የቫንኩቨር ኢትዮጵያዊያን ተደስተዋል – ቤተክርስቲያናቸው ቋሚ ቤተመቅደስ አግኝታለች

በጥቅምት 2009 ዓ.ም. የብሪቲሽ ኮሉምቢያ ጠቅላይ ፍርድቤት በ1990ዎቹ መጀመሪያ በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ቤተክርስቲያን ስር፡ በነአቡነ ዜናማርቆስ ቡራኬ የተመሰረተውን የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርትስቲያን አንስቶ ወደኢህአዴግ ለሚያጋድለው ስብስብ እንዲሰጥ ሲወስን፡ በስደተኛው ሲኖዶስ ስር የሚገኙ የቫንኩቨር ማርያም ልጆች አዝነው ነበር። የፍርድቤቱ ክርክር ሂደት በወቅቱ በኢትዮጵያ ዛሬና በሌሎች ድረገጾች ላይ ተዘግቧል።

ልምዱ ለሌሎችም ይጠቅም ዘንድ ወደፊትም እናትትበታለን።

ከዚያ አሳዛኝ የፍርድ ቤት ውሳኔ በሁዋላ የተራረፉት ምእመናን ተሰብስበው ህብረታቸውን አጠናክረው በመቀጠል፤ በሂደቱ አንዳንድ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙም፤ እነሆ ከብዙ እንግልትና ትጋት በሁዋላ፤ ከስፍራ ስፍራ፤ ከአዳራሽ አዳራሽ ስትንከራተት የነበረችው ቤተክርስቲያን ማረፊያ ቤተመቅደስ አግኝታ፤ በነገው እለት፤ ማለትም እሁድ ኦገስት 4 ቀን፤ 2013 ዓ.ም. አዲሱ ቤተመቅደስ በይፋ ትውውቅና ምረቃ ይደረግበታል።

ይሄንን የ100 በላይ እድሜ ያለውንና በጥንታዊቷ የብሪቲሽ ዋና ከተማ፡ ኒው ዌስትሚኒስተር፡ በ628 ሮያል መንገድ ላይ የሚገኘውን ቤተመቅደስ በቫንኩቨር፡ ካልጋሪ፤ ሲያትል፤ ፖርትላንድና አካባቢው የሚገኙ ምእመናን ተገኝተው ምረቃ ያደርጉለታል።

በእለቱ 3ኛው የቫንኩቨር ኢትዮጵያ ፌስቲቫልና የምእራብና ሰሜን አሜሪካ ከተሞች የእግር ኳስ ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን፡ ለፌስቲቫሉና ለእግርኳስ ጨዋታ ውድድሩ ከጎረቤት አገሮች የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ለቤተመቅደሱ ምረቃ በዓል ድምቀት እንደሚሰጡት ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ፤ በቤተመቅደሱ መገኘት የተደሰቱና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የቤተክርስቲያኒቷ የረጅም ግዜ አባል፡ በስደት የሚገኘው ሲኖዶስም ይሁን የአገረስብከቱ ሊቀጳጳስ ተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢጻፍላቸውምና በበአሉ ላይ ተገኝተው ቡራኬ እንዲሰጡ ቢጋበዙም፤ እስካሁን ድረስ ምላሽ አለመስጠታቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

ምእመኑ ቫንኩቨር በካናዳ የምትገኝ ከተማ ብትሆንም አንድ ቀን ከሚያስጉዘው ከካልጋሪ ይልቅ ሁለት ሰዓት ለምትርቀው ሲያትል ስለምትቀርብ የቤተክርስቲያናቸው ሰበካ ወደሲአትል ዋሽንግተን እንዲጠቃለል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በጢስ አባይ ውጊያ ከተማረኩ ሁለት አዛዦች ጋር የተደረገ አጭር ቆይታ

 

Share