የአዲስ አበባና የፌዴራሉ ህገ ወጥ መጅሊሶች የኢደል አድሃ (አረፋ) በአል ዝግጅትን ሙሉ ለሙሉ ለመንግስት አስረከቡ

ድምፃችን ይሰማ እንደዘገበው፦

የኢድ በአል አከባበርን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ደረጃ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተደረገው ስብሰባ መንግስት ሙሉ ሃላፊነቱን እንደተረከበ ተገለፀ ፡፡ ከነገ ወዲያ ማክሰኞ ጥቅምት 5 \2006 እንደሚከበር የሚጠበቀው የኢደል አደሃ (አረፋ) በዐል ላይ የፌዴራልም ሆነ የአዲስ አበባ ህገ ወጥ መጅሊስ አመራሮች (ሸህ ኪያርንና ዶክተር አህመድን ይጨምራል) ወደ ሃጅ በመሄዳቸው የበአል አከባበሩን ሙሉ ሃላፊነት ለመንግስት እንደተሰጠ የመንግስት ሃላፊዎቹ ግልፅ አድርገዋል ፡፡

በዛሬው ስብሰባ ከአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሃላፊዎች ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኢንተሊጀንስ ፣ የፌዴራል ፖሊስ ሃላፊና ኢንተሊጀንስ ፣ የአዲስ አበባ መረጃና ደህንነት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በአሉ መንግስት በሚፈልገው መልኩ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ መመሪያዎችን አውርደዋል ፡፡ ከወረዱት መመሪያዎች በዋነኝነት ለሁሉም ክፍለ ከተሞች ወደ ስታዲየሙ የሚገቡበት የቴዲየም በር ቁጥር ስለሚሰጣቸው ክፍለ ከተሞቹ የየራሳቸውን የመንግስት ደጋፊ ሙስሊሞችን(አህባሾችን )ና ካድሬዎችን በመያዝ አንድ ላይ ከየአካባቢያቸው እንዲነሱና እስከ ከጠዋቱ አንድ ሰዐት ድረስ የስታዲየሙን የመጀመሪያ ሶፍ እንዲይዙ ታስቧል ፡፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በእለቱ ተቃውሞ ማድረጉ እንደማይቀር መንግስት ያመነ ሲሆን ይህን ለመከላከል በየክፍለከተማው የሚገኙ አህባሾችና የመንግስት ደጋፊዎች ፣ እንዲሁም ከሁሉም አደረጃጀቶች (ከነዋሪዎች ፎረም ፣ ከሴቶች ፎረም ፣ ከወጣቶች ፎረምና መሰል አደረጃጀቶች) የተውጣጡ ካድሬዎች እስከ ጠዋቱ አንድ ሰዐት ባለው ግዜ ውስጥ ስቴዲየም ቀድመው በመግባት ተቃውሞ አድራጊዎቹ የመጀመሪያዎቹን ረድፎች እንዳይዙት መቅደም እንዳለባቸው ትእዛዝ አውርደዋል ፡፡

በእለቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ወይም ተወካያቸው ፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁ አንድ ተወካይ በመገኘት የመንግስትን አቋም የሚያንፀባርቅ ንግግር እንዲያደርጉ እቅድ የተያዘ ሲሆን ተቃዋሚዎች ይህን ንግግር እንዳያስተጓጉሉና ሚዲያውም የበአሉን አከባበር በነፃነት ማስተላለፍ እንዲችል በስታዲየም ውስጥ የተቃዋሚዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሚና መቀነስ መቻል አለብን ብለዋል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Hiber Radio: ኤርትራ ሕወሓት አስቀድሞ የካደውን ጦርነት ይፋ አደረገች - አሜሪካ ኤርትራን አስታርቃለሁ አለች

