ከነቢዩ ሲራክ
የማለዳ ወግ … በጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋየ ገብረ አብ ላይ የቀረበው ክስ መረጃ አንድ እውነታ !
ከሶስት ቀናት በፊት ቀትር ላይ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሰኝ ። አንድ እዚህ ጅዳ የሚገኝ ወዳጀ ነበር ። ይህ ወዳጀ በስደተኛ ዜጎቻችንና በኮንትራት ሰራተኞች ላይ የከፋ ግፍ ሲፈጸም ፣ ዜጎች በራሳችን መንግስት ተወካዮች በጅዳና ሪያድ መጠለያዎች ፍዳቸውን ሲያዩ ፣ ኢትዮጵያውያን ሲያመን ህመሙ ዘልቆ ሲያመው እና የአረቡ መገናኛ ብዙሃን ስማችን አጉድፈው ክብራችን ቀንሰው መረጃ ሲያሰራጩ በስጨት ብለው ከሚደውሉልኝ ወዳጆቸ መካከል ብርቱው ወዳጀ ነው። ብርቱው ወዳጀ የኢትዮጵያ ነገር አይሆንለትም …
ያኔ የማይረባ የባድመ ድንበር ጦርነት ተቆስቁሶ የሁለት ሃገራት አንድ ህዝቦችን ታዳጊ ወጣቶች ነፍስ ሲቀጠፍ አንዳንዶች ኢትዮጵያን ተንኳሽ እያደረጉ በሳውዲ ጋዜጦች ጨለምተኛ ፕሮፖንጋዳቸውን በመንዛት የተጠመዱ እኩዮች ብቅ ብቅ ብለው ነበር ። በዚህ ጭንቅ ሰአት በጣም ጥቂት የጅዳ ነዋሪዎች ለፕሮፓጋንዳው መልስ ይሰጡ የነበረ ሲሆን ይህ ወዳጀ ደግሞ ቀዳሚ መልስ ሰጭ እንደነበር አውቃለሁ። እናም ለዚህ መሰል ሃገር ፍቅሩ ክብር አለኝ !
ይህ ብርቱ ወዳጀ ከደወለልኝ ሰንበትበት ቢልም ዛሬ ቁም ነገር ይዞ መደወሉን አላጣሁትም !
” የት ጥፋህ ባክህ! ” ብሎ መልሴን ሳይጠብቅ ወደ ጉዳዩ ዘው ብሎ ገባ … ልጆቸን ከትምህርት ቤት ለመመለስ ነበርኩና ጎረምሶች እስኪመጡ አናት ከሚሰነጥቀው የቀትር ጸሃይ በመኪናየ ውስጥ ተከልየ ብርቱ ወዳጀን ማድመጤን ቀጥያለሁ … ወዳጀ በጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋየ ገብረ አብ ዙሪያ የተጻፈውን ጽሁፍና የቀረበበትን መረጃ ከላይ እስከታች አንብቦ እንደጨረሰ ነበርና የደወለልኝ መሰሪ ባለው የተስፋየ ኢትዮጵያን የማድማት እኩይ ስራ መበሳጨቱን አውግቶኝ ሊጨርስ ሲቃረብ …”ወረቀት ካለህ ይህን ስልክ ጻፍና አጣራው? ” ሲል አንድ ቁጥር ሰጠኝ … “ስሙ ኢብራሂም ነው! ይህ ሰው በተስፋየ የመጽሃፍ ስርጭት መረብ የተስፋየን መጽሃፍ የሚያከፋፍል ነወና አጣራው! ” ብሎ የምደርስበትን እንድነግረው ተማጽኖኝ ስልኩን ዘጋን …
ወዲያው ስልኩን እንደዘጋሁ ወደ ተባለው አካፋፋይ ወንድም በመደወል ማጣራቴን ያዝኩ … ወዳጀ የሰጠኝ ስም ትክክል አለመሆኑን እና አማን ኢብራሂም እንደሚባል በመጀመሪያው ዙር ማጣራት ደረስኩበት! … የተስፋየን መጽሃፍ ለመግዛት ጠይቄም አፈላልጎ እንደሚያመጣልኝ ቃል ተገብቶልኛል …
በተስፋየ ገብረአብ ዙሪያ በዳኛ ወልደ ሚካኤል መሸሻ የተጻፈው በድረ ገጾች በተለጠፈ ቅጽፈት ባየውም እንደቀደመው እሰጣ እገባ ጽሁፍ መጻፉን ገመትኩ፣ ተስፋየ ኬንያ ላይ ይጠቀምበት የነበረ በኤርትራ መንግስት የተሰጠው መታወቂያ ጉዳይም ቢሆን ለወግ ማጣፈጫ የተቀነባበረ እንዳይሆን በጥርጣሬ መመልከቴ አልቀረም ። እናም መጣጥፉን ከነመረጃውን መመልከት ግድ አለኝ …
ከተስፋየ ጋር በጉርብትና ይኖር ነበር ከተባለው ወጣት አክቲቪስት አለማየሁ መሰለ መረጃው ተገኘ ፣ ዳኛ ወልደ ሚካኤል መሸሻ ይርዘም እንጅ በግሩም የመረጃ ግብአትን እያስዋቡ የአለማየሁን ውሃ የሚያነሳ ሰነድ አሳዩን ፣ አስነበቡን ! የሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል ለሚል መጣጥፉ ረጅም ቢሆንም ወግ በወግ የተሰናዳ በመሆኑ አይሰለችም ። በጉጉት ፣ በአግራሞት እና በአድናቆት አነበብኩት! ከላይ ከጅዳው ብርቱ ወዳጀ የተሰጠኝም ስምም የተስፋየን መጽሃፍ ጅዳ ውስጥ የማከፋፈል ስራውን የሚያሂዱ ግለሰብ መሆናቸውን የሚጠቅሰውን ሰነድ ኮፒ ገጽ 31 ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል! እንዴት ነው ነገሩ ? አልኩ ! ! !
ወዳጀ መነሻ ሆኖኝ በግል ዳስሸ ያገኘሁት ተጨባጭ እውነታ እና በቀረበው መጣጥፍ የቀረበው ሰነድ እውነታ በውስጤ ሌላ ስሜት መፍጠር ያዘ ፣ ቀድሞውኑ ስል ተስፋየ ገብረአብ ተጽፎ ሳይ “በተስፋየም በተቃዋሚዎቹም የቀጠለው ስም የማጠልሸት እስጣ ገባ አለያም የተስፋየ ገብረአብ ቀጣይ መጽሃፉን ለማሻሻጥ የተደረገ ረቂቅ የገበያ ፍለጋ ዘመቻ ነው !” የሚለውን ጥርጣሬ ነበረኝ! ከሰአታት በፊት ያነጋገርኩት አከፋፋይ አና ከመጣጥፉ ጋር የቀረበው ሰነድ ግን አጉል ጥርጣሬየን ብንን አድርጎ አጠፋብኝ … !
በአለማየሁ በኩል ከጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋየ ገብረአብ ጉያ ተገኙ ከተባሉትን ሰነዶች መካከል ማረጋገጥ የቻልኩት ሰነድ ብዙ አርቆ አሳሰበኝ … በዚህ ዙሪያ ከራሴ ጋር ስሞግት ግራ የተጋባችው ባለቤቴ ቁርጠት የሚያጣድፋትን እርጥብ ልጃችን ማህሌትን ከደረቷ ላይ ለጥፋ ከምታባብልበት ቀረብ አለችና ” አብረን ማንበብ ጀመረን ብቻህን ጨረስከው አይደል? ” ብላ ስትጠይቀኝ የሆነውን ሁሉ አጫወትኳት … “ምን ሆነሃል እኔም ደስ አላለኝም ፣ ይህ ነገር እውነት ሳይሆን አይቀርም ! የቡርቃ ዝምታን አንብበው እስኪ ?” በማለት ከመጽሃፍ መደርደሪያው የተወሸቀውን የተስፋየ ገብረአብ የቡርቃ ዝምታ መጽሃፍ የት አንደገዛችው እና በጅዳና አካባቢው በሰፊው የተከፋፈለበት መንገድ አወጋችኝ! ኢትዮጵያን ትወዳለችና የመረጃውን እውነታ የቀረበው ሰነድ ተጨባጭነት አጉልቶ እንዳሳሰባት አጫዎተችኝ … ወደዚህ አለም ከመጣች ገና አስራ አምስት ቀን የደፈነቸው ልጃችን ማህሌት ይህን ሶስት ቀን ንጭንጭ ብላ ታለቅሳለች! ከትናነት በስቲያ ሃኪሟ ዘንድ ሄጀ “አዲስ ለተወለዱ ህጻናት ይህ መሰል ቁርጠት ከወተት ጋር የሚመጣ የተለመደ ነው!” ብሎ ምክር ቢጤ ስለሰጠኝ ብዙ አላሳሰበኝም አልልም ! ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በአለማየሁ ተገኝቶ በዳኛ ወልደ ሚካኤል የቀረበው መረጃና ያጋጠመኝ ግጥምጥም ጉዳይ ሳይሆን ቢቀር አሳስቦኛል! እናም ብርቱ ወዳጀን ያመመው ኢትዮጵያዊ ህመም አመመኝ ! ግን ለምን ተስፋየ ? አልኩ … ትንሿ እውነተኛ የመረጃ ፍንጭ ጠልቃ ብታደማኝ…
ብዙም ሳልቆይ አንዳች ነገር ሰውነቴን ወረረው ! በግላጭ አግኝቸው በተጨባጭ ሳልይዘው ያለፍኩት መረጃ ትዝ አለኝና ከአልጋየ ተስፈንጥሬ በመነሳት ወደ ተስፋየ ገብረአብ መጽሃፍ አከፋፋይ ስልክ ደወልኩ … ስልኩ ተነሳ !
“ጤና ይስጥልኝ ? ”
“ጤና ይስጥልኝ ! ”
“እንደምን አደሩ !?” ቀጠልኩ
“አልሃምዲላህ ! ” መለሰ
ከዚህ ቀደም ያገኘሁት ወንድም ነው። የማወራው ከምፈልገው ሰው ጋር መሆኑን ለማረጋገጥ መስመር ውስጥ ያገኘሁትን ወንድም “አቶ አማን ነወት? “በማለት ጠየቅኩት ፣ አማን መሆኑን ካረጋገጠልኝ በኋላ ማንነቴን ሲጠየቀኝ ።… ከሁለት ቀን በፊት የተስፋየ ገብረአብን መጽሃፍ አፈልጌ ደውየ እንደነበር ስገልጽለት አስታወሰኝ …በመቀጠልም . ..
” አዎ መጽሃፍ የሚሸጠውን ሰውየውን ፈልጌው ነበር አላገኘሁቱም ፣ የትኛውን መጽሃፍ ነው የምትፈልገው ? የ . … የፈልግከው ? “ሲል ጠየቀኝ ፣
አዲሱ መጽሃፍ ካለ መልካም ከሌለ ያለውን ባገኝ ቅር እንደማይልሰኝ ገለጽኩለት
” ያለው አይመስለኝም ድሮ ይህ ሰውየ ያመጣው የነበረው የጋዜጠኛው ማስታወሻ የሚል ነው ። ” ሲለኝ አስከተልኩና “እሱስ አለህ ? ” ስል ጠየቅኩት…
“እሱ ካለ እጠይቀዋለሁ ! ሰውየውን አላገኘሁትም ይሸጠው የነበረው . ..ስንት ነው የፈለግከው ? ” በማለት7በድጋሜ ሲጠይቀኝ መግዛት የምፈልገውን መጽሃፍ ብዛት ደርዘን አድርሸ መለስኩለት አቶ አማን መለሰ ” አገኘኋለሁ እና ቢጠፋ ቢጠፋ እሁድ አገኘዋለሁ ! እነግርሃለሁ ! ” አለኝ
አቶ አማንን በማስከተል የአዲሱን መጽሃፍ መምጣት መረጃ አና ስለ አከፋፋዩ ጠየቅኩት
” I don’t know ከእርሱ አዲስ ስለመኖሩ አላውቅም ፣ የበፊቱን ከእርሱ አግኝቸው ነበር ከዚህ በፊት . … አንተ እንግዳ ነህ ለጅዳ ?” በማለት አከታትሎ ጠያቂውን ያጠየቀ ጥያቄ ከወደ አቶ አማን ቀረበልኝ ፣ ለሃገሩ ባዳ ነኝ የሚል ነጭ ውሸት ዋሸሁት…
“የት ነው ያለህው ?”ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ ” ማነው ይህን ስልክ የሰጠህ ? ” የሚለው ጥያቄ ከወደ አቶ አማን ተከታትሎ ቢቀርብልኝም ለስራ ጉዳይ ጅዳ ብመጣም የምኖረው ራቅ ወዳለች አንዲት የሳውዲ የጠረፍ ከተማ መሆኑን በማስረዳት እዚያ ላሉ ኢትዮጵያውያን መጽሃፉን ለማከፋፈል እንደምፈልግ ገለጽኩለት ፣በማከልም የእርሱን አድራሻ ያገኘሁት አውሮፓ ከሚኖር ወዳጀ መሆኑን አስረዳሁት ። ከዚያም አቶ አማን ጥያቄዎቹን በመግታት መጽሃፉን ከአከፋፋይ ካለው ሊጥይቅልኝ ቃል ገብቶልኝ ስልኩን ዘግተን ተለያየን …
አዎ ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋየ ገብረ አብ ተወልዶ ያደገባትን ፣ ለወግ ማዕረግ አብቅታ ያስተማረችውን ሃገር የኢትዮጵያን ህዝብ የሚጎዳ ስራ መስራቱን ለመቀበል ከባጀና ከከረመ አመታት ተቆጥረዋል። ተስፋየ እንደ ደራሲና ጋዜጠኛም ባይሆን እንደ ሰው ተፈጥሯዊ ሃሳብ የመግለጽ የማይገሰስ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን አምናለሁ። ዳሩ ግን ተስፋየ እንደተባለው እስከ ጥግ በሚጠቀመው መብቱ እንደ ዘርን ከዘር የሚያጋጭ መረጃን ማስተላለፉን አልቀበለውም። ተስፋየ ገብረአብ የኢህአዴግ ባለስልጣን እያለ ጀምሮ የጻፈውን ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ላስተዋለው ያሳዝናል። ተስፋየ ገብረ አብ በኢህአዴግ መንግስት ታማኝ ሆኖ እና በወሳኝ የሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ከፍተኛ ስልጣን ተቀምጦ የሚጎዳንን ፣ የሚለያየንን በቡርቃ ዝምታን መጽሃፉ ጀባ ብሎናል ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎችን በልዩነት በደጋፊና ተቃዋሞ ዙሪያ ያዘባራው ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋየ ገብረአብ በቡርቃ ዝምታ የተሰቀዘው የብዙዎች ልብ በቀጣይ ስራዎቹ ለማባበል አልገደደውም ።
እርግጥ ነው ተስፋየ በልዩ የአጻጻፍ ክህሎቱና አልፎ አልፎ በሚያነሳቸው “ጮማ ” የፓለቲካ ወጎቹ እና በቀጣይ ባቀረባቸው ወጥ ልብ አንጠልጣይ የድርሰት ስራዎቹ የተቃወሙ እና የሸሹት መልሶ ምርኮኛ ማድረግን የተካነ የጥበብ ሰው መሆኑን ላፍታ እንኳ መካድ አይቻልም። ዛሬ ሌላ ቀን ቢሆንም የተስፋየ የጥበብ ትጋት እና እየጣለ የሚያነሳን ያልረጋው የሃገራችን ፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስብስብ ባህሪ ጋርዶብን የተስፋየ ገብረ አብ ድጋፍ ሰጭ የነበርን የተጎጅዋ ሃገር ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም !
እርግጥ ነው ተስፋየ ገብረአብ ከተባለው ረቂቅ ሴራ በተጓዳኝ ጠቃሚ ጠቃሚ የሚባሉ መረጃዎችን ይፋ በማድረጉ ረገድ የሰራው መልካም ስራ የሚዘነጋ አይደለም። በስልጣን በቆየባት ሃገር ለተሰራው ሁሉ እሱም ከተጠያቂነት ባያመልጥም በስልጣን ዘመኑ በሃገሬ ምድር በአደባባይ እና በስውር ተሰርቶ ያየውን ባያጠግበንም ብዙ አካፍሎናል ። እማኝነቱን በሰጠባቸው የአንድ ቡድን የበላይነት የነገሰበት ሃገር ፣ የመብት ገፈፋና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ያቀበልን መረጃዎች የስነጽሁፍ ጥበቡን ጨምሮ ብዙ ትምህርት ማግኘታችን የሚካድና የሚዘነጋ አይደለም ።በተስፋየ ዙሪያ ዛሬ ሌላ ቀን ያባተ ይመስላል።
ዛሬ ሌላ ቀን ሆነና በወጣቱ ሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ በአለማየሁ ትጋት በመረጃ ተደግፎ የተጋለጠው የተስፋየ የከራረመ ሴራ በዳኛ ወልደ ሚካኤል መሸሻ ጥናታዊ ዘገባ በዝርዝር ይፋ ሆኗል። ይህንን መረጃ እያየሁም በተስፋየ ክህደት ዙሪያ እየተጠራጠርኩ ለማንበቤ ከተስፋየ አንደበት የሰማኋቸው የጸና ኢትዮጵያዊነት የአቋም መግለጫዎቹ እንደሆኑ ውስጤ አሁንም ያምናል ! አንዲህ ሆኖም የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ስየ አብርሃን ጨምሮ በአካባቢያቸው ያሉትን ሃገር ወዳድ ተቃዋሚዎች እና አዛውንቱ የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚድንት ዶ/ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ሳይቀሩ በተስፋየ ዘራፍ ብዕር ተወርፈዋል። ይህን ዘለፋውን ደጋግሜ ተምልክቸ ልቤ አልቀበል እያለው ብቸገርም ከተራ ጥላቻ የዘለለ የለመድነው የመቦጫጨቅ ፖለቲካ ነው በማለት ችላ እለው ነበር ። ዛሬ ግን ያ ሁሉ በትር ያዘነበባቸውን ወገኖች የማጥቃት አለማ አውጥቸ አውርጀ እመዝነው ዘንድ ግድ ይለኛል! ዛሬ የቀረበልን ጭብጥ ሰነድ ቢያንስ ተስፋየን እና ይጠላቸው የነበሩትን ሁሉ ሳይሆን ይወዳቸው የነበሩትንም ፖለቲከኞቻችን መላለሰሸ እገመግማቸው ዘንድ ተገድጃለሁ! ዛሬ ቢያንስ በግል በተስፋየ እጅ የተጻፉ ሰነዶች ጋር ለቀረበውን ቅንጣቢ መረጃ ማረጋገጫ ካጋገኘሁ ወዲህ ቢያንስ በተስፋየ ላይ ስለሚሰነዘረው ውንጀላ የጥርጣሬ ግርዶሹ ተገፎልኛል !
የማለዳ ወጌን ለመደምደም ዳኛ ወልደ ሚካኤል መሸሻ በቀረበው 44 ገጽ ጥናታዊ ጽሁፍ በገጽ 31 ላይ እዚህ ጅዳ በአከፋፋይት የተጠቀሱትን ወንድም ካነጋገርኩ በኋላ በሰነዱ ጎን የሰፈረው መግለጫ አስታወስኩ … አንዲህ ይላል “…ከዚህ በላይ በሻጭነት የተመለከቱትን ምናልባትም በየአገራቱ ከምትገኙ ኢትዮጵያዊያን ቢያንስ አንዳችሁ አንዱን ታውቁ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። እናም፣ ከእንግዲህ ልብ ልንል ይገባል። ባለማወቃችን፣ ባለማስተዋላችን ተታልለናል። ካወቅን በኋላ ደግሞ እንነቃለን። በቃህ! ወደዚያ! እንላለን። ኢትዮጵያዊነት ኩራት መሆኑን እንነግራቸዋለን ማለት ነው!” ይላል!እርግጥ ነው ከተለቀቀው መረጃ ውስጥ የተጠቀሰውን አንድ መረጃ መረጋገጥ በመቻሌ እኔም በመልካም ጥበብ ተደቁሶ የተቀመመውን መርዝ ላለመጋት “በቃ!” ብያለሁ ! አዎ ! አትዮጵያዊነት ከጥበብ ሁሉ የላቀ ጥበብና ኩራት መሆኑን እነግራቸዋለሁ !
በቃ ይህን ነው የምለው . . . ኢትዮጵያ ለዘልአለም ትኑር !
ነቢዩ ሲራክ