የሁለት ትውልዶች ወግ ከቀይ ሽብር እስከ ሰሃራ – ከበልጂግ ዓሊ

የዘሐበሻ ጋዜጣና ድረ ገጽ “የቀለበቴን ስጧት“ ደራሲ የሆነው በልጅግ ዓሊ “የሁለት ትውልዶች ወግ“ በሚል በተከታታይ ያቀረበውን ጽሁፍ ለአንባቢያን አቅርበን ነበር። ቀጣዩ ጽሁፍ ቀደም ብሎ የተጻፈ ይሁን እንጂ አሁንም ወቅታዊ ሆኖ አግኝተነዋል። በአሁኑ ወቅት በሰሃራ በረሃ በአፍሪካውያን ላይ በተለይም በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ችግር እየጨመረ የመጣ በመሆኑ ይህ ጽሁፍ ለአንባቢያን ይጠቅማል ብለን ስላሰብን ጽሁፉን እንደገና ለማውጣት ወስነናል።

በልጅግ ዓሊ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያውን ላይ በሰሃራ በርሃ ውስጥ የሚደርሰውን ችግር ከቦታው ሆኖ ለመመልከት በሊቢያ በኩል ያደረገው ጥረት በጸጥታ ምክንያት ስላልተሳካ በቲኒዚያ በኩል ሌላ ሙከራ አድርጓል። በዚህም ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ከሰሃራ በርሃ ሆኖ በስልክ ተነጋግሮ የተጠናከረ ሪፓርት እንደሚቀርብልን ቃል ገብቷልናል።

ሪፖርቱ ደርሶን ለአንባቢያን እስከምናቀርበው ድረስ “የሁለት ትውልድ ወግን“ እነሆ ፡ –

የሁለት ትውልዶች ወግ ከቀይ ሽብር እስከ ሰሃራ

በምኖርበት አካባቢ በተለያየ መንገድ ወደ አውሮፓ የመጡ ወጣቶች አሉ። እድሜያቸው በሃያዎቹ አካባቢ ይሆናል። እንዴት ወደ አውሮፓ እንደመጡ ታሪካቸውን ያጫውቱኛል። ከወጣቶቹ ጋር ምንም በአማርኛ ብንነጋገር አንዳንዴ እነርሱ የሚጠቀሙባቸው ቃላቶች ዘመን አመጣሽ ስለሆኑ ለመረዳት ማብራሪያ እጠይቃቸዋለሁ። እነርሱም ይተረጉሙልኛል። ጨዋታቸው፣ ቀልዳቸው ሁሉ ይጥመኛል። የወጣትነት ዘመኔን ሰለሚያስታውሰኝ እነርሱን ሳገኝ ደስተኛ ነኝ። አንድ ቀን ከመካከላቸው አንዱ፣ –
“ተሾመ ቶጋን ታውቀዋለህ ?” ብሎ ጠየቀኝ።
“ስሙን ሰምቻለሁ ማን ነበር እሱ ? አላስታውሰውም ” አልኩት።
“የፓርላማው አፈ ጉባዔ ነው። አንድ ቀን ታዲያ የመለስ ልጅ መጫወቻ ካልተገዛልኝ ብሎ አምርሮ ያለቅሳል። የወያኔ ባለሥልጣናት በሙሉ ተጨንቀው መጫወቻ እየገዙ ይመጣሉ። ልጁ ግን ማልቀሱን አላቆመም። የወያኔ ባለሥልጣናት ምን ዓይነት መጫወቻ ነው የምትፈልገው? ብለው ልጁን ይወተውቱታል። ልጁም እኔ የምፈልገው ተሾመ ቶጋን ነው ብሎ መለሰ። የወያኔ ባሥልጣናትም ልጁን፣ አትቀልድ እሱን አታገኝም። እሱ የአባትህ መጫወቻ ነው አሉት።”
ቀልዱ በጣም አሳቀኝ ።
ብዙ ጊዜ ሰለቀይ ሽብር እንድነግራቸው ይጠይቁኛል። አንዳንዴ አንግባባም። የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለነሱ በሚመጥን መልኩ መመለስ ያቅተኛል። የጊዜውን ልዩነት አጉልቶ ስለሚያሳየኝ እደነቃለሁ። ስለ ቀይ ሽብር ከቤተሰቦቻቸው ከሚሰሙት በስተቀር የጠለቀ ዕውቀት እንደሌላቸው ለመረዳት ከባድ አይደለም። ያን ጊዜ እንዲህ ተደረገ፣ ወጣቶች እንዲህ አደረጉ፣ ሰልፍ ወጡ ፣ እዚህ እናንተ የምትቆሙበት ቦታ ላይ የእገሌ ሬሳ ወድቆ ነበር፣ እዛ ጋ እገሊት ተጥላ ነበር ፣ እንደዚህ ዓይነት ንግግሮችን ያዳምጡ እንጂ ምክንያቱን ምን እንደነበረ ያስረዳቸው ያለ አይመስልም። ኢሕአፓ የታገለበትን ዓላማዎች አያውቁም።
ከነዚህ ወጣቶች ጋር ተገናኝተን ያሳለፍነቸውን የሕይወት ገጠመኞች ስንጨዋወት የዚያን ዘመን ትውልድ እውነተኛ ታሪክ ለተከታይ ትውልድ ማስተላለፍ አለመቻል የሚያመጣውን የአስተሳሰብ መዛባት መረዳት ችያለሁ። በወቅቱ የነበሩትን ወጣቶች ቆራጥነት ያደንቃሉ። በቀይ ሽብር የተፈፀመውን ፋሽስታዊ ጭካኔ ለማመን ያዳግታችዋል። እነርሱ ከእኔ ስለ ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) ታሪክ መስማትን ይፈልጋሉ። እኔ ደግሞ ከእነርሱ ስለ ሱዳን፣ የቻድ፣ የሰሃራ በረሃዎች፣ ስለ ሊቢያ፣ ሜዲትራንያን ባሕር የጀልባ ጉዞ፣ ስለ ማልታ፣ ጣልያን፣ ቱርክ፣ ቡልጋሪያ፣ ግሪክ . . . ወዘተ የስደት ሕይወት እንዲያጫውቱኝ እፈልጋለሁ። ከወጣቶቹ ጋር ውይይታችን ሁል ጊዜ የሚጥም ነው።
ከወጣቶቹ እንደተረዳሁት በትምህርት ቤት ውስጥ የኢትዮጵያን ታሪክ በተለይም ቀይ ሽብርን በሚመለከት ምንም ዓይነት ትምህርት አይሠጥም። በመረጃ በተደገፈ መልክ እውነቱ ተፅፎ አልተቀመጠም። ቀይ ሽብርን በተመለከተ ከጠየቁኝ ውስጥ አንዱ ጥያቄ ላይ ልንግባባ አልቻልንም። ብዙ ተወያይተንበታል።
“ተወልዳችሁ ባደጋችሁበት አዱ ገነት አዲስ አበባ) ውስጥ እንዴት እጃችሁን ሰጥታችሁ ትገደላላችሁ? አታሳብሩም (አትጠፉም)እንዴ? ” የሚለው ጥያቄ ነበር። ከዚህ ጥያቄ የምንረዳው ወጣቶቹ በሃገራችን ለተፈጠረው ችግር ሁሉ መፍትሄው ማሳበር (ከሃገር መውጣት) መሆኑን ነው የሚያምኑት።
“በዚያን ወቅት ከሃገር መውጣት መፍትሔ ነው ብለን አናምንም ነበር። ሕዝባዊ መንግሥት ቢኖር የኛ ብቻ ሳይሆን የሃገራችንን ችግር ይፈታል ብለን ነበር የምናምነው። ያንንም ሥርዓት ለማምጣት ነበር የምንታገለው። ያም ሆኖ ግን እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ወይም ክፍለ ሃገር ለመጥፋት ይሞከር ነበር። ወዴት ይጠፋል? ዙሪያው በሙሉ እኮ መሄጃ የለም። አዲስ አበባም ሆነች መላው ሃገሪቱ በፋሽሽቱ ደርግ አብዮት ጥበቃና ካድሬዎች ተሞልተዋል። የኢሕአፓ መዋቅራችን ተሰባብሩዋል። ከደርግ ጋር የሚሠሩ አንጃዎች (ከኢሕአፓ ክደው ወደ ደርግ የገቡ) ተፈጥረው ነበር ። እነርሱ ይከታተሉናል። ነፃ እርምጃ እየተካሄደ ነበር”።
” ነፃ እርምጃ ማለት ምን ማለት ነው?” ብለው ጠየቁኝ።
“ነፃ እርምጃ ማለት የደርግ የምርመራ ክፍል ሠራተኞች ከኢሕአፓ ውስጥ ከወጡ አንጃዎች ጋር በመሆን በመኪና እየዞሩ የኢሕአፓ አባል የመሰላቸውን በዘፈቀደ ባገኙበት እንዲገድሉ ፍቃድ ያገኙበት ጊዜ ነበር። የኢሕአፓ አባል ከመሰላቸው ይገድሉታል። ከዛም ቀይ ሽብር ተጀመረና ብዙዎቻችን ታሠርን። ወጣቶች በየመንገዱ እየተገደሉ ይጣሉ ጀመር። በተወለዱበትና ባደጉበት ሠፈር ውስጥ ሬሳቸው ተጣለ። አባትና እናት የተገደሉ ልጆቻቸውን መንገድ ላይ ወድቀው አገኙ። ምንም መሄጃ ቦታ አልነበረም።”
“አዱ ገነት(አዲስ አበባ) ውስጥ መጥፋት ከበደ?” ብለው ጠየቁኝ። ተኮላትፎ ወላጆቹን እንዳሳቀ ሕፃን ልጅ በፍቅር እየተመለከቱኝ በማይምነቴ ተዘባበቱብኝ። ነፃ እርምጃና ቀይ ሽብር በመላ ሃገሪቱ፣ በጠቅላላው ሕዝብ ላይ የታወጀ ግድያ መሆኑን አልተገነዘቡትም ነበር።
አንደኛው ጉሮሮውን በሳል አፅድቶ እንዲህ አለ፣
“ጋሼ በእናንተ ጊዜ የደረሰባችሁ የሚያሳዝን ነው። ነፃ እርምጃ የምትለው ዓይነት እኛ በየቀኑ አሁን በጭላዎቹ (በወያኔ) ጊዜም እየኖርነው ነበር። በእናንተ ጊዜ ወግ ያለው ሞት ነበር። እኛን እኮ ተቃዋሚ ከመሰልናቸው ሌባ ነው ብለው ነው የሚጠብሱን (የሚገድሉን) አሁንም ቢሆን ልዩነት የለውም። ሃገራችን ውስጥ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መኖር አንችልም። ሌላው እየበላ እየተዝናና እኛ ገና በወጣትነታችን የበይ ተመልካች መሆን ያስጠላል። ዛሬ ደልቶት የሚኖረው ዘመድ ውጭ ሃገር ያለውና ከወያኔ ጋር የተሰለፈ ብቻ ነው። በተለይ ውጭ የሚኖረው ሕዝብ ሃገር ቤት ተመልሶ መጥቶ ሲደሰት ስናየው እዛ ከመሰቃየት ማቅጠንን (መጓዝን ፣መጥፋትን) እንመርጣለን፡፡
“እናንተ ላይ የደረሰውን ሠፈር ውስጥ በወሬ በወሬ እንሰማለን። ፖለቲካ ውስጥ መግባት ችግር እንደሚያመጣ እንረዳለን። እናንተ የታገላችሁት ለአርሶ አደሩ፣ ለላብአደሩ ነው ብለኸናል። እኛ ለራሳችን ነው የምንታገለው። ለእኛ የሚታገልልን የለም። ስለዚህም እናሳብራለን (ከሃገር እንጠፋለን)። ለምሣሌ በእኔ ላይ የደረሰውን ልንገርህ። አንተ አዲስ አበባ ውስጥ መሄጃ አጣን ትላለህ። ልብ ብለህ ስማኝ።”
“ከአዱ ገነት እስከ ሱዳን ያለውን ተወው እሱ አልጋ ባልጋ ነው። አልጋ ባልጋ ነው ስልህ ቀላል ነው ማለት ሳይሆን በአጠቃላይ በኛ ላይ የደረሰብንን ስንመለከተው ቀላል ነው። ከሱዳን ለእሬዎች( ኤርትራውያን) ከፍለናቸው ወደ ሊብያ ሊወስዱን ተነሳን። በአንድ ቶዮታ ፒክ አፕ መኪና ላይ የተጫንነው ሠላሳ ሦስት ነበርን። ከመካከላችን ዘጠኙ ሴቶች ነበሩ። ሌላ አንድ ቶዮታ መኪና አብሮን ነበር። ግን እዛ መኪና ላይ የተጫኑት ወንዶች ብቻ ነበሩ። ሰሃራ በረሃን አቋርጠን ሊቢያ ለመድረስ ነበር። ስለ ሰሃራ የምታውቅ ይመስለኛል። ከአሸዋ በስተቀር ምንም የማይገኝበት በረሃ ነው።”
“ውሃ፣ ዛፍ፣ ማረፊያ፣ መጠለያ፣ በፍፁም የለም። የምንጠጣው ውሃ እየተቆጠበ ነው የሚሰጠን። ለዛውም ውሃው ውስጥ ብዙ እንዳንጠጣ ቤንዚን ይጨምሩበታል። ጋሼ ጉዞው በጣም የሚያስመርር ነው። ግን ዓላማችን አውሮፓ መድረስ ስለሆነ ቆርጠን ነው የተነሳነው። ሰሃራ በረሃ ውስጥ አንድ ቀን ከተጓዝን በኋላ የቻድ ጥቁሮች እየተኮሱ መጡና ያዙን። ጭንቀት በመካከላችን ሰፈረ። ሴቶቹ ማልቀስ ጀመሩ። ተጨነቅን። ስለምናልመው የአውሮፓ ኑሮ ማሰብ ቀርቶ ስለ ሰሃራ ውስጥ ተቀብሮ መቅረት አዕምሮችንን አጣበበው። ሁላችንም የያዝነውን እንድናስረክብ ተነገረን። አንዳንዶቹ ሰጡ። ብዙዎቻችንን ግን ከክረን(ደብቀን) ዝም አልን። ቻዶቹ ፍተሻ ጀመሩ። የመጀመሪያው ልጅ ላይ ገንዘብ አገኙ። ከመካከላችንን አውጥተው በጥይት ጭንቅላቱ ላይ መትተው ገደሉት። ከዛም ሁላችንም የደበቅነውን እያወጣን ሰጠን። ከሱዳኖቹ ጋር ብዙ ከተጨቃጨቁ በኋላ ሴቶቹን አንድ መኪና ላይ ጭነው ይዘዋቸው ሄዱ። የዛ ሰዓት የነበረው ለቅሶና ጩኸት ልነግርህ አልችልም። እህቶቻችንን ለዘላለም የዝሙት ባርነት ተወሰዱ። ሕይወት አስጠላን።ጋሼ አዱ ገነት ውስጥ መሄጃ አጣን ትለናለህ? መሄጃ ማጣት ማለት ሰሃራ በረሃ ውስጥ ቻዶች ሲመጡ ነው። መሄጃ ማጣት ማለት የምትወዳት ጓደኛህ በቻዶች ስትወሰድ ስምህን እየጠራች አድነኝ ስትልህ ምንም ማድረግ ሳትችል ስትቀር ነው።” ብሎ ንግግሩን ደመደመ።
“በ1970 ዓ. ም. አንድ ጓደኛችን ሠንጋ ተራ አካባቢ ከሚገኘው የከፍተኛ ሦስት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ታስሮ ነበር።” ብዬ ጀመርኩ። “ይህ ልጅ በጣም የሚወዳት ፍቅረኛውን ሊያስሯት ሲመጡ አብሯት ስለነበር ነው የተያዘው እንጂ በኢሕአፓ ውስጥ ብዙም ተሳትፎ አልነበረውም። እሱ ምሥጢር ይነግረናል ብለው ገረፉት። ምንም ሰለማያውቅ ሊነግራቸው አልቻለም። ግን ጓደኛውን በጣም እንደሚወዳት ሰለሚያውቁ እሷን አምጥተው አጠገቡ ሲገርፏት ምንም ማድረግ ሰለ አልቻለ ቆሞ ያለቀስ ነበር። ከዛም እሷን ትተው እሱን ሲገርፉ ልጅቷ አልቻለችም። ልቀቁትና እኔ እነግራችኋለሁ አለቻቸው። እሱን ተውትና እሷ የምታውቀውን ነገረቻቸው። በኋላ ልጅቷ በቀይ ሽብር ሊገድሏት ሲወስዷት ስሙን እየጠራች እንደምትወደው እየነገረችው ነበር ጎትተው ወስደው የገደሏት። ይህ ዓይነት ታሪክ በእኛ ሃገር በገዛ ወገኖቻችንን ላይ የተፈፀመ ነበር።”
ሌላኛው ደግሞ ቀጠለና ፡-
“ጋሼ በእናንተ ጊዜ የተፈፀመውን ለማመን ያዳግተናል። ቆራጥነታችሁ ቢያስደስተንም ከዛ ሃገር ለመጥፋት አለመሞከራችሁ ይገርመኛል። እኔ እንደማምነው ሸገር (አዲስ አበባ) ከማንኛውም ደን የበለጠ ጥቅጥቅ ያለች ነች። ቢከፋህ የምትሸቅልባት፣ ብትደሰት የምትዝናናባት ነች። የኔን ደግሞ ስማ ልንገርህ።
ሰሃራን በቀላል አለ ችግር ነው የተሻገርኩት። ቻዶችም አላገኙንም። የሊብያውያንንም ዘረኝነት ግን ከሁሉ በላይ አስቃይቶናል። በተለይ ቤንጋዚ በነበርኩበት ጊዜ መንገድ ላይ ሳይቀር ዐረቦቹ ይደበድቡን ነበር። ትንሽ እንኳ ከተከላከልን ፓሊሶች ይዘው ስለሚያሰቃዩን እንሸሻለን እንጂ ምንም የምንወስደው እርምጃ የለም። ከተያዝክ ደግሞ ግርፋቱንና ድብደባው አይጣል ነው።”
“ሌላ በጣም የተሰቃየሁት ሜዲትርያንያን ባሕር ላይ ነው። በሰሃን ውስጥ አሸዋ ላይ በተቀመጠ ኮምፓስ እየተመራን በአንድ ዐረብ መሪነት ነፋሱ ጥሩ ነው ተብለን ባንድ አሮጌ ጀልባ ከሱማሌ፣ ከጋና፣ ከናይጄሪያ፣ ወዘተ የመጡ ስደተኞች ታጭቀን ጉዞ ጀመርን። ጉዟችን ወደ ጣልያን ነበር። ትንሽ እንደተጓዝን ማዕበል ጀመረ። ጀልባዋ ትናወጥ ጀመር። የጀልባዋ ካፒቴን ችግር ውስጥ እንደገባ አወቅን። እንደ ድንገት ጀልባዋ በጣም ተናወጠች። ጩኸትና ለቅሶ በረከተ። ሁላችንም መፀለይ ጀመርን። ሴቶቹ ማልቀስ ያዙ። መጮኽ ጀመርን። አንደኛው ልጅ በፍርሃት እየጮኸ ማልቀስ ጀመረ። የጀልባዋ ካፒቴን የሚያለቅሰውን ልጅ ወደ ባሕሩ እንድንጥለው አዘዘን። ጣልነው። ልጁ ባሕሩ ላይ ሆኖ ይለምን ነበር። ከዚያም ካፒቴኑ የተወሰኑ ልጆች ወደ ባሕሩ እንዲጣሉ አዘዘ። ተጣሉ። ጋሼ ሁል ጊዜ ሰለቀይ ሽብር ስሰማ የሚገርመኝ ለምን እንዳላቀጠናችሁ ነው። አዱ ገነት አይደለችም መደበቂያ የሌላት። ባሕር ላይ ብቻህን ስትጣል፣ ዋና ሳትችል የሚረዳህ ሳይኖር ወደ ባሕሩ ስትሰምጥ ነው መደበቂያ የሌለው። እናንተን ለመውቀስ አይደለም ግን ለምን እንዳልጠፋችሁ አሁንም አይገባኝም።” ብሎ ፈገግ አለ ።
እኔ ደግሞ በተራዬ ልንገራችሁ ብዬ ጀመርኩ። “አዱ ገነት እንደናንተው እናታችን ነበረች። ተወልደን አድገንባታል። መውጫ መግቢያዋን እናውቃለን ። ግን እኛ ላይ የደረሰው ቀላል አይደለም። በሃገራችን ጨቋኝ ሥርዓትን ለመቃወም በመደራጀታችን፣ በመታገላችን፣ ነፃነት በመጠየቃችን እንደ አውሬ እየታደንን በአደግንበት ሰፈር ከቤታችን እየተወሰድን ስንገረፍና ስንገደል ነበር። ቀይ ሽብር በብዛት በኢሕአፓ አባላት ላይ ይደረግ እንጂ የኢሕአፓ አባላት ያልነበሩ በተለያየ ምክንያት ተገድለዋል።”
“አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር ይህ ግድያ የሚፈፀመው። ከአንዱ ሠፈር ስትፈለግ ወደ ሌላ ሠፈር መሄድ አይቻልም። ደርግ ደህንነት፣ አብዮት ጥበቃ፣ ቀበሌ፣ የሚለውን የስለላ መዋቅሩን በሃገሪቱ ውስጥ በሞላ ዘርግቶ ነበር። ምንም መንቀሳቀሻ አይገኝም። እናት ልጇን አሳልፋ ለመስጠት ተገዳለች። አባት በግርፋት ብዛት የተደበቀ ልጁን አሲዞ እስከማስገደል የደረሰበት ወቅት ነበር። የነበረውን ሁኔታ አሁን ለመገመት ይቸግራችሁ ይሆናል። የማዕበሉንም ሆነ የቻድ ጥቁሮች ወይም የሊቢያ ዜጎች ያደረጉት ተግባር የሚያሳዝን ነው። ሁላችንም የደረሰብን አስቃቂ ታሪክ አለን። ጊዜውና ሁኔታው ይለያይ እንጂ ስቃዩ ሰቃይ ነው።”
“የእኔን እንውስድ አልኩና ቀጠልኩ ቀኑ ቅዳሜ ነበር ባላሰብኩበት ሰዓት ቀበሌዎች ሠንጋ ተራ ጋ ያዙኝ ከዚያም አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አሠሩኝ። አንድ ይግረም የሚባል ፋሽስት ነበር የያዘኝ። ከምኖርበት አካባቢ ጥቆማ ደርሶት ነው። በበነጋታው ዕሁድ ሸገር ውስጥ አሠሳ ነበር። አሠሳ ማለት ምን አልባት አታውቁም ይሆናል። አዲስ አበባ በሞላ በታንክና በከባድ መሣሪያ ተከባ አብዮት ጥበቃና ወታደሮች በየቤቱ እየገቡ ፍተሻ ማድረግ ነው። የዛኑ ቀን ወደ ደርግ ጽሕፈት ቤት ወሰዱኝ። ሰኞ ዕለት ወፌ ገለበጡኝ። ወፌላላ ማለት ታውቃላችሁ? ብዬ ጠየቅሁና መልስ ከነሱ ሳልጠብቅ ቀጠልኩ። ሁለት እጃችሁ በገመድ ይታሰርና ሁለቱ እግሮቻችሁ እንደተቀመጣችሁ በእጆቻችሁ መሐል ይደረጋሉ። በእግሮቻችሁና በእጆቻችሁ መካከል አጠና ይገባና ሁለት ሰዎች በግራና በቀኝ ሆነው ሲያንጠለጥሉዋችሁ እግራችሁ ወደላይ ጭንቅላታችሁ ወደ ታች ይዘቀዘቃል። ከዚያም ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይስቅሉዋችኋል ። እንዳትጮሁ አፋችሁን በጨርቅ ይጎሰጉሱታል። ከዚያም እንደ ጌሾ ወቀጣ ውስጥ እግራችሁን መቀጥቀጥ ይጀምራሉ። ይህን ጊዜ ነው መሄጃ ማጣት።” አልኳቸው የነእርሱን አነጋገር በመኮረጅ።
