October 4, 2013
25 mins read

ግልጽ ደብዳቤ ለብፁዓን ወቅዱሳን አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ማትያስ

ሚያዚያ 18 ቀን 2005 ዓ/ም

ግልጽ ደብዳቤ

ለብፁዓን ወቅዱሳን አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ማትያስ፤

ግልባጭ፤
– ለቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ፤ ለእግዚአብሔር፤
– ለእመቤታችን፤ ለቅድስት ማርያም፤
– ለሊቃነ መላእክት ለቅዱስ ሚካኤልና ለቅዱስ ገብርኤል፤
– ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን።

አቤቱታ፤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ለተጋረጡት ከባድ ችግሮች መፍትሔ አግኙልን!

“ዕርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።” ማቴ. ም5/9

ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች ሆይ!

በመጀመሪያ፤ ዝቅ ብዬ እጅ በመንሳት፤ መንፈሳዊ ሰላምታዬን በከፍተኛ አክብሮትና ትሕትና አቀርባለሁ።

በመቀጠልም፤ ምንም እንኳ ኢምንት፤ ተራ ምእመን ብሆንም፤ ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተጋርጠው ለሚገኙት ከባድ ችግሮች መፍትሔ ሊገኝ የሚችለው፤ በፍጡራን ደረጃ፤ ከሁሉም በላይ፤ ሁለታችሁ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች፤ በአምላክ በተጣለባችሁ ግዴታና ኃላፊነት፤ ተግባራችሁን ከናንተ በሚጠበቅ ብርታት ስትወጡ መሆኑን ስለማምን ይህንን ግልጽ ደብዳቤ፤ ለሚመለከታቸው ሁሉ ግልባጭ በማድረግ በታላቅ ትሕትና አቅርቤላችኋለሁ። መልሳችሁን በአክብሮት፤ በጥሞናና በጸሎት እጠብቃለሁ።

መከፋፈልና ዕርቀ-ሰላም አለመፈለግ፤

በቅድሚያ ላስታውሳችሁ የምፈልገው፤ ሁለታችሁም ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች በእግዚአብሔር ቸርነት፤ የጳጳስነት ማእረግ ያገኛችሁት፤ በአቡነ ተክለሃይማኖት ፕትርክና ዘመን፤ ጥር 5 ቀን 1971 ዓ/ም ነበር። ይኸው ደግሞ፤ በዚህ ዘመን በክብር ላይ ክብር ተጨምሮላችሁ ትገኛላችሁ። የዚህ ክብር መሠረታዊ ዓላማው፤ ለመንጋዎቻችሁ የእምነት ጥንካሬ፤ ደህንነት፤ ሰላም፤ አንድነትና ፍቅር ለማስገኘት ቢሆንም፤ እንደምታውቁት፤ በሃይማኖት ዶግማ ሳይሆን፤ በተከሰተው የሥልጣንና የጥቅም ሽኩቻና የማያባራ መናቆር ቤተ ክርስቲያናችን በአጠቃላይ በሶስት ጎራ ተከፋፍላ ትገኛለች። በአባቶች መከፋፈል ምክንያት፤ ምእመናን ሐገር ቤት በሚገኘው ሲኖዶስ፤ በስደት ባለው ሲኖዶስና ገለልተኛ በሆነው የተለያየ ወገን ተዘርተን እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በዚህ ምክንያት፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፤ በመጀመሪያው የቆሮንቶስ መልእክቱ በም.1/10-13 ያስጠነቀቀንን በመጣስ “እኔ የመርቆሬዎስ ነኝ። እኔ የማትያስ ነኝ” በማለቱ አባዜ ተዘፍቀን እንገኛለን። እንዲሁም፤ በፖለቲካ ጣልቃ-ገብነትና በሥልጣን ጥመኝነት ምክንያቶች፤ የዕርቀ- ሰላሙ ሒደትም ተኮላሽቶ ቀርቷል።

የቀኖና መፋለስ፤

አሁን በተከሰተው ሁኔታ፤ አንዱ ሌላውን ወገን በቀኖና አፍራሽነት ይከሳል። ውሱን ቢሆንም ባለኝ ግንዛቤ መሠረት፤ የቤተ

ክርስቲያን ቀኖና ዋናዎቹ መሠረቶች ፍትሕ ነገሥት፤ ቃለ አዋዲና፤ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ የወጣው የ1991 ዓ/ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን ናቸው።

