በቻድ አንድ የስነ አእምሮ ሐኪም ብቻ በኢትዮጲያስ? (ክፍሉ ሁሴን)

ቢቢሲ የ12 ሚሊዮን ሕዝብ ባለቤት በሆነችውና የተጠናወታት ድህነት ሳያንሳት በጦርነት ስትናወጥ በከረመችው ቻድ ያለው የስነ አእምሮ (psychiatrist) ሐኪም አንድ ብቻ ነው ይለናል።

ቻድስ ሰብ ሰሃራ አፍሪካ ተብሎ በሚታወቀው ቀጠና ከሚገኙት አገሮች ሁሉ በባሰ ሁኔታ የድሆች ድሆች መሆኗ ታውቆላታልና ዜናው አያስገርምም።ለመሆኑ ገዳይና አካል አሰናካይ የሆነው የልጅነት ልምሻ (polio ) ተመልሶ ተዛመተባት ከተባለ በኋላ በማግስቱ ደግሞ የሕጻናትን ሞት ቀነሰች በተባለችው “ልማታዊዋ” ኢትዮጲያስ ያሉት የስነ አእምሮ ሃኪሞች ስንት እንደሆኑ እናውቃለን?ትክክለኛው መረጃ እጄ ላይ ባይኖርም ከ86 ሚሊዮን በላይ ለሆነው የኢትዮጲያ ሕዝብ ያሉት የስነ አእምሮም ይሁን የሌላ ሐኪሞች ብዛት ከቻድ እምብዛም እንደማይለይ ፍርጥም ብዬ እወራረዳለሁ።

እስካሁንም ድረስ በአፄ ሃይለስላሴ ጊዜ ከተሰራው የአእምሮ ሕሙማን ሆስፒታል—አማኑኤልን ማለቴ ነው—-ሌላ እንደተጨመረ የሚያሳይ ምንም መረጃ አላገኘሁም።ይልቁንም በጥቅምት 1998 እስከ ጥቅምት 1999 በቃሊቲ ማጎሪያ ካምፕ ተቀፍድጄ በነበረ ጊዜ በነፍስ መግደል ወንጀል ተከሰው የታሰሩትንና የአእምሮ ሁኔታቸው አጠራጣሪ የሆኑትን ባለሙያ እንዲመረምራቸውና የተከሰሱበትን ወንጀል እንዲፈጽሙ ያደረጋቸው ይኸው የአእምሯቸው ሁኔታ መሆን አለመሆኑን እንዲመሰክር “ፍ/ቤት” በሚያዝበት ጊዜ በዚያ ለአገሪቱ አንድ ለናቱ በሆነው አማኑኤል ሆስፒታል ያሉት ባለሙያዎች ሊያዳርሷቸው ስለማይችሉ ረጅም ቀጠሮ እየተሰጠ እነዚህ አደገኛ ዝንባሌ ያላቸው ተጠርጣሪዎች በልዩ ልዩ ሰበብ ከታጎረው ሌላው ምስኪን ሕዝብ ጋር አብረው እንዲከርሙ ይደረጋል። የአእምሮ ሁኔታቸውም እየተባባሰበት መሄድ ብቻ ሳይሆን በሌሎች እስረኞች ላይ ከፍተኛ አደጋ ሲያደርሱ በአይን ምስክርነት ከማየት ባሻገር ካንዱ አደጋ በደቂቃዎች ልዩነት የተረፍኩበትንም አጋጣሚ አስታውሳለሁ።

ለማንኛውም የዛሬዎቹ ገዢዎች እድሜ ለሟቹ ባለ”ራዕይ መሪያቸው” በ”ልማት”የሚያህለን የለም ተመንድገናል ስለሚሉና ይህንኑም እንዲያስተጋቡላቸው የፈረንጅ ቱልቱላዎች (lobbyists ) ቀጥረው ራሳቸውን በመቀባባት ላይ ስለሆኑ ከኢትዮጲያ የሚወጣው ዜና እንደቻድ ሳይሆን በመልማታችን የተነሳ ሕዝቡ ደስተኛ ስለሆነ የአእምሮ ሕሙማን የሉም የሚል ሊሆን ይችላል፤ይሆናልም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመስዋዕትነት ወንጌል - ከጸጋዬ ገ.መድኅን አርአያ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአእምሮ ሕመምተኞች ሁሉ ምንም የማያውቁ ፉዞዎች አድርገን ለምንገምት ይልቁንም ብሩህ አእምሮ ያላቸው ሰዎች በፉዞዎች ምድር ለአእምሮ ሕመም እንደሚጋለጡ ለማናውቅ ቀጥሎ ያለው ታሪክ እያዋዛ ያስተምረናል።

አንድ ዘመናይ መኪናውን እያሽከረከረ ወደ ጉዳዩ ሲከንፍ አማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ ሲደርስ ጎማ ይተነፍስበትና ወደጥግ አቁሞ ለመቀየር ይገደዳል።እናም ኮፈኑን ይከፍትና የጎማውን ሳህን አውልቆ ብሎኖቹን ከፈታ በኋላ ሳህኑ ላይ አስቀምጦ ክሪኩንና ተቀያሪ ጎማውን ለማውጣት ወደኋላ ዞሮ ወደኮፈኑ ይመለሳል።ጎማውንም ክሪኩንም ካወጣ በኋላ ወደሚቀየረው ጎማ ሲመለስ ሳህኑ ላይ አስቀምጧቸው የነበሩት ብሎኖች ከነሳህኑ ተሰርቀዋል።በሴኮንዶች ልዩነት ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ከተደመመ በኋላ ወደመለዋወጫ ሱቅ ሄዶ ብሎኖች ለመግዛት አሰበና መልሶ ደግሞ “እዚችው ሆኜ በሴኮንዶች ውስጥ ብሎኖቼን ከሞጨለፉኝ መኪናውን ትቼ ዞር ካልኩማ ቅርጫ ያደርጉታል”በማለት እየተገረመም እየተከዘም ሲያስብ በዘመዶቹ እየተጠበቀ አማኑኤል ሆስፒታል ለመታከም ተራ በመጠባበቅ ላይ ያለ የ”አእምሮ ህምመተኛ”ያስተውለው ኖሮ “ወንድም! ለምን ትጨነቃለህ?ከሌሎቹ ደህነኛ ጎማዎች አንዳንድ ብሎን ፍታና ግጠምለት፤ሁሉም አንዳንድ ብሎን ቢጎድላቸውም እየነዳህ ከመሄድ ስለማያግደህ ረጋ ብለህ ገዝተህ ታሟላችዋለህ” ይለዋል።

ሲጨነቅ የነበረውም አሽከርካሪ በመፍትሄ ሃሳቡ ተደስቶ ማመስገን ከጀመረ በኋላ አንድ ነገር በድንገት ብልጭ አለለትና “ግን አንተ–!”ብሎ ሊጠይቅ ያሰበውን አንጠልጥሎ ሲተወው የ”አእምሮ ሕምመተኛው” ገብቶኛል ልትል ያሰብከው “ዳሩ እኔ እብድ እንጂ እንዳንተ ደደብ አይደለሁም።”ብሎ በአእምሮ ህመምና በደደብነት መካከል ያለውን ገደል አሳየው።

ቻድንም በውሸት ተቁዝረው እንድንቆዘር ለሚያስገድዱን የዘመኑ ገዢዎቻችንም ለኢትዮጲያ ሲባል ከዚህ አይነቱ ደዌ ይሰውርልን።

እ.ኤ አ መስከረም ወር 2013 ካምፓላ፤ዩጋንዳ ተጻፈ
ኢሜይል፤kiflukam@yahoo.c

Share