በሀሮማያ የተካሔደውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰዎች ታሰሩ

(BBN News) ትላንትና በሀሮማያ ከተማ የተካሔደውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰዎች መታሰራቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡ በትላንትናው ዕለት በከተማዋ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ህዝባዊ ተቃውሞ መካሔዱ ይታወቃል፡፡ በትላንቱ ዘገባችን ላይ እንደጠቀስነው፣ የከተማዋ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የህወሓትን አስተዳደር ያወገዘ ሲሆን፣ ከተማዋም ውጥረት ነግሶባታል፡፡ ዛሬ የወጡ መረጃዎች ደግሞ፣ ለምን ሰልፍ ወጣችሁ ተብለው የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ለእስር የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር አይታወቅም፡፡ ሆኖም ከተለያዩ ቦታዎች ተሰብስበው ፖሊስ ጣብያ ያደሩ ሰዎች መኖራቸውን ግን ምንጮቹ ያረጋግጣሉ፡፡ ከታሰሩት ሰዎች ሰዎች መካከል እስከ አስር ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ አስይዘው ከእስር ቤት እንዲወጡ የተነገራቸው ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ስርዓቱ ሰዎችን እያሰረ ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል ግን የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ ከፍሎ የወጣ ሰው አለመኖሩን ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በተለያዩ የሀሮማያ ክፍሎች የታጠቁ ፖሊሶች ሲዘዋወሩ እንደነበር እማኞች ገልጸዋል፡፡ ዛሬም በድጋሚ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል ግምት በከተማዋ የተበተኑት ፖሊሶች፣ በተሰማሩበት አካባቢ ቅኝት ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት እማኞች፣ ዛሬ ከተማዋ በተወሰነ ደረጃ ውጥረት ውስጥ እንደነበረችም እማኞቹ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው አገዛዝ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሳበት ተቃውሞ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Teddy Afro: "Hager"

2 Comments

  1. now , the government is expert in crowd control .

    THE GOVERNMENT HAS NOW LEARNED HOW TO MANAGE , CONTROL AND DIFFUSE VIOLENCE .

    GREAT LESSON FOR SECURITY FORCES .

  2. ተቃውሞን በሠለጠነ መንገድ ማሰማትም ሆነ መስማት ይለመድ!

    4 October 2017
    በጋዜጣዉ ሪፓርተር

    በሕዝብና በመንግሥት መካከል አለመግባባት የሚፈጠረው፣ ሕዝብ መብቱ እንዲከበርለት ሲጠይቅ መንግሥት ደግሞ ሲከለክል ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ግን የመንግሥት ቀጣሪ ሕዝብ ስለሆነ፣ ሁሌም የሕዝብን ፍላጎት ለመፈጸም ተፍ ተፍ ማለት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕዝብ ሲጠይቅ መንግሥት አያዳምጥም፡፡ የሕዝብ ቅሬታ ወደ ብሶት ተቀይሮ እስኪገነፍል ድረስ መንግሥት ንቅንቅ አይልም፡፡ ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶች ግድባቸውን ጥሰው ለዕልቂትና ለውድመት እስኪዳርጉ ድረስ በርካታ ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ በሕግ ዕውቅና ያገኙ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ የንግግር፣ የመሠለፍና የመሳሰሉት መብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበቡና እየጠፉ ችግር ሲፈጠር ቆይቷል፡፡ በሕግ ዕውቅና ያገኙ መብቶች ለምን ይከለከላሉ? ዜጎች የመሰላቸውን ሐሳብ በነፃነት ቢያራምዱ ማን ይጎዳል? በሠለጠነ መንገድ ተቃውሞን ማሰማትም ሆነ መስማት ባህል መሆን ሲገባው፣ ለአገር የማይጠቅሙና የሚያሳምሙ ጉዳቶች አጋጥመዋል፡፡