በፍትሐ ነገሥቱ ከተደነገጉት አንቀጾች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ፤

ሀ) ፍ/ነ 78፤ “በኋላ የሚድን ከሆነ በሚያልፍ በሽታ ምክንያት ሹመትን ከመያዝ ሰው ሁሉ የሚከለከል አይደለም። ፍጹም ድኅነትን እስኪያገኝ ድረስ ልትጸናለት ይገባልና።” ስለዚህ፤ በጊዜው በነበሩት የሲኖዶስ አባላት ፊርማ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የተወገዱበት ውሳኔ ቀኖናዊ ነበር ሊባል አይችልም።

ለ) ፍ/ነ 180፤ “ሊቀ ጳጳሳት . . . ከተሾመና እኒህን መዓርጋት ከተቀበለ በኋላ አንዲት ዕለት ወይም አንዲት ሰዓትም ቢሆን ቤተ ክርስቲያንን ያላገለገለ ቀጥሎም የተሾመበትን አገር ጥሎ የሸሸ ቢኖር እሺ ብሎ ወደ ቦታው እስኪመለስ ድረስ የአገሩ ሰዎች ይማልዱት። አልመለስም ቢል ሊኖር ከሄደበት አገርና ከምእመናን ጉባኤ ይለይ።”

ሐ) ፍ/ነ 206፤ “ኤጲስ ቆጶሳት ከሀገረ ስብከታቸው ወደ ሌላ አገር ቢሄዱ ከስድስት ወር የበለጠ አይኑሩ። ችግር

ሳይገጥማቸው ሊቀ ጳጳሱም ሳይፈቅድላቸው ከዚህ የበለጠ ቢኖሩ ወይም ሀገረ ስብከታቸውን ትተው በሌላ አገር በዓለ ትንሣኤን ቢያከብሩ ከሹመታቸው ይሻሩ።”

በ1991 ዓ/ም ስለ ሲኖዶስ በተደነገገው ሕገ ቤተ ክርስቲያን በአንቀጽ 16፤ ቁጥር 1 (ሀ፣ ለ፤ ሐ) ፓትርያርኩን ከማዕረግ ሊወርድ የሚያስችሉት ምክንያቶች ሃይማኖትን ማፋለስ፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አለመጠበቅ፤ በደለኛ መሆንና ቃለ መሐላን አለመጠበቅ ይገኙበታል። አፈጻጸሙም ፍትሕ መንፈሳዊ በሚያዘው መሠረት መሆን እንዳለበት በዚሁ አንቀጽ፤ ቁጥር 5 ተገልጿል።

ስለዚህ፤ ቀኖናን በማፍረስ ረገድ በሁሉም በኩል ተጠያቂነት እንዳለ ግልጽ ነው።

ውግዘት፤

እንደሚታወቀው፤ በብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች መሀል በተከሰተው መከፋፈል ምክንያት፤ እርስ በርሳቸው ስለ ተወጋገዙ የውግዘቱ ስለባ ሆኖ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰ ያለው፤ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ ነው። ምክንያቱም በተወገዘ ካሕን የተባረክ ውጉዝ መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና የታወቀ ነው።ውግዘቱን በተመለከተ ተከስቶ የሚገኘውን የተዛባ ሁኔታ ለመገንዘብ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሰውን ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 338 መመልከት ያስፈልጋል፤

“ከተወገዘው ወይም ከተለየው ጋር የተነጋገረ ወይም ከነርሱ ጋር የጸለየ ከቤተ ክርስቲያን ይለይ።”

በቅርቡ፤ በዳላስ ከተማ፤ አሜሪካ፤ በተከናወነው የከሸፈው የዕርቀ-ሰላም ስብሰባ፤ አባቶች ሲነጋገሩና አብረው ሲጸልዩ በግልጽ ታይተው ሳለ፤ ውግዘቱ በሁለቱም ወገን ሳይነሳ መቅረቱ፤ እጅግ የሚያሳዝን ጉዳይ ሆኖ ቀርቷል። የውግዘቱን ቀምበር ከመንጋዎቻችሁ፤ ከ50 ሚሊዮን ምእመናን ላይ አንስታችሁ ዕርቀ-ሰላሙ ላይ ማተኮር የብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች ተግባር መሆን አይገባውም?

