*ውህደቱ ከሰመረ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ
(መኢአፓ) የተባለ አዲስ ፓርቲ ሊፈጠር ይችላል
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የመኢአድ ፕሬዚዳንትነቱን ለወጣት አስረክበው የወረዱት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውልየመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)ን ለማዋሐድ ተቋርጦ የነበረው ውይይት ለመጀመር እየተሞከረ ነው። የውህደቱን ሂደት የሚመሩ ከየፓርቲዎቹ ሦስት ሦስት አባላት ያሉበት የውህደት አመቻች ኮሚቴ እንዲቋቋም በመርህ ደረጃ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ቀደም ሲል ሁለቱ ፓርቲዎች ለማዋሐድ አመራሮቹ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሌሎች ሀገር ወዳድ ምሁራን ጋር በመሆን በኢንጂነር ኃይሉ መኖሪያ ቤት ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ምክክር ሲደረግ መቆየቱን አንድ የአንድነት ከፍተኛ አመራር በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልፀዋል። ነገር ግን የሁለቱ ፓርቲዎች ድርድር አንድነት በመድረክ ውስጥ በመሳተፍና መኢአድ መድረክ በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች ስብስብ በመሆኑ መኢአድ ከፓርቲዎቹ ጋር የፕሮግራም ልዩነት እንዳለው በመግለፁ ድርድሩ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል። በመቀጠልም ባለፉት ሁለት አመታት መኢአድ በውስጥ ችግር በመቆየቱ ሁለቱን ፓርቲዎች የመዋሐድ ሐሳቡ ሳይንቀሳቀስ ቆይቷል።
ሆኖም ሰሞኑን መኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ ፕሬዝዳንት ከመረጠ በኋላ ተቋርጦ የነበረው ፓርቲዎቹን የማዋሐድ ኀሳብ እንደገና መንቀሳቀስ መጀመሩን ለሁለቱም ፓርቲዎች ቅርበት ያላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል ‘‘33ቱ ፓርቲዎች’’ ጋር አብሮ ለመስራት የነበረው ሂደትን ሰማያዊ ፓርቲ ለብቻው ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራቱ በሌሎች ፓርቲዎች በኩል መጠነኛ ቅሬታ በመፍጠሩ አሁን ሁለቱን ፓርቲዎች በማዋሐድ ትግሉን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ምንጫችን ጠቁሟል።
አንድ የመኢአድ ከፍተኛ አመራር ሁለቱ ፓርቲዎች በቅንነት ከተንቀሳቀሱ አዲስ ውህድ ፓርቲ መፍጠር እንደሚችሉና ከሁለት አመት በኋላ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ጠንካራ ሆነው ሊወጡ እንደሚችሉ ገልፀዋል። ውህደቱ ከሰመረ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ (መኢአፓ) የተባለ አዲስና ጠንካራ፣ ፓርቲ መመስረት እንደሚቻልም ግምታቸውን ገልፀዋል።
አስራት ጣሴየአንድነት ፓርቲ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ጣሴ ጉዳዩን በተመለከተ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ ቀርቦላቸው ‘‘ጉዳዩን ማንም የነካካው የለም’’ ካሉ በኋላ በመርህ ደረጃ ፓርቲዎቹን ለመዋሐድ የተጀመረው ጥረት እንደሚቀጥል ግን ተስፋቸውን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ አቶ አስራት ‘‘ጉዳዩን የነካካው የለም’’ ቢሉም ሰሞኑን በመኢአድ ጽ/ቤት መገኘታቸውን በተመለከተ ተጠይቀው በቀጣይ 33ቱ ፓርቲዎች ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከመኢአድ አዲሱ አመራር ጋር ለመወያየትና አዲሱን የመኢአድ ፕሬዝዳንት እንኳን ደስ አለህ ከማለት ባለፈ በጉዳዩ ላይ በኮሚቴ ደረጃ ውይይት አለመጀመሩን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የመኢአድ አዲሱ ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሓሪ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አቶ አስራት ጣሴ በፓርቲው ጽ/ቤት ተገኝተው ሁለቱ ፓርቲዎች በሚዋሐዱበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውይይት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።n
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ የረቡዕ ጁላይ 30 ቀን 2013