September 10, 2013
16 mins read

አዲስ ዓመት – በነተበ ሥርዓት

(ሩት ዳግም)

Enqutatash -Happy New Year
አዲስ ዓመት - በነተበ ሥርዓት 1

      ጊዚያቶች  ክንፍ  አውጥተው የሚበሩ ይመስላሉ። 2005 አምና ለመሆን በቅቷል። የተፈጥሮን ህግጋት ጠብቆ በዳመና የጠቆረው ዳመና  እየገለጠ፣   አበቦች እየፈኩ መድሪቷ የመስከረም ወር መጥባቱን ብታበስርም፤ በክፉ የወያኔ አገዛዝ ቀንበር ስር ለሚማቅቀው የአገሪትዋ ህዝብ ዛሬም እንጉርጉሮው የሀዘን ነው። የኑሮ ውድነቱ፣ የሰብአዊ መብት ጥስቱ፣ ፍትህ ማጣት እና በመሳሰሉ ስር በሰደዱ ችግሮች እግር ተወርች ተቀፍድዶ ነገን በተስፋ ተሞልቶ አዲስ ዓመት ይጠብቃል ማለት ዘበት ነው። ይልቁንም አዲስ ዓመት ይዞት በሚመጣው የኑሮ ጣጣ የሚቆዝመው ህዝብ ቁጥር እልፍ ነው።

     ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› የሚባል የወያኔ ዕድሜ ማራዘሚያ የተዘጋጀው እቅድ እንደተወራለት በአምስት ዓመት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ  ህዝብን የሚያሰልፍ አለመሆኑን ሁሉም ተገንዝቦታል። ይልቁንም የህውሃት ግዙፉ ድርጅት ኤፈርት በያዛቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች አመቻቺነት ጥቂት የወያኔ ባለስልጣናትን በሙስና ፈጣን ባቡር ወደ ሚልኒየር፣ ቢልየነር ተርታ  መላውን ህዝብ ደግሞ በድህነት ቀፍድዶ ወደአዘቅት የሚያደርስ ሆኗል። በዚህ አሳዛኝ ህይወት ላይ  ለሚገኝ ህዝብ አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ መጠበቅ የቀን ቅዠት ነው። ወትሮስ በዘረኝነት፣ በሙስና በሀገር ክህደት ብል እንደበላው ነጠላ የነተበ መንግስት የአገርን ገበና በምን አቅሙ ይሸፍናል??

     በአይነ ህሊና የዘመን አሮጌ ልብስ የደረበውን የዘንድሮ ዓመት መለስ ብላችሁ ብትቃኙት ቅንጣት ያህል አስደሳች ነገር ለማግኘት ይከብዳል። በ2005 ዓ.ም. በወያኔ መንግስት የስልጣን ሽኩቻና ሹም- ሽር ያየለበት፤ እስርና ግድያ በአደባባይ የተፈጸመበት፣ ፍትህ ማጣት ያየለበት፤ በኑሮ ወድነት፣ በመብራት መጥፋትና መምጣት፣ በውሃ መቋረጥ፣ በታክሲ፣ ዘይት፣ የስኳርና የስንዴ በመሳሰሉ ሰልፎች መሽቶ እስኪነጋ ህዝብ የሚደክምበት ተስፋ አስቆራጭ የቀን ጨላማ ነበር። በመንግስት ሚድያ ደግሞ “የታላቁ መሪ” አቶ መለስ ውዳሴ “ውርሳቸውን/ሌጋሲያቸውን” እናስቀጥላለን በሚል የማያባራ የቆሸሸ ፖለቲካ ህዝብን ማሰላቸት ሥራዬ ብለው ከርመውበታል። ይሁንና ይህ ወቅት አልፎ የመለስ እኩይ ተግባር፣ ክህደትና ተዘርዝሮ የማያልቅ ክፉ ተግባር ትውልድ ሁሉ በሚማርበት መልኩ በዚያው በሀገራችን፤ በዚያው ሚድያ የሚነገርበት ዕለት ይመጣል።

