የማለዳ ወግ … 83 ኛው የሳውዲ አረቢያ ብሔራዊ በአል ምልከታየ !

ከነብዩ ሲራክ (ጋዜጠኛ)

ጊዜው ይነጉዳል … አሁን አሁን የጊዜው መሮጥ የሳውዲ ቆይታየን እንደ እድሜየ እየቀናነስኩ ወደ መናገሩ ሊያዳዳኝ ቀርቧል! አዎ በሳውዲ ጅዳ ጎጆ ቀልሸ ስኖር ሳውዲዎች አገር አቀፍ ብሔራዊ 83ኛ የልደት በአላቸውን ሲያከብሩ ከ16 አመት ላላነሰ በአላቸውን አብሬ አያከበርኩ ነው !
በሳውዲ ቆይታየ አሮጌው በአዲስ አመት ሲተካ ደርሶ ማየት ከሚያስደስቱት ሃገር አቀፍ ታላላቅ በአላት መካከል ይህ ብሔራዊ የሳውዲ አረቢያ በአል ሲከበር ማየት ነው ። በአለሉ ልዩ ድምቀት አለው። ከዋዜማው ጀመሮ በዚህ ቀን የሳውዲ ከተሞችንና ሳውዲዎችን ማየት ያስደስታል። በተለይም የሃገሬው ወጣት ነዋሪ ቁጥር በአስገራሚ ፍጥነት እየተለወጠ በመጣባቸው ባለፉት አስርት አመታት የሳውዲ ብሔራዊ በአል አከባበር መልኩን ተለዋውጧል ። ምንም እንኳን የሳውዲ አረቢያ የንጉሳውያን ቤተሰቦች የስልጣን ወንበር ድልድል እና የሃብት ክፍፍሉ ወደ ቀረው ነዋሪ በፍትሃዊ መንገድ ባይወርድም በአረብ ሃገራት አመጻ ከተጀመረ ወዲህ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል። ዜጎች ስራ የማግኘት እድልና ስረ የሌላቸው የመንግስት ድጋፍ ያገኙ ጀምረዋል። የሳውዲ መንግስት የፖለቲካውን ትኩሳት ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ የዜጎቹን ጥያወቄ ያደምጣል ፣ እናም መንግስት ከሁኔታዎች ጋር ይለዋወጣል። ካሳለፍንው የአረቡ አልም የጸደይ አብዮት መባቻ ጀምሮ የወጣቱን ድምጽ ለማዳመጥና በስራ የታነጸ ዜጋ ለመፍጠር ከፍ ያለ ጥረት ለማድረጉ ረገድ የሳውዲ ንጉሳዊውን ቤተሰቦችን ነባራዊ ሂኔታዎች አስገድደዋቸዋል! ወደ ውስጥ አንገባም: )
የሳውዲ ብሔራዊ በአል ከአመት አመት ሲከበር ሁሉም ነገር በአረንጓዴ ሊሆን ግድ ይላል። ሁሉም ነገር በአረንጓዴው የሳውዲ አረቢያ ስንደቅ አላማ ቀለም ያሸበርቃል ! “ከአላህ ውጭ ምንም የለም ! “የሚል የቁርአን ጥቅስ በነጭ የተጻፈበት አረንጓዴ ሰንደቅ አላማ የትም ቦታ መድመቂያ ይሆናል። ከሚለበሰው ልብስ ፣ ከጫማ ፣ ከመነጽር ፣ ከጸጉርና ከፊት አልፎ በአውላላው መንገድ ላይ የሚሽከረከሩት የሚማምሩት ዘመናዊ መኪኖች ቀለም ሳይቀር በአረንጓዴው ባንዴራ አና በንጉሳውያን ቤተሰቦች ፎቶ ይሽቆጠቆጣሉ! ሁሉም ደመወቆ የሚታዩት በዚህ ይህ ብሔራዊ በአላቸው ነው ! ወጣቶች ባሸበረቀው መኪናዎቻቸው ጣራ ድረስ እየወጡ ብሔራዊ በአሉን በሚያዘክሩት ባህላዊ ዳንኪራ ማራኪ ነው … ዳንኪራው ደግሞ በአረብኛ የተወሰነ አይደለም ፣ እስከ “ሮክና ሮል ” ፈረንጅኛው ቅኝት ይዘልቅና የሳውዲ ጎዳናዎች ከዋዜማው ምሽት እስከ በአሉ መባቻ ይቀወጣሉ ! በደስታ ፊስታ ! ይህን ሲያዩ ሳውዲ ስለመሆንዎት ይጠራጠሩም ይሆናል! ግን እውነት ነው ሳውዲዎች ድስታቸውን ሲገልጹት እንዲህ ነው !
ሳውዲዎች በአብዛኛው ደግ ህዝቦች ናቸው! ከቀረቧቸው እንብላ እንጠጣ የቆየ ባህል አላቸው ! በአለም አንቱ የተባሉት ታላላቅ ባለሃብቶች የረመዳኑ ጾም ሲፈታ ከተራ ሰራተኞች እኩል ማዕድ ይቀርባሉ ! ሳውዲዎችን ለተወዳጀ ለቀረባቸው ደግሞ ቤታቸው የአብርሃም ቤት ነው …
ሳውዲዎች እንደቀረው ዜጋ ቡሉ በግለሰብ ደረጃ አክራሪ ዜጎች አላቸው ፣ በመንግስት ደረጃ ግን አክራሪ ብሎ ነገር የለም። በመገናኛ ብዙሃን በአክራሪነትና በደጋፊነት በሰፊው የሚወነጀሉት ሳውዲዎች እና እየሆነ ያለውን የተለያየ ነው ፣ የተሳሳተ መረጃ የመነገሩን አንድምታ ጠጋ ብየ ሳስበው የመረጃ ክፍተቱ ነገር ይገርመኛል። የሳውዲ መንግስት በአለማችን አክራሪነትን በመዋጋት የተሳካላቸው ጥቂት ሃገራት ቀዳሚ መሆኑን ብዙዎች የሚረዱት ስለማይመስለኝ አዝናለሁ! መንግስት አክራሪነት ያሰጋዋልና አይፈልገውም! ሳውዲ ውስጥ ጽንፈኝነትን ማራመድ አጥብቆ የተከለከለ ነው! ያከረሩት የከረረ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ያውቃሉና ይህችን መንገድ አይከተሏትም!
ሳውዲ ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተቀየረች ነው ። ሳውዲዎች እየዘመኑ ካሉት የአለማችን ሃገራት ተርታ ቀድማ እንድትጓዝ የሚያስችላት የጥቁሩ ወርቅ (ነዳጅ) የተከማቸ ገንዘብ ለሃገር ግንባታ መዋል ከጀመረ ወዲህ ታላላቅ ለውጦችን እያየን ነው ። እድሜ ለሰጠው ሳውዲ በቀጣይ አምስት አመታት ዛሬ ከምናውቃት ተለዋውጣ እንደምናያት ተስፋ የሚሰጡ ስራዎች እየተሰሩ ነው … እናም ሁለንተናዊ ለውጥ ለማየት ያብቃን!
ሳውዲ ሲኖሩ ህግና ስርአትን ካከበሩ መብትዎን የሚጋፋ የለም! እርግጥ ነው አልፎ አልፎ ችግር የለም አልልም ። ሰው በግፍ ይበደላል! ይሁን እንጅ የመብት ገፈፋው ምንጭ በመንግስታችን ተወካዮች ዘንድ የመብት ጥበቃ ስለማይደረግል መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል። ሳይጠቀስ የማይታለፈው ነገር የኮንትራት ስራተኞች በደል ሲሆን በግል በጋጠዎጥ አሰሪዎች በደል ሲደርስ በደል ሲደርስ በዳይን በእማኝ በዋቢ ይዞ ወደ ህግ ፊት የሚያቀርብልን ተወካይ እጦት ኑሮን በሰቆቃ እንድንገፈ አድርጎናለደ። መብት አስጠባቂ አካል ከተገኘ ፍትህ ርትዕ ሳውዲ ላይ ቅርብ ነው! ግናስ እኛን እዚያ ማን ያድርሰን ? ይህንንም ዛሬ አልነካውም …
ሳውዲ ውስጥ የፈለጉትን ያህል አመት ቢኖርም ሆነ እዚህው ተወልደው ቢያድጉ ዜግነት ማግኘት ብሎ ነገር የለም! አይታሰብም! የሳውዲ ኑሮ የኮንትራት ነው የሚባል ተረት ቢጤ አለ ። እውነት ነው! አሰሪዎ ከፈለገ በአሻው ጊዜ ከሃገር ሊያባርርዎ ይችላል ! ይህ ሁሉ ሆኖ ሌላ አማራጭ አጥቶም ሳይሆን ተመችቶት በሰላም የሚንኖረው ዜጋ ቁጥር ቀላል አይደለም!
ስለ እውነት ለማናገር በግሌ አሁን አሁን ሀገሬ እንኳ ብሄድ የማይሰማኝ ነጻነት ሳውዲ ስኖር ይሰማኛል ብል አትፍረዱብኝ ! መንግስት ከደሞዜ ቆርጦ ቀረጥ አያስከፍለኝም ፣ ለመንገድ ለህንጻው የምገብረው ግብር የለም! ለኑሮ ፍጆታየ መባልዕቱን እኩል ከዜጎቹ እገበያያለሁ ፣ ሰላማዊ እስሆንኩ ድረስ ሌሊት ላይ ቤቴ ተሰብሮ እታፈናለሁ ብየ አልሰጋም ፣ መንገድ ወታደር ፣ ፖሊስ ፣ደህንነት ይጠልፈኛል ብየ አልሰጋም ! እናም ከሃገሬ ባልተናነሰ ሳውዲ ሰኖር ነጻነት ይሰማኛል !
በርካታ አመታት በሳውዲ ስኖር ንብረት ባይፈራም ልጆች ወልጀ በስኬት እያሳደግኩ ያለሁባት ሃገር ሳውዲ አረቢያ ነው! 83ኛ አመት ብሔራዊ በአል ሲከበር በአሉን ለማዘከር በማለዳ ወጌ ይህችን ያህል ከተብተከተኩ ይበቃኛል!
ለሳውዲዎች መጭው የስኬት ጎዳና እንዲሆንላቸው መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ !
መልካም በአል!
ነቢዩ ሲራክ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከሙስናው በስተጀርባ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)
Share