    ሰሞኑን የኢሬቻ በዓል ሲከበር በሥፍራው የተገኙ ታዳሚዎች ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ውለው፣ በዓሉ በሰላም ተጠናቆ ወደ መጡበት በሰላም ተመልሰዋል፡፡ በወቅቱ ቅሬታቸውን፣ ብሶታቸውንና ቁጣቸውን ሲያሰሙ የነበሩት ወገኖች አንዳችም ዓይነት ኮሽታ ሳይሰማ በሰላም መመለሳቸው እንደ አገር ዕፎይታ የሰጠ ነበር፡፡ የክብረ በዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ሲሰማም በብዙዎች ዘንድ የነበረው የሥጋት ደመና ተገፏል፡፡ የዓምናውን አሳዛኝ ክስተት ለሚያስታውሱ ሁሉ ይህ ግልጽ ነው፡፡ አገር ሰላምና መረጋጋት ኖሯት ወደ ዕድገትና ብልፅግና የምታመራው ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ በነፃነት መንቀሳቀስ ሲቻል ነው፡፡ ዜጎች ነፃነታቸው ሲገደብ፣ በሕግ የተረጋገጡላቸው መብቶቻቸው ሲጣሱና ተቃውሞ የሚያሰሙበት መድረክ ሲያጡ ችግር ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ተቃውሞ ያላቸው ወገኖች በነፃነት ፍላጎታቸውን ሲገልጹ በሕይወትም ላይ ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አይደርስም፡፡ በዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ላይ የታየውም ይህ ነው፡፡ ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም፡፡

    በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ የተለያዩ ተቋማት የአዳራሽ ስብሰባ ማካሄድ ሲሳናቸው፣ የአደባባይ ሠልፍ ሲነፈጉ፣ በሰበብ አስባቡ ተቃውሞን የማቅረቢያ መንገድ እየጠፋ ስለዴሞክራሲ መነጋገር ይቻላል ወይ? መንግሥት ሁልጊዜ ከድጋፍ በስተቀር ተቃውሞን የሚከለክለው ለምን ይሆን? ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ የሚሰማ በመጥፋቱ ብቻ በተፈጠረ ቁጣ አገር ስትነድና የዜጎች ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ሲጠፋ ማን ተጠቀመ? ይልቁንም ሕዝብ የታመቀ ቅሬታውን እንዲተነፍስ በማድረግ መረጋጋት መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ብሶቱን ሲተነፍስ ምንም አይፈጠርም፡፡ በኢሬቻ በዓል ላይ የታየውም ይኼው ነው፡፡ ነገር ግን ተቃውሞን ማስተንፈሻ በማሳጣትና በግብታዊነት እንዲገነፍል በማድረግ የሚገኘው ጥፋት ብቻ ነው፡፡ የሕዝብ ዕልቂትና የንብረት ውድመት፡፡ ይህንንም ባለፈው ዓመት ከመጠን በላይ ዓይተነዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ችግሮች ለዚህ አባባል ሁነኛ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

    ፓርላማው የሕዝብ ብሶትና ብስጭት በተወካዮች አማካይነት የማይስተጋባበት ከሆነ፣ የአዳራሽ ሕዝባዊ ስብሰባዎችም ሆኑ የአደባባይ የተቃውሞ ሠልፎች የማይፈቀዱ ከሆነ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላትና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተለዋጭ መድረክ ይሆናሉ፡፡ እየታየ ያለውም ይኼ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች ሥርዓት ባለው መንገድ ተግባራዊ ቢደረጉ ግን ብሶቶች ይተነፍሳሉ፡፡ ሥልጡን የሐሳብ ልውውጦች እንዲኖሩ ጥርጊያው ይመቻቻል፡፡ ዴሞክራሲ የሚሰፍነው በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር ሥርዓት ማቆም ሲቻል ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ሒደቱ መስመር መያዝ አለበት፡፡ የፖለቲካ ተቃውሞዎች በበዓላትና በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ውስጥ ከሚሰሙ ይልቅ፣ መደበኛዎቹ መድረኮች ክፍት ይሁኑ፡፡ ይህንን እውነታ ችላ ማለትና ሁሉንም ነገር መዘጋጋት ራስ ላይ እንደ መተኮስ ይቆጠራል፡፡ በአገሪቱ ሁሉም ዜጎች የመሰላቸውን አመለካከት ይዘው፣ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይንቀሳቀሱ ዘንድ የሰሞኑ እውነታ ብዙ ይናገራል፡፡ ‘ከማየት በላይ ማመን የለም’ እንዲሉ፡፡

