August 4, 2013
4 mins read

የመቀሌ ሕዝብ የመሰብሰብ መብቱ ተረገጠ !ከሰሜን አሜሪካ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ግብረ ኋይል

አቶ ደምሴ መንግስቱ የአንድነት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕግና ሰባአዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፣ አቶ እንግዳ ገብረጻድቅ የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት አባል፣ እንዲሁም አቶ የማነ የድርጅት ጉዳይ ኮሚቴ አባል ፣ የአንድነት ፓርቲ በመቀሌ ሊያደርግ የነበረዉን ሰልፍ ለመምራትና ሕዝቡን ለመቀስቀስ፣ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት፣ በፖሊሲ ታግተዉ፣ ከመቀሌ አሮፕላን ማረፊያ አጠገብ በምትገኘዉ የኩያ ከተማ፣ ቀኑን ሙሉ እንዳይንቀሳቀሱ ከተደረጉ በኋላ ማማሻዉን ሐምሌ 26 ቀን እንደተለቀቁ ከስፍራዉ የደረሰው ዜና ያመለክታል።

ትላንት ሐምሌ 27 ቀን አቶ እንግዳና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሌሎች ሁለት አመራር እንደገና በጠዋቱ የታሰሩ ሲሆን፣ የአንድነት ፓርቲ የሚቀሰቅስባቸው መኪናዎች ላዉድ ስፒከሮች የመሳሰሉት በሙሉ በፖሊሲ ቁጥጥር ሥር ዉለዋል። በመቀሌ ማናቸውም አይነት ቅስቀሳ እንዳይደረግ እየከለከለ ሲሆን፣«እንኳን አንድነት ቅንጅትም መቀሌን አልደፈረም»በሚል ፍጹም አምባገነናዊነት፣ የመቀሌ ሕዝብ አማራጫ እንዳያገኝ፣ የመሰለዉንና የመረጠዉን እንዳይደግፍ፣ ድምጹን እንዳያሰማ በሃይልና በጉልበት እየተከለከለ ነዉ።

የትግራይ ሕዝብ አምባገነናዊ የደርግ ስርዓት ለመጣል ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈለ ይታወቃል። ነገር ግን የብዙ ትግራይ ልጆች መስዋእተንት እንደ ከንቱ ተቆጥሮ፣ አሁንም በሕዝቡ ላይ « እኛ የምንፈቅድልህን ብቻ ነዉ መናገር ያለብህ። ከኛ ዉጭ ሌላ አማራጭ አያስፈልግህም። እኛ ስንጠራህ አደባባይ ዉጣ። ከኛ ዉጭ ያሉ ቢጠሩህ ግን መዉጣት አይፈቀድልህም» እየተባላ፣ የፈለገዉን የመምረጥ፣ የፈለገዉን የመደገፍ፣ የፈለገዉን የመከተል መብቱ ተረግጦ፣ በዳግማዊ ደርግ አገዛዝ ሥር መሆኑ በይፋ እየታየ ነዉ።

ሐምሌ 27 ቀን ማምሻዉን፣ የአንድነት የሚሊዮን ድምጽ ለነጻነት ግብረ ኃይል በዚህ ሁኔታ በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍን ማድረግ በጭራሽ የማይቻል በመሆኑ፣ ሃይልን የበለጠ አሰባስቦ፣ በተጠናከረ መልኩ፣ በሌላ ጊዜ በቅርቡ ሰልፉ እስኪደረግ ድረስ፣ የዛሬዉ ሐምሌ 28 ቀን የመቀሌ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተላለፈ ገልጿል።

የአንድነት ፓርቲ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ፣ በመቀሌ ሰልፍ የሚደረግበትን ቀን እንደሚያሳዉቅ የገልጸ ሲሆን፣ ሕዝቡ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን፣ ገዢዎች የሚሰጡት ሳይሆን፣ እራሱ ታግሎ የሚያመጣው እንደሆነም አስረድተዋል።

ሰላማዊ ሰልፎች በአዲስ አበባ፣ በደሴና በጎንደር የተደረጉ ሲሆን፣ በአርባ ምንጭ ፣ በባህር ዳርና በጂንካ በተሳካ ሁኔታ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በሁሉም የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ሰልፎችን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ሙከራ ማድረጋቸው ይታወቃል። በመቀሌ ግን የታየው የክልሉ አስተዳዳሪዎች ምን ያህል ለመቀሌ ሕዝብ ንቀት እንዳላቸዉና አምባገነናዊ መሆናቸውን ነዉ።

ከሰሜን አሜሪካ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ግብረ ኋይል

Go toTop