አሜሪካንን ጠላሁዋት + አሜሪካንን ወደድኩዋት = _

ከዳንኤል ገዛኽኝ አትላንታ

ለኢትዮጲያ የስፖርት እና የባህል ፌዴሬሽን ምስጋና ይግባው እና በአንድነት እያሰባሰበ በየ አመቱ ደስ የሚል አይነት ትዝታ ያለው አጋጣሚ እንድናሳልፍ። በተለያዩ ስቴቶች እንዲሁም በተለያዩ አህጉሮች ከሚገኙ ከናፈቅናቸው…ከናፈቁን ጋርም እንዲሁ ተገናኝተናል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ስለሚያደርገን በድጋሚ ፌዴሬሽኑን እናመሰግነዋለን ከነ ችግሮቹም ቢሆን።

ዘንድሮ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ከሙያ ጉዋደኛዎቻችን ጋር ደስ የሚል አጋጣሚ አሳልፌያለሁ። የሆነው ሆኖ ለዲሞክራሲያዊትዋ ሃገረ-አሜሪካ ምስጋና ይድረሳት። ይህቺ ሃገር ዲሞክራሲያዊት ባትሆን ኖሮ በዲሲ የተመለከትኩት የሰዎች ህይወት እውን ባልሆነ ነበረ። ያም ሆኖ ግን በ ኢኮኖሚ የአለም መሪ በምትባለው በዚህች ሃገር በ አሜሪካ የመንግስትዋ መቀመጫ በሆነችው ግዛት በዋሽንግተን የተመለከትኩት ህይወት በጣም አሳዛኝ እና ስሜት የሚያደፈርስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በተለይም ደግሞ የዚህ ጽሁፌ የትኩረት አቅጣጫ የሚሆነው የዋሽንግተኑ ዩ ስትሬት የ ኢትዮጲያውያኑ ኑሮ ልቤን በሃዘን ሞልቶት ሃዘኔን አብዝቶታል በ እውነት ውስጤ አልቅሶዋል። እንደ እኔ እሳቤ ነው አካባቢው ከመጨናነቁ የተነሳ ነው መሰል በ ፊደል አልፋ ቤት እና በቁጥሮች የተሰየመ ነው አካባቢው። ከሁሉ ሁሉ ግን 7ስትሬት…9ስትሬት እንዲሁም ዩ ስትሬት አካባቢ የሚታየው የምሽት ትዕይንት አስገራሚ ነው።

በአካባቢው የ ኢትዮጲያውያን መዝናኛዎች እና ምግብ ቤቶች በርከት ብለው ይታያሉ። በተለይም ማራኪ…ሃበሻ…ዱከም ሬስቶራንት ከሁሉም ደንበኛ ያላቸው እና ግርግር የሚበዛባቸው ናቸው። ሌላው 7 ስትሬት እና 9 ስትሬት አክባቢ በስፋት ያሉት የሺሻ ዲጄ ምሽት ቤቶች ናቸው። ሙዚቃው በአጫዋቹ በዲጄው ይቀልጣል የሚደንሱ አጫጭር ቀሚሶች የለበሱ ሴቶች እና ወንዶቹም በተመሳሳይ ከሰውነታቸው ላይ የተጣበቁ ጂንስ ሱሪ አብዛኛዎቹ በተመሳሳይ የለበሱ ጥንድ ጥንድ አንዳንድ ጊዜም በቡድን እየሆኑ ጭፈራውን ልበለው ዳንሱን ያስነኩታል።

የኢትዮጲያውያንን ቀን ጁላይ 5 በበርድ ስታድየም ካከበርን በሁዋላ ያመራነው ወደ ሜሪላንድ ጆርጂያ ጎዳና ላይ ወደሚገኘው አንድ ታዋቂ ሬስቶራንት ነበረ። በዚያ ሬስቶራንት ሞገስ መብራቱን እና ከዝነኛዎቹ ደግሞ እንደ ኤሊያስ ተባባል አይነት ታዋቂ ድምጻዊ ከ አንድ ኪቦርድ ጋር ተቀናጅቶ ማሲንቆውን እየገዘገዘ ከመድረኩ ላይ ቆየት ያሉ ዜማዎቹን ይጫወታል። ሞገስ መብራቱ በድምጽም በኪቦርድ ተጫዋችነትም ያጅባል።

