ብሥራት ደረሰ
አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል፡፡ የወደቀም ግንድ ምሣር ይበዛበታል፡፡ ኢትዮጵያም ቀን ጣላትና፣ ቀን ጣላትናም በጠላቶቿ እጅ ወደቀችና፣ በጠላቶቿ እጅ ወደቀችናም የድፍን ስድና መረን ያደገ ዋልጌ ሁሉ የስድብና የዘለፋ አፍ ማሟሻ የመሆን ዕጣ ደረሳትና ይሄውላችሁ በየቀኑ ተነግሮ የማንሰማው ተጽፎም የማናነበው ነገር የሌለን ሆነን ዐረፍነው፡፡ የገዛ ልጆቿም እየከዷት አንዱ ወግጂልኝ ይላታል ሌላው ለርሷ ለመሞት ቆርጦ ተሰልፎላታል፡፡ ደርግ ጥሩ አማርኛ ነበረቺው፡- ‹የእናት ጡት ነካሽ› የምትል፡፡ ዛሬ ዛሬማ የእናት ጡት ነካሽ ብቻ ሳይሆን ባት ቆራጭም፣ ማጅራት ገትርም ማለቴ ማጅራት መቺም፤ አነጣጥሮ አናት በርቋሽም ልጅ ሞልቶናል – የልጅ በያይነቱና ማኅበራዊ በብፌ መልክ በሽበሽ ብሎ ፊታችን ላይ ተዘርግቶልናል (የምግብ ስሞች ናቸው)፡፡ የበዓሉ ግርማ የምናብ ፍጡር የሆነው የካድማስ ባሻገሩ አበራ፣ ገነት ሆቴል የፋሲካ ዋዜማ የጦፈ ዳንስ ላይ የአምቦዋ ሳዱላ ሉሊት ታደሰ ስሟን እንድትነግረው ሦስቴ ጨቅጭቆ ላለመንገር ደጅ ስታስጠናው ‹ከነስምሽ ገደል ልትገቢ ትችያለሽ› እንዳላት ዓይነት ጃዋር ሲራጅን ዓይነቱ ወያኔ ዘራሽ ጎረምሳ በ‹ጤፍ ብድር ሳይቸግር› እንዲያው ከሜዳ ይነሣና ‹ኦሮሞነቴን ካልተቀበላችሁ ከነኢትዮጵያችሁ ገድል ልትገቡ ትችላላችሁ› እያለ ይዝትብናል – ከነገር አባቶቹና አሰልጣኞቹ (አሰይጣኞቹ ብልም ያው ነው) ከነሌንጮ ለታ የቀሰመውን እንጂ እርሱማ በጥቂቶች ጥፋት የተነሣ ያን በክፉነት የሚታማውን ዘመን የት ደርሶበት፡፡ እኛ የኢትዮጵያዊነትን መቁነን የምንሰጥ ወይ የምንነሣ ይመስል በማናውቀው ነገር በትዝታና በታሪክ ዋሻ ውስጥ መሽገውና በአስተሳሰብ ላለማደግ ምለው ትናንትም ዛሬም እዚያው የሚኖሩ በሽተኞች ይነተርኩናል፡፡ ‹ጌታውን ቢፈሩ ገበር ገበሩን› ይባላል፡፡ አሁን ኢትዮጵያን ቀጥቅጦ እየገዛት ያለው አማራ ሳይሆን ወያኔ/ኢሕአዴግ መሆኑ እየታወቀ ‹ሞቶ መቃብር ውስጥ የገባ›ን አማራ መጨቅጨቅ ያስፈለገበት ምክንያት እንኳንስ ለሰው ዘር ለእግዜሩም ዕንቆቅልሽ ሣይሆንበት የሚቀር አይመስልም፤ ‹የሞተን› መውቀስ ደግሞ ከፈሪና ከባለጌ እንጂ ከጤናማ ሰው በጭራሽ አይጠበቅም፡፡ ጉደኛ ዘመን ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይሄ የበታችነትም በሉት የበላይነት የሚባል ምስቅልቅል ስሜት እንዴት ያለ መጥፎ በሽታ መሰላችሁ! Actually, psychologists say that there is no superiority complex as such; it is, they say, the extension or the byproduct of inferiority complex. Therefore, it is logically worthwhile to suggest that people who are busy of dismantling Ethiopia, in some instances, like the Woyanes’ seizure of political and economic power, along with voraciously plundering its resources and appallingly impoverishing the majority of its citizens, are people who are suffering from an overdose of inferiority complex. Otherwise, at normal conditions, you do not lay down your intrinsic identity to the negotiating table and bargain over it as if it is a commodity; identity is not an item to be given by someone nor should it be something to unreasonably bicker upon with somebody, that somebody being abstract or tangibly concrete. The Jawars and their likes of any ethnic group in Ethiopia are funnily engaged in this futile busy-ness and making us laugh. What is Ethiopianness after all? Who has the right to anoint Ethiopianness? What is the source of all this abracadabra and stupidity over Ethiopianness? Where the hell do people of other nations other than Ethiopians invest much attention and commotion on such unproductive and counter-productive matter? Who are more Ethiopians? The Amharas or the Oromos? The Tigrians or the ‘X and Y’s and others? How do some allegedly ‘erudite’ people become cunningly self-destructive to the extent of negotiating their inbuilt who-ness anew after leading an intermingled societal life for thousands of years presumably under one identity? What could be the nature of such an illness that makes people succumb to the traps of the astute who are there at the top of the tower of politics to merely exploit the idiocy of their prey? Anyways, whatever the present scenario might look like, believe me, these weeds of history will lament in the near future when Ethiopianness re-emerges with all its imaginable dignity and glamour. There are indications for the rise of the new sun and we surely will rejoice at the dawn of our freedom.
