚሊዮኖን ያህል ሃጃጅ ማስተናገድ በመቻሉ ግፊያ ፣ ልፊያን ተከትሎ አደጋ የለም ! ዛሬ ስለ ጀማራት ሲወራ ችግሩ የሃጃጅ ጸሎተኞችን ትርምስን ተከትሎ የሞትና የመቁሰል አደጋ አይወራም። ችግሩ ሁሉ በአብዛኛው ተቀርፎ ዛሬ በጀማራት አካባቢ አስገራሚ ግልጋሎት መሰጠት መጀመሩን እየሰማን እየተመለከትን “አጃኢብ !” እያልን እየተገረምን ነው።
አንድ ክንውን እንደ ምሳሌ ልጠቀስ …
በዘንድሮው ሃጅ የመካ ማዘጋጃ ቤት ያሰማራቸው ልዩ ግልጋሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ጀማራት የተካሔደውን የጸሎት ስነ ስርአት በተረጋጋ ሁኔታ መከወን መጀመር እንደ ምሳሌ የሚያሳይ ይመስለኛል። ተንቀሳቃሽ ግልጋሎት ሰጭ ትናንሽ ተሽከርካሪዎች ተመድበው ከሰው መካከል እየተሽኮለኮሉ ግልጋሎት ሲሰጡ ተስተውሏል። ይህች በስዕሉ የምትመለከቷት ሚጢጢ ተንቀሳቃሽ የሞባይል ስልክ ጥገና የሚከወንባት መኪና ናት። በውስጧ የተሟሉ የጥገና መሳሪያዎች እና ብቁ ባለሙያዎችን ይዛለች። በጀማራት ድልድይና በአካባቢው በሃጃጆች መካከል በቀላሉ እየተሽሎከለከች የስልክ ጥገና ድጋፍ ትሰጣለች! መሰልጠን እንዲህ ሆኗል ! ጀማራት ተቀይሯል፣በልፊያ፣ግፊያ፣ትርምስ ለጸሎት የመጣው የሰው ህይዎት እንደዋዛ አይቀጠፍባትም !
ሙና ሙዝደሊፋ – ጥንት ድሮ ድሮ በማይባል የቅርብ አመታት ትውስታ ሃጃጆች በሚያርፉባቸው የሙና ሙዝደሊፋ ኮረብብቶች የእሳት አደጋን ጨምሮ በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሃጃጆች ለካፋ አደጋ ይጋለጡ ነበር ። ዛሬ የሃጃጆች ድንኳን በጸረ እሳት ድንኳኖች በመሰራታቸው ብቻ ሳይሆን እሳት አደጋን ሊፈጥሩ የሚችሉት ሁሉ ቀዳዶች መንገድ ተዘይዶላቸዋልና የከፋ አደጋ ቀርቷል !
አቅማቸው የፈቀደ በእድሜያቸው አንድ ጊዜ ይፈጽሙት ዘንድ በሚታዘዘው የሃጅ ጸሎት አቅመ ደካማ ሃጃጆች በጸሎት ጉዞው በሚፈጠር መጨናነቅ ለከፋ አደጋ ይዳረጉም ነበረ ። የሃጃጅ አረጋውያን እንግልት ሲነሳም በሙና፣ ሙዝደሊፋና አረፋ የትራንስፖርት ችግር በዋናነት ይጠቀሳል። ዛሬ ያ ችግር የተቀረፈ ይመስላል ። ዘንድሮ ሃጃጅ አረጋውያን አቅመ ደካሞች ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩባቸው ተንቀሳቃሽ ወንበሮች በመንግስት ቀርበውላቸዋል። ምዕመኑን ለመደገፍ የተሰማሩት የሳውዲ ወታደር፣ ፖሊስና ደህነንነቱን ጨምሮ በጎ አድራጊ የረድኤት ማህበሮችን ጨምሮ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ግልጋሎት ሰጭ ሰራተኞች ለአቅመ ደካሞች ቅድሚያ በመስጠት ሲያስተናግዱ ተስተውሏል። ከዚህም አልፎ ተርፎ አቅመ አካሞችን ለመደገፍ ከአረፋ ወደ ሙናና ሙዝደሊፋ የጸሎት ቦታዎች ለማመላለስ የተዘጋጁት እጅግ ዘመናዊ ባቡሮች የሃጃጆችን እንግልት በማቅለል የትራንስፖርቱን ችግር በእጅጉ አስወግደውታል ።
በሃጃጆች መካከል የተላላፊ በሽታዎች ችግር እንዳይከሰት ማናቸውም ጸሎተኛ ገና ወደ ሳውዲ ሲገባ ክትባት በነጻ ይሰጠዋል። ድጋፍ ሰጭው ነዋሪውም ቢሆን በያለበት እና በተመደበበት የስራ መስክ የተለያዩ የመከላከያ ክትባቶችን እንዲወስድ ይገደዳል።
ነባር ችግሮች ተቀርፈዋልና ዛሬ በሙና ሙዝደሊፋ የማረፊያዎች የቃጠሎ ፣ የተላላፊ በሽታ ፣ የትራንስፖርትና ተመሳሳይ ችግሮች በአብዛኛው ከነስጋታቸው ተወግደዋል ማለት ይቻላል !