ሌሎችም ብዙ ታዋቂ ያልሆኑ ድምጻዊያን የምሽቱን ታዳሚያን ያዝናናሉ። ሆኖም ግን በድምጻዊያን አካባቢ በተለይ በሃገራችን በውጪም ሲኖሩ ሆነ በሃገር ቤት አንድ የተለመደ ነገር አለ። ባለሞያው ህይወቱን የሚመራበት ከሙያው ውጪ የሆነ ቢዝነስ በመክፈት ታላላቅ መድረኮች ላይ ሲጋበዝ ስራዎቹን ማቅረብ እና አመታቶችን ጠብቆ አዳዲስ ስራዎችን በአልበም መልክ አሳትሞ ለአድማጭ ማቅረብ ሲሆን ይህ ሲሆን ታዲያ በየምሽት ክለብ መጫወት ያቆማል ማለት ነው። ነገር ግን ገቢው ካልተሻሻለ የራሴ የሚለው ነገር ከሌለው ግዴታ ምሽት ክለቦች እየሄደ እየተጫወተ በሚያገኘው ገቢ ኖሮውን ይደጉማል ማለት ነው። አንጋፋውን የራስ ቲያትር ቤት ያፈራውን ድምጻዊ ተወዳጅ እና ቁምነገር አዘል ስራዎች በመስራት የሚታወቀውን ኤሊያስ ተባባል ዛሬም እንደ ጥንቱ ማሲንቆ እየገዘገዘ መጠጥ እየጠጡ ለሚዝናኑ ሰዎች በአንድ ተራ ምሽት ቤት ሲያቀነቅን ሳየው በ እውነት ስለ ሃገራችን ድምጻዊያን አዘንኩ። እርግጥ ነው ድምጻዊያኖቻችን ደረጃቸው እና ገቢያቸው ሁሉ ነገራቸው ይለያያል። ቢሆንም ኤሊያስ ግን አሳዘነኝ። ቢሆንም ህይወት ነው እና ምን ይደረግ።

ስንቅነሽ ከሚባለው የሜሪላንዱ የሃበሻ ሬስቶራንት በ አስጎብኚያችን ማሙዴ አማካኝነት ወደ ዋሽንግተን ዩ ስትሬት በረርን። ማሙዴ ጨዋታ የጀመረው ከምንጉዋዝበት የ2014 ፎርድ-ቶሬዝ መኪና በመጀመር ነው። ማሙዴ አይፎርሽም ያለማቁዋረት ያወራል። ንግግር ከጀመረ አያቆምም።

“ይሄን የመሰለ ዘመናዊ የልጥጥ መኪና ይዘህ አይደለም ካምሪ እንኩዋን ብትነዳ ተከታይህ ብዙ ነው እንዴ ጀለሴ እንዳው ለመድሃኒትም ቢሆን አንድ ቺክ መጫን ነበረባችሁ ወይ ፍሬንዶች ተሸውዳችሁዋል በጣም ትገርማላችሁ…”

የማሙዴ ነገር እኔንም ጉዋደኛዬንም አስፈገገን።

መካከለኛ ቁመት አለው ጠቆር ይላል…የፊት ጥርሶቹ መበለዝ ብቻም አይደለም ተሸራርፈዋል። የጥርሶቹ መበለዝ ታዲያ የናዝሬት የአዋሳ የመተሃራ ልጆች አይነት ከለር አይደለም ጠይቄዋለሁ “ሲጋራ እና ጫት ነው” የሚል መልስ ሰጥቶኛል። የት እንደሚሰራ ጠየቅኩት ማሙዴ ሊያወራ ሲል ሳቅ ሳቅ ፈገግ ፈገግ ይላል እንደልማዱ ሳቅ እያለ ንግግሩን ቀጠለ…

“ባይገርምሽ እኔ ከአምስት በላይ ዲግሪዎች አሉኝ…”

ሲለኝ አቁዋረትኩት እና የምን ዲግሪ ነው ይሄ ሁሉ ?…

ማሙዴ አሁንም ሳቅ አለ…

“የውልሽ እኔ ሸራተን ሆቴል ውስጥ የታወኩኝ ሃውስ ኪፐር ነኝ በጣም ይወዱኛል የየ አመቱ ኮከብ ተሸላሚ ነኝ ከአምስት አመት በላይ ሰሰራ በየ አመቱ ኮኮብ ተሸላሚ እየተባልኩ እሸለማለሁ በተሸለምኩ ቁጥር ሆቴሉ ዲግሪዬን ይሰጠኛል…”

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፍጅቱ እና እልቂቱ የማያልቅልህ ዐማራ - ሙላት በላይ

ታዲያ እሱ እኮ የ እውቅና ወይንም የምስጋና በለው ወይ ደሞ ለስራ ልምድነት የሚያገለግል ወረቀት ነው እንጂ ዲግሪ ይባላል እንደ ?

