ግርማ ካሳ
ሐምሌ 8 ቀን 2005 ዓ.ም
ከአርባ ሁለት በላይ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች፣ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ዛሬ እንደታሰሩ ፍኖት ነጻነት ዘገበ። ከታሰሩት ዉስጥ ሁለቱ ሴቶች ሲሆኑ አብዛኞቹም ወጣቶች ናቸው። በጎንደርና በደሴ የተደረጉ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፎችን ተከትሎ፣ በአዲስ አበባ ከተማ 23ቱ ወረዳዎች ያሉ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ፣ በተመሳሳይ ሰዓት በወረዳዎች ሁሉ በመሰማራት፣ ሕዝቡን በማነጋገር ፔቲሽኖች ሲያስፈርሙ ነዉ ፖሊሶች ያገቷቸው።
አብዛኛዉ የአመራር አባላቱ ከጎንደርና ከደሴ ገና ባይመለሱም፣ በ23ቱም ወረዳዎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች በእኩል ሰዓት የተደረጉት፣ የአንድነት ፓርቲ በየቦታዉ ጠንካራ አባላትና ደጋፊዎች ስላሉት ነዉ። ኢሕአዴጎች እነ አንዱዋለም አራጌንና ናትናኤል መኮንን ቢያስሩም፣ ይኸዉ ከየቦታዉ አንዱዋለም አራጌዎች፣ ናትናኤል መኮንኖች ትግሉን እያጧጧፉት ነዉ።
የአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለደህንነት ሰራተኞችና ፖሊሶች፣ አበባ በማበርከት፣ ፍጹም ሰላማዊና የሰለጠነ ፖለቲካ እንደሚያራምዱ፣ በደሴዉና ጎንደር ሰልፍች ማሳየታቸው፣ በሰፊዉ የተዘገበ ጉዳይ ነዉ። በሰልፎቹ አንድ ጠጠር እንዳልተወረወረ፣ የተሰበረ መኪና፣ የተጎዳ ሰው እንደሌለ በገሃድ ተመስክሯል። አፍቃሪ ኢሕአዴግ አይጋ ፎረም ሳይቀር፣ አንድነት ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረጉን አመስግኗል።
የአንድነት ፓርቲ፣ አበባ እንጂ ጥይት እንደማያበረክት፣ የሰላም እንጂ የጠብና የጦርነት ፓርቲ እንዳልሆነ እየታወቀ፣ በጎንደርና በደሴ ይሄንኑ አስመስክሮም፣ ገዢው ፓርቲ ግን አሁንም አንድነትን ሕጋዊ ፍቃድ እንዳለዉ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን፣ እንደ «ጠላት» እየቆጠረዉ፣ በአባላቱ ላይ ዱላ እየሰነዘረ ነዉ። እርቅ፣ ሰላም፣ የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባትን ሳይሆን፣ ሕዝብን ማሸበርንና በጉልበት አፍኖ መግዛትን የመረጠ ይመስላል።
የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት «የድርጅታችን ጽ/ቤቶች በሙሉ እስኪዘጉና ሁላችንም እስክንታሰር ትግላቸን ይቀጥላል» በሚል ቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል። ገዢዉ ፓርቲ ጥቂቶችን ቢያስር ሚሊዮኖችን ሊያስር እንደማይችል የሚነገሩት አንድነቶች፣ አገዛዙ የሕዝብ ትልቅ ድጋፍ በየክልሎቹ፣ ያለዉን ድርጅት ከመጋፋትና እንደ ጠላት ከማየት፣ አብሮ ለመስራትና ለእርቀ ሰላም እራሱን ቢያዘጋጅ መልካም እንደሆነ ያሳስባሉ።
የጎንደርን ደሴ ሰልፍ ተከትሎ፣ በመቀሌ ታላቅ ሕዝባዊ ሰብሰባ በቅርቡ ይደረጋል። ቀጥሎም በጂንካ (ከአርባ ምንጭ ወረድ ብሎ በደቡብ ኦሞ ዞን) እና በወላይታ ሰላማዊ ተቃዉሞ ሰልፎች ይደረጋሉ። አዳማ፣ ባህር ዳር፣ አዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ እያለ ይቀጥላል። የመብት፣ የነጻነት የእኩልነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ በምንም ተዓምር ዜጎችን በማሰር አይታፈንም።
አዲስ አበባ ብቻ አይደለም። ይኸዉ በጎንደርና፣ በደሴ ታይቷል። ብዙዎች ከማያውቋት ከጂንካም የዴሞክራሲና የነጻነት ደዉል ይደወላል። የኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ ሕወሃት እምብርት ከነበረችውም መቀሌ፣ የጀግናዉ ኣጼ ዮሐንስ ከተማ፣ ዜጎች ከአንድነት ፓርቲ ጀርባ በመሰለፍ ኢትዮጵያዊነትን ያወጃሉ። ለዘር ፖለቲካ፣ ለኢፍትሃዊነትና ኢሰብዓዊንት ፣ ለሙስናና ዜጎችን የማሰርና የማሸበር ፖለቲካ ላይ ያላቸውን ተቃዉሞ ይገልጻሉ። የዴሞክራሲ ድምጽና ደዉል፣ ከሁሉም አቅጣጫ ነዉ የሚመጣዉ። ይሄን ድምጽ ገዢዎች በፍጹም ሊያፍኑት አይችሉም። ቢፈልጉም ፣ ቢሞክሩም እንኳን አቅም አይኖራቸዉም። የሚያዋጣቸው ፀሐይ ሳትጠልቅ፣ ለሕዝቡ ፍላጎትና ፍቃድ ራሳቸዉን ማስገዛት ብቻ ነዉ። አመራሮቹ ቢያስቡበት ይሻላል እላለሁ።
የታሰሩ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎችን ስም ዝርዝርን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !
https://www.andinet.org/archives/13064
http://www.fnotenetsanet.com/?p=4953
ሁለት ማሳሰቢያ አለኝ ፡
- ለነዚህ ወገኖቻችን ያለንን ድጋፍ በተግባር እንግለጽ። የታሰሩት ፔትሽን ሲያስፈረሙ ነዉና እኛም ይሄንን ፔትሽን በመፈረም፣ ሌሎችን በማስፈረም፣ እነርሱ በአካል ለጊዜዉ የማይሰሩትን በመስራት የነጻነትን ድምጽ እናስተጋባ !
- ሰልፎችን፣ ህዝባዊ ስብሰባዎች ለማድረግ የራሱ የሆነ ወጭ አለዉ። በጎንደርና በደሴ አብዛኛዉን ወጭ የሸፈነው፣ የኑሮ ዉድነት እየከበደዉም፣ አገር ቤት ያለው ሕዝባችን ነዉ። በዚህ ረገድ በኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ያለነዉ በዉጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዉያን ብዙ ይጠበቅብናል።
ፔትሽን ለመፈረም ፣ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴን በገንዘብ መርዳት ለምንፈልግ ወደ ሚከተለዉ ድህረ ገጽ አድራሻ እንሂድ፡
http://www.andinet.org/
http://www.fnotenetsanet.com
http://www.thepetitionsite.com/174/997/377/millions-of-voice-for-freedom-/?taf_id=9605862&cid=email_na