ከቦጋለ አበበ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ክለቦች እየተዘዋወሩ መሆናቸውን የሰሞኑ የአገራችን እግር ኳስ ትልቅ ዜና እየሆነ መጥቷል። የተጫዋቾቹ ዝውውር አሁንም እየተጧጧፈ የሚገኝ ሲሆን፤ ድርድር ላይ የነበሩ ተጫዋቾችም ዝውውራቸውን እያሳኩ ይገኛል።
የዘንድሮው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ «መለስ ዋንጫ» በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ የሚገኘው የደደቢቱ የፊት መስመር ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ከዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ክለቦች ከሚያመሩ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው መሆን ችሏል።
ጌታነህ ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቪት ዊትስ በመፈረም ዝውውሩን የፈፀመ ሲሆን፤ ከእዚህ ክለብ ጋር የሦስት ዓመት ኮንትራት እንደተዋዋለም ታውቋል። ጌታነህ በክለቡ የሦስት ዓመት ቆይታው ከአምስት መቶ ሃምሳ ሺ ዶላር በላይ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።
ቢድቪት ዊትስ ክለብ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ሲሆን፤ በአገሪቱ ጠንካራ ከሚባሉ ክለቦች መካከል የሚመደብ ነው። በእዚህ የውድድር ዓመትም በደቡብ አፍሪካ ኢቢኤስኤ ፕሪሚየር ሺፕ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ክለብ ነው።
ጌታነህ ከአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኝ ወጣት ተጫዋች ሲሆን፤ በተለይም በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ ቦትስዋናን በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ ባስተናገዱበት ጨዋታ አንዳንድ ግቦችን በማስቆጠሩ ይታወሳል። ከአሥራ አምስት ቀን በፊት ዋልያዎቹ ደቡብ አፍሪካን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት ሜዳቸው ላይ ሲያሸንፉ ጌታነህ ወሳኝ ግብ ከመረብ በማሳረፍ ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል።
ጌታነህ በእዚህ ዓመት ለደደቢት ሃያ ሁለት ግቦችን እስከአሁን ድረስ በማስቆጠር ክለቡ ሁለት ጨዋታ እየቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን እንዲሆን አስችሏል። ክለቡም ዋንጫውን ነገ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።
ጌታነህ በአገር ውስጥ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ከመሆኑ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለብሔራዊ ቡድኑ ስኬታማነት ያበረከተው አስተዋፅኦ የደቡብ አፍሪካ ክለቦችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ ክለቦችም ዓይናቸውን እንዲጥሉበት አስገድዷቸዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ የጨዋታ አቀጣጣይ ሽመልስ በቀለ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የማናየው ሌላኛው ተጫዋች መሆኑን አረጋግጧል። በቀልጣፋነቱና በማራኪ የአጨዋወት ስልቱ የሚታወቀው ሽመልስ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ አቅንቶ የአልሂታድ ክለብን መቀላቀሉን አረጋግጧል።
ሽመልስ ከእዚህ ክለብ ጋር የሦስት ዓመት ኮንትራት መፈራረሙ የታወቀ ሲሆን፤ በወር የሚከፈለው ደመወዝም ስድስት ሺ ሰባት መቶ ዶላር መሆኑ ተረጋግጧል። ሽመልስ በየጊዜው በክለቡ ለሚያበረክተው አስተዋፅኦ የገንዘብ ጭማሬ እንደሚደረግለትም ታውቋል።
ሽመልስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ውጤታማ ጊዜን ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን፤ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚያሳየው ማራኪ እንቅስቃሴም ምስጉን ተጫዋች እንዲሆን አስችለውታል።
ዳዊት ፍቃዱ፤ አስራት መገርሳ፤ ምንያህል ተሾመ፤ ዳዊት እስጢፋኖስና በኃይሉ አሰፋን የመሳሰሉ የዋልያዎቹ አባላት ወደ እሥራኤል፤ ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ክለቦች ለመዘዋወር አስፈላጊውን ድርድር እየጨረሱ ይገኛሉ።