የኔ ጥያቄ ነበረ…

“ሞኝ ነሽ መሰለኝ ! ያው እኮ ነው እንዳውም ከዲግሪም በላይ ነው እሱን አሳይቼ ዲግሪ አለን ከሚሉ ሰዎች በላይ በተፈላጊነት እቀጠራለሁ…”

አሁንም እየሰራህ ነው ?

“አሁን እንኩዋን አቁሜያለሁ”

ለምን አቆምክ?

አስከትዬ ጠየቅኩት…

“ሃገሬን ማየት ፈልጌ ነበር እና ፍቃድ ሰጡኝ አልኩዋቸው አንፈቅድም አሉኝ ትቼላቸው ወጣሁ…”

ታዲያ ሃገር ቤት ሄድክ ?

“አይ በቅርቡ እሄዳለሁ…አሁን እዚህ ስታድየም ውስጥ ከሃይሌ ኩዋሴ ጋር ቢዝነስ እየሰራን ነው በቅርቡ ሃግሬን ሄጄ አይቼ እመለሳለሁ…”

ማሙዴ ደስተኛ ቢጤ ነው ምንም የሚያስጨንቀው ነገር እንደሌለ ነው ሁኔታው የሚያሳብቅበት። አስከትዬ ጥያቄ  ወረወርኩለት።

ግን እንዴት ነው እነዚያ ዩ ስትሬት አካባቢ ያየሁዋቸው ሰዎች ወጪ የሚኖሩት ?

“ምን ምርጫ አላቸው አንዳንዱ የገቨርንመንት እርዳታ ጥሞት የሚኖር አለ ሌላው ደግሞ ከምኑም የሌለ አለ በቃ አይተሃቸዋል አይደል በጣም ያሳዝናሉ በይበልጥ ደግሞ ከ9 እና ከዩ ስትሬት የትም አይሄዱም እዛው ናቸው በቃ እዛው ይፈልጣሉ…እዛው ይቀፍላሉ እዛው ለሽ ይላሉ…”

አልገባኝም ?

አልኩት…

“ነፍሴ ሳይሽ ሃሪፍ ነገር ነሽ ወይንስ አውቀሽ ፋራ ለመምሰል ነው በቃ አይገባሽም እንዴ እዛው እየለመኑ እዛው ያድራሉ ላይፋቸው ይሄ ነው…ያረጁትን ያቺን አሮጊትዋን አይተሃታል ሼባውንም አይተኽዋል ሼባው እንዳውም ዲግሪ ሁሉ አለው እንዳውም አንተ ከመጣህበት ስቴት ነው ወደ ዲሲ ሙቭ አድርጎ እዚሁ በድራግ እና በመጠጥ ህይወቱ ተበላሽቶ ዩ ስትሬት የወደቀው…ወጣቶች አሉልህ 24…27 ዓመት የሚሆናቸው ወላ ሴቶች ወላ ወንዶች እንዴት ያሳዝኑሃል መስለህ…”

አለ እና አንገቱን ነቀነቀ።

“ግን ጀለሴ ይህንን ሁኔታ አይታችሁ ዝም አትበሉ እስቲ ኮምዩኒቲው ዜጎቹን ከዚህ እንዲያወጣቸው የበኩላችሁን ትረት አድርጉ…እዚህ ማንም ስለማንም አይገደውም…”

ማሙዴን ቀስ ብዬ አየት አደረግኩት። ፊቱ ክስል ብሎዋል በጣም ጠቁሮዋል ድምጹ ዝግትግት ያለ ነው። ድምጹ ከተፈጥሮው ለወጥ ያለ መሆኑ ያስታውቃል ይሄ ደግሞ መጠጥ ዕና አንዳንድ ነገር ከማዘውተር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገምቻለሁ። መኪና ውስጥ ባለማጨሱ ተጨናንቆዋል ብዙ ረጅም ባይባልም ከ አርባ ደቂቃ በላይ መንዳት አለብን ዩ ስትሬት ለመድረስ።

ማሙዴ ጨዋታው የሚያልቅ አይደለም…እንዲያው ግን ማሙዴ ይቅርታ አድርግልኝ እና ቨርጂኒያ…ሜሪላንድ…ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጲያውያን እንዳው እንደ ናሙና ስታያቸው እንዴት ነው ምን ይመስሉሃል ላንተ ?

