“ሚዲያዎች የአማራውን ብሶት በአግባቡና በሚመጥነው መልኩ እየዘገቡት ስላልሆነ በቅርቡ ራድዮ እንከፍታለን” – ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ሐሙስ ኅዳር ፴ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. ቅፅ ፬ ፣ ቁጥር ፬
የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ

የአቋም መግለጫ

እኛ የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት እሑድ ኅዳር ፳፮ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. (Sunday December 6, 2015) ባደረግነው የማዕከላዊ ምክር ቤቱ ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባ ፣ በማዕከላዊ ምክር ቤቱ ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ በጸደቁት የ፮(ስድስት) ወራት የሥራ ዕቅዶች አፈጻጸም ምዘና ሪፖርት፣ በድርጅቱ የቁጥጥርና ፍተሻ የአካላትና የአባላት የሥራ እንቅስቃሴና የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ሪፖርት በአንክሮ አዳምጠን አስፈላጊውን ውይይት በማድረግ ሪፖርቶቹ ከምክር ቤቱ አባሎች የቀረቡትን ገንቢ ሀሳቦችን አካትቶ የድርጅቱ ቋሚ ሰነድ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ ወስነናል።

ከሁሉም በላይ በዚህ መደበኛ ስብሰባ ምክር ቤቱ አጽንዖት ሰጥቶ ሠፊ ጊዜ ወስዶ የተወያየበት «የድርጅቱን ዓላማና ተልዕኮ በተሻለ መንገድ እንዴት ማከናወን ይቻላል?» ለሚለው ጥያቄ ተገቢና ሁነኛ መልስ ለማግኘት ነበር። በተደረገው ውይይት ከአባላቱ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በውይይቱ ሚዛን ደፍቶ የቀረበው ኃሣብ ዐማራው ከተከፈተበት የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ራሱን ተከላክሎ ዘሩን ማትረፍ የሚችለው፣ ሲነቃ፣ ሲደራጅ እና ሲታጠቅ እንደሆነ ምክር ቤቱ አምኗል። ራሱን መከላከል ያልቻለ ማኅበረሰብ ተዋራጅ፣ ተገዥ፣ ተጨቋኝና በመጨረሻም ጠፊ እንደሚሆን ከታሪክ የታየና የታወቀ ነው። ስለሆነም በዐማራው ላይ እየተደረገ ያለው መጠነ-ሠፊ ዘመቻ የሚያመለክተው ብቻ ሳይሆን፣ እየሆነ ያለው የነገዱን መጥፋት ስለሆነ፣ ሞረሽ ወገኔ ሁለንተናዊ አቅሙን አጠናክሮ ዓላማውን ከሚጋሩት ኃይሎችና ቡድኖች ጋር በመተባበር የዐማራውን ነገድ ከፈጽሞ ጥፋት የሚታደግበትን ማናቸውም ዓይነት ተገቢ ሥልት በመከተል የዐማራውን ኅልውናና ማንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ከምንጊዜውም በላቀ ቁርጠኝነት እንዲቀሳቀስና አባላትም የተጠየቁትን ማናቸውም ዓይነት ተገቢ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በሙሉ ድምፅ ተስማምተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፍተኛ ባልስልጣናትን ገድለዋል የተባሉት ከ15 ዓመት- እድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ተሰጠ፡

ማዕከላዊ ምክር ቤቱ ይህን ቁርጠኝነት በተግባር ለመግለጽ እንዲቻል የቀጣዩ እንቅስቃሴ አቅጣጫ አመላካች ከሆኑ አቋሞች ላይ ደርሷል። በዚህም መሠረት የድርጅቱ አካላት፣ አባላት እና ደጋፊዎች ለመጭዎቹ ስድስት ወሮች በሚከተሉት አቋሞች ዙሪያ ኃይላቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን አስተባብረው እንዲቀሳቀሱ የጋራ ውሣኔ ላይ ደርሷል።

1. ኢትዮጵያን የሚመለከት የብዙኃን መገናኛ ተቋሞች ያሏቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች የዐማራውን ጉዳይ በአግባቡና በሚመጥነው መልኩ እያስተናገዱት እንዳልሆነ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ችለናል። ይህም ዐማራው እየተፈጸመበት ያለው ግድያ፣ እስራት፣ መፈናቀል፣ ንብረት ነጠቃ፣ ግፍና በደል ዐውቆ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል እንዳይችል መረጃ እንዳይደርሰው ያደረገ ስለሆነ፣ ዐማራው ብሦቱንና ችግሩን የሚገልጽበት የራሱ የሆነ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያስፈልገው ሁኔታዎች በተጨባጭ አሳይተዋል። መረጃ የማድረግ ብቃት ማረጋገጫ ከመሆኑም በላይ የኃሣብ አንድነትን ገንብቶ ድርጅታዊ ኃይል ለመሆን የሚያስችል የትግል መሣሪያ ነው። ስለሆነም ዐማራው የተጋረጠበትን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ለመቋቋም የሚችለው ትክክለኛው መረጃ በአግባቡ ሲደርሰው ነው። ያላወቀ፣ ያልነቃና ያልተደራጀ ማኅበረሰብ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ መሆኑ ዕውቅ ነው። ስለሆነም ዐማራው ከተከፈተበት ሁለንተናዊ ጥቃት ራሱን መከላከል እንዲችል አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ሊደርሱት ይገባል። በዚህም ምክንያት ዐማራው የራሱ የሆነ አንደበት የመኖሩ ጉዳይ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። በመሆኑም የተጀመረውን የሬዲዮ ፕሮጀክት ሥራ ለማስፈጸም የሚያስችለው ገንዘብ በአስቸኳይ ተሰባስቦ የሞረሽ ሬዲዮ በኢትዮጵያ አየር ላይ እንዲናኝ እንዲደረግ የሚፈለግብንን ሁሉ አስተዋፅዖ በትጋት ለመወጣት የየበኩላችን ጥረት እናደርጋለን።

2. ሞረሽ ወገኔ ያነገበውን ጥልቅና ሠፊ ዓላማ እንዲሁም ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት አስተማማኝ የሆነ የገቢ ምንጭ ያሻዋል። ያለገንዘብ የድርጅቱ ዓላማ የትም ሊደርስ እንደማይችል ይታወቃል። ገንዘብ የሁሉም ነገር የማድረግና የበላይነት መገለጫ ሁነኛ መሣሪያ መሆኑ ግልጽ ነው። ያለገንዘብ ምንም ነገር ማድረግ እንደማይቻል ይታወቃል። በመሆኑም ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት፣ ድርጅቱ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ ጥረቱም የቋሚ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት አጥንቶ ለተግባራዊነቱ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ስለሆነም፣ ለፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር የሚያስፈለግውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የተያዘው ጥረት በተፋጠነ ሁኔታ በማከናወን ፕሮጀክቱ ባስቸኳይ ሥራ ላይ እንዲውል፤ ለዚህም አካላትና አባላት የሚፈለግባቸውን እንዲወጡ የበኩላችን ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአቡነ ጳውሎስ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኘው ሃብት አነጋጋሪ ሆኗል

3. ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ከሚታገልላቸው ዓላማዎች አንዱ በዐማራው ነገድ ላይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የፈጸሙ ቡድኖችና ግለሰቦችን ለፍትኅ ማቅረብ ነው። ይህን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በነገዱ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ከጥርጣሬ ውጭ በሆነ ሁኔታ፣ ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ወገን ማስረዳትና ማሳመን የሚችሉ ዝርዝር መረጃዎች እንዲሰበሰቡ ጥረት ተደርጓል። በዚህም መሠረት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የመረጃ አሰባሳቢና አጥኝ ቡድን ተቋቁሞ ባዘጋጀው ፕሮጀክት መሠረት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በዐማራው ላይ የተፈጸሙ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀሎችን በተጨባጭ የሚያረጋግጡ መረጃዎች ተሰባስበዋል። የጉባኤው ተሣታፊዎች እኒህ መረጃዎች ለተፈላጊው ግልጋሎት እንዲውሉ በአመራሩ በኩል አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስነናል።

4. ድርጅቱ ወደፊት በተሳካ ሁኔታ መጓዝ የሚችለው ዕውቀት፣ መረጃ፣ ጊዜ እና ገንዘብ በበቂ መጠን ሲኖሩት ነው። የእነዚህ አስፈላጊ ጉዳዮች ብቸኛ ምንጭ ደግሞ ሰው ነው። ስለሆነም የሞረሽ ወገኔን ዓላማ ለማሳካት ቁልፉ ጉዳይ የአባላት ምልመላ ስለሆነ፤ እያንዳንዱ የምክር ቤት አባል ለሚቀጥሉት ስድስት ወሮች ተጨማሪ አባላት በመመልመል ለሰው ኃይል ማደራጃና ዝግጅት መምሪያ እንዲያሳውቅ ምክር ቤቱ ወስኗል።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!

3 Comments

  1. Well done brothers and sisters. I for one will gladly contribute all that I can to help your wonderful plan achieve.
    Amara will prevail!

Comments are closed.

Share