    ሁልጊዜ እንደምንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በጣም ጨዋ፣ ትሁት፣ አስተዋይ፣ ሰላም ወዳድና እርስ በርሱ የሚከባበር ነው፡፡ ይህ ድንቅ ሕዝብ ያለውን ተካፍሎ ክፉ ጊዜን በጋራ ማሳለፍ የሚችል ከመሆኑም በላይ፣ ጥሩ መሪ ካገኘ ደግሞ ተዓምር መሥራት አይሳነውም፡፡ ይህንን ኩሩና ተምሳሌታዊ ሕዝብ መብቱን በማክበር በአገሩ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ተሳትፎ እንዲኖረው ማድረግ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ነው፡፡ ‘የመሪ እንጂ የተመሪ መጥፎ የለውም’ እንደሚባለው፣ ይህንን ሕዝብ በአግባቡ አለመምራት ማስጠየቅ አለበት፡፡ በመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ በፍትሕ መዛባትና በሙስና ብቻ የሚሳበበው የአመራር ጉድለት በፍጥነት ታርሞ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በብሔራዊ መግባባት መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ትክክለኛው በሽታ ሲታወቅ ብቻ ነው፡፡ ‘በሽታውን ያወቀ መድኃኒት አያጣም’ እንዲሉ፣ ያልታወቀ በሽታን ለማከም መሞከር ከኪሳራ በስተቀር ትርፍ የለውም፡፡ መንግሥት ሕዝብን በአግባቡ ማዳመጥ ሲጀምርና ፍላጎቱን ሲረዳ መፍትሔው በጣም ቅርብ ነው፡፡ ከኮንሰርት ክልከላ እስከ ተቃውሞ አፈና የሚገባው ግን ከዚህ በተቃራኒ ሲኬድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ይብቃ፡፡

    ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት የብዙኃን አገር ናት፡፡ ዜጎች ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው የመብት ጥያቄ ሲያቀርቡ ተቀብሎ የማስተናገድ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት በትክክል የሕዝብ አገልጋይ ነኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ማዳመጥ ያለበት ሕዝብን ብቻ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር እየተናቆሩ አገር ማስተዳደር አይቻልም፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት ሕዝብ ነውና፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ አገር እስከሚያስተዳድረው መንግሥት ድረስ ለሕግ መገዛት ተገቢ ነው፡፡ መብቱን የሚጠይቅ ዜጋ ግዴታውን የመወጣት ኃላፊነት አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ ደግሞ በሕግ የታወቁ መብቶች ይከበራሉ፡፡ እነዚህን መብቶች የሚጠይቁ ዜጎችም በሕጉ መሠረት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ በዚህ መሠረት አገር ስትራመድ ድንጋይ መወርወር ተረት ይሆናል፡፡ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ በሠለጠነ መንገድ ይነጋገራል፡፡ የዜጎች ሕይወትም በሰበብ በአስባቡ እንደ ቅጠል አይበጠሰም፡፡ ነፃነቱን የሚያውቅ ዜጋ መብቱን ሲጠይቅ መንግሥት ወዶ ሳይሆን ተገዶ ያከብራል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው በሠለጠነ መንገድ ተቃውሞ ማሰማትም መስማትም ይለመድ የምንለው!

Comments are closed.

Share