አልኩት…

ማሙዴ እንደ ልማዱ ፈገግ… ሳቅ አለ እና…ንግግሩን ቀጠለ…

“አባ ምን እንዳለ ታውቂያለሽ ሜሪላንድ አካባቢ እንዳው ለኩዋሱ ከመጣው ከ እንግዳው ህዝብ ባሻገር ስታያቸው በ እድሜገፋ ያሉ ሴቶች እና ወንዶች የተሰባሰቡበት ነው…ቨርጂኒያን ደሞ ስታያት እዚያ ያሉት በአብዛኛው የተማሩ ምሁራኖች…አርቲስቶች…ታዋቂ ሰዎች የተሰባሰቡበት ነው…ወደዲሲ ስትመጣ የኔ ቢጤዎች ችሰታዎች የሚበዙበት ነው… ብዙዎቹ ህይወቱን የሚወዱትም የማይወዱትም የተማረሩ ዲሲን እንዴት ብለን እንልቀቃት የሚሉ ከሃገራቸው ከሃያዎቹ አመታት በፊት ወጥተው ወደሃገራቸው እና ወደ ቤተሰቦቻቸው ዞረው ማየት ያቃታቸው ናቸው። ምክንያቱም ዲሲ ጠዋት ማታ ጭፈራ ጠዋት ማታ መጠጣት መዝናናት የሚበዛባበት አካባቢ ነው…ባይገርምሽ መንግስቱም ይህንን ሁኔታ ያወቃል መኖሪያ ቤቶቹ እንኩዋን የተጨናነቁ እና አንድ ክፍል ውስጥ ለአራት ለአምስት ነው የሚኖሩባቸው ይሄ የሆነው ደግሞ ኑሮ ውድም ስለ ሆነ ነው…”

የ ማሙዴ አገላለጽ ግምገማው አስገራሚ ነው። እንደምንም ከግማሽ ሰአት ያላነሰ ጉዞ አድገን ዲሲ ከተቃጠለው ሰፈር ደረሰን። ሆኖም ግን መኪናችንን ፓርክ የምናደርግበት ቦታ አጥተን ቦታ ፍለጋ ስትሬቶቹን ሁሉ ስንዞር ቆየን። የአካባቢው ፖሊስ ስራ በዝቶበታል። በድንገት ታዲያ መኪናችንን እንዳቆምን አንድ ለየት ያለ ቀልባችንን የሚስብ ጉዳይ አጋጠመን። አንድ የሰው አካል ከመንገዱ ጥቂት ሜትሮች ወጣ ብሎ ተመለከትን ሰውየውን ጠጋ ብዬ ተመለከትኩት። በትክክል እንቅልፍም አይደለም ሰውየው እስከ ወዲያኛው አሸልቦዋል። ዝርግትግት ብሎ ወድቆዋል። ከኛ እይታ በሁዋላ ለአካባቢው ሰዎች ለሚዝናኑት ሁሉ ብዙም ትኩረት ያልሳበው የወደቀው ሰው ወዲያው የፖሊሶችን ትኩረት ሳበ እና ፖሊሶች ከበቡት። አክባቢው ከነበረው ትርምስ የበለጠ በትርምስ ተሞላ። እኛም ብዙ አልቆየንም ቦታውን ተተን በአስጎብኚያችን በማሙዴ መሪነት ወደ ማራኪ አመራን።

ማራኪ ጠባብ ቤት ነች። ነጭ ሸሚዝ እና ጥቁር ሱሪ የለበሱት አስተናጋጆች አቅላቸውን እስኪስቱ ከወዲያ ወዲህ እያሉ ባልኮኒ እና በተለምዶ ባለጌ ወንበር እያልን የምንጠራው መቀመጫ ላይ የተቀመጡ ደንበኛዎቻቸውን ያስተናግዳሉ። ብዙዎቹ ባልኮኒውን ታኮ ባለው ባለጌ ወንበር ላይ ሆነው ሺሻ ወይንም ሁካቸውን ያንቦለቡሉታል ከእያንዳንዱ አፍ የሚወጣው ባለ ረጅም ጭስ እየወጣ እየሄደ ይበተናል። የኔም ሃሳብ ከጭሶቹ ጋር እየተከተለ ብትን ይላል። ሆ! አልኩ ለራሴ የሰውም ሃሳብ እንደዚሁ ብትን ይላል አልኩ ለውስጤ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ምሑራን በዲሞክራሲ ትግል ውስጥ በስፋት አለመሳተፍ በለውጥ ትግሉ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

“ያቺውትልህ ያቺውትልህ…የምታሳዝን የሃያ አራት አመት ወጣት ናት መንግስት ይረዳታል ግን በቃ ኑሮዋ እዚሁ ዩ ስትሬት አካባቢ ነው ያጠመደ ሰው ከናይን ስትሬት እና ከዩ ስትሬት አያጣትም ታሳዝናለች…”

ማሙዴ የረሳው ነገር እንዳለ ሁሉ ከደረት ኪሱ የተጨማደደች የሲጋራ ፓኮ …ከሱሪ ኪሱ ደግሞ ላይተር አውጥቶ ከፓኮው የመዘዛትን ሲጋራ ከ አፉ ጫፍ ለጎማት እና አቀጣጠላት። ሲጋራዋን አከታትሎ ምጎ በ አፉ የሳበውን ጭስ ሙሉ ለሙሉ አውጥቶ ሳይጨርስ በችኮላ መናገር ጀመረ…

የ ኔ አይን አንዴ ከማሙዴ አንዴ ዥንጉርጉር የተጨማደደ ቀሚስ ለብሳ ቀይ ትልቅ ቦርሳ ከትከሻዋ ላይ ካንጠለጠለችው ልጅ ላይ አነጣጥራለሁ። ጆሮዎቼ የማሙዴን ንግግር እየተጠባበቁ ነው…ልጅትዋ ከጭኖችዋ ላይ ከተንጠለጠለችው የተጨማደደች ቀሚስ በታች ጥቁር ታይት ሱሪ ለብሳለች በቀኝ እጅዋ ተጭሳ ግማሽ የደረሰች ሲጋራ በጣቶችዋ ሰክታለች…ጠባብዋን ማራኪን አቁዋርጣ ወደ አነስተኛዋ ፎቅ ዘለቀች።

ሌሊቱ ተጋምሶዋል ታይተው ገብተው…ወጥተው የማያልቁ የሰከሩ…የሚጣደፉ…የሚጉዋተቱ የሚያማምሩ ወጣት ሴት እና ወንዶች ይታያሉ ብዛታቸው አይጣል ነው። አንድ ወጣት ሴት ቀልቤን ሳበችው የትነው የማውቃት በሚል ሃሳብ ተወጠርኩኝ። አዎ አወቅኩዋት በ አንድ ወቅት በቴሌቪዥን ድራማዎች የማውቃት ወጣት አማተር ተዋናይት። ከቲቪ እይታ ከጠፋች ቆይታለች። ወይ ዲሲ ወይ አሜሪካ ውጣ አስቀርታት ነው አልኩ በውስጤ። አይታዬን ከወዲያ ወዲህ ቀጠልኩ… በአንድ ወቅት በአንድ በተለያዩ የሙዚቃ ክሊፕ ውስጥ የታየች በሞዴሊስትነት ትሰራ የነበረች ሌላ ወጣት ነይልኝ…ነይለት በሚለው የዘፈን ክሊፕ ከማውቃት የበለጠ በግንባር አውቃት የነበረች ወጣት ሞዴሊስት…አንድ ወጣት ወንድ እጅዋን ይዞ እየጎተታት ማሙዴ እንደነገረኝ ከማራኪ ባር ውስጥ ካለው የሺሻ እና የዲጄ ጭፈራ ከሚቀልጥበት አነስተኛ ፎቅ ደረጃ እየወረደች ከጭኖችዋ ላይ ከተጣበቀው ቁምጣ ጋር አየሁዋል። የሚጎተታትን ወጣት እየተከተለች ከማራኪ ወጣች።

እውነት ነው የምለው ብዙ ሰዎች ተመለከትኩኝ። ግን በተለየ አለም ውስጥ ናቸው ያሉት። ማሙዴ ጨዋታውን ቀጥሎዋል።

“ታውቂያለሽ እኔ ራሴ ሃያ አመታት አስቆጥሬያለሁ አሁን ግን ወስኛለሁ ሃግሬ መሄድ አለብኝ በቃ ዲሲ አልለቅ ብላኛለች አሁን ግን እፋታታለሁ…”

