አንዱዓለም በቀለ(ሰዊስ 2013)
ግሪኮች ናይሎስ..ብለዉ ቢሰይሙህ፣
አኒል አኒል…ብሎ አረብ ቢያሞካሽህ፣
ኢታሩ “ታለቅ ወንዝ“…ሃፒ ሃፒ አሉህ፣
ደስታ ቢያገኙብህ………………..
ጥንት ግብጻዊያን…ህይወት ቢዘሩብህ፤
በሰላሳ ስሞች…ቢጠሩ ቢያጅቡህ፣
ዓባይ የኛን ዓባይ…እኛ መች አጣንህ፤
ከላይ ከከፍታ…ቁልቁል ተወርዉረህ፣
ከአለት ተጋጭተህ…ጢስ ሆነህ ተነስተህ፣
በፏፏቴህ ዜማ…ልዩ ድምጽ አዉጥተህ፣
ንገራቸዉ እስቲ…ከረቂቅ ሚስጥርህ።
የኤደን ትሩፋት…የፊሾን ተከታይ፣
የነ ኤፍራጥስ…………………
የጤግሮስ ወንድም…የተፈጥሮ ሲሳይ፣
እነዴት ሆኖ ባንተ…ዛሬ እንለያይ?፣
ዓለም ስትፈጠር…አብረህ ተፈጥረሃል፣
ሐዋርያት እንኳን…ከትበዉልሃል፣
በቅዱስ መጽሐፍ…ስምህ ይጠቀሳል፣
የኤደን ስጦታ…ግዮን ተብለሀል፣
እንኳን እኛ ሰዎች…ፈጣሪም ያቅሃል፤
እንዴት ሆኖ ታዲያ…………….
ዛሬ ስለ ክብርህ…ሰዎች ይነግሩናል!፣
ሁለት አሥርት ዓመት…መች ተፈልገሀል!፣
ተዉ ባክህን ግዮን…ተዉ ባክህን ዓባይ፣
እነሱ ላንተ ሟች…ሌላዉ አንተን ገዳይ?!
እነሱ አልሚዎች…ሌላዉ አነተን በዳይ?!
ተወን እነጂ ግዮን…እባክህን ዓባይ፣
በቂ ተዘርቶልን…ጎሪጥ እሚያስተያይ፣
እየቦጠቦጠን የደም…የዘር ተባይ፣
ደሞ ሁሉም ቀርቶ…በንተ ልንለያይ?!
አቤት ያንተ ያለህ!…ባዋይ በመጀንህ!፣
ምሁራን ልሂቃን…እንዳልመከሩብህ፣
የቀድሞ አባቶች…እንዳልደከሙልህ፣
ጭራሽ እንዳልታየህ…ድሮ እንደሌለህ፣
ከሃያ ዓመት በላይ…ስትፈለግ ኖረህ፣
………………ዛሬ ላይ ተገኝተህ!፣
የልማቶች ሁሉ…ምሣሌ ተደርገህ፣
ጥፋት መሸፈኛ…ማዘናጊያ ሆነህ፣
እድሜ ማራዘሚያ…መዳኒት ተደርገህ፣
ሁሉም ተነሳና…ዓባይ ዓባይ አለህ፤
የማዉራት የመፃፍ…የሃሳብ ነፃነት፣
በህግ የመዳኘት…የዲሞክራሲ መብት፣
የድህነት ማብቂያ…ያኢኮኖሚ እድገት፣
አጀብ ምኑ ቅጡ…መቻሉን ከሰጠህ፣
የችግሮች ሁሉ…መፍቻ ዘዴ ሆነህ፣
ጦስ ጥንቡሳስ ሁሉ…ባንተ ተጥሎብህ፣
ከተፍ አልክልና…ዓባይ ካባ ሆነህ!።
መች ከፋ ነበረ…ስላንተ መጣሩ፣
ስላንተ ማዜሙ…ባንተ መፎከሩ፣
ግራ ቢሆን እንጂ…ቢጣረስ ነገሩ፣
ምሬት ቢበዛ እንጂ…ሰዉ በገዛ አገሩ፤
እነዳንተ እንደ ወንዙ…እነደ ፈሳሽ ጅረት፣
ሰዉ ሃገሩን ጠልቶ…ሲጣደፍ ለስደት፣
በየ በረሃዉ ላይ…እንደ በግ ሲበለት፣
ባህር ሰምጦ ሲቀር…ህይወት እንደዘበት፣
ሴቶች ሲሸቀጡ…ለዐረብ በረከት፣
ተዋልዶ ተፋቅሮ…ከተቀመጠበት፣
ማፈናቀል ይቅር…ይከበር የሰዉ መብት፣
ከድንጋይ ከብረት…ከአፈር ካአለት፣
ሥርዓት ይገደብ…ይሄ ይቅደም ማለት፣
እንዴት ያስፈርጃል…እንደ ልማት ጠላት?!
