(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ የወተት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መከሰቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ:: ይህን ተከትሎ የአንድ ማኪያቶ መሸጫ ዋጋ 8 ብር መግባቱም በከተማዋ አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷል::
በአዲስ አበባ የወተት እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎች በይፋ መናገር መጀመራቸውን ያስታወቁት መገናኛ ብዙሃኑ በወተት ላይ እጥረት ብቻ ሳይሆን የዋጋ መወደድም መስተዋሉ እያስቆጣቸው መሆኑ ታውቋል::
በካፌዎች የአንድ ስኒ ማኪያቶ ዋጋ እስከ 8 ብር መድረሱን የካፌ ተጠቃሚዎችም እየተናገገሩበት መሆኑን የሚዘግቡት መንግስታዊው ሚዲያዎች የካፌ ባለቤቶች የወተት መጥፋት ለእነሱም ስራ ማነቆ መሆኑን በመግለፅ ቀደም ሲል ከሚገዙበት ዋጋ በላይ ለመግዛትም አንዳንዴ ጨረታ እንደሚገቡም ብሶታቸውን ገልጸዋል::
ከዚህ በፊት ለጋዝና ለዳቦ እንደነበረው ወረፋ ሁሉ በአሁኑ ወቅት በስድስት ኪሎና በሌሎች አካባቢዎች በተለይ ጠዋት ጠዋት ወተት በማከፋፈያዎች ሱቅ በር ላይ ረጃጅም ሰልፎችን ማየት የተለመደ እየሆነ የመጣ ሲሆን በእነዚህ ማከፋፈያዎች ውስጥም አንድ ሊትር ወተት እስክ ከ16 እስከ 18 ብር ድረስ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑ ተዘግቧል::