የዘመኑ መንፈስ (በእውቀቱ ስዩም)

ባገራችን ባሁኑ ጊዜ ብዙ ተከታይ ያለው ሃይማኖት ብሄርተኝነት ይባላል፡፡የብሄርተኝነት ምእመን ከሆንክ የነፍስ አባት ይኖርሀል፣በጭፍን የምትቀበለው ቀኖና ይኖርሀል፣ነገ የምትገባባት የተስፋ ምድር ይኖርሀል፣ከሁሉ በላይ ደግሞ ብርቱ ችግርህን የምትደፈድፍበት የመስዋእት በግ ይኖርሀል፡፡

ሃይማኖቶች ምእመናንን ብቻ ሳይሆን መናፍቃንንም ያፈራሉ፡፡ብሄርተኞች በስሜት የሚነድደውን ምእመን ብቻ ሳይሆን የኔ ቢጤውን መነፍቅም እንደሚያፈሩ አንርሳ፡፡በነገራችን ላይ ሃይማኖትን መካድ ማለት ሃይማኖት የሚያነሳቸውን አብይ ጥያቄዎች መካድ ማለት አይደለም፡፡እንዲሁም፣ ብሄርተኝነትን መካድ ማለት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ህልውና መካድ ማለት አይደለም፡፡በዚህ ጉዳይ ፣መናፍቅ መሆን ማለት፣ የብሄርተኛ ነቢያት ሰለ ጭቆና ስለ ነጻነት ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቡትን አጉል እምነት መጠራጠር ማለት ነው፡፡

ከኢትዮጵያዊነት እንጀምር፡፡

ከዘመናችን የብሔርተኝነት ነቢያት አንዱ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ከእንቁ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ላይ ስለኢትዮጵያዊነት የሚከተለውን ይላል፡፡

‹‹…ኢትዮጵያን የመሠረታት የሶሰትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡በአማራው፣በኦሮሞው፣በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭት እና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡…የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው››

ጃዋር የኢትዮጵያን መሠረት የሦስት ብሄረሰቦች የስልጣን ግብግብ አድርጎ ወስኖታል፡፡ በመጀመርያ፣ ሌሎች ብሄረሰቦች በግብግቡ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ

Bewketu Seyoum is a young Ethiopian writer
በእውቀቱ ሥዩም
ጉድለት ነው፡፡ ግን ዋናው ቁምነገር ይሄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ውጤት ብቻ እንደሆነች አድርጎ ማቅረቡ ነው ትልቁ ስሕተት፡፡ ሲጀምር፣ የግብግብ ታሪክ መሠረት ይንዳል እንጂ መሠረት አይገነባም፡፡ እንደኔ ግምት፣የኢትዮጵያ መሠረት የሆነው ብሄረሰቦች ለጋራ ሕልውና ሲሉ የሚያደርጉት የመደጋገፍ ታሪክ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ፣ ታሪክ ከላሾች፣የብሄሮችን የ‹‹ግብግብ››ታሪክ ሞቅ አድርገው፣አኳሽተው ሲጽፉ፣የብሄሮች መደጋገፍ ታሪክን ግን ቸል ይሉታል፡፡ አለያም እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት፣ በጥቂት መስመሮች ብቻ ጨረፍ አድርገው ያልፉታል፡፡ለነገሩ፣ከፋፋይነትን ብቸኛ ያስተዳደር ፈሊጥ አድርጎ የሚቆጥር ሰው በታሪክ ገጾች ውስጥ መመልከት የሚፈልገው ክፍፍልን ብቻ ነው፡፡ታሪክ ግን ብዙ በጎ የትብብር ገጠመኞችን መዝግቧል፡፡ለምሳሌ ጀግናው አጼ ዮሐንስ አራተኛ በበዛሬይቱ ኤርትራ የግብጽን ወራሪ ጦር ድል የነሡት የትግራይ ጀግኖችን ብቻ አሠልፈው አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ከግብጽ ጎን ሆኖ፣የተዋጋው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይ እንደመሠከረው ወልቃይቶች፣ጥልጣል የተባሉ የአፋር ንኡስ ክፍሎች፣የወረኢሉ ኦሮሞዎች ለንጉሰነገስቱ ድጋፍ ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡በራስ ወሌ የሚመሩ የአማራ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡የጎንደር ቀሳውስት ለጦርነቱ ድጋፍ ለማድረግ አድዋ ገብተዋል፡፡ የጎጃሙ ራስ አዳል የደርሼልሀለሁ አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡ የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ በቅሎዎችንና ማበረታቻ ልከዋል፡፡ ዝርዝሩን ማንበብ ለሚፈልግ Muslim Egypt Christian Abyssinia የተባለውን የዚህ ደራሲ ማስታወሻ ገጽ 291-292 ያንብብ፡፡ መጽሐፉን በኢንተርኔት ቤተ-መጻህፍት ውስጥ በብላሽ ማግኘት ይቻላል፡፡

ከተለያየ መአዘን የመጡ እኒህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ቃላት ይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊ ባህል እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹‹የአማራ ባህል ››ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለው አይመስለኝም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:   የተመድ የሠላም አስከባሪ ኃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ይግባ!!! ሀርማ ሙራ! ሀርካ ሙራ! ኖርሜ ሙራ!  ከመጠምጠም ትምህርት ይቅደም!

ጃዋር‹‹አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች›› በማለት ሳይወሰን ‹‹የኢትዮጵያ አገራዊ መለያ ማንነት የምንለው አማራ ብሄራዊ ማንነት ነው›› ሲል ይጨምራል፡፡ ጎበዝ ኧረ በህግ አምላክ!!! የኢትዮጵያ ባህልኮ ካንድ አለት የተጠረበ ሕንጻ አይደለም፡፡ ከብዙ የመዋጮ ጡቦች የተገነባ ነው፡፡ ጃዋር እያንዳንዱን ጡብ ቀርቦ ቢመረምረው እዚህ የደረሰበት እርግጠኝነት ውስጥ የሚደርስ አይመስለኝም፡፡

እስቲ ከደቃቅ ምሳሌ እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡና ስነ-ስራታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም ፣ባለሹርባ ሴት፣ያበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስል በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ይህ ችክ ያለ ምስል በስነ-ስእል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቢዮንሴና ጆን ኬሪ አገራችንን በጎበኙበት ሰአት የቡና ስነስርአት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡና ስርአታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው፡፡ ለዋለልኝ መኮንን እና ለጃዋር መሀመድ ይህ የአማራ ባህል መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ እይታ ይመስላል፡፡ ጉዱ ዝርዝሩ ላይ ነው፡፡ የሴትዮዋ ሹርባ ከሐማሴን ወይም ከተንቤን ሴቶች ልማድ ጋር ስምም ነው፡፡ ያበሻ ቀሚሱን የሽሮሜዳ ጋሞ የሸመነው ሊሆን ይችላል፡፡ ጀበናው የጂማ ሙስሊም ኦሮሞዎች ያስተዋወቁት ነው፡፡ አቦል ቶና በረካ አረብኛ ወይም የተወላገደ አረብኛ የተገኙ ቃላት ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ትንሳኤ በአል በሉባንጃ የሚታጀብ ቡና የማያፈላ ክርስትያን ኢትዮጵያዊ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከጥቂት መቶ አመታት በፊት ግን ቡና የእስላም ልማድ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ የቡና ትርኢት የሙስሊም አበው በኢትዮጵያ ባህል ላይ የጨመሩት በጎ መዋጮ እድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ጊዜ በተባለው አናጢ ከብዙ ጡቦች የተገነባች ናት የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ጃዋር አማራው የራሱን ባህል በኦሮሞው ላይ እንደጫነ ሲያምን ተገላቢጦሹ ያለው አይታየውም፡፡ ኦሮሞ በረጅም ዘመን፣በሠፊ ምድር፣ ሰፍሮ የመኖሩን ያክል በጎረቤቶቹና በወደረኞቹ ላይ የባህል ተጽእኖ አላሳደረም ማለት ብርቱ ባህል የለውም ከማለት አይለይም፡፡ ባገራችን ዋና ዋናዎቹ የባህል ቀራጺዎች ጦርነትና ሐይማኖት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፣ጀግኖችን እና ነገስታትን አባ በዝብዝ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው አባ ነጋ ወዘተ እያሉ መሰየም ገናና ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን የማናውቀው ይህንን ባህል ያስተዋወቁት ለግማሽ ምእተአመት ያክል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ቼ በለው በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እንዲህ በማለት ያረጋግጣሉ-