ፍጡራን ሲራቡ…ንፁሀን ሲሞቱ፣
ዜጎች ያለ ጥፋት…ወህኒ ሲከተቱ፣
መፃፍ ወንጀል ሲሆን…ሰዉ በገዛ ጣቱ፣
አትናገር ሲባል…በገዛ አንደበቱ፣
ቢመሳቀል እንጂ…የሁዋለና ፊቱ፣
መቅደም የሚገባዉ…የሰዉ ነፃነቱ፣
ፍጹም ተዘንግቶ…ተደፍቶ ባናቱ፣
እንዲህ ቢሆን እንጂ…ነገሮች ቢምታቱ፣
ደሞ የምን ገንዘብ…አረ ምን አባቱ!፣
ይታወቅ የለ እንዴ…በዓለም እዉነቱ፣
የጥቁሮች ኩራት…ኢትዮጵያዊነቱ፣
ጭራሽ ለሃገሩ…ለአንዲት እናቱ!?
ለሌላዉም ለጋሽ…ሩህ ሩህ አንጀቱ፣
ለነፃነቱ ሟች…ይሄ ክንደ ብረቱ፣
ሀገር ያቆየልን…በደሙ ባጥንቱ፣
አዬ ምነዉ ጎበዝ!…አረ ባርባራቱ፣
ለቀባሪዉ ማርዳት!?…ልክ እንደ ተረቱ!፣
ተወን ባክህ ዓባይ…እስቲ በፈጠረህ፣
መሸሹ ቀርቶብህ…አንተም ተሰብስበህ፣
በሰዉ በረሃ ለይ…መባከን ቀርቶብህ፣
ሲሳይ ለወገንህ…መድን ለልጆችህ፣
እንደቃሉ ግዮን…ያምለክ ፀበል ሆነህ፣
ለሚገዘትብህ…እንደዚ በስምህ፣
እዉነቱን አጥርተህ…ዉሸቱን አጋልጠህ፣
ዲያቢሎሱን ሁሉ…ፈዉሰዉ አጥምቀህ፣
ህሊና ሥራለት…ኢትዮጵያዊ አርገህ።
ሚስኪኑንም….እርዳዉ፣
እነደዛ በዙሪያህ…ለተኮለኮለዉ፣
አንተ አባቱ እያለህ…ጠኔ ለጠለፈዉ፣
ከፍሰትህ ጨልፈህ…አንጀቱን አርጥበዉ፤
እባክህን ዓባይ…እበክህን ስማን፣
ከፀበልህ እርጨን…በጢስህ እጠነን፣
ሀሉን በሚያረገዉ…በኤደን ፈጣሪህ፣
አቅፎ ባሳደገህ…በጣናዉ አባትህ፣
ባክህ ተለመነን…ባክህ እሺ በለን፣
በጢስህ እጠነን…በዳመናህ ጋርደን፣
ከጎረቤት ቡዳ…ከነገር ጠብቀን፣
ለም አፈሯን ትተህ…ጠላቷን አጥፋልን፣
ቆሌህን አስቆጣዉ…አለሗችሁ በለን፣
ከዉስጥም ከዉጭም…ቆልፎ ከያዘን፣
ዲያቢሎስ መጋኛ…እባክህ ገላግለን፣
…………..ፈዉስ ፀበል ሁነን፣
ኤሎሄ ኤሎሄ…ዓባይ ፍቅር ስጠን፤
ኤሎሄ ኤሎሄ…ዓባይ ሰላም ሁነን፡ ፡
“ ግንባታ እሚጀምረዉ ከታች ከመሠረት ነዉ!እናም ምንም ክፍያ የሌለዉን በተፈጥሮ የተሰጠ የሰዉ ልጆች ነፃነትን፣ሰብአዊ መበትን እና የዜግነት ክብርን መሠረት ያላደረገ የይስሙላ ግንባታ የእንቧይ ካብ ነዉ።”
አንዱዓለም በቀለ
[email protected](Switzerland)