አልወለድክም ?…አላገባህም ?…

አከታትዬ ጠየቅኩት…

“እንዴት ያለች ሚስት አለችኝ መሰለህ ሚስቴ ነጭ ነች ከወደ ሚሺጋን ነች ግን አልወለድኩም መውለድ አትችልም እስዋ ምክንያቱም ማይሌጅዋ ሄዶዋል…”

አነጋገሩ ግራ ገባኝ ምን ማለት እንደፈለገ በ እርግጥ ጠርጥሬያለሁ…

“ጀለሴ በቃ ዝምብለሽ ነው ምንም አታርፊም ማይሌጅዋ ማለቴ እድሜዋ ሄዶዋል አርጣለች መውለድ አትችልም የፈረንጅ አሮጊት ናት ልልህ ፈልጌ ነው…”

ማሙዴ ሌላ ሲጋራ አቀጣጠለ አስተናጋጅዋ መጥታ ታዘዘችን እኔ የምርጫዬን አዘዝኩ…ማሙዴም ምርጫውን አዘዘ ግን ምን አይነት መጠጥ እንዳዘዘ ስሙ አሁን ትዝ አይለኝም አብሮኝ ያለው ጉዋደኛዬም የሚፈልገውን አዘዘ…በኔ   ምርጫ ግን ማሙዴ ተገረመ እና…

“ፍሬንዴ ታውቂበታለሽ አንቺኛዋ የገባሽ ነሽ አንቺ ግን በቃ ደንበኛ ሸዋ ነሽ…”

አለኝ እና ሳቁን ለቀቀው…

ምክንያቱን ታውቅ የለ እንዴ?… አንድ ሁለት ማለት አላቃተኝም። እያየሃቸው አይደለ እንዴ ፖሊሶቹን ስራ በዝቶባቸው…

አልኩት…

“ውይ ውይ ይቅርታ ለነገሩ ዲ ዩ አይ …”

ጠጥቶ በመንዳት ስላለ ወንጀል ማለቱ ነው…

“የሚበረታው እኮ አትላንታ ነው አንቺ ከመጣሽበት ከተማ ዲሲ ብዙ አያካብዱም ደስ የሚልሽ በየመጠጥ ቤቱ እና መዝናኛው ደጃፍ ተኮልኩለው የምታያቸው ፖሊሶች መጀመሪያውኑ ሰክረህ ወይንም ሞቅ ብሎህ ገድገድ ብለህ ሲያዩህ ሰር ጠጥተህ መንዳት አትችልም እንዳትነዳ ብለው ይገላግሉሃል…”

በአካባቢው የማያባራ ግርግር እና ሁካታ በሰዎች ሁኔታ እየደጋገምኩ ስገረም…

ማሙዴ በስጨት ብሎ…

“ጀለሴ አይግረምሽ ላፍ እዚህ ዛሬ ነች በቃ ነገ ብሎ ንገር የልም እዚሁ ይበላል ይጠጣል ሲነጋ ትንሽ ለሽ ተብሎ ወደ ስራ ታቀጥኚዋለሽ የሰራሽውን እዚሁ ነው የምታወድሚው በቃ ዲሲን ቶሎ ለቀህ ሙቭ ካላደረግሽ መቃብርሽም እዚሁ ነው…”

ይሄን እያወራን እየተጨዋወትን ሳለ ጉዋደኛዬን ዞር ብዬ ስመለከተው በስልኩ ከፌስ ቡክ ጋር ቢዚ ሆኖዋል ልረብሸው አልፈለግኩም። በዚሁ ቅስበት ሁለት ወጣት ሴቶች ማሙዴን እየጮሁ እየጠሩት በየተራ ተጠመጠሙበት ለእኔ እና ለጉዋደኛዬ ሰላምታ አቅርበውልን ሲያበቁ…

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁሉንም መንግሥታዊ ጉዳዮች ከህዝብ እና ከሀገር ጥቅም አንፃር መመልከት ይበጃል። (ትህዳ ኃሣኤ ዘ ኢትዮጵያ)

አንደኛዋ…

“ማሙዴ ጋብዘን ወይ እንጋብዝህ…”

አለችው…

“እኔም ተጋባዥ ድምጻዊ ነኝ ዛሬ…”

ሲላት…

“ታዲያ መርከቡ ቦታ ካለው እኛንም አሳፍረና ምን አለበት…”

