የማለዳ ወግ …አምላክ ሆይ ! የአዲሱ አመት ተስፋና ምኞታችን አሳካው !

ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ

አንድየ ሆይ! ያላንተ እዚህ መድረስ አይታሰብምና ከሁሉ አስቀድሜ ለከበረው ስምህ ፣ ለማይደፈር ለማይገሰሰው ሰማያዊ ክብርህ ፣ ለቸርነት ፣ ምህረት ይቅርታህ ምስጋና ይድረሰው ! አባታችን አዳም ትዕዛዝክህ ተላልፎ ታላቁን ስህተት ፈጸመ ፣ ከገነትም ተባረረ ! አባት ሆይ ! አዳም አጠፋ ብለህ አልተውከንም ! የምህረት አምላክ ነህና መንግስትህን እንወርስ ዘንድ በህግ ትዕዛዛትህ እንድንመራ አዘዝከን! ዳሩ ግን ትዕዛዛት ህግ ቀኖናህን ስንጥስ ኖርን … ይህ ሆነ ብለህም አልተውከንም …
ያለባላ በዘረጋህው ሰማይ ፣ ያለመሰረት ባነጠፍከው ምድር ፣ በእጹብ ስራህ የምድር መቀነት አድርገህ ባንሰራፋህው ውቅያኖስ እና ወንዝ ደምቀን ስታኖረን የምንበላው የምንጠጣውን የምንለብስ የምንጠለልበት በመለኮታዊ ስልጣን ከቸርነት እና ከምህረትህ ጋር ያልተውከን አንተው ብቻ ነህ ! እናም እናመሰግንሃለን ! ዘመን በዘመን ሲተካ ፣ ትውልድ በትውልድ ሲታደስ የዛሬ ባለተሮች ሆነናልና ለቀኖና ህግ የምንገዛ ለሰማያዊ ትዕዛዝህ የምናከብር አድርገን ! በይቅርታ ቸርነትህ ተጠብቀን አዲሱን አመት ስንቀበል የአዲሱ አመት ምኞታችን ብዙ ነው …ከሁሉም በላይ የሰው ልጅን ኢትዮጵያን እና ህዝቧን አንድነታችን ከሚያናጋ ፣ ህብረታችን ከሚንድ እኩይ ስራ ሁሉ ትጠብቃት ዘንድ ምኞቴ ነው ! በአዲሱ አመት መባቻ አሮጌው አመት ለመሸኘት ስንሰናዳ የሃገር የወገናችን ጉዳይ የሚያሳስበን የሚያስጨንቀን ተጠራርተን እንዲህ ብልን የህብረት ምኞት ተመኘን … አዲሱ ዓመት ሲጠባ፣ በአዲስ መንፈስ አዲስ ሕልም ለአገራችን ብሩህ እድገት ለወገኖቸቻችን ሰላም ጤና ህብረት ጥንካሬ የማለሙንቀዳሚ የምኞት ህልም ለማጠናከር ቃል ገባን። ኢትዮጵያ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የሃብት፣ የትምህርት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ሌሎችም ልዩነቶች አብሮነታችንን የማያደናቅፉባት፤ ከነልዩነታችን በጋራ እድገት የምንጠቀምባት፤ ለሁላችንም እኩል ዕድል እና ተጠቃሚነት የሚቀርብባት፤ ሁላችንም እንደ የችሎታችን ለጋራ ነጻነታችን፣ ደኅንነታችን እና ብልፅግናችን የምንሠራባት ሃገር ትሆን ዘንድ ተመኘን . …ለሃገራችን ብሩህ መጻኤ ህይዎት በጋራ ስኬታማ የምንሆንባት፤ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያፈቅራት፣ በዜግነቱ የሚደሰትባትና የሚኮራባት ኢትዮጵያ እንድትሆን በጋራ የአዲስ አመቱን አዲስ ምኞት ተመኘን ! አቤቱ የጭንቀት ምልጃ ልመናችን ተቀበለው ! ተስፋ ምኞታችን አሳካው !
ስደት ክፉ ነገር ነው … በስደት ረክሰናል ፣ በስደት ተዋርደናል ፣ በስደት መልካሙ ገጽታችን ከፍቷል ! ለስደቱ የከፋ መከራ አማኝ ለመሆኔ የአረብ አለም የገፋሁት ህይዎት አማኝ ምስክር መሆኔን በፊትህ ስመሰክር አንተ አታውቀውም ብየም አይደለም ! እናም ለቀሩው ትምህርት ቢሆን ደግሜ ደጋግሜ እናገረዋለሁ !

ተጨማሪ ያንብቡ:  ! …. ባህር ዳር አነባች…….!

ለአመታት በከተምኩበት የአረቡ አለም የስደተኛ የከፋ መከራ የከፋ ነው ! የተሻለ ኑሮን ለመግፋት ከሚለው የተሻለ ኑሮ ፈላጊ ይልቅ የኑሮ ውድነት እና ድህነቱ አፈናቀሏቸው ወደ አረብ ሃገራት የሚሰደዱት ወገኖች ስቃይ በቃላት ሊገልጹት የሚቻል ያለመሆኑ ምስጥር ስደቱ ከሞት ጋር ተፋጦ የሚከወን ነው! ይህ በመኖርና አለመኖር መካከል በሚደረገው አሰቃቂ ስደት በሶማሌና በጅቡቲ እና በሳውዲ በቀይ ባህር ማዕበል እና ጭልጥ ባሉ በርሃዎች እልፍ አእላፍ ዜጎች ውሃውና በርሃው እየበላቸው በሃዘን ተለይተውናለል ! በራሳችን አዘዋዋሪ ዜጎች በንዋው ፍቅር ተለክፈው ጨክነው ጎድተውናል! ዜጎች በዘላን ሴሰኛ አረቦች እየተደፈሩ ሊናገሩት የሚሰቀጥጥ ግፍ እየተፈጸመባቸው እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል ! ነፍሳቸውን ይማረው ! በባህር እና በበርሃዎች የቀሩትን ዜጎችስቃይ ህልፈት እያመመን ሲቀጥል በውል በማይታይ የማይጨበጥ የሃገራት የህግን ማዕቀፍ ወደ አረብ ሃገራት በኮንትራት ስራ ስም የሚሰደዱ ዜጎች ሰቆቃም ከህገወጡ ስደት ባልተለ የከፋ ሆኗል! ያሳለፍነው አሮጌ አመት ዜጎች ያለ ጠባቂ መብት አስከባሪ እንደጨው ሲበተኑ የሚሰደርስባቸው ፈተና ቀላል አልሆነም! ድህነትንና የኑሮ ውድነትን ሸሽተው የመጡ እድሜ ያልጠገቡ እህቶች እና ወንድሞች መሪር የመከራ ጩኸት ከፍ ብሎ ተሰምቷል ! ብዙዎች ድምጻቸው ሳይሰማ በግፍ ጠፍተዋል ፣ ከሞት የተረፉት በአካልና በመንፈስ ሁከት ደዌ ተሸብበው አብደውና ጨርቃቸውን በአደባባይ ጥለው ያየንበት አሰቃቂ ሰቆቃ ተስተናግዷል ! ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም ለመብት ማስጠበቁ የተሰየሙ ምስለኔዎቻችን የፈየዱልንን የመብት ጥበቃ ከማውሳት የበደሉንን በቁጭት ማዘከሩ ይቀላል ! ይህ ሆነ ብለን ግን አንተን ከማመስገን እና በጎ በጎውን ከመመኘት አንቦዝንም !
አቤቱ አምላክ ሆይ ! የምህረት የቸር አምላክ ነህና በአዲሱ አመት በስደት የተሰበረ ልባችን አጽናው ! ለሃገሩ ለወገኑ ቀናኢ መንግስት ስጠን ! ከተሰየሙለትና ከቆሙለት ሃገር ወገናዊ በጎ አላማ ይልቅ በቡድናዊ ስሜት ኑሯችን ያጨለሙትን ልብ አቅናው ! በመዋዕለ ንዋይ ታውረው በወገን ደም የሚበለጽጉትን አዘዋዋሪ ደላሎች በጭካኔ የታበለ ልብ አራራው !
ከህብረት ይልቅ መለያየትን ፣ ከሰላም ይልቅ ብጥብጥን ከመመኘት ሰውረን ! ክፉ ክፉ ከሚያሳስበን እኩይ ሰይጣናዊ ምግባር እቅበን ! ልዩነታችን ከፍቷልና በህብረት አንድነት ትስስር አሽረው ! አንድ አድርገን ! አዲሱን አመት በአዲስ ተስፋ እጀምረው ዘንድ በማወቅና ባለማዎቅ ያስቀየምኩ ፣ ያስከፋኋቸው ይቅርታየን ይቀበሉ ዘንድ ልባቸውን አራራው ! አቤቱ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ ! አንተም በይቅርታህ ጎብኘን ! ዘመኑን የምህረትና የይቅርታ ዘመን አድርግልን !
አቤቱ ሁሉንም ማድረግ የማይሳንህ አምላክ ሆይ ! የአዲሱ አመት ተስፋና ምኞታችን አሳካው !
አሜን ! ! !
ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 1ቀን 2006 ዓ.ም
ከሳውዲ አረቢያ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ እውነተኛ ልጇን አጣች
Share