ለቤተ ክርስቲያን ስለሚያስፈልገው እርዳታ፤

እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ደብሮች፣ ገዳሞችና የአብነት ትምሕርት ቤቶች እንዳሉ የታወቀ ነው። ነገር ግን፤ በተከሰተው መከፋፈል ምክንያት፤ ምእመናን በቂ እርዳታ እያበረከትን አንገኝም። ለምሳሌ፤ በየዓመቱ፤ ውጭ ሐገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሐገራችን የሚያስተላልፉት ገንዘብ መጠን ከ$3 ቢሊዮን እንደማያንስ ተገልጿል። ከዚህ ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው እርዳታ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ራሱ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶችን ሊያሳስብ የሚገባ ነጥብ ነው።

ስብከትና ትምሕርት፤

በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከናወነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት የቤተ ክርስቲያናችን አማኞች ቁጥር እድገት ከሌሎች እምነት ተከታዮች አኃዝ ጋር ሲወዳደር ዝቅ ማለቱ ተገልጿል። በተጨማሪም፤ እንደ ኮፕቶች ያሉ እሕት ቤተ ክርስቲያኖች እንደ እንግሊዝኛ ባሉት የዓለም ቋንቋዎች በመጠቀም፤ እምነታቸውን ማስፋፋት ሲችሉ በኛ ቤተ ክርስቲያን በኩል ተመሳሳይ ጥረት ሲደረግ አይታይም። እንዲሁም፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናን ውጭ ሐገሮች እንደሚኖሩና በትውልድም እየተስፋፉ መሆናቸው ቢታወቅም፤ ተገቢ የሆኑ ማሠልጠኛዎችና ኮሌጆች አልተቋቋሙላቸውም። የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት፤ የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች ጊዜ የሚባክነው እንደዚህ ያለውን ከባድ ችግር ለማስወገድ አለመሆኑ ነው።


የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር ድክመት፤

ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተከስተው ከሚገኙት ከባድ ድክመቶች የሚከተሉትን መጥቀስ ተገቢ ነው፤

1ኛ/ ግልጽ የሆነ፤ ለቤተ ክርስቲያናችን ለዘለቄታ የሚጠቅም፤ ራእይ፤ ሥልት፤ እቅድና ፕሮግራም የለም፤

2ኛ/ አስተዳደሩ፤ እጅግ ደካማ የሆነ፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት/ቁጥጥር የጎደለበት፤ በሙስናና በጎሰኝነት የተተበተበ፤ ቃለ አዋዲው ተሻሽሎ የአሠራር ቅልጥፍና የሚያስፈልገው መሆኑ፤

3ኛ/ ለልዩ ልዩ የሥልጣን እርከኖች፤ በግልጽ የተመዘገበ፤ ለሹመትና ለቁጥጥር የሚያመች፤ ለሥራ ውጤት መለኪያ መስፈርት አለመኖሩ፤

4ኛ/ የቤተ ክርስቲያናችንን የፓትርያርክ ምርጫ ሥርዓት በጥንቃቄ ለተመለከተው፤ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ፤ እጅግ ውሱንና ደካማ በመሆኑ ለ50 ሚሊዮን ምእመናን ተወካይ ሆነው የሚመርጡት 800 ብቻ ናቸው።

ስለዚህ፤ በአባቶች መሀል ሰላም ቢሰፍን፤ ባለሞያ ምሑራንን በማሰማራት በቤተ ክርስቲያናችን የተሟላና የቀለጠፈ አገልግሎትና ቀጣይ መሻሻል ማስገኘት ይቻላል።

የፖለቲካ ጣልቃ-ገብነት፤

በሐገር ቤትም ሆነ በውጭም የተከሰተው ሁኔታ በግልጽ የሚያሳየው፤ ፖለቲከኞች በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ-ገብ መሆናቸው ነው። ይህንንም ሁኔታ ያባባሰው የብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች እርስ በርስ መኖቆር ነው። ስለዚህ፤ በዓለም አቀፍ መሠረታዊ መርሆና በኢትዮጵያም ሕገ መንግሥት መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን ነጻነቷን እንድታረጋግጥ ማድረግ የአባቶች አንደኛው ታላቅ ተግባር ነው።

የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ችግር ስለ መመከት፤

እንደሚታወቀው፤ በውጭም በውስጥም የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ተቃዋሚዎች፤ በኛ በኩል በተከሰተው የመለያየት መዳከም በመጠቀም፤ እርስ በርሳችን እንድንጋጭና በሚከፈተው በር ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እየተጠናከረ ነው። ስለዚህ፤ የቀድሞ ክርስቲያን ሐገሮች ላይ የደረሰው በኛም ላይ እንዳይደርስ፤ ከወዲሁ ጥንቃቄ የሰፈነበት እርምጃ እንዲወሰድ ያስፈልጋል። በተለይ በሐገራችን በክርስቲያኑና በእስላሙ መሀል “የጠላትህ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል የተዛባ መመሪያ ሳይሆን ለዘለቄታው ጸንቶ የሚኖር መከባበር፤ መቻቻል፤ ለሐገር ልማት ሕብረት የሚያስገኝ ግልጽና ቋሚ የሆነ ሥልት ማስፈን ይገባል።

ቤተ ክርስቲያናችንን የሚመለከቱ ዓለም-አቀፍ ጉዳዮች፤

በተከሰተው የአመራር ችግር ምክንያት፤ በቂ ትኩረት ያላገኙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው፤

1ኛ/ ኢየሩሳሌም የሚገኘው፤ ታሪካዊው “ዴር ሡልጣን” ገዳማችን፤ የግብጽ ኮፕቶች በፈጠሩት የይገባኛል ችግርና

የእሥራኤል መንግሥትም በያዘው አቋም፤ ከሁሉም በላይ ግን በቤተ ክርስቲያናቸን በኩል ተገቢው ጥረት ባለመከናወኑ፤ ሕንጻው የመፍረስ አደጋ ላይ ነው። ስለዚህ፤ ታሪካዊ ቅርሳችንን ለማዳን በሕብረት፤ ተግተን እንድንታገል ያስፈልጋል።

2ኛ/ ሌላው ዓለም-አቀፍ ትኩረት የሚገባው ከባድ ጉዳይ፤ በቫቲካን ድጋፍ ፋሺሽቶች ለፈጸሙት ግፍ እስካሁን ድረስ ሐገራችንም ሆነች ቤተ ክርስቲያናችን ተገቢ ካሣ ካላማግኘታቸው በላይ፤ የተዘረፉባቸው ንብረቶች አለመመለሳቸው፤ እንዲሁም ለወንጀሉ ተጠያቂ የሆኑት የኢጣልያ መንግሥትና ቫቲካን ይቅርታ አለመጠየቃቸው ነው። ከፈጸሙት ወንጀል ውስጥ፤ አቡነ ጴጥሮስን፤ አቡነ ሚካኤልን እንዲሁም በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የደብረ ሊባኖስ ገዳምተኞችን እንዲሁም ሌሎችን መጨፍጨፋቸው፤ 2000 ቤተ ክርስቲያኖችን ማውደማቸው፤ በቫቲካንም እጅ ክ500 በላይ የሆኑ ከሐገራችን የተዘረፉ ሰነዶች እንደሚገኙ የታወቀ ነው። ስለዚህ፤ ለሐገራችንንና ለቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ፍትሕ የሚቆም አመራር እንዲኖር ሰላምና አንድነት ያስፈልገናል።

ምእመናንን ከእግዚአብሔር ሕግ አፍራሽነት ስለ ማዳን፤

በብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች መሃል ሰላም ቢሰፍን መንጋዎቻቸውን ከእግዚአብሔር ሕግ አፍራሽነት ማዳን ይችላሉ።

እንደሚታወቀው፤ ስለ ቅዱስ ቁርባን እጅግ ከፍ ያለ የነፍስ ጥቅም ብዙ የተነገረን ቢሆንም፤ እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን (99%)፤ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ የሆነውን፤ ታላቅ የአምላክ ስጦታ፤ በልዩ ልዩ ምክንያቶች፤ ባለመቀበላችን፤ በቅዳሴው መጀመሪያ ራሳችን በምናዜመው፤ ከዚህ በታች በተጠቀሰው መሠረት፤ የእግዚአብሔርን ሕግ አፍራሾች ሆነን እንገኛለን።

“ሃሌ ሉያ! በቅዳሴ ጊዜ ክምዕመናን ወገን ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባ ሰው ቢኖር፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሳይሰማ፤ የቅዳሴው ጸሎት እስኪፈጸም ባይታገስ፤ ከቁርባኑም ባይቀበል፤ ከቤተ ክርስቲያን ይለይ (ይወገድ)፤ እግዚአብሔርን ሕግ አፍርሷልና። የሥጋና የነፍስ ፈጣሪ በሚሆን በሰማያዊ ንጉሥ ፊት መቆምንም አቃሏልና። ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው እንዲህ ብለው አስተምረውናል።”