ኦረንቴሽኑን እየሰጡ ከነበሩት የመንግስት ሃላፊዎች መካከል አንዱ “ እኛ ከስታዲየሙ ውጪ ችግር የለብንም ፡፡ ውጪውን የሚጠብቅ የራሱ ባለቤት አለው ፣ መረባረብ ያለብን በስቴዲየም ውስጥ እንዳይረብሹን ነው ፡፡ ከሰላት በፊት በስታዲየሙ ውስጥ የሚደረጉ ንግግሮችና ሌሎች መሰል ፕሮግራሞች በሁከት መቆም የለባቸውም ፡፡ ከኢደል ፊጥር በአል ባገኘነው ተሞክሮ ተቃዋሚዎቹ ስታዲየም ውስጥ አይገቡም ማለት አይቻልም ፡፡ እንኳን እነሱ ይቅርና ባነራቸውንም አስገብተዋል” ያሉት የመንግስት ሃላፊው “ ቁም ነገሩ ግን አሁን የሚፈለገው ማክሰኞ ስታዲየም ውስጥ ገብተው የሚቃወሙትን ሀይሎች የኛ ካድሬዎች በማስደንገጥ ማስቆም መቻል አለባችሁ ፡፡ እነሱ መጮህ ሲጀምሩ የኛ ደጋፊዎች ደግሞ ዞር ዞር እያሉ እንዲገለምጧቸውና አጠገባቸው ያሉትም ምንድን ነው የምትጮሀው እያሉ ማስደንበር አለባቸው፡፡ ስቴዲየም ውስጥ ስለሆኑ ደንግጠው ያቆማሉ ፡፡ በዛ ላይ ለኢደል ፊጥር የደረሰባቸውን ስለሚያውቁ ይፈሯቸዋል፣ ስለዚህ ይህን መመሪያ በጥንቃቄ እንዲተገበር ወደ ታች እንድታወርዱ ” ብለዋቸዋል ፡፡

ሌላኛው የመንግስት ሃላፊ በበኩላቸው “ ከስግደት በኋላም ቢሆን ተቃዋሚዎቹ ሲረብሹ የኛ ሰዎች በመጡበት አኳኋን ወደ እስታዲየሙ በገቡበት በሮች ግር ብለው መውጣት ነው ያለባቸው ፡፡ ምክንያቱም ተቃውሞ አድራጊዎቹ ከስግደት በኋላም እንደተለመደው ረብሻቸውን ሲጀምሩ የኛ ደጋፊዎ ድንገት ግር ብለው እየደረመሷቸው ሲወጡ ብቸኝነት ተሰምቷቸው ተቃውሟቸውን ያቆማሉ ፡፡ ከወጣችሁም በኋላ የትም ቦታ አትቁሙ ፡፡ ቀጥ ብላችሁ ወደቤታችሁ ነው መሄድ ያለባችሁ ፡፡ ፖሊስም ሆነ ደህንነት የሚረዳው ወደ ኋላ የሚቀር ሁሉ ረብሻ ፈላጊ ነው ብሎ ነው ፡፡ ይህ ኮዳችን ነው ፡፡ ከሰላት በኋላ የኛ መጅሊስ ሰዎችና ካድሬዎች ምንም ሳይቆሙ ወደ ቤታቸው ነው መንገድ መጀመር ያለባቸው ፡፡ ወደ ኋላ የሚቀረው ግን ተቃዋሚዎች ናቸው ብለን ነው የምናምነው ” ብለዋል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደብረማርቆስ አዳማ እና ቁጫ ሰኔ አንድ ቀን ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎች ይካሄዱባቸዋል።

