እውነት – ከየጎንቻው

አንድ ቃል ቋጠሮ ረቂቅ ሚስጥር፤
በቋንቋ፤ በቦታ፤ በጊዜ በኅይዎት በሃሳብ ቀመር፤
ዝጎ የማይሻግት በየብስ፤ በባህር፤ በሕዋም ሲኖር፤
የወርቅ ተምሳሌ ቀልጦ የሚጠራ በአፎት ሲነጠር፤
ዋጋው የከበረ ውበቱን ጠብቆ እያደረ እሚያምር፤
የአንገት ሃብል ቀለበት፤ቃል ኪዳን መቋጭ ጽኑ ትሥሥር፤
የእምነት፤ የፍቅራችን ዋቢ መገለጫ የአብነት እድር፤
የመንፈስ ቡራኬ የጽናት መሰረት እጡብ ድንቅ ምግባር፤
ከእትብታችን ግማድ አገር በቀል ወይራ አጥኖን እሚኖር፤
እውነት አይጸድቅም ወይ? እንደ ዋርካ ገዝፎ ዘመን ባሻገር።
እየተንኰባቸ በአዕምሯችን ጓዳ በአፋችን ሲብላላ በቃል ተዥጎድጉዶ፤
ሃሳብ ዳዴ ብሎ አፍ እጅ ተቀባብሎ እግርም እንደ መራው በየፊናው ነጉዶ፤
‘ወርቅ’ ተቀምሮ፤ በ‘ሰም’ ተሞሽሮ፤ ስንኝ ተደርድሮ፤ ትርጉም ከብዶ ወልዶ፤
ትክሻን እስኪያጎብጥ ናላ እስኪጎራብጥ በደቀ መዛሙርት እውነት ጫፍ ተንጋዶ፤
ያጨፋጭፈናል ትውልድ አጎብድዶ፤አናዳጅ ተናዳጅ ቅርንጫፍ የሚያዘም አበሻ ምን ገዶ፤
ስሜት አኰብኩቦ በሰያፍ አንደበት እየተጠራራ ውርጅብኝ ተማግዶ፤
ምላጭ በጣት ስቦ፤ ምላስ በአፍ አሳቦ፤ ተደናቁሮ ጩኸት ጠብ በዳቦ አሳዶ፤
ሰው አውቆ ከጠፋ፤ ዘመን አንገዳግዶት፤ ወድቆ ካልተነሳ፤ በቀን ተሽመድምዶ፤
ማን ያኑር አደራ፤ እውነትን ማን ይንገር? ከቶ እስከ ወዲያኛው ክህደትን አስክዶ፤
እውነት ታርግ ይሆን? እንደ ጢስ ንግሯ፤ አገር አመድ አፋሽ ወይ ከስሎ፤ ወይ ነዶ።

ዓለምን ከሞሏት የውሸት አረንቋ ከርሰ ምድር ስፍራ፤
እንደ ፈርጥ የሚያፈዝ ብርⷅዬ ማዕድን ደምቆ የሚያበራ፤
የተፈጥሮ ጸዳል የዓላማችን ማማ ከአካል የገዘፈ የመንፈስ ተራራ፤
በአንጀት ይሆን በልብ ተቀርጾ የሚኖር ሁሌ የሚዘከር ድንቅ ገድል ሥራ፤
የት ይሆን ማደሪያው? እውነት በሰው አካል በዚህ በዚያም ጐራ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሜሪካውያን/ምዕራባውያኑ ‘ኢትዮጵያን አንድነት እና የኢትዮጵያኒዝምን' እንቅስቃሴ ስለምን ይፈሩታል?! - በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

የሞራል፤ የሳይንስ፤ የእምነት፤ ፍልስፍና የሚዛን ሰንደቅ፤
ዘላለም የጸናች በቀነኛ ጀምበር ቀን ወጥታ እማትጠልቅ፤
ግዝት ትሆን፤ አንድ ወጥ ሰማያዊ፤ ገነት ደቂቅ ረቂቅ፤
ወይስ እጀ-ሰብ ነች ስንዝር የተለካች በጣታችን አጥቅ፤
አንዲት ቅንጣት ገመድ በውል ተሸርባ ተጥመልምላ ማቅ፤
በምናብ ተባዝታ በእይታ ተነድፋ ከእንጥቁል ነጭ ልቅ፤
በልክ የተሰፋች ለእርቃናችን ሽፋን ዓለማዊ ጨርቅ፤
ሽሙንሙን ነጠላ የህይዎት መስተዋት የእራስ ነጸብራቅ፤
የሰው ፈትል ጥለት እውነት ጥልፍልፏ የመርፌ ጥቅጥቅ፤
በእንዝርት ተሹራ ከራ መጥበቅ እንጅ አላልታም አታውቅ፤
የህልም ድርና ማግ የምኞት ቀረጢት ውስብስብ ሽምቀቅ፤
እውነት ሰው ሰራሽ ናት ጠበው የሚዘርፏት የሰምና ወርቅ።

የጐንቻው! yegonchaw@yahoo.co.uk
እነሆ በየፊናች ‘እውነት’ ብለን ለምንጠራት ‘አንጡራ እሳቤ’ ማስተዋሻ ትሁን! 19.07.2013
የጐንቻው
ግጥሙን PDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

Share