ሃጃጆች እና የባለደርሻዎች ድጋፍ …
ሃጅ በመጣ በሔደ ቁጥር የሃይማኖት ትዕዛዛቸውን ለመከወን ወደ ሳውዲ መካና መዲና የሚገቡት የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ይዘዋቸው ከሚመጡ የየሃገራቱ የሃጅ ኮሚቴዎች በተጨማሪ ሳውዲ ተቀማጭ የሆኑ ቆንስል ፣ ኢንባሲዎችን ጨምሮ በሳውዲ በሚኖሩ ዜጎቻቸው በኩል ድጋፍ ይደረግላቸዋል። እኒህ ባለድርሻ አካላት ጸለተኞች ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የሚሰጡት ድጋፍ ለወገኖቻቸው የሰመረ የጸሎት ሒደት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻለው ግን ኢትዮጵያን ሃጃጆችን ይዞታ ሲወሳ አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ሃጃጆችና እንግልታቸው ..
የሃጅ ጸሎት ስርአት ሁሉም የሃጅ ጸሎተኛ የየሃገሩን ባንዴራ ከፍ አድርጎ በሚከውነው የጸሎት ስነ ስርአት ነው። ለታደለ ይህ አጋጣሚ የሃገር ባንዴራን ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ማንነቱን በማሳዎቅ ይጠቀምበታል። የባንዴራው ከፍ በሎ መውለብለብ እንደ ኢትዮጵያ በእስልምና ሃይማኖቱ ከፍ ያለ ቦታ ለሚሰጣት ሃገር ደግሞ ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው። ሌላው ሁሉ ቢቀር የመጀመሪያው የመካ ሙአዝን የቢላል አል ሃበሽ ታሪክ እንዳይጠለፍ ካማስታወስ አልፎ የባንዴራው ከፍ ማለት ሃገርን በሚሊዮን ለሚቆጠር የተለያየ ሃገር ዜጋ ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ የሚውልበት አጋጣሚም ነው ። ባንዴራን እያውለበለቡ በህብረት በመትመም ከመካ ሙና ሙዝደሊፋ አረፋትና ጀማራት የሚደረገው ጉዞ አመት በመጣ ባሰለሰ ቁጥር ኢትዮጵያንም በወጉ የሚያደራጅ የሚያስተባብራቸው ብዙ ባይገኝም በመካና አካባቢው ኢትዮጵያን ድጋፍ እያገኙ የሃገራቸውን ባንዴራ ይዘው ተሳታፊ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው !
ከዚህ ባለፈ ጸሎተኞች ከገቡበት ቀን እስከ ጸሎት ፍጻሜው ባመጣቸው ኮሚቴ ሳይሆን ለነብሴ ባሉ ሳውዲና የራሳቸው ጥቂት ዜጎች ብቻ ከመታገዝ ባለፈ የሃጅ ኮሚቴ በቅንጅት ሲመራ የተስተዋለባቸው ጊዜዎች በጣም ውስን ናቸው ማለት ይቻላል። ጥቂት ወደ ውስጥ ገባ ብለን ከተመለከትነው ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሰው የሚመጡ ዜጎቻችን ሁለንተናዊ አያያዝ ለመናገር የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሰፍር ሆኖ የተስተዋለባቸውን በርካታ አጋጣሚዎችን የታዘብኩባቸው ወቅቶች አልፈዋል። በዚህ ረገድ ካገር ቤት ለጸሎት የመጡ አቅመ ደካማ አዛውንት ሃጃጆች ከበድ ያለ የእንግልት ምስክርነታቸውን የሰጡኝ መረጃ አሁን ድረስ ከአእምሮየ አይጠፋም !
“ዘንድሮ ከከራረመው የተሻለ ድጋፍ አግኝተዋል!” የሚል መረጃን ከአስተባባሪዎች አግኝቻለሁ። በአንጻሩ “የዘንድሮው ካለፈው ይሻል እንጅ ብዙ መሻሻል ያለበት የግልጋሎት ሂደት አለ!” በማለት ቅሬታና ጥቆማቸውን የሰጡኝ ጸሎተኞች በርካታ ናቸው ! አቅሙ ከፈቀደ ስለ ዘንድሮው ጸሎተኛ ምዕመን ይዞታ የምለው አይጠፋም! እስከዚያው ግን መልካሙን እየተመኘሁ በሃጅ ዙሪያ ያጠነጠነውን የማለዳ ወጌን እዚህ ላይ ልግታው !
ቸር ይግጠመን !
ነቢዩ ሲራክ
ከሳውዲ አረቢያ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰሞኑ ‹‹የኦሮምያ ግርግር›› ግራ ገብቶኛል - መስፍን ወልደ ማርያም
Share