አለችችው…

ሌላዋ ቤቱ ውስጥ ከተለቀቀው የ እንግሊዘኛ ሙዚቃ በላይ ከስፒከሮቹ የሚወጣውን ድምጽ ድምጽዋ በልጦ እንዲሰማ እየጣረች…

ጉዋደኛዬ አነጋገርዋ ገርሞት ነው መሰል እሱም ድምጹ እንዲሰማ ጮክ እያለ መለሰላት…

“ለጊዜው መርከብ አይደለም እያሽከረከርን ያለነው…”

ቢላት…

ማሙዴ ፈጠን ብሎ…

“ጢሎ ገባሽ ልጆቹ ጀልባ ነው የያዙት ጀልባ ደግሞ ታውቂያለሽ ብዙ ሰው አታሳፍርም ትቂት ሰው ነው የምትይዘው…አንዳቸው ካፒቴን አንዳቸው ረዳት እኔ ደግሞ አሳ አጥማጅ ሆነን ነው የዲሲውን ባህር በ አነስተኛ ጀልባ እያቁዋረትን ያለነው…”

ብሎ ሁለታችንንም አሳቀን። ግን ግብዣ ነው የጠየቁት ለሃገራችን ልጆች ያን ያህል ንፉግ መሆን እንደሌለብን እናስባለን እና እኔም ጉዋደኛዬም ያሻቸውን እንዲያዙ ፈቀድንላቸው። ከተንጠለጠልንበት የባለጌ ወንበር ባለግማሽ ማ ዕዘን ጠረጴዛ እንዲጋሩን አመላከትኩዋቸው። አዘው መጨዋወት ጀመርን። አለባበሳቸው የ እርቃን ያህል ነው።

ሆኖም ጥቂት እንደቆየን አንደኛዋ ፈጠን ፈጠን የምትለው…

ካላስቸገርናችሁ እራት አልበላንም…

አለች…

ታዲያ ምን ችግር አለው እዘዙዋ አብረን እንበላለን አለ…ጉዋደኛዬ…

“እንደዛ ከሆነ ሃበሻ እንሂድ እዛ ነው ጥሩ ምግብ ያለው…

አለች ፈጣንዋ…

በአንድ ሃሳብ ተስማማን እና ሂሳባችንን ዘግተን ከማራኪ ልንወጣ ስንጣደፍ ያስተናገደችን አስተናጋጅ…

“ይሄን ያህል ሂሳብ ከፍላችሁ አስር ብር ቲፕ ትንሽ አይከብድም…”

እያለች ገላመጠችን…

“የተውንላትን ያህል ጨምረንላት አመስግነን ወደ ሃበሻ ተጉዋዝን እዚያው ፊትለፊት።

ሃበሻ ምግብ የሚሸጥበት ቤት ነው። ምግብ ለማግኘት ታዲያ ባልኮኒው ፊትለፊት መሰለፍ እና ቀይ መብራት ያለው ቦኖ መቀበል ያስፈልጋል። ተራችንን ጠብቀን ምግባችንን አስቀርበን እየተመገብን ሳለን የት እንደሚኖሩ ጠየቅኩዋቸው።

ሁለቱም ቨርጂኒያ እንደሚኖሩ ነገሩኝ። የዚህን ጊዜ ማሙዴ እጁን አስጠግቶ ቆንጠጥ አደረገኝ…

ምንድነው በሚል መንፈስ አየት ሳደርገው…

ወደጆሮዬ ጠጋ ብሎ…

“እዚሁ ዲሲ ዩ ስትሬትን ያቃጠሉ ከሁለት በላይ ቦይ ፍሬንዶች ያሉዋቸው አምታቾች ናቸው”

ሲለኝ በውስጤ ፈገግ አልኩኝ…

ማሙዴ ጣጣ የለውም መናገር ጀመረ…

“ጀለሴ እዚህ እኮ ልክ ሃገር ቤት የጨርቆስ ልጆች ሰፈራቸውን ሰትጠይቂያቸው ቦሌ…እንደሚሉት ነው ገባሽ አይደለ …”

ብሎ ሲስቅ…

አንገቴን እየነቀነቅኩ በምልክት እንደገባኝ አሳየሁት…

ፈጣንዋ እና ቀለብላባዋ ፈጠን ፈጠን እያለች…

“ምን ለማለት ፈልገህ ነው ?…

ብላ ማሙዴን ገላመጠቸው።

ቀጠልኩኝ…

የት ነው የምትሰሩት ?

አልኩዋቸው ሁለቱንም በየተራ እየተመለከትኩዋቸው…

ቀለብለብ የምትለው…

“ስራ ምን ያደርጋል…”

እንዴ ታዲያ እንዴት ትኖራላችሁ ?

አልኩዋት በግርምታ…

“እነ ቢልዬ…ኪርዬ እና ራይድዬ የት ሄደው…”

ማሙዴ ሳቁን ለቀቀው…

አልገባኝም አልኩዋት…

ማሙዴ ፈጠን አለ…

“ኪርዬ ቤት ኪራይ ይከፍላል…ቢልዬ ቢል ይዘጋል…ራይድዬ ደግሞ የተፈለገበት ቦታ ያደርሳል ይመልሳል…ያመላልሳል…”

በድጋሚ ሳቁን ለቀቀው…

እኔ እና ጉዋደኛዬ በ አግራሞት ተያየን…

“አሁንስ ገባሽ ጀለሴ…”

አለኝ…

አሁንም አንገቴን ነቀነቅኩለት።

ማሙዴ ተቁነጠነጠ …

“በቃ ፍሬንዶች ስልካችሁን ይዣለሁ እደወልላችሁዋለሁ አሁን እቸኩላለሁ…”

ብሎን ጥሎን እብስ አለ።

እኛም ሰአታችንን ተመለከትን ልጆቹን ተሰናብተናቸው ወጣን። ዩ ስትሬትን እየተዙዋዙዋርን ቃኘን። የሚያሳሱ አንዳንድ ፍሬ ልጆች በአስራዎቹ እና በሃያዎቹ መግቢያ የሚገኙ ወጣቶች ይተራመሳሉ ከክለብ ክለብ…ከቦታ ቦታ ከሰው ሰው ይቀያየራሉ ይራወጣሉ ይጋፋሉ …ያጩዋጩሃሉ…ይጠራራሉ…ይሰዳደባሉ። ፖሊስ እዛም እዚም መብራት እያበራ ሳይረን ያሰማል። የሃገሬ ህዝብ ነቅሎ መጥቶዋል አልኩት ለጉዋደኛዬ።

በነገራችን ላይ ዲሲ እና አካባቢዋን የቃኘሁበት ጽሁፍ በዚህ አያበቃም ስለሁለተኛው ሳትለን ስለሶስተኛው አትበሉኝ እና በቅርብ ለንባብ ከሚበቃው መጽሃፌ በሁዋላ የሚከተለው ሶስተኛው የመጽሃፌ ክፍል “አሉንባኮት” የትኩረት አቅጣጫው አሜሪካ እና የስደት ህይወት በሃበሻውያን ላይ አጠቃላይ ሁኔታ ዙሪያ በመሆኑ እመለስበታለሁ።

ግን ግን ዩ ስትሬትን እና 9 ስትሬትን ስመለከት በ እውነት ነው የምላችሁ ካዛንቺስ ከነ አቡዋራዋ ትምጣብኝ ብያለሁ በቃ ቁርጥ የ አዲስ አበባውን ቺቺኒያ። እንዳውም ካዛንቺስ እና ቺቺኒያ ምስጋና ይጡ። ይሄን ብቻም አይደለም የሃገሬ ህዝብ እንደዚያ በተዘበራረቀ ባልተጠበቀ የ አኑዋኑዋር ሁኔታ ውስጥ ሳየው የኮሜዲያን ደረጀ ሃይሌን የሞባይል ቀልድ አስታውሼ እኔም ተበታትነናላ…ተበታትነናላ እያልኩ ከጉዋደኛዬ ጋር ወደማረፊያችን ወደ ሜሪላንድ ኮሌጅ ፓርክ እብስ አልን። ሰላም።

4 Comments

  1. This article can be called ZEBZENKE Article is the week. What is your point or do you assume people like to hear your personal Daily Zuret. Ato Daniel next time try writing something substantial or stick to your Radio

  2. ይህ ነው ጽሑፍ ማለት። ሁሉንም በዓይነ ኅሊናችን ተሥሎ እንድናየው ነው ያደረከን። ከሌላ ቦታ ለሚሄድ ሰው ዲሲና አካባቢው አስደንጋጭ መሆኑ አያጠያይቅም። የኅብረተሰብ ማዕከላትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ትልቅ ጥረት ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ በበኩሌ። ይህ ባልሆነበት ሌላውን እናደርጋለን ማለት የማይመስል ነገር ነው።

  3. It is very sad. Is there any good thing to tell us? why only the bad side? I think it is a little bit exagurated.

Comments are closed.

Share