አሁን ባለው የጨለመ ድባብ አዲስ አመት ሲመጣ ህዝቡ እንደ ወግ ልማዱ

“ከብረው ይቆዩ ከብረው

በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው

ሠላሳ ጥጆች አስረው

ከብረው ይቆዩ ከብረው” የሚል የልጆቹን ዜማ ተቀብሎ እያዜመ ነገን በተስፋ ያልማል ማለት የአብዛኛውን ህዝብ ኑሮና የተጫናበትን መከራ ያለማወቅ ነው።

 

ይሁንና ይቺን መከራኛ አገር ላይ ተፈናጠው እንዳሻቸው ደንገላሳ ለሚጋልቡዋት የህውሀት ባለስልጣናትና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው  ግን ሁሌም አዲስ ዓመት፤ ሁሌም በዓል ነው ያቺ ቀን እስክትመጣ . . . በሙስና በዘር ፖለቲካ ውርስ በተባለ አስማታዊ ብልሃት ከባዶ ኪስ ተነስተው በአንድ ሌሊት ከሚልኒየር ተርታ የሚሰለፉ የዘመናችንን ጉዶች ማየት የተለመደ ሆኗል።

ግና በመዲናችን በየመንገዱ ዳር ተገጥግጠው ከሚታዩት በመስተዋት ካሸበረቁት ህንጻዎች ጀርባና በየመንገዱ ዳርና በየጎዳናው ድህነት ጠልፎ እንደ ጉድፍ የጣለውን በርካታ ህዝብ ማየት ያማል። እናም የሀገሪቱን የሁለት ዲጂት ዕድገት ቱልቱላና የሆነውን በማመዛዘን የአዲስ ዓመት ፌሽታ ባይገባው ይደንቃል? እፍረት አልባው መንግስት ሀገራችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ተርታ ተመድባለች እያለ እውን ያልሆነውን ህልም ሊያሳይ ቢሞክርም ዩናትድ ኔሽን ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት በ Multidimensional Poverty Index መሰረት ኢትዮጵያ ከመንግስት አልባዋ ሱማሌ ጭምር ተበልጣ ከመጨረሻው የድሀ አገር ተሰልፋለች። የበለጠችው አገር ኒጀርን ብቻ መሆኑ ነው። “ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም !” እንዲሉ።

በሥራ አጥነት፣ በየተልካሻ ምክንያት ከሥራ በተባረሩ፣ በዘራቸው ሳቢያ በተሰደዱ፣ በሃይማኖታቸውና በፖለቲካ አመላካከታቸው ሳቢያ ለእንግልትና ስቃይ በተዳረጉ በርካታ ቤተሰቦች ባሉበት አገር ደስታን ለማጣጣም እንዴት ህሊና ይቀበላል? ለእውነትና ለህሊናቸው ብቻ ስለቆሙ በአሰቃቂ እስር ቤት ታጉረው ከሚወዱት ቤተሰብ በግፍ የተነጠሉ ወገኖቻችንን አስበልተን ምን አይነት የበዓል ድግስ ይኖረናል??

ሀገራችን ኑሮ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፍትህ ማጣት እንደ ጎርፍ ጠራርጎ ጎዳና ላይ ካወጣቸው እጅግ በላቀ ሁኔታ ለልመና መውጣት አፍረው በየቤታቸው በችግር አለንጋ የሚገረፉት እጅግ እጅግ በርካታ ናቸው፤ ዛሬ ልጆቻውን በቀን አንዴ እንኩዋን ለመመገብ የማይችሉ ቤተሰቦች የተበራከቱበት ሃገር ሆናለች። ታዲያ ዓለምን ያነጋገረው በስደት በየበረሃውና በአረብ ሀገራት  የሚያልቀው ወጣት የሁለት ዲጅት ዕድገት ውጤት ይሆን?