“ጋሼ አንተን በገዛ ሃገርህ ወፌ ከተው አስረው ያሰቃዩኽን ስናስታውስ ላንተ እናዝናለን። በሰሃራ በረሃ ውስጥ የቻድ ጥቁሮች አግኝተው ያሰሯትና ለብዙ ጊዜ ከእነርሱ ጋር ቆይታ በኋላ ግን መንገድ አግኝታ ወደ ሊቢያ የመጣች አንዲት የአዲስ አበባ ልጅ ኩርፋ ውስጥ አግኝቼ ነበር። ኩርፋ ከሰሃራ በረሃ ቀጥሎ ሊቢያ ውስጥ የምትገኝ አንዲት አነስተኛ የሊቢያ ከተማ ነች። እዛ ቦታ ወደ ሰሜን ሊቢያ ለመጓዝ ከመነሳታችን በፊት አንድ ቤት ውስጥ ከሊቢያ ፖሊሶች ተደብቀን ነበር። ሌሊት ሌሊት ያቺ ልጅ በኃይል ትቃዣለች። ፍርሃት ስለሚሰማት ትቀስቀሰንና ጠብቁኝ ትለናለች።”
“ከሁለት ወር ያህል እንደቆየን ጭንቀቷ እየበዛ መጣና እራሷን ለማጥፋት ትሞክር ጀመር። አንድ ቀን ታዲያ ደብዳቤ ጽፋልን ራሷን አጥፍታ አገኘናት። በድብቅ ስለምንኖር በድብቅ ከተሰቀለችበት አውርደን በድብቅ ቀበርናት። ለእናቷ የፃፈችው ደብዳቤ እስከ አሁን ትዝ ይለኛል። በደብዳቤው ላይ የደረሰባትን ስቃይ ጽፋ ነበር። የቻድ ጥቁሮች ሰሃራ በረሃ ውስጥ ያገኙዋቸውና ይዘዋቸው ወደሚኖሩበት ስፍራ ይወስዷቸዋል። በየተራ እየተፈራረቁ ይገናኟቸዋል። ለብዙ ጊዜ አለ ዕረፍት የተለያዩ ወንዶች ይቀያየሩባቸዋል። ብዙዎቹ ሴቶች በድብደባው ብዛት ሕይወታቸው በዚያው ይጠፋል። አንዳንዶቹ አርግዘው በስቃይ ይገላገላሉ። ያም ሆኖም ግን ወንዶቹ መፈራረቃቸው አይቀርም። በስንት መከራና ስቃይ ሕይወታቸውን በዚያው ውስጥ ይገፋሉ። ከዛ ማምለጥ የማይሞከር ነው። ከተቻለም ደግሞ ከዛ አምልጠው የመጡት ከፍተኛ ጭንቀት አለባቸው። እራሳቸውን ከማጥፋት ሌላ አማራጭ የላቸውም። ጋሼ ይህ ነው መሄጃ ማጣት።”
“እንደዚህ ዓይነት አረመኔያዊ ተግባር በእኛ ሃገር አልተደረገም ማለት አይደለም” ብዬ ጀመርኩ። “አዲስ አበባ ያሉ ቀበሌዎች ሁሉ ወደ እስር ቤትነት ተለውጠው ነበር። የቀበሌ ባለሥልጣኖች በሙሉ የመግደል ሥልጣን ነበራቸው። በዛን ጊዜ የነበሩት እህቶቻችን የደረሰባቸውን ስቃይ ልታውቁት ይገባል። እነዚህ አረመኔዎች ብረት በብልታቸው ውስጥ እየከተቱ ያሰቃዩዋቸው ነበር። ጡታቸውን በሳንጃ የተወጉ ብዙ ናቸው። እነዚህ ቦዘኔ የሆኑ አብዮት ጥበቃዎች በምርመራ ስም ከእስር ቤት እያወጡ እግርና እጆቻቸውን አስረው ይገናኙዋቸው ነበር። ከዚያም አሰቃይተው ይገሏቸዋል። ሬሳቸውንም መፈክር ጽፈው እየለጠፉ በተወለዱበትና ባደጉበት ሰፈር ውስጥ ይጥሏቸዋል። የአዲስ አበባ ምድር በደም የተበከለች ነች። ታሪካችንም የቆሸሸ ነው።”
በመካከላቸው የምትገኘው ሴት ልጅ ደግሞ እንዲህ አለች። “አይ ጋሼ አሁን ላለነው ወጣቶች እኮ የተለያየ ወንዶች አለፍላጎታችን ሲገናኙን ነው የኖርነው። ከዚያም ውጭ የምናውቀው ኑሮ ሰለሌለ ይህንን ተግባር እንደ ወንጀልም አንቆጥረውም። ገና የወር አበባችን ሳይጀምረን ነው ለሽርሙጥና የምንዳረገው። በእናንተ ጊዜ ያሉት ሴቶች ክብራቸውን ይዘው ለሃገራቸው ሲታገሉ ስለሞቱ እንቀናባቸዋለን። ”
“ለምሣሌ እኔን ውሰድ። እኔ አሚቼ ( አዲስ አበባ የተወለዱ ቤተሰቦቻቸ ኤርትራውያን የሆኑ ) ነኝ። አዲስ አበባ ነው ተወልጄ ያደግሁት። መለስና ኢሣያስ የተጣሉ ጊዜ ወደ አስመራ ቤተሰቦቼ ሲላኩ እኔም አብሬ ሄድኩ።ከቤተሰቤ ተለይቼ አዲስ አበባ ልቅር ብል የሚጠብቀኝ ሽርሙጥና ነበር። ይህ ለመወሰን የተገደድኩት ገና የአስራ ሦስት ዓመት ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ነው። ወደ አስመራ ለመሄድ እኔ ስወስን ትልልቅ ወንድሞቼና እህቶቼ ግን ለመሄድ ሰላልፈለጉ ቀሩ። እኔ ገና ኤርትራ ከመድረሳችን እንኳን ከሕዝቡ ከዘመዶቻችንም መስማማት አልቻልኩም። ደበረኝ ፣ደበተኝ። ያም ሆኖ ሦስት ዓመት በጭንቀት ኖርኩ። አንድ ቀን ታዲያ ሻዕቢያ ጠረጋ(እናንተ አሰሳ የምትሉት) ጀመረ። ሻዕቢያዎቹ ለሳዋ(ኤርትራ ውስጥ የሚገኝ የወታደር ማሰልጠኛ ) ወጣቶችን ፍለጋ ይዘው ነበር። ቤተሰቦቼ የዛን ቀን እንድደበቅ ነገሩኝ። ለእኔ ግን ያ ቀን የመወሰኛዬ ቀን ሆነ። ቆረጥኩ። አዱ ገነት መመለስ አለብኝ። ከሃገሬ ማንም ሰው ሊያሰወጣኝ አይችልም ደርምሼው መሄድ አለብኝ ብዬ ወስንኩ። አቀጠንኩ (ተጓዝኩ) በአሥራ አምስት ቀኔ በጎንደር አድርጌ አዱ ገነት ገባሁ።”
“ወያኔ እንድኖር በከለከለኝ አዲስ አበባ ውስጥ ማንም ሳይከለክለኝ ተዝናንቼ ኖርኩ። ወደ ኤርትራ ቤተሰቤ በወያኔ መላኩን የሚያውቁ ጎረቤቶቻችንን ከተመለስኩ በኋላ አግኝተውኝ ያውቃሉ። ግን ማንም ለወያኔ አሳልፎ የሰጠኝ የለም። ኤርትራዊ ኢትዮጵያዊ የሚለውን ያመጡት ወያኔዎች ናቸው እንጂ ሕዝቡ አይደለም። እኛ አብረን ተወልደን አብረን ያደግን ነን። ከአማርኛ በስተቀር ሌላ ቋንቋ አላውቅም ። ከወያኔዎቹ የተሻለ አማርኛ እናገራለሁ። በድብቅ አዲስ አበባ ውስጥ መሸቀል ጀመርኩ። ያ እጠላው የነበረውን ሴተኛ አዳሪነት በአሥራ ስድስት ዓመቴ ጀመርኩ። ከብዙ ጨካኝ ወንዶች ጋር ተኛሁ። አሁን ኤድስ በበዛበት ጊዜ ኮንዶሙን ካላወጣሁ ብሎ የሚደባደብ ስንት አለ መሰለህ? በመጨረሻም በሸቀልኩት ገንዘብ ተጠቅሜ ወደ ዐረብ ሀገር ሰው ቤት ለመቀጠር ሄድኩ።”
“የሄድኩት ቤይሩት ነበር። እዛ ሰው ቤት ተቀጥሬ ነበር የምሠራው። ዐረቦች ቤት ግርድና ላይ ምን እንደሚገጥመን ታውቃለህ? ለእመቤቲቱ ገረድ ፣ ለባልየው ደግሞ ጭን ገረድ ነው የሆንኩት። እዛም ቢሆን ዐረቦቹ እየተፈራረቁ ነው የሚጫወቱብን። አንድ ቀን ባልየው እንደለመደ እኔ ጋ እንደመጣ ሚስቱ ደረሰች። ከዛ ቀን ጀምሮ ያ ቤት ለእኔ ሲዖል ሆነ። ኑሮም እየከበደኝ መጣ። ሚስትየዋ ቀኑዋን ጠብቃ እንደምትገለኝ አወቅሁ። በየቀኑ በእንደዚህ ዓይነት መኖር እየደወከኝ (እየሰለቸኝ) መጣ። ወደ አውሮፓ ማቅጠን እንዳለብኝ ተረዳሁ። እሁድ እሁድ አበሾች የምንገናኝበት ቤተክርስትያን አለ። አውሮፓ እንዴት መሄድ እንደሚቻል ከዛ ጠየቅሁ። ወደ ግሪክ 375 ዶላር ተከፍሎ መሄድ እንደሚቻል ነገሩኝ። ነገሩ ሁሉ ቀላል መስሎ ታየኝ። እዚህ በዐረቦች ከመገደል ይሻላል ብዬ ወሰንኩ። ገንዘቡን ለሚመራኝ መሪ (ማፍያ) ከፍዬ ጉዞዬን ጀመርኩ።”
“ጉዞዬን የጀመርኩት ከሊባኖስ ዋና ከተማ ከቤይሩት ወደ ሶርያ ነው።” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች ። ጭውውታቸን ተረበሸ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለኔልሰን ራህላሂላ ማንዴላ!

የሊቢያ እስር ቤት

ከወጣቶቹ ጋር ውይይት ካደረግን ከጥቂት ቀናቶች በኋላ አንዱ ከመካከላቸው ወደ ቤቴ መጣ። የመጣው አንድ የማስተረጉምለት ደብዳቤ ይዞ ነው። ስለ ደብዳቤው ይዘት ከተወያየን በኋላ ቀስ ብለን ሁለታችንም በየልባችን በጉጉት ወደምንጠብቀው ውይይት ገባን። ያቋረጥነውን የየትውልዳችንን ወግ ቀጠልን።
በእጁ የያዘውን ወረቀት እያየ፣ ፊቱን ቋጠር ፈታ እያደረገ “ጋሼ እንዴት ነበር የከርቸሌ እስር ቤት?” ብሎ ጠየቀኝ።
“አሁን ተመልሼ ወደ ኋላ ሳየው ከርቸሌን እንደ እስር ቤት ማየት ይከብደኛል” አልኩት ።
“እንዴት?”
“ምክንያቱም ከመከራውና ከችግሩ ባሻገር ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ። እንደምታየው ክራር መምታት፣ ሹራብ መሥራት እዛ ነው የተማርኩት። መፅሐፍ ማንበብም በሰፊው የጀመርኩት እዛው ነው። መከራው ግን መከራ ነው። ምን ጊዜም በእኔም ሆነ በወቅቱ አብረውኝ ታስረው ከነበሩ ጓዶቼ አዕምሮ የሚጠፋ አይደለም። ከደርግ ፅሕፈት ቤት እስረኛ ለመውስድ በየቀኑ አንድ መኪና ትመላለስ ነበር። ቀን ቀን የሚገረፉትን፣ ማታ ደግሞ ለመግደል የሚፈልጓቸውን ለመውሰድ ትመጣለች። መኪናዋ መጥታ እስከምትሄድ ጭንቀት፣ ከሄደች በኋላ ደግሞ ሃዘን ግቢውን ያጥለቀልቀዋል። የገዛ ስምህ ያስጠላሃል። ስምህ ቢረሳና ሳትጠራ ብትቀር ትመኛለህ። ጓደኛህን ከአጠገብህ ወስደው ገርፈው፣ ሽባ አድርገው ያመጡታል ። ቁጭ ብሎ ሲጫወት የዋለውን ወስደው ይገሉታል። ማታ ስሙ የተጠራው ልጅ በደቂቃ የሚችለውን ያህል ተናዞ፣ ያለ ንብረቱን አውልቆ ሰጥቶ ውልቅ ይላል። ላይመለስ ይሄዳል። እኔ ካለሁበት የተወሰዱና የተገደሉ ወጣቶች ፊት ዛሬም ከዓይኔ አይጠፋም። እሁድ ደርሶ ቤተሰቦች ምግብ ይዘው ልጃቸውን ሊጠይቁ ሲመጡ እቃውን ስንሰጣቸው የሚጮኹትን እናቶች አስባቸው። ልጄን አያለሁ ብላ የመጣች እናት የልጇ ጨርቅ ሲሰጣት የሚሰማትን መራራ ሃዘን አስበው” አልኩት።
ዝምታ በመካከላችን ሰፈነ። ግን አንድ ነገር ሊነግረኝ እንደመጣ ገባኝ።
ከጥቂት የዝምታ ደቂቃዎች በኋላ የእናንተስ ጉዞ እንዴት ነበር? አልኩት ከዛም ትንሽ ሲያሰላስል ቆየና ስለ ሰሃራ ጉዞው እንዲህ ሲል ቀጠለ።
“ይህንን አሁን የምትለኝን ስሜት ሰሃራ በረሃ ላይ ተሰምቶኝ ነበር። አንድ አብሮን የነበረ ልጅ ጉዟችንን በጀመርን በአስረኛው ቀን ደከመብን። መተንፈስ አቃተው። የመኪናውን ጣራ አንኳኩተን ሾፌሩ እንዲቆምልን ለመነው። እየተነጫነጨ አቆመልን። ልጁን አወረድነው። ትንሽ እንደቆየ አረፈ። ቀበርነው። አሸዋ አለበስነው። ሁላችንም ደነገጥን ግን የማይለመድ የለምና ሞትንም እየቆየን ለመድነው። የደከመ ሰው ካልሞተ በስተቀር መኪናውን ማስቆም ተውን። መኪናው ቢቆምስ ምን ይጠቅማል? ጥላ የለ፣ መጠለያ የለ፣ ከሥር አሸዋ፣ ከጎን አሸዋ፣ ከላይ ፀሐይና ንዳድ።”
“ከሱዳን ወደ ሊቢያ መጓዝ በጣም ከባድ ነው። ከሁሉም የሚያስፈራው ከኸምሲን ነው። ከኸምሲን የበረሃ ውስጥ ነፋስ ነው። ከኸምሲን ሜዳውን ተራራ የሚያደርግ ፣ አሸዋውን ከአንድ ቦታ አንስቶ ወደ ሌላ የሚከምር፣ ወቅቱን ያላወቀን ተጓዥ በቁሙ የሚቀብር፣ የሰው ልጆች ጠላት ነው። ከኸምሲን የሚነሳበትን ወቅት በልምድ የሚያውቁ የሰሃራ በረሃ ነዋሪዎች ጉዞ አይጀምሩም። በዚህ ምክንያት አምስት ወር ሱዳን ውስጥ ተቀመጥን። ከዛም የከኸምሲኑ ወቅት አልፏል ተብለን በሦስት ቶዮታ ላንድ ክሩዘር ተሞልተን ጉዟችንን ወደ ሰሜን አፍሪካ ሊቢያ አመራን። አሁን ጊዜው አልፎ ሲያወሩት እንዴት ይቀላል ? መኪናው ሙሉ በሙሉ ዕቃ ተጭኖበት ከላዩ ደግሞ ከሠላሳ በላይ ሆነን ተጭነን። ለ6-7 ቀን የሚደርስ ምግብና ውሃ ይዘን ነበር። መኪናው ላይ አልተመቸኝም፣ ጠጋ በልልኝ፣ እግሬ ላይ ነው የተቀመጥከው፣ እግሬን ደነዘዘኝ በሚሉ ምክንያቶች መጣላት ጉዞውን እንደጀመርን የተለመደ ነበር”።
“ገና አንድ ቀን እንደተጓዝን አንደኛው መኪና ሰለተበላሸ ሾፌሮቹ እሱን መጠገን ጀመሩ። ብልሽቱ ከባድ ሰለነበር አንዱ መኪና ተመልሶ ዕቃ ለማምጣት ይከንፍ ጀመር። እዛች ቦታ ተቀምጠን ሦስት ቀን አለፈ። የፀሐዩ ሙቀት ንዳድ ነው። ከሥር አሸዋው ያቃጥላል። መነጋገር ቆመ። መጠበቅ፣ መጠበቅ፣ አሸዋ፣አሸዋ ከሦስት ቀን በኋላ መኪናው ተሠራና ተነሳን።”
“ወደ ሰሃራ እየጠለቅን ስንመጣና የሚጠብቀን ጉዞ በጥል ሳይሆን በመስማማት እንኳ አዳጋች መሆኑን እያወቅን ስንመጣ፣ በትንንሽ ምቾቶች መጣላታችንን አቆምን። ከሁሉ አስደንግጦ ዝም ያሰኘን አንድ ቦታ አንድ የተበላሻ መኪና በአሸዋ ተሸፍኖ አገኘን። ሾፌሩ ጠጋ ብሎ ተመልክቶ በጣም በደነገጠ ሁኔታ ወደ እኛ ይመለከት ጀመር። ሁላችንም እየሮጥን ወደዚያ ሄደን ስንመለከት የአንድ ሰው አፅም አየን። ምን አልባት ደክሞባቸው የተበላሸ መኪና ላይ ጥለውት ሄደው ይሆናል። ዕድላችን ከከፋ የሁላችንም መጨረሻ ይህ እንደሚሆን ገባን። ምግብም ሆነ ውሃ ከዛ ሰዓት ጀምሮ መቆጠብ ጀመርን።”
“አንድ ቀን ከመካከላችን አንዱ ልጅ ከመኪናው ላይ ወደቀ። ሁላችንም መጮኽ ጀመርን። ከፊት የነበሩት የመኪናውን ጣሪያ ይመቱ ጀመር። አንድ ሁለት ኪሎሜትር ከተጓዝን በኋላ ሾፌሩ አቆመ። ወደ ኋላ ተመልሶ ልጁን እንደገና ጫነው። ሁኔታው በማናችንም ሊደርስ ስለሚችል ፍርሃት ያሳድራል። ከዚያም የማያልቀውን መንገድ ተያያዝነው። አንድ የአሸዋ ክምር ተራራ ላይ ስንደርስ ሾፌሩ ወርደን በእግር እንድንጓዝ ነገረን። መኪናዋ ቀስ ብላ ወደ ተራራው ጫፍ ብቻዋን ወጣች። ከስር አሸዋው ያቃጥላል፣ ከላይ ፀሐዩ ሌላ ነው። አራት ሰዓት የሚሆን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ተጓዝን። ጋሼ አሁን ድካሙን ልነግርህ አልችልም። አንዳንዶቻችን እዛው ሞተን ብንቀበር ደስታውን አንችለውም። እንደምንም መኪናው ጋ ተደረሰ። ጉዞ ተጀመረ። ተኛን።በተኛንበት የለበስነው አንሶላ አሸዋ ይሞላዋል። ሰለመኝታው ምንም ልነግርህ አልችልም። ለመሆኑ እንዴት ነበር ከርቸሌ የምትተኙት?”
“ከርቸሌ የመኝታችን ሁኔታ የተሻለ ነው። ወደ ደርግ ጽህፈት ቤት ከመወሰዴ በፊት አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን አድሬ ነበር። እዛ ውስጥ አንዲት አራት ሜትር በአራት በሆነች ክፍል ውስጥ ከሥልሳ በላይ እስረኞች ነበሩበት። አሁን ሳስታውሰው እስር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜዬ ነበርና ምንም እንዳልተኛሁ ነው። ከዛም ደርግ ጽሕፈት ቤት ነበር የተወሰድኩት። በጣም አነስተኛ ጠባብ ክፍል ነው። ወቅቱ አሰሳ (እናንተ ጠረጋ የምትሉት ዓይነት ) ነበርና ያቺ ጠባብ ክፍል በአንዴ ሞላች። ውስጥ የተገረፉትም፣ ያልተገረፉትም አንድ ላይ ስለነበርን በጣም ተፋፍገን ነበር። የነበረው ሁኔታ በጣም አሰቃቂ ነው። መተኛት የለም ሁሉም ቆሞ ነው የሚያድረው። ሙቀቱም የሚቻል ዓይነት አልነበረም።”
“የተነፈስነው ትንፋሽ ዝናብ ሆኖ ይወርድብን ነበር። ከዛም ባለፈው እንደ ነገርኳችሁ ከብዙ ሰቃይ በኋላ ወደ ከርቸሌ ተወሰድን። በመጀመሪያ ከርቸሌ ውስጥ ሐኪም ቤት የሚባል ቦታ ነበር የተወሰድኩት። ከዛ ከኛ የባሰ የተገረፉ ፣ መንቀሳቀስ የማይችሉ፣ ጥፍራቸው የተነቀለ፣ ጣታቸው የተቆረጠ፣ ጀርባቸው የተቃጠለ በብዛት ሲመጡ እኛ ደግሞ ትንሽ የተሻለን ወደ ዓለም በቃኝ እና ቀጠሮ ተዘዋወርን። እኔ ቀጠሮ ነበር የደረሰኝ።”
“የታሰርንበት ክፍል ትልቅ ነው። ውስጡ የተለያየ የመተኛ ሁኔታዎች አሉ። በግድግዳው በኩል ብዙ ዓመት የታሠሩ እስረኞች በድሪቶ(የተሰበሰበ አሮጌ ጨርቅ) የተሠራ ፍራሻቸውን ቆልለው እንደ አልጋ ይከምሩታል። በእስር ቤት አጠራር “ሰኔቻ” ይባላል። ከክፍሉ አንድ በኩል ደግሞ የአለቀ የተቀጣጠለ የሽቦ አልጋ አለ። ይህ የሽቦ አልጋ ላይና ታች አለው ። ክፍሉ መሃል ላይ የሚተኙት ደግሞ “ደቦቃ” ይባላል። ደቦቃ ላይ የሚተኛ ቀን ቀን ፍራሹን ማጠፍ አለበት። አለበለዚያ መተላለፊያ አይኖርም። የከርቸሌ መኝታ ፍራሽ ይገባ ስለነበር ከሁሉም የተሻለ ነው። ያም ሆኖ ይህ ከርቸሌም ቢሆን አስቸጋሪ ኑሮ ነበር።”