ይሄን ስም ዐውቀዋለሁ፡፡ ‹ጉረኛ!› እንዳትሉኝ እንጂ ያለ ብዙ ማጋነን ውሎና አዳሬ ከዚሁ ከድረ ገፆች ንባብ ጋር በመሆኑ ብዙ የብዕርና የእውነት ስሞችን መያዝና ማስታወስ አያቅተኝም፡፡ ይሄ ያሬድ የሚባለውን ስም ታዲያ የማውቀው በዚሁ ወያኔና አስመሳይ ቅጥረኞቹ ከተቃውሞው ጎራ ጋር በምናብ ጦርነት በሚተጋተጉበት የድረ ገፅ ዘመቻ ነው፡፡ በሌላ የያሁ ግሩፕም ሲበጠብጠን የነበረ ይመስለኛል፡፡ በጥባጭ መኖሩ ጥሩ ነው፤ ወያኔም በታሪካችን ብቅ ብሎ “ሰውና ሀገር ከኖሩ ለካንስ እንዲህም ያለ ጉድ አለ! ለካንስ በርግጥም ‹ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል› እሚባለው ነገር እውነት ነው” እንድንልና ለወደፊቱ እንድንጠነቀቅ ማስታወሱ ለበጎ ነው፡፡ ሁሉም ክፉ ነገሮች ክፉ አይደሉም፤ በአንድ ወይ በሌላ መንገድ አስተማሪ ናቸው፡፡ ትምህርቱ በዝቶ እንዳሁኑ ናላን እንዳያናውዝና መፈጠርን እንዳያስረግም ግን ሁሉም ነገር መጠን ቢኖረው ደግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኛ ችግር መጠኑን አለፈና በየቀኑ የሚፈልቀው ጉድ አጃኢብ እያሰኘን ማስደመሙን ቀጥሏል፤ በተሎ ዕልባት ካላበጀንለት ከአሁኑ የባሰ መጥፎ ደረጃ ላይ መድረሱ ግን ይሰመርበት፡፡
በቅድሚያ የያሬድን የመሰለ በቅርበት ብቻም ሳይሆን በርቀትም ክፉኛ የሚከረፋና አንዳች አንዳች የሚል ሃሳብ ለማስተናገድ መድረክ መገኘቱ የሀገራችን ልጆች በርግጥም የምዕራቡ ዓለም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ በጎ ልማድ እየማረካቸውና ተቃራኒ ሃሳቦችን በአንድ ማዕድ ማስኬድን እየለመዱ መምጣታቸውን በጉልህ ያሳያልና ይህን መነሻና መድረሻው የማያስታውቅና በአዛኝ ቅቤ አንጓችነት የሚቅመደመድ ጽሑፍ ያነበብኩበትን የዘሃበሻ ድረገፅ ማመስገን እፈልጋለሁ፤ በእግረ መንገድም ይህን ጽሑፌን እንዲቀበሉኝና በተመሳሳይ መድረክ እንዲያስተናግዱልኝ እማጠናለሁ፡፡
በቅድሚያ ያሬድ አይቼህ የተባለ ሰው ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ – የብዕር ስም እንዳይሆን በመስጋት፡፡ አለም ከተባለ ችግር የለብኝም፡፡ ችግሩ ሃሳቡ እንጂ ስሙ አይደለም፡፡ አማራ ነኝ የሚለውን ተረት ግን ይሂድና ሌላውን ይብላ(አፄ ኃ/ሥላሤ ኒክሰን የተባለ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ለጉብኝት መጥቶ ሳለ ከሽሮ ሜዳዎቹ ዶርዜ ሃይዞዎች የተሸለሟትን ባለጥበብ ድንቅ ነጠላቸውን ሊለካት እንደወሰደባቸው ላለመመለስ ሲያቅማማ ባዩት ጊዜና Nixon, go and eat another, answer my singular – ብለው በማሣፈር አስመልሰውታል አሉ – ለዚያውስ ፈረንጅ ማፈር ሲያውቅ አይደል፡፡) እናም ያሬድ ‹አማራ ነኝ›ነቱን እዚያችው ራሱ ይብላት ወይም ለማያውቀው ወስዶ ያብላት፡፡ ያሬድ አማራ ብቻም ሳይሆን ባይገርመውና ባይገርማችሁ ኢትዮጵያዊም አይደለም፤ በኢትዮጵያውያን መካከል ወይም ኢትዮጵያውያን ቢሆኑ ሊያሣፍራቸው በማይገባ ወገኖች መሀል ሽብልቅ የሚቀበቅብ ያሬድ፣ ‹የዱሮ አማሮች ለኢትዮጵያ መፈረካከስ መነሾዎች ናችሁና ገደል ግቡ፤ ሀገር እንደዳቦ የሚጠፈጠፈው በየመቶ ዓመቱ ስለሆነ ከዜሮ የጀመረች አዲስ ኢትዮጵያ ታንጻለችና በዚያች ኢትዮጵያ ካልተስማማችሁ ከነአሮጌ ኢትዮጵያዊ ማንነታችሁ እንጦርጦስ ውረዱ፣ ጃዋራዊ መሆን ካልቻላችሁ ዐርፋችሁ ተቀመጡ› የሚል ያሬድ አማራ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊም፣ እንዲያውም ከነአካቴው ሰውም አይደለም ቢባል ስህተቱ ለክፉ የሚሰጥ አይሆንም – ለዚህ አቋም ኃላፊነቱን እወስዳለሁ፡- በዚህ ልዩ የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ቢያንስ እኔ አልሳሳትም ፡፡ ይህ ዓይነቱ ወንድምን ከወንድም ለማናከስ ቆርጦ የተነሣ በግብርና በአስተሳሰብ በሀገር ላይ የወየነ ግለሰብ በእናቱ ማኅፀን ሳለ ቢጨነግፍ ይሻለው ነበር፡፡ ይሄ ‹ሰው› በሰው አምሳል የተፈጠረ የሰይጣን ስሮት የትውልደ አጋንንት ውጤት ነው፤ ሰይጣን ደግሞ ይሉኝታና ሀፍረት ስለሌለው፣ ዜግነትና ሀገርም ስላልተበጀለት ድርጊቱም ሆነ ንግግሩ እንደልቡ ነው – ለዚህ ነው ይህ ያሬድ የሚባል ‹ሰው› በምግባሩ ሳቢያ አማራ ቀርቶ ሰው አይደለም በማለት ልከራከር የወደድኩት፡፡ የአንባቢ ሥጋት ይገባኛል – ‹የኢትዮጵያዊነትንና የአማራነትን መክሊት ለማበጀትና ማንነትን በመቁነን ለማደል አንተ ማነህ?› ቢለኝ ትክክል ነው፡፡ ያሬድ በብሔረሰብና በዜግነት የማንነት ችግር ውስጥ መዘፈቁን እንኳንስ እኔ ተሰዳቢው፣ አሰዳቢውና አሰዳዳቢው እንዲሁም አሳዳቢው ሁሉ ያውቃል፡፡ አማራ ነኝ እያልክ አማራን መሳደብ ማለት የውሸት ማንነትን መናጆ በማድረግ የስድብ ኳስህን ወደተፈለገው ግብ መለጋት ማለት ነው – ተዓማኒነትን ለማግኘት፡፡ አማራ ሳትሆን አማራ ነኝ እያልክ አማራነትንና በዚያም ተንጠላጥለህ ኢትዮጵያዊነትን መዝለፍ የጤና ሳይሆን ከኅልፈት መልስ ምድራዊ ፈውስ የማይገኝለት ትልቅ ደዌ ነው፡፡ ያሬድ አማራ ሊሆን አይችልም – በጭራሽ! ይህ የነቢባዊ ክርክሬ ማዕከላዊ ጭብጥ እንጂ አማራ ሆነው በዕብደት ምክንያት ከአማራነት ተራ የወጡ ብዙ ወፈፌዎች ስላሉና እያደረጉ የሚገኙትን በማድረግ ላይ ስለሚገኙ ይህ ሰው አማራ ሊሆን የሚችልበት በርና መስኮት ሁሉ ተከርችሟል የሚል ዝግ ውሳኔ እንደሌለኝ ልጠቁም እፈልጋለሁ – ግን ራስህን በራስህ ትቃረናለህ ብትሉ የለሁበትም፤ ከተግባራዊው የደምና የአጥንት አሌታዊ ፍልስፍና ባለፈ ዋናው እሳቤየ ግና ሰውዬውን በኢ-አማራነት ለመፈረጅ መነሻየ ተግባሩ እንጂ ደሙ አይደለም፤ አማራነትን መንጥሮ የሚያሳይ የደም ምርመራ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና አልገባም መሰለኝ፡- ያም አለ ይህ ያሬድ እንደወያኔ ሁሉ ለአማራ ጥፋት የቆመ እንጂ ለሌላ ገምቢ ነገር ያልቆመ በመሆኑ እሳት ካየው ምን ለየው ነውና ፀረ አማራ ፍጡር ነው – አማራ ሆነም አልሆነም፤ ትግሬው ገብረ መድኅን አርአያ የአሉላ አባነጋነትን የሀገር ወዳድነት ሽልማት የተጎናጸፈው ታሪክ ሲዘክረው በሚኖር መልካም ሀገራዊ ተጋድሎው እንጂ አማራን ወይም ሌላውን ዘውግ በሌላው እንዲጠላና እንዲጨፈጨፍ ለማድረግ በተበረከተ ሰይጣናዊ አስተዋፅዖ አይደለም – ከዚህ ጀግናና የኢትዮሰማይ ድረ ገፅ ዋና አዘጋጅ ባለቤት ከሆነው ጌታቸው ረዳን ከመሳሰሉ ፀረ ወያኔ ግለሰቦች ብዙ የምንማረው አለና ዕዝነ ልቦናችንንና ዐይነ ኅሊናችንን ፈጣሪ ለበጎ ነገር እንዲከፍትልን እንጸልይ ይልቁናስ፡፡ ሁሉንም ወያኔ ማለቱ ፋሽኑ ስላለፈበት እንጂ ይህ ሰይጣን ሰው ወያኔ ነው ማለትን በወደድኩ ነበር፤ ለወጣቱ ትውልድ መወናበድና ለኢትዮጵያዊነት መውደም የበኩሉን ተልእኮ በመወጣት ላይ የሚገኝ ከወያኔም በበለጠ እየሠራ ያለ መሠሪ ሰው ነው ቢባል ለማስረገጫው የዛሬ ጹሑፉን ዘሀበሻ ድረ ገፅ ላይ ማንበብ በቂ ነው ፡፡ ባለጌን ባለጌ ካላሉት በማያውቀው ጉዳይ ጥልቅ እያለ መፈትፈቱን ተውትና ዛሬና አሁን ወይም እየቆዬ ‹ጭንቅላታችሁን በደንብ እንዳገኘው ወረድ ብላችሁ ቁሙልኝ ማለቱ አይቀርም› – ሊሸናብን፤ የባለጌዎች መጨረሻ እንደዚህ ነው፡፡ መንግሥቱና መለስ በተፈጥሯቸው ያን ያህል ባለጌዎች ላይሆኑ እንደሚችሉ በበኩሌ ይሰማኛል – ሰው ነው እያጃገነና እያሽበለበለ እንደዚያ ጭምልቅ ያሉ ባለጌዎች ያደረጋቸው፡፡… ይህን የመሰለ ሰው ማኅበራችንን እንዲያውክ መፍቀድና በስሱ ገላችን እየገባ ሚጥሚጣና በርበሬ እንዲነሰንስብን፣ ምሣርም እንዲሰቀስቅብን ነጻ መልቀቅ ስህተት ነው፡፡ የዴሞክራሲን ዐይን እንደመደንቆል ስለሚቆጠርብኝ እንጂ የዚህን ከንቱ ዜጋ ጽሑፍ፣ የዚህን በዘጠኝ ወር ሳይሆን በአምስት ወሩ የተወለደ ሕይወት ያለው ጭንጋፍ ሰውዬ መጣጥፍ ለዳግመኛ አናንብ ብዬ በማይም ቃሌ ብገዝት ደስ ባለኝ፤ ምን ሊሠራልን? ለመናደድና ወርቃማ ጊዜያችንን በመንጨርጨር ልናሳልፍ? ወያኔዎች እኮ የኛን መትከንና መብገን በጣም ነው የሚፈልጉት፡፡ ስንናደድ አንጀታቸው ቅቤ ይጠጣል፡፡ ምክንያቱም ሀዘን አምላኪዎች ናቸውና፡፡ በዚህ ሰውዬ ጽሑፍ ግርጌ ከ100 የሚበልጡ – ብዙዎቹ ግን በተመሳሳይ ስሞች የተደጋገሙና በወያኔያውያን አፈ ቀላጤዎች የተጻፉ የሚመስሉ አስተያየቶችን ተመልክቼ ለነዚህ አስተያየቶች የባከነውን ጊዜ ሳስብ አዘንኩ፤ በስንቱ ወያኔያዊ ሥራ አስፈቺ ጊዜያችን እንደሚቃጠልም ታወሰኝ፤ ይሄው እኔም እንቅልፌን ትቼ በንዴት መብከንከኔን ተያያዝኩላችኋ! ምን ይደረግ? ጊዜው ማለቴ እኛው በሞኝነታችን ባመጣነው ጣጣ ተቸገርን፡፡ ማን ተከፋፍላችሁ ተነታረኩ አለን? ከዚህ በበለጠ ፍሬያማ ተግባር ላይ ጊዜያችንን ማዋል አንችልም ነበርን?
ያሬድም ሆነ ያሬዳውያን ጃዋርን ከወደዱት – በዓላማ ቁርኝት ማለቴ እንደሆነ ይሰመርልኝ – አዝለውት አገር ላገር ሊዞሩ ይችላሉ – ይህን መብት ማንም አይሰጣቸውም ወይም አይነፍጋቸውም፤ እኔም ሆንኩ እኛ በዚህ አንቀናም፡፡ አንድ ጥግ ላይ ተወትፎ የወያኔን አጀንዳ ማራመድ መጨረሻው እንደማያምር ግን የሚመለከተውን ሁሉ ማርዳት እፈልጋለሁ፡፡ በወሬ ሕዝብና ሀገርን ለማፍረስ መሞከር ቀላል ሊመስል ይችላል – ለጊዜው ብዙ ወጭ የለውም፤ የኢትዮጵያ አምላክ የፍጻሜውን ፍርድ ሲሰጥ ግን አሁን እንዲህ ቀን ሰጠኝ ብሎ በሀገር ሀብትና በሕዝብ ሥነ ልቦና ላይ ሲዘባነንና በወረት ፍቅር ተጠምዶ እየቀላመደ ሲዘባርቅ የነበረ ሁሉ ደብቁኝ ደብቁኝ እንደሚል መታወቅ አለበት፡፡ ከጠላት ወገን ቀለብ እየተሰፈረለትና ወርሃዊ ምንዳ እየተቀበለ የጠላትን አሉቧልታ በጮርቃውና ታዳጊው ትውልድ ላይ የሚያናፍስ ተባባሪ ሁሉ ዋጋውን የሚያገኝበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ይሁዳ ክርስቶስን የሸጠበትን 30 አላድ ሳይበላው በገዛ እጁ ዛፍ ላይ ተንጠልትሎ ሞቷል፤ የነ ያሬድና መሰል ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የወደፊት ዕጣ ፋንታም ከዚህ የተለዬ አይሆንም፡፡ ሁለቱ ክህደቶች የጊዜ እንጂ የይዘት ልዩነት የላቸውም፡፡ ለነጃዋር ባላችሁ ቀረቤታ ወይም ለእኔ ባላችሁ ያልተገባና በቂ መደላድል የሌለው ሊባል በሚችል ግምት የተነሣ ይህን እውነት አዘል ደብዳቤ ልኬላችሁ የማታወጡ ድረ ገፆች እንደምትኖሩ ከልምድ አውቃለሁ፤ ለዚህም ፍርዱን የምጠብቀው ቢውል ቢያድርም ከእውነት ፈራጁ ከኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ደግሞም እውነት ትዘገያለች እንጂ ተደብቃ አትቀርም፤ ትቀጥናለች እንጂ አትበጠስም፡፡ ስለዚህ እውነትን እንዳለች ማስተናገድ ሲገባ በጠቆረ ነጣ፣ በወፈረ ከሣ ሚዛን የማያነሳ ቅድመ አእምሮ ፍርድ ተመሥርታችሁ ‹ባለጌና ውሻ በቤቱ ይኮራል› እንዲሉ በራችሁን ብትጠረቅሙብኝ የእውነት ዘገር ሌሊት እየመጣች ታስጨንቃችሁ፡፡ እውነትን እንዳመጣጧ እናስተናግድ እንጂ በምንም ዓይነት ቡልኮ ጀቡነን ጓዳችን ውስጥ ቀብረን ማስቀረት አይኖርብንም፤ ይህ ዓይነቱ ቸልታ ቆምንለት ከሚሉት ዓላማ የሚያስወጣ ከመሆኑም በላጥ ትልቅ ኩነኔ ነው – ሲያንስም ነውር፤ በዚያ ላይ የኅሊና ትዝብትም ቀላል አይደለም፡፡ ለማንኛውም ‹እኔ እያስመዘገብኩ ነው›፡፡ ይሄ ይታወቅልኝ፡፡ ፀረ ኢትዮጵያ መንጋ ሁሉ እንዲህ በአደባባይ እንደፏለለ ይቀራል ማለት ደግሞ ዘበት ነው ፡፡ ሰማይ ምድር ያልፋሉ፡- እግዚአብሔር በአመፀኞች ላይ የሚያሳልፈው ብያኔ ግን መቼም አይቀርም፡፡ ይህ ተብሎ ተብሎ ያለቀ አጠቃላይ እውነታ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞንም ይሄው ያሬድ በአባ መላ ላይ የጻፈውን ተመልክቼዋለሁ – በዚያ ጽሑፉ አባ መላን እያበሻቀጠ ስሎታል፤ ሰው መለወጥ እንደማይችል፣ በአንድ አቋም የሚታወቅ ሰው በዚያው አርጅቶ መሞት እንደሚጠበቅበት… በተዛዋሪ የሚገልጸው ያ ጽሑፍ በአስቀያሚነቱና በምቀኝነት ልክፍቱ ወደር የማይገኝለት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰው የሰውን ዕድገትና ለውጥ ለምን እንደሚመቀኝና ትኩር ጥምድ አድርጎ እንደሚይዝ አይገባኝም፡፡ የአንዳንድ ሰው ተፈጥሮ ይገርመኛል – የሰውን ዕድገትና መለወጥ እንደሥጋት ስለሚያይ ይመስለኛል – አንድ ነገር በሆነ ማግሥት ያን ሁኔታ ጥላሸት ለመቀባት እንቅልፍ አጥቶ ያድራል፤ ክፉኛ መረገም ነው፡፡ በሀገራችን ውድ ከሆኑ ቃላትና ሐረጋት ውስጥ ‹አመሰግናለሁ፤ ይቅርታ፣ ልክ ነህ/ሽ/ናችሁ፤ ኦ! ተሳስቼ ነበር› የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው፤ ምቀኝነትና ሰውን በተንኮል ለመጥለፍ ማሤር እንዲሁም ሰዎችን ለማደኽየትና ለማሳበድ በየጠንቋይ ቤቱ ማፋደስ ግን በብዛት ይስተዋላሉ – በዚህ ዓይነት ጉዞ ሀገር እንዴት ወደፊት ልትራመድ ትችላለች?
ይህ ያሬድ የሚባል ሰው በተለይ በረት እንደሚበጠብጥ ቀንዳም ፊጋ በሬ ዓይነት ነው፡፡ ያኔ ልጽፍ ፈለግሁና ረሳሁት ወይም ንዴቴ እንዳሁኑ በጣም አላስፎገላኝም ነበር ማለት ነው ተዘነጋኝና ተውኩት – ደግሞስ በስንቱ ላይ ተጸፎ ይዘለቃል፡፡ የአሁኑ ግን ወጥ ረገጠና አናደደኝ፡፡ እናም እውነቱን ‹እስከዶቃ ማሰሪያው› ልነግረው ፈለግሁ፡፡ ከባለጌ ሰው ብዙ አይጠበቅምና ከዚህ በላይ ስለዚህ ሰው መናገር አስፈላጊም ተገቢም አይደለምና በእግረ መንገድ ሌላ ጉዳይ አንስቼ ጽሑፌን ላብቃ፡፡ (በነገራችን ላይ በግለሰቦች ላይ እንዲህ ተናድጄ ጽፌ አላውቅም፤ በዚህም አንባቢን ከፍተኛ ይቅርታ እጠይቃለሁ – አይለመደኝም ጓዶች! ምን ላድርግ – የምንንጨረጨርበት ነገር በዛ እኮ፡፡)
ሌላኛው ስመ ጥር ወያኔ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት መሆን አማረኝ እያለ መሆኑን ዛሬም በድጋሚ ሰማሁ፡፡ በክበበው ገዳ አንደኛው የቀልድ ሲዲ ውስጥ እንደሚገኘው እንደሸምሱ ነፍሰ ጡር ሚስት እኔ መቶ ብር ያምረኛል – ኃይሌ ደግሞ ፕሬዚደንትነት ያምረዋል፡፡ ያምሮቶች መለያየት ግን አይገርምም ትላላችሁ? የኢትዮጵያ መሬት መረገም እጅጉን ይገርመኛል፡፡ እርግጥ ነው – በአንድ በኩል ይህ ሹመት ሲያንሰው እንጂ አይበዛበትም – ቤት ለመጠበቅና ተሹዋሚ አምባሳደሮችን ተቀብሎ ለመሸኘት እንኳንስ እርሱ ታዋቂው ሯጭ እኔም አያቅተኝም ባይ ነኝ፡፡ በዚያ ላይ ሌባ ግቢውን አይደፍርም – የተሰጣ እህልና ልብስም ፈጣንነቱን በተማመነ የመንደር ጩልሌ አይደፈርም ፤ ኃይሌ እንደአቦሸማኔ በሚፈተለኩ እግሮቹ ሩጦ ስሊውን ያንቀዋላ – ከዚህ ሌላ ምን የረባ ሥራ ሊኖረው እዚያ ቦታ፡፡ ግን ኃይሌ ይህን ቦታ ለምን ፈለገው?[Is he a real moron? I couldn’t get the point as to why he excessively wished to grab the scepter of Woyane’s fake presidential post.] ለካምፓኒዎቹ ዋስትና ለማሰጠት አስቦ ይሆን? ለተበደለው ጭቁን ኢትዮጵያዊ ፍትህና ርትዕ ሊያመጣ ፈልጎ ይሆን? ከአንጀት ለሕዝብ ሊሠራ ነው ወይንስ ለታይታና በሩጫው ሲያረጅ በአዲስ ጉልበት ወደፖለቲካው ገብቶ ስሙ አየር ላይ እንደተንጠለጠለ ሳይረሳ እንዲቆይ ሊያደርግ አስቦ ነው? ምን ዓይነቱ … ራስ ነው ወገኖቼ! በቅጥር የግል አስጠኚና በግል ጥረት ‘is’ን ከ’was’ ለየና ራሱን ምሁር ማድረጉ ይሆን? ኢትዮጵያ ሰው አጣች ብትባል ጊዜ ይህ ነው የሚባል የትምህርት ደረጃም ሆነ የአመራር ችሎታና ብቃት ሳይኖረው ከመሮጫ ትራክ በቀጥታ ወደቤተ መንግሥት ቢገባ ሀገር የሚያልፍላት መስሎት ይሆን? ወይንስ ለመለስ ሞት ያለቀሰ ሁሉ ለፕሬዚደንትነት ቢወዳደር የሚከለክለው የለም ያለው ይኖር ይሆን? ያኔ ናዝሬት ላይ – መለስ ሳይሞት – ‹የተሸለምኩትን ካናቴራና ፓንት ለውዱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በማስታወሻነት አበረክታለሁ› ብሎ እጅ መንሻ ያስገባው ለዚህ ይሆን እንዴ? የምን መጃጃል ነው? ደግሞስ በዕድሜስ ቢሆን ገና ትንሽ ነኝ ይላል አይደለም እንዴ? እንዲህ ምን አጣደፈው? ትንሽ ቆየት ቢል ይደርስበት ነበር እኮ! ኃይሌም ሆነ ሌላ ማንኛውም ዜጋ ለየትኛውም የሥልጣን ቦታ በገዛ ሀገሩ መወዳደርና ማቸነፍ መብቱ ነው – እኔ አሁን አምርሬ እየተቃወምኩ ያለሁት በዋናነት ጊዜውን ነው – the timing – ፡፡ ከጊዜው ጋር በተጓዳኘም የሰውዬውን ተፈጥሮ ገባ ብሎ ከመመርመር አኳያ የተገነዘብኩትን ነገር ስገመግመው የምለውን ነገር እንዳልል የሚገፋፋ በቂ ምክንያት አጣለሁ፤ እናም እላለሁ – ኃይሌ ይህ ህልሙ ይቅርበትና የሁላችንም አንጡራ ሀብት እንደሆነ ይቆይ፤ የሥልጣን ፍላጎቱ ትዝብት ውስጥ እንዳያስገባውና ነገ መሪያችን እንዲሆን ብንፈልገው ያን ዕድል እንዳናጣ አሁን ‹አይነጅሰን› ነው አንዱ መልእክቴ፡፡ እውነትን ብቻ እንነጋገር ካልን – በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ልጆቹ ከኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ተለይተው በእንግሊዝኛ ቋንቋና በፈረንጅ ባህል ማደጋቸውን ባይናችን በብረቱ እያየን በምን ወደደንና ልምራችሁ ብሎ ይጫረት ያዘ? ምንስ ጎደለበት? መጀመሪያ ልጆቹን ኢትዮጵያዊ ማድረግ ይቀድማል ወይንስ ‹ስለኢትዮጵያና ህዝቧ ተጨንቆ› ለፕሬዝደንትነት ዕጩ ሆኖ መቅረብ ይቀድማል? ትንግርት እኮ ነው ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም አባቶችና እናቶች!
ለነገሩ መለስ አባ ለጥፍ ደህና አድርግ በነገር አቅምሶታል አሉ – የመሌ ምላስ ባትታሠር ኖሮ ይሄኔ ስንቶቻችንን በስድብ ውርጅብኝ አሽሮን ነበር፡፡ የኃይሌን የሥልጣን ጥም ሰምቶ እንዲህ አለው አሉ፡ – ‹ሀገር እኮ በአእምሮ እንጂ በሩጫ ክሂሎት አትመራም፡፡› የልኬቱን መጠን ነግሮታል፡፡ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት አንጻር ወደዚያ መግባቱ ነውር ነው እንጂ ለጫማ ጠራጊና ለመኪና ጠባቂ ከስሙኒ በላይ የማይወጣው ንፉግና ቆንቋና ለሰውም የማያዝን ዜጋ በየትኛው የሞራል ብቃቱና በየትኛውስ ማኅበረሰብኣዊ ዕውቀትና ችሎታው ነው ለፕሬዝደንትነት አብቁኝ የሚለው? አናውቀውም እንዴ? ‹እንደኔ ፈግታችሁ በላባችሁ አግኙ› የሚለው ፈሊጡ ለሥራ መትጋትን ከማበረታታት አንጻር መልካም አባባል መሆኑ የማይካድ ሆኖ ለተቸገረና ላጣ ለነጣ እንዲሁም ለታመመና ድንገተኛ አደጋ ለደረሰበት ዜጋ የሞራልም ሆነ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ቢያደርግ ምኑ ይጎዳል? እስኪ ኃይሌ እገሌን አስታምሞ አዳነ፤ ለእገሌ መታከሚያ ‹ይህን ያህል ዕርዳታ ሰጠ› ሲባል ሰምተን እናውቃለን? ተው እንጂ – አታናግሩኝ እባካችሁ፡፡ መለስ ራሱ እኮ ስለኃይሌ የበጎ አድራጎት ሥራ ሲጠየቅ አሉ – ‹ይልቅስ ስለቻቺ ጠይቁኝ› ብሏል ይባላል፡፡ እናም ኃይሌ በዓለም የስፖርት አምባዎች ባንዲራችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ከማድረግ በተጓዳኝ በማኅበራዊ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ብዙ ይጠበቅበታልና በዚያ በኩል ይበርታልን – በነገራችን ላይ ስለ ኃይሌ ከምለው ውጪ የምታውቁት ነገር ካለ ንገሩኝና አስተካክሉኝ፡፡ በመሠረቱ ማንንም አለመርዳት መብቱ ነው – ግን በልባችን እንዲገባ ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ የሕዝብን ልብ ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ ቸርነት ደግሞ አንዱ የቀልብ መግዣ መንገድ ነው፡፡ እያለህ የሌለህ መሆን ወይም መምሰል በባህላችን ነውረኛና ንፉግ ያስኛልና ይህችን ቀላል ነገር በመረዳት በሚያልፍ ዓለም የማያልፍ ትውፊት ትቶ ማለፍ ከብልሆች ይጠበቃል፡፡
ምንም እንኳን ለወያኔ ሹመት ታማኝነት እንጂ ዕውቀትና ችሎታ ባያስፈልግም በብዙ አሉታዊ ነገሮች የማውቀው ኃይሌ ምን ቢንቀን ነው ፕሬዝደንታችሁ ልሁን ብሎ ጠላታችን ወያኔ ጫማ ሥር እየተደፋ የሚጎናበሰው ብዬ ማሰቤ ደግሞ አልቀረም፡፡ ከገንዘብና ከዝና አጥሮች ውጪ መኖር የሚሣናቸው ኃይሌን መሰል በሽተኞች ያሳዝኑኛል፡፡ ያለውን ሳይበላ ለሀብት ብዙ የሚስገበገብና ስመጥርነቱ ሳያንሰው ለተጨማሪ ዝና አላግባብ የሚንሰፈሰፍ ሰው ስሜቴን ያጎፈንንብኛል፡፡ በእውነት እናንተስ አልተናደዳችሁበትም? እንደዘፈኑ ግጥም ‹የራስጌ ወለባ ያንገት ሀብል ናቸው› ብላችሁ እንዳትቀልዱብኝ እንጂ ለመሆኑ ሩጫና አመራር ምንና ምን ናቸው? ብንወደው ጊዜ ለምን ይቀልድብናል? የወደድነውስ በሩጫ እንጂ በማኅበራዊ ሣይንስ ዕውቀቱና በተመራማሪነቱ ነው እንዴ? ስንትና ስንት ሺህ ምሁራን በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ሞልተውን ሳለ ነገር ግን በሁኔታዎች አለመስተካከል ምክንያት አንገታቸውን ደፍተው ቀን እየጠበቁ ባሉበት ሁኔታ የትናንት ኃይሌ ገና ለገና በሩጫ እታወቃለሁና ቦታውን ይሰጡኛል ብሎ እንዲህ ያለ ጣጣ ውስጥ መግባቱ ማንን ለማስደሰትና ሳይታወቀውም ቢሆን ማንንስ ለማስከፋት አልሞ ይሆን? በውነቱ ከያሬድ ይልቅ በዚህኛው ጉዳይ በጣም ተናድጃለሁ፡፡ የያሬድ ለዓላማ ስለሆነ ነገር ከመጠረቅና የተዳፈነ ብሶትን ከማውጣት ባለፈ ያን ያህል ልናደድበት እንደማይገባኝ እረዳለሁ፡፡ በኃይሌ ግን አንጀቴ ነው የጨሰው – የማምነውን!
የብሶት አቅማዳየን ላስር ነው፡፡ ደህና ሁኑልኝ፡፡ ኃይሌንም ይቅናው፤ ውድ ፕሬዚደንታችን ኃይሌ ሣቅ በሣቅ ሆነው እንግዳ ሲቀበሉና ሲሸኙ እያየሁ ከአሁኑ መዝናናት ይዣለሁ፡፡ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ለአርባ አራት ሰባት ካልተጠበለ ችግሩ የሚቀረፍ አይመስልም፡፡ ለማንኛውም ቸር እንሰንብት፡፡