በየቤታቸው በችግር የሚጠበሱትን ወገኖች ካነሳሁ ከጥቂት ወራት በፊት ያጋጠመኝን ልጥቀስ አዲስ አበባ ኡራየል አካባቢ አንዲት አነስተኛ ሱቅ የምፈልገውን ዕቃ በመሸማመት ላይ ነበርኩ፤ እናም ከሁዋላዬ አንዲት በእድሜና በኑሮ ጉስቁልና ወገባቸው የጎበጠ ጠይም እናት ብዙ ደቂቃ መቆማቸው ስለሰቀቀኝ “እናቴ እርሶ ግዙና እኔ እቀጥላለሁ” አልኩዋቸው። ሽቁጥቁጥ በሆነ ትህትና መርቀውኝ ባለሱቁን “ቡና ይኖርሃል?” አሉት

“ቡና አለ! ኪሎ ባለመቶ ሃምሳ፣ ባለምቶ ሃያ ወይም ባለመቶውም ጥሩ ነው . . .” በእጁ እየዘጋገነ ሊያሳየቸው ሞከረ

ዓይናቸው ዓይኖቻችንን የሚሸሹ መሰለኝ፣ ጥቂት አሰቡና “ የአስር ብር አድርግልኝ”

“እማማ አያዋጣኝም…’’

“እንግዲያውስ የሩብ ሩብ ስጠኝ’’ ሀዘን፣ ሸንፈት የኑሮ ድካም በደማቁ ጠይም ፊታቸው ላይ ይነበባል።

“በዚህስ ዘይት ትሸጥልኝ?’’ በፌስታል የያዙትን ትንሽ የዘይት ጠርሙስ አውጥተው እያሳዩት

“እኔ ጋር በችርቻሮ የለኝም። እታች ካለው ሱቅ ይሞክሩ” አላቸው

ተስፋ በቆረጠ መንፈስ “ዘይቱ ቢቀርም ግድ የለም። ብቻ ይቺ ቡና ሱስ  ነው ያስቸገረች . . .’’ አሉና ወገባቸው ላይ ክታሰረችውን መቀነት ፈትተው ብሩን ቆጥረው ከፍለው ሄዱ።

በዓይኔ ተከተልኳቸው ይህ የበርካታ የሀገራችን እናቶች ኑሮ መሆኑን ባውቅም፤ ያለፉትን የኑሮ ውጣውረድ ወለል አድርጎ የሚያሳይ ገጽታቸው፤ ሽቁጥቁጥነታቸው ለልመና እጃቸውን ለመዘርጋት ያልተረታ መንፈሳቸው፤ ነገር ግን ድህነት አንገዝግዞ ሊጥላቸው ያቃረበው የተጎዳ አካላቸው ከፊቴ ላይ እየተጋረጠ ፋታ ነሳኝ .  . . ለምን አንድ ኪሎ ቡና እንኩዋን ሳልገዛላቸው. . . ቁጭት ያዘኝ፤  ደጋግሜ ራሴን ወቀስኩ፤ አሮጊትዋ  ግን ከዓይኔ ርቀዋል።  ባለሱቁን መኖሪያ ቤታቸውን ጠየኩት። አልፎ አልፎ ወደ ሱቁ እንደሚመጡ ቤታቸውን ግን እንደማያውቀው ነገረኝ። በሌሎቹ ቀናት ደጋግሜ ባለሱቁን ብጠይቀውም አይቶአቸው እንደማያውቅ ነገረኝ። ለባለሱቁ ይህ ደጋግሞ የሚያየው የህይወት ትዕይንት ስለሆን ቁብ አልሰጠውም።