“ከዛስ ሰሃራ በረሃ ውስጥ እንዴት ሆናችሁ?” ብዬ በተራዬ ጨዋታውን እንዲቀጥል ጋበዝኩት።
“ሰሃራን አቋርጠን የሰው ዘር ለመጀመሪያ ያየነው ኩርፋ የሚባል የሊቢያ ከተማ ነው። እዛ ብዙ አልቆየንም። ሣር በጫነ መኪና ውስጥ ሆነን ወደ ቤንጋዚ ጉዞ አደረግን። የዛን ቀንም ሆነ ዛሬ ስለ እስር ቤት ስታወራን በደንብ እሰማህ ነበር። የዛን ቀን ከርቸሌ ውስጥ በጣም እንደተቸገራችሁ ስትነግረን በጣም በሃሳብ ስለተጠመድክ ዝም ብለን ሰማንህ። ከርቸሌ ብዙዎቻችንን ከነበርንባቸው እስር ቤቶች ጋር ሲወዳደር እንደ እረፍት ቦታ ነው የምንቆጥረው”።
“ከሊቢያ የተነሳሁት አንድ ሸራ በተሸፈነ ጀልባ ነው። ጀልባ ውስጥ ሃያ እንሆናለን። የጀልባው ሃላፊ ቱኒዛያዊ ነው። ስለ እሱ ብዙ ጥሩ ነገር ይወራል። ማንም ተጓዥ ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት የሚጠይቀው ስለ ካፒቴኑ ዕውቀት ነው። አንዱ ባሕር ላይ ነው የተወለደው፣ ባሕሩን እንደ ጓዳው ነው የሚያውቀው ይላል፣ ሌላው ደግሞ የሊቢያ ባሕር ኃይል ነበር ይላል፣ ሌላው ባለፈው ሰንጥቆ በተጨበጨበለት ጊዜ ነው ማልታ ጠብ ያደረጋቸው ይላል። እንደ ንግዱ ብዛት የካፒቴኑ ጉብዝና አብሮ ይነጉዳል። የካፒቴኑ ጉብዝና ሲጋነን የመጫኛው ዋጋ ይንራል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዕጣ ፋንታህ በሆነው ጀልባ መጫን ነው።ጉዞውን ስንጀምር በምሽት እየተዝናናን ነበር። ባሕሩ ላይ ነጋብን። አንድ ትልቅ መርከብ በአጠገባችን ሲያልፍ ማዕበል እንደሚነሳ በድምጽ ማጉያ ነግረውን ከባሕሩ እንድንወጣ አሳሰቡን። እኛ የምሄድበት ብቻ ስለምናስብ ሰለ ማዕበል የነገሩንን ማመን አልቻልንም።”
“ካፒቴኑ መመለስ አለብን አለ። እኛ አይሆንም አልን። ከዛም ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ማዕበሉ ጀመረ። ያቺ ትንሽ ጀልባ ትናወጥ ጀመር። ማዕበሉ እየፀና እየበረታ ሲሄድ እንኳን መመለስን ልንቃወም፣ የሕይወታችንን መትረፊያ መለመን ጀመርን። ጀልባው ላይ የሚያስታውክ አለ፣ የሚያለቅስ አለ፣ የሚጮኽ አለ፣ የሚፀልይ አለ። ጀልባዋ እላይ ደርሳ ትመለሳለች”።
“በማዕበሉ ግፊት ተመልሰን ወደ ሊቢያ ተጠጋን። የሊቢያ የባሕር ጠባቂዎች መጥተው አተረፉን። ሕይወታችን መትረፏን እንጂ ሊቢያ ውስጥ ምን እንደሚገጥመን አላወቅንም ነበር። የሊቢያ ፖሊሶች ያዙንና ታሰርን። እስር ቤቱ በጣም ይሞቃል። ሁሉም ነገር ያስጠላል። እኔ ለአንድ ዐረብ እስረኛ በተላላኪነት ተመደብኩ። መጀመሪያ ምንም አልመሰለኝም። ለሥራ ብቻ የሚፈልገኝ ብቻ ነበር የመሰለኝ። አንድ ሁለት ቀን ካደርኩ በኋላ ሰውነቴ መለስ አለ። ልብስም ተሰጠኝ። ገላዬን ታጠብኩ። ማታ ላይ ያ ዐረብ እኔ የምተኛበት መጣና አጠገቤ ለመተኛት ሞከረ። እንቢ አልኩት። በበነጋታው ደበደበኝ። ሌሎችም አገዙት። አሰቃየኝ። ሲኪኒ (ጩቤ) አወጣና ቂጤ ላይ ወጋኝ። በሦስተኛው ቀን ተመልሶ መጣ። አሁን ግን ከጓደኛው ጋር ነው የመጣው። እጄን ያዙኝ። ሱሬዬን አወለቁት። በሰው ላይ ይደረጋል የማልለው በእኔ ላይ ደረሰ። ሰውነቴን ሁሉ ሰቀጠጠው። ደሜ ፈሰሰ። ሰው ጠላሁ። አንተ ጨርቅ ነው አፍህ የጎሰጎሱት፣ እኔን ግን ተወኝ ጋሼ ይቅርብህ ባትሰማው ይሻልሃል። እኔ ከአሁን በኋላ ሰው አይደለሁም። ረክሼአለሁ። በሕይወቴ አንድ ነገር እመኛለሁ። ያንን ዐረብ አግኝቼ በተበቀልኩት። አቅሙም ግን የለኝም። ቂሙ ሆዴ ውስጥ አለ። የተደላደለ የአውሮፓ ኑሮ እንኳ ይህ የደረሰብኝንን ያስረሳኛል ብዬ አላምንም። ጋሼ ይህንን የምነግርህ ምንአልባት እስከ አሁን ለማንም ያልነገርኩትን ምሥጢር ነው አለኝ።”
ይህንን ተናግሮ በጣም አለቀሰ ። እኔም አብሬው አለቀስኩ። ይህንን የመሳሰሉትን ግፍ የሚፈፅሙትን ዐረቦች ባገኝ እኔም የምበቀላቸው እንደሆንኩ ተሰማኝ። አዘንኩ። ከዛ ከበረሃ ተርፈው ያልፍልናል ሲሉ በሊቢያ እስር ቤት ለሚማቅቁ ኢትዮጵያውያን በሞላ አብረን አለቀስን። ከረጅም ጊዜ ፀጥታ በኋላ ጨዋታውን እንዲህ ሲል ቀጠለ።
“በአጠቃላይ ሲታይ የሊቢያ ሕዝብ ጥሩ አይደለም። የተማረ ብዙ አይገኝበትም። ለኛ ለኢትዮጵያውያን ያላቸው ጥላቻ ብዙ ነው። ለእነርሱ ኢትዮጵያዊ ሆንክ ኤርትራዊ ምንም ልዩነት የለውም። አበሽ አበሽ ነው። በመንገድ ላይ መጥተው ያለህን ይቀሙሃል። ሲፈልጉ ይደበድቡሃል። ዘረኝነታቸውም ከማንኛውም ሃገር ዜጋ ዘረኛነት ይበልጣል። የሊቢያ መንግሥት እንዲማሩ፣ እንዲያውቁ አይፈልግም። ጭካኔቸው ከማይምነት የመጣ ይመስላል። ይህ ደግሞ የብዙ ዐረቦች ፀባይ ነው።”
“ለምሳሌ ሱዳን ውስጥ በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ላጫውትህ። ወደ ሊቢያ መሄድ የምትፈልግ ኢትዮጵያዊ ሴት በተለይ ቆንጆ ከሆነች ስቃይ ይበዛባታል። እያንዳንዱ በዚህ ቢዝነስ(ንግድ) የተሰማራ ማፊያ ያችን ልጅ መላጥ(የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ) ይፈልጋል። እንቢ ካለች አትሄጅም ብሎ ይከለክላታል። እሺ ካለች ደግሞ መከራ ነው። ሱዳኖች በኮንደም ማድረግ አይወዱም። ብዙዎቹ ሴቶች የሰሃራን በረሃ የሚጓዙት እርጉዝ ሆነው ነው።አንዳንዶቹን ደግሞ እዛው ጉዞ ላይ ያስወርዳቸዋል። ሰሃራ ውስጥ የሚቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው።
“ሴቶቻችን በመገደድ ብቻ ሳይሆን በገንዘብ እጥረት ሴተኛ አዳሪነት ይጀምራሉ። ይህ በተለይ ሊቢያ ውስጥ የጦፈ ቢዝነስ ነው። አንድ ሴት ሻይ ቤት ተቀጥራ ከሠራች የምትሠራው ይታወቃል። በድብቅ ትሸቅላለች ማለት ነው። እህቶቻችን እንደዚህ እየሠሩ ለእኛ ገንዘብ ሲጎድልብን ይሞሉልናል። በጠገበ ዐረብ እየተደበደቡ በስቃይ የሚኖሩ ብዙ ናቸው። ለእኔ ዐረብ በእኛ ላይ የፈፀመው ግፍ ከጣሊያን ወረራም ከቀይ ሽብርም በላይ ነው። ምንአልባት በሃገርህ ሰውና በሌላ ሃገር ሰው መጠቃት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለተጠቃው ሰው ግን የግፉን ጥልቀት አይቀንሰውም። ጋሼ በኛ ላይ የደረሰው ከቀይ ሽብር አይተናነስም። ይህ የምነግርህ ትንሹን ነው። እስኪ ከሴቶቹ ተግባባና ያጫውቱህ። የኛ ሴቶች ዓይን አፋርነት ሰላላቸው እውነቱን ግልፅ አድርገው አይነግሩህም። ቢነግሩህ ግን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆንን ትገነዘባለህ። የተሰቃየነውን ተሰቃይተን አውሮፓ ገብተናል።”
“ዐረቦቹ እስር ቤት ውስጥ ያለኝን ገንዘብ ሁሉ ወሰዱብኝ። ድሮ እስር ቤት ውስጥ የሻማ እንደሚባለው ማለት ነው። ይህንን እንኳ እኔ አላውቅም ነበር። ሌሎች ሲወሩ ነው የሰማሁት። እድሜ ለኢሕአፓ የሻማን አስቆመ ብለው ሲያወሩ አዱ ገነት እያለሁ ሰምቼ ነበር።”
“ለምንድነው ኢሕአፓ የሻማ መክፈልን ያስቆመው? “ብሎ ጠየቀኝ።
“እኛ እስር ቤት በነበርንበት ወቅት የሻማ የሚባለው ድብደባ አልነበረም። ግን ሲወራ እንደሰማሁት አንድ አዲስ እስረኛ እንደመጣ ያለውን ንብረቱን ለሻማ እንዲሰጥ ይጠይቁታል እንቢ ካለ ይደበድቡታል፣ ያሰቃዩታል። የኢሕአፓ አባላት መታሰር ከጀመሩ በኋላ ግን ይህ አስቃቂ ተግባር አስቆሙት። ሁሉም በፍቅር ያለውን ተካፍሎ መብላት ተጀመረ። የወንጀል እስረኞች በፖለቲካ እስረኞች እየተመሩ እስር ቤቱን የፍቅር ቤት አደረጉት። እዛው እስር ቤት ውስጥ ወንጀለኛ የነበሩ በኢሕአፓ አቋም አምነው ወደ ፊት ጥሩ ተግባር ለመፈፀም የወስኑ ብዙ ነበሩ”።
ወጣቱ ልጅ ከመለያየታችን በፊት “ስለ ዐረቦች ብዙ ለማወቅ ከፈለክ እስኪ ሩትን ጠይቃት ። እሷ ትነግርሃለች አለኝ። ልጅቷን ፈልጌ ስለ ጉዟዋ እንድትነግረኝ ጠየቅኋት ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዲያስፖራ ሆይ! ዘራፊዎች እንደገና ሊያፈርሱት ተሚችሉት ጎጆ በፊት ፋኖን ገንባ!

ከቤይሩት እስከ አውሮፓ

ከብዙ ቀጠሮና መመላለስ በኋላ ይህን ታሪክ የነገረችኝን አገኘኋት፡ እንዲህ ብላ ታሪኳን አጫወተችኝ።
“ዐረቦች ብቻ አይደሉም በኛ በኢትዮጵያውያን ላይ ጨካኞቹ እርስ በራሳችንም እንጨካከናለን። አንተን ያሰቃዩህ አበሾች ናቸው። እኔ ፈረንሳይ ውስጥ አንድ አበሻ ቤት ተቀጥሬ ነበር። ሙሉቀን ምግብ ሠርቼ፣ ልጅ ጠብቄ፣ አስቤዛ ገዝቼ፣ አልጋ አንጥፌ ሁሉንም አድርጌ 350 ኤሮ ነበር የማገኘው። ሰዎቹ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ አበሾች ነበሩ። እንደ ገረድ ነበር የሚያዩኝ። በዛ ሃገር 350 ኢሮ በቀን 2 ሰዓት በሳምንት አምስት ቀን ተሠርቶ የሚገኝ ነው። እኔ የፈቃድ ወረቀት ስለሌለኝ ብቻ ነበር ከአስር ሰዓት በላይ ሣምንቱን ሙሉ የምሰራው። ደግሞ ቋንቋ ስለማልችል አበሻ ቤት ይሻላል ብዬ ነበር።”
“አንዳንዴ ሴትየዋ ኢትዮጵያ ውስጥ 350 ኢሮ ማለት ስንት ነው? ብላ ትጠይቀኛለች። ይህ ምን ማለቷ እንደሆን ተውቃለህ? ብዙ ነው የምከፍልሽ ለማለት ነው። እሷ በእኔ ችግርና ወረቀት አለመኖር እንደምታተርፍ እየረሳችው እንደምትረዳኝ አድርጋ ለመመፃደቅ ነበር። ይገርመኝና ሴትየዋ ምግብ የምሸምተው አዲስ አበባ ይመስላት ይሆን ? ብዬ አስብ ነበር። መቼም ቤተሰቤን መርዳት ስለነበረብኝ ነው እንጂ አልሠራም ነበር። እድሌ ሆኖ ነው እንጂ እኔም እንደሷ አውሮፓ መኖሬን ትረሳዋለች።”
“ባለፈው እንደነገርኩህ የቤት ሠራተኛነት የጀመርኩት ቤይሩት ውስጥ ዐረቦች ጋር ነበር። በመጀመሪያ ቤይሩት በጣም የምታምር ሃገር ሆና ከሌሎች የዐረብ ሃገሮች ጋር ስትወዳደር ነፃነት ያላት ሃገር ነች። በሃገሪቱ የውጭ ሃገር ዜጎች በብዛት ይኖሩባታል። ዜጎቿም በኑሯቸውም ይሁን በነፃነታቸው ደስተኞች ናቸው። የሃገሪቱ ሕዝብ የበለፀገና የሠለጠነ ነው። ለምሳሌ በእምነትህም ሆነ በአለባበስህ የሚቃወምህ ወይም የሚነካህ የለም። በቤይሩት ከተማ ውስጥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1998 በግምት 27,000 አካባቢ አበሻ ይኖር ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ወንዶች ከ100 አይበልጡም። ቤይሩት ውስጥ ሴቶች የሚሠሩት ሥራ ግርድና ነው። በሥራው ብዛትና በአሠሪዎቹ ድብድብ ብዙ እህቶቻችን አሰቃቂ ስቃይ ያለበት ሕይወት ነው የሚኖሩት።”
“በተለይ አክራሪ እስላሞች ቤት የምትሠራ ከሆነችና የሚሉትን ሁሉ ካልፈፀመች የሚደርስባትን ስቃይ ልትገምተው አትችልም። በጣም ከባድ ነው። ለምሣሌ ቀንም ይሁን ማታ በሥራ ላይ መገኘት አለባት። ዕረፍት ፣የመኝታ ሰዓት የሚባል የለም። እነርሱ በፈለጓት ጊዜና ሰዓት መገኘት ግዴታዋ ነው። ትንሽ ከዘገየች ጥፊና እርግጫ ይከተላታል። እንደጥፋትህ ዓይነት ቅጣቱም ይጠነክራል። ለምሳሌ ሸሚዝ ካቃጠልክ፣ ከተላክበት ቶሎ ካልተመለስክ፣ በመንገድ ላይ ሌላ ሃበሻ ወይም የውጭ ዜጋ ስታነጋገር ከተገኘህ፣ የታዘዝከውን በሙሉ እነርሱ በፈለጉት ጊዜ ካላደረስክ የሚደርስብህ ዱላ አይጣል ነው። ሌላው ደግሞ ሲገቡ ሲወጡ በሌላም ነገር ከተናደዱ ንዴታቸውን የሚያበርዱት አንተን በመምታት ነው። አንዳንድ ጊዜ በትክክል ሥራውን ብትሠራውም ቅጣት አይቀርም። ሥራውንም እንደገና እንድትሠራው ትታዘዛለህ።”
“የምትፈራረመው ኮንትራት ሦስት ዓመት ሲሆን ይህንን መጨረስ አንዳንዴ አዳጋች ይሆናል። ይህን ወቅት መታገስ አቅቷቸው እራሳቸውን ከፎቅ የሚወረውሩ ብዙ ናቸው። ከሥራ ብዛት የወገብ በሽታ ላይ ወድቀው የመሥራቱም ሆነ የመኖር ዕድላቸው ጨልሞባቸው የሚሰቃዩትን ቤት ይቁጠራቸው። ከሌላ ሰው ጋር መገናኝት በጣም ከባድ ስለነበር የአዕምሮ ጭንቀት የያዛቸው ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም። ዐረቦቹ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከተገናኘን ይጠፋሉ ብለው ስለሚያስቡ ቁጥጥራቸው የበዛ ነው። በአካባቢው የሌላ ሃገር ሰው የሆነ አይጠፋም። የበረታ ሰው ከውጭ ሰዎች ጋር መነጋገርንን መታገል ይኖርበታል። አለበለዚያ ግን ብቸኝነቱ ራሱ በሽታ ነው። ራስን ለማጥፋትና ለማበድ ይዳርጋል።”
“አንዳንዶቹ እህቶቻችን ደግሞ የተሳሳተ ወሬ(ኢንፎርሜሽን) ይዘው ይመጡና ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ከአሠሪዎቻቸው ጋር የመመላለስም ጠባይ ያመጣሉ። ከባለቤቱ ወንዶች ጋር ይተኛሉ። ያንን በግልጽ ለማሳየት ይጥራሉ። ከሚስቱ ጋርም መናናቅ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ሚስትየዋ የምትሆነውን ታጣለች። ይህንን ለፈፀመች ልጅ ከዚያ በኋላ የመከራ ጊዜ ይጀምራል። ባልየው ዝም ነው የሚለው። ለእሷ ሲል ከሚስቱ አይጣላም፣ ቤተሰቡን አይበትንም። በሌላው ደግሞ ወንዶቹ ማስቸገር ይጀምራሉ። እንቢ ካልክም በየቀኑ መደብደብ ነው። እሺ ካልክም ሚስትየዋ ያወቀች ጊዜ መከራ ነው። ይህንን ዓይነት ችግር በብዛት ይደርሳል።”
“እኛን ኢትዮጵያውያንን ምን እንደነካን አላውቅም። ትላንት እዚህ እኛ ጋ አንድ ልጅ ራሱን ሰቀለ። እሺ እሱ ምን ሆኖ ነው ትላለህ? እዚህ አውሮፓ ውስጥ ነው፣ ሥራ አለው፣ ችግር የለበትም፣ ሥራስ ባይኖረው የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ የሚኖርበት፣ የሚለብሰው አያጣም፣ ቤተሰብ መርዳት ይችላል። ምን ሆኖ ነው እራሱን የሚገድለው? ግን በዐረብ አገር ባርነቱ ሲበዛብን ከፎቅ ወርደን ለመፈጥፈጥ ያልሞከርን የለንም። ሞት ከዚህ ባርነት ይሻላል ብለው ያሰቡትም እራሳቸውን አጥፍተዋል።”
“ባለፈው እንደነገርኩህ በሚስትየው ምክንያት ቤቱ ሲዖል ሆነ። በሳምንት አንድ ቀን እረፍት ነበረኝና ቤተክርስቲያን ሄጄ መጥፊያ መንገድ መፈለግ ጀመርኩ። አንዳንድ ጓደኞቼ ስለ አውሮፓ ጉዞ ነገሩኝ። በአውሮፓ የተሻለ ኑሮና ጥሩ ኑሮ እንደሚገኝ ሰማሁ። ጠፍቼ ለመሄድ ወሰንኩ ይህንን ስትወስን ማወቅ ያለብህ ጉዞው አዳጋች መሆኑን ነው። ይህንን ሥራ የሚሠሩት ግን መንገዱ አዳጋች እንዳልሆነና ትንሽ ሰዓት ብቻ በእግር እንደምትጓዝ ሌላው ግን በመኪና እንደሆነ ነው የሚሰብኩህ።”
“ሦስት ኢትዮጵያውያን ሴቶችና አንድ የሲሪላንካ ወንድ ልጅ አራት ሆነን ነበር የተነሳነው። ግን እሱ ምን ወንድ ይባላል! ከእኛ በላይ ነው እየተንሰቀሰቀ የሚያለቅሰው። ጉዟችን ወደ ቱርክ ከተማ ካንታኪያ ነው። ከሊባኖስ ስንነሳ ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ከሰዓት በኋላ ነበር። ሁለት ሰዓት በመኪና ከተጓዝን በኋላ አንድ ጫካ ስንደርስ በፍጥነት መሮጥ አለባችሁ ተባልን። ይህ ማለት ደግሞ ወደ ሶርያ ድንበር መድረሳችን መሆኑ ነው። ድንበሩን መሻገር የምንችለው በእግር ሰለሆነ በጨለማ ጉዟችንን ጀመርን፡፡ አርባ አምስት ደቂቃ ከተጓዝን በኋላ ከአንድ ወንዝ ደረስን። የወንዙ ጥልቀት እሰከ ደረታችን ይደርስ ነበር። ለመሻገር የወሰደብን ጊዜ ከፍርሃቱ ጋር ሠላሳ ደቂቃ ነው። ከዛም በፍጥነት በእግር መጓዝ ነበረብን። ሁለት ሰዓት እንደ ተጓዝን የሶሪያን ድንበር ጥሰን ገባን። ሶርያ ጫካ ውስጥ ሌላ አንድ ልጅ ተጨመረ። ዕረፍት ሳናደርግ ጉዟችንን ቀጠልን።”
“ጋሼ የጨለማ ጉዞ ምን ይመስልሃል? ከባድ ነው መደናበር ነው። የምትረግጠው ጉድጓድ ሊሆን ይችላል፣ የሚወጋ እንጨት ወይም ብረት ይኖራል። ደግሞ መፍጠን ያስፈልጋል መደበቂያው ቦታ ሳትደርስ ከነጋብህ መያዝህ ነው። ብሩህ ሆኖ የሚታይህን የአውሮፓ ኑሮ እያሰብክ፣ ሰው ከደረሰበት እደርሳለሁ ብለህ እየተመኘህ መጓዝ ነው። በየመሃሉ ደግሞ የአምስት ደቂቃ እረፍት ይሰጥሃል። የሶሪያን ግዛት ለመጨረስ ሌሊትና አንድ ቀን መጓዝ ይጠይቃል። በበነጋታው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ቱርክ ድንበር መድረስ አለብን። ካልሆነ ግን የሚጠብቀን ሰው ላይኖር ይችላል። በአንዳንዶቻችን ላይ አደጋ ስለደረሰብና ከሚመራን ሰው ጋር ገንዘብ ጨምሩልኝ በሚል አለመግባባት ስለተፈጠረ ዘግይተን ከምሽቱ አራት ሰዓት ደረስን። እኔ ላይ የደረሰብኝ አደጋ በመጀመሪያ አንድ ትልቅ መንገድ ለመሻገር አጥር ስንዘል ብረት እግሬን መታኝና አቆሰለኝ። በሌላ ጊዜ እንደዚሁ ብረት ሆዴን ወጋኝ። ይህ ሁሉ በቀን ቢሆን ላይደርስ ይችል ነበር።በሌሎቹም ላይ እንደዚሁ አደጋ ደርሶባቸዋል።”
“በመዘግየታችን ምክንያትና በሌሎች ምክንያቶች የሚቀጥለው ጉዞ ተሰረዘና አንድ ወንዝ አጠገብ እንድናድር ተዘጋጀ። በጣም ደክሞን ስለነበር ተኛን። ቁስሌ እየባሰብኝ መጣ። ሌሊቱን በሕመም ስቃይ በማሳለፌ የሚመራን ሰውዬ አዝኖልኝ ወደ ገጠር ሄዶ መድሃኒት አመጣልኝ። ወንዙ ጋ ተደብቀን አምስት ቀን አደርን። ሌሎች ተጨምረው በቁጥር 20 ሆንን። ከነርሱም ውስጥ አበሾች ሦስት ብቻ ነበርን ። ሌሎቹ ከተለያዩ ሃገር የመጡ ናቸው። በስድስተኛው ቀን ከምሽቱ 2 ሰዓት ጉዞ ጀመርንና በበነጋታው አንድ ሰዓት ላይ ካንታኒካ ደረስን። ሁላችንም እንደገና ተበታተንን ። በተለያዩ ሰዎች ቤት ውስጥ ተመደብን ። ከዛ በአውቶብስ 50 ዶላር ከፍለን ወደ ኢስታንቡል ጉዞ ቀጠልን ። ከአስራ ስድስት ሰዓት ጉዞ በኋላ ኢስታንቡል ገባን።”
“ኢስታንቡል ላይ ሌላ መንገድ አዋቂ ማፈላለግ ነበረብን ። በጀልባ ወይም በእግር ወደምትሄድበት ሃገር የሚወሰነው እዚህ ነው ። መጀመሪያ ዓላማዬ ወደ ጣልያን ለመጓዝ ነበር ግን ሰላልተሳካልኝ ጉዞዬን ወደ ቡልጌሪያ ጀመርኩ ። ሌሎቹ አብረውኝ የነበሩት ሴቶች ገንዘብ ከዘመድ ስለተላከላቸው ቀድመው ሄዱ ። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከኔ ጋር ሁለት አበሾችና 27 የሌላ ሃገር ዜጎች ሆነን ተነሳን።”
“ስድስት ሰዓት ከተጓዝን በኋላ ቱርክ ቡልጌሪያ ድንበር ደረስን። የቱርክ ድንበር የሚጠበቀው በውሻ ነው ። ውሻው ካገኘህ እስክምትሞት ድረስ ቢነክስህም የቱርክ ፖሊሶች አያስቆሙልህም ። ይህ በጣም አደገኛና የተለመደ አጋጣሚ ነው ። እኛን የወሰደን ግለስብ ግን በደንብ ሁኔታውን አጥንቶ ሰለነበር ይህ አጋጣሚ አልደረሰብንም ። ዋናው ያስቸገረን የፓውዛ መብራቱ ነው ። መብራቱ ወደኛ በሚበራበት ጊዜ መደበቅ አለብን ። ድንበሩ በሽቦ የታጠረ ስለነበር መሬቱን እየቆፈርን ድንበሩን ተሻግረን ጉዞ ቀጠልን ። ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ድንበሩን ተሻገርን ። አሁን ሳስረዳህ ነገሩ ይቀላል እንጂ የዛ ጊዜ እዛው መሞትን ትመርጣለህ ። በውሾች የተነከሱትን ሰዎች ታሪክ ለሰማ ሰው ቡልጌሪያ ክልል እስከምትገባ ሰውነትህ በእያንዳንዱ ኮሽታ ይሳቀቃል።”
“ሲነጋ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ መኪና ጠበቀንና ወደ ሶፊያ ቡልጌሪያ ዋና ከተማ ይዞን ሄደ ። ከዛም ወደ ግሪክ ለመጓዝ ጥረት ጀመርኩ ። ሁለት ጊዜ አልተሳካልኝም ተመለስኩ ። በሦስተኛው ግን ተያዝኩና ሶፍያ እስር ቤት ተከተትኩ ።በሶፍያ እስር ቤት ለሁለት ወር ቆየሁ ። እስር ቤቱ በጣም አስቀያሚ ነው ። ቢሆንም ከወንዶች ለሴቶች በጣም ይሻላል ። ወንዶቹን የቡልጌሪያ ፖሊሶች በጣም ይደበድቧቸዋል ። ምግቡ የሻገተ ድንችና የሚሸት ውሃ ነበር የሚሰጡን ። ከሁለት ወር በኋላ ተፈታሁና እንደገና ሳልሞክር አምስት ወር በችግር ቡልጌሪያ ውስጥ ኖርኩ።”
“ከዛ በእግር ጉዞ ወደ ግሪክ አደረግሁ ። ጉዞው ከባድ ነው ። ስድስት ተራራ መውጣትና መውረድ አለብህ ። ተራራ ስልህ ደግሞ ትንሽ እንዳይመሰስልህ ። ድንጋይ ብቻ የሆነ ቀጥ ብሎ የቆመ ተራራ ነው ። አንዳንዴ ላይ ደርሶ ተንሸራቶ መውረድ አለ ። በመንፏቀቅ እጃችን ሁሉ ቆሰለ ። ሦስት ሱሪ ለብሰን እሱን አልፎ ሰውነታችንን ይጎዳናል ። ከአራት ቀን መከራ በኋላ ተሰሎንቄ ግሪክ ገባን። አንተ ደርግ አሰቃይቶ ጠባሳ እግርህ ላይ እንደተወልህ አሳይተኸናል። የግሪክ ተራሮች እኛም ሰውነት ላይ ጠባሳ ትተው አልፈዋል ። የተንፏቀቅንበት ቂጣችን ጠባሳው አለ።”
“ከተሰሎንቄ ወደ መጨረሻው ግሪክ በባቡር ነው የሄድኩት ። የማልመው አውሮፓ አቴንስ ደረስኩ ። እዚህ እንደመጣሁ ሌላ ችገር ገጠመን። ለካ ያ እንደዛ የጓጓንለት አውሮፓ የራሱ ችግር አለው።”
“አውሮፓ ስንገባ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ይመስለናል ። ግን አይደለም። እንደምታውቀው በመጀመሪያ የመኖሪያ ፈቃድ ያስፈልጋል ። እሱን ለማግኘት አቴንስ ውስጥ ማንንም አላውቅም ነበርና አንድ ናይጀራዊ ረድቶኝ መኖሪያ ችግሬን አቃለለልኝ። ሥራም ፈልጎ አሲያዘኝ። ትንሽም ገንዘብ አጠራቀምኩ። ከዛም ሱዳኖችን ተዋወቅኩና አንዲት ከአቴንስ በለቀቀች ሱዳናዊ ስም በየስድስት ወሩ የሚሰጠውን መታወቂያ አወጣሁ። ዐረብኛ ስለተማርኩ ምንም ችግር አልነበረብኝም። ከዛ በኋላ የራሴን ኑሮ ጀመርኩ። ምንም ሬስቶራንት ውስጥ ተቀጥሬ ጥሩ ኑሮ ብኖርም ሥራው እየከበደኝ ወገቤን እያሳመመኝ መጣ። እንደምንም ብዬ ከፍዬ መርከብ ውስጥ ተደብቄ ወደ ናፖሊ ኢጣልያ መጣሁ። ናፖሊ ውስጥ ፈረንሳይ ይማሩ የነበሩ ሃበሾች ከፍለውልኝ ወደ ሮማ በመኪናቸው ወሰዱኝ። ሮማ ከተማ ማንንም አላውቅም ነበር። መንገድ ላይ አበሾች አግኝቼ እንዲረዱኝ ጠየቅኋቸው ። እነሱም ተባበሩኝ። ከዛም ለባቡር የሚሆን አሰባስቤ ወደ ፓሪስ መጣሁ። ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ ለመግባት ይቻላል ስለተባለ ነበር አመጣጤ። ከሮም ስመጣ ከአንዲት ልጅ ጋር አብረን ነበርንና እሷ ፓሪስ ዘመድ ስለነበራት ብዙም አልተቸገርንም ። ከፓሪስ ውጭ በሚገኝ ቦታ እጄን ሰጠሁ። ጊዜያዊ ወረቀት እስከማገኝ ሁለት ወር መንገድ ላይ እያደርኩ፣ ለምኜ እየበላሁ ቆየሁ። ወረቀቱን ሳገኝ ተመልሼ ፓሪስ መጣሁ። ከፓሪስ ወደ እንግሊዝ የምትሄደው በኮንቴነር ስለነበር ጉዞ ስናደርግ መኪናው ተገልብጦ እግዜር አዳነኝ ። ከዛ በኋላ የእንግሊዙን ጉዞ ሰርዤ ወደ ጀርመን ገባሁ።”
“አሁን ይህንን ስተርክልህ ቀላል ይመስልሃል ። አይደለም በጣም አደገኛ ጉዞ ነው ። እኛ አዲስ አበባ ውስጥ መሄጃ አጣን ስትሉ እንደማናምናችሁና ነገሩን እንደምናቃልለው አንተም ችግሩን ሁሉ ብነግርህ አትረዳውም ። የኛን ኑሮ መኖር አለብህ ። ታሪክ ሲነገር ቀላል ነው ። ሲኖሩበት ግን ከባድ ነው።”
“ስለ ጀርመኑ ደግሞ ምን ልንገርህ ፈረንሳይ የተነሳሁት አሻራ እንዳይገኝ ለብብት ፀጉር መላጫ ፈረንጆቹ የሚጠቀሙበት መድሃኒት ፈልጌ አሻራዬን ለማጥፋት ስንት ታገልኩ መሰለህ? ባለፈው የደርግ ጽሕፈት ቤት መኪና ከርቸሌ ስትመጣ እንደምትሳቀቁት እኛም ደግሞ ፖሊስ በአካባቢያችን ካለፈ አሻራችን ተገኝቶ ሊመልሱን ነው እያልን እየተሳቀቅን ብዙ ዓመታት ኖርን። ይኸው ፈጣሪ አምላክ ይመስገን እስከ አሁን ምንም አልተገኘብኝም። ከአሁን ወዲያም ይመጣል የሚል ፍርሃት የለኝም።”

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያማራ ሕዝብ ሆይ ትልቁን ዠማ (ዐባይን) ተሻግረሃል፣ የቀረችህ ትንሿ ዥረት (ቀበና) ናት፣ መመለስ የለም

ማጠቃለያ

ከነዚህ ውይይቶች ብዙ ነገር ተምሬአለሁ። ምን አልባት ወጣቶቹ ሃገራቸውን ለቀው በሰው ሃገር የሚደርስባቸውን ችግር አቃለን የምንመለከትና ድሎትን ፍለጋ ከሃገር እንደሚወጡ የምናስብ እንኖራለን ። ይህ ግን ትክክል አይደለም ። በሃገሪቱ ውስጥ ባለው ችግር ምክንያት የሚሰቃዩ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባንም። በዓለም ላይ በየሃገሩ በሚገኙ እስርቤቶች ውስጥ ቁጥራቸው በጣም ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ። በየዐረቡ ሃገር የሚሰቃዩ እህቶቻችንን ማሰብ ይኖርብናል ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከተፈለገ ባጠቃላይ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግር መዋጋት ያስፈልጋል ። ይህ በስደት የሚያልቀው ትውልድ በቀይ ሽብር ካለቀው ትውልድ በጣም ይለያል። የሃገሪቱን ችግር ሃገር ውስጥ ሆኖ ለመፍታት መታገልን የመፍራት ባሕሪ ይታይባቸዋል። ይህ ፍርሃት መጀመሪያ በደርግ አሁን ደግሞ በወያኔ የተፈጠረው የሽብር አገዛዝ ውጤት ነው ።
በሌላ በኩል ደግሞ ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍም አስፈላጊ ነው ። በቀይ ሽብር መስዋዕትነት የከፈሉ የሃገሪቱ ምርጥ ልጆች ታሪክ በሰፊው ሊነገር ይገባል። በትምህርት ቤትም ውስጥ እንዲማሩት ቢደረግ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ እንዳይደረግ ይረዳል ። መስዋዕትነት የከፈሉ የጀግኖች ታሪክ ለሚቀጥለው ትውልድ መተላለፉ ለትውልድ ብዙ ጥቅም አለው ።
መስዋዕትነት ለአንድ ሃገር ለሁለት ቁም ነገሮች አስፈላጊ ነው ። በመጀመሪያ የሚቀጥለው ትውልድ በሠሩት ቁም ነገር ፣ ሕይወታቸውን ለሃገራቸው በመክፈላቸው ሲኮራባቸው በሌላ በኩል ደግሞ ተከታዩ ትውልድ የተሰውትን ታሪክ እየሰማ ፣ ምሳሌነታቸውን እየወሰደ እንደ እነርሱ ለመሆን ጥረት ስለሚያደርግም ነው። ስለዚህም ዜጎች በሃገራቸው ውስጥ የተነሱትን ታላላቅ ሰዎች፣ መስዋዕትነትን የከፈሉትን በሙሉ ታሪካቸውን ሊያውቁት ይገባል ። ሃገራቸው በምን ዓይነት ሁኔታና ታሪክ እዚህ እንደደረሰች የማያውቅ ግለሰብ ስለ ሃገሩ ያለው ግንዛቤ ያነሰ ይሆናል ። ለጥፋትም ይነሳል ። አስተሳሰቡም አድማስን አያቋርጥም ።

ስለ የሚቀጥለው ትውልድ የሚያስቡ በሰላም ይክረሙ !!!
ጀርመን፣ ግንቦት 2009።

1 Comment

Comments are closed.

Share