በዚህ መሰረት እያንዳንዱ የከፍለ ከተማ መጅሊስ ሰብሳቢዎች ከኢማሙ ቀጥሎ ባለው የመጀመሪያው ሶፍ ላይ እንዲሆኑ ፣ እያንዳንዱ የክፍለ ከተማ መጅሊስ ምክትል ሰብሳቢዎች በሁለተኛው ሶፍ እንዲሆኑ ፣ እያንዳንዱ የክፍለ ከተማ መጅሊስ ፀሃፊዎችና ቀሪዎቹ አራቱ አመራሮች ደግሞ ከበር እስከ መድረክ በመያዝ እንግዳ እንዲቀበሉ ፣ እንዲከታተሉና እንዲያስተናግዱ እቅድ ወጥቷል ፡፡ የአህባሽ ሱፊ ማህበር አባላት ደግሞ ከነዚህ ኋላ ያለውን ሶፍ እንዲይዙ ማብራሪያ ተሰጥቷል ፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ የክፍለ ከተማ አመራሮች ፣ ከተለያዩ ዘርፎች የተዋቀሩ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ደግሞ ክፈለ ከተማቸው እንዲገቡ በተነገራቸው የስታዲየም በር ቁጥር በመጠቀም ቦታቸውን መያዝ እንዳለባቸው መመሪያ ወርዷል ፡፡

ልደታና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ለስቴዲየሙ ቅርብ እንደሆኑ ስለሚታሰብ በጠዋት ተነስተው ወደ እስታዲየም በእግራቸው እንዲሄዱ የተነገራቸው ሲሆን ሌሎቹ ግን መኪና እንደሚታዘዝላቸው ታውቋል ፡፡
ተልእኮ

1) ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ በተቃዋሚዎቹ ሲደረግ ባሉበት ቦታ ሆነው በአንድ ድምፅ “ዝም በሉ አትጩሁብን ” በማለት ለማስቆም መሞከር

2) ከተሰገደ በኋላም ሁሉም አባላት መንገዱን ቶሎ በማስከፈት ግር ብሎ በሁሉም የስቴዲየሙ በሮች በመውጣት ተቃዋሚዎቹን በማስደንገጥ መበተን ፡፡ ሙሰሊሞቹ ተቃውሞ በሚያደርጉበት ወቅት ሁሉም አባል በአንድ ላይ በሁሉም በር ግር ብሎ ሲወጣ ህዝበ ሙስሊሙን የመበተን እድል ይኖራል የሚል መላምት ቀርቧል ፡፡

ሆኖም በስብሰባው የነበሩ አመራሮች “ የኛ የመጅሊስም ሆኑ ሌሎች አባላቶች ይህን መመሪያ በተቀላጠፈ ሁኔታ ይተገብሩለናል ወይ ብዙዎቹ ይፈራሉ ወይም በሰዐቱ ላይገኙ ይችላሉ “ የሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም ይህን ተከታትላችሁ ማስፈፀም የናንተ ግዴታ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢሕአፓ የኢሕአፓ መስራችና ከፍተኛ አመራር ኮሚቴ ጋር የተደረገ ውይይት ክፍል 3

በመጨረሻም የመጅሊሱ ሁሉም አመራሮች ወደ ሃጅ ስለሄዱ መድረኩ በመንግስት ሰዎች ብቻ እንዳይያዝ ከሰላት በፊት ህዝቡን ተክቢራ የሚያስብሉና መጅሊሱን ወክለው ንግግር እንዲያደርጉ ከክፍለ ከተሞች የመጅሊስ አመራሮችና ለመንግስት ቅርብ የሆኑ ኢማሞች እንዲመለምሉ ክፍለ ከተሞች ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ፡፡ የኢድ ስግደት የሚከናወነውም ከጠዋቱ 2 ሰዐት ላይ እንደሚሆን ወስነው ስብሰባቸውን አጠናቀዋል ፡፡

በነገው እለትም ለየክፍለ ከተማ ህገ ወጥ መጅሊስ ሰባት አመራሮች ኦረንቴሽን እንደሚሰጥም ታውቋል ፡፡

አላህ ከተንኮለኞች ሴራ ይጠብቀን

ድል ለኢትዬጲያ ሙስሊሞች!!!

አላሁ አክበር!!

Share