ቅዱስ ሃብት በላቸው (ከአውስትራሊያ)
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበሩት አውደ-ዓመቶች አንዱ ነው።
የቤተክርስቲያናችን የታሪክ መፅሃፍት እንደሚገልፁት አይሁዳውያን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ደብቀው ቀብረውት ከ300 ዓመታት በላይ ስፍራው ሳይታወቅ ቆይቷል። በ326 ዓ.ም. ላይ ግን የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ፣ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ የት እንደሆነ ፍንጭ አገኘች። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት ባቀጣጠለችው ጊዜ፣ ጢሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች።
ንግሥተ እሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንኑ ታሪክ ተንተርሶ ነው።
የመስቀል በዓል በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙት በጉራጌ፣ በጋሞ፣ በከምባታ፣ በሃድያ፣ በወላይታ …ወዘተ ብሔረሰቦች ዘንድ ከሌሎቹ የቤተ ክርስቲያኗ በዓላት በተለየና በደመቀ መልኩ እንደሚከበር ይታወቃል።
በተለይም በጉራጌዎች ዘንድ ከሌሎች የሃይማኖቱ በዓላት ይበልጥ ደምቆ የሚከበር አውደ-ዓመት በመሆኑ ሁሉም በከፍተኛ ናፍቆት የሚጠብቀው ነው። በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ በጠንካራ ሰራተኝነታቸው የሚታወቁት ጉራጌዎች ዓመቱን ሙሉ ጥረውና ግረው ያገኟትን ጥሪት በመቋጠር በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወደትውልድ መንደራቸው ይተማሉ። በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ በተለይም በመስቀል በዓል ወቅት የሚሰጠው የአባትና እናትም ሆነ የሌሎች ሽማግሌዎች ምርቃት ትልቅ ቦታና ክብር የሚሰጠው በመሆኑ ይህ እንዲያልፈው የሚፈልግ የጉራጌ ልጅ የለም ማለት ይቻላል።ለመስቀል ልጆቻቸው ሳይመጡ የቀሩባቸው ወላጆች የበታችነት ስሜት ስለሚሰማቸው ከፍተኛ ቅሬታ ያድርባቸዋል።
በገጠር ለዚህ በዓል ዝግጅት የሚጀመረው ቀደም ተብሎ ሲሆን፣ ራቅ ያለ አካባቢ የሚኖሩ ልጆች ገጠር ለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ፣ ሳሙና፣ ጨው፣ ጋዝ፣ ልብስ፣ ….ወዘተ ይልካሉ። በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችም በጋራ ሆነው ለበዓሉ ግብዓት የሚሆን እንሰት ይፍቃሉ፣ ለእንግዶች መቀመጫ የሚሆን ምንጣፍ (ጅባ) እንዲሁም ከቃጫ የሚሰራ የምግብ ማቅረቢያ በጋራ ይሰራሉ። ባንፃሩ ወንዶችም ለማገዶ የሚሆን እንጨት በመፍለጥ ያዘጋጃሉ። ይህም በብሔረሰቡ አነጋገር «የዌሬታ» በመባል ይታወቃል።
የበዓሉ ቀን እየተቃረበ ሲመጣም ሴቶች አረቄ በማውጣት፣ ጠላ በመጥመቅ፣ ሚጥሚጣ … ወዘተ በማዘጋጀት ስራ ይጠመዳሉ። መኖሪያ ቤቶችም ኖራ እና ቀለም እየተቀቡ አሸብርቀው እንግዶችን ለመቀበል ይሰናዳሉ።
በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል መከበር የሚጀምረው ከመስከረም 13 ቀን ጀምሮ ነው። ይህም ቀን «የሴቶች በዓል» በመባል ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን በዕለቱም በቅቤና በአይብ ያበደ የጎመን ክትፎ ለበዓሉ ታዳሚዎች ቀርቦ በቆጮ ይበላል። ይህም እንደ ሴቶች ሙያ መፈተሻ ተደርጎ ስለሚወሰድ ምግቡ የሚዘጋጀው ከወትሮው በተለየ እጅግ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው።
ተከታዪ ቀን (መስከረም 14) ደግሞ «ይፍት» በመባል የሚታወቅ ሲሆን በዋነኛነት የልጆች በዓል ተደርጎ ይወሰዳል። በዕለቱ በየመንደሩ የተተከሉ ትናንሽ ደመራዎች ተለኩሰው በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በጋራ ተሰባስበው እየበሉና እየጠጡ ሲጫወቱ ልጆችና ወጣቶች እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። ይህ በዕለቱ የሚለኮሰው ዳመራ «የዴንጊ እሳት» ይባላል።
http://youtu.be/0-OuGl2wBYk
መስከረም 15 ቀን ደግሞ ዋናው የበዓል ቀን ነው ማለት ይቻላል። በዕለቱ ቤተ ዘመዶች በዕድሜ አንጋፋ ከሆኑት ሽማግሌ ቤት ተሰብስበው ወንዶች ሊታረድ የተዘጋጀው ከብት ላይ እጃቸውን በመጫን በሽማግሌዎች ይመረቃሉ። የምርቃቱ ስነስርዓት እንደተጠናቀቀም ከብቱ ተጥሎ እየተበላና እየተጠጣ ጭፈራው ይቀልጣል። ይህ ስነስርዓት በአገርኛው ቋንቋ «ኬር» በመባል ይታወቃል።
መስከረም 16 ቀን ሁሉም ሰው ያዘጋጀውን ችቦ ይዞ የአካባቢው ማዕከል የሆነ ቦታ አስቀድሞ ወደተተከለው ግዙፍ ዳመራ ያመራል። በሃይማኖት አባቶችና በሽማግሌዎች ፀሎትና የምርቃት ስነስርዓት ከተከናወነ በኋላም ዳመራው ይለኮሳል። ቀደም ባለው ዓመትም ስለት ተስለው የደረሰላቸው ሰዎች ስለታቸውን ያቀርባሉ። በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል የተኳረፈ የሚነጋገርበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የበደለ የሚክስበት፣ ነው። በዚህም የተነሳ በአካባቢው የተጣሉ ሰዎች ካሉ እርቅ ሳይወርድ በምንም አይነት ዳመራው አይለኮስም። በዚህ በኩል የአካባቢው ሽማግሌዎች ደም የተቃቡ ባለጋራዎች እንኳን ቢሆኑ ይቅር እንዲባባሉ በማድረግና ፍፁም ዕርቅ እንዲወርድ በማድረግ ከቀደምት አባት እናቶቻቸው የወረሱትን የሚያኮራ ባሕል ተግባራዊ ያደርጋሉ። በዚህ ስነስርዓት ላይ የታረቁ ሰዎችም ከዚያ በኋላ ወደቀደመ ጠባቸው መመለስ መጥፎ ነገር እንደሚያመጣ (እንደሚያስቀስፍ) ስለሚታመን በዳመራው ዕለት የታረቁ ባለጋራዎች መሃል የወረደ ሰላም ዘላለማዊ ነው ማለት ይቻላል።
መስከረም 17 ቀን ደግሞ ከቀናት በፊት ለበዓሉ የታረደው በሬ ሻኛ (ንቅባር) እንዳይበላሽ በጥንቃቄ ከተቀመጠበት እንዲወጣ ተደርጎ በአባት ወይንም በታላቅ ወንድም ቤት ውስጥ በሚጥሚጥና በቅቤ እየተለወሰ እየተበላና እየተጠጣ ጨዋታው ይደራል። በዚህ መልኩ በደመቀ ሁኔታ የሚከናወነው የመስቀል በዓል የሚጠናቀቀው እርዱ በተከናወነ በሳምንቱ ሲሆን ዕለቱም «አዳብና» በመባል ይጠራል።
ባጠቃላይ ከ«ንቅባር» (በዓሉ ከተጀመረበት ዕለት) አንስቶ እስከ አዳብና ድረስ የሚከበረው የመስቀል በዓል ለቤተ-ጉራጌዎች የመጠያየቂያ፣ የመደሰቻ፣ በሽማግሌዎች የመመረቂያ፣ ለአቅመ አዳም የደረሱት ለጋብቻ የመተጫጪያ፣ ለተጣሉ የመታረቂያ፣ በመሆኑ ለመስቀል ጓዙን አሰናድቶ ወደትውልድ አገሩ የማያቀና የብሔረሰቡ ተወላጅ ጥቂት ነው ማለት ይቻላል።
መልካም በዓል ይሁንልን!