እንግዲህ “ሁለት ዲጂት…” ይህን መሰል የበርካቶችን ህይወት ያለመዳሰሱ ቀልድ ህሊናን ይኮሰኩሳል? በየመንገዱ በጠኔ በህመም ወድቆ በአደባባይ ያለምንም ረጂ ሊሞት የሚያጣጥር ወገን እንደ ዋዛ ማየት በተለመደበት አገር፤ ከየመንገዱ የበቀሉ ደሃውን በግፍ አፈናቅለው በበቀሉ ህንጻዎች መመዘኛ ዕድገትን መለካት ፌዝ ነው። የለየለት ቧልት ነው። በየመንግስት ትምህርት ቤቱ ደጃፍ ብትቆሙ ርሃብ ጉስቁልና እንደለበሱት ልብስ አመድ ያስመሰላቸው ልጆችን በመቶ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠር ታያላችሁ። ከዚህ ሁሉ የኑሮ ቀዳዳ ጥቂቱን አለመድፈን ደግሞ ሌላ ስቃይ ነው። በአንዲት ትንሽ ብልቃጥ ለምትለካ መጠጥ ብቻ 2 እና 3 ሺህ ብር በመክፈል በየዕለቱ ሸራተን በመሳሰሉ ትላልቅ ሆቴሎች በዘረፉት ገንዘብ የሚምነሸነሹ የሞሉበት አገር መሆኑ ደግሞ የአገሪቷ ሥርአት ለመኮላሸቱ ሌላው ማሳያ ነው። በየኮንፌሽየስ  እንደተገለጸው በመጥፎ አስተዳደር ስር በሚገኝ አገር የጥቂቶች ብልጽግና የሚያሳፍር ነው። ሰሞኑን የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ኑሮ ጠንቆች ሲል ባስጠናውና ይፋ ባደርገው መረጃ መሰረት ከሚልዮን የሚልቁ በልመና የሚተዳደሩ አሉ። እውነታው ከዚህም ይከፋል።

ይባስ ብሎ የመጨረሻ በሌለው ድህነት ተውጠን  አንድ  ቁጥር ዘረኛና አምባገነን ስርአት የተጫነብን ምን ፍርጃ ነው ያሰኛል። ኢትዮጵያን በዘር ፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ከፋፍሎ የህዝቡን አንድነት ለማጥፋት የሚጥረውን አገዛዝ መቃወም ደግሞ “አሸባሪ’’ የሚል ታርጋ አስለጥፎ ዘብጥያ ያስወረውራል። በወያኔ እኩየ ስራዓት የህግ የበላይነት የለም፤ ዲሞክራሲ ተደፍጥጡዋል፤ የደህንነት ዋስትና የለም፤ ነፃ ፕሬስ ተረት ሆኗል፣ የብዙሃን ፓርቲ ያልምንም እፍረት ተገፍትሮል። የሲቪክና ሙያ ማህበራት የማሽመድመዱ ተግባር ተከናውኗል።

ይለቁንም ዘረኞች ግፈኞች፣ ወንጀልኞች፣ አምባገነኖች፣ ሙሰኞች እንዳሻቸው ዛሬም እየፈነጩ፤  በተቃራኒው ፍትህና እኩልነት ለህሊናቸው፣ የሚታገሉና የሚዋረዱበት፣ የሚሰደዱበት የሚታስሩበት አገር መሆኑ ያስቆጫል።

በርግጥ የታፈኑ ብሶት ገንፍሎ የነጻነት ደማቅ ፀሐይ የምናይበት ጊዜ እንደሚመጣ ቅንጣት አልጠራጠርም። ያኔ በርግጥም ክረምቱ ያልፋል፣ ምድሪቱም በነጻነት ጸበል ይለመልማል፤ ሰማያችን ከክፉ የዘረኝነት ዳመና ይጠራል። ከተራራ ተራራ “አበባ አየሆሽ” ዜማ ይናኛል።

“የእማምዬን ቤት

ወርቅ ይዝነብበት

የአባብዬን ቤት

ወርቅ ይዝነብበት” በርግጥም ትርጉም ይኖረዋል። መልካም ዘመን ያምጣልን። አሜን!!

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop