ይድረስ ለወዳጄ….

ተፃፈ ለርዕዮት አለሙ

ይድረስ ለወዳጄ
ሰዉ እምነቱን ሲኖር ፈተና ሚሆነዉ
ሌላ ማንም አይደል የራሱ ህሊና ነዉ
በሚል እሾህ ሀሳብ ልቤን እያቆሰልኩ
ዉስጤን እያደማሁ
ብቻዬን መስዬ ካንቺ ጋር ነዉ ያለሁ፡፡
አጓጉል መካሪ ‘ይቅርብሽ’ ብሎ ሲል
ፍርሃት ሲገምድብሽ
ራስን ከመዉደድ ስሜት እዉነት ይሉት ቢሒል
ገዝፎ ሲያይልብሽ
ምን ነበር ሙግትሽ?
ምን ነበር ጭንቀትሽ?
ምን ነበር ፀሎትሽ?
ምን ነበር ምኞትሽ?
ካገዘፍሻት እምነት ሀሰተኛዉ በልጣ
ከላይ አንግሰዋት
የያዝሻትን እዉነት ከጉያሽ ፈልቅቀዉ
በ ‘ርቃን’ ሰዉተዋት
ለስምሽ ቅጥያ ሌላ ስም ሰጥተዉሽ
ገሀድ አደባባይ ምና ምን . . . ብለዉሽ
ከሞት አዛምደዉሽ
ካሻቸዉ ድረዉሽ
እጣ ሲጥሉብሽ
ከዝምታሽ መሀል ሸሽገሽ የያዝሽዉ
ግን ገፅሽ ላይ ያለ
ድፍረትሽን የሚሰብክ ለኔ የሚነበበኝ
ስንት ነገር አለ፡፡
ከተሰጠሽ ጥቂት ካለሽ ላይ ቀንሰሽ
ዝም ካልነዉ ሁሉ
ከፈራነዉ ሁሉ ጩኸት ያስመረጠሸ
ምንድን እንሆነ ብለካ ብመትር
አግራሞት አሰረኝ
የኖርሽዉ ገዝፎብኝ የኔ ሞት ፍርሀት
አንገት አሰበረኝ፡፡
ደግሞ . . . ይህንን አዉቃለሁ
መንገስም በድንገት በቀላል አይገኝ
ወዳጄ ፅናትሽ . . .
አንቺን ብቻ አስታዋሽ፣ ስምሽን ደጋሚ
ተብሰልሳይ አረገኝ
ከህመም ከስቃይ ከሞት ሁሉ ኋላ
ባመንሽዉ ትንሳኤ ፍርሀትን ገለሽ
ኖርን ካልነዉ በላይ ስምሽን አኑረሽ
አንቺ ግን አሁንም በነፃነት አለሽ
አየሽ . . .
ሰዉ እምነቱን ሲኖር ፈተና ሚሆነዉ
ሌላ ማንም አይደል የራሱ ህሊና ነዉ
እናምልሽ ይኸዉ . . .
ዝም ያልኩኝ ብመስልም ሰቀቀን ላይ ቆሜ
‘እንዴት? ‘ ይሉን ግዙፍ ዉስሜ ተሸክሜ
እኔ ነኝ የታሰርኩ አንቺማ አንድ’ዜ
የሻሽን መርጠሻል
ካመንሽዉ ጥግ ላይ በግዝፈት ቆመሻል
እዉነት እልሻለሁ አንቺ ነፃ ሰዉ ነሽ
ይብላኝ ማለት ለኔ ቅዥት ላነገበኝ
ፍርሀት’ና እዉነት መካከል ወዝቶ ለሚያንገረግበኝ
አዎን ይብላኝ ለኔ!
አንቺ ግን ነፃ ነሽ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላማዊ ወይስ የትጥቅ ትግል ወይስ ማንፈራጠጥ - ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

ለጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ
ከ ገጣሚ ትዕግስት ማሞ

2 Comments

Comments are closed.

Share