‹‹ነገስታቱ በ‹‹አባ›› ወይም የእገሌ ባለቤት በሚል ቅጽል ስም መጥራት የጀመሩት የኦሮሞዎችን ወይም የወረሸሆችን ልምድ በመከተል ነው ከ1838 ዓም ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ወትሮ ግን በተለይም 1474-1713 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ቅብዓ መንግሥቱ በሚደረግላቸው ሰአት ይወጣላችው የነበረው የግርማ ስም ወይም ስመ መንግስት ‹‹ሰገድ›› የሚል ኃይለቃል በመጨመር እንደነበር ቀጥሎ ያለው ያረጋግጣል፡፡ ወናገድ ሰገድ፣ አጽናፍ ሰገድ፣ አድማስ ሰገድ፣ መለክ ሰገድ፣አድያም ሰገድ ሉል ሰገድ››በማለት ይዘረዝራሉ፡፡

ከጥቅሱ ሦስት ፍሬ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡

1- ይህ ባህል ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመነጨ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያበባው ታደሰ ጥድፊያ፤ ገዳይ ቢዘገይ ሟች ይገሰግሳል

2- ባህሉ ብርቱ ተጽእኖ ከመፍጠሩ የተነሳ አማራና ትግራይ ነገስታት ለረጅም ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውን የስያሜ ዘይቤ ሽሯል፡፡

3- አማራው ታሪክ ጸሀፊ ለባህሉ አስተዋዋቂዎች የባለቤትነት እውቅና ሰጥተዋል፡፡

በሃይማኖት ረገድም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ አቴቴ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድ ሲተረጉሙ ‹‹ዛር፣በሴት ስም የምትጠራ፣ ውቃቤ ፣ አማሮች ከኦሮሞዎች የወረሷት ጨሌ የሚያጠልቁላት አቴቴ ጊንቢ ሐራ አቴቴ ዱላ እያሉ እንቀት የሚቀቅሉላት አምልኮ ባእድ፣ትርጓሜ ጠባቂ ማለት ነው››ይላሉ፡፡

‹‹አምልኮ ባእድ ››የሚለውን አሉታዊ ሐረግ፣የክርስትያን አድልኦ ያለበት ፍርድ አድርገን እንለፈው፡፡ ዋናው ፍሬ ነገር፣ የአሮሞው ባህል በአማራው ባህል ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ማወቃችን ነው፡፡ ይህም አንዱ ብሄረሰብ ሁልጊዜ ጫኝ ፣ ሌላው ብሄረሰብ ሁልጊዜ ተሸካሚ እንደነበረ አድርገው ሊነግሩን የሚፈልጉትን ሰዎች ያስተባብላል፡፡ በሁለቱ ግዙፍ ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ግኑኝነት የእኩዮች ልውውጥ ነው፡፡ የባህሎች ውርርስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የማንኩሳ ዘመዶቼ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥማቸው ‹‹አቲቲን ወሰድከው›› ይላሉ፡፡ ቀልቤን ገፈፍከው ለማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ተጽእኖ በወለጋ ድንበር ላይ ቆሟል ያለው ማነው?

ስለጉዲፈቻ ባህል ብዙ ሰዉ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ በጦርነት ወቅት ምርኮኞችን ባርያ ማድረግ ወይም መግደል በብዙ ማህበረሰቦች የተለመደ ነው፡፡ በኦሮሞ አበዋዊ ባህል ውስጥ ግን ምርኮኞች በልጅነት ይታቀፋሉ፡፡ ከሌላ ብሄረሰብ ቢመጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጋቸው ያድጋሉ፡፡ ይህንን ልማድ በአማራው ማህበረሰብ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በጎጃሙ ንጎስ ተክለይማኖትና በወለጋ መሳፍንት መሀል በተደረገው ጦርነት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራን እንደልጅ አሳድገውታል፡፡ ክርስትና አስነስተው ተክለኢየሱስ አሰኝተውታል፡፡ ራሱ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በጠጅና በስጋ አደግሁ›› በማለት የመሳፍንት ልጆች ያገኙት የነበረውን ምቾት ሳይነፈገው ማደጉን ይመሰክራል፡፡ ነገሮ ፣ ከማእረግ ወደ ማእረግ እየወጣ የንጉሱ ጸሐፌ ትዝዛዝ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ተመሳሳይ መልኩ በሸዋ ምርኮኛው ቆሴ ዲነግዴ በቤተመንግስት እየተቀማጠለ አድጎ ሐብተጊዎርጊስ በሚል ስመ ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ምኒስትር እስከመሆን ደርሷል፡፡ ሰዎችን በልዩ ቋንቋቸው ምክንያት ባይተዋር ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡

እኩዋን ባህላችን አማርኛችን እንኳ የጉራማይሌነታችን ምስክር ነው፡፡ አሁን ኦሮምኛ ያልተነካካ አማርኛ ማግኘት ይቻላል?፡፡ እሰቲ ለናሙና ያክል ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከተባለው የዮሐንስ አድማሱ ምርጥ የአማርኛ ግጥም ውስጥ ጥቂት መስመሮች ልቆንጥር፡፡

1) ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ

2) ሜዳና ተራራ በመሐል ሸለቆ
ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ

3) ሐቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ
ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ

4) ብልጭ ብሎ ጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ

በመረጥኳቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙት ‹‹ይፋ፣ ጨፌ፣ መልቲ፣ ሎቲ፣ አንጋፋ፣›› የተባሉት ቃላት ኦሮሚኛ ናቸው፡፡ ካንድ የአማርኛ ግጥም ይህን ያህል ኦሮሚኛ ከተገኘ በሙሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ምን ያህል ሊገኝ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን ያክል ነው የተዋሀድነው፡፡

የኢትዮጵያ ባህል የተውጣጣ ባህል እንጂ ጃዋር እንደሚለው የአማራ ባህል ብቻ አለመሆኑን በመጠኑም ቢሆን ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ ጃዋርን እዚህ ላይ ላሰናብትና ለማጠናቀቂያ የምትሆን አንዲት አንቀጽ ልጨምር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወገኖቻችንን ለዘመናተ የጨረሰው አደገኛው ዘንዶ፡-የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት - ሰርጸ ደስታ

ባህልን ማክበር ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስሜት ሚነድደው የብሄርብሄረሰብ ፖለቲካችን፣ ዜጎች ለባህል ያላቸውን ፍቅር ወደ ጭፍን አምልኮአዊ ፍቅር እያዘቀጠው ነው፡፡

ባባቶቻችንና በእኛ መካከል የባህል ፋይዳ ልዩነት ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶች ባህላቸውን ያገኙት በኑሮ ጣጣ አስገዳጅነት ነው፡፡ ለምሳሌ የኔ አያት ቁምጣ ሱሪ የሚታጠቀው ከሌሎች ብሄረሰቦች ለየት ብሎ ለመታየት አይመሰለኝም፡፡ በቂ አቡጀዲ ስላላገኘ ነው፡፡ ወይም ለስራ እንዲያመቸው ባጭር መታጠቁ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ቁምጣ ለብሼ ራሴን በማስጎብኘት እንድኮራ ይጠበቅብኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!!! ጋቢ በጥንት ጊዜ የሙቀት ምንጭ ነበር፡፡ ዘንድሮ የኩራት ምንጭ ሊሆን ይቃጣዋል፡፡

የዛሬዎቹ ባህል አምላኪዎች ባህል ሲያስቡ ለውጥን ይረሳሉ፡፡ ባንድ ወቅት የሚያኮራው ያንድ ብሄረሰብ ባህል በሌላው ወቅት ይናቃል፡፡ ባንድ ወቅት የሚያስሸልመው በሌላ ጊዜ ያስቀጣል፡፡ ከጥቂት መቶ አመት በፊት ዝሆን መግደል በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚያጎናጽፍ ተግባር ነበር፡፡ ዝሆን የገደለ ልዩ አምባር ክንዱ ላይ ያጠልቃል፡፡ እስኪ ዛሬ ያባቶቼን ባህል ለማክበር ነው ብለህ ፓርክ ውስጥ አርፎ የተኛውን ዝሆን ግደል፡፡ በአምባር ምትክ ካቴና ይጠልቅልሀል፡፡

የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት የተባለውን የተደጋገመ ግን ያልታሰበበት ቃል ከዚህ አንጻር ቃኙት፡፡ ሲጀምር ፣ዛፍ እንኳ ቅርፊቱን በሚቀያይርበት ዓለም፣ብሄር ብሄረሰቦች በየጊዜው አልባሳታቸውን አይቀያይሩም ወይ?፡፡ የብሄረሰቡ አልባስ ሲባል በየትኛው ዘመን የሚለበሰው ነው? የእንዳለጌታ ከበደ እናት ሲነግሩን፣ ዛሬ በጉራጌ ዘፈን ላይ በቲቪ የምናየው የሴቶች ሻማ ቀሚስ በደርግ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ሸማ ነው፡፡ ከሸማው በፊት ደግሞ የቆዳ ቀሚስ ይለበስ ነበር፡፡

ሌላው፣ አንድ ማህበረሰብ አልባሳት በየማእረጉ ልዩ ልዩ ልብሶች ይኖሩታል፡፡ ወታደሩ ያባ ገዳውን ልብስ የሚለብስ አይመስለኝም፡፡ ባሮች ከጌቶች ልብስ ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንዲለብሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ በፊውዳል ማህበረሰብ ከላይ አስከታች መልበስ መከናነብ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ይህንን በሸዋና በትግራይ ብቻ ሳይሆን በቅድመ ምኒልክ ከፋ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ባንጻሩ፣ባሮች በከፊል ተራቁተው መታየት አለባቸው፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አለባበስ በበሄረሰብ ላይ ሳይሆን በመደብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የብሄር አልባሳት የሚባለው እንደ ማንኛውም ሾላ በድፍን ሐሳብ በጥርጣሬ መታየት አለበት፡፡

ትውልዱ የባህል ፈጣሪ መሆን ሲገባው፣የባህል ሙዚየም ሆኖ ተተክሏል፡፡አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ባንድ ወቅት እንዳለው ‹‹ካባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ፣ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል››

ማሳረጊያ

ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ያቆያት የነገስታቱ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያ የተሸመነችበትን ውስብስብ ክር ማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያን በታትነን ክልላችንን እናድናለን ብለው ባደባባይ ሳያፍሩ የሚናገሩ ሰዎችን የምናይበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ማእበል ከበረታባት እንደ ታይታኒክ ትሰጥም ይሆናል፡፡ግን መርከቢቱ ስትሰጥም የመርከቢቱ ሳሎን ብቻውን አይንሳፈፍም፡፡የመርከቢቱ ጓዳ ብቻውን አይተርፍም፡፡ኢትዮጵያ ስትከስም ብሄሮች ተነጥለው ይለመልማሉ ማለት ተፈጥሮ አመሏን እንደ ግትቻ የትም ጥላለች ማለት ነው፡፡

18 Comments

  1. ሥዩመ እውቀት በለው! ያልነበሩ ያልጠፈጠሩ ያልታወቁ ግን እኛ (ወያኔ/ህወአት/ኢህዴግ)ጨፍልቆ የሰራቸው “በአብዮታዊ ዲሞክራሲ”የተጠመቁ የብሐየር ብሔረሰብ እና መሬት በመግዛትና በመከራየት ባሌት የሚሆኑ (ሕዝቦች) ሲሳሳቅ ኢረገዛል ግን ማን ያዋልዳል ምን አልባት ያስወርዳል፣ይመክናል የጨነግፋል ለመሆኑ ብሐር ብሔረሰብ ተርፎ መርከቡ ይሄዳል ወይንስ ብሀሀር ብሔረሰብና መርከቡ ሰምጦ ተመልካቹ ይተርፍና ይስቃል?ኦሮሞን ለአክራሪ ሙስሊም ለመጀወር የተነሱ መልዕክተኞች(ጃዋሪያን) እንዳትሸጥ ተጠንቅቅ በለው!

  2. yes this’s the real history of our heritage.and proud.but we see the people who does know nothing and the people who see them selves down are talking too much. because they have got complexity vs impact

  3. እንደው ምን አባቴ ላርግህ በውቀቱዬ?
    እንደዚህ በሂደት ያገኘነውን ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ሁሉም የየራሱን ሊያነሳና ሊሄድ ሲፈልግ ምን ያህል እርስ በርስ በባህል በቋንቋ በደም እንደተወሳሰብን እና እንደ ተራባን የረሱ ባዶ የሆኑ አንጎሎች አሉ::
    እኔ ለዚህ ዌብሳይት ባለቤቶች የምናገረው እንዲህ አይነት የሚያስገርም ጽሁፍ ስታገኙ እባካችሁን ቶሎ አታንሱት ይክረም ይነበብ ይደገም ይሰለስ…..
    bewketu seyoum, you are one genius ethiopian keep it up. go write again and again…..

  4. These idiots don’t understand mother natures law. They are struggling against nature and the result will be ending up in identity crisis like the Eriterians. Why do you think they are missing Enjera, Kitifo, habesha kemis, habesha music…..they were actually habesha but they deny it.

    Culture is not static!!! but HUMANITY IS!!

  5. selam bewketu,

    good article. just not forget:
    Gojjam culture portrayed with shorts is because of affordability. Okay then Ethiopian culture portrayed by the traditional coffee pot not miss of coffee machine? Funny!

  6. Bewqetu..endew minabate ladrgik..lik likachewn new yenegerkachew lezemenu yebhertegna susegnoch…….Wsha beqededew jib ygebal endilu Weyane basayachew menged enezih zeregnoch bihonim aydenkenm neger gin Ewnetu tedebqo ayqerm…..Death to Weyane

  7. Thank you Bewketu. Oh what a feeling! I think we Ethiopians lack confidence on what we have as a culture. We have to respect it, we have to enjoying on it and at most we have to know about it in detail rather than comparing it with the white game.please before to write and post it to public try to read and know the history of Ethiopia it is more than to say somethingtrush like Jawar. In my opinion Jawar needs an operation for his attitude on Ethiopia. For me and for most of us Ethiopia means just more than word to explain. I think we have to be proud of what we have un exploited culture like other African countries. Unless we think as ones for Ethiopia , thinking ethinic based is a life long medicine for TPLF/woyane.

  8. Admins what is going on? the board should respect and give a special status for people like Bewuktu Seyoum a great Ethiopian icon. I didnt see anything wrong on his article. Why do you allow some law graded people to insult him. I dont think it is good for your contributors or to your site if this is not corrected your site will serve a tabloid type information or ethio love service in paltalk. In reality this will diminish the value of your effort Bewuktu didnt attack any people rather glamorizing our unity and tolerance and insult is not what he deserve. if this people have the gut, knowledge and capability let them show us theirr work. Please read the contents before you displayed them for your readers.

  9. How beautiful when one speaks his own mother tongue. In the same way it is derogatory when one tries to speak others language. The best example is the Oromo people. Oromo has nothing common with Habesha. Nothing!!! Oromo can benefit much if it live as neighbor than as one land. Believe me. Time will show all.

  10. Ato bewketu,ure a good poet &i admire u for that.But, coming to ethiopian history the picture is completely d/t from what u try to write.I think u don’t miss the fact that history is’nt all about cooperation as u try to picturize,it also embrace conflicts as tesfaye elucidate it step by step.Rather than responding with rational arguments those who commented are rushing for abuse as its always common on this blog.what’s wrong with presenting the opposite of what the writer said?shame on u all.Had it been unanimous cooperation in bldg ethiopia,no oromo including jewar said i am oromo first and ethiopia is imposed on me.i don’t know why ethiopianist writers+u are turning a blind eye to past wrongdoings and always recite about our mewaled,yemelkachin memesasel,blah blah,ye emnetachin and mehon.Ye getamina ye tarik sewu sira eko enkerdadun ke sindewu meleyet newu meseleny?.Dare to ask the dark history of ethiopia and shed a light on it.when we all did that,we can live together without imposing one’s value upon another. Oromia shall be free.

  11. Bewketu, Please write more and more and more ….etc!
    I just cant get enough of what you write all the time. please do write more.

  12. Wow Bewketu simin melaekt
    yilalu
    Betam wektun yetebeke article enam bisletihin yemiasay ahunem bewket lay ewket yichemirlih write…….and more pls?

Comments are closed.

Share