ዓይናለም ኃይሉ፣ አዲስ ህንጻና ጀማል ጣሰው ኢትዮጵያ ላለባት ወሳኝ ጨዋታ አይሰለፉም

(ዘ-ሐበሻ) ኦገስት 9 ቀን 2013 በኮንጎ ብራዛቪል ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክንን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቅጣት የተነሳ ወሳኝ ተጫዋቾን እንደማያሰልፍ የፊፋ ድረ ገጽ ዘገበ። እንደ ድረገጹ ዘገባ ከሆነ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በኮንጎ ብራዛቪል ላለባት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አይናለም ሀይሉን፣ አዲስ ህንጻንና ጀማል ጣሰውን እንደማታሰልፍ ድረገጹ ዘግቧል።

እንደ ድረገጹ ዘገባ ከሆነ እነዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋቾች የማይሰለፉት በማጣሪያ ጨዋታዎች ካርድ በማየታቸው ሲሆን በጨዋታው የማይስለፉ ተጨዋቾችን ለመተካት ለብሄራዊ ቡድኑ ከባድ ፈተና እንደሚሆን የሃገሪቱ የስፖርት ጋዜጠኞች እየተቹበት ነው። መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሀገሯ ያለውን አለመረጋጋት ምክንያት በማድርግ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ በኮንጎ ብራዛቪል እንዲሆን ፊፋ መወሰኑን ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም የዘገበች ሲሆን በዚህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሸነፍ ካልቻለ የተፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ ያጣል። ደቡብ አፍሪካና ቦትስዋና በሚያደርጉት ጨዋታ አቻ ከተለያዩ በቀጥታ ኢትዮጵያ ማለፍ የምትችል ሲሆን ከሁለት አንዱ አሸንፈው ኢትዮጵያ ከተሸነፈች ወይንም አቻ ከወጣች ከውድድሩ ትሰናበታለች።

መልካም ዕድል ለዋሊያዎቹ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦሮሞ ብልፅግና ውስጥ ያሉ ብዙዎቹ ከኦነግ ጋር የሚሰሩ ክኦነግ ጋር ድርድር እንዲደረግ የሚፈልጉ ናቸው - ግርማ ካሳ
Share