ይህ ከባድ ሁኔታ፤ ለምእመናን ብቻ ሳይሆን ለካሕናትና ለቤተ ክርስቲያንዋ በአጠቃላይ መፍትሔ የሚያስፈልገው ግዙፍ ችግር መሆኑ የታወቀ ነው። የካሕን አገልግሎት የሥራ ውጤት መስፈርት አንደኛው፤ ምእመናን ንስሐ እየገቡ ወደ ቅዱስ ቁርባኑ እንዲቀርቡ ማድረግ መሆን እንደሚገባው አያከራከርም። ይህ ባለመሆኑ፤ በቤተ ክርስቲያናችን የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ፤ ለምእመናን የነፍስ ማዳኛ የተደገሰውን የአምላክ ስጦታ፤ ሥጋ ወደሙን፤ በአብዛኛው፤ የሚያጠናቅቁት፤ ራሳቸው ካሕናትና ዲያቆናት እንዲሁም ኃጢአት የሌለባቸው ሕጻናት ብቻ ናቸው! ስለዚህ፤ ምእመናንን ከቅዱስ ቁርባኑ አርቀው የሚገኙትን የባሕል ግንዛቤዎችና የማስፈራሪያ ሥርዓቶችና እንቅፋት የሆኑ ተግባሮች በጥልቀት በማጥናት፤ አመቺ በሆነ ቀልጣፋ የንስሐ አገልግሎት እንዲተኩና ምእመናን ከእግዚአብሔር ሕግ አፍራሽነት እንዲድኑ ማድረግ እጅግ የሚያስፈልግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣን፤

በ1991 ዓ/ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን፤ አንቀጽ 5፤ ቁጥር 1፤ በተደነገገው መሠረት፤

“በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅ/ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ፍተኛ
ሥልጣን ባለቤት ነው።”

ነገር ግን፤ እንደሚታወቀው፤ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ምሳሌዎች መገንዘብ እንደሚቻለው፤ የቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን በተገቢው ደረጃ እየተከበረ ነው ማለት አይቻልም፤

1ኛ/ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲፈርስ የወሰነው የአቡነ ጳዎሎስ ኃውልት አሁንም ቆሞ ይገኛል።

2ኛ/ በቀድሞው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሕሊና አቋም የያዙትን ጳጳሳት የደፈሩ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ አልተወሰደም።

3ኛ/ አንዳንድ ጳጳሶች ማእረጉን ያገኙት በጎሳ፤ በጥቅምና በፖለቲካ ትስስር መሠረት ስለ ሆነና ከነዚሁ ውስጥ ጥቂቶቹ ደግሞ የሚኖሩት በምንኩስና ሥርዓት ሳይሆን እጅግ በተንዛዛ የቅንጦትና የሙስና ኑሮ መሆኑ ስለሚታወቅ፤ ተሳትፏቸውን አጠያያቂ አድርጎታል።

ስለዚህ፤ የቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣን ሙሉ ክብር እንዲያገኝ ለመንፈሳዊ ግዴታቸው በጽንዓት የሚቆሙ ቤተ ክርስቲያኗን የማያስደፍሩ አባቶችና ለዚሁ ብቁ የሆነ ሥርዓት እንዲኖር ያስፈልጋል።

መደምደሚያ፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተጋርጠው የሚገኙ ብዙ ችግሮች አሉ። ዋናው ጠንቅ ግን የአመራሩ መፈረካከስ ነው። ለዚህም ያለው መፍትሔ አንድ ብቻ ነው። ይኸውም፤ ሁለታችሁ ብፁዓን ወቅዱሳን አባቶች፤ አቡነ መርቆሬዎስና አቡነ ማትያስ፤ ከእግዚአብሔር በተቸራችሁ ማእረግ፤ በዓለማዊነት ሳይሆን በምንኩስነታችሁ በመጠቀም፤ በታሪክ በሚያስወቅስ መከፋፈል ፋንታ፤ በቤተ ክርስቲያናችን ሰላም፤ አንድነትና ፍቅር እንዲሰፍንና ዘላቂነት ያለው መሻሻል እንዲገኝ የበኩላችሁን መፈጸም ነው። ለዚህም እጅግ ከፍተኛ ዓላማ ብቁ እንድትሆኑ ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ እንዲረዳችሁ እማጸናለሁ።

ከፍ ካለ የአክብሮት ሰላምታ ጋር፤

ኪዳኔ ዓለማየሁ

ምእመን።

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop