የሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞ ቀጥሏል

· በአጣሪ ኮሚቴው የቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲተገበሩ ጠይቀዋል
· የአቡነ ጢሞቴዎስን የሹመት ሐሳብ በማውገዝ ርምጃ ለመውሰድ ዝተዋል
· ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ይወያያሉ

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ውለዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ረፋድ ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በከፍተኛ ቁጥር በማምራት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስን ለማነጋገር ያደረጉት ሙከራ ወደ ግቢው እንዳይገቡ በጥበቃ በመከልከላቸው ምክንያት አለመሳካቱ ተነግሯል፡፡

የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ታምሩ አበራ ከጥቂት የደቀ መዛሙርቱ ተወካዮች ጋራ የተገናኙ ሲኾን፣ ደቀ መዛሙርቱ÷ ከአምስት ወራት በፊት ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በአጣሪ ኮሚቴ ከታዩ በኋላ የተሰጡት የመፍትሔ ሐሳቦች በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረጉ፣ ከኮሌጁ እንዲባረር በአጣሪ ኮሚቴው የተጠቆመበትን የቀን መርሐ ግብር ሓላፊ ዘላለም ረድኤትን የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ በዋና ዲንነት ለማሾም ማሰባቸውን በመስማታቸው ይህን ከማስፈጸም እንዲታቀቡ ለልዩ ጽ/ቤት ሓላፊው ማሳሰባቸው ተዘግቧል፡፡

በልዩ ጸሐፊያቸው አማካይነት መልእክት ያስተላለፉት ፓትርያሪኩ፣ በነገው ዕለት ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ኮሌጁ እንደሚልኩና በጉዳዩ ላይ ከእነርሱ ጋራ እንዲወያዩ እንደሚያደርጉ ለደቀ መዛሙርቱ ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ትላንት ሌሊት በኮሌጁ አዳራሽ ተሰብስበው ለጥያቄያቸው በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚያገኙ በተሰጣቸው ተስፋና ውሎ አድሮ በታየው ኹኔታ ላይ በስፋት መወያየታቸው የተዘገበ ሲኾን ቀጣይ አካሄዳቸው የኮሌጁን መግቢያና መውጫ ከመቆጣጠር ጀምሮ በሓላፊዎች ላይ የሚወሰድን የኀይል ርምጃ ሊያካትት እንደሚችል ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመልክቷል፡፡

አጣሪ ኮሚቴው ሲያካሂድ በቆየው ማጣራት÷ ለኮሌጁ ሙሉ ሥልጣን ያለው ዋና ዲን እንዲሾምና ምክትል ዋና ዲን የሚለው ስማዊ ሥልጣን እንዲቀር፣ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በማስተማር እንዲወሰኑና በምትካቸው አግባብነት ያለው ሰው እንዲተካ፣ የቀን መርሐ ግብር ሓላፊው ዘላለም ረድኤት ከኮሌጁ እንዲወገዱና ከነገረ ክርስቶስ እና ክብረ ቅዱሳን ጋራ በተያያዘ በቀረበባቸው የሃይማኖት ሕጸጽ እንዲጠየቁ በደረሰበት የመፍትሔ ሐሳብ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጋራ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ እንዲፈጸም መወሰኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
(ምንጭ -ሐራ ተዋሕዶ)

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም አካል እንዲያስመዘግቡ ተጠየቀ
Share